Tag Archives: Politics

”የህዝብ ህይወት እና የሀገር ደህንነት ጉዳይ ከየትኛዉም የፖለቲካ አጀንዳ በላይ ነዉ” ተቀኛቃን የኦሮሞ ድርጅቶች

Continue reading ”የህዝብ ህይወት እና የሀገር ደህንነት ጉዳይ ከየትኛዉም የፖለቲካ አጀንዳ በላይ ነዉ” ተቀኛቃን የኦሮሞ ድርጅቶች

አገራዊ ለውጡ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እስኪያገኝ ጊዜ እንደሚፈልግ የታሪክ ፕሮፌሰሩ ባህሩ ዘውዴ ገለጹ

አገራዊ ለውጡ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እስኪያገኝ ጊዜ እንደሚፈልግ የታሪክ ፕሮፌሰሩ ባህሩ ዘውዴ ገለጹ። ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው ”የለውጥ ሂደቱ ያጋጠሙት ችግሮች የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶ መገምገም አለባቸው” ብለዋል።

የኢትዮጵያ አገራዊ ለውጥ ሂደት ወቅታዊ ሁኔታ፣ እድል፣ ተግዳሮትና ስጋቶች’ በሚል ሰሞኑን በተደረገው ስብሰባ ተሳታፊ የነበሩት የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፈሰር ባህሩ ዘውዴና ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው በተለይ ለኢዜአ አስተያይት ሰጥተዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ኤምሬትስ ፕሮፈሰሩ ባህሩ ዘውዴ፤ ኢትዮጵያ በስርዓተ መንግስት ታሪኳ ለውጥ ማካሄድ አዲሷ እንዳልሆነ ይናገራሉ።

በዘመናዊ ታሪኳ እንኳን ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን ለማዋሃድ መነሳታቸውን፣ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ደግሞ ተቋማትን በማቋቋም ዘመናዊ የሲቪል ሰርቪስ ቢሮክራሲ ምስረታ ማስጀመራቸውን፣ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በርካታ መንግስታዊ ስርዓት ማሻሻያ ማካሄዳቸውን ያስታውሳሉ።

ዳሩ ግን የዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ለውጥ ሳይሳካ የለውጥ አራማጁ ህይወት መቀጠፉን እንዲሁም በመጨረሻ ንጉሳዊ ስርዓት በአጼ ኃይለስላሴ ዘመን በርካታ ለውጥ ቢደረግም የለውጥ ሂደቱ ሳይሰምር መቅረቱን ገልጸዋል።

በተለይም ሁለት ህገ መንግስቶች ቢወጡም ሁለቱም ድክመት የነበራቸው፣ የንጉሱን ሃይል ለማጠናከር፣ መሳፍንቱን ለመቆጣጠር እንጂ የህዝብን ጥቅም ማዕከል ያላደረጉ፣ መብቶችን ያላስከበሩ እንደነበር ገልጸዋል።

በዚህም በውርስ ንጉሳዊ ስርዓት የተመሰረተው ለውጥ የንጉሰ ነገስቱ ስልጣን በህገ መንግስት ባለመገደቡ፣ አብዮቱን ያስከተለውና አገሪቱን ወደሌላ ቀውስ የከተተው ለውጥ እንዲከሰት ማድረጉን አውስተዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ ከውጭ ሳይሆን ከውስጥ የመጣ መሆኑን የሚገልጹት ፕሮፌሰር ባህሩ፤ ለውጡ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እስኪያገኝ ድረስ ጊዜ እንደሚፈልግ አስገንዝበዋል።

ለውጡን ስኬታማ ለማድረግና የአገር ህልውናን ለማስቀጠል የብሄር ማንነትና ኢትዮጵያዊነት ሳይቃረኑ ተሳስረው እንዲሄዱ ማስቻል ተገቢ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ማህበራዊ እሴቶችንና ባህላዊ ሃብቶችን የፖለቲካ ስርዓት ግብዓት ሆነው እንዲጠቅሙ ማድረግ ተገቢነት እንዳለው ፕሮፌሰር ባህሩ አንስተዋል።

ሌላው ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው የአሁኑ የኢትዮጵያ አገራዊ ለውጥ ሲጀመር በህዝብ ዘንድ ተስፋ የተጣለበትና ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘ እንደነበር አንስተዋል።

ይሁንና አንድ ዓመት ከስድስት ወር ያስቆጠረው አገራዊ ለውጥ ህዝቡ በሚፈለገው ዘለቄታዊ መፍትሄ ባለመራመዱ ህዝቡን ለጥርጣሬ እየዳረገ እንደሆነ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

መዋቅራዊ ዴሞክራሲ የሚጠበቅ ቢሆንም የለውጡ ሃይል ስለለውጡ ችላ እያለ መሆኑን በማንሳት፣ ገዥው ፓርቲ ሽኩቻ ውስጥ መግባቱን ገልጸዋል።

”ለውጡ ካሉት በጎ ጎኖች ይልቅ ችግሮቹ ሲመዘኑ ይጎላሉ” ያሉት አቶ ልደቱ፤ የለውጥ ሂደቱ ያጋጠሙትን ችግሮች የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀትና መገመግም ተገቢ እንደሆነ አንስተዋል።

ኢዜአ

በአማራና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ግጭት ዳግም እንዳይነሳ እየተሰራ ነው

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር በአማራና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ግጭት ዳግም እንዳይነሳ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡የሁለቱ ክልሎችን የዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር በሰላም እና መረጋጋት በተሰሩ ስራዎች ዙሪያ የሁለቱ ክልሎች ርዕሰ መሰተዳድሮች ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እንዳሉት የሰላምና የልማት ትብብሮች በሁለቱ ክልሎች መካከል በቀጣይ የህዝቦችን ሰላም ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው።

ግጭቶች ዳግም እንዳይቀሰቀሱም አመራሩን በመፈተሽ በህግ የሚጠየቁ አካላት ተለይተዋል፤ በቁጥጥር ስር ያልዋሉ አመራሮችን ለመያዝም ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡

በሁለቱ ክልሎች ወሰን አካባቢ ማንኛውም ህገ ወጥ እንቅስቃሴን በማቀብ በልማት የማስተሳሰር ስራ ላይ ትኩረት ተደርጎበት እንደሚሰራም ነው የተናገሩት ።

በተለያዩ ግጭቶች ከቀያቸው የተፈናቀሉትንም መልሶ የማቋቋም ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል ። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው፥ የተሻለ ስራ መስራት ቢጠበቅም የባሰውን አደጋ በመፍታት አጎራባች አካባቢዎችን በፍጥነት ወደ ተለመደው ሰላማቸው ለመመለሰ የተደረገው ርብርብ ውጤታማ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በሁለቱ ክልሎች ወሰን አካባቢዎች የጸጥታው መደፍረስ በአካባቢው ያሉ ህዝቦችን አደጋ ላይ ጥሎ ከማለፍ በስተቀር ግጭቱ ለዘመናት የተገመደውን በአብሮነት የመኖር እሴት እንዳልቀየረው ነው የሚናገሩት፡፡ በህዝቦች መካከል ያለው ጉርብትና እና አብሮ የመኖር ባህል ዛሬም የጠነከረ ነው ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለሰ በተደረገው ጥረትም ከ7 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን አንስተዋል። በቀጣዩ መስከረም ወርም የህዝብ ለህዝብ የውይይት መድረክ ይዘጋጃል ነው ያሉት፡፡

በሀይለየሱስ መኮንን –  (ኤፍ.ቢ.ሲ)

በሃይማኖት ተቋማት ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች በአስቸኳይ ሊቆሙ ይገባል ! – ኢዜማ

አለምን ያስደመመ የስልጣኔ ፋና ወጊ የሆኑ የቁሳዊ፣ ባህላዊና ሐይማኖታዊ እሴቶች ባለቤት የሆነችው አገራችን የብዙ ሺህ ዓመታትዝክረ-ታሪክም ለእኛ ለዜጎቿ ታላቅ ኩራት ነው፡፡በርካታ የታሪክ ቅርሶችዋ የሥልጣኔን የትየሌለነትን አጉልተው የሚዘክሩ ናቸው፡፡ኢትዮጵያ በርካታ ብሄረሰቦቿ በፈጠሩት ማኅበራዊ መስተጋብር የተዋበች፣ የተለያዩ ሐይማኖች በመቻቻል፣ በመተሳሰብ ተደጋግፈው ኩራት የሆኗትታሪካዊት ሀገር ናት፡፡

ዜጎቿ የባህል፣የሐይማኖት፣ የቋንቋ እና የዘር ወዘተ … ልዩነቶቻቸው ለኢትዮጵያዊነታቸው ልዩ ውበት እንጂ ጋሬጣ ሆኖባቸው አያውቅም ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊያን የአገራቸውን ሉዓላዊነት ከውጭ ወራሪ ኃይል ለመከላከል የውስጥ ልዩነቶቻቸውን አቻችለውበአንድ ረድፍ ስለመሰለፋቸው በታሪክ ድርሳናት ተከትበው የሚገኙ ናቸው፡፡ ይህ አኩሪ የሆነ ታሪካቸው ሳይሸረሸር ለቀጣዩ ትውልድይተላለፍ ዘንድ ዛሬ ላይ እየታዩ ያሉ ችግሮችን ማረቅ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የተለያዩ ሐይማኖት ተከታዮች እርስበእርስ በመደጋገፍ እና በመፈቃቀር የሚኖሩባት አገር መሆንዋ እሙን ነው፡፡ ክርስቲያኖች ከሙስሊሞች ሙስሊ.ሞች ከክርስቲያኖች ጎን በመቆም ሃዘንና ደስታን በጋራ የሚጋሩባት ምድር እንጂ እርስ በእርስየሚቆራቆሱባት አገር አይደለችም፡፡ አንዱ ሐይማኖት ለሌላኛው የቅርብ አጋርና ተቆርቋሪ በመሆን ኢትዮጵያዊነትን ያደምቃሉ እንጂ በጠላትነት አይፈራረጁም፡፡

ይሁን እንጂ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት በነበረው የፖለቲካ ትኩሳት ዘርና ቋንቋን ተገን አድርጎ በዜጎች መሀከል የተለኮሰው እሳትወላፈኑ ተፋቅረውና ተከባብረው ይኖሩ የነበሩ ሐይማኖቶችን ማወኩን ተመልክተናል፡፡ በአዲስ አበባ፣ ሶማሌ፣በኦሮሚያ፣በደቡብና በአማራ ክልሎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፣መስጂዶችና ፀሎት ቤቶች ላይ የደረሱ ጥቃቶች የታሪካችን ማፈሪያ መሆናቸውን ልናስተውል ይገባል፡፡ በጅግጅጋ እና በሲዳማ ዞን ወረዳዎች በቅርብ ተከስተው በነበሩ ግጭቶች በርካታየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸውና መፈራረሳቸው የአገሪቱን መፃኢ እድልና ህልውና ሊፈታተን እንደሚችል ማመን ይኖርብናል፡፡

ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ የሚፈጠረው ቀውስ መብረጃ አይኖረውም፡፡ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ይህንን አገራዊ እየሆነ የመጣውን ችግር ከወዲሁ ማስቆም ይቻል ዘንድ የበኩሉን ያላሰለሰ ጥረት ለማድረግ ቁርጠኘነቱን እየገለፀ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ ያስተላልፋል፡

1. ከተለያዩፖለቲካዊና የማንነት ጥያቄዎች ጋር በተያያዙ ግጭቶች በተነሱ ቁጥር በሐይማኖት ተቋማት ማለትም
በቤተክርስቲያን፣በመስጂድ እና በፀሎት ቤቶች ላይ የሚሰነዘሩትን ጥቃቶች አጥብቀን እያወገዝን መንግሥት የድርጊቱን ፈፃሚዎች እየተከታተለ ለፍርድ እንዲያቀርብ እና የችግሩን ምንጭ እንዲያደርቅ ጥሪ እናስተላፋለን፤

2. ከ95% በላይ የሚሆነውየኢትዮጵያ ሕዝብ የተለያዩ ሐይማኖቶች ተከታይ በሆነባትና እነኚህም ተቋማት ፍቅርና ሰላምን በሚሰብኩባት ምድር በብሄርና በቋንቋ ሰበብ የሚነሱ ግጭቶችን ወደ ሐይማኖት ለማስጠጋት መሞከር አገርን ለማፈራረስ የሚደረግሙከራ ስለሆነ አጥብቀን እናወግዛለን፤

3. የሐይማኖት ተቋማትና መሪዎች በመንፈሳዊ ሥርዓት ሰላምን የሚሰብኩ፣ ቅራኔዎችን የሚፈቱ፣ የተጣላን የሚያስታርቁ፣ አጥፊን የሚገስፁ መሆን ሲገባቸው በተለያዩ ጊዜያት የእምነት ተቋሞቹን ከጥቃትበመከላከል አጀንዳ ተጠምደው የቆሙለትንመንፈሳዊ ተግባር ማከናወን አለመቻላቸው ተገቢ አለመሆኑን እንገልፃለን፤

4. በተለያዩ ጊዜያት በተፈጠሩ ግጭቶች ጥቃት የደረሰባቸውን እና የፈረሱ ቤተ-እምነቶችን መልሶ የመገንባት ሥራ ላይ መንግሥት ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርግ፣ በየአካባቢው የሚገኘው ማኅበረሰብም የእምነት ልዩነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ቤተ-እምነቶችን በጋራ ከጥቃት እንዲከላከል መልሶ ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴም የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክትና ተከባብሮ የመኖር ዘመናት እሴቱን እንዲያጠናክር ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

በመጨረሻም የሐይማኖት ተቋማትና መንፈሳዊ አባቶች ከምንም በላይ የአገርን ሰላምና የሕዝብን መረጋጋት በሚያሰፍኑ ሐይማኖታዊና መንፈሳዊ ተግባራት ላይ ትኩረት በመስጠት ለቀጣይ ትወልድ የምትሻገር የጋራ አገር እንድትኖረን ትኩረት ሰጥተው እንዲንቀሳቀሱ የአክብሮት ጥያችንን እናስተላልፋለን፡፡

የጥላቻ ንግግሮች የገነኑት መደበኛ መገናኛ ብዙሃን ስራቸውን ስላልሰሩ ነው – ምሁራን

መደበኛ መገናኛ ብዙሃን የጥላቻ ንግግሮችን የመቀልበስና ለህዝብ ትክክለኛውን መረጃ የማድረስ ሚና ቢኖራቸውም ይህን ማድረግ እንዳልቻሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህራን ተናገሩ።

መምህራኑ ከአገሪቱ የፖለቲካ ለውጥ ማግስት ጀምሮ እየመጣ ያለውን የመፃፍና የመናገር ነፃነት ተከትሎ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ክብርን የሚነኩ የጥላቻ ንግግርች እየገነኑ መምጣታቸውን ይናገራሉ።

በተቋማትና በግለሰቦች ላይ የሚደረጉ የጥላቻ ንግግሮች በተለያዩ አካባቢዎች የግጭትና የግንኙነት መሻከር መንስኤ እየሆኑ መምጣታቸውንም ጠቁመዋል።

የጋዜጠኝነት መምህሩ አማኑኤል አብዲሳ እንደሚሉት በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ መረጃዎች የተአማኒነት ችግር ያለባቸውና በሂስና በጥላቻ ንግግር መካከል ያሉ በመሆናቸው ጉዳታቸው ያመዝናል።

ይህም የሆነው ማህበራዊ ሚዲያው የሚመራበት አሰራር ባለመኖሩና መደበኛ የመገናኛ ብዙሃኑ የስራ ውስንነት ስላለባቸው ነው ብለዋል።

ሌላው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር ዶክተር ሙላቱ አለማየሁ እንደሚሉት በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮች በአብዛኛው ከፖለቲካ ለውጥ፣ ከኢኮኖሚ ልዩነት መስፋትና ተያያዥ ሁኔታዎች ጋር ተያይዘው የሚነሱ ናቸው።

መረጃው እውነትም ይሁን ሐሰት በህዝቡ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት መረጃውን እንደሚፅፈው ሰው ተቀባይነትና እንደ መረጃ ተጠቃሚው ግንዛቤ ደረጃ ይለያያል። ይሁንና በዚሁ ከቀጠለ ለአገሪቱ የፀጥታ ስጋት ነው።

የጥላቻ ንግግሮች በተለይ መረጃዎችን በትክክል አመዛዝኖ አገናዝቦ የሚጠቀም ማህበረሰብ ባልተፈጠረበት አገር የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑንም አንስተዋል።

ይሁን እንጂ ለጥላቻ ንግግር መግነን ምቹ ሁኔታን የፈጠረው የመደበኛ መገናኛ ብዙሃን ወቅታዊ፣ ትክክለኛና ሚዛናዊ የሆነ መረጃን ማቅረብ አለመቻል መሆኑንም ይናገራሉ።

አሁን ያለው ሚዲያ “ፍርሃት የሸበበው፣ መርጦ የሚዘግብ፣ ፈጣን ያልሆነ እና ዝም ያለ ነው” ያሉት ዶክተር ሙላቱ የጥላቻ ንግግርን መቀልበስ ይቅርና ትክክለኛ መረጃን ለማድረስም ውስንነት እንዳለበት ገልፀዋል።

በመሆኑም በማህበራዊ ሚዲያው የሚለቀቁ ያልተረጋገጡ የጥላቻ ንግግሮች ህዝብን ወዳልተገባ ተግባር እንዳያስገቡ ከተፈለገ መደበኛ መገናኛ ብዙሃን ስራቸውን በአግባቡ ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።

መደበኛ መገናኛ ብዙሃኑ በለውጡ ማግስት ጀምረውት የነበረውን የአገራዊ መግባባት ውይይት በአሁኑ ወቅት መቀነሳቸው በራሱ ቀጣይነት የሌለው የዘመቻ ስራ መስራታቸውን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የማህበረሰቡን ችግር ነቅሶ የመዘገብና ፈጣንና ትክክለኛ መረጃን የማቅረብ ስራቸውን ቀጣይ ቢያደርጉ ችግሮቹን መቀነስ ይቻላል ሲሉ ነው ምክረ ሃሳባቸውን የለገሱት።

ኢዜአ ነሀሴ

ʻክልል እንሁንʼ ጥያቄዎችን ከህገ-መንግስታዊ መብትነታቸው ባሻገር ፣ … ደኢህዴን

– በዴሞክራሲያዊ ብሄረተኝነትና በውጤቱ መነጽር ማጤን !

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ – መንግስት በአንድ ክልል ውስጥ የተካተቱ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች ፣ ህዝቦች የራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት አላቸው ሲል ይደነግጋል፡፡

ይህ ህገ-መንግስታዊ መብት እንደ መብት ህገ – መንግስታዊ እውቅና የተሰጠው መብት ነው፡፡ ይህ መብት የህጎች ሁሉ የበላይ በሆነው በህገ-መንግስቱ ውስጥ የሠፈረ መብት በመሆኑ መብቱን ማክበርና ማስከበር ተገቢ መሆኑን በአንድ ጫፍ መያዝ፣ በሌላኛው ጫፍ ደግሞ ለአብነት በደቡብ ውስጥ 56 ብሔሮችና ብሔረሰቦች ፣ አስራ ስምንት ዞኖች፣ ከአራት በላይ ልዩ ወረዳዎች በአጠቃላይ ከሃያ ሶስት በላይ የዞንና የልዩ ወረዳ የብሄረሰብ አስተዳደር ምክር ቤቶች መኖራቸውን እዲሁም ብሄሮች ፣ ብሄረሰቦቹም ሆኑ የብሄረሰብ ምክር ቤቶቹ ክልል ሆነው የመውጣት መብታቸው በመርህ ደረጃ ህገ – መንግስታዊ መብት መሆኑን ተረድቶ ሀላፊነት በተላበሰ መንገድ ሁኔታውን ማገናዘብ ጠቃሚ ነው፡፡

አዲስ ክልል የመሆን መብት በህገ መንግስቱ የተሰጠው በነባሩ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ሁሉም ብሄሮችና ብሄረሰቦች መሆኑን ፣ በደቡብ ክልል ውስጥ ደግሞ 56 ብሄሮችና ብሄረሰቦች መኖራቸውን ፤ ሁሉም ደግሞ በመርህ ደረጃ እኩል መብት ያላቸው መሆኑን መረዳት የዴሞክራሲያዊ ብሄረተኝነት ማሳያ ነው፡፡ አዲስ ክልል ሆኖ የመውጣት መብት እንደ መብት በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠ ቢሆንም በኢትዮጵያ ከዚህ ጉዳይ ጋር የተያያዘ በተግባር የተደገፈ ልምድ ባለመኖሩ ምክንያት በተግባር ሂደት ምን ሊያጋጥም እንደሚችል መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡

በተለይም አስራ አንድ ዞኖች ክልል እንሁን ጥያቄ ማቅረባቸው ብቻ ሳይሆን ያልጠየቁትም ቢሆን በመርህ ደረጃ ከጠየቁት እኩል መብታቸው የተጠበቀ መሆኑን ባጤነ የዴሞክራሲያዊ ብሄረተኝነት አግባብ ጉዳዮን መመርመር የኃላፊነት ስሜት መገለጫ ነው፡፡

በህገ-መንግስቱ ላይ የተቀመጠውን ʻክልል የመሆን መብትʼ በደቡብ ተጨባጭ ሁኔታ ማየት ጠቃሚ ነው፡፡ 56 ብሄሮችና ብሄረሰቦች በአንድ ክልል ውስጥ ከሃያ አራት ዓመታት በላይ አብረው መዝለቃቸውን ማስታወስ፣ የጋራ ጉዟቸውን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ማገናዘብ ያስፈልጋል፡፡ በሂደት የገነቡትን የጋራ የማንነት እሴትና ፋይዳ መረዳት ነገሩ ‘የነቶሎ ቶሎ ቤት ግረግዳው ሰምበሌጥ’ ዓይነት እንዳይሆን ይረዳል፡፡ ከሃያ አራት ዓመታት በላይ እድሜ ያለውን ህብረ- ብሄራዊ የጋራ ጉዞ ለተጓዙ 56 ብሄሮችና ብሄረሰቦች ʻክልል መሆን መብትʼ ነው ከሚለው ድንጋጌ በላይ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ብሄረተኝነትን ማዕከል ያደረገ መፍትሄ ማፈላለግ እንደሚጠይቅ ማስታዋል ይጠቅማል፡፡

ጉዳዩን ከ56ቱም ብሄሮችና ብሄረሰቦች ጥቅምና ጉዳት እንዲሁም ከአገራዊ አንድነትና ከለውጡም መንፈስ አንጻር መመርመር ይገባል፡፡ ግጭቶችንና አለመግባበቶችን አስቀድሞ በመከላከል መነጽርም ማየት ያሻል፡፡

የጥያቄውን አንድና ሁለት ጫፍ ይዞ የቀሪ ሃምሳና ከዚያ በላይ የሆኑትን ብሄርና ብሄረሰቦችን ህልውና መብት ዘንግቶ ጥሎ በማለፍ ሂሳብና በከረረ ብሄረተኝነት ተሸብቦ መንቀሳቀስ ሊያስከትለው የሚችለውን ቀውስ ከወዲሁ አሻግሮ ማየት በተለይም ለሊህቃኖች ትልቅ የቤት ስራ ሊሆን ይገባል፡፡ አንዳንድ ሊህቃን ያዛቡት ጉዳይ ህብረተሰብንም ሊያዛባና አገርንም ሊያቆረቁዝ ይችላል፡፡ ህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠውን መብት መሬት ላይ መተግበር ጥበብና ኃላፊነትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ጥያቄውን በህገ መንግስቱ ላይ በተቀመጠው መንገድ ብቻ እንደወረደ እንወጣው ቢባል አንኳን የሚያስከትለው ቀውስ ምን ሊሆን እንደሚችል አስቀድሞ መገመት ብልህነት ነው፡፡ የሀሳብ መፈክር በተግባር ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት ተገቢ ነው፡፡

በህገ-መንግስቱ ላይ የተቀመጠው ʻክልል የመሆን መብትʼ በክልሉ ውስጥ ለሚገኙ ለሁሉም የብሄረሰብ አስተዳደር ምክር ቤቶች ወይም ለ56ቱም ብሄሮችና ብህረሰቦች የተፈቀደ መብት ነው፡፡ ይህ መብት የጋራ መብት ነው ብለን ወስደን ሁሉም የብሄረሰብ አስተዳደር ምክር ቤቶች ወይም 56ቱም ብሄሮችና ብሄረሰቦች ክልል ለማቋቋም ቢንቀሳቀሱ ምን ያህል የማያባራ ውጥንቅጥ ሊፈጠር እንደሚችል በሀላፊነት ስሜት ማጤን ተገቢ ነው፡፡ 
ህገ-መንግስታዊ መብቱ የʻስለት ልጅምʼ ይሁን የʻእንጀራ ልጅʼ እንደሌለው እና ለሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች እኩል መብት የሰጠ መሆኑን በልቦና መያዝ ያሻል፡፡ ይህንን የጋራ መብት በአግባቡ ለመጠቀም ደግሞ ምክንያታዊና ዴሞክራሲያዊ ብሄረተኛ ከመሆን ባሻገር የሞራል ልእልናንም ማረጋገጥ ያስፈልጋል ፡፡ ህገ-መንግስታዊ መብቱ እንደ መብት ለሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች የተከፈተ የመብት በር መሆኑን ማስተዋል ከችግሩ መውጫውን መንገድ ለማማተርና ለማቅለል ያግዛል፡፡

ህገ-መንግስታዊ መብት ለሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች የተዘረጋ እድል እንጂ የህዝብ ቁጥራቸው አነስተኛ፣ የመሬታቸው የቆዳ ስፋትም መለስተኛ የሆኑትን ያገለለ በሚያስመስል መንገድ እና ሰፋ ያለ የህዝብ ብዛትና የመሬት ቆዳ ስፋት ላላቸው ደግሞ ልዩ ዕድል የሚሰጥ ተደርጎ የሚወሰድበት አንዳንድ አተያይም ከሚዛናዊነት አንጻር ሊስተካከል የሚገባው ነው ፡፡ መብቱ ለ5 ሚሊየኖችም ፣ ለ500 ሺህዎችም፣ ለ5 ሺህዎችም ከዚያ በታች ለሆኑትም የተፈቀደ መብት መሆኑን መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ደግሞም አንዳችን ያለአንዳችን ውበታችንም ይሁን ጉልበታችን ጎዶሎ መሆኑን ልብ ይሏል ፡፡

የህዝቦች ዕጣ ፈንታ በጋራ ራዕይና ጥረት ላይ በተመሰረተበት ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ፣ የህዝቦች ትስስር ዘመን ተሻገሪና ከአደረጃጀት ወሰንም የላቀ ሀያል የስበት ሀይል በሆነበት እውነታ ውስጥ ሆነን አንዳችን ስለሁላችንም ፣ ሁሉም ደግሞ ስለእያንዳንዱ የማይጨነቅ ከሆነ እንደማህበረሰብም ይሁን እንደ ሀገር እንዴት በጠንካራ መሰረት ላይ መቆም ይቻለናል ?

ስለሆነም በደቡብ ተጨባጭ ሁኔታ ʻ ክልል እንሁንʼ የሚሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ ስንሞክር ህገ-መንግስታዊ መብቶችን ከማክበርና ከማስከበር የተሻገረ አርቆ አሳቢነትና መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ እና አሻጋሪ መፍትሔ ማፈላለግ ወሳኝ ነው ፡፡

ʻክልል እንሁንʼ የሚሉ ጥያቄዎችን በህገ መንግስቱ ላይ እንደተቀመጠው ʻ ብሔሮችና ብሔረሰቦችʼ የራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት ተጠቅመው ይወጡት በሚለው መንገድ መሔድን ብቻ ከመረጥን ዙሪያው ገደል እንዳይሆንብን ያሰጋል፡፡ በደቡብ ውስጥ ʻ ክልል እንሁን የሚል ጥያቄ ያቀረቡ አሥራ አንድ ዞኖች “ የእገሌ ክልላዊ መንግስት” የሚል ታፔላ እየለጠፉ ደቡብ ውስጥ በትንሹ አሥራ አንድ አዳዲስ ክልሎች ተፈጠሩ ማለት ነው፡፡

የዚህን ሁኔታ ጉዳትና ጥቅም ለመለየት ደግሞ የግድ በቀውስና በውድቀት ቅርቃር ውስጥ መዘፈቅ አይጠበቅብንም፡፡ የማንኛውም ህግ ዓላማና ግብ ህዝቦችን መጥቀም ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ላይ በቀናናት የተቀመጡት መብቶች መሬት ላይ በተግባር ሲፈተሹ፣ በህዝቦች ጥቅም ሲመነዘሩ ችግር የሚያጋጥም ከሆነ ህግ መንግስቱን እሰከማሻሻል የሚሄድ መፍትሄ ማፈላለግ እንደሚገባስ የታወቀ ጉዳይ አይደለምን ? ህግ በሰዎች ፣ ለዜጎች ጥቅም ሲባል የሚደነገግ ድንጋጌ አይደለምን ?

ከህዝባችን 80 በመቶ አርሶ አደርና አርብቶ አደር በሆነበት ሁኔታ መጨነቅ የሚገባን ገጠርንና ግብርናን በማዘመንና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ላይ ወይንስ ውስኑን በጀት በሚቀራመት አዳዲስ መዋቅር ዝርጋታ ላይ? …

በጉዳዩ ላይ በአግባቡ እንምከርበት ፡፡ ተጨማሪ የወጪ ሜኖ ከመደርደር ይልቅ ለምርታማነትና ለገቢ እድገት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ በሚችሉ አማራጮች ብንዳክር ዕጣፈንታችን ያመረ ሊሆን ይችላል፡፡

ስለዚህም ʻ ክልል እንሁንʼ የሚሉ ጥያቄዎችን ከህገ-መንግስታዊ ቅቡልነታቸው ባሻገር ቀውስን በሚቀንሱ በሌሎች አማራጮች እንሞከረው ማለት ሀላፊነት ከሚሰማው ወገን የሚመነጭ አማራጭ እንጂ ህገ-መንግስታዊ መብቶችን የመደፍጠጥ ተልዕኮ እንዳለው ተደርጎ ባይታይ የተሻለ ነው ፡፡ ግልጽና ተጨባጭ ቀውስ የሚያስከትልን ጉዳይ በተነፃፃሪነት በተሻለና ቀውሱን በሚቀንስ መንገድ እናስተናግደው ማለት ሀገርንና ህዝብን የመታደጊያ መንገድን መምረጥ እንጂ ህግን መፃረር ተደርጎ ባይታይ መልካም ነው፡፡ ህጎች ደግሞ የህዝቦችን ጥቅም ማስከበሪያ መሳሪያዎች ናቸውና በቃላቱ ብቻ ሳይሆን ከቆሙለት ዓላማም አንጻር እንፈትሻቸው፡፡

ʻክልል እንሁንʼ የሚሉትን ጥያቄዎች ከህገ-መንግስታዊ ቅቡልነታቸው ባሻገር በሳይንሳዊ ጥናት በተደገፈ አግባብ ለማስተናገድ መሞከር ለምን ተመራጭ አማራጭ ይሆናል በሚለው ላይ በቅድሚያ ግልጽነት ካልተፈጠረ የጥናቱን ሂደት ፣ ግኝትና ምክረ ሀሳቦችን መቀበል ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡

ʻክልል እንሁንʼ ለሚሉ ጥያቄዎች መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መንገድ ፖለቲካዊ መፍትሄ ማፈላለግም ከሀላፊት ስሜት የሚመነጭ ነው፡፡ ደኢህዴን የ56 ብሄሮችና ብሄረሰቦች ወኪል በመሆኑ የ56ቱም ጉዳይ ያገባዋልና ክልል እንሁን የሚለው ጥያቄ ከህገ መንግስታዊ መብትነቱ ባሻገር ተጨማሪ አማራጮችን የሚፈልግ መሆኑን ደኢህዴን ስላመነበት ጥያቄው ጥናትን መሰረት አድርጎ እንዲስተናገድ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ፡፡

ጥያቄውን በህገ መንግስቱ ላይ በተቀመጠው መንገድ ብቻ እናስተናግደው ብንል ይህ አማራጭ መሬት ላይ ካሉት እውነታዎች ምን ያህል ይጣጣማል ? አማራጩስ የ56ቱንም ብሄሮችና ብሄረሰቦች ህልውናና መብት ያከበረና ሀላፊነት የተሞላበት ይሆናልን ? ተከትለው ሊመጡ የሚችሉ አካባቢያዊና ሀገራዊ ቀውሶችንስ ምን ያህል ያገናዘበ ነው? የሚሉትንና መሰል ጉዳዮችን በቅን ልቦናና በዴሞክራሲያዊ ብሄረተኝነት መንፈስ ማገናዘብ መልካም ነው ፡፡