ኢሳያስ ” በሽታ የለብኝም… የለመድኩት ወሬ ነው “

 “ እኛ ተመስገን ብለን አስራ ሁለት ሰዓት ስንተኛ፣ ውሸታሞቹ ሃያ ሶስት ሰዓት ከሃምሳ ዘጠኝ ደቂቃ እንቅልፍ የላቸውም ”

እንደተለመደው በቀላል አለባበስ አደባባይ ወጥተው “ እድለኛ ነኝ፣ በሽታ የለብኝም፣ በሽታው ወሬው ነው ” በማለት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፉወርቂ ሲወራባቸው ለነበረው ሁሉ ምላሽ ሰተዋል። ፕሬዚዳንቱ ለERI – TV ለሰላሳ ደቂቃ በሰጡት  መግለጫ ሞተዋል፣ በጠና ታመዋል፣ አይተርፉም በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ “ የለመድኩት ወሬ ነው፤ ፊትም አልሰጠሁትም ” በማለት ሲወራባቸው የነበረውን ሁሉ በዜሮ አባዝተውታል።

ኤፕሪል 28/ 2012 በአስመራ አቆጣጠር 8 pm ላይ መግለጫ የሰጡት አቶ ኢሳያስ ይህ ሁሉ ሲወራባቸው ለምን ምላሽ እንዳልሰጡ ለተጠየቁት ሲመልሱ የሰጡት ምላሽ ግልፅ ባይሆንም ባለፈው ሳምንት አገር ቤት እንዳልነበሩ አላስተባበሉም። ስሙን ካልጠቀሱት የሄዱበት አገር ሲመለሱ ጋሽ ባርካን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የፕሮጀክቶች ጉብኝት ላይ ነበሩ። አስራ አራት ሰዓት ያለማቋረጥ ጉዞ እንዳደረጉ ያመለከቱት አቶ ኢሳያስ፣ ረጅም ሰዓታት በድካም መተኛታቸውን አስረድተዋል።

ከዚያም እንቅልፉ ሳይለቃቸው የፕሬስ ፀሃፊያቸው ከሰጠቻቸው ወረቀቶች ላይ ስለሳቸው ሲወራ የነበረውን መመልከት እንደቻሉ ተናግረዋል። “ሞባይል የለኝም፤ ኢንተርኔትም አልጠቀምም ” የሚሉት አቶ ኢሳያስ የተወራውን ሁሉ እንደንፋስ እንደሚቆጥሩት አስምረውበታል። ውሸት በተወራ ቁጥር ቴሌቪዥን ላይ በመውጣት ማስተባበያ መስጠት እንደማይቻል በመጠቆም የተወራባቸውን ክፉ ወሬ ያመከኑት ፕሬዚዳንቱ “ እኛ ተመስገን ብለን አስራ ሁለት ሰዓት ስንተኛ፣ ውሸታሞቹ ሃያ ሶስት ሰዓት ከሃምሳ ዘጠኝ ደቂቃ እንቅልፍ የላቸውም ” ብለዋል።

“ አሁን ” አሉ አቶ ኢሳያስ “ አሁን ውሸቱ ሁሉ አርጅቷል። አልቋል ” የኤርትራ ህዝብም ሆነ በውጪ አገር ያሉት ተረጋግተውና  በየሚሰሙትን ሁሉ እንደማስታወቂያ ባለመቀበል ህይወታቸውን እንዲመሩ ጥሪ አቅርበዋል። እስካሁን ለምን ዘገዩ በሚል ለተጠየቁት ውሸታሞች የሚሉዋቸው  ራሳቸውን እንዲያስተካክሉ እድል ለመስጠት በማሰብ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ስለ እሳቸው መጥፎ ሲወራ አስር ዓመት በላይ መቆየቱን ያወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ መንግስት ቢቀየር ፖለቲካው አንድ አይነት መሆኑን፣ የሚቀየር ነገር ቢኖር የፖለቲካው ገጽ እንደሆነ አመላክተዋል። “ ሁልጊዜ አንድ እብድ ወይም ውሸታም በተናገረ ቁጥር የቴሌቪዥን መስኮት ላይ እየቀረቡ መናገር ቁብ እንደሌለው ደጋግመው ተናግረዋል።

አሜሪካ ውሽጥ ያለ አንድ የሽያጭ ሰራተኛ ለገበያ ለማቅረብ  ያሰበውን እቃ እንዴት እንደሚያስተዋውቅና የተጠቃሚዎችን አዕምሮ በማሳመን  እንዴት እንደሚሸጥላቸው እንደሚያስብ ሁሉ፤ ዝም ብሎ እንደሚነፍስ ንፋስ የተሰየሙት ውሸታሞች የመገናኛ ቴክኖሎጂን በተሳሳተ መንገድ በመጠቀም የስነልቦና ጦርነት ማካሄዳቸውን ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል። በዚሁ መነሻ አሉ የሚባሉት ታላላቅ አገሮች ቴክኖሎጊን ህዝብ ለማስጨነቅ፣ ለመረበሽና ለማደናገር  እንደሚጠቀሙበት አመልክተዋል።

የጠጣርና የፈሳሽ ቸኮሌት ማስታወቂያ በመመልከት የቱ ይጠቅመናል ብለው ሳያስቡ መጎምጀት እንደማይጠቅም አቶ ኢሳያስ የተናገሩት ወደፊት ብዙ ይወራልና የምትሰሙትን ሁሉ አትመኑ የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ነበር። ስምንትና ዘጠኝ ታላላቅ አገራት ውስጥ  “ ዴሞክራሲ ተብዬ ”  እንጂ እውነተኛ የሰው ልጆች መብት አንደማይከበርባቸው ያወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ አገራቱ ከወታደራዊ በጀታቸው በላይ የስለላ በጀታቸው እጅግ የናረ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደሚፈለገው እድገት ባይመዘገብም አሁን ያለው ጅምር አበረታች መሆኑን መላልሰው የጠቀሱት አቶ ኢሳያስ እንዲህ ያለው ወሬ ለምን እንደተወራባቸው፣ ምንጩ ከየት እንደሆነ፣  የሚያወሩት ሰዎች፣ ….የማወቅ ፍላገት እንዳላቸው አቶ ኢሳያስ አልሸሸጉም። አያይዘውም  የወሬው መነሻ ምክንያት ግልፅ እንዳልሆነላቸው ገልፀዋል።

በመግለጫቸው ማንንም በስምም ሆነ በድርጅት ደረጃ ጠርተው ለጉዳዩ ተጠያቂ ሳያደርጉ መግለጫ የሰጡት አቶ ኢሳያስ ህክምና ስለማድረጋቸውም ሆነ፣ አለባቸው ስለተባለው ህመም አንድም የተናገሩት ነገር የለም። የሳቸው መግለጫ እንዳበቃ በኢትዬጵያ መንግስት የሚደገፈውና ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ሰዓት ተጋርቶ ዝግጅት የሚያቀርበው ዳሃይ ኤርትራ በፕሮግራም ለኤርትራ ህዝብ ጥሪ አቅርቧል።

የፕሬዚዳንት ኢሳያስን የጤና መጓደል በተመለከተ “ አጋጣሚውን በመጠቀም አዲሲቷን ኤርትራ ለመመስረት እንነሳ ” ሲል ለወታደሮችና ለህዝቡ ጥሪ አቅርቧል።

በትናንትናው እለት የኤርትራ ጀነራሎች አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ የስራ ክፍፍል ማድረጋቸውንና የፕሬዚዳንቱ ጤንነት የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን ያስታወቀው ከፈረንሳይ የሚተላለፈው ERENA ኢሬና ራዲዮ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አደባባይ ወጥተው መግለጫ ስለመስጠታቸው  ያቀረበው  አስተያየት የለም። ዜናውንም አላስተባበለም።

ኢሬና ራዲዮ ጁላይ 15/2009 ከኤርትራ በተሰደዱ ጋዜጠኞች የተቋቋመና በሪፖርተር ዊዝ አውት ቦርደርስ የሚታገዝ፣ በኤርትራ ያለውን የፕሬስ ነፃነት ለማመጣጠን የሚሰራ ሚዲያ ነው።

” በኤርትራ የጀነራሎች አስቸኳይ ስብሰባ አደረጉ… የ”ጂ” – 15 እስረኞች …” ኢሬና

Imageሰሞኑን ፕሬዚዳንት ኢሳያስን አስመልክቶ  የሚናፈሰው ወሬ ከታማኝ የዜና ምንጮች ማስተባበያ ባይሰጥበትም በህይወት የመቆየታቸውና የመኖራቸውን  ጉዳይ የመጨረሻው ቁርጥ  መቃረቡን  የሚያመላክቱ  መረጃዎች ወጥተዋል።የኢሬና  ታማኝ ምንጮች እንደሚሉት ደግሞ ኤርትራ እንዴት ትቀጥል በሚለው ጉዳይ ጀነራሎች ስብሰባ ተቀምጠው ውሳኔ ማስተላለፋቸውን ተናግረዋል።ራዲዮ ኢሬና / ERENA / በመባል የሚታወቀው የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚ  ሚዲያ  በዛሬው እለት በየሰዓቱ በሚያስተላልፈው ዜና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ኮማ ውስጥ እንዳሉ እየገለፀ ይገኛል። 

ኢሬና በተደጋጋሚ እንደዘገበው  የኤርትራ ጀነራሎች በትናንትናው እለት አስቸኳይ ስብሰባ ተቀምጠው ታሪካዊ የተባለ ውሳኔና ሹመት  አካሂደዋል። በዚሁ  ስብሰባ ፕሬዚዳንቱ በጊዚያዊነት አገር እንዲያስተዳድሩ የሰየሙዋቸው ጀነራል ተክሌ ማንጁስ ውክልናቸውን ተነስቷል። በዚሁ ውሳኔ መሰረት  ጀነራል ስብሃት ኤፍሬም ጦሩን እንዲመሩ፣ የማነ ቻርሊ የፕሬዚዳንቱን ጽ/ቤት እንዲያስተዳድሩ፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ የማነ ገብረ አብ የፖለቲካ ጉዳዮችን በበላይነት እንዲቆጣጠሩ ሃላፊነት ሰጥቷል።

ጀነራሎቹ ቀጣዩን የኤርትራ ጉዳይ “ አገራዊ መግባባት “ በሚሰፍንበት መልኩ ለማስተቀጠል ይቻል ዘንድ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፉወርቂ ላይ ኩዴታ ለማካሄድ ሲያሴሩ ተደርሶባቸዋል በሚል በእስር ላይ ያሉት ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲፈቱ ወስኗል። የሞቱም ካሉ ለቤተሰቦቻቸው እንዲነገር ከስምምነት ላይ ተደረሷል ሲል ኢሬና አስታውቋል።

በኢትዮጵያ የስደት መንግስት ያቋቋሙትን የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚዎች ስብስብ “ የኤርትራን ነፃ አገርነት አሳልፈው የሸጡ ከዳተኞች “ በማለት የሚጠራው ይህ ራዲዮ በቅርቡ በአየር ሃይል ውስጥ ከፍተኛ ሃላፊነት ስለተሰጣቸው        የፕሬዚዳንት  ኢሳያስ ልጅ  ያለው በግልፅ የሰጠው አስተያየት የለም።

ጀነራሎቹ ያሳለፉትን ውሳኔ  ከኩዴታ ጋር ያያዘው ኢሬና ራዲዮ የፕሬዚዳንት ኢሳያስን ጤንነት አስመልክቶ ከኳታር ወደ ዱባይ መዛወራቸውን ምንጮቹን በመጥቀስ አስታውቋል። በዘገባው በተደጋጋሚ ፕሬዚዳንቱ ራሳቸውን እንደማያውቁ አመልክቷል።በማያያዝም ወደ ዱባይ የተዛወሩት ለጉበት ለውጥ መሆኑንም ተናግሯል።

ክትትል እያደረገ በየሰዓቱ መረጃ የሚያቀብለው ሬዲዮ የኢትዮጵያ መንግስት በኤርትራ ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንደሌለበት እየወተወተ ነው። ከኢትዮጵያ በኩል ምንም ዓይነት መረጃ እስካሁን ድረስ ባይሰጥም በኢትዮጵያ መንግስት ሙሉ በሙሉ የሚደገፈው  የተቃዋሚዎች ህብረት በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ በኤርትራ አስተማማኝ ሰላምና ዴሞክራሲ የሚሰፍንበት ቀን መቃረቡን የገለፀው ህዝቡን በመማፀን ነው።

ቀደም ሲል ለነፃነት የተደረገውን መስዋዕትነትና የትግሉን ሰማዕታት ገድል በማስታወስ የኤርትራ ህዝብ የነፃነት ፍራውን የሚያጣጥምበት ወቅት እንደሚያጣጥም አመልክቷል። ይፋ ካልወጡ መረጃዎች ለመረዳት እንደተቻለው ኢህአዴግ የኤርትራን ቀጣይ እጣ ፈንታ በተመለከተ የቀይ ባህር ጉዳይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየመከረ እንደሆነ ተሰምቷል። የኢህአዴግ ርምጃ እንግዳ ባይሆንም በስውር የሚደረገው ግንኙነት የኤርትራን ጀነራሎች የያዘ ስለመሆኑ የታወቀ ነገር የለም።

የፕሬዚዳንቱ ጉዳይ እልባት ባላገኘበት በአሁኑ ሰዓት በኤርትራ ውስጥ ሊፈጠር የሚችለው የፖለቲካ ለውጥ፣ ከክልሉ  ልዩ ጸባይና  በሌሎች ተመሳሳይ የፖለቲካ ትግል አኳያ  ሁሉንም ወገኖች ያጓጓ መሆኑ አብዛኞች የሚስማሙበት ቢሆንም  ኢሳያስን አስመልክቶ ከገለልተኛ ወገን የተሰጠ ነገር የለም።

ከማስታወሻዬ

የመኪና  ሌቦች  ድራማ  ሰማሁና  ሶማሌ ተራና  አብነት  ጆስሃንሰን  ቅኝት  ካደረኩ  በሁዋላ  የጻፍኩትን ጽሁፍ  ዛሬ ስመለከተው  ገረመኝ። ምክንያቱም  በየመንገዱ የቆሙ  መኪኖች ወሳጅ  ማጣታቸውን  ለነዛ  ቀመኞጭ  ማን ይንጋቸው !!
ማስታወሻሪፖርተር ጋዜጣ ስሰራ በነበርኩበት ወቅት ደላላው አምድም ላይ እጽፍ ነበር።አምዱ ላይ ስም መጻፍ ክልክል በመሆኑ ጽሁፌም እኔም በነጻነት አውሮፓ ተገናኘን።በሪፖርተር ጋዜጣ የታተመ መሆኑን እየገለጽኩ መጠነኛ ማዳበሪያ አክዬ በማስታወሻዬ ላይ አኖርኩት 

                                                                አወራራጆች

… ብልት አውጪዎች፣ የመኪና የሆድ እቃ አውላቂዎች፣ የሚያስፈሩ፣ ደረታቸው ሰፋፊ፣ ጡንቻቸው ትልልቅ፣ ቁመታቸው ረጃጅም የመኪና ቀዶ ጥገናአድራጊዎች፡፡በላቾች!! 

የመኪናን የሆድ እቃ፣ የመኪናን ማጋጌጫ፣ የመኪናን ዓይኖች በደቂቃዎች ውስጥ ከቆርቆሮ የመለያየት አቅም ያላቸው፣ መኪናን እርቃን የሚያስቀሩ፣ ሞተር ለሁለት አንጠልጥለው የሚያወርዱ በስፖርት ዳብረው፣ የበላችነት ኮርስ ወስደው፣ በቅርጫ የሚተዳደሩ የለሊት ጭልፊቶች፣ የቀን ድብርታሞች … 

ደላላው አምበርብር ስለበላቾች የሰማው  ከባልንጀራው ጋር ሶማሌ ተራ፣አብነት አካባቢና አንድ ትልቅ የተዘጋ ግቢ ውስጥ ተዛውሮ ስላለው የመኪና እቃ ገበያ ግብይት በተመለከተበት ወቅት ነው፡፡የብለታ ድራማና የበላቾች መደራደሪያ አስገረመው።“አሁን እኔም ደላላ እባላለሁ?”ሲል ጠየቀ።ደላላው አምበርብር የድለላ አቅሙን ማሳደግ ቢገባውም በብለታ ደረጃ እንዳልሆነ ግን ወዲያው አምኗል።የመኪና አወራራጆች የስራ ክፍፍልና መለያ አላቸው። 

“ጉዳተኛ ” የሚባሉት መኪናቸውን በቆሙበት ተዘርፈው የራሳቸውን እቃ ለመግዛት እቃው ያለበት ሰፈር ለድርድር፣ ለልመናና ለምልጃ የሚሄዱ ናቸው፡፡ “ጋቡ “ዎች የመኪናውን ጋቢና የሚከፍቱ”የሚበረግዱ ” ሰርሳሪዎች ናቸው፡፡ “ቂማ ” ስትራቴጂ የሚነደፍበት ጊዜ ሲሆን፣ ለሊት ለሥራ የሰው አጥር የሚዘሉ፣ ጎዳና የሚያስሱ በላቾች ተኝተው ውለው አመሻሽ ላይ የሥራ እቅድ ለማውጣት የሚመርጡት ጊዜ ነው፡፡ ደላላው አምበርብር በደረሰው መረጃ መሠረት መኪና “ከነገባው ” ከተሰራ (እንዳለ ከተወሰደ ) “ዝግ ተዘጋ ” ይባልና በላቾቹ እንደ አራስ በዝግ ለሳምንታት ይቀለባሉ፡፡ በዝግ ይዝናናሉ፣ይጠጣሉ፣ ሁሉንም ነገር ያደርጋሉ፡፡ ይጨሳሉ፣ ይጫጫሳሉ . . . 

መኪና “የሚያጫውቱ ” ዋና በላቾች ቃፊር አላቸው፡፡ ቃፊሮች “ገበያ ተኮር” አሰሳ ያካሂዳሉ፡፡ በግቢ ውስጥ የቆሙ መኪኖችን የዓይን ራጂ (X-Ray) ያነሳሉ፡፡ ቃፊሮቹ መረጃቸውን አጠናክረው ለበላቾች ይሰጣሉ፡፡ አምበርብር ምንተስኖት ያሰባሰበው መረጃ በርካታ ነው፡፡ የብለታ ሥራ በትዕዛዝ እንደሚሰራም አውቋል፡፡ 

የመኪና ስርቆት በትዕዛዝ ይሰራል፡፡ ትዕዛዝ በተዋረድ መጥቶ እንዲህ ያለ መኪና፣ እንዲህ ያለ ዕቃ፣ ይምጣ ይባላል፡፡ ዋጋውና የመኪናው ሞዴል አስቀድሞ ይነገራል፡፡ የሚፈለገው የተሽከርካሪ ዓይነትና እቃ በሞባይል ፎቶ ተነስቶ ይቀርባል፡፡ ቃፊሮች በተሰጣቸው የስዕል መረጃ መሰረት ተፈላጊውን እቃ የያዘ ወይም ተፈላጊው እቃ ያለበትን ተሽከርካሪ ያድናሉ፡፡ አግኝተው ሪፖርት ያቀርባሉ፡፡ በሪፖርቱ መሠረት በላቾች እቅድ ይነድፋሉ፡፡ትዕዛዙን አሳክተው በድል ይመለሳሉ፡፡ ባይመለሱም በመንገድ በድንገት ለሚገጥማቸው ችግር ራስን የመከላከል አካላዊ ድርጅታቸውን በቁሳዊ አቅማቸው አስደግፈው እንዳመጣጡ ይመልሱታል።

በሰላም እንዳያድሩ የተፈረደባቸው “ተጎጂዎች”የለፉበትን በሰዓት ልዩነት ተነጥቀው ባዶ ይቀራሉ።በሰላም ተመስገን ብለው ከተኙበት ሲነሱ መኪናቸውን ያጡ፣አገር አማን ብለው መኪናቸውን ዘንድ ሲደርሱ አይናቸውን ማመን አቅቷቸው አሁን ድረስ ህልሙ ያልለቀቃቸው፣የጠፋባቸውን መኪና ፍለጋ በእግር መንገድ ጀምረው አሁን ድረስ ጉዞ ያላቋረጡ እግረኞች፣…..ቤት ይቁጠራቸው።የቀናቸውም ወደ ማገገሚያ ይወርዳሉ።   

“ማገገሚያ”የመኪና እቃ የተሰረቀባቸው እቃቸውን የሚያገኙበት ሰፈር ነው፡፡ ተሰራቂ (ጉዳተኛ ) ከራሱ መኪና የተሰረቀውን እቃ ለመግዛት ሶማሌ ተራ ወደ አሜሪካን ግቢ መግቢያ ጎራ ሲል እንደ ሌባ የሚሸማቀቀው ራሱ ነው፡፡ ደላላው አምበርብር ያስገረመው ጉዳይ ይህ ነበር፡፡ 

አንድ ወዳጄ በሰላም መኪናቸውን ግቢያቸው አስገብተው አቁመው ይተኛሉ፡፡ እሳቸው ሲተኙ የነጋላቸው መኪናዋን ሲበልቷት አድረው ባዶ ያስቀሯታል፡፡ የተሰረቀው እቃ አንድ ብሎን ሳይጎድለው የሚገኝበት ሰፈር ስለሚታወቅ አብረን አቀናን፡፡ እቃው ሙሉ በሙሉ ተገኘ፡፡ እቃው እንዳለ የተናገሩት አንድም መደናገጥ አይታይባቸውም፡፡ 

የበላቾቹና የተበለተው እቃ፣ አንዳንዴም ሙሉ መኪና ተሰርቆ የሚገባበት ሰፈር ይታወቃል፡፡ሰፈሩ ፈረሰ ሲባል ተጠናክሮ የሚገነባ ነው፡፡ ተዘጋ ሲባል ቅርንጫፍ ቢሮዎችን አጠናክሮ በመክፈት የአገልግሎት ሥራውን ያሰፋል፡፡ ባለሟሎቹ በቁጥጥር ስር ዋሉ ሲባል እንደ አሸን ይፈላሉ፡፡ በግልጽ በአደባባይ ለሰረቁት እቃ የባለንብረቱን ኪስ እንደገና ያራቁታል፡፡ ደላላው አምበርብር ተገረመ፡፡ “እንዲህ ዓይነት አዲስ አበባ “ሲል ተነፈሰ፡፡ “አይናውጣዎች ” ሲል ተራገመ፡፡ የወጣትነት፣ የጉርምስና ጊዜውን ናፈቀ፡፡ በሽመል ቀልጥሞ ሊጥላቸው፡፡ 

ነገሩ ይገርማል፡፡ በየጊዜው የሚሰረቅ የመኪና ሆድ እቃ በአደባባይ ይሸጣል፡፡ ክሪክ፣ ባትሪ፣ ጌጅ፣ ሰዓት፣ ዳሽቦርድ፣ ጎማ፣ መብራት፣ መስተዋት፣ ስፖኪዮ፣ ቴፕ፣ ዲናሞ፣ ሞተሪኖ፣ የቴስታታ መዝጊያ፣የዝናብ መጥረጊያ፣ የተለያዩ ጎሚኒዎች . . . ተሰቅለው ይሸጣሉ፡፡ እቃዎቹ ላይ ያልተለጠፈው የተሰረቁበት ቦታና የመኪናዋ ታርጋ ብቻ ነው፡፡ ህጋዊ ሱቅ ከፍተው ህገወጥ እቃ ይሸጣሉ . . . “ደላላውአምበርብር እንቅልፍም የለኝ ከሰው አልጣላ ” ሲል የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድቶ ተናገረ፡፡ 

አምበርብር ከማንጠግቦሽ ጋር እየሄደ ያጋጠመውን አስታወሰ፡፡ የጋራዥ ሰራተኛ ቱታ ለብሰው መንገድ ላይ የሚቆሙ አሉ፡፡“ ሁጳዎች ”ይባላሉ፡፡ በሰላም የሚሄደውን መኪና እግር ስር ችግር እንዳለው አድርገው ምልክት ይሰጣሉ፡፡ ምልክት ያየው አሽከርካሪ ያቆማል፡፡ በተለይ ሴት አሽከርካሪዎች ለዚህኛው ሥራ ይመረጣሉ፡፡ መኪናው ከቆመ በኋላ “መኪናው እግር ተገንጥሎ ሊሄድ ነው ” በማለት የመኪናውን መሪ ወደ አንድ በኩል ይጨርሱና በጡንቸኛው ክንዳቸው ጎማውን እያወዛወዙ ያሳያሉ፡፡ ባለመኪናዋ ደንግጣ ይሰራልኝ ትላለች፡፡ ያልተበላሸው መኪና ይሰራ ይባላል፡፡ ክሪክ፣ የጎማ መፍቻ፣የመተኛ ምንጣፍ እያሉ መኪናውን ይበረብራሉ፡፡ በመጨረሻም ለሙከራ ብለው እየነዱ የአሽከርካሪዋን ቦርሳ ይበረብሩና ባዶ ያስቀራሉ፡፡ አንዷ አሽከርካሪ በእንዲህ መልኩ ተዘርፋ፣ መዘረፏን ካወቀች በኋላ ደንግጣ ለከበቡዋት ሰዎች የሆነችውን ስትተርክ ነበር፡፡

ያዲሳባ ሌብነት አድጓል።መኪና እየሄደም አስቁመው የወስዳሉ።ሲቆምም ይሰርቃሉ።የቀናው አላርም “የደህንነት ደወል” ነጋዴ ነው።አስመጪዎቹ ደግሞ እነ እንትና ናቸው።ህጉም፣ጥበቃውም እንዲላላ የተደረገው ላስመጪዎቹ ሲባል ስለመሆኑ አምበርብር መረጃ የለውም።  

ሰርቆና ተሰርቆ መለያየት ያለ ነው፡፡ ከተሰረቁ በኋላ የራስን እቃ እንደገና ለመግዛት መለመን ሞት ነው፡፡ ሰው የራሱን እቃ እንዴት በሺህ የሚቆጠር ብር አውጥቶ ይገዛል ? ደላላው አምበርብርጠየቀ፡፡ ሰው የራሱን ንብረት ለመግዛት ከተስማማ በኋላ እቃው ሲመጣለት እንኳን እንዴት ወንድነቱ አይመጣም ? ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ ወንድ ጠፋ፣ ሲዘረፍ የሚናገር የለም፡፡ የዘረፈውን አይቶ ዝም ማለት ተለመደ፡፡ ለዘራፊዎች በተዘዋዋሪ ፈቃድ የሰጡት “ጉዳተኞች ” ናቸው፡፡ ተጎድተውም ዝም የሚሉ ዜጎች እየበዙ ናቸው፡፡ ሰው ንብረቱን የዘረፈውን ሰው አይቶ እንዴት ዝም ይላል ? የሰው ልጅ ወኔከ ዳው፡፡ ወኔ የሌላቸው እየበዙ ናቸው፡፡ “ወኔ የሌላቸው ነዋሪም አኗኗሪም አይሆኑም፡፡ ለመኖር ሞራል ያስፈልጋል፡፡ አኗኗሪ ለመሆን ደግሞ ልብ ይጠይቃል፡፡ ልብ ስልህ ይገባሃል ?” በማለት ማንጠግቦሽደጋግማ ትጠይቃለች፡፡ ልብ የለም፡፡ ልብ ያላቸው ጠፉ፡፡ ለንብረታቸው የሚቆረቆሩ ታጡ፡፡ ንብረታቸው ለራሳቸው ሲሸጥ እልል ብለው፣ ለምነው፣ ተቅለስልሰው፣ አሸርግደው፣ ተዋርደው፣ አልቅሰው የሚገበያዩትን ደላላው ረገመ፡፡ ወዳጁንም ረገማቸው፡፡ “አሁን የእኔ አሟሟት አሟሟት ነው ወይ . . . ” የሚለው ዘፈን ትዝ አለውና መረጠላቸው፡፡ 

ቀበኞች በዝተዋል፡፡ የቀበኞቹ መብዛት ሳይሆን ለቀበኞቹ ባሪያ ሆኖ መኖር አንበርብር ምንተስኖትን አስደንግጦታል፡፡ ቀበኞች ህግ አይፈሩም፡፡ ቀበኞች ፖሊስ አይፈሩም፡፡ ቀበኞች የጎዱትን ሰውአይፈሩም፡፡ ቀበኞች ጨለማ አይፈሩም፡፡ ቀበኞች የሚፈሩት ፀሐይ ብቻ ነው፡፡ ቀን ይተኛሉ፡፡ አመሻሽ ላይ እቅድ ይነድፋሉ፡፡ በደንብ ሲመሽ አፈፃፀማቸውን ያቀላጥፋሉ፡፡ በሌላኛው ቀን የእቅዳቸውን አፈፃፀም ይገመግማሉ፡፡

አምበርብር ምንተስኖት በላቾችም ግምገማ እንደሚያደርጉ ሰምቷል፡፡ ግምገማ የሌለበት የለም፡፡ በግምገማ መታደስ አለ፡፡ የቀማኞች መታደስ ምን ይሆን ? ደላላው ጠየቀ፡፡ የሰው ንብረት ለመዝረፍ፣የሰው አጥር ግቢ ለመዝለል፣ የሰው እቃ በፍጥነት ስለመስረቅ፣ የሰው እቃ ሰርቆ ስለመሮጥ፣ ድንገት ችግር ቢፈጠር ስለሚወሰድ እርምጃ ቀበኞች ግምገማ ያካሂዳሉ፡፡ የስርቆት ሪከርድ ለማሻሻል ስልት ይቀየራል፡፡ በዚህ መልክ የተጎዳችሁ ቤት ይቁጠራችሁ፡፡ ደላላው አምበርብር ከጉዳዩ ነፃ ነው፡፡ ችግሩ አይመለከተውም፡፡ ችግሩ ባይመለከተውም በሰማው ግን አዝኗል፡፡ በተመለከተው ተገርሟል፡፡የሰማውንና ያየውን ለማንጠግቦሽ ማጫወት አለበት፡፡ የራሳችሁን እቃ በልመና የምትገዙ ከፍርሃታችሁ ንቁ፡፡ንብረታችሁን በልመና ለማስመለስ የምትቅለሰለሱ ተገረዙ። ሰላም ሁኑ፡፡ ሰላም !