Category Archives: Socity / ማህበራዊ

11 ልጆች ከወለዱ በኋላ ወደ በረሃ ትግል የገቡት እናት

By አለማየሁ

11 ልጆች ከወለዱ በኋላ ወደ በረሃ ትግል የገቡት እናት

በኢትዮጵያ ሴቶች ትግል ውስጥ ስማቸው በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ጥቂት ሴቶች አንዷ ናቸው፡፡ በደርግ ዘመን 11 ልጆች ከወለዱ በኋላ ልጆቻቻን ጥለው ለትግል ወደ በረሃ ገብተዋል፡፡ የኢህአፓ ሠራዊት አባል በመሆንም ለ17 አመታት ታግለዋል፡፡ ከልጆቻቸው ይልቅ ለህዝብ መብት መታገልን የመረጡት እኚህ እናት፤ ከ42 አመታት የበረሃ ትግልና የስደት ኑሮ በኋላ ከሰሞኑ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ልጆቻቸውን አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የ87 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት ወ/ሮ ሙሉነሽ አደራ፤ ስለ ትግል ህይወታቸው ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡

– ለ17 ዓመት የኢህአፓ ሠራዊት አባል ሆኜ በበረሃ ታግያለሁ

– ላለፉት 42 ዓመታት ከልጆቼ ጋር አልተገናኘሁም

– ትግል ያሰለጠንኳቸው ልጆቼ ናቸው አሜሪካ የወሰዱኝ

– አሁን የሚያስፈልገው ወደ ሰውነት ከፍታ መውጣት ነው

እስቲ ከውልደትዎና እድገትዎ እንጀምር —-

እዚሁ አዲስ አበባ ነው የተወለድኩት:: እድገቴ ደግሞ አብዛኛውን አዲስ አበባ፣ ለተወሰነ ጊዜ ደግሞ ጅማ አድጌያለሁ፡፡ ስራ የጀመርኩት የቼኮዝሎቫኪያዎች ጥይት ፋብሪካ ውስጥ ነው:: እርሳስ፣ ጥይትና ባሩድን አገጣጥሞ ጥርት አድርጐ የሚያወጣ ማሽን ላይ ነበር የምሠራው፡፡ እዚህ ማሽን ላይ ሦስት አመት ከአምስት ወር ሠርቻለሁ:: እዚያ እየሠራሁ ሳለ አንበሳ አውቶቡስ ሴቶች ይቀጥራል ሲባል፣ እዚያ አመልክቼ በ60 ብር ደመወዝ ተቀጠርኩ:: እንግዲህ አንበሳ አውቶቡስ መስሪያ ቤት 20 አመት ሠርቻለሁ፡፡ 10 አመት በገንዘብ ተቀባይነት (ቲኬት ሽያጭ)፣ ቀሪውን አስር ዓመት ግን በቢሮ ውስጥ ነበር የሠራሁት፡፡

አንበሳ አውቶቡስ እያሉ፣ ሠራተኞችን ለፖለቲካ ትግል ያነሳሱ ነበር ይባላል፡፡ ስለሱ እስቲ ይንገሩን?

አዎ! በአንበሳ አውቶቡስ ውስጥ ማህበር መስርተን ነበር፡፡ እንደ መረዳጃ ማህበር ነበር የመሠረትነው፡፡ ማህበሩ ሠራተኞች ሲታመሙ የምንረዳዳበት፣ ሠራተኞች ያለ አግባብ ከስራ ሲባረሩብን በጋራ የምንጮህበት ነበር፡፡ የሹፌሮች መረዳጃ ማህበር ብለን ነበር የመሰረትነው፡፡ በኋላ በ1957 ዓ.ም የሠራተኞች አንድነት ማህበር ተቋቁሟልና እዚያ እንድትገቡ ተባልን፡፡ እኛም የመሰረትነውን ማህበር እንደያዝን የሠራተኞች አንድነት ማህበሩን ተቀላቀልን፡፡ በዚህ ማህበር በኩል የደመወዝ ጉዳይ፣ የሠራተኞች መባረር ሲያጋጥም ድምፃችንን እናሰማለን፡፡ በዚህ የመብት ማስከበር እንቅስቃሴ፣ ከጃንሆይ ፊት ቀርበን ድምፃችንን እስከ ማሰማት ደርሰን ነበር፡፡ በዚህ የሠራተኛውን መብት የማስከበር እንቅስቃሴያችን ከስራቸው የተባረሩትን ተሟግተን ወደ ስራቸው የማስመለስ፣ የማስመለስ ጥረቱ ካልተሳካልን ደግሞ በሌሎች መስሪያ ቤቶች የማስቀጠር እንቅስቃሴ እናደርግ ነበር፡፡ ከፍተኛ የመተባበር መንፈስ የነበረው ማህበር ነው፡፡ ከ1951 ዓ.ም ጀምሮ እኔ እስከለቀቅሁበት 1968 ዓ.ም ድረስ ማህበራችን ጠንካራ ነበር፡፡

እርስዎ በሴቶች ትግል ውስጥ የነበርዎት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ብዙ ጊዜ ይጠቀሳል፡፡ እስቲ ስለዚያ ትግል ያስታውሱን?

እንደውም ድርብ ታጋይ ነበር የሚሉኝ:: የሴቶች ትግልን በፊት ለፊት የጀመርነው በአንድ አጋጣሚ ነው፡፡ አንበሳ አውቶቡስ ውስጥ ስንሰራ በመውለዳችን ከስራ ያባርሩን ነበር:: ሴቶች እየወለዱ አስቸገሩ ሁሉ ተብለናል፡፡ ድርጅቱ ከሠረ ብለው ነበር በአንድ ላይ ከስራ ያሰናበቱን:: እንደውም በ1968 ዓ.ም በዚህ ጉዳይ ላይ ቲያትር ሁሉ ሠርተንበት ነበር፡፡ ሴቶች ወለዱ ተብለን ነው እንግዲህ ከአንበሳ አውቶቡስ ተጠራርገን እንድንወጣ የተፈረደብን፡፡

ምን ያህል ነበራችሁ የተባረራችሁት?

ከ15 በላይ እንሆናለን፡፡ ሁላችንም እየወለዳችሁ ስራ በድላችኋል በሚል ነበር የተባረርነው፡፡

እናንተ ታዲያ ምን አማራጭ ተከተላችሁ?

ወዲያው የድርጅቱ አስተዳዳሪ፣ እኛን አስወጥተው፣ የራሳቸውን ዘመዶች ሊቀጥሩ ነው የሚል ክስ ነበር ለበላይ ኃላፊዎች ያቀረብነው:: ኃላፊው አቶ ተፈሪ ሻረው ነበሩ:: እሣቸው፤ “ልጆቼ እኔ ምን ላድርግላችሁ፣ መስሪያ ቤቱ ከሠረ ነው የሚሉን፤ መስሪያ ቤቱ እንዲከስር ማድረግ የለብኝም” የሚል ምላሽ ሰጡን:: እኛም በዚህ ሳናበቃ በወቅቱ የሀገር ግዛት ሚኒስትር የነበሩት ራስ አበበ አረጋይ ጋ ሄድንና አቤቱታችንን አቀረብን፡፡ ከብዙ ምልልስ በኋላ ነው እሣቸው ጋ የደረስነው፡፡ እሣቸውም ቀጥታ እኔን “ልጆች አሉሽ?” የሚል ጥያቄ ነው ያቀረቡልኝ፡፡ አዎ ስላቸው፤ “ታዲያ ችግሩ እሱ አይደል” የሚል መልስ ነው የሰጡን፡፡ በኋላም በቃ የ6 ወር ደመወዝ እየሰጣችኋቸው አሰናብቷቸው የሚል ትዕዛዝ ተሰጠልን፡፡ መስሪያ ቤቱም የ6 ወር ደመወዝ እንዲከፍለን ተደረገ፡፡ ያንን ብር ይዘን ወጣን፡፡ በኋላ አመለወርቅ ኢዴኤ የምትባል ጓደኛዬ ነበረች፡፡ አሁን እንኳ እሷን አገኛለሁ ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር የመጣሁት፡፡ መሞቷን ሰምቼ በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ እሷ ለራስ አበበ አረጋይ፣ እኔ ደግሞ ለራስ ስዩም አመለከትን፡፡ በኋላ ሁላችንም ወደ ስራችን መመለስ ችለናል፡፡ ለመመለስ ግን ከፍተኛ ትግል ነበር ያደረግነው፡፡ እንዲህ ያለ ትግል ነው ስናደርግ የነበረው፡፡

ሠላማዊ ሠልፍም አስተባብረው ይመሩ ነበር ይባላል?

አዎ፤ በ1968 “ለእኩል ስራ እኩል ክፍያ” የሚል መፈክር ይዘን ወጥተን ነበር:: “ልጃገረዶች ት/ቤት ይግቡ፣ ይማሩ” የሚል ሠልፍም አካሂደናል:: “ለእኩል ስራ እኩል ክፍያ” የሚለውን ንቅናቄ የጀመርንበት መነሻ፣ ወንድና ሴት ሠራተኞች እኩል እየሠሩ ክፍያ ላይ ግን ከወንዶቹ በግማሽ ያህል ያንሱ ነበር፡፡ ወንዱ 4 ብር ሲከፈለው፣ ሴቷ 2 ብር ነበር የሚከፈላት:: ይሄ ከፍተኛ በደል ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ በወቅቱ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ገና ታዳጊ ልጃገረዶች መማር ሲገባቸው፣ ቡና ለቀማ ተቀጥረው ይሰሩ ነበር:: አሠሪውም እነዚህን ልጃገረዶች በአነስተኛ ዋጋ እየቀጠረ፣ ጉልበታቸውን ይበዘብዝ ነበር:: ይሄ ለምን ይሆናል በሚል ነበር ሠላማዊ ሠልፍ የወጣነው፡፡

ይህ ተቃውሟችሁና ጥያቄያችሁ ምን ምላሽ አገኘ?

በወቅቱ ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም፣ በኛ ላይ ጥርስ መንከስ ጀምሮ ነበር፡፡ “የማትረባ ፍየል ዘጠኝ ትወልዳለች፤ ልጆቿም ያልቃሉ እሷም ትሞታለች” ተባለ፡፡ ወዲያው የብርሃንና ሠላም ማተሚያ ሠራተኞች ኃላፊ የነበረችውንና ልትወልድ 15 ቀን ብቻ የቀራትን ዳሮ ነጋሽን ገደለ፡፡ ከሷ ጋር ስምንት የብርሃንና ሠላም ሠራተኞች ናቸው ተገድለው በአንድ ቀን የተቀበሩት፡፡ ያኔ እኔም ይህ እስኪገጥመኝ ቆሜ መጠበቅ የለብኝም ብዬ ነው፣ ወደ በረሃ ትግል የገባሁት፡፡ ዝም ብዬ ከምሞት አንድ ለአንድ ተናንቄ ለምን አልሞትም ብዬ ወደ ትግል ገባሁ:: እኔ ወደ አሲምባ 11 ልጆቼን ትቼ የገባሁት በዚህ መነሻ ነበር፡፡

ወደ አሲምባ ለትግል የገቡት ከእነማን ጋር ነበር?

ከሴቶች ጋር ነበር ወደ ትግል የገባሁት፡፡ እነ ፀዳለ፣ ሠላማዊት ዳዊት፣ ትርሲት (የተፈሪ በንቲ ልጅ)፣ ንግስት፣ ፍቅርተ ገ/ማርያም፣ ፀዳለ (የብርሃኑ እጅጉ እህት) እና ሌሎችም አብረውኝ ነበሩ፡፡

ልጆችዎን ትተው በረሃ ለመግባት መወሰን አያስቸግርም?

ብኖርም እኮ አላሳድጋቸውም ነበር፡፡ ዳሮ ነጋሽ እኮ ልጆቿን አላሳደገችም፡፡ ህፃናት ልጆቿን ሜዳ ላይ በትና ነው የሞተችው፡፡ እኔ ብሞት ግድ የለኝም ነበር፣ ነገር ግን ለምን ታግዬ አልሞትም ብዬ ነው ልጆቼን ትቼ በረሃ የገባሁት፡፡ እኔ በረሃ ስገባ አንደኛዋ ልጄ በደርግ ተገድላለች፡፡ የ17 አመት ታዳጊ ተማሪ ነበረች፡፡ “የማትረባ ፍየል ዘጠኝ ትወልዳለች ልጆቿም ያልቃሉ እሷም ትሞታለች” ብሎ ስም ዝርዝራችንን ደርግ አውጥቶ ነበር፡፡ ስለዚህ ልጆቼን ትቼ ወደ ትግል ከመውጣት ውጪ ምንም አማራጭ አልነበረኝም፡፡

የአሲምባ ቆይታዎስ ምን ይመስላል?

አሲምባ አንድ አመት ነበር የቆየነው፡፡ ከህወሓቶች ጋር በምንነጋገርበት ወቅት “እኛ ለትግራይ ነፃነት ነው የምንታገለው፤ እናንተ አማራ ናችሁ፣ ለአማራ ነው የምትታገሉት” በማለት “መሬታችንን ለቃችሁ ውጡ” አሉን፡፡ በኛ ላይ ጦርነት ከፈቱብን፡፡ ወያኔዎች ሁልጊዜ ጦርነት የሚከፍቱት ህዝቡ ውስጥ፣ ት/ቤት ውስጥ፣ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነው ነው:: እኛ ለእነሱ የመልስ ተኩስ ስንሰጥ የምናጠፋው የተከለሉበትን አካል እየሆነ ተቸገርን:: በመጨረሻ እኛ መሬቱን ለቀንላቸው ወደ በጌምድር ወጣን፡፡ በዚያም ትግላችንን ቀጠልን::

እርስዎ በየትኞቹ ጦርነቶች ላይ ነው የተሳተፉት?

በዚህ ቦታ ማለት አልችልም፡፡ ለ17 አመታት በረሃ ላይ ቆይቻለሁ፡፡ በተመደብኩበት ቦታ ሁሉ ተሳትፎ አድርጌያለሁ፡፡ ከ1969 እስከ 1981 ዓ.ም ድረስ የኢህአፓ ሠራዊት አባል ሆኜ በበረሃ ቆይቻለሁ፡፡

ወደ በረሃ ሲገቡ የመጨረሻው ልጅዎ እድሜው ስንት ነበር?

አንድ ዓመት ከ7 ወር የሆነውን ልጄን ነው ትቼ የሄድኩት፡፡

ከዚያ በኋላ ከልጆችዎ ጋር ተገናኝተዋል?

ላለፉት 42 አመታት አልተገናኘንም:: ምክንያቱም ደርግ ሲወድቅ ስልጣን የያዘው ወያኔ ነው፡፡ ወያኔ ባለበት እንዴት ወደዚህ ሀገር እመጣለሁ? እንደውም ልጆቼ እንዳይታወቁብኝና ጥቃት እንዳይፈፀምባቸው በሚል በምንም መንገድ አላገኛቸውም ነበር፡፡

እርስዎ ወደ አሜሪካ እንዴት ሊሄዱ ቻሉ?

ያሳደግኋቸው፣ ትግል ያሰለጠንኳቸው ልጆቼ ናቸው መንገዱን አመቻችተው የወሰዱኝ:: በነገራችን ላይ የኢህአፓ ህዋስ በበርካታ የአለም ሀገራት አለ:: አውስትራሊያ፣ ኔዘርላንድ፣ ስዊዘርላንድ፣ ጀርመን፣ አሜሪካ የመሳሰሉ ሀገራት የኢህአፓ ታጋዮችን የተቀበሉ ሀገራት ናቸው፡፡ ቀድመውኝ የወጡ ልጆቼ የምላቸው የትግል አጋሮቼ ናቸው የተቀበሉኝ፡፡

በ42 አመታት የበረሃና የስደት ቆይታዎ ልጆችዎን ለማግኘት ምንም ጥረት አላደረጉም?

የልጆቼ ደህንነት ያሳስበኝ ነበር፡፡ ስለዚህ እኔ የእነሱ እናት እንደሆንኩ እንዲታወቅ አልፈልግም ነበር፡፡ አሁን‘ኮ ዶ/ር ዐቢይ ሲመጣ ነው የመጣሁት::

ከእነዚህ አመታት በኋላ አሁን ልጆችዎን ማግኘት ምን ዓይነት ስሜት ይፈጥራል?

በጣም አስደሳች ነው፡፡ የሞቱትም ሞተው ያሉትም ኖረው አግኝቻቸዋለሁ፡፡ ሶስት ልጆች ሞተውብኛል፡፡ አልቅሼ ለመቅበር እንኳ አልታደልኩም፡፡ አሁን ስምንቱ በህይወት አሉ:: ሶስቱ እኔ ጋ አሜሪካ መጥተዋል፡፡ አንዱ ጀርመን ነው ያለው፡፡ ቀሪዎቹ አራቱ እዚህ ነው ያሉት:: አላሳደገችንም ብለው አኩርፈው ሊያገኙኝ ያልፈለጉ ልጆቼም አሉ፡፡ አናውቃትም፤ አላሳደገችንም ብለው አኩርፈው ሰላም እንኳ አላሉኝም፡፡ እኔም ያሉበት ቦታ ሄጄ ሠላም እንኳ እንዳልላቸው ፈርቼ ቀረሁ፡፡ በዚህ መልኩ ያጣኋቸውም ልጆቼ አሉ፡፡

ባለፉት ከ50 አመታት በላይ እልህ አስጨራሽ ትግል ተደርጐ አሁን የለውጥ ተስፋ መጥቷል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ የታገልንለት አላማ ግቡን እየመታ ነው ብለው ያምናሉ?

ትልቅ ተስፋ ነው የተፈጠረው፡፡ ግን ህዝቡ ደግሞ አሁን ራሱን መግዛት፣ ራሱን መቆጣጠር፣ አርቆ ማስተዋል አለበት፡፡ ሰው ራሱን ይመልከት፤ እኔ ለሀገሬ ምን ላድርግላት ማለት አለበት፡፡ ይህ የለውጥ ተስፋ ፍሬያማ የሚሆነው ወደዚህ መንፈስ ካመራን ብቻ ነው:: ዋናው ነገር ሰው፣ ሌላው ሰው ላይ ከማተኮር ይልቅ ራሱ ላይ ያተኩር፡፡ በ42 ዓመት ውስጥ የተፈጠረው ትውልድ ማድረግ ያለበት፤ ሰው ለመሆን መሞከር ነው፡፡ በብሔር ጐሣና ዘር መከፋፈል ከሰው በታች መውረድ ነው፡፡ አሁን የሚያስፈልገው ወደ ሰውነት ከፍታ መውጣት ነው፡፡ እኔ ድሮ የማውቀውን የኢትዮጵያን ህዝብ ስነ ልቦና አይደለም አሁን እያየሁ ያለሁት፡፡

የሴቶች ትግልስ በኢትዮጵያ ፍሬ እያፈራ ነው ማለት ይቻላል?

አይ አይመስለኝም፡፡ እንዲሁ ልባስ ነው ያለው እንጂ ትክክለኛው የሴቶች ጥያቄ ጐልቶ አልወጣም፡፡ አሁን ያለው የመታያ ነገር ነው፡፡ ለውጭ ሀገር ሰዎች ለማሳየት የሚደረጉ ነገሮች ናቸው የሚበዙት፡፡ ዛሬም ለእኩል ስራ እኩል ክፍያ የለም፡፡ ሴት ህፃናት በቤት ውስጥም በሌላም ቦታ ያለ እድሜያቸው ኃላፊነት ወስደው፣ ለጉልበት ብዝበዛ እየተዳረጉ ነው፡፡ እኩል የትምህርት እድል እያገኙ አይደለም፡፡

ጠ/ሚኒስትሩ ግማሽ ካቢኔያቸውን ሴቶች አድርገዋል፤ የአገሪቱ ፕሬዚዳንትም ሴት ናቸው:: ይሄንንስ እንዴት ያዩታል?

እነሱ በስራቸው የሚመዘኑ ይሆናል፤ ለህዝብ ሠርተው ማሳየት አለባቸው፡፡ በተግባር የሴቷን ህይወት መቀየር ካልቻሉ፣ አሁንም መታያ ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡

ልጆችዎን ትተው በረሃ በመግባትዎ የሚፀጽትዎት ነገር አለ?

ፈጽሞ የለም፡፡ ትቻቸው በመውጣቴ ምንም አይቆጨኝም፡፡ በአቅሜ ለኢትዮጵያ ህዝብ ታግያለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ 17 አመት በበረሃ ታግያለሁ፡፡ ለኔ ይሄ ለሀገሬ ያበረከትኩት አስተዋጽኦ ነው፡፡ ስለዚህ ባደረግሁት ሁሉ አልፀፀትም፡፡ ባደረግሁት ትግል እኮራለሁ፡፡

አሁን ላለው መንግስትና ህዝብ ምን ይመክራሉ?

ሹመት ማለት እዳ እንጂ ክብር አይደለም:: ሹመት ማለት ህዝብን የማስተዳደር ኃላፊነት ነው:: የተበላሸውን ስርአት ማቃናት ያስፈልጋል:: ላለፉት 40 ዓመታት የተበላሸ ስርአት ነው የነበረው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ከመጣ በኋላ ህዝቡን ማረጋጋት ችሏል፡፡ ይሄን መረጋጋት ተጠቅሞ ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርበታል:: ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያዋጣው አንድ ላይ መቆሙ ነው፡፡ ኢህአፓ ሲታገል ከ14ቱም ክፍለ ሀገር በተውጣጣ ሠራዊት ነው፡፡

የልጅ ልጆች አግኝተዋል?

አዎ፤ በጣም ካስደሰተኝ ነገር ዋነኛው ይሄ ነው:: እዚያ በረሃ ሆኜ ተርፌ ልጆቼን አያለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ አሜሪካ ከገባሁ በኋላ ግን ፈጣሪን እድሜ እየለመንኩ፣ እንደው አንድ ቀን የልጅ ልጆቼን ሰብሰብ አድርጌ፣ መሃከላቸው ሆኜ፣ ፎቶግራፍ ለመነሳት እመኝ ነበር፡፡ ያ ምኞቴ ሠምሮ፣ አንድ ቀን ማታ፣ ከልጅ ልጆቼ ጋር ሆኜ ፎቶ ተነስቻለሁ፡፡

ከተማውን ከአንድ ሚሊዮን የፕላስቲክ ጠርሙሶች ነጻ ያደረገው ጀግና!

የ36 ዓመት ወጣት ነው፤ ነዋሪነቱ በአማራ ክልል መርሳ ከተማ ነው። በጫማ ማሳመር ሙያ ተሰማርቶ ረዥም ዓመታትን አሳልፏል፤ ዘይኑ ሀሰን።

‹‹ኑሮዬን ለማሸነፍ በርካታ የሥራ ዓይነቶችን ያለመታከት እሠራለሁ›› የሚለው ዘይኑ ከዓመታት በፊት በአንዱ ቀን አካባቢውን እያፀዳ ለራሱም ገቢ የሚያገኝበት የሥራ ሐሳብ ብልጭ አለለት።

‹‹በየመንገዱ የተጣሉ ፕላስቲኮችን ለምን እየለቀምኩ አላጠራቅምም? በዚያውም ከተማዬን ከቆሻሻ የፀዳች አደርጋታለሁ ብየ አሰብኩ›› ይላል ሥራውን ስለጀመረበት አጋጣሚ ሲናገር።

‹‹ሲበዛ ጠንካራ ነኝ፤ ተስፋ አልቆርጥም፤ ብዙ ጊዜ ምን መሥራት አለብኝ? ምን ብሠራ ይሳካልኛል? ብየ አስባለሁ›› ሲል ይናገራል ዘይኑ።

በየቀኑ ጠዋት ከ12:00 እስከ ረፋድ 3:00 እንዲሁም ከሰዓት በኋላ ከ8:00 ጀምሮ እስከ ምሽት ድረስ በከተማዋ አውራ ጎዳዎች እየተዘዋወረ ያለመታከት የኘላስቲክ ለቀማውን ማከናወን ጀመረ።

ከጊዜ ወደ ጊዜ የፕላስቲክ ጠርሙሶቹ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ፕላስቲኮችን ለማከማቸት የሚሆን ቦታ ጥበት ገጠመው። ሥራውን ለማከናወን የሚሆን ቦታ እንዲመቻችለት የሚኖርበትን ቀበሌ ከዚያም የመርሳ ከተማ መዘጋጃ ቤትን ቢጠይቅም በወቅቱ መፍትሔ አላገኘም ነበር፡፡

‹‹የቦታ ጥያቄዬ ባለመመለሱ ተስፋ አልቆረጥኩም፤ እንዲውም ይበልጥ እንድጠነክር አድርጎኛል›› በማለት በወቅቱ የተሰማውን በመግለጽ ጥረቱ መቀጠሉን አስረድቷል። ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ በመጨረሻም ወይዘሮ ፋጡማ የሱፍ አህመድ የተባሉ ሴት ፕላስቲኮቹን በመኖሪያ ቤታቸው ግቢ እንዲያጠራቅም ፈቀዱለት።

ይህንን ሥራ ከጀመረበት ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2009 ዓ.ም ድረስ 400 ሺህ ፕላስቲኮችን መሰብሰብ የቻለው ዘይኑ ከሁለት ወራት በፊት ያቀደውን ቁጥር ማሳካት መቻሉን በኩራት ይናገራል። ‹‹አሁን ዕቅዴ ተሳክቷል፤ ከተማዬን ከአንድ ሚሊዮን የፕላስቲክ ጠርሙሶች ነጻ ማድረግ ችያለሁ›› ብሏል። ዘይኑ የፕላስቲክ ጠርሙሶቹ አንድ ሚሊዮን ሲደርሱ በአንድ ሚሊዮን ብር የመሸጥ ዕቅድ እንደነበረው በአንድ ወቅት ከአማራ ቴሌቪዥን ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል።

ይህ ብርቱ ወጣት አሁን የፕላስቲክ ጠርሙሶቹን የሚገዛው እያፈላለገ ነው፤ የሚረዳው ድርጅት ካገኘ ደግሞ ቆሻሻውን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።

ይህን ተግባር በመፈፀሙ የከተማው ንፅህና እንዲጠበቅ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳበረከተም በኩራት ይናገራል።
አሁንም ሌሎች የፕላስቲክ ዓይነቶችንም እየለቀመ ማጠራቀሙን ቀጥሏል። በኢትዮጵያ ውስጥ 6 ቢሊዮን የውኃ የፕላስቲክ ጠርሙሶች ከየፋብሪካዎች ታሽገው ጥቅም ላይ እንደዋሉ ሪፖርተር ጋዜጣ ባንድ ዘገባው ላይ ጠቅሶ ነበር።
ይሁን እንጅ ፕላስቲኮችን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋልም ሆነ ይዘትን ቀይሮ በመገልገል ደረጃ የተሳካ ሙከራ አለመደረጉን መረጃዎች ያስረዳሉ።

ጎረቤታችንን ኬንያን ጨምሮ አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት የፕላስቲክ ጠርሙሶችን መልሶ በመጠቀሙ በኩል አበረታች ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ። አንዳንድ ሀገራት የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ ፕላስቲክ ነክ ቁሶች ጨርሶ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የሚያደርጉ ሕጎችን እስከመደንገግ የሚደርስ ቁርጠኝነት እያሳዩ መሆኑም ይታወቃል።

ወጣቱ ይህን በሚሰራበት ወቅት ስላጋጠመው ችግር ሲገልጽ ‹‹ከማጠራቀሚያ ቦታ ችግር በተጨማሪ ፕላስቲኮቹን ስለቅም ብዙ መሰናክሎች ቢገጥሙኝም ሁሉንም አልፌያቸዋለሁ። ብዙዎች ‹አበደ› ብለውም ሸሽተውኛል›› ብሏል።
አሁን ግን በርካታ የከተማው ወጣቶች ጥንካሬውንና አርዓያነቱን በስፋት እየመሠከሩለት ነው፡፡
ምንጭ፡- አረንጓዴ ሐሳቦች

(አብመድ)

ተመድ በየመን ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ የታሰሩ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ 3 ሺህ ስደተኞች እንዲለቀቁ ጠየቀ

ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት /አይ ኦ ኤም/ በደቡባዊ የመን ኢፍትሃዊ በመሆነ መንገድ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የታሰሩ 3 ሺህ ስደተኞች እንዲለቀቁ ጠየቀ። ድርጅቱ እንዳስታወቀው አብዛኛዎቹ በእስር ላይ የሚገኙት ስደተኞች ኢትዮጵያውን ናቸው።

ስደተኞቹ የታሰሩት በኤደንና ላህጅ በተባሉ ከተሞች ሲሆን፥ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዕውቅና የሰጠው መንግስት በሚያስተዳድራቸው አካባቢዎች ውስጥ እንደሚገኙም አስታውቋል።

ድርጅቱ 2 ሺህ 500 የሚሆኑት ስደተኞች ኤደን በሚገኝ አንድ ስታዲየም ውስጥ መታሰራቸውን ጠቅሶ፥ ኮሌራ መሰል በሽታዎች እንዳይከሰቱ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም ገልጿል። እንዲሁም ከየመን መንግስት ጋር ስደተኞቹ በሚለቀቁበት ሁኔታ ላይ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም አንስቷል።

በተጨማሪም  አይ ኦ ኤም ላህጅ በተባለው ቦታ በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ የታሰሩ 1 ሺህ 400 የሚደርሱ ስደተኞች ስለመለቀቃቸው ሪፖርት ደርሶታል ሆኖም 14 ስደተኞች በውሃ ወለድ በሽታዎች አማካኝነት ህይወታቸው ማለፉ ተጠቅሷል።

የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት 237 የሚደርሱ በፈቃደኝነት ወደ ሀገራቸው የሚመለሱ ኢትዮጵያንን ለመመለስ እየተዘጋጀ ስለመሆኑም ነው ያስታወቀው።

(ኤፍ.ቢ.ሲ)

“እንደ በሬ እየታረስኩ ለሶስት አመት ቆይቻለሁ”-በታንዛኒያ ከእስር የተፈታ ኢትዮጵያዊ

 

ባለፉት ሶስት ወራት 800 ገደማ ኢትዮጵያውያን ከታንዛኒያ እስር ቤቶች ተፈተው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። ኢትዮጵያውያኑ በቀን አንድ ጊዜ እየተመገቡ የጉልበት ሥራ ይሰሩ ነበር። የታሰሩት ተፈተው ሲመለሱ አዲሶቹ መንገድ ላይ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ግን በታንዛኒያ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ፈታኝ ሆኗል

ለአመታት ከታሰሩባቸው የታንዛኒያ ማረሚያ ቤቶች ተፈተው ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ዝግጅት የጀመሩ ወጣቶች አብዛኞቹ ጸጉራቸውን በአጭር ተቆርጠዋል፤ የተላጩም አሉበት። ፊታቸው የገረጣ፤ ያለፉ አመታት የታንዛኒያ እስር ቤት ኑሯቸው በፈተና መሞላቱን የሚመስክር ወጣቶችም ከመካከላቸው ይታያሉ። ነገር ግን ደስተኛ ናቸው። ቢያንስ ከእስር አስፈትተው ወደ ኢትዮጵያ መመለስን ላመቻቹላቸው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባልደረቦች ያን ይናገራሉ። ወጣቶቹ ባለፈው ሳምንት ከታንዛኒያ ባጋሞዮ በሚባል ግዛት ኪንጎንዶኒ ከሚባል ማረሚያ ቤት የተፈቱ ናቸው። በዳሬ ሰላም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተፈቺዎቹ ኢትዮጵያውያን ያለፉበትን ውጣ ውረድ በትውልድ ቀያቸው ላሉ እንዲያጋሩ በፌስቡክ ገፁ ባሰራጨው ቪዲዮ “የኃያላን ሁሉ ኃያል ነው፤ የነገስታት ሁሉ ንጉስ ነው” እያሉ ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑት ወጣቶች እንደሚሉት በታንዛኒያ እስር ቤቶች በጉልበት ሥራ ሰርተዋል፤ ተደብድበዋል፤ በቂ ምግብም ሳያገኙ ቆይተዋል።

ጥቂት ምግብ ብዙ የጉልበት ሥራ፤ -ኢትዮጵያውያኑ በእስር ቤት

በዱራሜ ዞን ከምትገኘው ዱዬ ገና ወረዳ የትውልድ ቀዬው ተነስቶ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት መንገድ የጀመረው ጸጋዬ ወልደ ኪዳን በታንዛኒያ ጸጥታ አስከባሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ለአመታት አስከፊውን ኑሮ በእስር ቤት ግብግብ ከገጠሙት መካከል አንዱ ነው። “አመት ሙሉ ለሊት አስራ ሁለት ሰዓት ላይ እየወጣሁ ማታ አስራ ሁለት ሰዓት እየገባሁ ቀን እና ለሊት እየሰራሁ ቆይቻለሁ” የሚለው ጸጋዬ ያለፈበት ስደት በእሱ ብቻ እንዲበቃ ይመኛል።

ጫካ መመንጠር እና ሩዝ መትከል ጨምሮ የጉልበት ሥራ ላይ የቆየው ጸጋዬ “ምግብ በ24 ሰዓታት አንድ ጊዜ ኡካሊ የሚባል በበቆሎ የተሰራ ገንፎ አለ። እሱ አንድ የ15 አመት ሕፃን ልጅ እንኳ በልቶ የማያጠግበው ነው። ከባድ የሆነ ስራ ሰርተን ያንን እንበላለን። ያንን የምናገኘው እንደገና 24 ሰዓት ቆጥረን ከ24 ሰዓት በኋላ ነው እንደገና ከሥራ መልስ የምናገኘው። እሱንም ቶሎ ብሉ ተብለን በዱላ እንመታለን” ሲል ያለፈባቸውን አመታት አስከፊነት ይገልፃል። በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምኒስትር ካውንስለር አቶ ቴዎድሮስ ግርማ “ከታንዛኒያ መንግሥት ጋር ባደረግንው ውይይት አግባብነት የሌላቸው ሥራዎች እንደማያሰሯቸው ነው የሚነግሩን። ልጆቹ ደግሞ ውሀ እንቀዳለን፤ እርሻ እናርሳለን፤ ድንጋይ እንፈልጣለን ይላሉ” ሲሉ ስለ ሁኔታው አስረድተዋል። 

130 ሺሕ ብር ለሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከፍሎ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመጓዝ የሚከረው ጸጋዬ እሱ እና መሰሎቹ በእስር ቤት የደረሰባቸውን ግልምጫ እና ስድብ ከባድ ይለዋል።

በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምኒስትር ካውንስለር አቶ ቴዎድሮስ ግርማ እንደሚሉት ኢትዮጵያውያንኑ በመንገዳቸው ስለሚገጥማቸው ውጣ ውረድ ምንም አይነት መረጃ አልነበራቸውም። አቶ ቴዎድሮስ ከ120 እስከ 150 ሺሕ ብር የሚደርስ ገንዘብ ለሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የከፈሉት ኢትዮጵያውያን “ከአገራቸው ሲወጡ በደላላ ከሶስት እስከ ሰባት በሚደርሱ ቀናት ደቡብ አፍሪካ ትደርሳላችሁ ተብለው ነው። ምንም የሚያውቁት ነገር የለም” ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኤምባሲ በታንዛኒያ እስር ቤቶች ባደረገው አሰሳ ከተገኙ ሰዎች መካከል “በጣም የታመሙ ሰዎች” መኖራቸውን የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ በቂ ምግብ አለማግኘታቸውን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል።

ከአዲስ አበባ ተነስቶ አውስትራሊያ ሊሻገር መንገድ የገባው ሐፍቱ በርሔ በበኩሉ “ጎሞዦ የተባለ መጥፎ እስር ቤት ጉድጓድ ውስጥ ሳይሞቱ የተቀበሩ ልጆች አሉ። እኛ ሳንሞት ተቀብረን የነበርን ሰዎች ነን” ሲል ያለፉበትን ፈተና ይገልጸዋል። “ከዚህ አገር ለመውጣት እንኳን እግዚአብሔር አበቃኝ እንጂ ይቺን አገር ዞሬም አላይም” ባይነው ሐፍቶም።

የኢትዮጵያ ኤምባሲ አሰሳ

ጸጋዬ እና ሐፍቱ በታንዛኒያ ባጋሞዮ በሚባል ግዛት ኪጎንዶኒ በተባለ እስር ቤት ከተገኙ 80 ኢትዮጵያውያን መካከል ናቸው። በታንዛኒያ ዋና ከተማ ከሶስት ወራት ገደማ በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የተከፈተው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቅድሚያ ከሰጣቸው ሥራዎች መካከል የአገሪቱን ማረሚያ ቤቶች ማሰስ ነበር። የኤምባሲው ምኒስትር ካውንስለር ኢትዮጵያውያኑ “ያሉበትን እስር ቤት ለመለየት ሞከርን። ከዚያ አንድ ባንድ መዞር ነው የጀመርንው” ሲሉ ጅማሮውን ይገልጹታል። ወደ ደቡብ አፍሪካ መንገድ ጀምረው የታሰሩት ኢትዮጵያውያን “በየግዛቱ እስር ቤት ነው ያሉት። መጀመሪያ ብዙ ቁጥር ያለው እስረኛ ያለበትን ነው የለየንው። እነሱ ላይ አሰሳ ጀመርን። ሔደን ያየንው ነገር ልባችንን ነው የሰበረው” የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ  ታንጋ በተባለ እስር ቤት ብቻ በአንድ ቀን 447 ኢትዮጵያውያን መገኘታቸውን ገልጸዋል።

በታንዛኒያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአገሪቱ እስር ቤቶች ባደረገው አሰሳ የሚያገኛቸውን ዜጎች አስፈትቶ የጉዞ ሰነድ በማዘጋጀት ወዲያውኑ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ያደርጋል። አቶ ቴዎድሮስ “ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ወደ 800 የሚደርስ ኢትዮጵያዊ ልከናል” ሲሉ ተናግረዋል። ከእስር የተፈቱትን ወጣቶች ወደ አገራቸው ለመመለስ እስካሁን የኢትዮጵያ መንግሥት ከ187 ሺሕ ዶላር በላይ ወጪ አድርጓል። ዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት (IOM) ኢትዮጵያውያኑን ለመመለስ መጠነኛ ድጋፍ ማድረጉን የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ

በተለያዩ መንገዶች ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀኑ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት ያጠኑት አቶ ዮርዳኖስ ሰይፉ ከኬንያ እና ከታንዛኒያ ሕግ አስከባሪዎች ለመሸሽ ስደተኞች እና አሻጋሪዎች በጀልባ በመሳፈር በሕንድ ውቅያኖስ ዳርቻዎች መጓዝ መምረጣቸውን ይናገራሉ። አቶ ዮርዳኖስ “ከኬንያ እና ታንዛኒያ ድንበሮቹን ተናግረውም ሆነ ሙስና ሰርተው አሊያም በሕንድ ውቅያኖስ ተሻግረው ታንዛኒያ እና ማላዊ ድንበር እንዲሁም ታንዛኒያ እና ሞዛምቢክ ድንበር የሚያርፉ ወጣቶች በጣም ቁጥራቸው ብዙ ነው።በተለይ በማላዊ ፓሮንጋ እና ዛሌካ የሚባሉ ቦታዎች አሉ። በእነዚህ ቦታዎች በጣም ብዙ ኢትዮጵያውያን እና የሌላ አገር ስደተኞች በብዛት አሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

ከማላዊ ተነስተው ወደ ዚምባብዌ እና ሞዛምቢክ የሚዘልቁ ብዙ ልጆች አሉ። ማላዊንም ተሻግረው ሞዛምቢክ እና ዚምባብዌ የሚሰፍሩ ብዙ ወጣቶች አሉ። ሞዛምቢክ እና ዚምባብዌ ወደ ደቡብ አፍሪካ መግቢያ የጎረቤት አገራት ስለሆኑ ብዙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እነዚያ አገራት ውስጥ ሊገኙ ይችላሉ። ስለዚህ ማላዊ ሞዛምቢክ እና ዚምባብዌ ብዙ ስደተኞች ሊገኙ ይችላሉ የሚል ሐሳብ አቶ ዮርዳኖስ ከእስር ቤቶች ባሻገር ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ቦታዎች ሊገኙ እንደሚችሉ ጥቆማ አላቸው። በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያውያንን አኗኗር የፈተሸ ጥናት በሰሩበት ወቅት በማላዊ፣ በሞዛምቢክ እና በዚምባብዌ ጫካዎች፤ ሥራ ፈት ሕንፃዎች፤ የድሮ ትምህርት ቤቶች እና በደላሎች ማጎሪያዎች ይቆዩ እንደነበር መረጃ ማግኘታቸውን የሚናገሩት አቶ ዮርዳኖስ “ያልተያዙ፤ ያልታሰሩ፤ በአሻጋሪዎች እጅ፤ በደላሎች እጅ ያሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ” ብለዋል።

ውሀ ቅዳ ው መልስ?

በዳሬ ሰላም የሚገኘው ኤምባሲ ሁለት ሕፃናት እና ከሶስት እስር ቤቶች የተፈቱ 25 ወጣቶችን ወደ አገራቸው በሸኘበት ባለፈው ሳምንት ሌሎች ሌሎች 31 ኢትዮጵያውያን በታንዛኒያ የጸጥታ አስከባሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ይኸ የአቶ ቴዎድሮስን እና የባልደረቦቻቸውን ሥራ ፈታኝ አድርጎታል።

አቶ ቴዎድሮስ “እኛ ወደ አገር ቤት ከምናስገባው ባልተናነሰ ቁጥር ሌላው ወደዚህ እየመጣ ይታይሃል። ተስፋ የምናደርገው ምንድነው አብዛኞቹ ከአንድ አካባቢ የመጡ እንደመሆናቸው በእዚያ አካባቢ ጠንከር ያለ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ቢሰራ ቶሎ ይኸን ነገር ማስቀረት የሚቻልበት ዕድል እንዳለ ተስፋ ይሰጠናል” ሲሉ ቀሪው የቤት ሥራ ከፍ ያለ መሆኑን ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት ወራት በተለያዩ አገሮች በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ወደ አገር የመመለስ ብርቱ ሥራ ላይ ይገኛል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትናንትናው ዕለት እንደገለጸው ከሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች የተፈቱ 1,400 ኢትዮጵያውያንን ለመመስ ዝግጅት ላይ ይገኛል። የርስ በርስ ጦርነት ባደቀቃቸው የመን እና ሊቢያን በመሳሰሉ አገሮች መፈናፈኛ ያጡ ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ።

እሸቴ በቀለ – ነጋሽ መሐመድ  read the original story here DW

ኢትዮጵያውያን በየመን ኤደን ከተማ በስታዲየም ውስጥ ታስረው ይገኛሉ- አይ ኦ ኤም

“በረሃብና በኮሌራ እየተሰቃዩ የሚሞቱ ኢትዮጵያውያንም አሉ … ወደ ወታደራዊ ካምፑ የተወሰድነው 400 እንሆናለን፤ እዚያ ስንደርስ ግን ከ3ሺህ በላይ ስደተኞችን አይተናል።”

BBC Amharic – በየመን አደን ከተማ በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን በስታዲየም ውስጥ መታገታቸው ተሰማ። እነዚህ አፍሪካውያን በደቡባዊ የመን በሚገኙ በአደን፣ ላዥ እና አቢያን ከተሞች ታስረው እንደሚገኙ በየመን የአለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት፣ አይ ኦ ኤም፣ ቃል አቀባይ የሆኑት ኦሊቪያ ሔዶን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከታገቱት አብዛኞቹ ወደ ሳኡዲ አረቢያና ሌሎች የአረብ ሀገራት ለመሻገር የመን የገቡ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ ቃል አቀባይዋ አስረድተዋል። ከኢትዮጵያውያን ባሻገር የሶማሊያና የጅቡቲ ዜጎችም መታሰራቸውን ኦሊቪያ ሔዶን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

እነዚህ ኢትዮጵያውያን የተያዙት በየሥፍራው በተተከሉ የፍተሻ ጣቢያዎች ሲሆን በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላም ወደ ጦር ካምፖችና ኤደን ከተማ ወደ ሚገኘው ስታዲየም አምጥተዋቸዋል ብለዋል።

ቃል አቀባይዋ ስደተኞቹ በተያዙበት ሥፍራ በመገኘት እንዳረጋገጡት ሥፍራው በጦርነቱ ምክንያት የፈራረሰ ሲሆን ስደተኞቹን ለማቆያ ብቁ አይደለም ብለዋል።

ወደ የመን ላዥ ከተማ ከመጣ 25 ቀን እንደሆነው የሚናገረው አወል ሼህ ናስር በታጠቁ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ውሎ በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ታስሮ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግሯል። አወል ወደ የመን ከገባ በኋላ መኪና በማጠብ ሥራ ላይ የተሰማራ ቢሆንም ፖሊስ መጥቶ ገንዘቡን ተቀብሎ እንዳባረረው ያስረዳል።

በኋላም በከተማው በሚገኝ የሀገሩ ልጅ ቤት ተደብቆ ሳለ ፖሊሶች መጥተው ከብበዋቸው ወደ ወታደራዊ ካምፑ እንደተወሰዱ ለቢቢሲ አረጋግጧል።

“ወደ ወታደራዊ ካምፑ የተወሰድነው 400 እንሆናለን፤ እዚያ ስንደርስ ግን ከ3ሺህ በላይ ስደተኞችን አይተናል።” የሚለው አወል በአንድ መጋዘን ውስጥ አስገብተዋቸው እንደቆለፉባቸው ያስታውሳል።

አወል እንደሚለው ከመጋዘኑ ለመፀዳዳትም ሆነ ንፋስ ለመቀበል መውጣት አይቻልም፤ ተፋፍገው እና በሙቀት ታፍነው ባሉበት ሁለት ስደተኞች በመታመማቸው በሩን ገንጥለው ልጆቹ አየር እንዲያገኙ እንዳወጧቸው ያስረዳል።

በዚህ ጊዜ ነው ጠባቂዎች በሥፍራው እንደሌሉ ተረድተው በቡድን በመሆን ያመለጡት። በቁጥር በርከት ብለው ያመለጡት በድጋሚ በቁጥጥር ሥር ውለዋል የሚለው አወል እርሱ ግን ከአንድ ጓደኛው ጋር በመሆን በማምለጥ አማን መግባቱን ነግሮናል።

በአማን ከተማ ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ መሆኑን የሚናገረው አወል በየስፍራው የፍተሻ ጣቢያ በመኖሩ ወደ አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ሄዶ ለመመዝገብ እንኳ እንዳልቻሉ ይናገራል።

ከሰንዐ ወጣ በሚል የገጠር ከተሞች በአንድ ቀን ብቻ ከሶስት ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ተይዘው ታስረዋል ሲሉ ለቢቢሲ የተናገሩት ደግሞ በሰንአ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ከድር በከልቻ ናቸው።

የሰንዐን ከተማ የሚቆጣጠሩት የሁቲ አማፂያን እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ከድር መንግሥት የሰጣቸውን የስደተኝነት ሰነድ እንዲቀይሩ እንደሚያስገድዷቸው ከቀየሩ ደግሞ የየመን መንግስት ወደሚያስተዳድራቸው ሥፍራዎች መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ያስረዳሉ።

አቶ ከድር “የሁቲ አማፂያን ወደ ተለያዩ የአረብ ሀገራት ለመሻገር ወደ የመን የሚሰደዱ ኢትዮጵያንን እየያዙ ወደ ውትድርና ያሰማራሉ” ሲሉ ይከሳሉ።

እነዚህ በግዳጅ ወታደር የሆኑ ኢትዮጵያውያን በየመን መንግሥት በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ኢትዮጵያውያን በገፍ መታፈስ መጀመራቸውንም ያስረዳሉ።

“በረሃብና በኮሌራ እየተሰቃዩ የሚሞቱ ኢትዮጵያውያንም አሉ” ይላሉ -አቶ ከድር። በዚህም ባለፈው ሳምንት ብቻ ከሰንዐ ወጣ ብላ የምትገኝ ረዳ በምትባል አነስተኛ ከተማ አምስት ኢትዮጵያውያን መሞታቸውን ተናግረዋል።

በየመን ህጋዊ ወረቀት ያላቸው ኢትዮጵያውያንም ጭምር በአሁን ሰዓት የተለያዩ ችግር ውስጥ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ከድር ሁቲዎችን ትደግፋላችሁ በሚል መንቀሳቀስ መከልከላቸውን ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሁቲ አማፂያን ታጣቂዎች አንዲሁም በየመን መንግሥት እንግልት እንደደረሰባቸውና ሕገወጥ ደላላዎች እንደሚያሰቃይዋቸው ያስረዳሉ።

በየመን የሚገኙ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ፍላጎት ያላቸው ቢሆንም ከከተማ ወጥቶና እንደልብ ተንቀሳቅሶ ጉዳያቸውን ማስፈፀም እንዳልቻሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚያው የሚገኙ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ስደተኞችም እንደሚናገሩት በሀገሪቱ የተለያዩ ሥፍራዎች የማይታወቁ እስር ቤቶች እንደሚገኙ፣ እስር ቤቶቹ ጠባብና የተፋፈጉ መሆናቸውን በዚህም የተነሳ ኮሌራን ጨምሮ ለተለያዩ በሽታዎች መገለጣቸውን ጨምረው ገልፀዋል።

በአደን በእስር ላይ ከሚገኙት ወንዶችና ሴቶች በተጨማሪ 800 ሕፃናት እንደሚገኙበት የሚናገሩት የአይ ኦ ኤም ቃል አቀባይ፣ ሕፃናት የሆኑ ብቻ ሳይሆን ታዳጊ ልጆችም ከእስረኞቹ መካከል እንደሚገኙበትና የተለያዩ መንገላታቶች እንደሚደርስባቸው አስታውቀዋል።

ቃል አቀባይዋ ያነጋገሯቸው አብዛኞቹ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው መመለስ እንደሚፈልጉ የገለፁ ሲሆን አይ ኦ ኤም እነዚህን ስደተኞች ለመመለስ የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጿል።

Image copyrightAFP – ኢትዮጵያን ስደተኞች በታጣቂዎች እጅ

ከጤና ሚኒስቴር የተሰጠ መግለጫ

በሚያዚያ 26 2011ዓ.ም ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ ከጤና ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች መፍትሄ አግኝተዋል ካሏቸዉ መካከል የተወሰኑት ፤

.

1. የሀኪሞች እና የሌሎች ባለሙያዎች የስራ ምደባ በተመለከተ

.

– አሁን በስራ ላይ ያሉ ሀኪሞችንም ሆነ ሌሎች የጤና ባለሙያዎች የአለም የጤና ድርጅት ባስቀመጠው ዝቅተኛ ስታንዳርድ (health work force density) መሰረት በሰራ ለይ ያሉት ባለሙያዎች ቁጥር ህብረተሰቡን ለማገልግል በቂ ስላልሆነ በሚቀጥሉት ኣመታት የሚመረቁ ሀኪሞችም ሆነ ሌሎች ባለሙያዎች መመደብ እንዲቻል ክልሎች በጀት እና ተጨማሪ መደብ እንዲያስፈቅዱ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

.

– ከግንቦት ወር 2011ዓ.ም ጀምሮ በክልሎች እና በዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ስፖንሰርነት 3800 የስፔሻላይዜሽን ትምህርት እየተከታተሉ የሚገኙ ሀኪሞች ደሞዝ፣ መደብ እና ጥቅማጥቅም በጤና ሚኒስቴር እንዲሸፈን በመወሰኑ ተጨማሪ 3800 ሀኪሞችን በክልሎች እና በዩኒቨርሲቲዎች ለመቅጠር ያስችላል፡፡

.

2. የስፔሻላይዜሽን ስልጠና በተመለከተ፡

– በግል ፈተና ወስደው መሰልጠን ለሚፈልጉ ባለሙያዎች የስፔሻላይዜሸን ትምህርት እንዲከታተሉ ተፈቅዷል፡፡

.

3. የሀኪሞችን የወጪ መጋራት በተመለከተ፡

– ከግንቦት ወር 2011ዓ.ም ጀምሮ ከዚህ ቀደም የትምህርት ማስረጃ ለማግኘት የሚከፈለው ብር 470,000.00 እንዲቀር እና ሃኪሞችም እንደማንኛውም የመንግስት ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች በወጪ መጋራት ህግ መሰረት የሚስተናገዱ ይሆናል፡፡

.

4. ከፌደራል ተቋማት የትርፍ ሰዓት እና የጥቅማጥቅም ክፍያ ላይ የሚቆረጠውን ታክስ በተመለከተ፡

– በፌደራል ሆስፒታሎች ከዚህ በፊት ሲቆረጥ የነበረው የትርፍ ሰዓት እና የጥቅማጥቅም ክፍያ ታክስ ከግንቦት ወር 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በፌደራል መንግስት እንዲሸፈን ተወስኗል ። በተመሳሳይ እስከ አሁን ይሄንን ተግባራዊ ያላደረጉ ክልሎች በአጭር ጊዜ ጉዳዩን ወደ ክልል ካቢኔ አቅርበው እንዲያስወስኑ ስምምነት ለይ ተደርሷል።

.

5. የባለሞያ ካሪየር ስትራክቸርን በተመለከተ፡

– ከ2009 ዓ.ም ደሞዝ ጭማሪ ጋር ተያይዞ በፌደራል ሆስፒታሎች ከዚህ በፊት ወደ ጎን የነበረውን የካሪየር እድገት ከግንቦት 2011ዓ.ም ጀምሮ ወደ ላይ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ በተመሳሳይ እስካሁን ይሄንን ተግባራዊ ያላደረጉ ክልሎች በአጭር ጊዜ ጉዳዩን ወደ ክልል ካቢኔ አቅርበው እንዲያስወስኑ ስምምነት ለይ ተደርሷል።

.

6. የጤና ተቋማትን ስታንዳርድ ማሻሻል በተመለከተ

ከዚህ በፊት የተጋነኑ የሚመስሉ የግል ጤና ተቋም ለመክፈት ሲጠየቁ የነበሩ መስፈርቶች እንዲሻሻሉ ተደርጓል፡፤ ከግንቦት 2011ዓ.ም ጀምሮ ወደ ስራ የሚገባ ይሆናል፡፡

.

7. የተቀናጀ የቀዶ ህክምና ባለሙያዎችን የትምህርት እድል በተመለከተ፡

– ከመስከረም 2012 ዓ.ም ጀምሮ የተቀናጀ የቀዶ ህክምና ባለሙያዎች የትምህርት እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ካሪኩለም በመዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡

.

8. በግል የህክምና ትምህርት ቤቶች የሚማሩ የህክምና ተማሪዎችን በተመለከተ፡

– በግል የህክምና ትምህርት ቤት የሚማሩ የኢንተርን ሀኪሞች ትምህርት ቤቶቹ በሚሰጣቸው የጊዜ ገደብ የተደራጀ ሆስፒታል እስኪኖራቸው በመንግስት ሆስፒታሎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እና ወርሃዊ ደሞዛቸውንም የሚመደቡበት የመንግስት ጤና ተቋም እንዲከፍላቸው ተወስኗል፡፡

.

– ከግል የህክምና ትምህርት ቤቶች የተመረቁ እና የሚመረቁ ሀኪሞች እንዲሁም ሌሎች የጤና ባለሙያዎች ባሉት ክፍት መደቦች መቀጠር እንዲችሉ እድሉ ይመቻቻል።

.

– ከሀምሌ 2010 ዓ.ም ጀምሮ ከግል ህክምና ትምህርት ቤት የተመረቁ ሀኪሞች ከዚህ በፊት 179,000 ብር እንዲከፍሉ ወይም ሁለት አመት እንዲያገለግሉ ያስገደድ የነበረው መመሪያ እንዲቀር ተደርጎ የትምህርት ማስረጃቸው እንዲወስዱ ተደርጎአል።

.

9. የኢንተርን ሀኪሞችን ጥያቄ በሚመለከት፡

– ከላይ በተሰጡት መፍትሄዎች የተመለሱ ጥያቄዎች እንደተጠበቁ ሆነው ሌሎች በጤና ባለሞያዎች ለተነሱ ተጨማሪ ጥያቄዎች የጤና ሚኒስቴር በተዋረድ ከሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ፣ ከዩኒቨርሲቲዎች እና ከዩኒቨረሲቲ ሆስፒታሎች ጋር በመሆን እንዲፈቱ ይደረጋል፡፡

.

10. በክልሎች እና በፌድራል ተቋማት እየተደረጉ የሚገኙት የተለያዩ የጤና ባለሞያ ጥቅማጥቅም ክፍያዎችን በተመለከተ፡

– በክልሎች እና በፌድራል ተቋማት እየተደረጉ የሚገኙት የተለያዩ የየጤና ባለሞያ ጥቅማጥቅም ክፍያዎች ወጥ እንዲሆኑ በ2005 ዓ.ም በወጣው የጥቅማጥቅም መመሪያ መወሰኑ ይታወቃል። ሁሉም ክልሎች ይሄ መመሪያ ተግባራዊ እንዲሆን በአጭር ጊዜ ጉዳዩን ወደ ክልል ካቢኔ አቅርበው እንዲያስወስኑ ስምምነት ላይ ተደርሷል። በ2005ዓ.ም በወጣው የጥቅማጥቅም መመሪያ ላይ ያልተካተቱ የሙያ ዘርፎች የተጋላጭነት ክፍያን አስመልክቶ በአጭር ጊዜ እንዲካተቱ ይደረጋል፡፡

.

11. የጤና ፖሊሲን በተመለከተ፡

– ከህብረተሰባችን የጤና ፍላጎት እና የአለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ የጤና ፖሊሲ እንዲኖረን ለማድረግ ነባሩ የጤና ፖሊሲያችን እንዲከለስ ተወስኖ የተለያዩ የጤና ባለሙያች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶች መደረጋቸው ይታወቃል፡፡ በተዋረድ በሚደረጉ ተጨማሪ ውይይቶች እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛውም የጤና ባለሙያ ፖሊሲው ላይ አስተያየት መስጠት እንዲችል በመከለስ ላይ የሚገኘው የፖሊሲ ሰነድ የጤና ሚኒስቴር የምረጃ መረብ (ዌብ ሳይት) ላይ ተጭኗል፡፡

.

12. ለጤናው ሴክተር ትኩረት ሰጥቶ ስለመስራት፡

-መንግስት ለጤናው ሴክተር የሚያሰፈልገውን ትኩረት መስጠቱን እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ለመጥቅስ ያክል የግዢ ስርዓቱን ማሻሻል አንዱና ዋነኛዉ ነዉ፡፡ እንደማሳያም ባለፈው አንድ አመት ውስጥ የመድሃኒት እና የ ህክምና መሳሪያዎች ግዥ ፍጥነት እና ጥራት ለማሻሻል ከተወሰዱት እርምጃዎች ውስጥ

.

* የላቦራቶሪ መመርመሪያ መሳሪያዎች ማለትም ሄማቶሎጂ/ኬሚስትሪ/ጉሉኮሜትር እና ሪኤጀንቶች/ኬሚካሎች ግዢ በፍሬምወርክ ስምምነት ከአውሮፓ እና አሜሪካ ድርጅቶች ጋር ውል ተገብቶ ዘመን አፈራሽ ማሽኖች ከድርጅቶቹ በነጻ እንዲቀርብ እና ሪኤጀንቶች/ኬሚካሎች ሳይቆራረጡ ከ3-5 ዓመታት ማቅረብ እንዲችሉ ስምምነት ላይ ተደርሶዋል፡፡ በዚህ ስምምነት በመጀመሪያ ዙር ከተካተቱ 500 ተቋማት ውስጥ 50 ተቋማት ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን 450 ተቋማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በቀጣይ አመት ሁሉንም ጤና ተቋማት እንዲያካትት ይደረጋል፡፡

* ለ2012 ዓ.ም የ 80 አይነት መድሃኒቶችን ግዢ በረጅም ግዜ የ ግዥ ፍሬም ወርክ ስምምነት እንዲፈጸም ተወስኗል።

.

– ባለፈው አንድ አመት ጊዜ ብቻ የጤና ሚኒስቴር ለጠቅላይ ሚኒስቴር ያቀረባቸው አምስት የበጀት ጭማሪ ጥያቄዎች ተፈቅደዋል፡፡ ከጸድቁት የበጀት ጭማሪ ጥያቄዎች መካከል፦

i. ለፌዴራል ሆስፒታሎች የትርፍ ሰዓት እና ጥቅማጥቅም ክፍያዎች የሚቆረጠውን የስራ ግብር ለመሸፈን 70 ሚሊዮን ብር በወር

.

ii. ለ3,800 የስፔሻላይዜሽን ተማሪ ሀኪሞች ደሞዝ እና ጥቅማጥቅም የሚውል ግማሽ ቢሊዮን ብር፣

.

iii. ለ50 የማህበረሰብ ፋርማሲ መክፈቻ 50 ሚሊዮን ብር

.

iv. ለጥቁር አንበሳ እና ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎች ለመድሀኒት እንዲሁም ለህክምና መሳሪያዎች ግዢ እዳ የሚከፈል ከ ግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ እና

.

V. ለመድሀኒት እና ለህክምና መሳሪያዎች ግዢ የሚውል በእርዳታ ከምናገኘዉ ውጪ ቀድሞ ይመደብ ከነበረው ከ30 ሚሊዮን ዶላር ወደ የ130 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ከመንግስት በጀት በዚህ ዓመት ተፈቅዷል፡፡

.

– የምግብ ፤ መድሀኒት ፤ ጤና ተቋም እና የጤና አገልግሎት አስተዳደር እና ቁጥጥር ባለስልጣን (FMHACA) ተደራራቢ ሀላፊነቶች ወስዶ እየሰራ በመቆየቱ የሚፈለገውን ያክል ውጤት ማምጣት ባለመቻሉ በዚህ አመት በአዋጅ ወደ መድሀኒት እና ምግብ ቁጥጥር (FDA) እንዲቀየር ተደርጓል፡፡

.

13. የዩኒቨርስቲ ሆስፒታሎችን በተመለከተ፡

– እነዚህ ሆስፒታሎች በሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር ስር ባሉ ዩኒቨርሲቴዎች እንዲሚተዳደሩ ይታወቃል። በእነዚህ ሆስፒታሎች ለይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከጤና ሚኒስቴር እና ከ ሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር የተውጣጣ የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ የችግሮቹን መንስኤ እና መፍትሄ አጥንቶ በአጭር ግዚው ውስጥ የውሳኔ ሃሳብ ያቀርባል፡፡

.

** ከእነዚህ በተጨማሪ የተነሱ ጥያቄዎችን እያየ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለውሳኔ የሚያቀርብ ቡድን ከጠቅላይ ሚኒስቴር እና ከጤና ሚኒስቴር እንዲሁም ከሌሎች የሚመለከታቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ተቋቁሞ በአጭር ግዜ ውሳኔዎችን ያሳውቃል።

ምርምርና ቅመማቸው የተጠናቀቀ 3 ባህላዊ መድሃኒቶች ጥቅም ላይ ሊውሉ ነው

ምርምርና ቅመማቸው የተጠናቀቀ ሶስት ባህላዊ መድሃኒቶች በሚቀጥለው ዓመት ጥቅም ላይ ሊውሉ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የጤና ሚኒስትርሩ ዶክተር አሚር አማን በሶስት ባህላዊ የህክምና መድሃኒቶች ሲደረግ የቆየው ምርምርና ቅመማ ስራ መጠናቀቁን በመግለጽ በሚቀጥለው አመት ጥቅም ላይ እንደሚወሉ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በየሁለት አመቱ የሚያካሂደው አራተኛው ሀገር አቀፍ የጤና ጉባኤ ዛሬ በተከፈተበት ወቅት ነው፡፡

በሀገሪቱ የባህላዊ መድሃኒቶች እውቀት እንዳለ ቢታወቅም ይህን አውቀት በጥናትና ምርምር ለመደገፍ ውስንነቶች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

ወደፊት ዘርፉን በጥናትና ምርምር መደገፍ ጠቃሚ መሆኑን በመግለጽ አሁን ላይ ሶስት ባህላዊ መድሃኒት ላይ ምርምርና ቅመማ ተጠናቅቆ በሚቀጥለው ዓመት አገልግሎት ላይ ይውላሉ ነው ያሉት፡፡

በዚሁ ጉባኤ ላይ እተከለሰ ለሚገኘው የጤናፖሊሲ በግብዓትነት የሚያገለግሉ በርካታ የዘርፉ የምርምር ጽሁፎች እንደሚቀርቡም ነው የተገለጸው፡፡

መድረኩ በባህላዊ መደሃኒቶች የላባራቶሪ የአገልገሎት ጥራት፣ የስነ ምግብ ጥራት የጤና መረጃዎችና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ ትኩረቱን ያደርጋል ተብሏል፡፡ ጉባኤው ለለሚቀጥሉት ሶስት ቀናት እንደሚካሄድም ከጉባኤው የድርጊት መርሃ ግብር መረዳት ተችሏል፡፡

በአፈወርቅ አለሙ -(ኤፍ.ቢ.ሲ) 

ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ በሰቆጣ

“እናንተ ባትመርጡኝ እንኳን አካባቢው ከዳስ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ እስኪወጣ አምባሳደራችሁ ሆኜ እሰራለሁ፡፡” አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ

‹‹ገንዘብህን ብቻ ልከህ ትምህርት ቤቱን ማሰራት እንደምትችል ብናውቅም መምጣትህ ብቻ ለዋግ ህዝብ ዜና ነው፡፡›› የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች፡፡

አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ ሰቆጣ ገብቷል፤ የሚያስገነባውን ትምህርት ቤት የመሠረት ድንጋይም ዛሬ ያስቀምጣል።

በዓለም የአትሌቲክስ ውድድሮች እያሸነፈ ሰንደቁን ከፍ አድርጎ ኢትዮጵያውያንን የደስታ እንባ ያራጨ፤ በደስታ ያስፈነደቀ፡፡ የሌላ ፕላኔት ፍጡር እስከመባል የደረሰ፡፡ ማሸነፉ ሳይሆን መሸነፉ ለዓለም ጆሮ ዜና ይሆን ዘንድ የተናፈቀለት፡፡ ከማሸነፉ በፊት የማይናገር፡፡ በውድድር ላይ በቡጢ ተነርቶ ሁሉ በፍቅር ያቀፈ የተግባር ሰው፡፡ ኢትዮጵያን በዓለም መድረኮች ከፍ አድርገው ካሳዩዋት ኢትዮጵያውያን መካከል ተጠቃሽ ነው፤ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ።

የሁለት ጊዜ የ10 ሺህ ሜትር የኦሎምፒክ ውድድር እና የአራት ጊዜ የርቀቱ የዓለም ሻምፒዮን አሸናፊም ነው፡፡ ከ1 ሺህ 500 ሜትር እስከ ማራቶን ከስቶትጋርት እስከ አትላንታ፣ ከሲድኒ እስከ ዙሪክ፣ ከሎንዶን እስከ አቴንስ፣ ከቤጂንግ እስከ በርሊን እያቀያየረ አሸንፎ ያላጠለቀው ሜዳሊያ፣ ያልበጠሰው ሪቫን፣ ያልሰባበረው ክብረ ወሰን እና ያላሻሻለው ሰዓት የለም፡፡ 27 ጊዜ በአትሌቲክሱ ዓለም ክብረ ወሰኖችን በመሰባበር ዓለምን ያስደመመው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ፡፡

አሁን ደግሞ በሌላ የህዝብ ፍቅር እና እምባ ታጅቦ በዋግ ሹሞች መናገሻ ሰቆጣ ትናንት ማምሻውን ገብቷል፡፡ ተማሪዎች ኃይሌ ኃይሌ እያሉ የከተማዋን መንገዶች በፍቅር ዞሩ፡፡ ወጣቶች በአካባቢው የባህል ልብስ ተውበው በጀግና አቀባበል ተቀበሉት፡፡

የአባቶች ምርቃት የኦሎፒክ መልስ ትዝታውን ቀሰቀሱት እና አይኖቹ እምባ አቀረሩ፡፡ ኃይሌ ትናንት ማምሻውን ሰቆጣ ከተማ ሲገባ ልዩ አቀባበል እና ስጦታዎች ተበረከቱለት እና ብዙ መናገርን በማይሻው አንደበቱ ይህችን ብቻ ተናገረ ‹‹እናንተ ባትመርጡኝ እንኳን አካባቢው ከዳስ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ እስኪወጣ አምባሳደራችሁ ሆኜ እሰራለሁ፡፡›› ተባብረን ያሁኑን ታሪክ በመቀየር ወደ ቀደመ ዝናችን መመለስ ‹‹ይቻላል›› ስለዚህ ሁላችሁም በየድርሻችሁ የተግባር ሰው ሁኑ፡፡

አክብረኸን ስለመጣህ፣ ድምፃችንን ስለሰማህ እና ዛሬም እንደ ትናንቱ አርአያችን ስለሆንክ እናመሰግንሃለን ያሉት ዋጎች ቀጥለውም እንዲህ አሉ ‹‹ገንዘብህን ብቻ ልከህ ትምህርት ቤቱን ማሰራት እንደምትችል ብናውቅም መምጣትህ ብቻ ለዋግ ህዝብ ዜና ነው፡፡››

አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ ዛሬ ከሰቆጣ 45 ኪሎ ሜትር ርቀት አካባቢ በምትገኘው የፃግብጅ ወረዳ በገልኩ አንደኛ ደረጃ የዳስ ትምህርት ቤት በመገኘት ትምህርት ቤቷን ደረጃዋን ጠብቆ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ትምህርት ቤቱን በቶሎ አስገንብቶ ለቀጣዩ የትምህርት ዘመን ለማድረስ ኃይሌ ቃል መግባቱ ይታወሳል።

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ስድስት መደበኛ ትምህርት ቤቶች የዳስ ናቸው፡፡ በብሄረሰብ አስተዳደሩ በተለያዩ አከባቢዎች ደግሞ 324 የዳስ ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ በሳተላይት ትምህርት ቤቶችም 550 የዳስ መማርያ ክፍሎች እንደሚገኙ የብሔረሰብ አስተዳደሩን ትምህርት መምሪያ ዋቢ አድርገን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው – ከሰቆጣ Amara mass media

የዶክተር ነጋሶ አስከሬን ሽኝትና አቀባበል

የመንፈስ ጽናት በኩራት በአደባባይ መስክረዋል። ወይዘሮ ሬጂና ኢትዮጵያ ውስጥም በሙያቸው በህመም እና በምጥ የሚሰቃዩ በርካታ ችግረኛ ወገኖችን በመርዳት ታላቅ አገልግሎት ማበርከታቸውን በቅርበት የሚያውቋቸው እና የስራ ባልደረቦቻቸው ያስረዳሉ።

የዶክተር ነጋሶ ሽኝት
Negaso-2

                               
ባለፈው ቅዳሜ ፍራንክፈርት ዛክዘን ሃውሰን ሆስፒታል ዉስጥ በሕክምና ላይ እያሉ ያረፉት የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት የነጋሶ ጊዳዳ አስክሬን ዛሬ ወደ አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ ተሸኘ።አስከሬኑ ከመሸኘቱ በፊት ፍራንክፈርት በሚገኘዉ የካቶሊክ የሱስ ክርሽየ ቤተ ክርስቲያን ፀሎትና ሟቹ ጀርመን በነበሩበት ዘመን ያከናወኗቸዉን ምግባራት የሚዘክሩ ንግሮች ተደርገዋል።በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ባለቤት ሬጊና አልበል፣ ልጆቻቸዉ ኢብሳና ጃለኔ ነጋሶ፣ ሌሎች የቤተሰቦቻቸዉ አባላት፣ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለስልጣናት፣ የካቶሊክ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶና የመካነየሱስ አብያተ ክርስቲያናት ተጠሪዎችና መንፈሳዊ አባቶች  ተገኝተዋል።የፍራንክፈርቱ ወኪላችን እንዳልካቸዉ ፈቃደ የሽኝትና የፀሎት ሥርዓቱን ተከታትሎታል።
 በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አምባሳደር ወይዘሮ ሙሉ ሰለሞን  ” ዶክተር ነጋሶ ስልጣን ከለቀቁ በኋላ በእግራቸው እና በታክሲ ሲሄዱ አስታውሳለሁ:: ዕውነትን መከተል ምን ያህል ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍል አስተምረውን ያለፉ ታላቅ ሰው ናቸው ” ብለዋል::
ስልጣን ለህዝብ አገልግሎት መዋል አለበት የሚል ዕምነትን  ጨምሮ ለፍትህና ለመርህ መገዛትን ጽኑ ዓላማቸው ያደረጉት ዶክተር ነጋሶ እንደ ጎሮሮሳውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ 2001 ዓ.ም የፕሬዝዳንትነት ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ አያሌ የሕይወት ፈተና እንደገጠማቸው በሕይወት በነበሩበት ወቅት ተናግረዋል ::ከሽግግር መንግሥቱ  ወቅት ጀምሮ አገሪቱን በተለያየ የመንግሥት ኃላፊነትና በርዕሰ ብሄርነት ለበርካታ ዓመታት ማገልገላቸው ቢታወቅም ከመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በፖለቲካ የአስተሳሰብ ልዩነት ምክንያት በተፈጠረው ውዝግብና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማምጣት ከተቃውሞ የፖለቲካ ጎራ ጎን  በመሰለፋቸው ምክንያት ማግኘት የሚገባቸው ጥቅማጠቅም እንዲቋረጥ ብሎም ከሚኖሩበት የመንግሥት ቤት ለቀው እንዲወጡ በተደጋጋሚ የኃይል ሙከራ እንደተደረገባቸውም ራሳቸው የደረሰባቸውን በደል በተለያዩ መድረኮች በአንደበታቸው ሲገልጹ ቆይተዋል::

Deutschland Abschied für Negasso Gidada in Frankfurt (DW/E. Fekade)

ለረጅም ዘመን የሚሰቃዩበትን የልብ ህመም ጨምሮ የገጠማቸውን የጤና ዕክል በውጭ አገራት ወተው ለመታከም ከባድ ፈተና ገጥሟቸው እንደነበረም ዶክተሩም ሆኑ ወዳጆቻቸው በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገልጹ የቆዩት ጉዳይ ነው:: በዚህ ሁሉ ፈተና ግን ከ 30 ዓመታት በላይ በትዳር አብረዋቸው የቆዩት ጀረመናዊቷ አዋላጅ ነርስ የህክምና ባለሙያ ባለቤታቸው ” ኢትዮጵያ ውስጥ ካንተው ጋር እሞታለሁ እንጂ ጥዬህ የትም አልሄድም ” ማለታቸውን በማስታወስ የባለቤታቸውን የመንፈስ ጽናት በኩራት በአደባባይ መስክረዋል:: ወይዘሮ ሬጂና ኢትዮጵያ ውስጥም በሙያቸው በህመም እና በምጥ የሚሰቃዩ በርካታ ችግረኛ ወገኖችን በመርዳት ታላቅ አገልግሎት ማበርከታቸውን በቅርበት የሚያውቋቸው እና የስራ ባልደረቦቻቸው ያስረዳሉ:: በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ የመጀመሪያዋ የውጭ ዜጋ የቀድሞዋ ቀዳማይት ዕመቤት ጀርመናዊቷ ወይዘሮ ሬጂና  አልበል  በበኩላቸው ነጋሶ አገሩን የሚወድ ሙያውን የሚያከብር እና በዛ ሁሉ ፈተና መሃል እንኳ የሚገጥመውን ውጣ ወረድ ተቋቁሞ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን በአቅሙ ለመርዳት እስትንፋሱ እስካለፈችበት ቀን ድረስ ሳይሰለች የደከመ መንፈሰ ብርቱ ሰው ነበር ሲሉ የዶክተሩን ጠንካራ ሰብዕና በተለያዩ ቃለ መጠይቆች ተናግረዋል::
እንደ ጎርጎራውያኑ አቆጣጠር በ 1984 ዓ.ም  በአፍሪቃዊቷ ሩዋንዳ  በጀርመን የረድኤት አገልግሎት ድርጅት ውስጥየሚያከናውኑትን ተግባር አጠናቀው ወደ ፍራንክፈርት ከተማ ሲመለሱ ከትዳር አጋራቸው ዶክተር ነጋሶ ጋር ትውውቅ የፈጠሩት “ድጋፍ ለሶስተኛው ዓለም አገርት ህዝቦች” ወይም “Das Dritte Welt” በተሰኘው ማዕከል ውስጥ እንደነበር ወይዘሮ ሬጂና ነግረውናል ::ወቅቱ ጎልማሳው ፖለቲከኛ ዶክተር ነጋሶ ጀርመናውያን ግራ ዘመም የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኞች ፍራንክፈርት ከተማ የመሰረቱት የዚሁ የሶስተኛ ዓለም አገራት መርጃ ነጻ ማህበር ዳይሬክተር ሆነው የተመረጡበት ሲሆን ሬጂናና ሴት ጓደኛቸውም  ይህንኑ ለአፍሪቃ ላቲን አሜሪካና ለሌሎችም የሶስተኛው ዓለም ሕዝቦች መብት መከበር የሚታገል የዴሞክራቶች ገለልተኛ ማህበር ለማገልገል በመጡበት ወቅት ዶክተሩ የስራ ቱታቸውን ሰብስበው የማዕከሉን ህንጻ ቀለም እየቀቡ ሲያድሱ በማየታቸው ተደምመው ከዛች ቅጽበት ጀምሮ በሁለቱ መካከል የተጸነሰ ፍቅር ለትዳር መብቃቱን ዛሬ በሽኝት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተናግረዋል:: ” ለመላው ኢትዮጵያውያን የሃሳብ እና የዲሞክራሲ መብት መከበር በጽናት የታገለ ታላቅ ሰው ነበር ” ሲሉም ፕሬዝዳንት ነጋሶ በአገሪቱ ያበረከቱትን በጎ ተግባር ጠቅሰዋል:: ዶክተር ነጋሶ በተለይም በፕሬዝዳንትነት የስልጣን ዘመናቸው አያሌ ውጣ ውረዶችን እና ፈተናዎችን ቢያሳልፉም በህይወት እስኪለዩ ድረስ በጽናት አብረዋቸው በትዳር ዘልቀዋል:: በትዳር በነበራቸው ቆይታም የአንዲት ሴት ልጅ ወላጆች ለመሆን ችለዋል :: ወይዘሮ አልበል በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ከተማ አዲሱ ገበያ በሚባለው አካባቢ በመሰረቱት እና ” ሬይጂና የቤተሰብ የጤና እና ማሕበራዊ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ” በተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አማካኝነትም ወላጅ አልባ ለሆኑ እንዲሁም ለችግረኛ ሕጻናት እና ሴቶች የጤና እና የምክር ግብረሰናይ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ:: የመጀመሪያ ልጃቸው ኢብሳ ነጋሶም ” ከአባቴ ጋር ብዙ ማከናወን የምንፈልጋቸው ጉዳዮችና ዕቅዶች ነበሩ :: አለመታደል ሆኖ ውጥናችንን ከግብ ሳናደርስ በህይወት ተለየን:: ዛሬ በሞቱ ብናዝንም መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቤተሰባችን አድርጎ ጥሎልን ስላለፈ እንጽናናለን ብሏል ::
 
ዶክተር ነጋሶ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት በተማሩበት ሙያ እና በፖለቲካ ተሳትፎ የተለያዩ ግልጋሎቶችን ያበረከቱ ሲሆን  ከከፍተኛ የትምህርት ትቋም በተመረቁበት ትምህርትም የኦሮሞን ባህል፣ ታሪክ እና እሴት የሚያንፀባርቁ እና የኢትዮጵያን አንድነት የሚያጠናክሩ የተለያዩ ጥናቶችን አካሂደዋል። በጀርመን የፍራንክፈርቱ ዮሃን ጎቴ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ እና ማህበራዊ ሳይንስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ካገኙ

Deutschland Abschied für Negasso Gidada in Frankfurt (DW/E. Fekade)

በኋላም በዛው በዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ የኦሮምኛን ቋንቋ ሰዋሰው እና ሥነልሳን ማወቅ ለሚፈልጉ ተማሪዎች ያስተማሩ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ እስኪመለሱም በአንትሮፓሎጂ የትምህርት ተቋምም ላይብረሪ ውስጥ ማገልገላቸውን ግለ ታሪካቸው ያስረዳል:: ባደረባቸው ህመም ከሁለት ሳምንታት በፊት በፍራንክፈርት ከተማ በህክምና የቆዩት ዶክተር ነጋሶ ባለፈው ቅዳሜ በ 76 ዓመታቸው ዛክዘን ሃውሰን በተባለ ሆስፒታል ውስጥ በልብ ህመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ከአስክሬን ምርመራው ውጤት ለማረጋገጥ ተችሏል:: በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ወይዘሮ ሙሉ ሰለሞን በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳን የአስክሬን ሽኝት ሥነ ሥርዓት ላይ ፕሬዝዳንቱ በስልጣን ዘመናቸው ለአገሪቱ አያሌ ተግባራትን ያከናወኑ ታላቅ ሰው መሆናቸውን አውስተዋል:: በዛሬው ዕለት የጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የፍራንክፈርት ቆንጽላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት እና ቤተሰቦቻቸው በፍራንክፈርት የካቶሊክ የሱስ ክርሽየ ቤተክርስቲያን ያዘጋጁት ሥነ ሥርአት እንዳበቃም አስክሬናቸው ወደ ፍራንክፈርት አውሮፕላን ማረፊያ ተሸኝቷል:: አስክሬናቸውን የያዘው አውሮፕላን ነገ ማለዳ ከንጋቱ 12 ሰዓት ኢትዮጵያ እንደሚደርስ የሽኝት መርሃግብሩ አስተባባሪዎች ገልጸዋል:: ዶክተር ነጋሶ ባለትዳር እና የሶስት ልጆች አባት ነበሩ:

የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ አስክሬን ዛሬ ማለዳ ላይ አዲስ አበባ ገባ።

አስክሬናቸው ከጀርመን ተነስቶ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች፣ ከፍተኛ የፌደራል እና የክልሎች ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተገኝተዋል።

በነገው እለትም በሚሌኒየም አዳራሽ አስክሬናቸው የሽኝት ስነ ስርዓት የሚከናወንለት ሲሆን፥ ከሰዓት በኋላም የቀብር ስነ ስርዓታቸው የሚከናወን ይሆናል።

ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ባለፈው ቅዳሜ ነበር በጀርመን ሀገር ህይወታቸው ያለፈው።

እንዳልካቸዉ ፈቃደ – ነጋሽ መሐመድ –  እሸተ በቀሌ 

DW አውዲዮውን ያዳምጡ

የቤተ እስራኤላውያን ልዑክ ለስሜን ብሔራዊ ፓርክ መልሶ ማገገምና ዘላቂ ልማት እንደሚሠራ አስታወቀ፤

በአምባሳደር በላይነሽ ዛቫድያ የተመራው የቤተ እስራኤላውያን ልዑክ ለስሜን ብሔራዊ ፓርክ መልሶ ማገገምና ዘላቂ ልማት እንደሚሠራ አስታወቀ፡፡የቤተ እስራኤላውያን ልዑክ ለስሜን ብሔራዊ ፓርክ መልሶ ማገገምና ዘላቂ ልማት እንደሚሠራ አስታወቀ፡፡

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 26/2011ዓ.ም (አብመድ) የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በእሳት አደጋ የደረሰበትን ጉዳት ለማዬትና በቀጣይ የሚያስፈልጉ ድጋፎችን ለመለየት በአምባሳደር በላይነሽ ዛቫድያ የሚመራ ልዑክ ከሰሞኑ ወደ ስፍራው ማቅናቱ የሚታወስ ነው፡፡ ልዑኩ የፓርኩን የጉዳት ሁኔታ ተመልክቶና ከአካባቢው ማኅበረሰብና አመራር ጋር ተወያይቶ ወደ ባሕር ዳር ተመልሷል፡፡

በባሕር ዳር ከተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ምክክር ማድረጉም ታውቋል፡፡ የልዑካን ቡድኑን የሚመሩት አምባሳደር በላይነሽ ዛቫድያ ‹‹በፓርኩ እሳት መነሳቱን ስንሰማ በጣም አዝነናል፤ ፓርኩ በርካታ ብዝኃ ሕይወት ያለበትና ከዓለም ትልልቅ ፓርኮች አንዱ የሆነ ሀብታችን ነው፡፡ አሁን ያጋጠመው አደጋ ቢወገድም ለወደፊት እንዴት መጠበቅ እንዳለበትና እንዲያገግም ምን መሥራት እንደሚያስፈልግ ለመለዬት የሚያስችል ግብዓት ለመውሰድ መጥተናል›› ብለዋል፤ የሚፈልጉትን ያህል መረጃ ማግኘታቸውንና ወደ እስራኤል ተመልሰው ከሚመለከታቸው ጋር እንደሚመክሩበትም አስታውቀዋል፡፡

የልዑካን ቡድ አባላት የተለያዬ የሙያ ስብጥር ያላቸውና ለዘላቂ ድጋፍ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ መሆናቸውም ታውቋል፡፡ የልዑካን ቡድኑ አባላት አምስት ናቸው፤ ከእነዚህም ውስጥ ዲፕሎማት፣ የደን ባለሙያ፣ የታሪክ ተመራማሪ እና አውሮፕላን አብራሪ ይገኙበታል፡፡

ልዑካኑ በደባርቅና ጎንደር ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል አመስግነዋል፤ በተለይ የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በእሳት አደጋ መከላከል ዙሪያ ትምህርትና ስልጠና ለመስጠት ፈር ቀዳጅ ሆኖ ሐሳቡን መቀበሉ እንዳስደሰታቸውም ገልጸዋል፡፡
የልዑካን ቡድኑን በባሕር ዳር ያነጋገሩት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደረጃ የአማራ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደን ነው፡፡ ‹‹ቤተ እስራኤላውያኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻን መሆናቸውን እናውቃለን፤ ያውቃሉ፡፡ አሁን ደግሞ በችግራችን ጊዜ ደርሰው ትክክለኛ የቁርጥ ቀን ወዳጆቻችን መሆናቸውን አሳይተውናል፡፡ ወደፊት ተቋማዊ በሆነ መልኩ ግንኙነታችንን የምናጠናክርበትና ከእስራኤል በርካታ ልምዶችን የምንቀስምበትን ሁኔታ እናመቻቻለን›› ብለዋል፡፡

እስራኤላውያን አነስተኛ የተፈጥሮ ፀጋን ለላቀ ጥቅም የማዋል ጥበብ እንዳላቸው ያስታወሱት አቶ ምግባሩ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በትምህርትና ስልጠና፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በስፋት ለመሥራት የክልሉ መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

‹‹ቤተ እስራኤላውያኑ አብዛኞቹ የተወለዱት ኢትዮጵያ ነው፤ አንዳንዶቹ እስራኤል የተወለዱም እንኳን ቢሆኑ ወላጆቻቸውና አያት ቅድመ አያቶቻቸው ከኢትዮጵያ ናቸው፤ ስለዚህ ሀገራችን ሀገራቸው ናት፡፡ የፀሎት ቦታዎቻቸው፣ መካነ መቃብሮቻቸው፣ ባድማዎቻቸው … አሁንም በክልላችን ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ መጥተው በክልላችን እንዲያለሙ ጭምር እንፈልጋለን›› ነው ያሉት፡፡
‹‹ከዚያም ሆነው ልባቸው ከዚህ እንደሆነ እናውቅ ነበር፤ በችግራችን ጊዜ ደርሰውም ይህንን አረጋግጠውልናል፡፡ ስላደረጉልን እገዛ በክልሉ መንግሥት ስም ቤተ እስራኤላውያንና መላው እስራኤላውያንን እናመሠግናለን›› ብለዋል፡፡

የኢፌዴሪ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳውም በሁለት ዙር የመጡትን የልዑካን ቡድን አመሥግነዋል፡፡ እስራኤላውያን ሰደድ እሳትን በመቆጣጠር ያላቸውን ልምድ መሠረት አድርጎ የኢፌዴሪ መንግሥት ሲጠይቅ የእስራኤል መንግሥት ፈጣን ምላሽ መስጠቱን አድንቀው ‹‹ቤተ እስራኤላውያኑ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው አደጋውን ለመጋፈጥና አሁንም አካባቢው እንዲያገግም አስተዋጽኦ ለማድረግ መምጣታቸው እጅግ የሚያስመሰግን፤ ከትክክለኛ እህትና ወንድም ደግሞ የሚጠበቅ ነው›› ብለዋል፡፡

በቀጣይ በተለያዩ ዘርፎች በትብብር ለመሥራትና በተለይ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ከቤተ እስራኤላውያኑ ልምድ እንደሚወሰድም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አብርሃም በዕውቀት –

Amhara Mass Media Agency