Category Archives: opinion/ ምልከታ

ይህ ገጽ ሙሉ በሙሉ ነጻና የአዘጋጁን አቁዋም የማያንጸባርቅ ነው።

“የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ” ወይስ ሌላ?

የባህርዳሩ ክስተት “የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ” ወይስ ሌላ?

መንደርደሪያ

ሰኔ 15 በባህርዳር የተከሰተውን ሁኔታ ተከትሎ እያነጋግሩ ካሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ ክስተቱ ምን ተብሎ መጠራት አለበት የሚለው ነው፡፡ ሁኔታውን ‹‹መፈንቅለ-መንግሥት›› ብለው የጠሩትና ቃሉን ለመጀመሪያ ጊዜ በደምበኛ(ሜይንስተሪም) ሚዲያ የተጠቀሙት በመንግሥት ሚዲያ የመጀመሪውን መግለጫ የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ አፈቀላጤ ንጉሡ ጥላሁን ናቸው፡፡ ከወደ አፍሪካ መሰል ዜና መስማት ብርቃቸው ያልሆነው የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም ይህንን ዜና ከጫፍ ጫፍ ተቀባብሎ ርዕሰ-ዜና ለማድረግ ጥቂት ጊዜ ብቻ ነበር የወሰደባቸው፡፡

ሁኔታው በዚህ መልኩ መገለጹ ያልተዋጠላቸው የኢንድኮት ኮሌጅ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ሰማኸኝ ጋሹ አበበ ‹‹መፈንቀለ መንግሥት ብላችሁ አትጥሩት›› ሲሉ ለኢትዮጵያ ኦብዘርቨር ጻፉ፡፡ የክርክራቸው ማዕከላዊ ነጥብ የመፈንቅለ መንግሥቱ ዋና ተዋናይ ሆኖ የተገለጸው ሰው ካለው የውትድርና ልምድና የፖለቲካ ንቃት አንጻር እንዲህ ዓይነት ሊሳካ የማይችልና ቢሳካ እንኳ በምን መልኩ ሊፀና ይችል እንደሆነ ግልጽ ያልሆነ እንቅስቃሴ ውስጥ ይገባል ብሎ ማሰብ ይከብዳል የሚል ነው፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የፈረንሳይ የዜና ወኪል ‹‹አምስት ጥያቄዎች በኢትዮጵያ ቀውስ ላይ›› በሚል ርዕስ ባተመው ጽሑፉ ላይ ያነጋገራቸው ዠራር ፕሩንዬ የተባሉ የአፍሪካ ቀንድ ተማራማሪ ‹‹መፈንቅለ-መንግሥት ትርጉም ያለው የወታደር ንቅናቄ ወይም እንደ አየርማረፊያና ሚዲያን የመሰሉ ወሳኝ ተቋማትን መያዝ የሚያካትት ክስተት በመሆኑ የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ የለም›› ሲሉ ተከራከሩ፡፡ ለዚሁ ትንታኔ ሀሳብ ያዋጣው ዊሊያም ዳቪሰንም አገራዊ ሥልጣንን የመቆጣጠር ሙከራ አልታየም ሲል የፕሩንዬ ሀሳብን ደግፏል፡፡

ደፋሩ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በፍትህ ጋዜጣ ላይ ‹‹ድንቄም መፈንቅለ መንግሥት›› በሚል ርዕስ ባስነበበው ረጅም ሀተታው ሁኔታውን ‹‹ግርግር›› ብሎ ለመጥራት አንድ አንቀጽ አልወሰደበትም፡፡ ‹‹መፈንቅለ-መንግሥት የሚያስብለው ነገር የለም›› ብሎ የደመደመው በሦስት ጉዳዮች በመንተራስ ነው፡፡ የመጀመሪያው በኢትዮጵያ ታሪክ ‹‹መፈንቅለ-መንግሥት›› ተብለው የሚታወቁ አጋጣሚዎችን ከክስቱቱ አኳያ በድጋሜ በመፈተሽ ነው፡፡ ሁለተኛውና ሦስተኛው ከሞላ ጎደል ቀደም ሲል ከቀረቡት ሀሳቦች የሚቀራረቡ ሆነው በመንግሥት መግለጫ ውስጥ የተጣረሱ መረጃዎች መኖራቸውና መፈንቅለ መንግሥቱ ‹‹ቁልፍ ተቋማትና ወሳኝ ዒላማዎችን›› የዘነጋ መሆኑ ጋር ተያያዘው የተነሱ ናቸው፡፡ እነዚህን ክርክሮች ከመጨረሻው በመጀመር ለማሄስ እንሞክር፡፡

መፈንቀል መንግሥት ምንድነው? ያልሆነውስ?

መፈንቅለ መንግሥት ምቹ ሁኔታዎቹ፣ መንስኤዎቹ፣ ስኬቱና ክሽፈቱን የሚያብራሩ ምክንያቶች በሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር ውስጥ የሚሸፈኑ ሁለንተናዊ ጽንሰ-ሀሳብ ነው፡፡ በተለይም በላቲን አሜሪካና በአፍሪካ ተደጋግሞ በመከሰቱ እስከ ቅርብ ጊዜ ድርስ ትልቅ ትኩረት የሚስብ የጥናት ርዕስ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ሰፊ ጽንሰ-ሀሳብና አድማሰ-ሰፊ ክስተትን በኢትዮጵያ ታሪክ ታጥሮ ለመበየንና ለመፈተሸ መሞከር ጉዳዩን ለኢትዮጵያ ብቻ የተሰጠ ‹‹ዋልያ›› ጽንሰ-ሀሳብ አድርጎ ከማቅረብ አይተናነስም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ምልከታ ምናልባትም የተወሰነ ስሜት የሚሰጠው በኢትዮጵያ ሕግ ‹‹መፈንቅለ-መንግሥት››ን በግልጽ የሚበይን ሕግ ካለ እሱን መሠረት አድርጎ ጉዳዩን የመተንተን ሙከራ ቢከተል ነበር፡፡ ይህም እጅግ ፖለቲካዊ የሆነውን ጉዳይ ጠባብና ህግ-ተኮር በሆነ አቀራረብ በመቃኘቱ ከትችት አያመልጥም፡፡

የመፈንቅለ መንግሥት ጉዳይን የመፈተሻው ተገቢው መንገድ በንጽጽራዊ የፖለቲካ ጥናት፣ እንዲሁም በታወቁ በጉዳዩ ላዩ የተጻፉ ድርሳናት መፈንቅለ-መንግሥት ተብሎ የሚጠራው ተግባር ዘመድ አዝማድ ከሆኑት ሥልጣንን በእጅ ለማስገባት ከሚያስችሉት ከሕዝባዊ አብዮት፣ ከአርነት ንቅናቄ፣ ከእርስ በርስ ጦርነት፣ ከውጭ ወረራ ባንድ በኩል፤ በሂደታቸው ከሚሳሰሉት ወታደሮች ጥቅምና መብታቸውን ለማስከበር ከሚያደርጉት አመጽና እገታ፣ ሽብርተኝነት፣ ከፖለቲካዊ ግድያና ከውንብድና ግርግር በሌላ በኩል፤ ተለይቶ የሚቀርብበትን ብያኔ በማስቀመጥ ነው፡፡

ይህ አቀራረብ የባህርዳሩን ክስተት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መሆኑን ወይም አለመሆኑን ለመወሰን፤ ካልሆነ ደግሞ ቀደም ሲል ከተጠቀሱት ተመሳሳይ ሁኔታዎች ወደ አንዱ ለመመደብ ይረዳናል፡፡ በቀጥታ ጉዳዩን በዚህ መልኩ ከማየት በፊት መፈንቅለ መንግሥትን በተመለከተ መረጃ የሚያደራጁ አንዳንድ ተቋማት ‹‹የመፈንቅለ መንግሥት ሴራ(በውጥን ላይ ሳለ የከሸፈ)(1)፣ ያልተረጋገጠ የመፈንቅለ ሴራ (ሴራ ተብሎ የቀረበ ነገር ግን ሴራው ለመኖሩ አስተማማኝ መረጃ ያልተገኘለት)(2)፣ ያልተሳካ መፈንቅለ መንግሥት(3)ና የተሳካ መፈንቅለ መንግሥት(4) ብለው በመልክ በመልክ እንደሚያስቀጧቸው ማንሳት ጠቃሚ ነው፡፡

የኤድዋርድ ሉትዋክ ‹‹መፈንቅለ መንግሥት፡- ተግባራዊ መመሪያ›› የተሰኘው መጽሐፍ በርዕሰ-ጉዳይ ከተጻፉ ድንቅ መጽሐፍት መካከል አንዱ ተደርጎ በብዙዎች የሚጠቀስ ነው፡፡ ደራሲው መፈንቀለ መንግሥት በሰፊው ሕዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ የማይታገዝና እጅግ ግዙፍ የሆነ የጦር ውጊያን እንደማያካትት ያትታል፡፡ በተጨማሪም መፈንቅለ መንግሥት ድርጊቱ ከተሳካ በኋላ ሊወሰድ የሚችለው የፖሊሲ አቅጣጫ በግልጽ የሚታወቅ አለመሆኑን በመጥቀስ መፈንቅለ መንግሥት ‹‹consists of the infiltration of a small but critical segment of the state apparatus, which is then used to displace the government from its control of the remainder.› ሲሉ ይበዩናታል፡፡ (የተቀረው(የመፈንቅለ መንግሥቱ ተሳታፊ ያልሆነው) የመንግሥት ክፍል ያለውን የሥልጣን ቁጥጥር ለመግፈፍናና ለመተካት አነስተኛ ግን ወሳኝ የሆነ የመንግሥት መዋቅር ክፋይን የማስረግ ሂደትን የያዘ ተብሎ በግርድፉ ሊተርጎም ይችላል፡፡)

ክላየን ማዕከል ለዴሞክራሲ የተባለ ተቋም በመፈንቅለ መንግሥት ፕሮጀክቱ መፈንቅለ መንግሥትን ድንገተኛና ኢ-መደበኛ (ሕግ በጣሰና በሕግ ባልተደነገገ አግባብ) በራሱ የቆመ መንግሥትን አስፈጻሚ አካል ማስወገድና ፈንቅሎ ሥልጣኑን በቁጥጥር ስር ማዋል ብሎ ይተረጉመዋል፡፡ ሴንተር ፎር ሲስተሚክ ፒስ የተሰኘ ተቋም በበኩሉ ከማኅበራዊ አብዮት፣ በእርስበርስ ጦርነት አማጺ ኃይሉ አሸናፊ ከሚሆንበት ሁኔታና ከሕዝባዊ አመጽ የተለየ መሆኑን በማስመር መፈንቅለ መንግሥት በአንድ አገር የገዥ ወይም የፖለቲካ ልሂቃን መካከል አፈንጋጭ ወይም ተቃዋሚ በሆነ አንጃ በማስገደድ የሚደርግ የሥልጣን ንጥቂያ አድርጎ ያቀርበዋል፡፡ አንድ መፈንቅለ መንግሥት ተሳካ የሚባለው መፈንቅለ መንግሥቱን ያሴረው ጥቂት ሀይል ሥልጣን ነጥቆ የራሱን ሥልጣን ማንበር ሲችል ነው፡፡ በአንጻሩ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ደግሞ እንዲህ ዓይነቱን ዓላማ ለማሳካት የተወሰዱ እርምጃዎች የተነሱበትን ግብ እውን ሳያደርጉ ሲከሽፉ የሚፈጠረውን ሁኔታ የሚገልጽ ነው፡፡

ከላይ ከቀረቡትና ከሌሎች በርካታ ተመሳሳይ ብያኔዎች እንደምንረዳው መፈንቀለ መንግሥት ወይም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ግዴታ ደም አፋሳሽ መሆን ባይጠበቅበትም ከሴራና ዕቅድ ባሻገር ራሱን ትርጉም ባለው ደረጃ በተግባር መግለጽ አለበት፡፡ ዓላማውም አመራር ከመግደል፣ መብትና ጥቅምን ከመጠየቅ ባለፈ ሕግን ባልተከተለ አግባብ አስፈጻሚውን ለመገልበጥ ዒላማ ያደረገ መሆን ይገባዋል፡፡ እዚህ ላይ አብዛኞቹ ብያኔዎችም ‹‹መንግሥት›› ሲሉ በአመዛኙ በማዕከል ያለ መንግሥትን እያሰቡ መሆኑን ማስታወስ ይገባል፡፡ በፌዴራል ሥርዓት ሁለት መንግሥታት መኖራቸው ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት አሁን ትርጉም ያለው የአመጽ ሀይል የሚያዝ በተግባርም የፌዴራል መንግሥቱን በአንዳንድ ሁኔታዎች ለመገዳደር የበቃ የክልል መንግሥት የተፈጠረበት ሁኔታ ላይ እንደምንገኝ ግንዛቤ ውስጥ መክተት ይገባል፡፡ በመሆኑም በክልል ደረጃ የሚደረግ መንግሥትን የመገልበጥ ድርጊት ከልማድ አንጻር ሲታይ እንግዳ ነገር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የክልል መንግሥት የሚባል መዋቅር እስካለና በዚሁ ደረጃ የሚደረግ ትርጓሜውን የሚያሟላ እንቅስቃሴ ከተደረገ መፈንቅለ መንግሥት ተብሎ ቢጠራ የተገባ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ቢያንስ አንድ መፈንቅለ-መንግሥት ተብሎ የሚጠራ ድርጊት በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ ይህም በ1898 በአሜሪካ Wilmington, North Carolina በአካባቢ መንግሥት ላይ የተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ነው፡፡ በመሆኑም በክልል ደረጃ መፈንቅለ መንግሥት ሊደረግ አይችልም ብሎ መደምደም ስህተት ነው የሚሆነው፡፡

ቁልፍ ተቋማትና ሚዲያ መቆጣጠር፡- እንደ መፈንቅለ መንግሥት መለኪያ?

በሰሞኑ በሶሻል ሚዲያ ከሚሰጡ አስተያየቶችና መግቢያው ላይ ከተወሱት አስተያየቶች እንደምንረዳው አንድ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሚዲያና አየር ማረፊያን ካልተቆጣጠረ ሊያጠቃው የሚችለውን ሃይል አስቀድሞ ካላጠቃ በዚህ ስም ሊጠራ አይገባም የሚሉ ዓይነት ክርክሮች ይደመጣሉ፡፡ መፈንቅለ መንግሥቶች በጣም የተለያዩ የመሆናቸውን ያክል የሚከተሉት ስልትም የተለያየ ነው፡፡ የድርጅትና የቅንጅት አቅማቸው፣ የዕቅዳቸው ጥራት፣ የሚያሰማሩት የሰው ኃይል ብዛትና ጥራትም እንዲሁ፡፡ እርግጥ ነው መፈንቅለ መንግሥቶች የሚሳኩት ከሞላ ጎደል ማድረግ የሚገባቸውን ሁሉ ሲያደርጉና በጥንቃቄ በተተለም ዕቅድ በምቹ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ድባብ ላይ ሲካሄዱ ነው፡፡ በአንጻሩ የከሸፉ ሙከራዎች ግን የከሸፉት ማድረግ የሚገባቸውን ስላላደረጉና የተካሄዱበት ወቅትና ሁኔታ ድርጊቱን የማይደግፍ ሲሆን ነው፡፡

ስለዚህ ክርክሩ መሆን ያለበት አንድን በግልጽ መንግሥትን በኃይል ለመገልበጥ አስቦ የተንቀሳቀሰ አካል ‹‹ይህን ስላልተቆጣጠረ›› የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሊባል አይችልም ሳይሆን የተሳካ እንዲሆን ይህን መቆጣጠር ነበረበት ተብሎ ነው መቅረብ የሚገባው፡፡ በሌላ አነጋገር በተዘረከረከ ሁኔታ የታቀደና የተተገበረ መንግሥትን የመገልበጥ ጥረት ወሳኝ ግቦች ሳይሳካ ባጭሩ ቢቀጭ ዕቅዱና አተገባበሩ ሊተች ይችል ይሆናል እንጅ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተብሎ ከመጠራት ውጭ ሌላ ዕድል የለም፡፡ በመሆኑም ሚዲያና መሰል ወሳኝ ተቋማትን መቆጣጠር ከመፈንቅለ መንግሥት መሳካት/መክሸፍ ጋር ካልሆነ በስተቀር ከአንድ ክስተት መፈንቅለ መንግሥት(የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ) መሆን/አለመሆን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የለውም፡፡

በሌላ በኩል የሚዲያው ጉዳይ ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ የቀረበውን ችክ ያለ ክርክር ስንመረምረው ሀሳቡ በተወሰነ መልኩ ሃያኛው መቶ ክፍለ-ዘመን ላይ ተቸክሎ የቆመ እንደሆነ ይገባናል፡፡ እንዲህ ሶሻል ሚዲያ በሌለበት፣ የግል ሚዲያ ባልተስፋፈበትና አንድ ብሔራዊ ሚዲያ የመንግሥት ምልክትና ራሱ መንግሥት ሆኖ በሚታይበት ባለፈው ምዕተ ዓመት(በተለይም በአዳጊ አገራት) በእርግጥም ሚዲያን ሳይቆጣጠሩ የተሳካ መፈንቅለ መንግሥት ማካሄድ የማይታሰብ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በዚያ ዘመን ሚዲያን መቆጣጠር ብቸኛውን የመንግሥት ልሣን መዝጋትና በዚያም የራስን መልዕክት ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን ወሳኝ ትዕምርታዊ(symbolic) ዋጋ ያለው ተግባር ነበር፡፡ የመንግሥት ሚዲያ ይህ ዓይነቱ ሚና አሁን ላይ አለው ማለት ያስቸግራል፡፡ የመንግሥት ሚዲያ ከሚዲያዎች መካከል አንዱ ወደ መሆን ወርዷል፡፡ ሚዲያን መቆጣጠር ለመፈንቅለ መንግሥት ስኬት ያለውን ሚና ማናናቅ ባይገባም የቱርኩ ፕሬዝዳንት በቅርቡ የተቃጣውን መፈንቅለ መንግሥት እንዲከሽፍ ማድረግ የቻሉት በፌስታይም በተላከና በግል ሚዲያ በቀረበ የቪዲዮ መልዕክት መሆኑ ስለዘመኑ መቀየር የሚነግረን ነገር ትልቅ ነው፡፡

‹‹ስሜት አይሰጥም ስለዚህ መፈንቅለ መንግሥት ሊሆን አይችልም!››

ሁኔታውን የ‹‹መፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ›› ብላችሁ አትጠሩት የሚሉት ሰዎች የሚያነሱት ሌላው ሀሳብ፣ የክስተቱ ዋና ተዋናይ ሆነው የቀረቡት ሰው የፌዴራል መንግሥቱ በቀላሉ እንደሚያከሽፈው የታወቀ በክልል ደረጃ እንዲህ ዓይነት ምንም ስሜት የማይሰጥ ተግባር ሊፈጽሙ አይችሉምና ጉዳዩ መፈንቅለ መንግሥት ሊሆን አይችልም የሚል ነው፡፡ የዚህ ክርክር አስኳል ‹‹ሊደረግ አይችልም›› እንጅ መደረጉ ቢረጋገጥ ጉዳዩ የ‹‹መፈንቅለ መንግሥት›› ሙከራ ተብሎ አይጠራን የሚያካትት አይመስልም፡፡

እዚህ ላይ ሁለት ነገር ማንሳት ይገባል፡፡ የመጀመሪያው የትግራይ ክልል ሕግንና የፌዴራል መንግሥቱን ሥልጣን በመጋፋት የፌዴራል ፖሊስ የሚያግትበት፣ የሀገር መከላከያ እንቅስቃሴን የሚያስተጓጉልበት፣ በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች ምሽግ የሚሆንበት ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ባለበት፤ በክልል ደረጃ የተሳካ መፈንቅለ መንግሥት አድርጎ መሰንበት በጭራሽ አይቻልም ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ከባድ ነው፡፡ ሁለተኛ ድርጊቱን መሩ የተባሉት ሰው ነገሮችን የሚገመግሙበትን ሚዛን፣ የነበሩበትን አጠቃላይ ሁኔታና ወደዚህ ዓይነት ውሳኔ ሊገፋቸው የሚችለውን ምክንያትና ስሜት በሚገባ የማያውቅ ሰው ባልተሟላ መረጃ ሀሳባቸውን በሩቅ ‹‹ወለፈንዲ›› ነው ብሎ መደምደምም የሚቸግር ነገር አለው፡፡ ሌላው ደግሞ እጅግ የተራቀቀ አዕምሮ አለው የምንለው ሰው ሁሉ አንዳንዴ በጎዶሎ ቀን በተስፋ መቁረጥ፣ በተለያዬ ሀይል ግፊትና የስሜት ውጣ ውረድ ‹‹የሕፃን ጨዋታ›› የሚመስል ነገር ለመሥራት ሊሠናዳ የሚችልበትን ዕድል ዝግ አለመሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡

መውጫ

ቀደም ሲል የቀረቡት አናቅጽ ለመጠቆም እንደሞከሩት፣ የባህርዳሩን ክስተት (ከአዲሳባው ጋር ሳይገናኝ) በመንግስት ከቀረቡት መረጃዎች መካከል በተመረጡ የመንግሥት ተቋማት ላይ የተወሰዱት እርምጃዎች በጸጥታ ቢሮ ኃላፊው የተመሩ መሆናቸውና ይህም እርምጃ የተወሰደው ለጋዜጠኛው በስልክ እንዳብራሩለት ‹‹የአማራን ጥያቄዎች ቀልብሷል›› ያሉትን አመራር ማስወገዳቸውና እንዲሁም ትዕዛዝ ከሳቸው እንዲመነጭ መፈለጋቸው እውነት መሆኑ ብቻ ክስተቱን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ብሎ ለመጥራት በቂ ነው፡፡ በኔ ግምገማ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ጥያቄ ሊነሳ የሚችል ቢሆንም እነዚህ አጠቃላይ ሁለት መረጃዎች ውሸት ናቸው ብሎ ለመጠራጠር በቂ ምክንያት ስለሌለኝ ክስተቱን በዚህ ስም መጠራቱ ‹‹ድንቄም›› የሚያሰኝ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ይሁንና ሙከራው በክልል ብቻ ታጥሮ የታቀደ መሆኑ የመጨረሻ እውነት ከሆነ ቢያንስ ዒላማው ባደረገው የሥልጣን ማዕከል ጋር በተያያዘ መፈንቅለ መንግሥቱ ‹‹እንግዳ›› ባሕርይ ያለው አድርገን እንድንቆጥረው ያስገድደናል፡፡

አንድን ጉዳይ ‹‹ መፈንቅለ-መንግሥት›› ብሎ መጥራት በሚፈጥረው አጠቃላይ ድባብ፣ መንግሥት ምላሽ አድረጎ በሚያሰማራው ኃይልና የእርምጃ ደረጃ ጋር በተያያዘ የሚያስከትለው መዘዝ ስላለ፣ ስም ማውጣት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ውይይት “what is in the name?’’ ብልን ልናጣጥለው የምንችለው ዓይነት አይደለም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ግን ክስተቱ የፈለቀበትን ህመም፣ ፖለቲካዊ አንድምታውን፣ ከሁኔታው አገግመን በሁለት እግራችን የምንቆምበት መንገድ ላይ ከምናደረገው ወሳኝ ውይይት ልናጠፋው ከሚገባው ጊዜ ሰርቆ እንዲወስድብን መፍቀድ የለብንም፡፡ ለምን ሆነ? ምን ሆነ? መንግስት ምን ምላሽ ሰጠ? በክልሉና በሀገር ፖለቲካ ምን ዳፋ አስከተለ? ጉዳት ቀንሰን በአጠረ ጊዜ እንዴት እናገገም? ወ.ዘ.ተ ጥያቄዎች ላይ መወያየት የበለጠ ይበጃል፡፡

source syome teshome fb

ለውጡና … ሕዝብ መስፍን ወልደ ማርያም

አንዳንድ ሰዎች ለውጥ የለም ሲሉ አንዳንዶቹ ደግሞ ስር-ነቀል ለውጥ ተደርጓል ይላሉ፤ ለእኔ ግን ከደርግ የመጀመሪያ ዓመት የሚመሳሰል እንዲያውም ከፍ ያለ ለውጥ አይቼበታለሁ፤ ሆኖም እዚህ አጉል ክርክር ውስጥ አልገባም፤ነገር ግን የተከታተልሁትን ያህል እንደገባኝ እኔ ለውጥ የምለውን ልናገር፤ በዘር ፖሊቲካ የተለያዩ ወንጀሎች እየተለጠፉባቸው ከዕድሜ ልክ እሰከሞት በአሻንጉሊት ዳኞች እያስፈረዱ እስርቤቶቹን ሞልተው እንደነበረ እናውቃለን፤ ዛሬ እነዚህ ሰዎች ሁሉ በነጻ በየቤታቸው ናቸው፤ ይህ ለብዙ ቤተሰቦች ለውጥ ነው፤ ከሁሉም በላይ ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት ጋዜጦች፣ ራዲዮኖችና፣ ቴሌቪዥኖች እንደልባቸው እንዲጨፍሩ አድርገዋል፤ ይህም በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ለውጥ ነው፤ የፖሊቲካ ቡድኖች ሁሉ እንደልባቸው በነጻነት እየተሰበሰቡ ፐሮግራማቸውን መግለጽና መዘዋወር ችለዋል፤ እንዲውም አንዳንድ የፖሊቲካ ቡድኖች ለውጡ ያመጣውን ነጻነት ወደስድነት ለውጠውት ብዙ ጥፋትን ሠርተዋል፤ ስለዚህ የአገዛዙ ኃይል በለውጡ ምክንያት ሲላላ እኩይ ኃይሎች ይበረታሉ፤ እስከዛሬም ቢሆን እኩይ ኃይሎች እንደተጠናከሩ በመሆናቸው ብዙ ሰዎች መንግሥት መኖሩን ይጠራጠራሉ፡፡

የማስታወስ ችሎታችን ያነሰ በመሆኑና አዲስ ትውልድ በመፍላቱ አናስታውስ ይሆናል እንጂ ደርግ ሥልጣን ሲይዝ ከአንድ ዓመት ያህል በላይ መንግሥት አልነበረም ይባል ነበር፤ ጸሐፌ ትእዛዝ አከሊሉ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት በፈቃዳቸው ሲሰናበቱ ወንበሩ ለብዙ ወራት ብዙዎችን እያጓጓ ባዶውን ተቀምጦ ነበር፤ ለጥቂት ወራት በጭንቀት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቢሮ በተከታታይ የያዙት ልጅ እንዳልካቸው መኮንንና ልጅ ሚካኤል እምሩ ነበሩ፤ጃንሆይ ከዙፋናቸው የወረዱት ጸሐፌ ትእዛዝ አከሊሉ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሰናበቱ ከዘጠኝ ወራት በኋላ ነው፤ በመሀከሉ የልጅ እንዳልካቸውና የልጅ ሚካኤል ጠቅላይ ሚኒስትርነት እንደነበረ አልረሳሁም፤ ነገር ግን በልጅነት የተቀጩ በመሆናቸውና ፋይዳም ስላልነበራቸው ችላ ብያቸው ነው፡፡

ደርግ ሥልጣን ሲይዝ መንግሥት አልነበረም ቢባልም ሥርዓት አልባነትን የመቆጣጠሪያ ጉልበትና ቁርጠኛነት ነበረው፤ አሁን ግን የተፈለገው ከጉልበት ይልቅ ሕጋዊነት. ከዚያም አልፎ ፍቅር፣ ይቅር ባይነትና ሰላም በመሆኑ ለማኅበረ እኩያን ሁኔታዎችን ያመቻቸ ይመስላል፤ ስለዚህም በኢትዮጵያ ያለው ሥርዓት አልባነት ቢያንስ ለጥቂት ወራት የሚቀጥል ይመስለኛል፤ ይህንን የሥርዓት አልባነት ዘመን ለማሳጠር በሥልጣን ላይ ያሉት ከያዙት የክርስቲያን መንገድ የማይቃረን ዘዴ በቶሎ ቢፈልጉ ከብዙ ጥፋት እንድናለን፡፡

1. ባለሥልጠኖችና ለውጡ

ዛሬ በሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች የኢሕአዴግ አባላት ናቸው፤ ሁለቱም ዓቢይና ለማ የኦሕዴድ አባላት ናቸው፤ እንግዲህ ለውጥ አድራጊዎቹ ሁለቱም የኦሕዴድ አባሎች ናቸው፤ የብአዴን ሰዎች ጎልተው አልታዩም፤ እነዚህ ሁለት የኦሕዴድ ባለሥልጣኖች በአንድ በኩል ራሳቸውን ከአደጋ ለመከላከል በጣም ከባድ ጥረት ያደርጋሉ፤ በሌላ በኩል ለውጡን ወደፊት ለመምራት ይለፋሉ፤

የለውጡ ባለሥልጣኖች በሦስት ኃይሎች ተወጥረዋል። በአንድ በኩል ሥልጣኑን የተቀማውና ያኮረፈው ቡድን ምቹ አጋጣሚ እየጠበቀ ሰላምን ያደፈርሳል፤ በየደረጃው በሥልጣን ላይ ያሉት ደግሞ እንዳይነጠቁ በየፊናቸው እንቅፋቶችን ይፈጥራሉ፤ በተጨማሪ ደግሞ ለውጡ ቀሰስተኛ ሆነብን እያሉ የሚጮሁ አሉ፤ ቆም ብሎ በማሰብ ፖሊሶችን፣ ዓቃብያነ ሕጎችን፣ ዳኞችን በሙሉ አስወጥቶ እንደሀገር መቀጠል እንደማይቻል መገንዘብ አያስቸግርም፤ በሌሎች የተለያዩ ሥራዎችም በወደቁት ባለሥልጠኖች የተሾሙት ሁሉ ስርስሩን መርዝ እየነሰነሱ የሚያደናቅፉ ናቸው፤ ትልቁ የለውጡ መሪዎች ፈተና በጎሠኞች መሀከል የተፈጠረው ፉክክርና ግጭት ነው፡፡

የለውጡ መሪዎች በአላቸው ችሎታ ሁሉ በሰላማዊ መንገድ ሕዝቡን መምራት ይፈልጋሉ፡፡

2. ምሁራንና-ለዉጡ

ምሁራን ማለትን በትክክል ያሳወቀን የለም፤ ስለዚህ እኔ ሆዱ ሰፊ የሆነና ስምንተኛ ክፍል ጨርሶ በፌስቡክ ላይ የሚጽፍ ሁሉ ምሁር ነው ብዬ እነሣለሁ፤ ከዚያ በላይ በአሥራ ሁለተኛ ክፍል በኩልም ይሁን በሌላ በአቋራጭ መንገድ የሚገኙትን የትምህርት መጠሪያ ጌጦች ሁሉ ከነዝባዝንኬያቸው የታቀፉ ሁሉ ምሁራን ናቸው፤ ቄንጠኛ ባርሜጣ ያደረጉና ጥቁር መነጽር የሚያደርጉትንም እጨምራቸዋለሁ፤ የሚሽሎከሎኩም ይኖሩ ይሆናል፡፡

አብዛኛዎቹ ምሁራን ለለውጡ ገለልተኞች አይደሉም፤ እንዲያውም አብዛኛዎቹ ምሁራን ለውጡ የመጣባቸው ናቸው፤ እነዚህ የአንጀራ ምሁራን በእንጀራቸው ለሚመጣ ነገር ዕድሜያቸውም ሆነ ምኞታቸው ለገለልተኛነት አያበቃቸውም፤ በአጠቃላይ ነባር ምሁራን ነባር ሁኔታው የተኙበት ነውና ለውጥን አይደግፉም፤ የእነሱን እንጀራ ለማያወፍር ለውጥ ተቃዋሚ እንጂ ደጋፊ ሊሆኑ አይችሉም፤ በመሠረቱም የእንጀራ ምሁራን ከለውጥ ጋር የሚሰለፉት የተሻለ ወፍራም እንጀራ የሚያቀርብላቸው ሲሆን ብቻ ነው፡፡

አንዳንዶቹ በአማካሪነት፣ በሎሌነት፣ ወይም በአጨብጫቢነት ከመሪዎቹ አጠገብ ለመጠጋት ይፈልጉ ይሆናል፤ አንዳንዶቹ ሥራቸውን፣ ችሎታቸውን በደህና ዋጋ ለመሸጥ ይጥራሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ መንጠላጠያ ጨብጠው ወደሌላ ዓለም ተምዠግዥጎ ለመብረር ይመኛሉ፤ በአገራቸው ተተክለው የሚቀሩ በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡

ለምሁራን ራሳቸውን ከፍ ለማድረግ የለውጡን መሪዎች ዝቅ አድርጎ መገመት መነሻቸው ይመስለኛል፤ ጥንት በአጼ ዘመን ካሣ ወልደ ማርያም የኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት እንዲሆን ሲሾም እኔ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ማኅበር ፕሬዚደንት ነበርሁ፤ በዚህም የተነሣ ለካሣ የምሥራች ደብዳቤ እንጻፍለት ብዬ ሀሳብ አቀረብሁ፤ በዚያን ጊዜ የሰማሁት ተቃውሞ ዛሬ በነዓቢይ ላይ ከሚሰነዘሩት የተለየ አልነበረም፤ ‹‹እኛ የምናውቀውን እነሱ አያውቁም፤ እኛ የምናየውን እነሱ አያዩም፤ እኛ የምንሰማውን እነሱ አይሰሙም፤›› ለድንገተኛ አዲስ ነገር በደመ ነፍስ እንዲህ ዓይነቱን አስተያየት ስንሰጥ እጅግም አያስደንቅም ይሆናል፤ ነገር ግን ሲውል ሲያድር አስተያየታችን ካልተሻሻለ ለውጡን ወደፊት ከመግፋት ይልቅ ወደኋላና ወደጠብ አጫሪነት የሚወስድ ይሆናል፤ የለውጡ መሪዎች ምሁራን ከሚባሉት ያላነሰ እውቀት እንዳላቸው ለመቀበል ትንሽ መመራመርና እውነቱን ማወቅ አስተያየታችንን ያቃናልን ነበር፤ እንዲያውም እንደዓቢይ አህመድ ያለ በብዙ መስኮች በቃሉ የማውረድ ችሎታ ያለው አላውቅም፤ ሊቅ የሚባሉት እንትና እንዲህ አለ፤ እንትና እንዲህ አለ በማለት የሠለጠኑ ናቸው፡፡

3. ሕዝብ

በአጠቃላይ በሕዝቡ በኩል ስለለውጡ ያለው ስሜት እኔ እንደምገምተው በቀል ነው፤ በተለያዩ ሁኔታዎች በድለውናል የሚሏቸውን ባለሥልጣኖች ከሥልጣን ማውረድ ዋናው ፍላጎት ይመስለኛል፤ ይህ ስሜት ወደወጣቶቹ ዘንድ ሲደርስ ኃይልና እልህ ጨምሮ ለግጭት ሊያደርስ ይችላል፤ የማይፈለጉት ባለሥልጣኖች ሁሉ በአንድ ጊዜ ከሥልጣናቸው ቢነሡ የሚከተለውን ትርምስ መገመት አያስቸግርም፡፡

ሕዝቡ እየተረገጠና እየተጠቃ ለዘመናት ይኖራል፤ በደሉንና ቂሙን ድብቅ አርጎ ይዞ ኖሮ የአገዛዝ ለውጥ ሲመጣ የትእግስት ቋቱ ከጫፍ ጫፍ ይተረተራል፤ ፍቅር፣ ውለታና ጉርብትና መቃብር ተቆፍሮላቸው ይገባሉ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቂሙን አይረሳም፤ ቂሙን ደብቆ በምሥጢር ይይዝና ለዘመናት ቆይቶ አጥቂ የነበረው ኃይል ጥቃት ሲደርስበት የኢትዮጵያ ሕዝብ እየፎከረና እልል እያለ በቀሉን ለመወጣት ይጥራል፤ በሰዎች ላይም ሆነ በንብረት ላይ የሚያደርሰው ጥፋት ከፍተኛ ነው፤ በእንደዚህ ያለው ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለበቀልና ለዘረፋ እየፎከረ ይወጣል፤ የሕዝቡ አትኩሮት ባለፈው በደሉና በበቀል ናፍቆቱ ላይ ነው፤ ወደኋላው እንጂ ወደፊት አያይም፤ የወደቀውን አገዛዝ በተሻለ ለውጦ የወደፊት ኑሮውን ለማሻሻል እንዲያስብ መወያየት ያልተለመደ ነው፡፡

ሦስቱም ሃይማኖቶች በነገሡባት አገር፣ ኢትዮጵያ፣ በታሪክ ጸሐፊዎች ሁሉ የክርሰቲያን ደሴት ትባል ነበር፤ ታሪኩን የጠቀስኩት ዓቢይን ለማስገባት ነው፤ ዓቢይ አህመድ በዓቢይ ስሙ ላይ አህመድን ጨምሮ ብቅ ሲል ያልተደነቁት ወሎዬዎች ብቻ ይመስሉኛል፤ ኢትዮጵያ የተደነቀችው ዓቢይ አህመድ ፍቅር፣ ይቅር ባይነት፣ ሰላም … እያለ ብርቅ የሆነበትን ክርስትና መስበክ ሲጀምር ነው! የእናቱ ወሎዬነት አደናቅፎበት አልፎት ይሆናል እንጂ ክርስትና በኢትዮጵያ ከተሰበከ ከሁለት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት በላይ ሆኖታል፤ አበሻ ክርስትናን ያሸነፈው በሆዱ ነው፤ አበሻ ለሆዱ ያለውን ፍቅር ዓቢይ መማር ያስፈልገዋል፡፡

ከተለያዩ የውጭ ኃይሎች ጋር የተቃቀፉ ኢትዮጵያውያን ስለኢትዮጵያ የወደፊት ሁኔታ እያጠቆሩና እያመረሩ ያወራሉ፤ ገና ካልደረሰችበት አፋፍ እያንከባለሉ ሊያወርዷትም ይዳክራሉ፤ ሲአይኤ ከሠላሳ ዓመታት በፊት የጠነሰሰውን የኢትዮጵያ ውድቀት ትንበያ ገና አሁን ያነበቡት ምሁሮች ያለማቋረጥ ዛሬ ያነበንቡታል፤ ኢትዮጵያን ትተው ሄደው አሁንም የዳቦ መብያቸው ኢትዮጵያ ነች፤ የፈረንጆችን ዓላማ ለማሳካት ኢትዮጵያን መደፍጠጥ ዳቦ የሚያበላ ሥራ አድርገውታል፤ ለውጡን ለመምራት፣ አቅጣጫውን ለማስለውጥ፣ ፍጥነቱን ለመቀነስ፣ አካሄዱን ለማደናቀፍ የሚጥሩ ክፍሎች በውጭ እርዳታ እንደልባቸው ይንቀሳቀሳሉ፤ ልናውቃቸው ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ አጆቿን ወደእግዚአብሔር ትዘረጋለች፤ ይዞ ይደግፋታል!

የጌታቸው አሰፋ አፈጣጠር – ጌታቸው አሰፋ እስኪገኝ…

ዋናው ሰውዬ (አቶ መለስ) ሰሞኑን የደህንነትና የስለላ ኃላፊ በሞት ከተለየ (ከተወገደ) በኋላ ያንን ለሥልጣን መዋቅራቸው ምሰሶ የሆነውን ቦታ ለማንም አሳልፈው መስጠት እንደሌለባቸው አምነዋል። በተለይ ከቅርብ የትግል ጓዶቻቸው በተደጋጋሚ እየተሰነዘሩባቸው የሚመክቷቸው በሥልጣናቸው ሕልውና ላይ የሚቃጡ ሙከራዎች፣ በደህንነቱ ቢሮ በኩል ከመጣ መቋቋሙ ሊከብዳቸው እንደሚችልም ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው ተገንዝበዋል። በዚያ ላይ የደህንነት ሹመኞችን እንዳይከዷቸው መለማመጡ፣ አንዳንዴም እሳቸው ከበድ ያለ ኦፕሬሽን እንዲካሄድ ፈልገው ቶሎ በመፈፀም ፈንታ “ይኼማ እንዴት ይሆናል” የሚሉ የሕግና የተገቢነት ጥያቄዎች መነሳታቸው ሲያበግናቸው ኖሯል።

ዋናው ሰውዬ ይህን ችግር ለመፍታት ለሁለት ሳምንታት ሙሉ ሲታገላቸው የከረመውን ሀሳብ አምጠው ወልደው መቋጫውን ስላገኙለት፣ የተጫጫናቸው የድካም ስሜት በአንዴ ሲለቃቸው ታወቃቸው። በሲጋራ ብዛት የጠቆረውን ከንፈራቸውን ፈልቀቅ፣ በጊዜ ዕጦት ጭፍርር ያለውን ጢማቸውን ገለጥ፣ አድርገው በበለዙ ጥርሶቻቸው ብቻቸውን ፈገግ አሉ። በሰሞኑ የቢሮ ውሏቸው፤ ሀሳባቸውን ለማቀጣጠል ያግዝ ይመስል በየ 30 ደቂቃዎቹ ሲያቦኑ የሰነበቱትን ሲጋራ፣ ለዕለቱ የመጨረሻቸው የሆነችዋን አንድ ፍሬ ኒያላ ከፓኳቸው አውጥተው በደስታ ስሜት እንደ ድል ችቦ ለኮሱ።

በደስታ ታጅበው ካሳለፉት ከስኬታማው ምሽታቸው በኋላ ወደ መኝታቸው ከማምራታቸው በፊት ስልካቸውን አነሱ። ከህወሓት አምስት፣ ከብአዴን ደግሞ ሶስት ቁልፍ ሰዎቻቸውን እና ሚስጥረኞቻቸውን መርጠው በጠዋት ጽ/ቤታቸው እንዲገኙ እንዲያደርጉ ለአቶ በረከት ጥብቅ መልዕክት አስተላለፉ። የተጠሩት ጓዶች ከአንድ ሳምንት በፊት ስለ ስብሰባው ርዕሰ ጉዳይ ፍንጭ በሚሰጣቸው መልኩ በሰውዬው ጽ/ቤት ለሌላ ጉዳይ በተገኙበት ወቅት ቀለል ያለ ገለፃ ተደርጎላቸው ነበር።

ሰውዬው በነጋታው ጠዋት ማልደው ከደረሱት ጓዶቻቸው ጋር ለምስጢራዊው ስብሰባ በጽ/ቤታቸው ተገኙ። ደስታቸውን ዋጥ ለማድረግ እየጣሩ ለመሆናቸው ሁኔታቸው እያሳበቀባቸው፣ በደህንነቱ ቢሮ አሰራር ዙሪያ አንድ ዕቅድ ስለመንደፋቸውና ሀሳባቸውን ለውይይት ለማቅረብ መሰናዳታቸውን ሲጋራቸውን የለኮሱበትን የክብሪት እንጨት ለማጥፋት እያወዛወዙ ገለፁ። ወዲያው ከወንበራቸው እመር ብለው ተነሱና…

“ጓዶች ባለፈው እንደተወያየነው የደህንነት ቢሮውን ሙሉ ኃላፊነት ለአንድ ሰው ብቻ አሳልፎ ማሸከም፣ በተደጋጋሚ እንዳየነው በተሰዉ ታጋይ ሰማዕታት ደም እጃችን የገባውን ሕገመንግሥታችንን እና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓታችንን አደጋ ላይ መጣል ነው። በመሆኑም ሕገመንግሥታዊ ሥርዓታችንን ከፀረ ሠላም ኃይሎች መከላከል የሚችል ብቃትና ልማታችንን ለማስቀጠል ማገዝ የሚችል አቅም ያለው፣ ከበላይ አመራር የሚሰጠውን አቅጣጫ ለመቀበል የማያንገራግር አንድ ብቁ ግለሰብ ማግኘቱ ቀላል እንዳልሆነ ግንዛቤ ወስደናል።

ስለዚህ እዚህ የምንገኘው ጓዶች የደህንነት መ/ቤቱን በምስጢር እና በጋራ እንድንመራው ዕቅድ ተነድፎ መጨረሱን ሳሳውቃችሁ ኩራት እየተሰማኝ ነው። አያችሁ ይኼን ቢሮ በዚህ መልኩ በቁጥጥራችን ስር ካዋልነው ከአሁን በኋላ 30 እና አርባ አመታት በሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችለንን መደላድል አመቻቸን ማለት ነው። ዋናው ነገር ጉዳዩን በተለመደው ኢሕአዴጋዊ ታላቅ ምስጢር ጠባቂነታችን ይዘን መቀጠል እንዳለብን አለመዘንጋቱ ላይ ነው።” አሉ ኮስተር ብለው።

ሰውዬው የዕቅዳቸውን አፈፃፀም ማብራራቱን ቀጠሉ። “ምን መሰላችሁ የምናደርገው… ከተሰዉ ከቀድሞ የትግል ጓዶቻችን መካከል የአንዱን ስም እንመርጥና የደህንነት መሥሪያ ቤቱ ሹመት ለእዚያ ሰው መሰጠቱን እናፀድቃለን። በዚያ ሰው ስም የሚዘጋጅ ፊርማና ማኅተም ተጠቅመን የደህንነት ቢሮውን እኛው በጋራ እንመራዋለን ማለት ነው።” ብለው ገባችሁ? በሚል አተያይ ጓዶቻቸውን ተመለከቷቸው።

ንግግራቸውን ቀጠሉ “ለምሳሌ በብዙ ታጋዮች ዘንድ ይኑር ወይ ይሰዋ የማይታወቀውን የድሮ የትግል ጓዳችንና በትግል ወቅት ጥሩ የስለላ አመራር ተሰጥኦ የነበረውን የታጋይ ጌታቸው አሰፋን ስም መጠቀም እንችላለን። በዚያ ላይ “ጌታቸው አሰፋ” የሚባሉ ከአንድ በላይ ታጋዮች ስለነበሩ “ጌታቸው የቱ ነው?” የሚሉ ከሕዝቡም ሆነ ከአባሎቻችን ሳይቀር ለሚነሱ ጥያቄዎች ራሱን የቻለ አቅጣጫ ማሳቻ እንደሚሆንልን ግልፅ ነው።

“አቶ ጌታቸው አሰፋ” በእኔ ጠቋሚነትና ምልመላ ለመረጃና ደህንነት መ/ቤቱ ዋና ኃላፊነት መሾሙን በዜና እናስነግራለን። ቀጥለንም ስለ ጌታቸው የስለላ ብቃትና ጥንቁቅነት ያፈተለኩ የሚመስሉ የፈጠራ መረጃዎችን አልፎ አልፎ እየለቀቅን ሕዝቡን እናጥለቀልቀዋለን። ዋናው ነጥብ እዚህ ካለነው ውጭ ያሉ የድርጅታችን አመራሮች እንኳ ስለ “ጌታቸው አሰፋ” ትክክለኛ ማንነት በፍፁም፣ በምንም መንገድ ፍንጭ ማግኘት እንደሌለባቸው አለመዘንጋቱ ላይ ነው።

በመሆኑም የነገሩን ዱካ ለማጥፋት በየጊዜው የተለያዩ ዘዴዎችን ልንጠቀም እንይላለን። ለምሳሌ “ጌታቸው አሰፋ” የመራው ስብሰባ መሳተፋችንን ልናስወራ እንችላለን። በህወሐት ማዕከላዊ ኮሜቴ ውስጥም መመረጡን መረጃ ልንለቅ እንችላለን። ሁሉም ካድሬዎቻችንና አመራሮቻችን ከቢሮው ጋር እንጂ ከኃላፊው ጋር የግድ በአካል መገናኘት ስለማያስፈልጋቸው አለቃቸውን አለማየታቸው፣ ከብቃቱና ከጠንቃቃነቱ የመነጨ እንደሆነ ሊያሳምናቸው ይችላል” አሉና የተጋመሰችውን ሲጋራቸውን አንድ ዓይናቸውን ጨፈን አድርገው፤ በአንድ ትንፋሽ እስኪቂጧ ድረስ መጠው ሳቧትና መተርኮሻ ላይ ደምድመው አጠፏት።

ተሰብሳቢዎቹ ሁሉ በግራ መጋባት ስሜት ዐይናቸው ፈጠጠ፣ እርስ በርስ ተያዩ። ደንገርገር አላቸው። ብዙም ባልገባቸው ጉዳይ ከብአዴኖቹ አንዱ ጓድ ፈጠን ብለው ነጥብ ለማስቆጠር የሚረዳ ንግግር አደረጉ። “ይኼን ቦታ ከመለስ በቀር ሊመራው የሚችል ሰው አልተፈጠረም፣ ብዬ ገና ድ…ሮ ተናግሬ ነበር። ያንን ለማድረግም እሱ ካሰበበት መላ አያጣም ብዬ ለበረከት አውርቼዋለው። ይኸው ያልኩት ሁሉ ሲሆን እያየሁ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ።” አሉና ኩራታቸውን ገለፁ።

የብአዴኑ ዋና ሰው ወዲ ስምኦን ደግሞ ፌዝ በተሞላበት ፈገግታ ታጅበው አጨበጨቡ። በሴራ ብቃታቸው የተመሰከረላቸው የስምኦን ልጅ በዚያው ሰሞን ስለዕቅዱ ከሰውዬው ጋር በድብቅ እየተገናኙ ሁለት፣ ሶስቴ ገንቢ በሆነ መልኩ ተወያይተውም ነበር። ዛሬ ጉዳዩን ሰውዬው በብቸኝነት ይምሩት እንጂ የሴራውንም ዋና ክፍል አብረው አቡክተው አብረው ነበር የጋገሩት።

ዋናው ሰውዬ ገለፃቸውን በመቀጠል “በደህንነቱ መ/ቤት በኩል መፈፀም የሚያስፈልጉ ጉዳዮች ሲገጥሙን፣ መወሰድ ስላለባቸው ርምጃዎችና ኦፕሬሽኖች እዚህ የምንገኘው ጓዶች በዴሞክራሲያዊ መንገድ በድምፅ ብልጫ እንወስናለን። በአስቸኳይ ጉዳዮች ላይ ደግሞ እኔ ውሳኔዎችን አሳልፋለሁ። ስለዚህ “ጌታቸው አሰፋ” የሚባለው ሰው በዚህ ሰአት በዚህች ጽ/ቤት የተገኘነው ነባር ታጋዮችና አመራሮች በአንድ ላይ ለራሳችን እና ለትግላችን የሰየምነው የቃል ኪዳናችን ሰነድ መጠሪያ ነው። ሁላችንም ጌታቸው አሰፋዎች ነን።” አሉና በስሱ ፈገግ አሉ።

በጥቅሉ ዋናውን የመረጃና ደህንነት ሥራውን የመምራት ሙሉ ኃላፊነቱን እሳቸው እንደሚወስዱና እንደሚመሩት አስገነዘቡ። ወዲያው ከባድ ፀጥታ ሰፈነ። እንደ ዕውነቱ ከሆነ ዋናው ሰውዬ ሁላችንንም ዕኩል “ጌታቸው አሰፋዎች” ነን ቢሉም፣ እሳቸው የበለጠ “ጌታቸው አሰፋ” መሆናቸው እንደማይቀር ተሰብሳቢዎቹ ሁሉ ያውቁ ነበር።

በቢሮዋ ውስጥ ከፍርሃት በመነጨ የሰፈነው ፀጥታ፣ የተሰብሳቢዎቹን የልብ ምትና በስብ ከተጨናነቀው ሆድ ዕቃቸው የሚወጣውን የትንፋሻቸውን ሲርሲርታ አግንኖ ያስደምጥ ነበር። ከአንድ አስር ሰከንዶች ረጭታ በኋላ ጥያቄዎችና ሥጋቶች መዥጎድጎድ ጀመሩ። ዋናው ሰውዬ አንድ ሀሳብ ካነሱ ከማስፈፀም እንደማይመለሱ የሚያውቁ ጓዶቻቸው፣ ሀሳባቸውን ተቃርነው ጥርስ ከመግባት ይልቅ፣ ይበልጥ የሚጠነክሩባቸውን መላዎችና ያልታዩባቸው ክፍተቶች ካሉ ለማጎልበት የሚረዱ ሀሳቦችን ይሰነዝሩ ጀመር። የሁሉንም ተስፋ፣ ሥጋትና የማጎልበቻ ሀሳቦች ከተንሸራሸሩ በኋላ ዋናው ሰውዬ ማብራሪያቸውን ቀጠሉ።

“ሁሉም ሥራ በጸሐፊዋና በምክትል የቢሮው ኃላፊ በኩል እንዲሳለጥ ይደረጋል። ሆኖም ግን ጸሐፊዋም ሆኑ ምክትሉ የደህንነት ኃላፊ ከአለቃቸው “ጌታቸው አሰፋ” ጋር በአካል እንደማያገኙት ገና ወደ ቢሮው ሲመጡ ጀምሮ እንዲያውቁት ይደረጋል። አስፈላጊ የመልዕክት ልውውጦችን እኔ ወይም በረከት እየደወልን በፋክስና በስልክ እንመራለን፣ እናስፈፅማለን።

ሌላው ድምፅ ማጎርነንና መቀየር የሚችል መሳሪያ በቢሮ ስልኬ ላይ አስገጥሜ ጨርሻለሁ። ስለዚህ አንዳንዴ በስልክ ማናገር አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች እኔ ራሴ ጌታቸው አሰፋ መሆኔን ገልጬ ትዕዛዝ እሰጣለሁ። የእኔ የቢሮ ስልክ ቁጥሩ ስለማይወጣና ስለማይጠለፍ በዚህ በኩል ሥጋት አይገባንም። ድምፅ መቀየሪያው ማሽን አንዴ ቋሚ ኮድ ከተሰጠው በኋላ ምንም ዓይነት ሰው ከወዲህ ቢናገር ከወዲያ በኩል የሚያስደምጠው ድምፅ ሁሌም አንድ ዓይነት ነው። ስለዚህ እኔም ሆንኩኝ አዜብ በዚህ ቁጥር ብናወራ ለአድማጩ የሚደርሰው አንድ ዓይነት ድምፅ ነው።

ይህን ቴክኖሎጂ ከሰሞኑ ለበረከትም ቢሮው ውስጥ ይገጠምለታል። ከእኔ ጋር እየተነጋገርን አስፈላጊ በሆኑባቸው ጊዜያት በረከትም፣ ጌታቸው አሰፋነቱን ይጠቀምበታል ማለት ነው።” እያሉ ስለ ረቂቁ ሴራቸው ማብራራያቸውን ቀጠሉ። ሰውዬው ማብራሪያቸውን በሰከነ አነጋገርና በአፅዕኖት ቀጠሉ። “አንዳንዴ የመረጃ እና ደህንነት ኃላፊው በውጭም ይሁን በሀገር ውስጥ በአካል የግድ መገኘት በሚያስፈልግባቸው ቦታዎች አንድ ዘዴ መጠቀም እንደሚቻልም አስረዱ። ለምሳሌ በውጭ ሀገራት “አቶ ጌታቸው” መገኘት አለበት ተብሎ ከታመነ፣ ሚሽኑን ለሚወስደው የደህንነት ባለሙያ ፓስፖርትም ሆነ አስፈላጊ ሰነዶች በ”ጌታቸው አሰፋ” ስም ይዘጋጅለታል።

ያንን ኃላፊነት የሚወጣውን ሰው መምረጡና ማዘጋጀቱ የቅርብ አለቃው ስራ ይሆናል። ‘አለቃህን ሆነህ እዚህ ቦታ ትገኛለህ’ ተብሎ ሚሽን የሚሰጠው የስር የደህንነት ባለሙያ ትኩረቱ ኃላፊነቱን መወጣቱ ላይ እንጂ ለምን ብሎ አይጠይቅም። ሙያውም የታዘዘውን እንዲፈፅም ብቻ ነው የሚያዘው። በዚህ መንገድ አንድ የደህንነት ሰው በቢሮ ዕውቅናና ድጋፍ ሚሽን እስከተሰጠው ድረስ “ጌታቸው አሰፋ” ነኝ ካለ ማንም ሰው አይደለህም ብሎ ሊከራከር አይችልም።

ሌላው ሚሽኑን የሚወስዱ የደህንነት ሠራተኞች በምንም መልኩ በሚዲያ የሚተላለፍ ዝግጅት ላይ እንዲገኙ፣ ፎቶ እንዲነሱ፣ ምስላቸው በካሜራ እንዲቀረፁና ቃለ መጠይቅ ላይ እንዲሳተፉ አይደረግም። በዚህ ሁኔታ በአንድ ቀንና ሰአት ውስጥ ጌታቸው አሰፋ አዲሳባም፣ መቀሌም ሆነ ሳውዲ ዓረቢያ እንዲገኝ ማድረግ እንችላለን። ሰዎችም በአንድ ሰአት ጊዜ ውስጥ በተለያየ ቦታ ማየታቸውን እየተማማሉ እንዲከራከሩና ሰውዬውን ወደ መንፈስነት የተጠጋ ስለመሆኑ እንዲያወሩ ማድረግ እንችላለን። ሃሃሃ

የፖለቲካ ሥልጣን ዘላለማዊ አይደለም። አንድ ቀን ከቁጥጥራችን ውጭ ሆኖ ከእጃችን ሊወጣ ይችላል። ኢሕአዴግ ብዙ የጥፋት ኃይል የሆኑ ጠላቶች አሉት። በዚህም የተነሳ ከበድ እና ረቀቅ ያሉ ምርምራዎችንና የስለላ ስልቶችን መከተል ይጠበቅብናል። በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ ተቃዋሚዎችም ሆኑ የመብት ተሟጋች ነን ባይ የሆኑት ነጮቹ በወንጀል ድርጊት ሊጠይቁን መነሳሳታቸው አይቀርም።

አያችሁ የጠበቀ ነገር የገጠመን ጊዜ አቶ “ጌታቸው አሰፋ” ወዳልታወቀ ሀገር ኮበለለ ብለን እናስወራለን። አብረን እናፋልጋለን። በዚህም ለሕገመንግሥታችን መከበርና ለድርጅታችን ሕልውና ሲባል ለሚወሰዱ ርምጃዎች እንደ አመራር የሚጠይቀን አካል አይኖርም። ሁሉም ነገር ከጌታቸው አሰፋ መጥፋት ጋር ይቀበራል” ብለው ለአጭር እረፍት በፈጣን ርምጃ ወደ ውጭ አመሩ።

 By Samson Getachew T S (ይህ ጽሑፍ ልብወለድ ነው)

ግንቦት 19 ቀን፣ 1993 ዓ.ም…

የኢትዮጵያ ጀግኖች መስዋእትነት ከ30 አመት በኋላ ሲታሰብ – ከደረጀ ደምሴ ቡልቶ

ማስታወሻ – እንደመግቢያ

የዛሬ ሰላሳ ዓመት ከሰዓት በኋላ ግንቦት 8 ቀን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተዋጊ ጄቶችና ሔሊኮፕተሮች በአዲስ አበባ አየር ላይ ባለተለመደ ዝቅታ በአስደንጋጭ ድምጽ ሲያፈተልኩና ሲያንዣብቡ ገና የሐያ ዓመት ወጣት ነበርኩ፡፡

ማንም ሳይነግረኝ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እየተደረገ መሆኑን በመገመት ወደ ቤት አመራሁ፡፡ብዙም ሳይቆይ የአባቴ አጃቢ የነበሩ ወታደሮች ከሌሎች ሁለት ወታደሮች ጋር በመሆን ቤታችን ፊት ለፊት እነሱን ለማውረድ ከቆመው የከባድ የጪነት መኪና ወርደው የግቢውን በር አንኳኳኩ፡፡ የጭነቱ መኪና ፊቱን ወደመጣበት፣ የቦሌ መንገድ እዙሮ ከጀርባ የታጨቁትን ወታደሮች ይዞ መንገዱን ጀመረ።

ከጭነት መኪናው ለወረዱት ወታደሮች በሩን የከፈትኩላቸው እኔ ነበርኩ፡፡ ሙሉ ትጥቅ ታጥቀዋል። የአባቴ አጃቢ ከነበረው የአስር አለቃ ጌታቸው ጋር ሰላምታ ተለዋውጠን፣ ወደ ውስጥ እንዲገቡ ጋብዝኳቸው፡፡ከአስመራ በአውሮፕላን ከብዙ ወታደሮች ጋር እንደመጡና እኛ ቤት ወርደው ጥበቃ እንዲያደርጉ በአባቴ መታዘዛቸውን ነገረኝ፡፡

ከእርሱ ጋር ያሉት የማላውቃቸው ሁለቱ ወታደሮች የጄኔራል ሁሴን አህመድ አጃቢዎች አንደሆኑና እነሱም እንዲሁ እኛ ቤት እንዲቆዩ መታዛዛቸውን አስረዳኝ፡፡ አውሮፕላን ወስጥ እያሉ ጄኔራል ቁምላቸው መንግስቱ ኃይለማርያም ተገድሎ ከስልጣን እንደ ወረደ የሚገልጽ ወረቀት ማደላቸውን ሲነግረኝ የገመትነው ዕውነት መሆኑን አራጋገጥን፡፡

ሁኔታው እስኪጣራ ድረስ እቤት ከመቀመጥ ወደ ማይጠረጠር ወዳጅ ቤት መሄድን መርጠን እቤት የነበረውን መሣሪያ ተከፋፍለን ቤታችንን ለቀን ወጣን፡፡ ትላቅ ወንድሜ ዮናስ ብሄራዊ ውትድርና አንደኛ ዙር ሄዶ ለሁለት እመት ተኩል ያገለገለ ነበር። ስለመሳሪያ አጠቃቀም ያውቃል። እኔ ደግሞ አባቴ በሚመራው የጦር ሰፈር በየመሳሪያ ግምጃ ቤቱ ጥይት በካርታ እንደጨዋታ ስሞላ፣ ክላሽንኮቭ መትረየስ እየፈታሁ እየገጠምኩ ስላደኩ የደረሰኝ ለአባቴ በስጦታ የተሰጠ የጀርመን ሉጋር ሽጉጥ ቢያንስ አነጣጥሬ መተኮስ እንደምችል አልተጠራጠርኩም። የመፈንቀለ መንግስቱ ሙከራ ከመጀመሩ መክሸፉን ማታ ብንሰማም ከአስመራ የሚተላለፈው ዜና ደግሞ ሙከራው እየቀጠለ መሆኑን ነበር የሚገልጸው፡፡ አባቴ ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ የሚመራውን የሁለተኛ አብዮታዊ ሠራዊት አስፈላጊ ከሆነ አዲስ አበባ ድረስ በከፊል በማምጣት ሙከራውን እስከመጨረሻው እንደሚገፋበት በአስመራ ሬዲዮ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መልዕክት አስተላለፈ፡፡

ለሶስት ቀናት የተለያዩ ክፍሎች ሙከራውን እንዲደግፉ ለማስተባበር ሞከረ፡፡ አስመራ የተደራጀ የአየር ሃይልና የኢትዮጵየ አየር መንገድ አውሮፕላኖች የሚገኙበት ስለነበረ ሁኔታው ካልተሳካ አገሩን ለቆ ይሄዳል የሚል ተስፋ ነበረን፡፡ የቤተሰብ ተስፋ፡፡ አባቴ ግን ያስተባበራቸውን የጦር ጓዶቹንና የሚወደውን አገሩን ጥሎ እንደማይሄድ ልባችን ያውቅ ነበር፡፡ እጁን አንደማይሰጥ ደግሞ ግልጽ ነበር፡፡ “አንድ የጦር መኮንን የጄኔራል ማዕረግ ከደረሰ እጁን ለጠላት መስጠት አገር መማዋረድ ነው ፣ ከቻለ ራሱን ማጥፋት አለበት ይል ነበር፡፡”

ይህን ደግሞ ብዙ የቀድሞ የጦር መኮንኖች የሚያምኑበት ነው፡፡ ጄኔራል መርዕድ ንጉሴ፣ ጄኔራል አምሐ ደስታ በመፈንቅለ መንግስቱ በአዲስ አበባ ራሳቸውን በመሰዋት፣ ጄኔራል ለገሠ አበጀ በትግራይ ፣ኮሎኔል ካሳ ገብረማርያም በናቅፋ፣ ጀ/ል ተሾመ ተሰማ በምጽዋ ራሳቸውን መስዋእት በማድረገ ያለፉትን ነፍሳቸው ያለችበት ቦታ ስትሄዱ ጠይቁ፡፡

ስለ መፈንቅለ መንግስት ሙከራው “አባቴ ያችን ሰዓት” በተሰኘው መጽሃፌ ዝርዝሩን ስለጻፍኩ እዚህ መድገም አልፈልግም፡፡ ከሰላሳ አመት በኋላ ማስታወስ ያለብን ሙከራውን ብቻ ሳይሆን በዛ ሙከራ ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ የጦር መሪዎች ለአገራቸው ያበረከቱትን አስተዋጽኦ፣ የከፈለኡትን መስዋእትነትና ከእነሱ ህይወት ይህ ትውልድ ሊቀስም የሚችለውን ትምህርት ነው። የመፈንቅለ መንግስቱን ሙከራ ከሰላሳ አመታት በኋ ሳስበው ጊዜው ምን ያህል እንደተቀየረና አገራችን ምን ያህል እንደተለወጠች አስተዋልኩ፡፡ አባቴና ጓደኞቹን የሚያስተሳስራቸው ለአገራቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የነበራቸው ፍቅር ነበር፡፡

መንግስቱ ኃይለ ማርያም በፍርሐት ከመኮብለሉ ሁለት አመት በፊት ጀምሮ ከዛም በኋላ ለ27 አመት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ስላደረጉት የጦር መሪዎች የተለያዬ ውሸቶ ተነግሯል፡፡ ተጽፏልም፡፡ ዕውነቱን የሚያውቀው ብዙ ስለነበር ታሪካቸው አንዳንዶች እንደተፈለገው አልጎደፈም፡፡የመንግስቱ ኃይለማርያም ደጋፊና ተቆርቋሪ የሆኑ አንዳንድ ካድሬዎችና የወታደራዊ ደሕንነት አባላት ይህን ነው ለማድረግ የሞከሩት። ሁሉም አይደሉም ከመካከላቸው ዕውነቱን የጻፉ አሉ። “ትውልድ ያናወጠ ጦርነት “ እንደ ምሳሌ ይጠቀሳል፡፡

እነዚህን አንጋፋ የጦር መሪዎች እንደ ግል ጥቅም ወይም ስልጣን ፈላጊ ከዛም አልፎ አልፎ አሻጥር እየሰሩ ጦሩን ሲያስጨርሱ እንደነበር አድርገው ሲጽፉ። ሌት ተቀን ስለ አገሩ ሲጨነቅና ሲቆረቆር ቢበዛ 4 ወይም 5 ሰዓት ብቻ እየተኛ ሌሊት ተነስቶ ወደ ተረኛ መኮንኖች ጋር እየደወለ የሰጠው ትዕዛዝ መፈጸሙን ሲከታተል የሚያነጋ ፣ ጦሩ ድል ሲያደርግ በደስታ የሚሞላ። ጦሩ ችግር ሲገጥመውና ጓዶቹ ሲሰዉ በሐዘን የሚዘፈቀውን አባቴን እያስታወስኩ የእነዚያን ጀግኖች ታሪክ በወረፋ ዕጃቸውን ለወያኔዎ እየሰጡ ህይወታቸውን ባተረፉ ሰዎች እጅ ሲጎድፍ ሳይ ከማዘንም አልፎ ያበሳጨኛል።

የኔ አባት ለ 38 አመታት አገሩን አገልግሏል፡፡ ኮርያ ዘምቷል፡፡ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ አየር ወለድ ጦር ካቋቋሙት ጥቂት መኮንኖች አንዱ ነው፡፡ ገና በአጼ ሃይለ ስላሴ ዘመን ሶማሊያ ኢትዮጵያን ስትወር በመጀመሪያው የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት፣ በቶጎ ውጫሌ ጦርነት የአየር ወለዱን ጦር መርቶ ድል አድርጓል፡፡ ከዚያ በባሌ ዘመቻ በሌ/ጄነራል ጃጋማ ኬሎ ስር የአየር ወለድ ጦር መርቶ ተዋግቷል፡፡ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የወታደራዊ ትምሕርት ዳሬክተር ሆኖ በታወቀው የሐረር ጦር አካዳሚ ብዙ ምርጥ መኮንኖችን አፍርቷል፡፡ በ1970 የሶማሌ ጦር አዋሳ ለመድረስ 60 ኪሎሜትር ሲቀረው የደቡብ ዕዝ አዛዥ ሆኖ እንደ አንድ የመስመር ጦር መሪ ከጦሩ ጋር አብሮ እየተዋጋ የሶማሌ ጦር ከኢትዮጵያ ምድር እስከሚወጣ ድረስ ጦሩን መርቷል፡፡ የአባቴን የግል ማህደር እልፎ አልፎ እያነሳሁ አነባለሁ። በየቀኑ የሚያደርገውን ይጽፍ ነበር። ለ 1000 ገጽ በላይ የሚሆን ማህደሩን በኮምፒውተር ስካን አሰደርጌ አስቀምጫለሁ። ለምሳሌ በኤርትራ ስለተደረገው የባህረ ነጋሽ ዘምቻ የጻፈውን ከመጽሃፌ ግርጌ አስገብቼ ነበር።

ከታች የተቀመጠው በደቡብ ኢትዮጵያ ፊሉቱና ዶሎን ለማስለቀቅ የተደረገውን የሶስት ቀን ጦርነት የሚገልጽ ነው። የጀግናው የኢትዮጵያ አየር ሃይል ጄት አብራሪ የጀ/ል ለገሰ ተፈራ ጄት ተመቶ የወደቀው በዚህ ጦርነት ላይ ነበር። የግል ማህደሩ ከ400 በላይ ጸረ ታንክና ጸረ ሰው ፈንጂ እያነሱ ወደፊት ተጉዘው የሶማሊያን ወራሪ ጦር እንደደመሰሱ ያሳያል።

ከሁሉ የገረመኝ ጽሁፉ ይህኛው ነው። “በ 3/7/70 0800 ሰአት ከዶሎ 17 ኪ/ሜትር ላይ ዋናው ጦር እንዲቆም ተደርጎ በአንድ ሻምበል ጦር (ወደ 400 የሰው ሃይል) ወደ ዶሎ ተነቃንቄ ዶሎ ከተማ ስንደርስ የሶማሌ ወታደር ከቀድሞው የጦር ሰፈራችን በመኪና ለማምለጥ ሲበር ተከታትለን ከነመኪናው ማረክን ሌሎችም 5 ወታደሮች ተታኩሰው ወደ ጫካ ስለገቡ መደምሰስ አልተቻለም።”

General Demissie Bulto's note.

ከዚያም ወደ ሐረር የምስራቅ ዕዝ አዛዥ ሆኖ በመሄድ የሶማሌን ጦር ከኢትዮጵያ ምድር በጠቅላላ ያስወጣውን ዘመቻ መርቶ ድልን ተጎናጽፏል፡፡

በመጨረሻም በኤርትራ ከረን ሊያዝ ሲል በአዛዥነት ተመድቦ የኢትዮጵያ ጦር ከረንን ተከላክሎ መልሶ በማጥቃት ወደ አፋ ቤት እንዲያመራ በማድረግ የነበረውን ሁኔታ ለመቀየር ችሎ ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሁለት የተቀነባበሩ ዘመቻዎችን ከሐረር በጊዜያዊ ምድባ ወደ ኤርትራ ተጉዞ በዘመቻ መሪነት አገልግሏል ፡፡ እነዚህ ሁለት ዘመቻዎች የቀይ ባሕርና የባሕረ ነጋሽ ዘመቻ የሚባሉ ባሬንቱን ከማስለቀቅ ባሻገር ናቅፋን ለመያዝ የተቃረቡበት ዘመቻዎች ነበሩ፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን አገሪቱ የነበረችበት አዘቅት በኢኮኖሚና በማሕበራዊ ፖሊሲ ምክንያት የተፈጠሩ ብዙ ችግሮች በጣም ያሳስቡትና ያስጨንቁት ነበር፡፡ የፖሊሲ ለውጥ እንዲደረግ በተደጋጋሚ የሚቻለውን አድርጓል፡፡ ከቅርብ ጓደኛውና ከትግል አጋሩ ከጄኔራል መርዕድ ንጉሴ ጋር ስለአገሪቱና ስለምትከተለው ፖሊሲ ብዙ ይወያዩ ነበር፡፡ የማይስማሙበት ፖሊሲ ብዙ ነበር፡፡ ለምሳሌ የሰፈራ ፖሊሲ፣ በሚሊታሪውና በሕዝቡ መሐል ብዙ ቅሬታን ፈጥሮ ነበር፡፡ በኤርትራና በትግራይ የሚደረጉት ጦርነቶች የብዙ ኢትዮጵያውያን ሕይወት በማጥፋት አገሪቱ ላይ ያመጣው ቀውስ እንቅልፍ ይነሳቸው ነበር፡፡

የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ውድቀት ለሰራዊቱ የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ፣ ከምግብ ፣ ከውሃ ጀምሮ በተገቢው ማቅረብ አለመቻሉ ያበሳጫቸው ነበር። የሚሰማ መሪ ባለመኖሩ መፍትሄ ማግኘት አልተቻለም።

ጄኔራል ፋንታ ከታሰሩ በኋላ በኢትዮጵየ ቴሌቪዥን የተቀዳው ቃለ መጠይቅ መንግስቱ ኃይለማርያም ከሸሸ በኋላ ለህዝብ ተለቆ ነበር፡፡ እሳቸው እንዳሉት የመፈንቅለ መንግስቱ ዓላማ ለጦርነቱ መፍትሔ ለመስጠት “ከወንበዴው ጋር ጭምር በጠረጴዛ ዙርያ ለመነጋገር ነበር”። ታዲያ አሁን አንዳንዶች ሲጽፉ ለስልጣን ብለው ነው ሲሉ ይገርመኛል፡፡ ለመሆኑ ስንቱ ናቸው ሰልጣን የሚይዙት? የአገር መሪ የሚሆነው አንድ ሰው ነው፡፡ ከአስመራ ብቻ ከ 20 በላይ የሚሆኑ ጄኔራሎች ተሳትፈዋል፡፡ አዲስ አበባም እንዲሁ፡፡ መፈንቅለ መንግስት ያክል ለሕይወት ተቆርጦ የሚገባበት ሙከራ በነዚህ ሰዎች ሁሉ ስምምነት ሲደረግ እንዴት ለስልጣን ነው ይባላል? ስልጣን ደግሞ ነበራቸው፡፡ እንዳልኩት ከአንድ ወይም ከሁለት ሰዎች ሌላ የቀሩት ከነበራቸው ስልጣን የሚጨምሩት ብዙም አልነበረም፡፡ ስልጣን መጨመር ከሆነ ዓላማው ለመንግስቱ ኋይለ ማርያም እያጎበደዱ ስልጣን መጨመር ይቀል ነበር፡፡ እዚህ ላይ መንግስቱ ሃ/ማርያምን ለምን በአክብሮት አንቱ እያልኩ እንደማልጽፍ ትንሽ ላስረዳ። በመጀመሪያ በታሪክ የተወሰኑ ግለሰቦች ሲነሱ አንተ ተብለው የሚጠሩ አሉ። የሰሩት አጸያፊ እና ጭካኔ የተሞላባቸው ተግባራት ምክነያት። ለምሳሌ ሙሰሊኒ፣ ሂትለር፣ ግራኝ አህመድ፣ በታሪክ ሲነሱ በእድሜም ይሁን በስራ የሚገኝ ከበሬታ አይሰጣቸውም።

አንዳንድ የመንግስቱ ሃ/ማርያም ደጋፊዎች በ 29 አመት በኋላም በአገራችን ላይ ያደረሰውን ጥፋት ረስተው ይሁን ወይንም ኣውቀው ለመሸፈን የሚናገሩትን ስሰማ ይገርመኛል። መንግስቱ ሀ/ማርያም አገራችን አሁን ለደሰችበት ቀውስ ዋነኛ ተጠያቂ ግለሰብ ነው። በሀገራችን ታሪክ አገሪቷን ወደ ተሻለና ትልቅ ደረጃ እንዳትደርስ ከፍተኛ ሚና ከተጫወቱ ግለሰቦች መካከል በዋናነኝነት የሚመደብ ግለሰብ ነው። እውቆ አደረገው ለማለት ባይቻልም። አገር ለማጥፋት ሆን ብሎ አውቆ አደረገው አልልም። ያደረሰው ጥፋት በአብዛኛው የኢትዮጵያን የሩቅ ዘመን ጥቅም ማየት አለመቻሉ፣ የሚወስነው ውሳኔ ከአገሪቷ የሩቅ ዘመን ጥቅም ላይ የተመረኮዘ ሳይሆን የራሱን ስልጣን ማጠናከር እና ማደላደል ያል የተመሰረተ በመሆኑ ነበር።

ለዚህም ነው ገና ሲጀመር የታሪክ ቅርጽ የሆኑትን እሱ እንደገና ጊዜ ቢፈጠር የማይመጥናቸውን እንደ ጸሃፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ እና ልጅ እንዳልካቸው መኮንን የመሳሰለቱን ኢትዮጵያውያን ያለፍርድ በግፍ የገደለው። ከዚያም እነ ጀ/ል ተፈሪ ባንቲን የወደፊት የአገሪቷን ጥቅም በማየት ከተቃዋሚ ድርጅቶች ኢህአፓንም ጨምሮ እንወያይ ሲሉ በተቀነባበረ መንገድ ገደላቸው። ጀ/ል አማን እንዶም የኤርትራን ችግር ለመፍታት መንገድ ሲፈልጉ አርቆ ማስተዋል ስለተሳነው ገደላቸው። ደጋግሜ እንደተናገርኩት በእኔ ቆጠራ ብቻ 54 ጀነራሎችን ገድሎአል። ከሁሉ የሚያሳዝነው በመፈንቅለ መንግስቱ በመጨረሻው ደቄቃ ተስማምተው ተሳትፈዋል ተብለው የተከሰሱትን 18 ምርጥ ጀነራሎች ከአንድ አመት እስር በኋላ አገራቸውን እንዲያገለግሉ ከማድረግ ይልቅ በግፍ ገድሏቸዋል። ከኤርትራ ብቻ 435 መኮንኖችን እስር ቤት ወርውሮ ጦሩ ያለብቁ የስትራቲጂክና የፊልድ መሪዎች እርቃኑን እንዲጋለጥ አድርጎአል።

ይህ በጦሩ ውስጥ ያደረገው በከፍል ነው። ሲቪሉን ህዝብ ደገሞ በሰፈራ፣ በብሄራዊ ውትድርና፣ በጸረ አብዮተኛነት፣ ውንጀላ ወዘተ ሲያጉላላና ሲያሰቃይ ለ17 እመት በሰአት እላፊ ገደብ ህዝቡን ሲያሰቃይ፣ የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመቃወም መብቶች ተነግፎ ይህ ሁሉ አልበቃ ሲለው የመንግስት ሰራተኛ የሚለብሰው ልብስ በሰሜን ኮሪያ ሞዴል የተሰራ ስማያዊ ካኪና የካኪ ቀለም ያለው በጣም የሚያስቀይም ጃኬትና ሱሪ እንዲሆን አዞ፣ ህዝብን መሳቂያ ያደረገ ሰው ነው።

ያን ግዜ አይደለም አሁን ለብዙ አመት በኋላ እንኳን ኢትዮጵያን የሚያክል አገር ለማስተዳደር የሚችል አእምሮ፣ ተመክሮ፣ እንዲሁም ምንአልባት አስተዳደጉም ጭምር የነፈገው ሰብእና እንዳልነበረው ግልጽ ነው። እስካሁን የሰራውን ስህተት አንድ ቀን እንኳን በጸጸት ገልጾ አያውቅም። በቅርቡ ዶ/ር አበይ የኢትዮጵያን ህዝን ዝቅ ብዬ ይቅርታ እጠይቃለሁ ሲሉ በመካከላቸው ያለው ትልቅ ልዩነት ጎልቶ ታየኝ። መግደል፣ ማሰር፣ ማሰቃየት ቀላል ነው። የጥሩ መሪ ባህሪ ግን አይደለም። ችግሮችን በህግ መፍታት፣ የዜጎችን መብት መጠበቅ፣ ለስልጣን ሳይሆን ለሀገር እና ለህዝብ አስቦ መወሰን ጥሩ አእምሮና ህሊና ይጠይቃል። መንግስቱ ትምህርቱም፣ እውቀቱም፣ ተመክሮ፣ ሰብእና፣ ስነምግባር፣ ራእይ፣ አስተዳደግ ወዘተ እንዳልነበረው ጭካኔዎቹ ይመሰክራሉ። አንድ አገር ተረክቦ ለሁለት ከፍሎ፣ ህዝቡን አራቁቶ፣ እነደጠላት እንዲተያይ አድርጎ፣ ብዙዎችን አፈናቅሎ፣ ለስደት ዳርጎ፣ ብዙ ጀግኖችን ገድሎ እስከ አንድ ስውና አንድ ጥይት የሚል የሞኝ መፈክር ሲያሰማ ከርሞ በመጨረሻ ቤተሰቡን አሸሸ፣ እሱም ፈረጠጠ።

በቅርቡ የታተመው የጄኔራል መርዕድ ንጉሴ መጽሐፍ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው ይህንኑ ሃቅ ነው፡፡ መጽሐፉ በልጆቻቸው ቢጻፍም በውስጡ የያዘው ሃሳብ በጄኔራል መርዕድ የዕለት ማስታወሻ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

ጄኔራል መርዕድን እንደ አጎት ነበር የማየው በጣምም ያቀርበኝ ነበር። ስለ አገሩ በጣም የሚጨነቅ ሰው አንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በአንድ ወቅት ከአባቴ ጋር ሐረር አንድ ቤት ውስጥ ለጥቂት ወራት ሲኖሩ እኔም ለክረምት ዕረፍት ሄጄ ብዙ ጊዜ አብረን አሳልፈናል፡፡ነገር ግን መጽሐፉን ሳነብ በጣም ተደነቅሁ፡፡ የነበረውን አርቆ አስተዋይነት አሁን ባለሁበት የእውቀት ደረጃ መለስ ብዬ ሳየው በዚያን ዘመን በዛ ውጥረት ይህን አይነት አርቆ አስተዋይ አዕምሮ በመኖሩ ተገረምኩ፡፡ ብዙ በቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር አባላት የተጻፉ መጻሕፍትን አንብቤያለሁ የዚህን አይነት የበሰለ የጦር ፣ ማሕበረ ሰብ፣ የኢኮኖሚ እንዲሁም የዲፕሎማሲ ዕሳቤዎች የያዘ ጽሑፍ አላየሁም፡፡

አንብቤ ስጨርስ የተሰማኝ ስሜት “ትላልቆቹ አልቀዋል” የሚል ነበር፡፡ አገራችን በዚህ አልታደለችም፡፡ የጀግኖቹን ታሪክ የሚጽፉት ጀግኖቹ ሳይሆኑ የተረፉት ናቸው ግማሾቹም የጀግኖቹ ገዳዮች፡፡

ወደ ኋላ ልመለስ፡፡

መፈንቅለ መንግስቱን የሞከሩት የጦር መሪዎችና ተከታዮቻቸውን ሳስብ አገራችን ምን ያህል እንደተቀየረች አስተዋልኩ ፡፡ ይህን ያልኩት ምክንያት እነዚያን ሰዎች ያገናኛቸው ብሔር ወይም ሃይማኖት ወይም የፖሊቲካ አመለካከት ሳይሆን ለአገራቸው የነበራቸው ፍቅር በመሆኑ ነው፡፡ ከዛም አልፎ ምንም እንኳን በአገሪቱ ከፍተኛ አመራር ላይ ቢሆኑም አገራቸው በአንድ ሰው አምባገነን አመራር ስር እየማቀቀች በጦርነት ተወጥራ መኖርና መቀጠል እንደሌለባት ስለወሰኑ ነበር፡፡ ኦሮሞ ፣ አማራ፣ ጉራጌ፣ ትግሬ ፣ ኤርትራ እንዲሁም ከሌሎች ብሔሮች የተውጣጡ ቢሆንም ያን እንደ ምክንያት፣ እንደ መሰብሰቢያ፣ እንደ ጥሩ ወይም አንደ መጥፎ ማሰብ ወይም ማንሳት ቀርቶ ከቁጥር ሳይከቱ ነገር ግን አንዱ የአንዱን ብሔር በማክበር ነበር የሚሰሩት፡፡ የብሔር ጭቆና አለ የለም የሚለው ጥያቄ ወደ ጦር ሠራዊቱ ውስጥ ስንገባ መልሱ የተለዬ ነበር፡፡ ከአባቴ ጋር ከከረን አልፌ ማሳህሊት ተራራ ላይ ሆነን ከጄኔራል በሃይሉ ክንዴ (ያኔ ኮሎኔል) በጦር ሜዳ ሬድዮ ጠርቶ ጋር በኦሮሚኛ ወታደራዊ ትዕዛዝ ሲሰጥ አይቻለሁ፡፡

ከሁሉ በላይ የሚያቀርበውና በስራው የሚመካበት ረዳት መኮንን ኮ/ል ተስፋ የትግራይ ተወላጅ የሐረር አካዳሚ ምሩቅ ነበር፡፡ የደቡብ ዕዝ የዘመቻ መምሪያ ኃላፊ ነበር፡፡ ከብዙ አመት በኋላ አባቴ ወደ ኤርትራ ሲመደብ ካለበት አስፈልጎ ኮ/ል ተስፋን ወደ ኤርትራ አዛወረው፡፡ ኮ/ል ተስፋ ከኤርትራ ተነስቶ አዲስ አበባ ዙሪያ ወረቀት አስበትኗል፡፡በመፈንቅለ መንግሥቱ ጊዜ፡፡ መፈንቅለ መንግስቱ ሲከሽፍ በአስመራ አየር ሃይል ግቢ እንደተገደለ ሰምቻለሁ፡፡ አስመራ ከተገደሉት ጄኔራሎች መሃል ያኔ የኤርትራ ክፍለ ሀገር የነበረችው ተወላጅ የሆኑት ጄኔራል አፈወርቅም ወልደ ሚካኤል ይገኙበታል፡፡ ሀሉንም ያገናኛቸውና ለአንድ ኣላማ ያሰለፋቸው ኢትዮጵያዊነታቸውና ለአገራቸው የነበራቸው ፍቅር ነው፡፡

በመጨረሻም ልጠቅሰው የምፈልገው በጄኔራል መርዕድ ንጉሴ አዲስ መጽሐፍ እንደተጠቀሰው የመፈንቅለ መንግስቱ ተሳታፊዎች ከተለያዬ የጦር ክፍል የተውጣጡ እንደነበሩ ነው፡፡ ከከብር ዘበኛ ሁለት (አባቴና ጄኔራል መርዕድ ንጉሴ) ከጦር ሠራዊት በጣም ብዙ (ጄኔራል ኃይሉ ገብረ ሚካኤል፣ ጄኔራል አበራ አበበ፣ ጄኔራል ቁምላቸው፣ ጀ/ል አለማየሁ ደስታ፣ ጀ/ል ነጋሽ ወልደየስ፣ ጀ/ል ወርቁ ቸርነት፣ የሃረር ጦር አካዳሚ ምሩቆች የነበሩት ደግሞ የሚከተሉት ናቸው። ከሳንድረስት የእንግሊዝ የጦር አካዳሚ 1ኛ ወጥቶ ከእንግሊዝ ንግስት ከፍተኛውን ሽልማት የተቀበልለው ጀ/ል ተስፋዬ ትርፌ፣ ጀ/ል ደሳለኝ አበበ፣ ጀ/ል እርቅይሁን ባይሳ፣ ጀ/ል ታደሰ ተሰማ፣ ኮ/ል አርጋው ባንቲይርጉን ጨምሮ) በተጫማሪም ከአየር ኃይል (ጀ/ል ፋንታ በላይ፣ ጀ/ል አመሃ ደስታ፡ ጀ/ል ሰለሞን ደሳለኝ)፣ ከባሕር ኃይል (አድሚራል ተስፋዬ ብርሃኑ) እንዲሁም ከፖሊስ (ጀ/ል ወርቁ ዘውዴ፣ ጀ/ል እንግዳ ወልደአምልክ) ሁሉ ተሳትፈውበታል፡፡

የኢትዮጵያን ያንን ግዙፍና ስመጥሩ ጦር መሳቂያና ማፈሪያ ያደረገው መንግስቱ ኃይለ ማርያም ነው፡፡ እንደ ምሰሶ ሆነው የተሸከሙትን የጦር አለቆች አስገድሎና ገሎ የቀሩትንም አስሮ ጦሩን ባዶ ካደረገ በኋላ እንደ ክብሪት ሲያጠፋው የኖረውን የሌላውን ሕይወት የሱ ህይወት አደጋ ላይ ሲሆን ግን ህይወቱ አጓጉቶት በፍርሃት አገሩን ለቆ ጠፋ።

ካለ መንግስቱ ኃይለማርያም አመራር ወደፊት መሄድ አትችልም እየተባለ ሲነገረው የቆየው ጦር መንግስቱ ሄደ ሲሉት ለመንግስቱ ሲዋጋ እንደኖረ ሁሉ መሳሪያውን ቢችል እየሸጠ ካልሆነም እየጣለ ወደ የቦታው ተበተነ፡፡

ቀድሞውንም ኢትዮጵያን የምታክል በአፍሪካና በአለም ከፍተኛ ቦታ የነበራትን አገር ለመምራት ብቁ አዕምሮም፣ ተመክሮችም፣ አስተውሎም፣ ብቃቱም እንዳልነበረው ግልጽ ነው፡፡ አሁን ወደኋላ ዘወር ብለን ስናስብ መንግሥቱ በዚህ ሁኔታ ያን የሚያክል አገርና ሕዝብ እመራለሁ ብሎ ሲነሳ ማሰቡ ራሱ የሚገርም ነው።

ጭካኔውን መለስ ብዮ ሳየው ምን ያክል ስብእና የሌለው ሰው መሆኑ ይገርመኛል። አባቴ 38 አመት አገሩን አግልግሎ ሲያልፍ አስክሬኑን እንኳን ለቤተሰቡ ተልኮ የቀብር ሰነስርአት እንዲደረግ አልፈቀደም። ወይም አላሰበውም። ከሁለት እመት በኋላ አገር ለቆ ሲሄድ እናቴ ኮሚቴ አቋቁማ የኢህአዴግን መንግስት አስፈቅዳ፣ አስመራ ድረሰ በመሄድ በኤርትራ መንግስትና የአካባቢ ህዝብ ባደረጉት ከፍተኛ ትብብር፣ ፈቃድ አግኝታ ፣ በጉዋዶቹ ጋር በአንድ ላይ የተቀበሩበትን ቦታ በአገሬው ህዝብ ተመርታ፣ አስከሬናቸውን ቆማ አስቆፍራ፣ አስወጥታ፣ ለአካባባዊው ህዝብ ፍየልና እና በግ አሳርዳ ጋብዛ፣ በአካባቢዊው በሚገኘው ቤተ ክርስቲያን አስቀድሳ፣ ተዝካር አብልታ፣ የጀግኖቹን አስክሬን ይዛ ተመልሳለች። በአገራችን ታሪክ የባለቤቷን አስከሬን ከወደቀበት አምጥታ በክብር ያስቀበረች የማውቀውን እናቴን ወ/ሮ አስቴር አዳሙን ብቻ ነው።

በቅርቡ ከአንድ የቀድሞ ጄኔራል ጋር በስልክ ሳወራ ለሃያ ሰባት አመት የቀድሞ ሠራዊት አባላትና ቤተሰቦቻቻው አንገታቸውን እንዲደፉ ተደርጓል አሉኝ፡፡ አባባላቸው ቢገባኝም የእኔን ስሜት ግን እንደማይገልጸው ነገርኳቸው፡፡ አባቴ ዕጁን ሰጥቶ ተማርኮ በእስር ቤት እዚህ ሂድ፣ እዛ ቁጭ በል ፣ ና ! ተመለስ ! ሲባል ባይ ኖሮ እርግጥ አንገቴን ደፍቼ እኖር ነበር፡፡ አባቴ በሞትና በሕይወት ውስጥ ይኖር እንደነበር አብሬው ጦር ሜዳ ድረስ ሄጄ ያየሁት ስለነበር የሞትን ሐቅነት ከተቀበልኩ ቆይቼ ነበር፡፡ እንደ አንድ የጦር መሪ ለቆመለት አላማ ሲታገል ሕይወቱ አልፏል፡፡ እንደ አንድ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ አገሩን አገልግሎ ለአገሩ ሲል የኢትዮጵያን ሕዝብ ከአምባ ገነን አገዛዝ ነጻ ለማውጣት በመረጠው መንገድ ተሰውቷል፡፡ የኢትዮጵያ ጦር የኢትዮጵያ እንጂ የደርግ እንዳልነበረ ከደርግ በፊት ያበረከተው 23 ዓመታት የውትድርና ዘመን ብቻ ሳይሆን በደቡብ በምስራቅና በሰሜን የከፈለው መስዋዕትነት በመጨረሻም ለአገሩ ያፈሰሰው ደም ይመሰክራል፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን የ 12 እና የ15 አመት ልጆቼ ስለአያታቸው በኩራት አንገታቸውን ቀና አድርገው ነው የሚያወሩት።

ECADF 

ሰላሌ/ሰላላ- የአማራ ጥንታዊ ርስት

ሰላሌ/ሰላላ- የአማራ ጥንታዊ ርስት

ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ አዛዥ፣ በ1953 ዓ.ም. እነ ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ላይ የሞከሩትን ስዒረ መንግሥት በቀዳሚነት ያከሸፉትንና ደርግ ከጭሰኞቻቸው ጋር በግፍ የረሸናቸውን የጄኔራል ታደሰ ብሩን ሐውልት በትናንትናው እለት በምድረ ሸዋ በጥንታዊቷ የአማራና ርስት በሆነችው በሰላላ/ሰላሌ መርቋል።

ጀኔራል ታደሰ ብሩ አባታቸው አቶ ብሩ ኬኔ ናቸው። አቶ ብሩ ኬኔ የከረዩ ኦሮሞ ሲሆኑ የትውልድ ሀረጋቸው እንደሚከተለው ነው፤ ብሩ ኬኔ ጅሩ ኡመቶ ጉታ ሞገር ደራ አቦቴ ሲንቼል ሲቡ ኢሌ አባዶ ሊበን ከረዩ ኦቦ። በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አዋሽን ተሻግሮ ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን ወደ ነበሩበት ወደ አማራ ምድር ወደ ግራርያ አውራጃ ሰላላ ወረዳ የመጣው የመጀመሪያው ትውልዳቸው አባዶ ሊበን ነው።

የጄኔራል ታደሰ አባት አቶ ብሩ ኬኔ ጸረ ፋሽስት አርበኛ የነበሩ ሲሆኑ ሕይዎታቸው ያለፈው ከራስ ካሳ ጋር በመዝመት ለአገራቸው ተሰልፈው ሲዋጉ በፋሽስት ጥሊያን የመርዝ ጭስ ነው። አባቱ ሲሞቱ የ13 ዓመት ልጅ የነበረው ታደሰ ብሩ የአባቱን ፈለግ በመከተል ፋሽስት ጥሊያንን ለመፋለም ዱር ቤቴ ባለበት ወቅት በፋሽስት ጥሊያን ተማርኮ ወደ ሞቃድሾ እስር ቤት ውስጥ ተሰቃይቷል።

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት እንደገና ሲቋቋምና ፋሽስት ጥሊያን ያሰራቸው የኢትዮጵያ አርበኞች ከሶማሊያ እስር ቤት ሲለቀቁ ወጣቱ ታደሰ ብሩም የጦር ሰራዊት አባል በመሆን አገሩን ማገልገል ጀምሯል። የኢትዮጵያ ፖሊስ እንደ ተቋም ሲመሰረት ጀኔራል ጽጌ ዲቡ ከሶስተኛው ክፍለ ጦር ወደ አዲስ አበባ ይዘዋቸው ከመጡት ወጣት የሰራዊቱ አባላት መካከል አንዱ ታደሰ ብሩ ነበሩ። በጊዜ ሂደት በሹመት ላይ ሾመት እየደረቡ በማደግ የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ አዛዥ ሆነው በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ተሹመዋል።

መግቢያ ላይ እንዳወሳሁት ጀኔራል ታደሰ ብሩ የተወለዱበት አገር ሰላሌ ኦሮሞ ወደ ቦታው ከመስፋፋቱ በፊት የአማራ አገር ነበር። በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የቱለማ የኦሮሞ ጎሳዎች ከብቶቻቸው እየነዱ ሸዋን ወረው ባለ ርስቱን ገበሮ፣ ጠለታና ገርባ በማድረግ የቦታውን ስያሜ ሰላሌ ብለው corrupt ከማድረጋቸው በፊት የቦታው ትክክለኛ መጠሪያ ሰላላ የሚል የአማርኛ ስም ነበር። ሰላላ አማርኛ ነው። ሰላላ የሚለው የአካባቢ መጠሪያ ኦሮሞ ወደ ቦታው ከመስፋፋቱ በፊት በተጻፈው የዐፄ ሱስንዮስ ዜና መዋዕል ውስጥ ተጠቅሶ ይገኛል። የዐፄ ሱንዮስ ጸሐፌ ትዕዛዝ አዛዥ ተክለ ሥላሴ ዐፄ ሱስንዮስ በአያታቸው ምድር በሸዋ ያሳለፉትን የወጣትነት ዘመን በገለጹበት የዜና መዋዕሉ ክፍል እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፤

“ወበውእቱ ምድረ ረከቦ ዓብይ ምንዳቤ ረኅብ እስከ በልኡ ሠራዊቱ አሣእነ እግሪሆሙ። እስመ ተኃጥ አእክል ለሲሳይ በእንተ ዘኮነት ይእቲ ምድር በድወ ወዓጸ። ወእምዝ ተንሥአ እምይእቲ ምድር ወአመልአ ፍኖቶ መንገለ ግንድ በረት ። ወእምዘ የሐውር በጽሐ ምድረ ሰላላ።” [Pereira, F. M. E. (1892). Chronica de Susenyos, Rei de Ethiopia: Texto ethiopico: destinado á X sessão do congresso internacional dos Orientalistas. Imprensa nacional; Page 22 ]

ትርጉም፤

ያንጊዜም ሐንገታሞ በሚባል ስፍራ ተቀመጠ። በዚያም ስፍራ ታላቅ የርሐብ ችግር ገጠመው፤ ተከታዮቹ የእግራቸውን ጫማ እስኪበሉ ድረስ። ለምግብ የሚሆን እህል ታጥቷልና፤ቦታዋ ምድረ በዳና ደረቅ ስለሆነች። ከዚህ በኋላ፣ ከዚያች ቦታ ተነስቶ ወደ ግንደ በረት ጉዞ አደረገ። ሲሄድም ሰላላ ደረሰ።

ሐንገታሞ ደብረ ብርሀን አካባቢ የሚገኝ አገር ነው። ግንደ በረትም አሁንም ድረስ ሸዋ ውስጥ የሚገኝ ቦታ ነው። ዜና መዋዕሉ እንደሚነግረን ዐፄ ሱስንዮስ ከደብረ ብርሀን አካባቢ ተነስቶ ወደ ግንደ በረት ለመሄድ ሰላላ አድሯል። ይህ ሁሉ ታሪክ የተፈጸመው ኦሮሞ ወደ ቦታው ከመምጣቱ ከአንድ ክፍለ ዘመን በፊት ነው።

ሰላላ በአማርኛ አነጋገር ውስጥ በብዛት ጥቅም ላይ ይውላል። ጎጃም ስናድግ ልጆች ሳለን የዘመን መለዋጫ በዓልን ሲከበር በወጣቶች በሚዜሙ ጥዑመ ዜማዎች ውስጥ ሰላላ ጥቅም ላይ ይውል ነበር። በበዓሉ እለት ከሚዜሙት ጥዑመ ዜማዎች መካከል ሴት ቆነጃጅት እንዲህ እያሉ ያዜሙ ነበር፤

የቅዱስ ዮሐንስ ያልዘፈነች ቆንጆ፣ 
ቆማ ትቀራለች እንደ ሰፈር ጎጆ፤ 
እቴ አደይ አበባ ነሽ፣ 
ዉብ ነሽ ዉብ ነሽ፤

ልጃገረዶች ይህንን ዜማ እንግጫ እየነቀሉ ሲያሰሙ፤ ጎረምሶች ወንዶች ደግሞ የሚከተለውን እያዜሙ ወደ ልጃገረዶች ይሄዳሉ፤

እንግጫችን ደነፋ፣
ጋሻዉን ደፋ፤ 
እንግጫዬ ነሽ ወይ፤

ኮረዶች ይህንን ሲሰሙ እንዲህ ብለው ይመልሳሉ፤

እሰይ እሰይ፣
የቅዱስ ዮሐንስ የመስቀል የመስቀል፤
የላክልኝ ድሪ ሰላላ መላላ፣
መልሰህ ዉሰደዉ ጉዳይም አይሞላ፤

በዚህ ጊዜ ጎረምሳው ለወደዳት ልጃገረድ ማተብ ያስርላታል። ጨዋታው እንዲህ እንዲያ እያለ ይደራ ነበር. . .

የሆነው ሆኖ የኦሮሞው ጀኔራል የታደሰ ብሩ መታሰቢያ ሐውልት የቆመበት አገር ስላሌ/ ሰላላ የአማርኛ ስም ያለው የአማራ ምድር ነበር። ሰላሌ ወደሚል የኦሮምኛ ድምጸት ያለው ስያሜ የተለወጠው ከኦሮሞ መስፋፋት በኋላ ነው።

ሐውልቱ የዘመኑን እውነት የሚያንጸባርቅ አይደለም። ጀኔራል ታደሰ ብሩ በደርግ ሲገደሉ ብቻቸውን አልነበሩም። ጄኔራል ታደሰ ብሩን ደርግ የገደላቸው ከጭሰኞቻቸው ጋር ነበር። ሐውልት ሲቆምላቸው ግን አብረዋቸው የተገደሉት የታደሰ ብሩ ጭሰኞች መታሰቢያ አልቆመላቸው።

ኦነጋውያን ጀግና ለመፍጠር ስለሚፈልጉ የነሱን ትርክት ፈጥረው በጄኔራሉ ታሪክ ዙሪያ የራሳቸው ትርክት ፈጥረው ብዙ ውሸት አምርተዋል። ኦነግ የጀኔራል ታደሰ ብሩን የኢትዮጵያ አርበኛነትና የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የፈጥኖ ደራሽ አዛዥ እንደነበሩ ማውሳት አይፈልጉም። በመኢሶን ቋንቋ ጀኔራል ታደሰ ብሩና ኮለኔል ኃይሉ ረጋሳ ፊውዳሎች ነበሩ። ጀኔራል ታደሰና ኮሎኔል ኃይሉ ጫካም የገቡት ኦነጋውያኑ እነ ባሮ ቱምሳ፣ ዲማ ነገዖና ዘገዬ አስፋው ያረቀቁትን የደርግን «የመሬ ላራሹ» አዋጅ ተቃውመው ነው።

ይህ ደርግና መኢሶን ያቀረቡት ትርክት ብቻ አይደለም። ለእድገት በኅብረት ዘመቻ የመሬት ላራሹን አዋጅ ሊያስፈጽሙ ከዘመቱ ተማሪዎች መካከል ጀኔራል ታደሰ ብሩ በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ መሬት ለጭሰኞች ለማከፋፈል ሲሞክሩ ጀኔራል ታደሰ ተማሪዎችን መሬት ለጭሰኞች ማከፋፈል አትችሉም ብለው ያባረሯቸው ተማሪዎችም አረጋግጠዋል። የኃይሌ ፊዳ ድርጅት መኢሶንም እነ ታደሰ ብሩና መለስ ተክሌ በአንድ ቀን በተረሸኑበት ወቅት በልሳኑ ባወጣው መግለጫ ተራማጆቹ እነ መለስ ተክሌ ከፊውዳሎቹ ከነ ታደሰ ብሩ ጋር መገደል የለባቸውም የሚል መግለጫ አውጥቶ ነበር።

ለማንኛውም ኢትዮጵያ እንዲህ ነች! በአማራ ጥንተ ርስት ላይ የኦሮሞ ጄነራል ሐውልት ማቆም የሚቻልባት ምድር ናት 

ከታች የታተመው ፎቶ መጋቢት 5 ቀን 1967 ዓ.ም. አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጀኔራል ታደሰ ብሩ ከነ ጭስኞቻቸውና ኮሎኔል ኃይሉ ረጋሳ በሻለቃ ተስፋዬ ገብረ ኪዳን [ኋላ ጀኔራልና ከመንግሥቱ ኃይለ ማርያም በኋላ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት የበነበረው – የኦሮሞ ነገድ ተወላጅ ] በሚመራው የደርግ አሳሾች በተያዙበት ወቅት የተነሱፎቶ ነው።

by  – Achamyeleh Tamiru

ግንቦት 20 – “አይ ኢትዮጵያ ለካ ሰው የለሽም!”

ግንቦት 20 – “አይ ኢትዮጵያ ለካ ሰው የለሽም!”

ሰዎች መለስ ዜናዊን ከኮለኔል መንግስቱ ኃ/ማርያምና አልፎ ተርፎም ከዓጼ ኃ/ስላሴ ጋር “ኢትዮጵያዊ ዲክታቶር” ብለው በአንድ ቅርጫት ውስጥ ይከቱታል። ይህ አባባል ሀቅነት አለውን? ይነበብ!

መለስ ዜናዊ 1) ሁለት መፃህፍት ጻፈ። ሁለቱንም ተጀምረው እስኪያልቁ በ”ኢትዮጵያ ቅኝ አገዛዝ ስር ለዘመናት ስለማቀቀቸው” ስለኤርትራ ነፃነት የሚያወጉ ናቸው።

2) አንድ ሰው ህወሃትን ሲቀላቀል የመጀመሪያ የሚቀርብለት ጥያቄ በኤርትራ ነፃነት ታምናለህ ወይ የሚል ነው።

3) ማንም የህወሃት አባል በኤርትራ ላይ – ለምሳሌ ኢትዮጵያን ደግፎ ስለ ወደብ አስፈላጊነት ካነሳ – ወድያው ይታሰራል፣ ቶርቸር ይደረጋል፣ በእምነቱ ፅኑ ሆኖ ከተገኘ ይገደላል።

4) 70ሺ የኢትዮጵያ ወጣት ተሰውቶ ያመጣውን ወታደራዊ ድል አዲስ አበባ ላይ ሆኖ፣ “ያይናቸው ቀለም ካላማረን እናባርራለን” እያለ እያጭበረበረ፣ በኢትዮጵያ ወታደር ተገርፎ ወደ ሱዳን ሲሸሽ የነበረውን የሻቢያ ወታደር አራት ኪሎ ላይ ሁኖ፣ ሬድዮ ላይ ወቶ “ጦርነቱ በ24 ሰዓት ይቆማል” ብሎ የጠላት ጦር እንዲመለስ አደረገ።

መጨረሻም ኢትዮጵያን እያዋረደ መኖር ነበር አላማውና፣ በራሱ አነሳሽነት ዘ ሔግ ፍ/ቤት እንዲቆም አስወስኖ፣ በየማነ ጃማይካ የሚመራው የኤርትራ ቡድን ከአዲስ አበባ ወደ ዘ ሔግ ተጓዘ። ሌላው ኤርትራዊው ቡድን ከአስመራ ተነስቶ ዘ ሔግ ገባ። ገለልተኛ ዳኞቹ የሁለት ኤርትራውያን ወግ መሆኑን ተገንዝበው፣ “አይ ኢትዮጵያ! ለካ ሰው የለሽም” ብለው ፋይሉን ኤርትራን በሚጠቅም መንገድ ዘጉ።

አሁን ከኢሳያስ አፈወርቂ ሺ ጊዜ ጽንፈኛ ኤርትራዊ ብሄርተኛ የነበረው፣ ማንም የህወሃት “ባለስልጣን” ትግሬ “ስልጣኑን” የመለስ ትእዛዝ ማክበር እንጂ ሌላ “ሓባ ስልጣን” እንዳልነበረው ዛሬ በሃፍረት ሻማ ተከናንቦ የሚያስታውሰውን፣ በብቸኝነት 100% ስልጣን ተቆጣጥሮ “ኦሮሚያ” የሚል እና ሌሎች ትንንሽ፣ ሲጋጩ እንዲኖሩ ተደርገው ተጠፍጥፈው የተሰሩ አገሮችን ፈጥሮ፣ የጥላቻ መርዙን ሲረጭበን የኖረው መለስ ዜናዊ የገዛበት ዘመን ምን ግራ የሚያጋባ ሆኖ ነው “የጠላት አገዛዝ ዘመን” ተብሎ በታሪክ የማይዳኘው?

ይህ ጉዳይ መለስን በጠላትነት ፈርጆ ቁጭ ለማለት ሳይሆን፣ ከተፈረጀ በኋላ መለስ ከኤርትራ እና ከሱዳን ጋር የተፈራረማቸውን ኢትዮጵያን ክፉኛ የሚጎዱ ውሎች ኢትዮጵያን ሊወክሉ እንደማይችሉ ለማስረገጥ (to make them null and void)፣ ሌሎች እንደ ዶ/ር አብይ አህመድ ከመሪ፣ እንደ ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ እንደ ዜጋ የመለስን ኢትዮጵያን የሚያዋርዱ ውሎችን ለማጽደቅ የሚጣደፉትን አደብ እንዲገዙ፣ እንደ ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም (‘አሰብ የማን ናት’ ደራሲ) እና ከአፋር ወገን የተገኘው አንደበተ-ርቱእ ኢትዮጵያዊው ምሁር ዶ/ር ኮንቴ ሙሳ በፅኑ ኢትዮጵያዊነት መንፈስ ትግሉን እንዲመሩ ለማድረግ፣ እና እንደ ቀይ ባህር የአፋር አገርን በህጋዊ መንግድ ከነ አሰብ ወደቡ ወደ ታሪካዊት ባለቤቷ ወደ ኢትዮጵያ ለማስመለስ በሚደረገው ትግል ለቀጣዩ ትውልድ ፅኑ የህግና የታሪክ መሰረት ሆኖ ስለሚያገለግል ነው።

የኢትዮጵያ ክብር በልጆችዋ ፅኑ ተጋድሎ ይመለሳል!

Abrha Belay

የኦቶማን መንፈስ በአፍሪካ ቀንድ

ቱርክ የአሁኑ ዘመን እንደ ትናንቱ አለመሆኑን የተገነዘበች አገር ነች። ይሄንን ለማለት የሚያስደፍረውም በምስራቅ አፍሪካ፣ በጥቅልም በአፍሪካ በተግባር የምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በቅድሚያ በአፍሪካ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍ ያለ ድርሻ እንዲኖራት ከመፈለግ የሚመነጭ እንጂ የአፍሪካን ባህል በእሰላማዊ መሠረት ላይ ለማስኬድ በመቋመጥ አይደለም። በአዲሱ የዓለም ሥርዓት ብርቱ የኢኮኖሚ ጥቅም ትስስር ከብርቱ ወታደራዊ እና ባህላዊ ትብብር በላይ አስፈላጊ መሆኑ የሚታይበት መሆኑ ለቱርክ ግልጽ ነው።

ቱርኮች የአፍሪካን ኢኮኖሚ ከትብብር እና ከድጋፍ ጋር አጣምሮ ለመቀራመት ከሚተጉ ቻይናን ከመሰሉ አገራት ጋር ተጋፍተው አብላጫ ድርሻውን ለማንሳት እጅግ ብረቱ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። አንዳንድ ፖለቲከኞች የቱርክ የአፍሪካ ቅርምት /Turkey scram­bles for Africa/ እያሉ እስከ መጥራት ለደረሱበት ብርቱ ፉክክር ተሰልፋ ተገኝታለች።

ዛሬ ላይ ቱርክ በአፍሪካ የ44 ኤምባሲዎች ባለቤት መሆኗን ስንረዳ በአፍሪካ ላይ ዓይኗን የጣለችበትን ደረጃም እንረዳለን። ቁጥሩ ከአንዳንድ የአውሮፓ አገራት አንፃር ሲታይ ሦስት እጥፍ እንደሚሆን ይነገራል። ቱርክ በአፍሪካ እስልምናን የማስፋፋት ፍላጎት አላት የሚሉ አካላት ቢኖሩም፤ የቱርክ ፍላጎት ግን በዚህ ላይ ብቻ የተመሰረተ አለመሆኑን በተግባር ይታያል የሚለው ሙግት ተቀባይነት ያገኘ ይመስላል።

ቱርክ ከፍተኛ የቢዝነስ መሰረት ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት ከሁሉም የአፍሪካ አገራት ጋር በሚባል ደረጃ መስርታለች። ከ15 ዓመታት በፊት ብዙ ጊዜ በአፍሪካ ፖለቲካ ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች በንቃት ክትትል፣ ተሳትፎ፣ ጣልቃ ገብነት፣ ትብብር ወዘተ… ስለሚያደርጉ አካላት ሲታሰብ አሜሪካ፣ ቻይና እና ራሺያ ጎልተው ይመጣሉ። ድምፃቸው ከልኩ በላይ ይሰማል። ቱርክ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ የእግራቸው ኮቴ ሳይሰማ በአፍሪካ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ውስጥ ተሳትፎ የማድረግ ፍላጎት ካላቸው እና እርምጃ ውስጥ ከገቡ አገራት መካከል ያላት ድርሻ ከፍተኛ መሆኑ አሌ አይባልም።

እስከ አሁንም በአፍሪካ ውስጥ የስድስት ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ተሳትፎ አላት። ከፍተኛ የሚባለውን የቻይና ኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለመጋራትም እየጣረች ነው። የወቅቱ ፕሬዚዳንት ራሴፕ ታዪፕ ኤርዶጋን ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ እንኳን በአፍሪካ የተለያዩ አገራት ከ30 ጊዜ ያላነሰ የጉብኝት መርሐ ግብር ነበራቸው። ራሳቸው ፕሬዚዳንቱ በተለያዩ የአፍሪካ ጉዳዮች መድረክ ላይ ‹‹አዲሱ የዓለም ሥርዓት እየተገነባ ባለበት በዚህ ወቅት ቱርክ አካሄዷን ከአፍሪካ ጋር ታሳምራለች።›› ሲሉ ተደምጠዋል። እንደ Middle East Eye ዓነቶቹ ሚዲያዎች ይሄንን ፈጣን እንቅስቃሴ አዲሱ የኦቶማን ተስፋፊነት /Neo Ottomans Expansionism / በማለት ይጠሩታል።

ቱርክ በአፍሪካ ያላት የኢኮኖሚ ፍላጎት የሰብአዊ እና የልማት ድጋፍንም አጣምሮ የያዘ በመሆኑ ፤ በአጭር ጊዜ እየተመነደገ እንዲሄድ በር ከፍቷል። ለዚህም የቱርክ ዓለም አቀፍ የትብብር እና ጥምረት ኤጀንሲ / TIKA/ ተግባራት ይጠቀሳሉ። ይህ ኤጀንሲ በ28 የአፍሪካ አገራት ውስጥ የሚተገበሩ ከ200 የማያንሱ ፕሮጄክቶችን ይመራል። ቱርክ ለአፍሪካ አገራት የምትሰጠውን ትብብር እና ድጋፍ በዚህ ኤጀንሲ በኩል ታስፈጽማለች። ከዚህ የልማት ትብብር እና ድጋፍ ጎን ለጎን ግን ቱርክ በአፍሪካ ያላት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ድርሻ እጅግ አነጋጋሪ በሆነ ደረጃ አይሏል።

በዐረብ አቢዮት የተናጠው የውጭ ግንኙነት ወቅታዊው የቱርክ የግንኙነት ፖሊሲም በአዲሱ የዓለም ሥርዓት ውስጥ ያሉ አንዳንድ ለውጦችን መነሻ ማድረጉ ባይካድም በምስራቅ አፍሪካ የውጭ ግንኙነት እና የደኅንነት ፖሊሲዋ ግን ነባሩን የታሪክ እና የባህል ግንኙነት የገደፈ ነው ብሎ ለመናገር ያስቸግራል።

ቱርክ ሁለት ቁልፍ የደኅንት ሥጋቶች አሉባት። አንዱ ከምዕራባውያን ጋር የጎሪጥ የምትተያይበት የቱርክ የተገንጣይ ኩርዶች እንቅስቃሴ ነው። ተገንጣይ ቡድኖቹን አሜሪካ እና ሸሪኮቿን ለመደገፍ የሚያሳዩት ዝንባሌ እና ተግባር በአፀፋው ቱርክ በምስራቅ አፍሪካ እና በሌሎች አካባቢዎች የተቻላትን ያህል በጥቅሞቻቸው ላይ የእጅ አዙር ትንኮሳዎች / ጫናዎች የማሳደር ዝንባሌ ያለው ፖሊሲ አላት። ሁለተኛው ቁልፍ ሥጋት አረባዊ ሙስሊሞች አረብ ባልሆኑ ሙስሊሞች ላይ ያላቸውን ፖሊሲ የሚገዳዳር ነው። ለዚህም አረባዊ እስልምናን ሳይሆን ሙስሊም ወንድማማችነትን መሰረት ያደረገ እስላማዊ ጫና እንዲስፋፋ ትፈልጋላች። ለዚህም ግብጽን ከመሰሉ አገራት ጋር የጎሪጥ የመተያየት እና የመገዳዳር ፖሊሲ አላት።

በምስራቅ አፍሪካ ያለው ወቅታዊ የቱርክ የውጭ እና የደኅንት ፖሊሲ የሚቀዳበት አንዱ ምንጭ እነዚህ ሁለት ሥጋቶችን የመቅረፍ አቅጣጫ ነው።

ከዐረብ አቢዮት ተከትሎ በግብጽ የሙ ስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ በምርጫ የበላይነትን ባገኘ ጊዜ ለቱርክ ከፍተኛ ፈንጠዝያ ተፈጥሮ ነበር። አፀፋዊ በሆነ አቢዮት ሙርሲ ከሥልጣን መንበራቸው ወርደው ወደ እስር መምጣታቸው ግን ቱርክን በከፍተኛ ደረጃ አስቆጥቷታል። ስለዚህም በምሥራቅ አፍሪካ የምትከተለው የግንኙነት አቅጣጫ የአልሲሲን መንግሥት ጫና ውስጥ የሚከት እንዲሆን በጥበቅ መሥራት ቀጥላለች።

የቱርክ አንዱ እርምጃ ‹‹የዘላለሜ ነሽ›› ከምትላት ሱዳን ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ጠበቅ በማድረግ በቀይ ባህር በሱአኪንደሴት ላይ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ከሱዳን መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ ደርሻለሁ ብላ ይፋ አድርጋለች። ይኸው ደሴት በሊዝ ግዥ ዓይነት በቱርክ እጅ መውደቁ ለግብጽ ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሯል። በሱዳን በኩል የተዘረጋው የቱርክ ፀበ ጫሪ እርምጃ በምሥራቅ አፍሪካ ውጥረት ሊፈጠር እንደሚችል ለየትኛውም የፖለቲካ ተንታኝ ግልጽ ነበር። እንደተሰጋውም የግብጽ መንግሥት ኤርትራ ላይ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ወደ ገነባችው ወታደራዊ ሠፈር በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ልካለች። ያንን ተከትሎም ሱዳን ከኤርትራ ጋር ያላትን ድንበር ዘግታለች። በሺህዎቸ የሚቆጠሩ ወታደሮቿንም ወደ ኤርትራ ድንብር አስጠግታ ነበር። የቱርክ እርምጃ ሁለቱን የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ኤርትራን እና ሱዳንን አፋጠጠ።

እንደ ሱዳን ትሪቢዩን ዘገባ ደግሞ ቱርክ ከሱዳን ጋር ያላትን ግንኙነት ጠንካራ ፈተና የሚያመጣው በወታደራዊ መስክ ያላቸው ትብብር ነው። ቱርክ በሱዳን ወታደራዊ ማሰልጠኛዎችን ለመክፈት እና መከላከያ መሥሪያ ቤቷን ለማጠናከር ያደረገችው ስምምነት ከጎረቤት አገራቱ በተለይም በግብጽ በዓይነ ቁራኛ የሚታይ ሆኗል።

ቱርክ ለአፍሪካ ወታደራዊ ሹማምንት (መኮንኖችም) ስልጠና ለመስጠት መትጋቷ ቢታወቅም፤ በመሥራቅ አፍሪካ ደግሞ በተለይ ለሱዳን፣ ለሶማሊያ፣ ለኢትዮጵያ፣ ለኡጋንዳ እና ለኬኒያ በዚህ ረገድ የምትሰጠው ድጋፍ ጠንካራ ነው። ቱርክ ይሄንን በምስራቅ አፍሪካ የምታደርገው በቀይ ባህር፣ በባብኤል ወደብ የባህር ወሽመጥ እና በኤደን ባህረሰላጤ ሊኖራት የምትፈልገውን የኃይል ሚዛን ለማስጠበቅ ነው።

ሱዳን ከቱርክ ጋር ለመሥራት ያላትን አቋም እንድታጠናክርም የቱርክ ፕሬዚዳንት በታህሳስ 2018 ላይ በሱዳን ባደረጉት ጉብኘት መልዕክት አስተላልፈዋል። ሱዳን እስከ አሁንም መፍትሔ ልትዘይድለት ብትቸገርም ኢኮኖሚዋን የበለጠ በመደገፍ እንዳታፈገፍግ ለማድርግ ቱርክ ወሳኝ እርምጃ ወስዳላች። ቱርክ ለነዳጅ ፍልጋ እና የነዳጅ መስክ ልማት የሚውል 100 ሚሊየን ዶላር ለመመደብ እና ሱዳን ለቱርክ ኩባንያዎች በሺዎች በሚቆጠር ስኩየር ማይሎች ያህል የግብርና መሬት ለቱርክ ባለሀብቶች እንድታቀርብ የሚያደርግ ሰምምንት ተፈራርመዋል። በግብርና መሬቱም ለቱርክ እና ለሱዳን የምግብ ዋስትና በሚበጅ ደረጃ እንደሚለማ ታቅዷል። የንግድ ግንኙነታቸውንም በዓመት ወደ 10 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ተስማምተዋል።

የቱርኩ Ziraat Participation Bank ቅርንጫፉን ካርቱም በመክፈት ከሱዳን ጋር ያለውን የገንዘብ ሴክተር ግንኙነት ለማሣለጥ አልሟል።

ሱዳን ያለባትን የምንዛሪ እጥረት ግን በጊዜው መፍታት በላመቻሏ ወደ ኢኮኖሚ ቀውስ ማምራት ግድ ሆኖባታል። በዚህም ምክንያት ህዝባዊ ተቃውሞ በመንግሥት ላይ ተነሥቷል።

ሕዝባዊ ተቃውሞውን ተከትሎ ቱርክ የነበራት ኢንቨስትመንት አሁን ካለበት ከ2 ቢሊየን ዶላር በተሻለ በስፋት በሱዳን መሬት የማሳደግ ዕቅድ ፈተና ሊገጥመው ይችላል። ቱርክ ራሺያ እና ኳታር በሱዳን ወቅታዊ ችግር ‹‹ከጎንሽ ነን›› ባሉት አግባብ ቱርክም በተመሳሳይ ያለውን ወቅታዊ ችግር ለመፍታትም የኢኮኖሚ ድጋፍ ለማድረግ ትብብሯን ገልፃለች።

 ዘመን መፅሄት መጋቢት 2011 ዓ.ም

 በማለደ ዋስይሁን

አዛውንቱ ጓድ መንግሥቱ ኃ/ማርያም በአዲስ አባ ጎዳና – ከሹፌሩ ማስታወሻ

የአስጎብኚ ድርጅት ሹፌር ነኝ፡፡ አለቃዬ አንድ ጥቁር እንግዳ በአ.አ ጎዳናዎች እንዳንሸራሽር አዘዘኝ፡፡ ጓድ መንግሥቱ በድብቅ ሀገር ውስጥ ገብተዋል፡፡ አንዳንድ ቦታዎችን በጥንቃቄና በሚስጥር አስጎብኛቸው ሲል በደፈናው ትዕዛዝ ሰጠኝ፡፡ መስተዋቱ በተሸፈነ “የደህንነት” መኪና ውስጥ ወደ ተቀመጡት ሰው አመራው፡፡ ሳያቸው ድንግጥ አልኩ፡፡ በእጃቸው አጭር በትር ይዘዋል፡፡ ዐይናቸው ጎላ ብሎ ይታያል፡፡

“ደህና ዋሉ?” ትኩር ብለው በግንባራቸው ቂጥ ዐዩኝና “በመጀመሪያ ወደ አብዮት አደባባይ ወስደኸኝ ስታበቃ፣ ቀጥሎ ወደ ወደ ቤ/መንግስቱ አካባቢ እናመራለን፡፡” የዚህ ድምፅ ቅላፄ ድንገት ወደ ልጅነት ዘመን ትዝታዬ አነጎደኝ፡፡ ቢጫና ቀይ ቀለም ያለው ዳንቴል ወደተሸፈነችው ሬዲዮናችን፡፡

በመንገዳችን በሙሉ ኮለኔሉ በተዋጣለት ፉጨት የድሮ የሀገር ዜማዎችን ማዜም ያዙ፡፡ በተለይ “ሽጉጥ መትረየሱን አንግቶታል፣ 
ያ ጥቁር ግሥላ ደም ሸቶታል…” የሚለውን ዜማ ዋሽንት በሚያስንቅ ፉጨት ቢያዜሙትም የሆነ ስሜት የሚረብሽና የሚያስፈራ ስሜት አመጣብኝ፡፡

ድንገት ኦሎምፒያ አካባቢ ስንደርስ ጥያቄ ሰነዘሩ “እኔ እምለው አንተ ወጣት፣ ዛሬ ንግሥ አለ እንዴ?” 
“ኧረ የለም?” 
“እሺ ወያኔ ሕዝቡን ሠልፍ ጠርታዋለች?” 
“ኧረ አልጠራችም” 
“እና ሠፊው ሕዝብ መንገድ ላይ ምን ይሰራል? የሥራ ሰዓት አይደለም እንዴ አሁን?” 
“ያው በዝተን ነዋ፡፡ ሁሌም እንዲሁ ነን፡፡ አሁን ጦርነት ስለሌለ በዝተናል ኮለኔል መንግሥቱ” አልኳቸው።
“አሽሙር መናገርህ ነው፡፡ ለእናት ሀገር መሞትን የወሊድ እንክብል ከመጠቀም ጋር ታወዳድራለህ? የነገሩህን ነው አንተ ምንታደርግ፡፡ አቁምልኝ አሁን እዚህ ጋ!” አሉ አብዮት አደባባይ ስንደርስ፡፡ መስታወቱን ዝቅ አድርገው ፀጥ አሉ፡፡ ፍዝዝ ብለው አካባቢውን ቃኙ ግን የሆነ ነገር አበሳጫቸው፡፡ ገና ሮጦ እንደቆመ ሰው ከላይ ከላይ መተንፈስ ጀመሩ፡፡

“ወያኔ ሀገሩን በመሉ፣ ታሪካችንን ሲያወድም መክረሙን ብንሰማም፣ በአብዮት አደባባይ ላይ ግን እንዲህ ያለው ግፍ ሲሰራ፣ ሰፊው ሕዝብ በዝምታ ይመለከታል ብዬ አልጠረጠርኩም፡፡

ስንት ታንክ፣ መትረየስ፣ ቦምብ፣ ሚሳኤል፣ ትርዒት ያሳየንበትን ከፍተኛ አብዮታዊ መልዕክቶችን ያስተላለፍንበትን ታላቅ መድረክ ሆን ብሎ ምሽግ በምሽግ ማድረግ የወንበዴ ሴራ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ይፈርዳል” ተበሳጩ፡፡ ዐይናቸውን በፍጥነት እንደ ጠረጴዛ ቴኒስ ኳስ ከግራ ወደ ቀኝ፣ ከቀኝ ወደግራ አመላለሱት፡፡ ዛሬም ያስፈራሉ፡፡

“ሕዝባዊት ቻይናን ጎብኝተናል፣ ሶቭዬት ሕብረትን ዐይተናል፣ የካስትሮን እናት ሀገር ተዘዋወረንበታል፡፡ አንድም ባቡር በታላላቅ አደባባዮች ላይ ሲንፏቀቅ፣ በቆጥ ላይ ሲሰቀል አላየንም፡፡ ሰው እንዴት ዕድሜ ልኩን ምሽግ ሲቆፍር ይኖራል? ይኼ ከምሽግ ቆፋሪነት ባሕሪ የመነጨ የፍልፈል ሥነልቦና ነው፡፡ መቆፈር፣ መቆፈር፣ መመሸግ፣ መመሸግ፡፡” ተቆጡ፡፡

“እስቲ ወደ ቤተ መንግሥቱ ውሰደኝ፡፡” አሉ፡፡ ሂልተንን አልፈን ወደ ዋናው ቤ/መንግሥት ስንቃረብ፣ አልቻሉም፡፡ ድምፅ ሳያሰሙ አለቀሱ፡፡ ፍዝዝ ብለው ወደ ውስጥ እያዩ በር ላይ ያለውን ጥበቃ ሲያዩት ከራሳቸው ጋር አወሩ፡፡ “ውይ ይኼኛው ወታደር ደግሞ የጀግናው አብዮታዊ ሠራዊታችን አባል ይመስል የለም እንዴ፡፡ እህ.. እህ.. እህ…” ሌላ ለቅሶ፡፡

በመንገድ ላይ አንድ አፍሮ ፀጉሩን ያበጠረ ጎልማሳ ሰው ሲያዩ “ይኼ ጓድ ፍቅረሥላሴ አይደለም እንዴ?” አሉ፡፡ “ኧረ እኔ አላውቃቸውም” በመሃል የከፈትኩት ሬዲዮ የቀትር ዜና ማሰማት ጀመረ፡፡ ድምፅ ጨምርበት አሉኝ፡፡ ጨመርኩበት፡፡ “ይህ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ነው” ሲል በደስታ በትራቸውን በሁለት እጃቸው ወደላይ እንደተሸለሙት ዋንጫ አነሱት፡፡ ፈገጉ። ወዲያው “ደርግ የተደመሰሰበት የዘንድሮው ግንቦት ሃያ በዓል በድምቀት ይከበራል፡፡” ብሎ ነገር አበላሸ፡፡ ወርጄ ለመሮጥ ሁሉ አሰብኩ፡፡ ዐይኔን በድንጋጤ አፈጠጥኩ፡፡ በመስታወቱ ቀስ ብዬ ሳያቸው፣ አቤት የተናደዱት መናደድ፡፡

“ደምስስልኝ ማነው አጥፋልኝ ይኼን የወንበዴ ሬዲዮ፡፡ በአድዋ፣ በማይጨው፣ በዶጋሌ ስንት በጀግንነት የተሰዉ ልጆ እንዳላፈራች፣ እናት ሀገር ኢትዮጵያ እንዲህ የወሮበላ መጫወቻ መሆኗ ያሳዝናል፡፡ ደርግ የተደመሰሰበት ይላል ይኼ የሽፍታ አፈቀላጤ፡፡ ደርግ ምን አደረገ? ወያኔና ሻዕቢያ አይደሉም እንዴ…”

ፌስቡክ እንዳስታወሰን (ድጌ)

Samson Getachew T S

በዘር የተደራጁ ፓርቲዎች እጣ ፋንታ አክቲቪስት መሆን ነው

ሰሞኑን በሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር ላይ ጎላ ብለው ካየናቸው ጉዳዮች አንዱ “ኋላቀር የፖለቲካ ባህላችን የወለዳቸው” ነባር ፓርቲዎች እንደየ ርዕዮተ-ዓለማቸው እየተሰባሰቡ መሆኑን ነው፡፡ የዚች የጽሁፌ ትኩረትም በዚሁ ዙሪያ የሚያጠነጥን ይሆናል፡፡ በቅድሚያ በዚህ መጣጥፍ የተካተቱትን ዋና ዋና ጉዳዮች ላስተዋውቅ፡፡ ከምርጫ ቦርድ በተገኘ መረጃ መሰረት በሀገራችን 108 ገደማ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ለመሆኑ ፖለቲካና ፓርቲ ማለት ምን ማለት ነው? ይህን ያህል ፓርቲ የተደራጀበት ምክንያት ምንድነው? አስፈላጊስ ነው? የፓርቲዎች ማህበራዊ መሰረት ምንድነው? የሌሎች ሀገሮች የምርጫ ድምፅ መነሻ (electoral threshold) ምን ይመስላል? ለምን ይጠቅማል? በሀገራችን የፓርቲ ፖለቲካ መቼ ተጀመረ? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ጥረት ይደረጋል፡

እንደ መንደርደሪያ…

የሰው ልጆች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎ ከማድረጋቸው አስቀድሞ ለመኖር ሦስት ነገሮች ሊሟሉላቸው እንደሚገባ ይታመናል፡፡ እነዚህም ሦስት ነገሮች ምግብ፣ አልባሳትና መጠለያ ናቸው፡፡ በፖለቲካ ድርጅት ስር ተሰባስቦ መብትና ጥቅምን ለማስጠበቅ መታገልም ይሁን ሌሎች ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ተግባራትን ማከናወን፤ ከላይ የተጠቀሱት ሦስት መሰረታዊ ፍላጎቶች ነፀብራቆች መሆናቸውን በመስኩ ምርምር ያካሄዱ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ አበው “እዬዬም ሲዳላ ነው” እንዲሉ፤ የሰው ልጅ ካልጎረሰና ካልለበሰ እንኳን ቁም ነገር ሊሰራ “እዬዬ” ብሎ ማልቀስም አይቻለውም፡፡

ፖለቲከኞቻችን በቀን ሦስት ጊዜ ጠግበን እንድንበላ ቢመኙልንም ምኞቱ ሳይሳካ 27 ዓመታት አለፉ፡፡ አማርጠን መልበስ አልታደልንም፡፡ የወፍን ያህል ለጎናችን ማሳረፊያ የሚሆን ጎጆ አልቀለስንም፡፡ ዳቦ አሮብን፣ እራፊ ጨርቅ ቸግሮን፣ በረንዳ አዳሪነት እጣፈንታችን የሆንን ዜጎች ቁጥር “ጥቂት” የሚሰኝ አይደለም፡፡ እናም ይህንን ጉድለታችንን እናሟላላችኋለን የሚሉ ፖለቲከኞቻችን በምርጫ ወቅት “ድምጻችንን” ስለሚፈልጉት እንደ ደላው ሰው የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረጋችንና “አውራ ፓርቲ” መምረጣችን ይስተዋላል፡፡ እንደ ዜጋ “ውሳኔ” ስንሰጥ ይታያል፡፡ በበኩሌ፤ እንዲህ ያለው ተሳትፎአችን በደመ-ነፍስ የምናደርገው እንጂ አስበን፣ አውጥተንና አውርደን የምናከናውነው መስሎ አይታየኝም፡፡ እንኳን ተራው ሕዝብ በርካታዎቹ ፖለቲከኞቻችን ጭምር ምን እያደረጉ እንደሆነ በቅጡ የተገነዘቡት አይመስለኝም፡፡ ያም በመሆኑ ፈረሱን ከጋሪው ማስቀደም ብቻ ሳይሆን፤ ጋሪውን እየጎተቱ፣ ፈረሱን እየሳቡ ሲባዝኑ ይስተዋላሉ፡፡ ባለፉት ዓመታት “ማህበራዊ መሰረቱን” ለይቶ ያላስቀመጠ ፓርቲ በምርጫ ለመወዳደር አደባባይ መውጣቱ ይህንን እውነት ግልጽ አድርጎ የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡

እዚህ ላይ “ለመሆኑ ‘ማህበራዊ መሰረት’ ማለት ምን ማለት ነው?” የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል፡፡ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ይሆን ዘንድ ከዚህ ቀደም የጣፍኳትን ሃሳብ መልሼ ልድገማት! ስለ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማህበራዊ መሰረት (Social Base) ምንነት ከመግለጼ በፊት ግን ስለ ፖለቲካና ስለ ፓርቲዎች በአጭሩ ጠቅሼ ማለፍን መረጥኩ – እሱን ላስቀድም!

የፖለቲካና የፓርቲ ትርጉም

“ፖለቲካ” የሚለው ቃል “ፖለቲከስ” (Politicus) ከሚለው የላቲን ቃል የተገኘ ሲሆን፤ “ፖለቲከስ” የሚለው ቃል ደግሞ “ፖሊስ” (Polis) ከሚለው የግሪክ ቃል የተገኘ መሆኑን ዕድሜ ጠገብ ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡ “ፖሊስ” የሚለው ቃል ትርጉም ደግሞ “ራሱን የቻለ ማህበረሰብ፣ ራሱን የሚያስተዳድር ከተማ ወይም አገር…” ማለት ነው ይላሉ ቀደምት የፖለቲካ ሣይንስ ልሒቃን፡፡

አንዳንዶች ደግሞ “ፖለቲካ ማለት የመንግስትና የህዝብ የግንኙነት ሂደት ነው…” ይላሉ፡፡ “ፖለቲካ ማለት ሰዎች በእለት ተእለት እንቅስቃሴአቸው የሚያከናውኗቸውን ተግባራት ለመምራትና ለማስተዳደር ስልጣንን መሰረት በማድረግ (በግድም በውድም እንዲፈጸም) የሚሰጥ ውሳኔ ነው” የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችም አሉ፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ሃሳቦች ያን ያህል የሰፋ ልዩነት ያላቸው አይመስለኝም፡፡ በአንድ የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ “አገር፣ ሕዝብ፣ መንግስትና የመወሰን ስልጣን” መኖራቸው የግድ ነው፡፡ እዚህ ላይ መነሳት የሚገባው ጥያቄ “የመወሰን ስልጣን” የት፣ በማን ቁጥጥር ስር ነው ያለው? የሚለው ነው፡፡

“የመወሰን ስልጣን” በእያንዳንዱ ዜጋ እጅ ተበታትኖ ነው የሚገኘው፡፡ ይህ የተበታተነ “የመወሰን ስልጣን” ተሰባስቦ አንድ ቦታ ላይ ካልተቀመጠ በየእለቱ የሚከናወኑ ሀገራዊ የጋራ ጉዳዮችን ለመፈጸምም ሆነ ለማስፈጸም አስቸጋሪ ነው፡፡ የሀገሪቱ ዜጎች በየእለቱ እየተሰባሰቡ በእያንዳንዱ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ይስጡ ቢባል የማይቻል ነገር ነው፡፡ (አንዳንድ የፌስቡክ “ሊቃውንት” የሚፈልጉት ግን እንዲህ እንዲደረግ ነው፡፡ ዶ/ር ዓብይ የሚናገራትን ቃል ጭምር እነሱን እንዲያስፈቅድ የሚፈልጉ አክቲቪስቶች ጥቂት አይደሉም) መንግስት የሚባለው አካል በሕዝብ ተመርጦ የእለት ከእለት ሥራዎችን እንዲያከናውን የሚደረገው በያንዳንዱ ጉዳይ ላይ በህዝብ ስም ውሳኔ እንዲወስን ነው፡፡ በሕዝብ ተመርጦ በሀገርና በሕዝብ ላይ የመወሰን መንግስታዊ ስልጣንን ለማግኘት ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያስፈልጋሉ፡፡

“ፓርቲ” የሚለው ቃል “ፓርት” (Part) ከሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የተገኘ ሲሆን፤ ትርጉሙም “የተወሰነው፣ ከፊሉ፣ ጥቂቱ፣… የህብረተሰብ ክፍል ተመሳሳይ ዓላማ ለማራመድ የሚሰባሰብበት የፖለቲካ ማህበር ነው” በዚህ ትርጉም መሰረት፤ ፓርቲ የሚቋቋመው የአባላቱንና የደጋፊዎቹን ብቻ ሳይሆን፤ በዋናነት የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መብትና ጥቅሞችን ለማስጠበቅ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህም መብትና ጥቅም የሚጠበቀው ፓርቲው የብዙሃኑን ይሁንታ አግኝቶ ስልጣን ሲይዝና በስልጣኑም አማካይነት ፖሊሲዎችን፣ ሕጎችንና ደንቦችን አውጥቶ ሥራ ላይ ሲያውል ነው፡፡

የፓርቲዎች ማህበራዊ መሰረት

አንድ ፓርቲ የሚቋቋምበት መሰረታዊ ዓላማ ይኖረዋል፡፡ በዚያ ዓላማውም መሰረት “መብትና ጥቅማችሁን አስጠብቅላችኋለሁ” ለሚላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ወገንተኛ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ አንድ ፓርቲ በአንድ ሀገር ላሉ ዜጎች ሁሉ በእኩልና በተመሳሳይ ደረጃ መብትና ጥቅማቸውን ሊያስጠብቅ አይችልም፡፡ ስያሜውም የሚያመለክተው ለተወሰኑት የህብረተሰብ ክፍሎች ጥብቅ የሚቆምና፣ ውግንና ያለው መሆኑን ነው፡፡ ለምሣሌ፡- የወዛደሩ ፓርቲ በዋናነት ለወዛደሩ መብትና ጥቅም የቆመ ነው፡፡ የቡርዧው ፓርቲ የታላላቅ ከበርቴዎችን ጥቅም አስጠባቂ ነው፣ ወዘተረፈ፡፡

የአንድ ፓርቲ ማህበራዊ መሰረትም በዋናነት “በማወጣቸው ፖሊሲዎች መብትና ጥቅማችሁን አስጠብቅላችኋለሁ” የሚላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ እነዚህም የህብረተሰብ ክፍሎች ለዚያ ፓርቲ አባል በመሆን፣ የገንዘብ መዋጮና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ፣ በስብሰባዎች ላይ በመገኘትና በማስተባበር፣ በምርጫ ወቅት ቅስቀሳ በማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ የሚገባው ነገር፣ አንድ ፓርቲ የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን “ጥቅም ያስጠብቃል፣ ውግንና አለው፣…” ማለት እግረ መንገዱን የሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ጥቅሞች ሊጫን ይችላል ማለት ነው፡፡

አባባሌን በምሣሌ ላስረዳ፡፡ የፕሬዝዳንት ኦባማ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ስልጣን የያዘው በባለሃብቶች ላይ ከፍ ያለ ግብርና ታክስ በመጣልና ገንዘብ በመሰብሰብ ለዝቅተኛው ብዙሃን ህብረተሰብ የሚጠቅም የትምህርትና የጤና ፖሊሲ አወጣለሁ በማለቱ ነው፡፡ ኦባማ እንዲህ ያለ ፖሊሲ በመከተላቸው ዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል ሲጠቅሙ የአገሪቱ ከበርቴዎች ገቢ ግን በሚጣለው ታክስ ምክንያት ይቀንሳል ማለት ነው፡፡

የእኛን ሀገር ሁኔታ ስናይ፤ ኢህአዴግ ማህበራዊ መሰረቴ የገጠሩ አርሶ አደር ነው ይላል፡፡ የአሁኑን አላውቅም እንጂ እኔ አመራር በነበርኩበት ዘመን ኢዴፓ “መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች፣ ወጣቶችና ሴቶች” በማለት ማህበራዊ መሰረቷን ማስቀመጧን አስታውሳለሁ፡፡ አሁን በመቋቋምና በመዋሃድ ላይ ያሉ ፓርቲዎች (እነ ኢዜማ) ማህበራዊ መሰረታቸው የትኛው የህብረተሰብ ክፍል ነው? የሚለውን ጥያቄ እንደ ዘበት ጣል አድርጌ ማለፍ እወዳለሁ፡፡ ምናልባት ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡

የሆነ ሆኖ ማህበራዊ መሰረቱን ለይቶ፣ ያንን የተለየ የማህበረሰብ ክፍል በማሳመን ወደ ምርጫ ካልተገባ በምርጫ ተወዳዳሪ እንጂ አሸናፊ መሆን ይቻልም፡፡ የሀገራችን ተቃዋሚዎች እንዲያሸንፉ ከማስያስችሏቸው ምክንያቶች አንዱ ይሄ ሁኔታ ይመስለኛልና ከወዲሁ ሊያስቡበትና ሊዘጋጁበት ይገባል፡፡

በሀገራችን የፓርቲ ፖለቲካ መቼ ተጀመረ?

በፊውዳሉ የኢትዮጵያ የአስተዳደር ዘመን “ፓርቲ” የሚለው ጽንሰ ሃሳብ የሚታሰብ አልነበረም፡፡ በዚያ ወቅት የነበሩት ልዑላንና መኳንንቱ የዘር ሀረግን መሰረት ያደረገ የስልጣን ማስተላለፍ ዘዴን ይከተሉ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የስልጣን ተቀናቃኝ ይነሳ የነበረውም እዚያው በዙፋኑ ዙሪያ ባሉ ዘመዳሞች መካከል ነበር፡፡ በርግጥ የአካባቢ ገዢዎችም ለማዕከላዊ መንግስት አንገብርም ብለው ያንገራግሩ ነበር፡፡ እሱም በጉልበት ይጨፈለቃል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርኩት አንድ የታሪክ ምሁር “… በአጠቃላይ እስከ ጣሊያን ወረራ ድረስ የፓርቲ ፖለቲካ በኢትዮጵያ የሚታወቅ አልነበረም፡፡ ከጣሊያን መምጣት ጋር የፓርቲ ፖለቲካ ፍንጭ ታይቷል፡፡ በተለይም በኤርትራ በግልጽ የታወቁ ፓርቲዎች ብቅ ብቅ ብለው ነበር፡፡… ከዚያ በኋላ የኦሮሞን ጥያቄ ያነሱ ማህበራትም ተፈጥረዋል” የሚል አስተያየት ሰጥቶኛል፡፡

በአብዮቱ ዋዜማ አካባቢ እነ ኢህአፓና መኢሶን በድብቅም በይፋም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመራቸው ይታወቃል፡፡ በአብዮቱ ሂደት በአስተሳብ ላይ የተመሰረቱ ብቻ ሳይሆን ዘርን መሰረት ያደረጉ “ነፃ አውጪ” ድርጅቶች ጭምር የብሔር ጥያቄን አንግበው መደራጀታቸውም ታይቷል፡፡

ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ በብሔር መደራጀት የህግ ድጋፍና እውቅና ተሰጠው፡፡ በዚህም ምክንያት የብሄር ድርጅቶች እንደ አሸን ፈሉ፡፡ በዚሁ ወቅት ህብረ ብሄራዊ ቅርጽ የያዙ ፓርቲዎች የተደራጁ ቢሆንም ብዙዎቹ ምን ዓይነት ርዕዮተ ዓለም እንደሚከተሉ፣ ማህበራዊ መሰረታቸው ምን እንደሆነ እና ኢህአዴግን ከመክሰስና ከመውቀስ ውጪ ከኢህአዴግ የሚለዩበትን አማራጭ ፖሊሲያቸውን በግልጽ ያስቀመጡበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያት በኢህአዴግ በኩል “ተቃዋሚዎች አማራጭ ፖሊሲ የላቸውም” የሚል ወቀሳ ደጋግሞ ያቀርብባቸው ነበር፡፡

በርግጥም ባለፉት 26 ዓመታት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያደርጉት የነበረው ትግል የፖሊሲ ፉክክር ሳይሆን የኢህአዴግን ድክመቶች የማጋለጥ፣ የመንግስትን የአፈጻጸም እጥረቶች የመተቸት፣ የፖለቲካ ምህዳሩ ይስፋ የሚል አቤቱታና ዓባላቶቼ ታሰሩ የሚል ክስ ነበር፡፡ ዶ/ር ዓብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ እነዚህ ክሶች ቀርተዋል፡፡ ምህዳሩም ሰፍቷል፡፡ ይህም በመሆኑ ፓርቲዎች ወደ ራሳቸው በማተኮር አደረጃጀታቸውን የመፈተሽ፣ በርዕዮተ ዓለም ማእቀፍ ውስጥ የመሰባሰብና አደረጃጀታቸውን በማስተካከል ሥራ መጠመዳቸው ይስተዋላል፡፡ ባለፈው ሳምንት የተመሰረተው “ኢዜማ” የተሰኘው ፓርቲም የዚሁ የአዲስ አደረጃጀት ውጤት ነው፡፡

ፓርቲና የህዝብ ቁጥር

በዚህ ወቅት የሀገሪቱ የህዝብ ቁጥር ከመቶ ሚሊዮን በላይ የደረሰ ሲሆን የፓርቲዎቹ ቁጥርም 108 ደርሷል፡፡ በዚህም መሰረት የህዝብና የፓርቲው ምጣኔ (Ratio) አንድ ፓርቲ ለአንድ ሚሊዮን ህዝብ እንደ ማለት ነው፡፡ ጎረቤት ሀገር ኬንያ የህዝቧ ቁጥር 53 ሚሊዮን ሲሆን፤ በኬንያ ያሉ ፓርቲዎች ብዛት ደግሞ 50 ነው፡፡ ይህም ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ የፓርቲና የህዝብ ምጣኔ ያላት መሆኑን ያሳያል፡፡

የፓርቲዎች ቁጥር መብዛት የአስተሳሰብ መበተንን ያሳያል፡፡ የአስተሳሰብ መበተን ደግሞ ለህዝብም ለፓርቲዎችም አይጠቅምም፡፡ በመደራደር ላይ የተመሰረተ የፓርቲ ፖለቲካ ባህል ለሌለው እንደ ኢትዮጵያ ላለ ሀገር የፓርቲዎች መብዛት የተረጋጋ መንግስትን ለመመስረት አያስችልም፡፡ በለይም ፓርላማዊ የፖለቲካ ስርዓት በሚከተሉ ሀገራት ፓርቲዎች በተጣሉ ቁጥር በድርድር የተቋቋመው መንግስት ስለሚበተን የተረጋጋ መንግስት ሊኖር አይችልም፡፡ ጣሊያን በዚህ የታወቀች ናት፡፡ በ50 ዓመታት ከ15 በላይ መንግስት ቀይራለች፡፡ ይሁን እንጂ የጣሊያን ፓርቲዎች የመደራደርና በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የመኖር የፖለቲካ ባህልን ያዳበሩ በመሆኑና ፓርቲዎቹም በዘር ሳይሆን በአስተሳሰብ የተደራጁ በመሆኑ የከፋ ችግር አልገጠማቸውም፡፡

የሀገራችን የፓርቲ ማቋቋሚያ አዋጅ ፓርቲዎች በቀላሉ ለመደራጀት እንዲችሉ እድል የሚሰጥ ነው፡፡ 1 ሺህ 500 የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ የቻሉ “ስብስቦች” ፓርቲ ማቋቋም ይችላሉ፡፡ ይህ ህግ የመደራጀት መብትን ከመጠበቅና ከማስከበር አኳያ ጠቃሚ ነው ቢባልም፣ በፓርቲዎች ውስጥ አንጃዎች እንዲፈጠሩ ከማድረጉም በላይ በሀገሪቱ ፓርቲዎች እንደ አሸን እንዲፈሉ ምክንያት መሆኑ ይስተዋላል፡፡

በአንድ ፓርቲ ውስጥ ያሉ ሰዎች በሁሉም ጉዳዮች ላይ አንድ ዓይነት አቋምም ሆነ ተመሳሳይ ፍላጎት ሊኖራቸው እንደማይችል ይታመናል፡፡ በዚህም ምክንያት የሃሳብ ልዩነት ሊፈጠር ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ የውስጥ የሃሳብ ትግል በማድረግ ልዩነትን ማጥበብ ሲቻል (ኢትዮጵያውን እኔ ያልኩት ብቻ መሆን አለበት የሚል ግትር ባህሪ ያለን በመሆኑ) ልዩነት በተፈጠረ ቁጥር ሃሳቡ የተሸነፈበት ወገን አንጃውን ይዞ ይወጣና “ካንተ ጋር ምን አጨቃጨቀኝ የራሴን ፓርቲ አቋቁማለሁ” ወደሚል አቅጣጫ ይገፋል፡፡ እና መፍትሄው ምንድነው? መፍትሄውማ በምርጫ የተገኘን ድምፅ መሰረት ያደረገ መነሻ ወለል (electoral threshold) ማስቀመጥ ነው፡፡

የምርጫ ድምፅን መሰረት ያደረገ መነሻ (electoral threshold) ምንድነው?

አንዳንድ ሀገሮች እንዲህ ያለውን የፓርቲዎች ልቅ የመደራጀት መንገድ ለመዝጋት የተለያዩ ዘዴዎችን ይከተላሉ፡፡ ለዚህም ትልቁ መሳሪያ ፓርቲዎች በምርጫ ህዝብ የሚሰጣቸውን ድምፅ መሰረት ያደረገ መነሻ ወለል (electoral threshold) አስልተው በጥንካሬ መለኪያነት በመቶኛ ያስቀምጣሉ፡፡ የምጣኔው መቶኛ እንደየሀገሩ የተለያየ ሲሆን የብዙዎቹ ሀገሮች ከ1 – 10 በመቶ ባለው ውስጥ ነው፡፡

አንዳንድ ምሳሌዎችን እንይ፡፡ በፖላንድ፣ በጀርመንና በኒዊዚላንድ የፕርላማ መቀመጫ ለማግኘት ከመራጩ ህዝብ 5% መነሻ ድምፅ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ በቱርክ 10% ሲሆን በስሎቬኒያ ቀደም 4% ነው፡፡ በኖርዌይ 4% ሲሆን፣ በመላ ሀገሪቱ 12% ድምፅ ያገኘ ፓርቲ በምርጫ ክልል (ወረዳ) ደረጃ ባለ ምክር ቤት መቀመጫ ተካፋይ ይሆናል፡፡ ከአፍሪካ ሩዋንዳና ሞዛምቢክ 5% መነሻ አስቀምጠዋል፡፡

ይህንን ሁኔታ ለማስረዳት የእስራኤልን ሁኔታ ላቅርበው፡፡ የእስራኤል ፓርላማ (ኬነስት) 120 መቀመጫዎች አሉት፡፡ በእስራኤል የምርጫ ወረዳ የሚባል ነገር የለም፡፡ መላ ሀገሪቱ እንደ አንድ የምርጫ ክልል ነው የምትታየው፡፡ እናም ሁሉም ዜጋ ለሚፈልገው ፓርቲ ድምፁን ይሰጣል፡፡ በእስራኤል መነሻ ድምፅ (electoral threshold) 3.25% ነው፡፡ በዚህም መሰረት (በንድፈ ሃሳብ ደረጃ) አንድ ፓርቲ ከመራጩ ህዝብ የአስር በመቶውን (10%) ድምፅ ካገኘ ከመቶ ሃያው መቀመጫ አስራ ሁለቱን ይዛል፡፡ ይሁን እንጂ ሌላ ሊታለፍ የሚገባው መሰናክል አለ፡፡ ይኸውም አንድ ፓርቲ ከአጠቃላዩ መራጭ ከ3.25% ድምፅ በታች ካገኘ በፓርላማ አንድም መቀመጫ አይሰጠውም፡፡ ከመራጩ ህዝብ ከ3.5% ድምፅ ካገኘ ግን አራት መቀመጫ ያገኛል፡፡ እንዲህ ያለው አሰራር ብዙዎቹን ፓርቲዎች የፓርላማ መቀመጫ ስለማያስገኝላቸው በቀጣይ ምርጫ ወይ ከሌላ ፓርቲ ጋር ይዋሃዳሉ ወይ ህዝቡ ሙሉ ለሙሉ ድምፁን ይነፍጋቸውና ይከስማሉ፡፡

በእኛም ሀገር እንዲህ ያለ ገደብና አሰራር ቢኖር በፓርቲዎች መካከል ያለውን የመወያየትና የመደራደር የፖለቲካ ባህልን ያዳብረዋል፡፡ የመቻቻል መንገድን ያጠናክራል፡፡ የፖለቲካ አጀንዳን በቅደም ተከተል የመፍታት አሰራርን ያዳብራል፡፡ ካለበለዚያ የድርድር ፖለቲካ ልምድ የሌለን በመሆኑ ለፓርቲዎች መከፋፈልና ተመሳሳይ ርእዮተ ዓለም የሚያራምዱ ፓርቲዎች በየጊዜው እንዲቀፈቀፉ ምክንያት ይሆናል፡፡

በግርጌ ማስታወሻ መልክ አንድ ጉዳይ አንስቼ ልሰናበት፡፡ የፓርቲዎች ዋነኛና ተቀዳሚ ተግባር በየደረጃው የሚያገለግሉ የሀገር መሪዎችን ማፍራት ነው፡፡ በመሆኑም ሰሞኑን ፓርቲዎች የጀመሩት በርእዮተ ዓለም አቅጣጫ የመሰባሰብ ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ፓርቲዎች ጠንካራ ተቋም ሆነው ሲደራጁ ጠንካራ፣ ራዕይ ያላቸው መሪዎችን ማፍራት ይችላሉ፡፡

በኔ እይታ በዚህ ወቅት ያልተመለሰ የብሔር ጥያቄ የለም፡፡ አለ ከተባለም ሀገሪቱ ባላት ህገ መንግስት መሰረት እልባት ማግኘት ይችላል ብየ አስባለሁ፡፡ በመሆኑም በዘመነ ግሎባላይዜሽን በዘር መደራጀት አስፈላጊ አይደለም፡፡ በዘር መደራጀት የዴሞክራሲ ምንጭ ሊሆን ስለማይችል እንዲያውም በህግ መታገድ አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዘር የተደራጁ ፓርቲዎች ለብጥብጥና ለሁከት ምክንያት ከመሆን ውጪ ሀገርና ህዝብ ለመምራት አይመጥኑም፡፡ እንደኔ እንደኔ በዘር የተደራጁ ፓርቲዎች እጣ ፋንታቸው አክቲቪስት መሆን ነው፡፡ ፈርሰው ሀብታቸውን ከሚበትኑ ወደዚያ ቢሸጋገሩ መልካም ነው፡፡ ዴሞክራሲያችን ስር እስኪይዝ ድረስ ከብሔራቸው ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችልን ችግርም በአክቲቪስትነት ጠንክረው በመስራት ሊመክቱት ይችላሉ ብየ አስባለሁ፡፡

   ጸሐፊውን በEmail: ahayder2000@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡