Category Archives: opinion/ ምልከታ

ይህ ገጽ ሙሉ በሙሉ ነጻና የአዘጋጁን አቁዋም የማያንጸባርቅ ነው።

ሚሊዮን ማቴዎስ ለህግ ይቅረብ ! ወይም እብዱ ኢሌን ፍቱ !

ዛሬ በሀዋሳና በታወቁ የሲዳማ የወረዳ ከተሞች የሆነው ነገር እጅግ አሳፋሪ ነው። የትኛውንም ያህል እንከን ይኑረው ህግና ስርአት ባለበት ሀገር የክልል ምስረታ በወጣት ሚሊሻዎች ሲታወጅ ይህንንም ለማስፈጸም የሲዳማ ፓለቲካ ሀይሎች በቅንጅት ሲሰሩ ህገወጥነት ሲሰፍን ታዝበናል ።

የሲዳማን ጥያቄ አስቂኝ የሚያደርገው ትዕግስት ያጡበት ምክንያት ባዶነት ነው። ሲዳማ ውስጥ ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት በተለይም ባለፈው አንድ አመት ፍጹም አፓርታይድ የሰፈነበት የሌሎች ብሄር ኢትዮጵያውያን የዜግነት ክብራቸው የተዋረደበት ሁኔታ ነው ያለው። ሲዳማዎች አሁን ባለው ሁኔታ እንኳን ራሳችንን እያስተዳደርን አይደለም የሚሉበት ብጣቂ ማስረጃ የላቸውም። የሲዳማ ዞን ከቀበሌ እስከ ዞን ድረስ 100 % በሲዳማዎች የተሞላ ነው። በአካባቢው ለዘመናት የኖሩ የሌላ ብሄር አባላት በየትኛውም የዞኑ ጉዳይ ድምጽ የላቸውም። ባለፈው አንድ አመት ኤጄቶ የሚባለው ሀይል ያልፈቀደው ሰው አይሾምም ፣ የደቡብ ክልል መንግስት እንኳን በሀዋሳ ከተማ ስብሰባ ማድረግ ተስኖታል ከዚያም ባለፈ ፓሊስ ጣቢያዎች ሳይቀሩ በኤጄቶ ሲመሩ ቆይተዋል።

67252330_10219560171135405_6131341440271253504_n

በዛሬው ቀውስ ህይወት ጠፍቷል ፣ ንብረት ወድሟል ከሁሉም ከሁሉም ዜጎች በብሄር እየተለዩ ሲሳደዱ ውለዋል ንብረቶቻቸው ተዘርፈዋል። ከመሸ እንደምንሰማው የሲዳማ ሚዲያ ኔትወርክ የቦርድ አባል አቶ በላይ በልጉዳን (Belay Belguda) አይነቱ የዚህ ሽብር አስተባባሪዎች ታስረዋል። መንግስት እንደ እነ ሚሊዮን ማቴዎስ አይነቱን አውራዎች በህግ ቁጥጥር ካላዋለ የሲዳማው ሰደድ ነገ ወደ ወላይታ ፣ ሸካ ፣ ጉራጌና ስልጤ እያለ በክልሉ በሚገኙት ሃምሳ ምናምን ብሄሮች መዛመቱ አይቀርም።

ሚሊዮንን ማሰር ካልቻላችሁ አብዲ ኢሊን ፍቱት – ጥፋታቸው አንድ ነውና !

by – Samson Michailovich

ለማን ብየ ላልቅስ? — አክሎግ ቢራራ (ዶ/ር)

አክሎግ ቢራራ (ዶ/ር)

“የገደለው ባልሽ፤ የሞተው ወንድምሽ!”
“ሃዘንሽ ቅጥ አጣ ምን ብየ ላላቅስሽ!”

“እኔ ለዐማራው ሕዝብ ህይወቴን ሰጥቻለሁ” ዶር አምባቸው መኮነን

የእኛ አገር ጉዳይ ቅጥ ያጣ ሆኗል። ወንድም ወንድሙን እንዲገድል ከጀርባ ሆኖ የሚቀሰቅሰው ማነው? የሚለውን ጥያቄ ለተመራማሪዎች ልተወው። የክልሉና የፌድራሉ ባለሥልጣናት ማን ገዳይ እና ማን ተገዳይ እንደሆነ ነግረውናል። ቁም ነገሩ፤ እነማን ናቸው ወይንም ከየትኛው ዘውግ ወይንም ጎጥ ናቸው አይደለም። ግድያውን በጎጥ መፈተሹ ራሱ አሳፋሪ ነው። ጎጣዊነትን ተጠቅሞ እርስ በርስ መወነጃጀሉ የሞቱትን ብቻ ሳይሆን የዐማራውንና የመላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ዝቅ አድርጎታል።

በአገር ወዳድነቱ ምንም እንከን የሌለው የዐማራው ሕዝብ ከሁሉም በላይ ለአገሩ ክብር፤ ነጻነትና ሉዐላዊነት መስዋእት ሲሆን ቆይቷል። ለጥቁር ሕዝቦች ያደረገውን አስተዋፆ ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ጥቁርና ነጭ ጽሃፊዎች መዝግበውታል፤ አድንቀውታል። በዚሁ አስደናቂ ታሪክ ልክ ግን፤ ይህን ከሁሉም ዘውጎች ጋር ተዋልዶና ተከባብሮ የሚኖር ሕዝብ በጠላትነት የሚያወግዙትና የሚያሳድዱት የውጭና የውስጥ ጠላቶቹ ብዙ ናቸው።

የተቀነባበረና ያልተቋረጠ ሴራ

ይህ ትንተና ስለ ዐማራ ታሪክና ስለ ከፈለው ዋጋ አይደለም። ግን፤ አንባቢ እንዲያጤነው የምፈልግው አስኳል ጉዳይ፤ በዐማራው ሕዝብ ላይ የሚካሄደው ግፍና በደል ዛሬ አለመጀመሩን ለመጠቆም ነው። የአውስትርያው ተወላጅና ዘረኛ ፕሮቻካ ሮማን (Prochaka Roman) the Abyssinia Powder Barrel, 1927 በጻፈው መጽሃፉ ላይ እንዳስቀመጠው የዐማራው ሕዝብ ራሱን ከፈረንጆች በታች አድርጎ የማይቀበል፤ በነጻነቱና በሉዐላዊነቱ የማይደራደር መሆኑን አስምሮበታል። ሆኖም፤ ፋሺስቶችና ናዚዝቶች፤ አስካሪዎችና ከሃዲዎች ይህን ሕዝብ እንደ ጠላት እንዲኮንኑትና እንዲጠፋ፤ ባይጠፋም እንዲሸማቀቅ አድርገው ያልተቆጠበ ፕሮፓጋንዳና ጦርነት አካሂደውበታል።

የኢትዮጵያ የውጭና የውስጥ ጠላቶች የዐማራውን ሕዝብ የሚጠሉበትና እንዲጠፋ የሚመኙት ለምንድን ነው? የዐማራው ሕዝብ የነጻነት፤ የአትንኩኝ ባይነት፤ የነጭ ሆነ የቢጫ ሕዝብ የጥቁር ሕዝብ የበላይ ዓይደለም፤ ሆኖም አያውቅም፤ እኔ ለቅኝ ገዢዎች አልንበረከክም ባይነት በነጮች በኩል ተቀባይነት አግኝቶ አያውቅም። ይህን አመለካከት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የናደው በአጼ ምኒልክ የተመራው የአድዋ ድል ነው። የአድዋ ድል ግን በተናጠል መታየት የለበትም። ኢትዮጵያ የራሷ ፊደል፤ የራሷ የቀን መቁጠሪያ፤ የራሷ የመንግሥት ስርዓት ያላት አገር መሆኑና ጭንቀት እንደፈጠረ ማጤን ያስፈልጋል።

ይህ ታላቅነት ያልተዋጠለት ሙሶሊኒና ተባባሪ የነበሩት የአገር ውስጥ ከሃዲዎችና አስካሪዎች ኢትዮጵያ እንደ ገና እንድትወረር አድርገዋል። ይህ የመጨረሽ የውጭ ወረራ ግን አገሪቱ የጣሊያን አካል እንድትሆን አላደረጋትም። የሃበሻ ጀብዱ የተባለው አስደናቂ መጽሃፍ እንደሚያሳየው ለአምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ጀግኖች በዱር በገደሉ ጣሊያኖችን ተዋግተዋል፤ ጣሊያንን አሸንፈዋል።

ሆኖም፤ አሁንም ቢሆን ፋሽስቶችና ናዚዝቶች ተክለውት የሄዱት የዘውግ ጥላቻና የከፈፍለህ ግዛው ስልትና ስሌት መፍትሄ አላገኘም። ኢትዮጵያ ታላቅ አገር እንዳትሆን የሚፈልጉ የውጭና የውስጥ ኃይሎች ዋና መሳሪያ አድርገው የሚጠቀሙበት የዘውግና የኃይማኖት ልዩነት ፖለቲካን ነው። የዘውግ ፖለቲካን በዜግነት ፖለቲካ መቀየር የአገር ህልውና ጥያቄ ነው።

ግድያው አሳፍሮኛል። ያሳፈረኝና ያስፈራኝ ምን ጨካኝና አረመኔ ግለሰብ ወይንም ቡድን ነው ይህን ወንጀል የፈጸመው የሚለው ነው። ግለሰቡ ወይንም ቡድኑ ግደል እንኳን ቢባል፤ ወገኖቸን ብቻ ሳይሆን፤ አንድን ግለሰብ ያለ ምንምም ምክንያት፤ ሳይተኩስብኝ ሌላው ቀርቶ ድንጋይ ሳይወረውርብኝ አልገልም ሊል ይችል ነበር። ይህን የሚያደርግው ግን ለህሊናው የሚገዛ፤ ወንድሙን ኢትዮጵያዊውን የሚወድ፤ ለሕብረተሰቡና ለሃገሩ የሚቆረቆር፤ በገንዘብ ሆነ በሥልጣን ህሊናውን የማይሸጥ ሰው ነው። ወንድም ወንድሙን ሲገድል ተሸናፊ እንጅ አሸናፊ የለም። ተጠቂ እንጅ አጥቂ የለም። ፈሪ እንጅ ጀግና አይኖርም። ጥቂቶችም ብንሆን፤ ተማርን የምንለው በስደት የምንኖር ኢትዮጵያዊያን ነጻነታችን እየተጠቀምን፤ ሃላፊነት የጎደለው የቃላት ጦርነት እያካሄድን ነው። ተጠቂውና ዋጋ ከፋዩ የዐማራው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና እናፈቅራታለን የምንላት ኢትዮጵያ ናት። ለአንድ ሰኮንድም ቢሆን፤ አእምሯችን ሰብሰብ አድርገን ለህሊናችን እንገዛ። ህወሓታዊ የጭካኔና ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያናክስ ስራ መስራትን እናቁም።

በቅንነቱ፤ በትሁትነቱና በአገር ውዳድነቱ የሚታወቀው ወንድማችን ዶር አምባቸው መኮነና ጓዶቹ ያለ ጊዜያቸው አልፈዋል። ኤታ ማጆር ሹሙ ጀኔራል ሰዓረ መኮነን መተኪያ  የሌለው የጦር መሪ፤ አስተማሪ፤ ከማንኛውም በላይ አገሩን አፍቃሪ፤ ጠባብ ብሄርተኝነትን ተቃዋሚ፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አስቀዳሚ አጥተናል። እነዚህ ጀግኖች የሚታወቁት ዐማራ ወይንም ትግሬ ወይንም ድብልቅ በመሆናቸው አይደለም። በኢትዮጵያዊነታቸው ነው። ከእልፈታቸው በኋላ “የኔ ነው! የኔ ነው! የዚያ ነው! የዚህ ነው! እያልን ዝቅ የምናደርጋቸው እኛው ነን። ‘የኔና የአንተ’ የሚለውን የህወሓቶችን ፈለግ ተከትለን። እየተፈራረቁ መግዛትና መብላት ለኢትዮጵያ አሳፋሪ ነው። ህወሓት ለሃያ ስምንት አመታት በልቷል! ዛሬ ደግሞ የኔ ፋንታ ነው! የሚሉትን የኦነጎችንና መሰሎቻቸውን ብሂል እየተከተልን ሁኔታዎችን ማባባሱ መቆም አለበት።

ሴራና ድንገተኛ አደጋ የተለያዩ ናቸው

በእኔ ግንዛቤና ዘገባ፤ ግድያውና “መፈንቅለ መንግሥቱ” በደንብ ታስቦበት፤ ብዙ ወጭ ተደርጎበት የዐማራው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ተተኪ መሪዎች እንዳይኖሯት፤ ለውጡ እንዳይሳካ የተደረገ ሴራ ነው። ሴራው እንዳይታወቅ ከተፈለገ ወንድም ወንድሙን እንዲገድልና እርስ በእርሳችን እንድንወነጃጀል ማድረግ ስልት ነው። የስድሳ ስድስቱን “አብዮት” ጭካኔ ብቻ ዞር ብሎ መገምገም ይጠቅማል።

እኔን እጅግ የሚያሳስበኝ፤ የሞቱትን አገር ወዳዶችና ጀግኖች ቀብረን ገና ሃዘናችን ሳንጨርስና ከሞታቸው ምን እንማራለን ብለን ሳንመራመር፤ የመሳፍንት ዘመን መሰል ቲያትር እያካሄድን ነው። ጎንደሬውና ጎጃሜው የእርስ በርስ ጦርነት እያካሄደ ነው። ወሎየውና ጎንደሬው እርስ በርሱ እየተወነጃጀለ ነው። የሸዋውና የሌላው ዐማራ እነዚህ “እብዶች እርስ በርሳቸው መናከስ ልምዳቸው ነው” የሚል መሃል ሰፋሪ ይመስላል። የሲዳሞ ወገኖቻችን የራሳችን ክልል ያስፈልገናል እያሉ ያስፈራራሉ። የክልል ድንበሩ የት ላይ ነው? ይህ አመለካከት አፍራሽ ነው።

ጀኔራል ሰዐረ መኮነን ነፍሳቸውን ይማርና ልንመራበት የሚገባን ትምህርት ለግሰውን አልፈዋል፡ “ጠላቶቻችን የሚጠቀሙብን በክልል ማሰብ ስንጀምር ነው።” ጎጠኝነት ደግሞ የሞት ሞት ነው። ዛሬ እኛ ኢትዮጵያዊያን ቀን ከሌት መስራት ያለብን ኢትዮጵያን ከመፈራረስ ማዳን ነው። ይህን ለማድረግ የምንችለው ደግሞ ከዘውግ በላይ “መንፈስና ሱስ ነው” ተብሎ በሚታወቀው በኢትዮጵያዊነት ስንሰበሰብና ስንተባበር ነው።

በግድያውን ማን ተጠቃሚ፤ ማን ተጠቂ ሆነ?

ግድያውንና “መፈንቅለ መንግሥት” ተብሎ የሚጠራውን ክስተት በተመለከተ አጥጋቢ የሆነ መረጃ የለም። ሁሉም እንደፈለገው ከባርኔጣ “ሃቅ ነው” ብሎ የሚያስበውን በመገናኛ ብዙሃን እያሰራጨ ሕዝቡ እርስ በእርሱ እንዲጠራረር በክሎታል። የዚህ ዋና ተጠቃሚ ኃይሎች በአገር ውስጥ ህወሓት፤ ኦንነግ፤ የብሄር ጽንፈኞችና የተወሰኑ ነጋዴዎች ናቸው የሚለውን እጋራለሁ። በውጭ ግብጾችና ሌሎች በኢትዮጵያ ላይ እቅድ ያላቸው መንግሥታትና ኢንቬስተሮች ናቸው። የተቀነባበረውን የሳይበር ጦርነት የሚያካሂደው ቡድን ህወሓት ነው። ህወሓት የዘረጋ እረጂም ክንድ፤ የካድሬዎች ሰንሰለትና መዋቅር ገና አልፈረሰም።

ስለዚህ፤ የትግላችንና የጉዟችን ኢላማው የዐብይ መንግሥት ሊሆን አይችልም። የአፈጻጸም ድክመቶች ያሉት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የዐብይ ቡድን የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነትጠበቃና ተከላካይ ነው። ኢላማው የህወሓት ሰንሰለትና መዋቅር እንዲፈርስ ማድረግ ነው። በተመሳሳይ፤ ኦነግና መሰል ድርጅቶች የህወሓትን መስመር ተከትለው ሊያደርጉ የሚሞክሩት ግፍ፤ በደልና ዘረፋ እንዲቆም መተባበር ነው። በተጨማሪ፤ ጃዋር ሞሃመድ መለስን ተክቶ ሕዝብ ከሕዝብ፤ ኃይማኖት ከኃይማኖት ጋር እንዲጋጭ እየታገለና እየሰበከ ነው።

ጃዋር አደገኛና አገር አፍራሽ መሆኑን የሚያመለክቱ ብዙ መረጃዎች አሉ።

 • በማያገባው ጣልቃ ገብቶ የዐማራው ሕዝብ እርስ በእርሱ እንዲናከስ ካደረጉት ሰዎች መካከል አንዱ እሱ ነው። ለምሳሌ፤ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አድርጎ ራሱን በመሾም የዐማራውና የቅማንቱ ወንድማማች ሕዝብ እንዲናከስ ቅስቀሳ አድርጓል። የወሎን ክፍለ ሃገር የኦሮምያ አካል ነው ብሎ ተናግሯል። ይህ ሴራ፤ የዐማራው ህዝብ ጎንደሬ፤ ወሎየ፤ ጎጃሜ፤ ሸየ ወዘተ በሚል መለያ ተለያይቶ መንደር የሚያክሉ፤ አቅም የማይኖራቸው ለተስፋፊነት የሚበጁ “ንኡስ ክልሎችን” ለመፍጠር ነው። በዐማራው መቃብር ላይ ታላቅ ሌላ አገር ለመመስረት የሚደረግ ሴራ ነው።
 • ይህ ግለሰብ የራሱን መንግሥት እንደመሰረተ ሆኖ ይሰብካል፤ ይንቀሳቀሳል። እድል በሚሰጠው በማንኛውም ሜድያ እየገባና በፖለቲካ ምህዳሩ ቤንዚን እየረጨ፤ ጎራዴ ምዘዙእያለ፤ ኢትዮጵያ የእርስ በእርስ የደም ምድር እንድትሆን ይናገራል፤ ይቀሰቅሳል። ከተቻለ “በሕገ-መንግሥቱ፤ አለያ በኃይል” የሚል የብሄር ጽንፈኛ፤ የኃይማኖት አክራሪ ከብሄርተኛውና ከዘረኛው ከህወሓት በምን ይለያል?
 • ጃዋርን የቅማንት ሆነ የወሎ ሕዝብ፤ የሲዳማ ሆነ የአዲስ አበባ ሕዝብ ጠበቃ አድርጎ የሾመው ማነው? ይህ ግለሰብ በሃላፊነት መጠየቅ አለበት።
 • ጃዋር ከኸርማን ኮህን ጋር ይመሳሰላል። ሁለቱም የዐማራውን ሕዝብ አውግዘው፤ ዐማራው ለ500 ዓመታት ገዝቷል የሚል ከእውነቱ የራቀ ዘገባ እያቀረቡ ዐማራው ለባሰ አደጋ እንዲጋለጥ እያደረጉት ነው።
 • በቅርቡ ስለ ሲዳሞ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ ሲናገር፤ ጃዋር በቀጥታ ኢላማ ያደረገው የዐብይን ፌደራል መንግሥትና አስተዳደር ነው። ይህ አቋም ከኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶችና ከህወሓት ሴራ በምኑ ይለያል?

ግድያውና “መፈንቅለ መንግሥቱ” ምን ፋይዳ አለው? ህወሓቶች፤ የተወሰኑ የዘውግ ልሂቃኖች፤ ጃዋር መሰሎችና የኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች የሚከተሉትን ስኬታማ አድርገዋል። ይህ የአጭር ጊዜ ድል ግን የከስራል።

 1. የማህበረሰባዊ ሜድያና የሳይበር ስፔስ ጦርነቱ በዐማራው ሕዝብ ላይ ያተኮረ ሆኖ፤ የእርስ በእርሱ ጦርነት በጎጠኝነት ዙሪያ እንዲካሄድ መደረጉና ዋናው ችግር እንዳይፈታ መሰናክል መሆኑ፤
 2. ይህ በዐማራው ክልል መንግሥት ዙሪያ ያለው የእርስ በእርስ ሹክቻና የሥልጣን ግብግብ ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን ለመላዋ ኢትዮጵያ የጸጥታና የአገር ህልውና ተግዳሮቶች ግብዓት መስጠቱ፤
 3. በአማራው ወጣት ትውልድ ድርጅቶች ለምሳሌ በአብን፤ በፋኖና በሌሎች እንቅስቃሴዎችና በዐማራው ዲሞክራቲክ ፓርቲ መካከክል ያለው ግንኙነት አሁንም ጤናማነትና ተደጋጋፊነት አለማሳየቱ፤
 4. ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ አሕመድ ስልጣን ከያዙበት ወቅት በኋላ በተከታታይ በሁሉም የዐማራ ክልል ከተማዎችና የትምህርት ተቋማት ለዐብይ ለውጥ ይደረግ የነበረው የማያሻማ ድጋፍ ወደ ጥርጣሬና ትችት መሸጋገሩና የዚህ ሂደት ዋና ተጠቃሚ ህወሓት መሆኑ፤
 5. የዐማራው ክልል አመራር የዐማራውን ሕዝብ “ዘላቂ ጥቅምና የህልውናውን ጥያቄ ዋና መርህ አድርጎ በማስተጋባት ፋንታ የዐብይ ደጋፊ ሆኗል” የሚለው በመረጃ ያልተደገፈ ብሂል መዛመቱ፤
 6. ለዚህ ክስ ግብዓት የሆኑት የቡራዩ ግድያ፤ የሰሜን ሸው ወረራ፤ የለገጣፎ ዜጎች መፈናቀል፤ የቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ የዐማራ ሕዝብ ግድያ፤ በራያን አዜቦ ቢያንስ የ 2,000 ዐማራ ወጣቶች በህወሓት ታፍነው ትግራይ ተወስደው መታሰራቸው ጉዳይ አለመፈታት፤ የወልቃይት ጠገዴ፤ የራያና አዜቦ፤ የመተከል ጉዳዮች ምንም አይነት መፍትሄ ያለማግኘታቸው ጉዳይ፤ በአዲስ አበባ የተቋቋመው “የባለአደራ ም/ቤት” አቋም በአግባብ ያለመታየቱና “ወገንተኛነትና አድልዎ ያሳያል” የሚለው ጥርጣሬ፤ በመቀሌ መሽጎ የሚገኘው “ለወንጀለኞች” ምሽግ ሆኗል የሚለው አመለካክት ምንም አይነት መፍትሄ አለማግኘቱ፤ የኦሮሞ ልሂቃንና ጃዋር “ወሎ የኦሮምያ አካል ነው” ማለታቸው፤ ልዩ ልዩ ክሎሎች የተለያዩ የፌደራል መንግሥት አስተዳደርና ውሳኔ ያሳያሉ የሚለው ዘገባ መኖሩ፤
 7. ጎንደሬው “የኦሮሞ ደም ደማችን ነው” ብሎ በአማራው ክልል ያካሄደው ትግል ተዛምቶ ለለውጡ ፋና ወጊ መሆኑ እየታወቀ ይህን ቀስቃሽ አስተዋፆ የማኮላሸት ፕሮፓጋንዳ መካሄዱ፤ ለውጡ ሕዝባዊ መሆኑ በተቋማትና በአመራር ገና ስር አለመስደዱ፤ ኢትዮጵያዊ መዋቅር አለመያዙ፤
 8. በግድያውና “በመፈንቅለ መንግሥቱ” ሰበብ የአብንና የባለአደራው ም/ቤት አባላት “በሽብርተኛነት” መከሰሳቸውና ይህ ሂደት ህወሓት መራሹ አገዛዝ በኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ የበላይነት ተተክቷል የሚል ክስና ወቀሳ ማስከተሉ፤
 9. ጠ/ሚንስትሩ ሚዛናዊ አቋም አይወስዱም የሚለው አመለካከት መዛመቱ፤ ለምስሌ፤ ጃዋር የሚናገረውና የሚሰራው ጽንፈኝነትና አክራሪነት ትኩረት ሳይሰጠው በጋዜጠኛ እስክንድር ላይ ግን ትችት መሰንዘሩ፤
 10. ጠ/ሚንስትሩ የሚታወቁበትና የሚለዩበት የሰብአዊ መብቶችና የመገናኛ ብዙሃን መብትና ነጻነት መከበር ጉዳይ “እየተናደ ነው” የሚለው ብሂል የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡና በመታገቡ ጥርጣሬ መከሰቱ፤
 11. ጸረ-ኢህአዴግነትና አማራጮችን ማቅረብ ለፌደራሉ መንግሥት ተግዳሮት መሆናቸው፤
 12. በዘውጋዊ አድልዎ የምትታወቀው ኢትዮጵያ ህወሓት መራሹ ቡድን ከስልጣን ከወረደ በኋላ በልዩ ልዩ ተቋማት በሞያ ብቃትነት (Competency and merit) ሳይሆን በዘውግና በታማኝነት ብቻ የፌደራል ስልጣን እየተሰጠ ነው የሚለው ብሂል መዛመቱ፤
 13. አሁንም ቢሆን እንደ ቀድሞው ህወሓት መራሹ ስርዓት፤ የዐማራው ሕዝብ “ጨቋኝ፤ ቀመኛ፤ ነፍጠኛ፤ ቅኝ ገዢ” ወዘተ በሚል ፕሮፓጋንዳና ለፈፋ እንዲጋለጥ እየተደረገ ነው የሚለው ሰፊ አመለካከት መኖሩ፤ ህወሓትና ኦነግ ይህን አመለካከት አለም አቀፍ በሆነ ትብብር ማስተጋባታቸውን መቀጠላቸው፤
 14. በኦሮምያና በሌሎች አካባቢዎች የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሃያ የሚደርሱ የባንክ ቅርንጫቾችን ዘርፈው ዘራፊዎቹ በሃላፊነት ለሕግ አለመቅረባቸው የሕግ የበላይነት የሚለው አስፈላጊ መርህ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ አይስተናገድም የሚለው ብሂል በሶሻል ሜዱያ መሰራጨቱና መፍትሄ አለማግኘቱ፤
 15. ህወሓትና ሌሎች ኃይሎች ስልኮችን እየጠለፉ በኢንተርኔትና በሌሎች መገናኛ ዘዴዎችበዐማራው ክልል አመራርና በተራው ሕዝብ ላይ፤ በዐብይ የለውጥ አመራር ብቃት ላይ የሃሰት ፕሮፓጋንዳ በየአካባቢው ሲያዛምቱ ይህን የሳይበር ጦርነት የፌደራሉ መንግሥትና “ተፎካካሪ” ነን የሚሉት ልሂቃንና ምሁራን ለመቋቋም አለመቻላቸው ሁኔታውን ማባባሱ፤
 16. የዐማራው ሕዝብ “ታሪካዊ ጠላታችን” ነው የሚሉ ኃይሎች መገናኛ ብዙሃን እየተጠቀሙ፤ እንደ ኸርማን ኮህን ካሉ ለኢትዮጵያ መፈራረስ ከፍተኛ አስተዋጾ ካደረጉ ግለሰቦችና ቡድኖች ጋር ቁርኝት በመፍጠር ይህ አገር ወዳድ ሕዝብ ራሱን ቀና አድርጎ ለራሱ ህልውና፤ ለአገሩ ግዛታዊ አንድነትና ሉዐላዊነት ወሳኝ ሚና እንዳያይጫወት የፕሮፓጋንዳ ጦርነት መጀመሩ፤
 17. በዐማራውና በኦሮሞው ሕዝብ መካከል የተፈጠረው ጠንካራ ግንኙነት በፈጠራ ወሬ እንዲኮላሽ ለማድረግ የኃይማኖትና የመሬት ይገባኛልነት (ወሎ ምሳሌ ነው) መስመሩን እንዲስት መደረጉ፤
 18. አንዳንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፤ ምሁራንና ሌሎች በኢትዮጵያ አማራጭ የለም፤ ያለውን አመራር ብቻ መደገፍ አስፈላጊ ነው እያሉ የሚናገሩት ሕብረተሰቡን የሚከፋፍል እመለካከት መዛመቱ። ይህ አመለካከት የኢትዮጵያን 110 ሚሊየን ሕዝብ መናቅ ከመሆኑም ባሻገር፤ ኢትዮጵያ ያላትን የተማረ ሰው እንዳትጠቀም ማድረጉ፤ አማራጭ መስጠት አሁንም እንደ ጠላትነት መቆጠሩ፤
 19. በተለይ በዘውግ ሳይሆን በዜጎች መብት ላይ የተመሰረተ የህገ መንግሥትና ሌላ የፖሊሲ አማራጭ ለመስጠት አለመድፈራችን ሁኔታውን ማባባሱ፤ እና፤
 20. ውይይቱ፤ ክርክሩና ድርድሩ የኦሮሞን፤ የዐማራንና የትግራይን ሕዝብ ብቻ እንደሚመለከት ሆኖ መቅረቡ ይገኙበታል። ይህ አመለካከት ሁሉን አቀፍ ሊሆን አይችልም። ኢትዮጵያዊነት እንዲጠነክር ከተፈለገ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ተሳታፊና ባለቤት መሆን አለባቸው።

ይህን አመልካች ስእል ለማጠቃለል፤ በኢትዮጵያ የሚካሄደውን አስፈላጊ ሰላማዊና ዲሞክራሳዊ ለውጥ ለማብረድ ሳይሆን ፈጽሞ ለማጥፋት የሚታገሉ፤ የውጭ ድጋፍ የሚሰጣቸው የተባበሩ ኃይሎች እንዳሉ ይታያል። ምንም እንኳን አስተማማኝ መረጃዎች ለማግኘት ባልችልም፤ ስህተቶችም አሉ የሚለውን ብቀበልም፤ ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ የሚመራው ለውጥ ስኬታማ እንዲሆን ከመተባበር ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም። ግድፈቶችን ጨዋነት ባለው መልኩና አማራጮችን በመጠቆም እያስተጋባን ሕዝብ ከሕዝብ ጋር እንዳይጋጭ ማድረግ ታሪካዊ ግዴታችን ነው። በለይ ኢትዮጵያን ከመፈራረስ ለማዳን ያልተቆጠበ ጥረት ካላደረግን ይህችን ታሪካዊ አገር ልናጣት እንችላለን።

በዐማራው ክልል፤ በባህር ዳር የተካሄደው ጭካኔን የሚያሳይ ግድያ የጠላቶች ሴራ እንጅ የወንድማማቾች ሴራ ሊሆን የሚችልበት ምንም መስፈርት ላገኝ አልቻልኩም። ግን፤ ግድያው ወደ አሳፋሪ ደረጃ እየተሸጋገረ ነው። ይህ የጎጠኞችና የቀን ጅቦች የሚመስል የጥቅም ጦርነት ወደ ጎጥ ዝቅ ያለ መወነጃጀል ቀስ በቀስ ወደ ሩዋንዳ መሰል፤ ወደ ሶሪያ መሰል፤ ወደ የመን መሰል፤ ወደ ሶማሊያ መሰልና ወደ ሱዳን መሰል አደገኛ እልቂት (Genocide) እና ኢትዮጵያን ወደማትመለስበት መፈራረስ (Balkanization) እንድታመራ እያደረገ ነው።

እኔ አገሬን ካየኋት፤ በተለይ የጎንደርን አካባቢ ሕብረተሰብ በቀጥታና በአካል ባየሁት ሁኔታ መስፈርት ከገመገምኩት ከአርባ ሁለት ዓመት በላይ ሆኗል። የማውቀውና የማስታውሰው የዐማራው ሕዝብ እንኳንና የራሱን ወገን የማረከውንም ፈረንጅ ሰብእናና ህይዎት የሚያከብር፤ ኃይማኖቱና ባህሉ አእምሮውንና ስራውን እንዲያመዛዝን የሚያስገድድ ህብረተሰብ መሆኑ ነው ትዝ የሚለኝ። የዐማራ ወንድ አባቱን ወይንም ወንድሙን ወይንም ልጁን ወይንም ሚስቱን ገዳይ አይምርም። ንጹህ ደም ማፍሰስ ግን ነው ሲባል ነው የማስታውሰው።

የፈለገውን ያህል ብንጮሕና ብናለቅስ ኢትዮጵያ ያፈራቻቸውን፤ መተኪያ የማይገኝላቸውን ወንድሞቻችን የገደሉትን ግለሰቦች ከጀርባ ሆኖ ማን እንዳዘጋጃቸው አናውቅም። የኢትዮጵያ መንግሥት ልዩ ክትትል፤ ጥናትና ምርምር ይደረጋል ቢልም የምናምንበት መስፈርት የለንም። ከዚህ በፊት በጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ ላይ የተደረገው የግድያ ሙከራ ምን ላይ ደረሰ፤ ማነው ከጀርባ ሆኖ ያቀነባበረው፤ ማን በሃላፊነት ፍርድ ቤት ቀርቧል?

ታላቁ የተሃድሶ ግድብ ኢትዮጵያ ከጀመረቻቸው መሰረተልማቶች መካከል አንደኛውን ደረጃ የያዘ ነው። ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ግዙፍና መለያችን የሆነ ሃብት ነው። ይህን ወደ አምስት ቢሊየን ዶላር የሚፈጅ ግንባታ አቀናብሮ ይሰራ የነበረው ኢትዮጵያዊው መሃንዲስ ስመኘው በቀለ “ራሱን ገደለ” ተብሎ ሲነገር ለአገራችን መንግሥትና ሕዝብ አፈርኩ። ይህ መሃንዲስ ራሱን የሚገልበት ምክንያት የለም። ብዙ ቢሊየን ዶላር በሚሰረቅባት ኢትዮጵያ ሌቦችና ተባባሪዎች ቢገድሉት ሊታመን ይችላል። ቁም ነገሩ፤ ኢንጅኔር ስመኘው “ራሱን ገደለ” ከሚለው ውጭ የኢትዮጵያ መንግሥት ፋይዳ ያለው መግለጫ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አላቀረበም።

ህወሓቶች በድብቅ ተቃዋሚዎቻቸውንና ተፎካካሪዎች ናቸው ብለው የሚጠረጥሯቸውን ሁሉ፤ በተለይ ዐማራዎችን በስውር እንደሚገድሉ የአደባባይ ምስጢር ነው። በዚህ ስልት የሚጠቀሙ ሌሎችም ኃይሎች አሉ። ልዩ ልዩ የሚገድል መርዝና መድሃኒት በምግብና በመጠጥ እየጨመሩ የድብቅ ግፍ የሚሰሩ አሁንም አሉ። ጋዜጠኛውና አገር ወዳዱ አቶ ደምሴ በለጠ አገሩን ለማየት ሄዶ አዲስ አበባ “ባልታወቀ ምክንያት” ከዚህ ዐለም ተለይቷል። ይህን አገር ወዳድና ጀግና እኔም አውቀዋለሁ። ጤናማ ነበር። እንዴት እንደሞተና ማን እንደገደለው እስካሁን አይታወቅም። ስለዚህ፤ ምርመራ ቢካሄድም ሃቁን ለማወቅ አይቻልም ያልኩበት ምሳሌዎች ስላሉ ነው።

እኛ ልምዳችን ጀግኖቻችን የምናስታውሳቸው ካለፉ በኋላ መሆኑ ማቆም አለበት። ጀግኖቻችን በህይወት በነበሩበት ጊዜ ምን አይነት ድጋፍ ሰጠናቸው? የሚል ጥያቄ ብንጠይቅ ይጠቅማል።

ካለፉት መተኪያ ከሌላችው ኢትዮጵያዊያን መካከል የማውቀውና ለጥቂት ደቂቃዎች ያነጋገርኩት ዶር አምባቸው መኮነንን ብቻ ነው። ይህ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ “ህይወቴን ለአማራው ሕዝብ ሰጥቻለሁ” ብሎ ለቤተሰቡ ፍቅር ቅድሚያ ሳይሰጥ በለጋ እድሜው አልፏል። አቶ ገዱ እንዳስቀመጠው፤ “ከዚህ በላይ ሞት የለም። እውነትና ንጋት እያደር ይጣራል” እንዲሉ፤ ምን አልባት የዚህ አገር ወዳድና ጨዋ ኢትዮጵያዊ ገዳዮችም የሚታወቁበት ጊዜ ሊመጣ ይችል ይሆናል። ቁም ነገሩ ግን እሱና ጓዶቹ፤ እሱና ጀኔራል ሰዓረ መኮነን ለምን አላማ ቆመው ነበር የሚለው ነው።

 • ለፍትህ፤ ለእውነተኛ እኩልነት፤
 • ለሕግ የበላይነት፤
 • ለኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነትና ሉዐላዊነት ወዘተ የቆሙትን ነው ኢትዮጵያ ያጣችው።

እኔ ለዶር አምባቸው ባለውለታው ነኝ። ባላውቀው ይሻለኝ ነበር። ምክንያቱም፤ ትህትናው፤ ፈገግታው፤ አገር ወዳድነቱ፤ ጨዋነቱ፤ ለዐላማ ያለው ቆራጠኛነቱ ስለሳቡኝ ሌላ ጊዜ አገሬ ስመለስ በሰፊው አነጋግራለሁ ካልኳቸው ኢትዮጵያዊያን መካከል የመጀመሪያውን ደረጃ የያዘው እሱ ነበር። የሚያውቁት ሁሉ የሚሉት ተመሳሳይ ነው። ይህ ወንድማችን ለሰላምና ለአብሮነት የቆመ ግለሰብ ነበር። ይህን ባለውለታችን የሌለ ስም እየሰጠን ስንከሰው ያመኛል። መስዋእት ከሆነው ወንድማችን፤ ከጓዶቹና ከጀኔራል ሰዐረ መኮነን በመማር ፋንታ ራሳችን ዝቅ አድርገን መንደርተኛ ስንሆን ያማል፤ አጸያፊ ባህርይ ነው። ከኢትዮጵያዊነት መንፈስ ጋር አብሮ የማይሄድ ነው። ዛሬም እንደ ወትሮው ልዩነትን በመሳሪያና በግድያ እንፈታለን የሚል ግለስብና ቡድን እብድ ነው። እብድ ህክምና ያስፈልገዋል። ሆነ ብሎ ያበደን ደግም በማባበል፤ በመምከርና በህክምና ለማዳን አይቻልም። ለዚህ ነው በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ መንግሥት መሪዎች ቀይ መስመር መወሰን አለባቸው እያልኩ የምከራከረው።

ለማጠናከር፤ የሕግ የበላይነት ወሳኝ ከሆነ፤ በክልል ደረጃ ሆነ በፌደራል ኢትዮጵያ ቀይ መስመር እንዲኖራት ያስፈልጋል። በቃ! ከዚህ ባሻገር አንታገስም የሚል መስመር ማለቴ ነው። ዶር አምባቸውንና ጓዶቹን፤ ጀኔራል ሰዐረ መኮንን የገደሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው። ሁኔታውን የሚያባብሱና የፈጠራ ወሬ የሚያሰራጩ ግለሰቦችና ቡድኖች በየትኛውም ዓለም ይኑሩ የተሳሳተ ወሬ ማሰራጨት እንዲያቆሙ ለሚኖሩበት መንግሥት በመረጃ የተደገፈ ክትትል እንዲደረግባቸው ጫና ማድረግ ያስፈልጋል።

የዐማራው ሕዝብ በመንደር ደረጃ ዝቅ ብሎ ህወሓት መራሽ የሆነውን ጎንደሬ፤ ወሎየ፤ ጎጃሜ፤ ሃረሬና ሌላ መለያ እየያዘ የመከፋፈል ዘመቻውን በአስቸኳይ ማቆም አለበት። ይህ እርግማን ነው። አባቶቻችን ትተውልን ከሄዱት እሴት ጋር አይመጣጠንም።

መለያየቱና መወቃቀሱ፤ መካሰሱና መወነጃጀሉ፤ በአጭሩ መንደርተኛነቱ ምን ፋይዳ አለው? በእኔ እምነት፤ ብሄራዊ ሃዘናችንን ወደ ብሄራዊ ውርደት አሸጋግረነዋል። ይህ ውርደት የሚያስከትለው አደጋ ምንድን ነው? ብለን ራሳችን እንጠይቅ። ኢትዮጵያ ሩዋንዳን ብትሆን፤ ኢትዮጵያ ዩጎስላቭያን ብትሆን ማንም ተጠቃሚ እንደማይኖር አሳስባለሁ። የሞቱት ወንድሞቻችን ኢትዮጵያዊያን ናቸው። የተጎዳችውና የምትደማው ኢትዮጵያ ናት። ከጀርባ ሆኖ ግድያውን ያካሄደው ኃይል ዐማራውንና ኢትዮጵያን የሚወድ አይደለም፤ ጠላት ነው። ለለውጡ ዋና መሰናክል ነው።

ዲያስፖራውን ስመለከት የምመክረው ሕዝቡን ከእልቂት፤ አገሩን ከመፈራረስ ለመታደግ የተቀነባበረ ዘመቻ ማካሄድ ታሪካዊ ግዴታችን የሚል ነው። ከእያንዳንዱ ዘውግ፤ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያስቀድሙ እንዳሉ አምናለሁ፤ ተስፋ የሚሰጡኝ እነሱ ናቸው። ኢትዮጵያ በተከታታይ የውጭ ጠላት ወሯት አሸንፋለች። የጉዲትን፤ የግራኝ ሞሃመድን እልቂት አልፋለች። ወደፊትም አትፈርስም።

አንዱ ብሄር ወይንም ዘውግ ከሌላው ጋር እንዲጋጭ የሚያደርጉ ኃይሎችን ለማሸነፍ እንችላለን፤ ከተባበርን። መጀመሪያ ግን ብሄር ተኮር ጥላቻና ዘመቻ የሚያካሂዱ ኃይሎችን ባለን አቅም መታገልና ማጋለጥ አለብን። የዐማራውና የኦሮሞው ሕዝብ እንደ ብረት የጠነክረ ግንኙነት እንዲጠነክር መታገል አለብን። ህወሓት የትግራይን ሕዝብ አይወክልም ለማለትና ደፍረን ሕዝቡ ሌላውን ወንድሙን እንዲቀላቀል፤ ለውጡን እንዲደግፍ ተደጋጋሚ ጥሪ ማድረግ አለብን። ህወሓትን ሆነ ጃዋርን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሽብርተኛ ቡድን ነው ብለን የምናጋልጥበት ወቅት አሁን ነው።

በዐማራው ክልል የተካሄደው ግድያ መወነጃጀልን አስከትሏል። መጠንቀቅ ያለብን ግን መረጃ ሳይኖረን ወገንተኛ መሆናችን እናቁም። አናውቅም፤ መረጃ የለንም ለማለት እንዴት አንችልም? እኛ ኢትዮጵያዊያን በማናውቀው ጉዳይ ላይ መፍረድ ይቀድመናል። እባካችሁ ይህን መጥፎ ባህል እናቁመው። ጠ/ሚንስትሩ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵይዊነትንእንደሚያስቀድም አምናለሁ። ግዙፍ ተግዳሮት ደግሞ እንደገጠመው አያለሁ፤ እሰማለሁ።

ግን ዐብይ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት አልቆመም የሚል የተሳሳተና ሃላፊነት የጎደለው ነገር ሲነገር ልክ የዶር አምባቸው ሞት እንደሚያመኝ ሁሉ ይህም ሃሜት ያመኛል።

ለማጠቃለል፤ እኔ ለዶር አምባችው ከዶር ንጉሴ ነጋ ቤት ተገናኝተን ሹክ ያልኩት “ከማንኛውም ስራ በፊት ቅድሚያ መስጠት ያለብህ፤ የዐማራው ሕዝብ ራሱን ቀና እንዲያደርግና በወንድማማቹ በአማራውና በትግራዩ ሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ወሳኝ ስለሆነ ስራየ ብለህ አጠናክረው” የሚል ነበር። ለዚህ ምሳሌ የጠቀስኩለትና አቶ ገዱንም አደራ ያልኩት በአማራውና በኦሮሞው ሕዝብ መካከል የተደረገው ታሪካዊ  የወንድማማችነት ጅማሮ እንዲጠናከር ነበር። በዚህ ቅንና “ለዐማራው ሕዝብ ህይወቴን ሰጥቻለሁ” ብሎ ቃል ለገባው ወንድማችን የሚገባውን እውቅና እንስጠው። ኃውልት ይሰራለት፤ መንገድ ይሰየምለት። ለጀኔራል ሰዐረ መኮነንም እንደዚሁ። እኛ ጀግኖቻችን ህያው እናድርጋቸው።

“ቅጥ ያጣው ሃዘናችን” ፋይዳ የሚኖረው በሰከነ አእምሮ የሞቱትን ወንድሞቻችን ዓላማ ስናጤነውና እነሱን የሚተኩ መሪዎች ቦታቸውን እንዲይዙ ተመክሮ በመስጠት ነው። ሰብሳቢው መርህ መሆን ያለበት የሞቱት ጀግኖቻችን ምን እሴትና መርህ፤ ምን አደራ ትተውልን አለፉ? የሚለውን ጥያቄ በጋራ ለማስተጋባት ቆርጠን ስንነሳ ነው።

በአካል ባላውቃቸውም፤ የዐማራው ክልል ፖለቲካ ፓርቲ የበላይ አመራር አባላት፤ ወጣቶቹ አቶ ምግባሩ ከበደና አቶ አዘዘው ዋሴ ከአጋር ወንድማቸው ከዶር አምባቸው ጋር አብረው አልፈዋል። እነዚህ ወጣት መሪዎች የተገደሉበት ዋና ምክንያት፤ የዐማራው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያ መሪዎች እንዳይኖሯት የሚያደርግ ድርጊት ነው። ወይንም፤ ሆነ ተብሎ የዐማራው ሕዝብ መሪ አልባ እንዲሆን ታስቦበት የተፈጸመ ሴራ ነው።

ዛሬ እኛ ኢትዮጵያዊያን ቀን ከሌት መስራት ያለብን ኢትዮጵያን ከመፈራረስ ማዳን ነው። ዶር አምባቸውና ጀኔራል ሰዐረ መኮን አልፈዋል።

የማያልፍ ታሪክ መስራት ያለብን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን መአከል አድርገን ለውጡ በማንም የውስጥና የውጭ ሴራ እንዳይቀለበስ ማድረግ ነው።

ኢትዮጵያ ሃገራችን ለዘላለም ትኑር!!

የኢትዮጵያ ሕዝብ እኩልነት ይለምልም!!

ወቅቱ የሚጠይቀው ሀገራዊ አርበኝነት

የአንድ ሰው ማንነት የተገነባው ከቤተሰቡ ጠባብ ክበብ ካስተዋላቸው ወይንም ከወረሳቸው ባህርያት፣ ከአካባቢ ማኀበረሰብ ከቀሰማቸው ልምምዶች፣ ከሚኖርበት ሰፊ ኅብረተሰብ ከተማራቸው ዕውቀቶችና ጥበቦች፣ ከአድማስ ማዶ ያለው ዓለም ካበረከተለት የዕውቀትና የክህሎት ተሞክሮና ግኝቶች ከተቀዱ ምንጮች ነው፡፡

ኅብሩ የሰመረው የተፈጥሮ ክስተት፣ የባህሉ፣ የወጉና የልማዱ ውበት፣ የተወለደበት ወይንም የኖረበት ቋንቋዎች መስተጋብር፣ የሃይማኖቱና የዕምነቱ ብርታት፣ ደስታውና ሃዘኑ የተገለጠባቸው የሕይወቱ ውጣ ውረዶች፣ የቀረፀው የትምህርት ሥርዓትና ሀገሩ ያለፈችበት የዘመናት የታሪክ ጉዞ ወዘተ… እነዚህ ሁሉ ግብዓቶች ያንን አንድ ዜጋ ይቀርፁትና ማንነቱን ያበጁለታል፡፡ እርሱ ከሌላው፣ ሌላውም ሰው ከእርሱ መለየቱን ወይንም መመሳሰሉን ያረጋግጡለታል፣ በመተባበር ያኖሩታል፣ ለክፉ ካዋለውም ለግጭት ሊዳርጉት ይችላሉ፡፡

የሀገር ዳር ድንበር ታጥሮ ሉዓላዊነት የሚከበረው፣ የሥልጣኔ ብርሃን በሀገር አድማስ ላይ ቦግ ብሎ የሚፈካው፣ ለዘመናት የተጣባን የድህነት እድፍና የቡቱቷችንን ክንብንብ ከራሳችን ራስ ላይ ለማውለቅና የእኔነትን ስግብግብ ባህርይ ለማራገፍ የሚቻለው በዋናነት የግልን “የአርበኝነት ተግባር” መፈፀም ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ቅድሚያ ለወገኔ አሰኝቶ ከራስ በፊት ሕዝብን አስቀድሞ ግለኝነትን በመስዋዕት ማቅረቢያ መሰዊያ ላይ ለማስቀመጥ ዜጋውን የሚያደፋፍረው ያ አንድ መሠረታዊ ማብላያና ቅመም በዘርፈ ብዙ መገለጫዎች የሚተነተነው የሀገር ወዳድ ዜጎች የአርበኝነት ወኔና መንፈስ ነው፡፡

የአርበኝነት ፅንሰ ሃሳብና የቃሉ ጥንተ አመጣጥ

አርበኛ (Patriot) የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የተገኘው “አባት ሀገር” ከሚለው የፈረንሳይኛ ቃል ሲሆን የቃሉ ሥረ መሠረት ደግሞ የግሪክ (የጥንታዊ ፅርዕ) ቋንቋ ነው፡፡ አርበኛም ሆነ አርበኝነት (Patriotism) በመዝገበ ቃላት ውስጥ ተካቶ በስፋት አገልግሎት ላይ የዋለውና በእንግሊዝ ሕዝብ አእምሮ ውስጥ ሰርፆ ሊገባ የቻለው የኤልሳቤጣዊያን ክፍለ ዘመን (Elizabethan Era, 1558 – 1603) እየተባለ “በወርቃማነቱ” በሚንቆለጳጰሰው ዘመን ነበር፡፡ ይህ ዘመን እንግሊዝ በሥልጣኔዋ ታላቅነት በዓለም ፊት ቁንጮ ሆና ለመታየት ከሌሎቸ ሀገራት ጋር ፉክክር ውስጥ የገባችበት፣ የተራቀቁ የኪነ ጥበባትና የሥነ ጥበባት ሥራዎች የተስፋፉበት፣ ዊሊያም ሼክስፒርን የመሳሰሉ አስደማሚ የሥነ ጽሑፍ ልሂቃን የገነኑበት፣ ስፖርታዊ ጨዋታዎች የደመቁበት፣ ኢኮኖሚያቸው የተነቃቃበት፤ በአጠቃላይም “በእንግሊዝ ፀሐይ አትጠልቅም” የሚለው የተስፋፊነትና የእኔ እበልጣለሁነት ፍልስፍና ያቆጠቆጠበት ዘመን ነበር

ከኤልሳቤጣዊው ዘመን ቀደም ብለው አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት አዳዲስ ቅኝ ግዛቶችን ለመያዝና ለመቀራመት በአሳሾቻቸው አማካይነት ዓለምን ዳር እስከ ዳር ያሰሱበትን ዘመናት በቁጭት በማስታወስም ፊት ቀዳሚ ለመሆን እንግሊዝ ተጠናክራ የተነሳችነበት ዘመን ነበር፡፡ ለምሳሌ፤ ከኤልሳቤጣዊው ዘመን ቀደም ብሎ ቫስኮ ዳጋማን (1460–1524) እና ፈርዲናንድ ማጂላንን (1480 – 1521) የመሳሰሉ ፖርቹጋላውያን አሳሾች የመርከቦቻቸውን መልህቅ ነቅለው በአጥናፈ ምድር ውቂያኖሶች ላይ እየቀዘፉ ሀገራትን የበረበሩበት፣ ለቅኝ ግዛት ተስፋፊዎችም በሩን ወለል አድርገው የከፈቱበት ወቅትም ነበር፡፡ የፖርቹጋላዊው የቫስኮ ዳጋማ ልጅ (እ.አ.አ 1516 – 1542) ክርስቶፎል ዳጋማ 400 ስልጡን ወታደሮችን እየመራ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በኦቶማን ኢምፓየር ተደግፎ ሀገሪቱን ከዳር እስከ ዳር ያመሳቀላትን የኢማም አህመድ ኢብን ኢብራሂም አል ጋዚ (በተለምዶ አህመድ ግራኝ እየተባለ የሚጠራውን) ለመመከት ለዓፄ ገላውዲዎስ የድረሱልን ጥሪ ምላሽ በመስጠት አጋርነቱን አረጋግጧል፡፡

በዚያን መሰሉ ቅድመ ኤልሳቤጣዊ ዘመን ቀዳሚዎቹ የአውሮፓ አሳሾችና የቅኝ ግዛት ተስፋፊዎች የነበራቸው ዝናና ገናናነት እንግሊዝን እረፍት ነስቷት ስለነበር፤ እርሷም በተራዋ ኩራቷን በይበልጥ ለማግነን በመሻት “Patriot, Patriotism” የሚሉት ቃላት በሕዝቧ ውስጥ ሰርፀው ይበልጥ እየተዋወቁ በዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴአቸው ውስጥ ሁነኛ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ ያደረገችበት ወቅት ነበር፡፡ ለታላቋ እንግሊዝ ኩራትና ልዕልና፣ በጦር ሜዳ ፍልሚያም ሆነ በተለያዩ ሌሎች የኪነ ጥበባትና የሥነ ጥበባት፣ የንግድና የሃይማኖት ዘርፎች ግንባር ቀደም ለሆኑት ልሂቃን አርበኞቿ “Partiot” የሚለውን ክብርና ሽልማት በስፋት በመስጠት የሀገራቸውን ገናንነት እንዲያፋጥኑ ወኔአቸውንና ሞራላቸውን በማነሳሳት ዜጎቿ የታላቋ እንግሊዝ ታላላቅ አርበኞች መሆናቸውን በስፋት ማስተማር ጀመረች፡፡

ከዚያን ጊዜ ወዲህ ነው አርበኝነት (Patriotism) የሚለው ፅንሰ ሃሳብ የጦር ሜዳ ድል አድራጊነትን አካቶና ከፍ ብሎ ለሀገርና ለወገን በኪነ/ሥነ ጥበባት፣ በእርሻ፣ በንግድና በኢንዱስትሪ ወዘተ… ዘርፎች ተሰማርተው ፋይዳ ያለው ውጤት ላስመዘገቡ ዜጎች የአርበኝነት ክብር መሰጠት የተጀመረው፡፡

“አርበኝነት” የሚለው ፅንሰ ሃሳብ እያደር ለብዙ የዕውቀት ዘርፎች ልሂቃን የመወያያ አጀንዳ እየሆነ በልዩ ልዩ ገፅታዎቹም መተንተኑ አልቀረም፡፡ አንዳንድ የፍልስፍና ጠቢባን አርበኝነትን የሚተነትኑት ከብሔረተኝነት ጋር በማነፃፀር ነው፡፡

ለምሳሌ፤ ጆርጅ ኦርዌል የተባለው ታላቅ ደራሲ “አርበኝነት ለአንድ ውስን ሁኔታዎችና የሕይወት እንቅስቃሴ ከልብ መሰጠት ነው፡፡ ይህ መሰጠት ደግሞ በዓለም ላይ እንደዚህ የተሻለ ጉዳይ አይኖርም ብሎ እስከ ማሰብ ያደርሳል፡፡ ይህ ጠንካራ እምነት ከራስ መሰጠት ባለፈ በሌላው ላይ በጎ ተፅዕኖ ለመፍጠር እንደሚያነሳሳም አስረግጦ ይገልፃል፡፡ እንደ ኦርዌል አገላለጽ አርበኝነት በባህሪው ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊም ሆነ ባህላዊ ጥቃትን የመከላከል ጠንካራ እምነት እንደሆንም አስረግጦ ይገልጻል፡፡

ጀርመናዊው ማርክስ ደግሞ በወዛደራዊ ዓለም አቀፍነት መርህ መሠረት፤ “ዓለም የሠርቶ አደሩ” ስለሆነች በውስን ድንበር ተከልሎ ከሚገለፅ አርበኝነትን የማቀንቀን ስሜት ሠራተኛው መደብ ነፃ ሆኖ የዓለም ማኅበረሰብ አንድ አካል እንደሆነ ማመን አለበት የሚል ፍልስፍናውን አስተዋውቋል፡፡ ትሮቲስኪና አለን ውድስን የመሳሰሉ ልሂቃንም ይህንን የማርክስን ተመሳሳይ ፍልስፍና በማቀንቀን “ወዛደራዊ ዓለም አቀፋዊነት የሀገሮችን ድንበር በማፍረስ ከጨቋኞች ብዝበዛ ነፃ የሆነ አንድ ብሩህ ሶሻሊስታዊ ዓለም መፍጠር ነው” በማለት በክልል የሚወሰን አርበኝነትን በመፃረር ተሟግተዋል፡፡

ለትውስታ ያህል “ያ ትውልድ” እየተባለ የሚጠቀሰው የ1960ዎቹ የሀገራችን ወጣት አብዮተኛ ትውልድ “እንደነ ሆቺሚን እንደ ቼጉቬራ!” እያለ ይዘምር የነበረው ያንን ዓለም አቀፋዊ የኮሚዩኒዝም ፍልስፍና ለመግለጥ ጭምር ይመስላል፡፡

አርበኝነት የሚለው ጽንሰ ሃሳብ በሀገራችን የተዋወቀበት ወቅትና ዐውድ

አርበኝነት “Patritotism” ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ መተዋወቅ እንደጀመረ የሚታመነው በዓፄ ዐምደ ጽዮን ዘመን (1314 – 1344 ዓ.ም) እንደሆነ ግምት አለ፡፡ ለግምቱ ማጠናከሪያ የሆነውም ንጉሡ የመንግሥቱን ግዛት ለማስፋፋት ከአካባቢ ሀገራትና ኃይላት ጋር ጦርነት እየከፈተ ወደፊት በሚገፋበት ወቅት “ሐርበኛ” እያለ በግጥም ይሞካሽ ነበር ወይንም ራሱን ያሞካሽ ነበር፡፡ በታሪክ ተመዝግቦ በሚገኘውና እርሱን በሚያሞግሰው ዘለግ ባለ ግጥም ውስጥ “ሐርበኛ ዐምደ ጽዮን፣ መላላሽ የወሰን፣ ውá እንደ ወሰን . . . ምን ቀረሽ በወሰን . . .” የሚለው ሃሳብ በስፋት ተጠቅሷል፡፡

ይህ ግጥም በኮሌጅ ደረጃ ለመማሪያነት የሚያገለግል ሲሆን በሥነ ጽሑፍ ምሁራን ዘንድም አማርኛ ቋንቋ ለሥነ ጽሑፍ ቋንቋነት ማገልገል የጀመረበት ዘመን እንደሆነ ግምታቸውን ይሰጣሉ:: ከዚህ እውነታ የምንረዳው የኤልሳቤጣዊያን ዘመን አርበኝነትን (Patriotism) በስፋት ከመተዋወቁ ሁለት መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ ቃሉ በእኛ ቋንቋ ዐውድ ውስጥ አገልግሎት ላይ ውሎ እንደነበር ነው፡፡

አርበኝነት “Patriotism” በዋናነት የዲፕሎማሲና የጦር ሜዳ አሸናፊነትን በማስተዋወቅ በሀገራችን ተዘውትሮ መገለፅ የጀመረው ከ1888ቱ የዐድዋ ድል በኋላ ቢሆንም፤ በዘርፈ ብዙ አገልግሎቱ አርበኛ ወይንም አርበኝነት በስፋት አገልግሎት ላይ እንደዋለ የሚታመነው ግን በአምስቱ ዓመታት የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት (ከ1928 – 1933 ዓ.ም) እና ከዚያም በኋላ ባሉት ዓመታት እንደሆነ በአንዳንድ ጥናቶች ውስጥ ተመልክቷል፡፡

ይሄው አርበኝነት የሚለው ጽንሰ ሃሳብ በሀገራችን ትርጉሙን እያሰፋ በመሄድ ለብዙ ጉዳዮች በገላጭነት መዋል ከጀመረም ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ “አርበኝነት” ማለት በአንድ ታሪካዊ ወቅትና ጊዜ የአንድን ሉዓላዊ ሀገር ክብር በመዳፈር ድንበር ጥሶ የመጣን ባዕድ ወራሪ ወይንም የሀገርና የሕዝቦችን ልዕልና አደጋ ላይ ለመጣል የተሰለፈን አጥፊ ኃይል ተፋልሞ ለመርታት በጦር ሜዳ የሚተወን የተዋጊነትና የጀግንነት ተግባር ብቻ አለመሆኑም በሚገባ ግንዛቤ ተገኝቶበታል፡፡

አርበኝነት ከራስ ምቾትና ጥቅም ይልቅ በፖለቲካው፣ በማኅበራዊውና በኢኮኖሚው ዘርፍ የሀገርንና የወገንን ልዕልናና ክብር የማስቀደም ታላቅ የዜጎች የመንፈስ ለጋስነት የሚታይበትና በተግባር የሚረጋገጥበት እውነታ ነው፡፡

የአንድ መንግሥት የአወቃቀር ሥርዓት አሃዳዊም ሆነ ፌዴራላዊ፣ ወይንም ሌላ፤ ዘመናዊም ቢሆን ወይንም ባይሆን፣ ሀገርንና ወገንን በአንድ ላይ አቅፈውና አስማምተው ወደፊት ከሚያራምዱትና አፅንተው ከሚያቆሙት ጠንካራ አምዶች መካከል አንዱና ዋነኛው የአርበኝነት የመንፈስ ውርስ ነው፡፡

አርበኝነት የሀገርንና የሕዝቦችን ክብር የማስጠበቅና የማስቀጠል ታላቅ ብሔራዊ ግዴታና የዜግነት ማረጋገጫ ከመሆኑ አኳያ ግለሰቡ የተገኘበት ብሔር ወይንም ጎሳ፣ ባህሉ ወይንም ቋንቋው፣ ፖለቲካዊ አመለካከቱ ወይንም እምነቱ ወዘተ… በአርበኝነቱ መንፈስ ላይ ጥላ አጥልቶበት “አያገባኝም” በሚል ውሳኔ ገለልተኛ ሊያደርገው እንደማይገባም ይታመናል፡፡ ከግል የተዛባ እምነትና ፍልስፍና በመነጨ ውሳኔም “በግለኝነት ስሜት ብቻ” ከሕዝቡ ጎራ ተለይቶ የሀገርን ጥቃት፣ ድህነት፣ ችግርና መከራ በሩቁ ሆኖ ለመመልከት መሞከር ወይንም የጥፋቱ አጋር ሆኖ መተባበር ትርፉ ከማኅበረሰቡ ባይተዋር ሆኖ መገለል ብቻ ሳይሆን ሕዝባዊ፣ ህሊናዊና ሕጋዊ ቅጣቱም ቀላል የሚባል አይሆንም፡፡

አርበኝነትን የሚያሰርፁና የሚያፀኑ መሠረታዊ ዓምዶች

አርበኝነት ራስን ለሀገርና ለወገን ሁለንተናዊና ሉዓላዊ ክብር አሳልፎ መስጠት ነው፡፡ አርበኝነት የኢትዮጵያ ታሪክ አካል ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ደግሞ በደመቀ ኀብረ ውበትና መዛነቅ የተዋበ ነው፡፡ ቋንቋቸው፣ ባህላቸውና ልምምዳቸው ሳይገድባቸው የሀገራችን ብሔረሰቦች በሙሉ የተጋመዱት በጋራ እሴቶችና መዛነቆች ተሳስረው ነው፡፡

የደጋው፣ የወይና ደጋውም ሆነ የቆላው ነዋሪ ወገናችን ለዘመናት ተሳስሮ የኖረው ተፈጥሮ በለገሰችው መኖሪያው ያፈራውንን የግብርናንም ሆነ የዕደ ጥበባት ውጤቶችን እየሸጠና እየተለዋወጠ ነው፡፡ ፡፡

ከዓለማችን በሞቃታማነቱና ከምድር ወለል በታች በዝቅተኛነቱ ክብረ ወሰን ከጨበጠው ዳሎል ጀምሮ እስከ የተራሮች ንጉሡ ራስ ዳሸን፣ ከስምጥ ሸለቆ የመሬት ስብርባሪ ገጽ እስከ ታላላቆቹ የወንዞቻችን ተፋሰሶች ኑሮውን ያደላደለው ኢትዮጵያዊ ወገን የዓየር ንብረት ለውጥ ሳይበግረው፣ የመልክዓ ምድር መዥጎርጎር ሳይገድበው ለዘመናት የኖረው እርስ በእርስ ተከባብሮና ተደጋግፎ ነው፡፡ የባህሉና የቋንቋው ኅብር ትስስሩን ይበልጥ አጥብቆለታል፡፡ በችግር ዘመን መደጋገፉ፣ በርሃብ ዘመን መረዳዳቱ፣ በመልካም ዘመን መደጋገፉ ባህሉ ነው፡፡

ሦስቱ ዋና ዋና ኃይማኖቶች (ክርስትና፣ ይሁዲነት እና እስልምና) በኢትዮጵያ የአምልኮ ሥርዓት ውስጥ ሁነኛ ስፍራ ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ ሕዝባችን እርስ በርሱ ተከባብሮ እንዲኖር የጣሉት መሠረትም እጅግ መልካም ነው፡፡ ይህ መዛነቅ በሰላም ጊዜ መደጋገፊያና መተሳሰቢያ፤ በችግር ጊዜ ደግሞ መረዳጃና የሀዘን መመከቻ በመሆን ለሕዝባችን የአርበኝነት መገለጫ እንደ መልሕቅ አንድነታችንን አጥብቆ ያቆራኘ መሠረታዊ እሴት ነው:: ስለዚህም ሀገር በወራሪዎች ስትደፈር ሕዝባችን እንደ ንብ ሠራዊት ሆ እያለ የሚተመው፣ ጦሩን እየነቀነቀና ሰይፉን እያወናጨፈ በጀግንነት ወራሪ ጠላትን ፊት ለፊት እየገጠመ የሚመክተው፣ በችግር ዘመንም የሚደጋገፈው ከላይ የተዘረዘሩት ንብርብር ዕሴቶቹ በአንድ የሀገር ፍቅርና የአርበኝነት መንፈስ ስለቃኙት ነው፡፡

የአርበኝነት ዋና ዋና መገለጫዎች

አርበኝነት መልከ ብዙ እንደሆነ ከላይ በዝርዝር ተገልጧል፡፡ ድንበር ዘለል ወራሪን ለመመከትም ሆነ ራስን ለሀገር ጥቅምና ክብር አሳልፎ መስጠት የአርበኝነት ተቀዳሚ መገለጫ መሆኑ ተጠቋሟል፡፡ አርበኝነት በሁለንተናዊ የልማት ተሳትፎ ውስጥም እንደሚገለጥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በፌዴራልና በክልል መንግሥታት አማካይነት ለሀገራችን ሞዴል አርሶ አደሮች፣ ለስኬታማ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፣ ለአምራቾችና የፈጠራ ባለሙያዎች “በአርበኝነት” ማዕረግ ዕውቅናና ሽልማት መሰጠቱ በመልካምነቱ የሚጠቀስ ተግባር ነው፡፡

በማኅበራዊ ተሳትፎ ውስጥም “አርበኝነት” የሚገለፅባቸው ዘርፎች ብዙ ናቸው፡፡ የፍትህና የርትዕ ሥርዓት እንዳይዛባ በፅናትና ያለ ይሉኝታ ዘብ መቆም፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት መስፈን የድርሻን በቀዳሚነት ማበርከት፣ በአርዓያነት ራስን ማሳወቅ፣ በበጎነት መልካም ተግባርን ማከናወን፣ ለተጎዱትና ድጋፍ የሚያሻቸውን መታደግ፣ በተሰማሩበት ተግባራት ሁሉ መልካም ተግባር በመፈፀምና ለሀገርንና ለሕዝብ ክብር ተፃራሪ ከሆነው የድህነት ውርደት ለመታደግ መጨከን ዋነኞቹ የዜጎች የአርበኝነት መገለጫ ተግባሮች ናቸው፡፡

የአርበኝነትን ስሜት የሚያደበዝዙ ተግዳሮቶች

 ስለ አርበኝነት የጻፉ ባለሙያዎች እንዳረጋገጡት አርበኝነት መጀመሪያውኑ የተቀሰቀሰበት ምክንያት ሲረግብ ስሜቱ እየቀዘቀዘ የመሄድ አደጋ ይጠናወተዋልና መንፈሱ እንዳይላላ ከሥር ከሥሩ እየተኮተኮተ በመደበኛ ትምህርት፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በኪነ ጥበባት፣ በሙዚዬም፣ በሐውልታትና በመሳሰሉት አማካኝነት ዘመኑን በሚመጥን እሳቤ እና ማስታወሻዎች እየታደሰ ህልውናው እንዲጠበቅ መደረግ አለበት፡፡ ወጣቱ ስለአርበኝነት ስልታዊና ማኅበራዊ በሆነ ዘዴ ካልቀረበለት በስተቀር በአለፍ አገደም በሚደርሰው የቃል መልዕክትና አደራ ብቻ ግንዛቤው አያድግም፣ በመንፈሱ ውስጥም አይሰርፅም፡፡

የአርበኝነት ስሜት መልካም ፍሬ እንደሚያፈራ ዛፍ ሊመሰል ይችላል፡፡ ከተከለው ዛፍ መልካም ፍሬ የሚጠብቀው ገበሬ ለዛፉ እንክብካቤ ማድረግ ያለበት ገና ከችግኝነቱ ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ ተፈጥሮ ራሷ ታስተምረናለች፡፡ ችግኙ ለም አፈር፣ ተስማሚ አየር፣ ማዳበሪያና ውሃ በተገቢው ሁኔታ ማግኘት ካልቻለ አይደለም ፍሬ መጠበቅ የችግኙ ህልውና ራሱ አደጋ ላይ ወድቆ ለድርቀት ሊጋለጥ ይችላል፡፡

አርበኝነትም እንዲሁ በአንድ ወቅት ቢፈጠርም ለተከታታይ ትውልዶች በመንፈስ ቅርስነት በተገቢው ሁኔታ እንዲተላለፍ ባለድርሻ ነኝ የሚል አካል ሁሉ ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ ሊያደርግለት ይገባል፡፡

የአርበኝነትን መንፈስ እንደ ህልውና እስትንፋሳችን በየሰኮንዱና በየደቂቃው ሊነቃቃና ሊታደስ ይገባል፡ ፡ የአርበኝነትን ስሜት በወቅት ወለድ ክስተቶች ብቻ ወስነን እንደ ክት ልብስ ከተጎናፀፍነው እርሱ አርቴፊሻል የስሜት ሙቀት ለመፍጠር ካልሆነ በስተቀር ዘላቂ ለውጥ ላያመጣ ይችላል፡፡ አርበኝነት በፅኑ የሀገር ፍቅር ስሜት በተሰለፉበት መስክ ሁሉ “ሀገሬ ለእኔ ምን አደረገችልኝ ብሎ ማኩረፍ ሳይሆን እኔ ለሀገሬ ምን በጎ ተግባር ፈፀምኩ” ብሎ ራስን መጠየቅና ወቅቱ ለሚጠይቀው ሕዝብ ተኮር አደራ መስዋዕት ለመሆን እስከ መወሰን መጨከንን ይጠይቃል፡፡

በዕለት ከዕለት የሕይወት እንቅስቃሴያችን፣ በተቀመጥንበት የአመራር ወንበር፣ ፍትሕን ለማስፈን ለማልነው መሃላ፣ በግል ጥቅም ልክፍት የሀገርን ክብር ከማዋረድና ከማሳፈር ከንቱ ድርጊት ራሳችንን በመጠበቅ ለሀገራዊ አጀንዳና ለሕዝቦች ልዕልና ተሟጋችና ምሳሌ ስንሆን ያን ጊዜ እውነተኛው የአርበኝነት ስሜት ያለ ገላጭ ቋንቋ በተግባራችንና በእርምጃችን ይገለጣል፡ ፡ በሀገርና በሕዝብ ላይ አደጋና ችግር ሲጋረጥ “እኔ ምን አገባኝ” በማለት የጲላጦስን ማስታጠቢያ አስቀርቦ እጅን መታጠብና ከአጥፊው ጋር ግንባር ፈጥሮ ለአደጋው መባባስ አባሪ ተባባሪ መሆን እውነተኛውን የአርበኝነት ስሜት ማሳደፍ ነው፡፡ የሀገርንና የሕዝቦችን ልዕልና የማስከበርን ጉዳይ ወደ መንግሥት ብቻ ጣትን እየጠቆሙ አያገባንም ማለት አይደለም፡፡ ዜጎች “እኔ ምን አገባኝ” ማለት ከጀመሩ በአርበኝነት ስሜት ላይ አደጋ እንደተጋረጠ ማረጋገጫ ሊሆን ችላል፡፡

የተወሰነ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋና ባህል ያልተጫነውን የአንድ ሀገር ብሔራዊ (ሁሉን አቀፍ) የአርበኝነት መንፈስ በዜጎች ውስጥ ለማስረፅ የሚፈታተኑ ተገዳዳሪ ሁነቶች በርካታ ቢሆኑም የዘርፉ ጠበብት በቀዳሚ ተርታ የሚያስቀምጡትን ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮችን ብቻ እንደሚከተለው ለአብነት ማመልከት ይቻላል፡፡

ፅንፍ የያዘ ብሔረተኝነት – አርበኝነት አንዳንድ ጊዜ ከብሔረተኝነት ጋር በተለዋጭነት ግልጋሎት ላይ ይዋል እንጂ ሁለቱ የተሸከሙት ፅንሰ ሃሳብ በእጅጉ የተራራቀ ነው፡፡ አርበኝነት አመለካከቱ ሰፊ፣ አምነቱ ሕዝባዊነት፣ ትኩረቱ ሉዓላዊነት፣ አተገባበሩ ሁሉን አቀፍ፣ ግቡ ሀገራዊ ነው፡፡ በአንፃሩ ፅንፈኛ ብሔረተኝነት በአመለካከት ጭፍንነት፣ የራስን ብቻ በማግነን ባህሉንና ውርሱን “እኛና እነርሱ” በማለት እያነፃፀረ የራሱን ገናናነት የሚያውጅና ሌሎቹን ዝቅ የሚያደርግ አመለካከት ነው፡ ፡ ይህን መሰሉ አመለካከት ሥር እየሰደደ የሚሄድ ከሆነ ሀገራዊ የአርበኝነትን ስሜት ማደብዘዙ አይቀርም፡፡

አፈንጋጭ ቡድናዊ ስሜት – ይህን መሰሉ ስሜት ክበቡ ጠባብ ይምሰል እንጂ በሀገራዊ የአርበኝነት መንፈስ ላይ የሚያጠላው ጥላ በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም፡፡ አፈንጋጭ ቡድን አንዳንዴ የሚያነሳቸው የመከራከሪያ ነጥቦች ውሃ የማይቋጥሩ ይምሰሉ እንጂ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ግን በቀላሉ ሊታዩ የሚገባቸው አይደሉም፡ ፡ “አርበኝነት በአንድ ወቅት የተፈጠረ ታሪካዊ ክስተት ስለሆነ ለእኔ ትውልድ ረብ የለውም” በማለት የሚሟገትና አርበኝነትን ከጦር ሜዳ ፍልሚያ ጀግንነት ጋር ብቻ በማያያዝ የሚከራከር ቡድን በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል ተብሎ ባይታመንም ሃሳቡ ግን ይብዛም ይነስ ጥቂቶችን ማሸፈቱ አይቀርም፡፡

“ብዙኃኑ የሚዘምሩት አርበኝነት እኔና ቡድኔን ጎዳን እንጂ ምንም አልጠቀመንም” የሚል የቡድንተኝነት ቅስቀሳም ውሎ አድሮ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡ አፈንጋጭ ቡድንተኝነት ዓላማውን ለማሳካት በተደራጀ መልኩም ሆነ በቡድኑ አባላት አማካይነት ስለሚቀነቀን ተልዕኮውን ለማሳካት ወቅትና ጊዜ አይመርጥም፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ አመለካከቶች በእጅጉ የተጣመሙ ቢሆኑም ውሎ አድሮ ግን ለሰሚዎችና ለተመልካቾች የአርበኝነትን መሠረታዊ ድንጋጌ በማዛባት በሕዝቦች መካከል መቃቃርን መፍጠራቸው አይቀርም፡፡

አርበኝነትና የዘመነ ሉላዊነት (Globaliazation) ተግዳሮቶች

ሉላዊነት የነፃ ንግድ ሥርዓትን፣ የካፒታል ዝውውርን፣ የዕውቀትና የሕዝቦችን እንቅስቃሴ “አርነት አውጥቶ” ዓለምን በአንድ መነፅር የመመልከት ወቅት ወለድ ፍልስፍና ነው፡፡ የፍልስፍናው ዋና ማስፋፊያ ደግሞ የተራቀቁት የመገናኛና የኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂዎችና በፈጣን ሁኔታ እየተዋወቁ ያሉ ሳይንሳዊ ግኝቶች ናቸው፡፡

ዛሬ ዓለማችን እያስተናገደችው ያለው የቅኝ ግዛት ወረራ በመደበኛ የጦር ሠራዊት የሚመራ ሳይሆን ስልቱ ያነጣጠረው የኢኮኖሚና የባህል ወረራ ላይ ነው፡ ፡ የጦርነቱ ፊት አውራሪ አዝማቾችም መገናኛ ብዙኃን፣ በቢሊዮን ቁጥር የሚገመቱ የድረ ገፅ ወረራዎች፣ ኢንተርኔት፣ ስፖርት፣ ሙዚቃና ፊልሞችን የመሳሰሉት ናቸው፡፡

የዘመነ ግሎባላይዜሽን ተፅዕኖ ከሚገመተውና ከሚታሰበው በላይ እጅግ የረቀቀና የተወሳሰበ ነው፡፡ የአጥናፈ ዓለምን ወቅታዊና ቅፅበታዊ ውሎ አዳር በሁለት ጣቶቻችን ውስጥ አስገብተን በረበርናት ወደማለቱ ፍልስፍና ዘልቆ ከተገባ ሰነባብቷል፡፡

ዛሬ ዓለማችን በጣታችን መሃል ገብታለች የሚለው ፍልስፍና መሠረቱ የሉላዊነት መርቀቅ ውጤት መሆኑ ለማንም ግልፅ ነው፡፡ ሉላዊነት የዓለም ሀገራትን ያመሳቅላል፣ ያቀላቅላል፣ ካልሆነለትም የማጥፋት አቅም አለው፣ ከበዛም ለታላላቅ ሀገራት ታናናሽ ሀገራትን የመስዋዕት በግ አድርጎ ያቀርባል፡፡

የኢኮኖሚ ወረራ ብቻ ሳይሆን የባህል ወረራም አንዱ የሉላዊነት መገለጫ ነው፡፡ ዛሬ በየትኞቹም ሀገራት የሚኖሩ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ ወጣቶች የሀገራቸውን የአርበኝነት ታሪክ፣ የድልና የነፃነት ዓመታት ወይንም አንዳች ታሪካዊ ክስተቶች የተፈፀሙባቸውን ኩነቶች አስታውሶ በክብር ከመዘከር ይልቅ ስለ ቫለንታይን ቀን፣ ስለ ሃሎዊን ቀን፣ ስለ ክሬዚ ቀን፣ ስለ ከለር ቀንና ስለመሳሰሉት ቀናት መተረክና መዘከር ይቀላቸዋል፡፡ የሀገራቸውን የአርበኝነት ገድል ከማንበብና ከማጥናት ይልቅም የሆሊውድን ተዋናዮች፣ የእንግሊዝን የእግር ኳስ “ጀግኖች”፣ የፋሽን ዲዛይነሮችንና የፊልም ባለሙያዎችን ታሪክ፣ ገድልና የግል ህይወት ቢያነቡና ቢያደንቁ ይመርጣሉ፡፡

የዓለምን ዋና ዋና የንግድ ተቋማት በሞኖፖል ለመቆጣጠር እየተጉ ያሉት ማይክሮ ሶፍትን፣ ማክዶናልድስ፣ ናይክ፣ ሆሊውድ የመሳሰሉት ታላላቆቹ ኩባንያዎችና ታላላቅ የስፖርት ፌዴሬሽኖች ዋነኛ ግብ አድርገው የሚንቀሳቀሱት ለዚሁ የሉላዊነት ፍልስፍና ተልዕኮ አስፈፃሚነት እንደሆነ ብዙ ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡

በሉላዊነት ፍልስፍናና የፍጥነት ጉዞ ዙሪያ የሚደረጉት ውይይቶችና ክርክሮች እጅግ የተለያዩ ፅንፎችን የያዙ ናቸው፡፡ አንዳንዶች የሉላዊነትን ጠቀሜታ አግዘፈው ለማሳየት ሲሞክሩ፣ አንዳንዶች ደግሞ አደጋውንና ተግዳሮቱን አግንነው ይከራከራሉ፡፡ ሉላዊነት እንደ ብዙ ምሁራን አገላለፅ (A Blessing in Disguise) ወይንም በእኛው አገላለፅ “በረከተ መርገም” እንደምንለው ነው፡፡ ጥቅሙ ላቅ ያለ ጉዳቱም የገነነ ሆኗልና፡፡

እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም በስዊዘርላንድ ዳቮስ ተደርጎ በነበረው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ላይ የወቅቱ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር እና የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን ስለ ግሎባላይዜሽን ሲናገሩ “ነፃ የገበያ ውድድርና ሉላዊ ማኅበረሰብ (Global Society)ን በዓለም ላይ ብናሰፍን የሀገሮችን የተመጣጠነ ብልፅግና እናረጋግጣለን፤ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ሁሉም ሀገራት የሚመሩበትን የሉላዊነት መርህ መፍጠርና ማስፈፀም ይኖርብናል” በማለት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ውሳኔ አከል መልዕክት አስተላልፈው ነበር፡፡

ከዓመታት በኋላ ወጤቱ ሲታይ ግን እንኳንስ የተመጣጠነ የሀገራት ዕድገት ሊመዘገብ ቀርቶ ዓለማችን ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ ትርምስ ውስጥ እንደገባች መረዳት ይቻላል፡፡ የአውሮፓን ኅብረት የመሠረቱት ሀገራት የሉላዊነቱ “በረከተ መርገም” አልጣጣም ብሏቸው ወደ መናቆርና ወደ መደናቆር እየወሰዳቸው ይገኛል፡፡ የእንግሊዝን ከኅብረቱ ለመውጣት ማኮብኮብ ተከትሎ ብዙ ቀውሶች እየተከተሉ ነው፡፡ ከኅብረቱ ለመውጣት ወፌ ቆመች እያለች ያለችው እንግሊዝም ወደ ጥንቱ “የዘርፈ ብዙ አርበኝነቴና ገናናነቴ” መመለስ አለብኝ ወደሚለው የቀዳሚ ዘመን ፍልስፍናዋ ለመመለስ ያሰበች ይመስል የጠነከረ አዋጅ በማወጅ ስሟን ከUnited Kingdom ወደ Great Britain ለውጣለች፡፡ የሀገሯ ሚዲያዎችና ተቋማትም ይህንኑ ስሟን እንዲያስከብሩላት ጥብቅ መመሪያ አውጥታለች፡ ፡ አሻፈረኝ ብለው በቀዳሚ ስሟ ካልጠራሁ ብለው የሚያንገራግሩትንም እንደምትቀጣ ውሳኔዋን በይፋ አስታውቃለች፡፡

የአፍሪካ መሪዎችም እ.ኤ.አ በ2063 በአንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ጥላ ሥር ለመሰባሰብ የጋራ አቋም ይዘዋል፡፡ መሪዎቻችን በወሰኑት አህጉራዊ ውሳኔ ላይ ሂሳዊ ክርክር ለመክፈት ወቅቱ ያለፈ ቢሆንም ከአርበኝነት አንፃር የዓለም አቀፉን አካሄድና የመሪዎቻችንን ውሳኔ አጠቃሎ ማየቱ ግን አግባብ ይሆናል፡፡ የአፍሪካ መሪዎች በጋራ የተስማሙት አንድ የተባበረ የፖለቲካ ማኅበረሰብ፣ የተጠናከረ የጋራ ባህል፣ ውርስና ዕሴቶች ለመፍጠር ነው፡፡ ይህ ህልም ደግሞ የአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሀገራትም በየአህጉራቸው ክልልና ቀጣናዎቻቸው ሊተገብሩት የሩቅና የቅርብ ዕቅድ ነድፈው ለተግባራዊነቱም በትጋት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ይህ አንድ የመሆን ፍላጎት እውን ተግባራዊ ቢሆንና በየሀገራቱ ፈጥኖ ቢተገበር ምን ውጤት ሊያስከትል ይችላል? የእኛ የምንለውና በዘመናት ውስጥ ሥር የሰደደው የአርበኝነት መንፈስ ሊደበዝዝ አይችልም? መልካም ብለን አክብረን የያዝናቸው ሀገራዊ ዕሴቶቻችንስ ዕጣ ፈንታቸው ምን ሊሆን ይችላል? በዜጎቻችን ላይ ሊደርስ የሚችለውን የማንነት ቀውስስ እንደምን መቋቋም ይቻላል፡፡ ሉላዊነትን ከሀገራዊ አርበኝነትስ ጋር አዛምዶስ እንደምን መጓዝ ይቻላል? ውይይት ሊደረግበት ይገባል፡፡

የአርበኝነትን ክብር ለማስጠበቅና ለማስቀጠል ከማን ምን ይጠበቃል?

የሀገራችን ዘርፈ ብዙ አርበኝነት መንፈስ በአግባቡ እየጎለበተ ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ የሚከተሉት ተቀዳሚ ባለድርሻ አካላት ትልቅ ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል፡፡

ዋናው ባለድርሻ መንግሥት ነው – መንግሥት የሕዝብን የሥልጣን አደራ ተቀብሎ የሚያስተዳድር ስለሆነ የዜጎች የአርበኝነት መንፈስ እንዳይቀዘቅዝ ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይገባዋል፡፡ የፖለቲካ ፕሮግራሙን ተቀብሎ ምራኝ ብሎ ሕዝቡ ለመንግሥት ስልጣኑን በአደራ ጭምር ያስረከበው የዕለት ዳቦ እንዲያቀርብለት፣ የሀገሩን ሉዓላዊ ክብር እንዲያስጠብቅለት፣ ደህንነቱን እንዲጠብቅለት፣ የዲፕሎማሲ ተግባር እንዲያከናውን፣ የትምህርትና የልማት ሥራዎችን እንዲያሳልጥ ብቻ አይደለም፡፡ ዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው ማድረግም ግድ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ መንግሥት የሕዝቡን ባህላዊ ውርስ ማስጠበቅ፣ የአርበኝነትን መንፈስ መንከባከብ፣ የቋንቋውንና የባህሉን የህብር ውበት ማስቀጠል ይጠበቅበታል፡፡

የአንድ ሀገር ዘርፈ ብዙ የአርበኝነት ስሜት ከሕዝብ መንፈስ ውስጥ ከጠፋ ተስፋው ይደበዝዛል፣ ኩራቱም ይመነምናል፣ ብሔራዊ ስሜቱም ይቀዛቀዛል፡ ፡ በውጤቱም ልማትም ሆነ ሀገራዊ የዜጎች ደህንነት ለአደጋ መጋረጡ አይቀርም፡፡

የአርበኝነት መንፈስ የሚጠበቀውና ቀጣይነት የሚኖረው ዜጎች በየተሰማሩበት የተግባር መስክ ከራስ ባለፈ ለሀገር የሚጠቅም ተግባር ፈጽመው ለሚያበረክቱት የአርበኝነት አስተዋጽኦ መንግሥት በዕውቅናና በሽልማት አጅቦ በይፋ ሲያመሰግናቸውና ለልዩ ልዩ ዘርፎች አርበኞች ባበረከቱት አስተዋፅኦ ልክ “ጀግኖቻችን” በማለት በሀገር አቀፍ ደረጃ በሕዝቡ ስም አክብሮቱን ሲገልፅላቸው ነው፡፡ የሲቪክስ ትምህርት ድርሻም እንደገና ተቃኝቶ ሊተገበር ይገባል፡፡

ወጣቶች ትምህርታቸውን ጨርሰው በሰለጠኑበት የሙያ ዘርፍ ወደ ሥራ ከመሠማራታቸው አስቀድሞ ቀደም ብሎ በሀገራችን ይደረግ እንደነበረው የብሔራዊ አገልግሎት ግዳጃቸውን እንዲወጡ ሥርዓት ቢዘረጋ ወቅቱ ለሚጠይቀው የአርበኝነት መንፈስ መነቃቃት ትልቅ ትርጉም ያለው ሥራ መስራት ይቻላል፡፡

የሲቪልና የሙያ ማኅበራት – የሲቪልና የሙያ ማኅበራት በዋናነት የተቋቋሙበትን ዓላማ የሚያስፈፅሙት በወገንተኝነት ለቆሙለት ቡድን ከመሆኑ አኳያ በየዘርፋቸው ከሚወክሉት ቡድንና ሙያ በምሳሌነት የሚጠቅሷቸውን የሀገር የሕዝብ ጀግኖችን ለሕዝብ ይፋ የማድረግ፣ በአቅማቸው ልክና ከመንግሥት ጋር በመተባበር ዕውቅና ሊሰጧቸው፣ ሊሸልሟቸውና በስማቸው መታሰቢያ እንዲቆምላቸው አጥብቀው ሊሟገቱና ሊተጉ ይገባል፡፡

የምርምርና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት – እነዚህን መሰል ሀገራዊ ተቋማት የአርበኝነትን መንፈስ ለማስረፅ የኃላፊነታቸው ወሰን የተመቻቸ ስለሆነ “የክብር ማዕረግ” መስጠቱን አጠናክረው ሊሠሩበት ይገባል፡፡

አገልግሎት ሰጪና አምራች ተቋማት – አብዛኛውን የሀገሪቱን ሠራተኞች አቅፈው የያዙት እነዚህን መሰል ተቋማት በልዩ ሁኔታ ለምርታማነታቸው ስኬትና ለአገልግሎታቸው ውጤታማነት በትጋት የሠሩትንና አዳዲስ አሠራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን ያስተዋወቁትን ባለሙያዎቻቸውን በይፋ ያለ ስስትና ያለ አድልኦ ሊያከብሯቸውና ሊሸልሟቸው ይገባል፡፡

የግልና የመንግሥት የሚዲያ ተቋማት- በየሙያ መስኩ ሀገራዊ የአርበኝነት መንፈስ ለማነቃቃትና የየሙያውን ተጠቃሽ አርበኞች ተግባራት ለአደባባይ ማብቃት ቅድሚያ ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል፡፡

ከራሳችን ተሞክሮ በዘለለ ሌሎች ሀገሮች ያለፉበትንም ልምድ ማየቱ ብልህነት ስለሆነ ሲንጋፖር ጥሩ ማሳያ ስለሆነች የእርሷን ተሞክሮ በአርዓያነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

በዘመናት ውስጥ በተለያዩ ወራሪዎችና የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎች ስትመሳቀል ኖራ በኋላም ቅርቧና ቤተኛዋ ከሆነችው ከማሌዥያ ውህደት በመፋታት በ1965 ዓ.ም ሙሉ ነፃነቷን የተጎናፀፈችው ሲንጋፖር ዛሬ በዓለም ማሕበረሰብ ዘንድ የምትታወቀው “የምድር ገነት ”First World Oasis in a Third World” እየተባለች ቢሆንም እዚህ ደረጃ ላይ ከመድረሷ በፊት አያሌ ውጣ ውረዶችን መቋቋም ግድ ብሏት ነበር፡፡

ሲንጋፖር እንደ ሉዓላዊ ሀገር ከማሌዥያ ሪፐብሊክ ጥገኝነት ተላቃ ራሷን በቻለችበት በ1965 ዓ.ም የሕዝቧ ቁጥር ከሁለት ሚሊዮን አይበልጥም ነበር፡፡ 63 ያህል ደሴቶች ተጣምረው የፈጠሯት ሲንጋፖር ነፃ በወጣችበት ዓመት ይህ ነው የሚባል ኢኮኖሚ ያልነበራት፣ ዜጎቿ በትምህርት ኋላ የቀሩ፣ ሊመነዘር የሚችልና ከድህነት ሊያላቅቃት የሚችል የሚያኮራ የተፈጥሮ ሀብትም አልነበራትም፡፡

ይህንን ያስተዋሉት ሩቅ አሳቢ መሪዎቿ ሀገራቸውን በአጭር ዓመታት ለማሳደግ በቆራጥነትና በትጋት መስራት ጀመሩ፡፡ ከዓለም ማኅበረሰብ ጋር በቀላሉ ለመቀላቀል እንዲረዳቸውም የተዥጎረጎረውን የማንድሪን፣ የማሌይ እና የታሚልን ቋንቋዎች እንደነበሩ አኑረው ብሔራዊ የሥራና የትምህርት ቋንቋቸውን ወደ እንግሊዝኛ ለወጡ፡፡

ዜጎቻቸውም ወደ ሰሜን አሜሪካና አውሮፓ ሄደው እንዲማሩ በሩን ወለል አድርገው ከፈቱላቸው፡ ፡ በተለያዩ ሀገራት ሄደው የመስራት ፍላጎት ያላቸውንም ሁኔታዎቹን አመቻቹላቸው፡፡ እያንዳንድ ዜጋ ሲሸኝም የሀገሩ እዳ እንዳለበትና ተምሮም ሆነ ሰርቶ እንዲመለስ በአደራ ቃል አሰሩት፡፡

ከዓመታት በኋላ ወደ ተለያዩ ሀገራት የተበተኑት ዜጎቿ እንዲመለሱ ሲንጋፖር “የእናት ሀገር ጥሪ አወጀች” ጥሪውን በመቀበልም በርካታ ዜጎቿ ዕውቀታቸውንና ሀብታቸውን ሰብስበው ወደ ሀገራቸው ጠቅልለው ገቡ፡፡

ነገር ግን ተመላሽ ዜጎቿ ሀብት እንጂ ብሔራዊ ስሜታቸው ቀዝቅዞ፣ ዕውቀት እንጂ የክብራቸው ጉዳይ ላሽቆ የማንነት ቀውስ ውስጥ ወድቀው ነበር፡፡ የሀገራቸው አርበኝነት ታሪክ ደብዝዞ፣ የታሪክ ኩራታቸው ደብዛው ጠፍቶ “ባዕድ ባለሀገር” ሆነው አረፉት፡፡ ከሀገራቸው ታሪክ ይልቅ የኖሩበትንና የተማሩባቸውን ሀገራት ታሪክ ማነብነብ ይቀላቸው ጀመር፡፡ በአባት በአያቶቻቸው የተከፈለው መስዋዕትነት ተዘንግቶ እስከ መረሳት ደረሰ፡፡

ይህንን መሰሉን የዜጎቻቸውን ውጥንቅጥ ማንነት ያስተዋሉት ጥበበኛ መሪዎቿ ዜጎቻቸው የገጠማቸውን የማንነት ቀውስ ለመፈወስ አዳዲስ ስልቶችን መቀየስ ነበረባቸው፡፡ ዜጎቻቸው ብሔራዊ ስሜታቸው እንዲያገግምና የአርበኝነት መንፈሳቸው እንዲያንሰራራ በአእምሯቸው ላይ አጥብቀው መስራት ጀመሩ፡፡ “ወደ ቋንቋችንና ወደ እሴቶቻችን እንመለስ” በሚል መሪ መፈክር እየተመሩ ቀን ከሌት በሕዝባቸው አእምሮና መንፈስ ላይ መሥራት ቻሉ፡፡

የሕዝባቸው ብሔራዊ ስሜት እንዲያብብም በመላው ሀገሪቱ የተለያዩ የውይይትና የትምህርት መድረኮች ተመቻቹ፡፡ የትምህርት ቤቶችና የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት አርበኝነትና ብሔራዊ ፍቅር ላይ አተኮረ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎቻቸውና ፓርላማቸው በራሷ ዕሴት፣ ባህል፣ ቋንቋዎችና ብሔራዊ ማንነት ላይ የተመሰረተች አዲሲቷን ሲንጋፖር ለማነፅ ተግተው መረባረብ ጀመሩ፡፡ ቤተ እምነቶች ሳይቀሩ ለአዲሲቷ ሲንጋፖር የአዋላጅነታቸውን ሚና አጥብቀው ተወጡ፡ ፡ ኪነ ጥበባቸው፣ ፊልሞቻቸው፣ ጋዜጦችና ሚዲያው በጠቅላላው ትጋታቸው ወደ ራስ ብሔራዊ ክብር ላይ መመለስና ዜጎቻቸው በሙሉ በየሙያ ዘርፋቸው የሀገራቸው የሲንጋፖር አርበኞች እንደሆኑ ባለመሰልቸት ማስተማር ቀጠሉ፡፡ የውይይቶቹ ርዕስ በመሉ “ለሲንጋፖር መሞት ወይንም ከሲንጋፖር ጋር አብሮ መሞት” የሚል ነበር፡፡

ጥረታቸው አልመከነም በተከናወነው ታሪካዊ ተግባራት የዛሬይቱ ሲንጋፖርን የመሰለች አዲስ ሀገር ግራ ከተጋባቸው ሲንጋፖራውያን ውስጥ ተወልዳ እነሆ “የምድር ገነት”፣ “የአንበሶች ከተማ”፣ “ሚጢጢዬዋ ቀይ ነጥብ” በሚሉ የክብርና የቁልምጫ ስሞችን ልትጎናጸፍ በቃች፡፡

የአርበኝነት መንፈስ ይታደሳል? በትክክል፡፡ ከግሎባላይዜሽን ትሩፋቶች እየተጠቀሙ የራስን ማንነት ማስጠበቅ ይቻላል፡- በትክክል? በአህጉርም ደረጃ ሆነ በዞን ደረጃ ከጎረቤት ሀገራት ጋር አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ መፍጠሩ እንደተጠበቀ ሆነ የራስን ብሔራዊ ጥቅም፣ ባህል፣ ቋንቋና የአርበኝነትን መንፈስ አስቀጥሎ መጓዝ ይቻላል? በሚገባ ይቻላል፡፡ ግን ብዙ መሰራት ይኖርበታል፡፡ ለዛሬይቱ ኢትዮጵያም እያንዳንዱ ዜጋ በተሰለፈበት የሙያ ዘርፍ በአርበኝነት መንፈስ እንዲነቃቃ ሁሉም የድርሻውን ቢወጣ የምንመኛትን ዓይነት ኢትዮጵያ፣ ለሕዝቦቿ ምቹ የሆነች እናት ዓለምን በቅርብ ዓመታት እንደምናዋልድ እርግጠኛ መሆን አይገድም፡፡ ሰላም ይሁን፡፡

አዲስ ዘመን ሰኔ 29/2011

 ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ

ዐብይ አንተም ስማ – እኛም ሰከን እንበል

ዶ/ር ዘላለም እሸቴ – ሁላችንም የኢትዮጵያ ችግር እንዴት እንደሚፈታ ጭንቀት ይዞን ሀሳብ ለማመንጨት በሀገራችን ጉዳይ ተጠምደን ለሌላ ነገር ጊዜ አጥተናል።  ብርቅዬ ምሁራን የኢትዮጵያ እንቆቅልሽ እንዴት እንደሚፈታ የመፍትሄ አሳብ እንደ ዝናብ ዘወትር ያሽጎደጉዳሉ።  ያልተፃፈ የለም።  ያልተባለ የለም።  የኢትዮጵያ ልጆች ችግር ሲፈጥሩ እንዳይፈታ አርገው መቋጠር ይችላሉ።  ያንኑ ያህል ደግሞ ውሉ የጠፋበትን እንቆቅልሽ ለመፍታት ብቃትና ብልሃት ያላቸው ብዙ ልጆች ኢትዮጵያ አሏት።  በኢትዮጵያ ልጆች እጅ ያለ መፍትኤ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለምም ይተርፋል።  ኢትዮጵያ እንዲህ ጥበብና መላን በማፍለቅ የበለፀጉ ልጆች ከቁጥር በላይ ቢኖራትም ያልታወቀላት ሀገር ናት።  ይህ ብቻ ሳይሆን እውቀትና ጥበብ ሳይጎድለን እንደ ጎደለን ራሳችንን ቆጥረን፥ ሌላ መፍትሄ ሀሳብ ለማፍለቅ ከመፍጨርጨር ላንዴም ዕረፍት መውሰድ አልቻልንም።

መፍትሄ እንዳናገኝ የያዘን በሽታችን ነው እንጂ፥ ጉዳዩ የጥበብ ማጣት ወይም ከእውቀት መጉደል አይደለም።  በበሽታ ተይዛ የተኛችው ኢትዮጵያ ከበሽታዋ የምትፈወስበትን መድሃኒት ምርጫችን ከማድረግ ይልቅ፥ ከአልጋዋ ገና ተነስታ ወደፊት ስለምትሰራው ሥራ ዕቅድ በማውጣት ተጠምደናል።

እግዚኦ! ያሰኛል።  ታመናል።  ሁላችንም የኢትዮጵያ ልጆች ታመናል።  ፈውስ የሌለው በሚመስል በሽታ ታመናል። በሽታው ሳያንስ አሁን አሁን ደግሞ የቃላት ውጊያና ጫጫታ ጨምረንበታል።  የድል አጥቢያ አርበኛው ሠርግና ምላሽ ሆኖለታል።  በዚህ ሁሉ ግርግር ውስጥ ዛሬም እንቆቅልሽ የሆነብንን ውስብስብ የኢኮኖሚ፥ የፖለቲካ፥ የዘረኝነት የመሳሰሉትን ችግሮች ለመፍታት እንራወጣለን እንጂ እየሰመጥን እንደሆነ አላስተዋልንም።  የነገሩን ክብደት ብናውቅ ነፍስ አድን ዘመቻን እናስቀድም ነበር።  ግራ የሚገባው ችግርን ከመፍታት በፊት የህልውና ጥያቄ የሆነው በሽታና ውጊያ ስፍራውን ይለቅ ዘንድ አለመታሰቡ ነው።  ስንኖር እኮ ነው ለችግራችን መፍትሄ የምንፈልገው።  በሽታችን እየገደለን ባለበት ወቅት ቅድሚያ ለፈውስና ለተኩስ አቁም ክህሎት ቅድሚያ እንስጥ።  ከቀን ወደ ቀን፥ በሽታችን ከውጊያው ትኩሳት ጋር ተደምሮ ከሰውነት ማንነት እያወጣን፥ እየጨረሰንና እያጫረሰን ባለበት ሁኔታ፥ ችግር ስለ መፍታት ማውራት ምን ይባላል?  አውቀን ሳናውቅ አለቅን።

ለበሽታችን መድሃኒት የሆነው ነገር፥ አንድ ሕፃን የሚያገናዝበው እውነት የሆነው አኳኋን (attitude) ነው።  ከዚህ ቀላልና ተራ ከሆነ ነገር ብንጀምር፥ ጥበብ እያለን ጥበብ እንደሌለን ሆነን የምንኖረው አካሄድ ያቆማል።  ይህ ትንሽ እውነት ወንድማችንን ከማጥፋት ላይ ፊታችንን አንስተን፤ ሁላችንም ፊታችንን ውስብስብ ወደ ሆነው እንቆቅልሾቻችን ዘወር እንድናደርግ አቅም ይሰጠናል።  የዚህ መድሃኒት ፍቱንነቱ በዋነኛነት የሚታየው ከሚያጠፋፋን ከእርስ በርስ ትንቅንቅ መገላገሉ ነው።  ይህን ትንሽ ግርድፍ ሀቅ ንቀን፥ ትልቅና ረቂቅ የሆነውን ጥበባችንን የሙጥኝ ካልን፥ እያለን እንደሌለን ሆነን፥ ከድጥ ወደ ማጡ እንዳንዘቅጥ እፈራለሁ።  እስቲ ለቅምሻ ያህል አስር አኳኋንን እንመልከትና ልባችንን በዚሁ መንገድ ላይ እናድርግ።

ዐብይ ሲታይ: ዶ/ር ዐብይና የለውጥ ሃይሎች ተመከሩ

አኳኋን (attitude) አንድ።  ከመስማት ምንጊዜም አትቦዝኑ።  ለሚቃወማችሁም ጆሮ አትንፈጉት።  በተለይ የአመራር ትኩረታችሁ ፍፁም ፍትሀዊ እንዲሆንና በዚህ ጉዳይ የምትከሰሱበት አውድ እንዳይኖር ከሁሉ በፊት ያለ አድልዎ መሆንን ቅድሚያ ስጡት።

አኳኋን (attitude) ሁለት።  ለመስተካከልና ለማስተካከል ዘወትር ፍጠኑ።  የሚሰራ ሰው ሁልጊዜ ይሳሳታል።  ስለዚህ ምክንያት ሳትሰጡ ለስህተት ሃላፊነትን ውሰዱና በጊዜ አርሙት።  ብድራታችሁን ዛሬ ከሚረዳችሁ የኢትዮጵያ አምላክ እና ነገ ከሚነገርላችሁ ታሪክ ጠብቃችሁ፤ ከትላንት በተሻለ ዛሬ ሁልጊዜ በአዲስ መንፈስ ለሥራ በፅናት መነሣትን አታሰልሱ።

ሕዝብ ሲታይ: በመረዳት እንደግፈው እንጂ በጭፍን አንፍረድበት

አኳኋን (attitude) ሦስት።  እንደ አመፀኛ ዳኛ ፍርደ ገምድል አንፍረድ።  ዶ/ር ዐብይ አንድ ሰው ነው። ዐብይ ማለት መንግስት ማለት አይደለም። ዶ/ር ዐብይ ያለበትን ጭንቅና ተግዳሮት አናውቅም።  ራሳችንን ከጫማው ውስጥ እናስቀምጥና የተጣደበትን እሳት አግለን ለማንደድ ልባችን አይጨክን።  ይህ ሲባል ዶ/ር አብይ ከሕግ በላይ አይነኬ ነው ማለት አይደለም።  ሲሳሳት ማረም ሃላፊነታችን ነው።  ቁም ነገሩ ስንናገር ሚዛናዊ መሆንና፥ በመልካም መንፈስ እርሱን ለማቅናት ካለን በጎ ፍቃድ የተነሣ፥ ቅንነትን መካከለኛ ማድረግ የሃላፊነታችን ሌላኛው ገፅታ መሆኑን ችላ እንዳንል ያስፈልጋል።

አኳኋን (attitude) አራት።  ሁሉንም በልክ እናድርግ።  ዶ/ር ዐብይን እስክናመልከው በመውደድ ንጉሥ ማድረግም ሆነ፥ ሩቅ ቆሞ ጣት በመቀሰር ማጣጣል ሁለቱም ጤነኛ አይደሉም።  እኛው ክበን፥ እኛው ንደን፥ ስራችን ሁሉ የዕብድ እንዳይመስል እንፍራ።

ጠላት ሲታይ: ከማስተዋል እንዳንጎድል ሁልጊዜ እንንቃ

አኳኋን (attitude) አምስት።  የጠላትን ሤራ አንሳተው።  ሰው ሁሉ ሰልፍ ሲወጣ፥ ዘፋኙ ሲዘፍን፥ ባለ ቅኔው ሲደረድር፥ ሴረኛው ከእኛ ጋር አልዘፈነም።  ታዲያ ተንኮለኛው የት ነበር?  ተንኮሉንና ሴራውን እንደ ቦንብ በየስፍራው እየቀበረ ነበር።  ቀስ በቀስ እየሸረሸረ፥ ዶ/ር ዐብይን ከሚወደው ሕዝብ የሚነጥል ነፋስ በመካከል ይሰድ ነበር።  የማይታየው ስውሩ ዕኩይ የሆነው ሤራው ሰምሮለት፥ እርሱ ምክንያት መሆኑ በሕዝብ ዕይታ እንዲሰወር ማድረግ ይሞክራልና እንንቃበት።

አኳኋን (attitude) ስድስት።  ለጠላት ሽፋን አንሁንለት።  ኑሮ ማሸንፍ አነሳስቶን፥ የሤራ ንግድ ትርፍ አምጥቶልን፥ ሀገር በፈጠራ ተረት እያተራመስን የምናገኘውን ብርና ዝና ተንተርሰን የምንተኛ፥ ህሊናችንን ሸጠናልና ሳይመሽብን ወደ ልባችን ቶሎ እንመለስ።  ሳናስተውል ቀርተን፥ የሴረኛው ፊትና ጭንብል ሆነን፥ አጥፊው ህቡዕ ሆኖ እጁ እንዳይታይ መተባበር ይቅርብን።  እውነት እንናገር ካልን መኖሪያውን አትርፎበት ጠብ ከሚናገረው፥ ጠብ ጥሞት የሚሰማው ይበልጥ ይገርማል።

አኳኋን (attitude) ሰባት።  ጠላት መሆንን እንፀየፈውና እንተወው።  እውነተኛው የኢትዮጵያ ጠላት ስጋና ደም ያለው አይደለም።  እኛም የኢትዮጵያ ልጆች ነንና ከዚህ እኩይ መንፈስ መጠቀሚያ ከመሆን ራሳችንን እናስመልጥ።  በሕዝብ ስም፥ በሕዝብ ላይ ቁማር መጫወት ምንም አይጠቅመንምና ይቅርብን። ከእልከኝነት ራሳችንን ታድገን፥ ለምን የግል ጥቅሜ ተነካ ብለን በሕዝብ ስም የሰይጣን እጅና እግር መሆንን አቁመን፥ ከመሃሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንቀላቀል።

ፈጣሪ ሲታይ: አሁንስ ተስፋችን ማነው?

አኳኋን (attitude) ስምንት።  ተስፋ ቆርጠን ያንኑ ተስፋ ቢስነት አንዝራ።  የኢትዮጵያ አምላክ ስንት ጊዜ በተዐምር ኢትዮጵያን እንደታደገ እንዴት ተዘነጋን?  አሁንስ የኢትዮጵያ ተስፋ ፈጣሪ እንደሆነ አናውቅምን?  ኢትዮጵያ አምላክ እንደሌላት ምን ያቆዝመናል?  የጨለመ የሚመስለው ይበራል።  የተበላሸ የሚመስለው ሁሉም ይስተካከላል።

አኳኋን (attitude) ዘጠኝ።  ተዉ የተገላቢጦሽ አናድርገው።  ቤተ እምነት መንግስትን በሞራል እየመራ ለመንግስት ሆነ ለምድራችን በረከት ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ፥ ዶ/ር ዐብይ ለሁሉም ቤተ እምነት በረከት ሆኖ አረፈው።  ይሁንና አሁንስ ለአገር ድነት የማንነሳው እስከ መቼ ነው?  ሃይማኖት ሳንለይ ኢትዮጵያዊ ከሆንን፥ ሁሉም የእምነት አባቶች በተቀናጀ መልክ ለኢትዮጵያ ፈውስ ቢያንስ አንድ ላይ ለወር ፆምና ፀሎት ሁሉም በየቤተእምነቱ እንዲያደርግ በምድራችን ላይ ማወጅ ለምን ተሳናቸው?  ሰው ከአምላኩ ጋር በጥሞና እና በሱባዔ ልቡን ወደ ፍቅርና ይቅርታ መለስ እንዲያደርግ በር ይከፍቱልን ዘንድ አደራ እንላለን።  እንዲህ ቢያደርጉ ወደፊት ለሚካሄደው ብሔራዊ እርቅና መግባባት መንገድ ጠራጊና ፋና ወጊ ይሆናሉ።  የሁሉ ችግር ስርና መሠረት የሆነው መንፈሳዊው ነውና ፊት ፊት እየሄዱ እንዲመሩን ፀሎታችን ነው።

አኳኋን (attitude) አስር።  ፀሎት በሥራ ይገለጥ።  አምላክን ለምነን ስናበቃ፥ የሚያዘንን በስራ ለመግለጥ ለምን አንነሳሳም?  ብዙ ሩቅ ሳንሄድ አምላክ አገራችንን እንዲባርክልን እየጠቅነው፥ እርሱ ከሰጠን ገንዘብ አንድ ዶላር በየቀኑ ለደሃ ሕዝባችን ላለመስጠት ለምን ሰንካላ ምክንያት እንደረድራለን?

ኢሜል፥  Z@myEthiopia.com

ተልባነት – ወደ ዉስጥም ተመልከቱ (ከፈተናዎቻችን)

1. ተልባነት

አማራ ግንባር ቀደም ሁኖ አጥንቱን ከስክሶ ደሙን አፍሦ በጠበቃት አገሩ ላይ ሠርቶ እንዳይበላ ተረጋቶ እንዳይኖር ያፈራዉን ሀብት እንዳይጠቀምበት እረፍት ለመንሳት አቅደዉ የሚሰሩ እና አጠቃላይ የሕይወት ጥሪያቸዉ በአማራ ላይ የሚችሉትን ያህል ጉዳት ለማድረስ በሚጥሩ እኩያን የታሰረበትን ሰንሰለት በሃያላን ልጆቹ በጣጥሶ በመጣል ላይ ነዉ። በዚህ እልህ አስጨራሽ የህልዉና ተጋድሎ መሀል ዝናና ገንዘብ ፈልገዉ ስልጣን ተጠምተዉ የአማራን ህዝብ ለጠላቶቹ ለመሸጥ እንደዉሻ ጂራታቸዉን ሲቆሉ ማየት ልብ ይሰብራል። እንደ ተልባ ስፍር ላይ እየደረሱ መመለስና ካስቀመጧቸዉ የክብር ቦታ ላይ ተንሸራተዉ መፈጥፈጥ ምርጫቸዉ የሆኑ « ወንዝ የማይሻገሩ» ወረተኞችን እያየን ነዉ።

በብዙ ሚሊየን የሚቆጠር አማራ ከነሱ በዉቀትና በአስተዉሎት እንደሚበልጥ አያዉቁም። ተቅለብልበዉ ከፊት ስለሆኑና ህዝቡ እዉቅና ስለሰጣቸዉ « ወደርየለሽ/irreplaceable>> ነን ብለዉ ያስባሉ። ስላከብርናቸዉ የናቁን ስለታገስናቸዉ ያሞኙን የመሰላቸዉ የቤት ዉስጥ አረሞች ከትግላችን ባቡር ዉስጥ ወደ ኋላኛዉ ፉርጎ መገፋት አለባቸዉ።

2. ጎጠኞች

ከየጎጣቸዉ ላይ ተቸንክረው ለአማራ የህልዉና ትግል ጋሬጣ በመሆን ላይ ያሉ እነ« ምንጭ አባዩና ዳቦ ፍሪዳዉ» ወደ ጎን ሁነዉ ለአማራ ህዝብ ቀናኢ የሆኑ ልጆች በሁሉም ዘርፍ ወደፊት መምጣት አለባቸዉ። ወላድ በድባብ ትሂድ እንጂ አማራ አይምሯቸዉ የሰላ አንደበታቸዉ የተባ ህሊናቸዉ የጸዳ ልጆች አሉት። አንዱ ሸርተት ሲል ሚሊየኖች ብቅ ይላሉ። ማናችንም ባማራነት ዉቅያኖስ ዉስጥ ያለን ጠብታዎች ነን። ከባህሩ ስንወጣ ባህሩ አይደርቅም እኛ ግን እንተናለን። ወንዜንት፣ ወረዳዊነት(ወራዳዊነት) ሃያ አራት ሰአት በሚያናፉ ጠላቶች ለተከበበዉ አማራ ላንድ ቀንም አይመከርም። ይህን ከማድረግ የማይመለሱ ወንድሞች የገነባንላቸዉን ስም አፍርሰን ያለብሳንቸዉን ክብር ገፈን ወደ እዉነተኛ ወረዳቸዉ/ቦታቸዉ ተመልሰዉ በትከክለኛ አማራዎች መተካት አለባቸዉ። ልብ በሉ ብዙ ትንታግ አማራዎች በተልባዎቹ ተጋርደዋል። ገለል በሉላቸዉ።ቶሎቶሎ ተንሸራተቱ።ቦታዉ ይፈለጋል።

ኢትዮጵያ ዉስጥ እንደ አማራ አንድ የሆነ ህዝብ የለም። ይሄ አንድነት የተጠናቀቀዉ ከብዙሺህ ዓመታታ በፊት ነዉ። አማራ አንድ ባይሆንማ ሌላዉን የኢትዮጵያ ክፍል አንድ ለማድረግ ግንባር ቀደም ሚና ባልተጫወተ ነበር።ብዙ ብሄርተኞች ብዙ ሰንደቅ አላማ አቸዉ። በየትም የሚኖር አማራ ግን ባንዲት ሰንደቅ አላማ ያለምንም ልዩነት ይስማማል።በስነ ልቡናዉ በባህሉ absolutely indistinguishable የሆነ ህዝብ ያለው ጥሩ ቢባል ከፍት የሚሰለፈዉ አማራ ነዉ።

3. አድፋጭነት

ብዙ የአማራ ምሁራን አሉ።ብዙ የአማራ ባለ ሀብቶች አሉ። ብዙ የአማራ ጋዜጠኞች አሉ። በዓለም የሚሆነዉን ሁሉ በትነዉ የሚያዉቁ ምጡቅ አማራዎች አሉ። አሁን ለአማራ ህዝብ እየትዋደቀ ያለዉ ግን ወጣቱ መጠነና ገቢ ያለዉና በትምህርት ከገፉት ጥቂቶች ናቸዉ። ሌላዉ ዳር ሁኖ ይመለከታል ። ይህ መቆም አለበት። አማራነት ማንም ለማንም ብሎ የሚሳተፍበት የቤት ሥራ አይደለም ።ለየራሳችን ህልዉና ለልጅልጆቻችን ህልዉና የሚደረግ ራስ አገዝ ዘላለማዊ ፕሮጀክት ነዉ። አሁን ችግሩ ቤንሻንጉል ባለዉ አማራ ሊሆን ይችላል።ነገ ግን በሁሉም አማራ ላይ ነዉ።ዛሬ ወለጋ ባለው፣ ቡኖ በደሌ ባለዉ ጂማ ባለዉ አማራ ላይ የሚፈጸም ኢሰባዊነት ነገ ወደ ሁሉም አማራ እንዳይዛመት መመክት የሁሉም ሀላፊነት ነዉ። ዛሬ በሀረር በድሬዳዋ ያለዉ የአፓርታይድ ሥራት ካገራችን እንዲጠፋ ካልታገልን ነገ ሁሉንም ቦታ ያዳርሳል። አንድ ጀርመናዊ ጋዜጠኛ «መጀመሪያ ሶሻሊስቶችን አሰሩ አንገላቱ ገደሉ ።ምን አገባኝ ብየ ዝም አልሁ። ሶሻሊስት አይደለሁማ! ቀጥለዉ የህብረት ሠራተኞች አሰሩ አንገላቱ ገደሉ። አሁንም ዝም አልሁ።እኔ በሠራተኞች ማህበር የለሁበትማ! ከዚያ አይሁዳዉያንን አሠሩ አሰቃዩ ገደሉ።ያኔም ዝም አልሁኝ።እኔ አይሁዳዊ አይደለሁማ። በመጨራሻ እኔን ያዙኝ ። አሁንም ሁሉም ተግዞ አልቋልና የሚናገርልኝ ከየት ይምጣ!First they came for the socialists, and I did not speak out—because I was not a socialist.Then they came for the trade unionists, and I did not speak out— because I was not a trade unionist.
Then they came for the Jews, and I did not speak out—because I was not a Jew.Then they came for me—and there was no one left to speak for me

የአማራ ህዝብ የሚያደርገዉን ተፈጥሯዊ ተጋድሎ ባለን አቅም ሁሉ ማገዝ «ምን አገባኝ» የሚባልበት ጉዳይ አይደለም።

4. ዝግነት

የትኛዉም ከአማራ ጥቅም ጋር የሚያያዝ ድርጅት ለአማራ ህዝብ የሚሠራዉን ሥራ ግልጥ ማድረግ ላዳዲስ ሰዎች እና ሀሳቦች ክፍት መሆን አለበት። ብ አዴን የሚባለዉ አማራን ለመታገል የተፈጠረው ድርጂትም ቢሆን በ አማር ህዝብ ወንበር ላንድ ቀንም መቀመጡ ካልቀረ ለአማራዎች ክፍት መሆን አለበት። አማራን የሚጠሉ እና ከአማራ ጠላቶች ጋር «ባንድ ቂጥ ካላራን» እያሉ የሚልወሰወሱ ከንቱዎች ከአማራ ትክሻ መዉረድ አለባቸዉ። ይሄን የሚያደርገው ሌላዉ አማራ ነዉ። ባዴን ፈርሶ ካልጠፋ ራሱ ወደ አማራነት እስካልመታ ድረስ ደፋር አማራዎች ወደ ድርጂቱ መሄድና መቀየር አለባቸዉ። የአማራ ህዝብ በባዴን ላይ መወሰን ያለበት ሰአት ላይ ነዉ። ወይ ጠርቶ ለ አማራ እንዲሰራ ማድረግ(የተማሩ ሰዎችን በማስገባት) ካልሆነ በዉስጡ የተሰገሰጉ አዳዲስ በረከት ስሞናች ተዳእሰ ጥንቅሹዎች ብቅ ብቅ እያሉ ስለሆነ ለሌላዙር ባርነት እያዘጋጁት እንደሆነ ይወቅል። ዝግ መሆን መዛግን ያመጠላ። መሽተት ያልፈለገ ላዳዲስ አሳቦች ራሱን ከፍት ያድርግ።
ሌሎች አማራዊ ተቋሞችም አሰራሮችቻእዉ አዳዲስ አሳብ ለመቀበል እና የተማሩ አማሮችን ከፊት ለማሰለፍ አሰራር መዘርጋት አለባቸዉ። ትግላችን በዉቀት በጥበብ በጀግንነት በሀብት የሚደረግ ማህበረሰባዊ ግብግብ ነዉ።

5. ወሰድ መለስነት

አማራን የሚታገሉት አይተኙም። ለአማራነት የሚታገሉት ግን ብቅ ጥልቅ ይላሉ ። ትግል ያዝ ለቀቅ ሲያደርጉት ይማግጣል።ግለቱ ሳያበርድ መቀጠል አለበት። በያንዳንዱ ቀን የምንሰራዉ ተደምሮ ነዉ እስካሁን ባጭር ጊዜ የተጎናጸፍናቸዉ ድሎችን ያገኘነዉ። ከጽናት የተለየ ትግል የትም አያደርስም። ጽኑ እንጽና!

(Struggle leads to progress and progress leads to success)

6. ትልቁን ስዕል አለመረዳት

የአማራ ትግል ዋና አላማ አማራ በርስቱ ተሹሞ በታሪኩ ተከብሮ በማንነቱ ታዉቆ የሚኖርበት ምህዳር መፍጠር ነዉ። ሁሉም እንቅስቃሴ ከዚህ ታልቅ ስ እል አንጻር መቃኘት አለበት።ይሄ የትግላችን አዉራ መንገድ ነዉ።ትናንሾቹ መንገዶች ለታላቁ አማራዊነት መንገድ ይገብራሉ። ጥቃቃን ህልሞች ለታልቁ ህልም ይሰዋሉ። እርምጃዎች ሁሉ ወደዚህ ማማ ከፍታ የሚያወጡ ደረጃዎች ናቸዉ።

7. አዳዲሶች መርሳት

ትግል ሂደትም ህይወትም ነዉ። አማራነት የሆነ ወቅት ተሰብኮ የሚያበቃ የሚመስላቸዉ አሉ። የሰሙት እንዲጸኑ ያላወቁት እንዲያዉቁ የተጠራጠሩ እንዲገለጥላቸዉ ደግመን ደጋግመን አማራነትን እንሰብካለን።ህጻናት ይወለዳሉ። በየጊዜዉ ሚሊየን ወጣቶች ለአቅመ ፖለቲካ ይደርሳሉ። ትዉልድ እንደወንዝ ነዉ የሚፈሰዉ ።የሰማዉ ሂዶ ያልሰማዉ ይመጣል። አማራነታችንን ከትዉልዶች ወንዝ ዳር ቁመን ከመሰንቋችን ጋር እናንቆረቁረዋለን።

አማራ በሃያላን ልጆቹ ታሪኩን ያድሳ (Amelework Shewangizaw)

#ቤተ-አማራ

መራራ እውነት በኢትዮጵያ ታሪክ

መራራ እውነት በኢትዮጵያ ታሪክ
በሚል ርዕስ መምህር ታዬ ቦጋለ ለጻፉት መጽሐፍ
በተዘጋጀ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት የቀረበ አስተያየት
ሰኔ 22 ቀን 2011 ዓ.ም 
አዲስ አበባ (ራስ ሆቴል)
ወርቅዓለማሁ ንጋቱ

ታሪክን ከነስህተቶቹና ስኬቶቹ በመቀበል ማወቅና መማር የሚያስፈልገው፣ለዛሬ ስምረትና ለነገም ተስፋ ያስቀመጠው ፣መጪውን ጊዜ የተሻለ ለማድረግ የሚያስችል ኃይል፣ ለዛሬ ማንነትና ለነገ ብሩኅ ግንኙነት የሚያስቀረው በረከት ስላለው ነው፡፡
በተለይ በኢትዮጵያ ሁኔታ ከታሪካችን ጋር ተያይዞ ባለው መረዳት የተለያዩ ጽንፎች የመኖራቸው እውነታ ዘመናችንን ዕጅ ለዕጅ በመያያዝ በሠላም፣ በፍቅርና በአንድነት ከመምራት ይልቅ በጥላቻ፣ በንትርክ ፣ በጥርጣሬ፣በመቆሳሰልና በመገዳደል መቀጠሉ፣ውጤቱ ተስፋ አስቆራጭ መራራ የድህነት ጽዋን እንድንጎነጭ አስገድዷል፡፡ ትናንትን መድገም ወይም የጊዜን ወደፊትነት ሕግ ሽረን ፣ምንጠላውንም ሆነ ምንወደውን ልንደግመው ባይቻልም፣ ጥቂቶች ዛሬን በትናንት ሂሣብ ለማወዳደቅ ብዙሃኑን ፍዳ እያበሉ የሚገኝበት አሳዛኝና አሳፋሪ ምዕራፍ፣ የሁላችንም ኢትዮጵውያን የዘወትር ዐቢይ መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኗል፡፡
ታሪክ ትናንት በብዙ ትውልዶች ውጣ ውረድ ያለፈ ረዥም ማህበራዊና ተፈጥሯዊ ሂደት ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ነው ፣ወደ ትናንትና ሊቀለበስ አይችልም፡፡ ትናንትም ያለፈና ስለነገም የትናንት ትውልዶች ተስፋ የማያደርጉበት እውነታ ነው ታሪክ፡፡ ስለ ታሪክ ያለንን የምዘና ፋይዳ በዚህ መነጽር ከተመለከትን አንዱ በክብርና በኩራት ሌላው ደግሞ በቁጭትና በጸጸት የሚያስቡትና የሚገልጹት የሰው ልጆች ሕይወት ዘርፍ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ነባር ሕዝቦች የብሄራቸው ወይም ጎሳ መሪያቸው ማንም ይሁን ማን ፣ለዘመናት እርስ በርስ ያስተሳሰራቸው የፈጠሩት ባህል፣ልማድ፣ ያቆራኛቸው ጥብቅና ረቂቅ ሥነልቦናዊ ትስስር አለ፡፡ አብረው እየሰሩ፣ እየነገዱ፣ እየተዋጉ፣ እየተጋቡ በሺ የሚቆጠሩ ዘመናት በማኅበራዊ መስተጋብር ተቀላቅለው ጉራጌነታቸውን፣ አማራነታቸውን፣ ትግሬነታቸውን፣ ኦሮሞነታቸውን ፣ ጋምቤላነታቸውን፣ ሶማሌነታቸውን፣ አፋርነታቸውን ወዘተ እንደያዙ በልዩነት የተዋበ፣ በጋራ የሚታወቁበት ኢትዮጵያዊ የወል ማንነት ፈጥረዋል፡፡ የተዛባ የታሪክ ትርክታቸውን ለፖለቲካ ዓላማቸውና ቅጥ ላጣ የሥልጣን ጥማቸው ማሳኪያ ማድረግ የሚሹ የጎሳ ፖለቲከኞች ሊቀበሉት የማይፈልጉት፣ ግን ሕይወታቸውና መገለጫቸው ሆኖ የሚኖሩት ይሄ ሂደት አሁንም ድረስ አለ፣ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡
ታሪካዊውን ኢትዮጵዊነት ለማደብዘዝ፣ ጥቂት የጎሳ ፖለቲከኞች ብድግ ብለው ራሳቸውን የዚህ ወይም የዚያ ብሄር ወኪል በማድረግ የራሳቸውን ፍላጎት ‹‹የብሄሩ ጥያቄ›› እንደሆነ በማንገብ፣ ማንነት የአንድ ብሄር አባላትን ብቻ የሚያቅፍ አድርገው በማቅረብ፣ የኢትዮጵያን የረዥም ጊዜ የተከበረ ታሪክ በውስን የትንታኔያቸው ፍረጃ በመበየን ትልቅ ስህተት በመፈጸም ላይ ይገኛሉ፡፡
በጽንፈኛ ብሄረተኝነት ታውረው ታሪካችን የፈጠረልንን የአሁን ኢትዮጵዊ ማንነት በመካድ የሁሉንም ኅልውና በሚያናጋ ድርጊት ተጠምደዋል፡፡ ለዚህም ታሪክ አባይ ግብር፣ ሽፋን ይሆናቸው ዘንድ ትናንት የነበረውን አንድ አስከፊ ገጽ ብቻ ለይተው ከልክ በላይ በማራገብ ፣ሠላማዊ አብሮነትን ልማትና ተስፋችንንም በጨለምተኛ ከፋፋይነት ለማዳፈን ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ታች ሲሉ ይታያል፡፡ 
ታሪክን የጠሉና ከታሪክ የተጣሉ ከየትኛውም ጎሳና ብሄረሰብ የወጡ ጽንፈኛ ብሄረተኞች ለአዲሱ ትውልድም ይሄንኑ የተሳሳተ አስተሳሰብና አመለካከት በመመገብ ረገድ ያለ እረፍት በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ እነዚህ ራሳቸውን በምሁርነት ማዕረግ የሚጠሩና የሚያስቀምጡ ሀኬተኞች፣ በቋንቋ መለያየታችንን እንደ ሀብትና ውበት ተቀብለው፣ በየቋንቋው ውስጥ ያለውን ዕውቀትና ጥበብ አንጥሮ በማውጣት እንወክለዋለን የሚሉትን የኅብረተሰብ ክፍልንም ሆነ መላውን ኢትዮጵያዊ ከመጥቀም ይልቅ፣ ቋንቋን የጠብና የመለያያ መሣሪያ በማድረግ ወጣቱን ትውልድ በማደናገር ረገድ አይዘልቅም እንጂ ለጊዜውም ቢሆን የተሳካላቸው ይመስላል፡፡ 
በተለይም እንደእኔ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ (አጋነንክ ባልባል አዳም ከተፈጠረ ጀምሮ) እንደ ኦሮሞ ሕዝብ ወደር የሌለው ባሕላዊ የአስተዳደርና የፖለቲካ ድንቅ አገር በቀል አስተዳደራዊ ሥርዓት የዘረጋ ስለመኖሩ የሚጠራጠር ሰው ፣ ሁኔታው ልብን በሚነካ ሀዘን እንደሚደቀድቅ ይታመናል፡፡ ዛሬ ቀለም ቀመስ ልጆቹ አስቀድመው ‹‹ የኦሮሞ ገዳ ሥርዓት በማይታይ ቅርስነት በዩኔስኮ ይመዝገብልን›› ብለው ወደ ዓለም አቀፉ ተቋም ከመጮኽ ይልቅ፣ በጥልቅ መርምረውና ዘመኑን በሚዋጅ አግባብ አዘምነውት ትሩፋቱ ለኢትዮጵያውያን፣ ለአፍሪካና ለዓለምም በደረሰ እንዴት መልካም ነበር፡፡
በዚህ ዘመን መልስ ያጣሁለት ጥያቄዬ ፣ ምነው ይህንን ህዝብ የሚመጥን የፖለቲካ ፕሮግራምና ዓላማ ያለው የበቃ ፓርቲና ተጽዕኖ ፈጣሪ ፣ሩቅ አሳቢ መሪ እንዴት ሊፈጠር አልቻለም ? የሚለው ነው፡፡ ልጆች አባቶቻቸውን አልሰሙም ይሆን ? ወይስ አባቶች ለልጆች እንዲሰርጽ አድርገው አልተናገሩም ? እስኪ የባዕድ ርዕዮተዓለሙንና ፍልስፍናውን ተወት በማድረግ፣ ወደ ቦረናና ጉጂ ባሕላዊ ማኅበረሰብ ወርደን በአገር በቀል አስተዳደራዊ ጥበባቸው ሥልጣን እንዴት እንደሚከፋፈሉና እንደሚጋሩ፣ ያለሁከት ወቅት ጠብቀው በትረ-ሥልጣኑን እንዴት እንደሚለዋወጡና ኅ/ሰቡም በፍጹም ልቡ እንዴት እንደሚምናቸው እንመልከት፡፡ ከዚህ ገሃድና አኩሪ እውነታ ጀርባ፣ ተምሬያለሁ ተመራምሬያለሁ የሚል፣ ልብና ልቦናውን በጥላቻ፣ በፍቅረ-ንዋይና ሰቀቀነ-ሥልጣን የሞላው የጎሳ ፖለቲከኛ፣ምንያህል ልቦናው ወደ መንደር ደረጃ ጠቦ እያደረሰ ያለው ጥፋት፣ ለኅሊናና ለታሪክ ፍርድ ፣ሞትና መቃብር በእማኝነት የሚቆጥሩት የውርደት ሪከርድ እንዳስመዘገበ መግለጽ ለማንኛችንም ግልጽ የአደባባይ ትርዒት ነው፡፡ 
ዛሬ የወገኖቹን ደም በከንቱ ከሚያፋስስ ነውጠኛ አማራጭ ይልቅ፣ በቀናው የመግባባት ፣ የመከባበርና የመረዳዳት መንገድ ቢሰለፍ፣ እወክላቸዋለሁ ከሚላቸው ወገኖቹ እግር ስር ቁጭ ብሎ ከዳበረ ዕውቀታቸው ቢማር ፣ከምን ‹‹ነፃ›› ሊያወጣቸው እንደሚገዳደር በአስቂኝ ሁኔታ ለመረዳት ዕድል ባገኘ ነበር፡፡ ቀደምቶች ከፈጣሪ የተሰጣቸውን የዕውቀት ፀጋና በረከት ቢያውቅ ቢያከብረውም ፣ከሥልጣንና ሀብት የበለጠ ክብር የሚያጎናጽፈው ማዕረግ ባገኘ፡፡ ሲሆን ሚታየው ግን ተቃራኒው ነው፡፡ 
በሠላም ከወገኖቻቸውና ከመላው ዓለም ጋር በፍቅርና በትጋት መኖር የሚገባቸውን የብሄረሰባውን ወጣቶች ልብ በጥላቻ መሙላት፣ ማስጨነቅና ግራ ማጋባት፣ በየትኛውም ሚዛን ተገቢ የሚሆንበት ዕድል ባይኖርም ሲያደርጉት ግን ይታያል፡፡ ሁልጊዜ በስሜታዊነት ተናግሮና ሰንዝሮ በመፀፀት ከማጎንበስ ይልቅ ፣ ቢመርምና ትዕግሥትን ቢፈታተንም ከፍጻሜ በፊት አብዝቶ ማሰላሰል ለሁሉም እንደሚበጅ ይታመናል፡፡ 
ቀደምት ኢትዮጵውን የኖሩበት አገረ-ምድር አሁን ያለውና ወደፊትም የምንኖርበት መሆኑን ዓለም ሁሉ የሚያውቀውና የሚመሰክረው ገሀድ እውነት ሆኖ ሳለ፣ ዛሬን እንዴት መኖር እንዳለብን በማያመለክት የክፋት አቅጣጫ እየገፉ እንዳችን ከሌላው ወገናችንና ቤተሰባችን እንዳንደራረስ ከውስጣቸውም ሆነ ከውጪ ደመኞች በሚፈጠር ግፊት ስለመለያየት ተግተው ይሰራሉ፡፡ በታሪክ ፀብ ምክንያት፡፡
አብሮ አለመኖር ለተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችም ሆነ ለጠቅላላው ሕዝብ ፍላጎትም ሆነ ችግር መፍትሄ እንደማይሆን ቢያውቁም ፣ ትናንትም ዛሬም በተቃራኒው ያለዕረፍት ይሰራሉ፡፡ የኛም የነሱም የሆነውን የጋራ ታሪካችንን ባለመቀበል፣ ማንም ሊለየውና ሊለውጠው የማይቻለውን ሕብረ ብሄራዊ የሆነውን ውብ ኢትዮጵዊነት፣ ለዚያውም በ‹‹ነፃነት›› ስም የመኮነናቸውና የመጥላታቸው ውጤት ምን እንደሆነ ከየክልሉ በየቀኑ የምንሰማውና የምናየው፣ ሰብዓዊነትን ያዋረደ አሳዛኝ ክስተት ሆኗል፡፡ 
የጎሣ ፖለቲካ አራማጅነት ፣ትናንት ከነበረና ዛሬም እየተሳተፍነው ካለ ታሪክ መጣላት ፣ራስን ያለማወቅና ማንነትን የመክዳት ያህል ከባድ ከመሆኑ በላይ፣ አይደለም ሰፊ ማኅበረሰብን ግለሰብን እንኳ የመቆሚያና የመለያ መሠረት እስከማሳጣት የሚወርድ፣ አበሰኛ የአስተሳሰብ ዝንፈት ነው፡፡ በአንድ ኢትዮጵያዊ የማንነት ዘርፈ ብዙ ሕይወት ውስጥ በባህሉ፣ በሥነ-ልቦናውና በደሙም ተዋሕዶ ያለውን ኦሮሞነት፣ አማራነት፣ ትግሬነት፣ እስላምነት፣ ክርስቲያንነት የቄፈታነት፣ እንደምን ባለ ምድራዊ ጥበብ መለየት ይቻላል ?
ነፃነት፣ ፍትህ፣እኩልነት፣ ብልጽግና ለእያንዳንዳችን፣ ለሁላችንም ኢትዮጵውያን ያለልዩነት የሚገቡን ሆነው ሳለ፤ እንወክለዋለን ወይም ቆመንለታል ለሚሉት የተለየ ብሄረሰብ ወይም ጎሣ ከሱም በቤተሰብ ደረጃ ወርደው ከአንዱ ነጥቀው ለሌላ፣ ከልጅ ነጥቆ ለአባት፣ ከሚስት ነጥቆ ለባል የሚሰጡት ዓይነት የመሆኑ እንቆቅልሽ ደግሞ፣ ግራ አጋቢና ከግርምትም በላይ፣ የሚባል ሚያሳጣ መሆኑን፣ በልቅሶም ሆነ በዘፈን ለመግለጽ የሚቸግር የመሆኑ ነገር፣ የአደናጋሪነቱን መባባስ የት እንደደረሰ ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡
የጋራ መገለጫ የሆነ የኢትዮጵዊ ማንነት ፣የተመሠረተበትን ዕምነት ባህልና ወግ፣ ማለትም በሀዘንም ሆነ በደስታ፣ በሠርጉም ሆነ በለቅሶው፣ በልደቱ፣ በምርቃቱ፣ በደቦው በጉዲፈቻው፣ በሰንበቴውና በተዝካሩ፣ በሠደቃውና በዘካው፣ በእነዚህና በሌሎችም የመንፈስና የነፍስ መጋራትና ጉድኝቶች የተጣመረ ተራክቦ ፣በታሪክ ዘመናት ሁሉ በውስጣችን አትመው ያስቀመጡት የማይነዋወጽ የአንድነት ፣የኑሮ መርህና ፍልስፍና ፣ አይደለም ለምድሩ ለሠማዩም መተማመኛችን የመሆኑን ነገር ቢያስተውሉ፣ ዛሬ ለዛሬው ትውልድ በሕብረት ልንሰራ የሚገባንን በማደነቃቀፍና በማጓተት ሊያውኩን ባልደከሙ ነበር፡፡ ከታሪክ ተጣልቶ ትውልድ ላይ ቀን ማጨለም ማለት ይህ ነው፡፡ 
በጎሣ ጥላቻ ሆድና ጀርባ ሆኖ መኖርና መጠላለፍ ምን ያህል ጎጂ እንደሆነ፣ የደረሰብን አሳምረን ከነህመሙ አይተነዋል እናውቀዋለን፡፡ የትናንት ታሪክ ፣ የዛሬ ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶቻችንና የነገም መድረሻ ግባችን፣ መነሻና ዕምብርት ከመሆኑ አንጻር ፣የጋራ ሀብታችንን የኢትዮጵያን ልዕልና ባከበረ/በተቀበለ ሚዛናዊነት ልናውቀውና በተግባራዊ ትምህርት ሰጪነቱ ልንገለገልበት በተገባ፡፡ እውነተኛ የታሪክ ምሁራን ሆይ የፍርሃት ካባችሁን በማውለቅ የሁላችንም የጋራ ሀብት ስለሆነው ታሪክ ወደ አደባባይ ወጥታችሁ ለትውልዱ ለመንገር ተነሱ፡፡
አንድ ሆነን በሠላምና በፍቅር መነጋገር የተከለከልን እስኪመስል ድረስ፣ ጫፍና ጫፍ ይዘን ከተማ ገጠሩን፣ ተማሪ ሠራተኛውን በጠቅላላው አገር ምድሩን በጥላቻ፣ በመለያየት፣ በዕምባና በደም በክለን ስናበቃ፣ እንደ እንደበጎ አድራጊ ፣ያለሀፍረት በሸንጎ ፊት የምንቆምና የምንናገር፣ የገዛ ወገናችንን ቅስም ሰብረን ፣ደርሶ እንደ ጥሩ ሕግ አስከባሪና ፍትህ አደላዳይ የምናስመስል፣ ባቃጠልነው፣ ባፈረስነው፣ ባወደምነው፣ በገደልነውና ባስገደልነው ሳንፀፀትና ሳናፍር፣ በየሚዲያው አደባባይ በድል አድራጊነት መንፈሥ የምንቦርቅ፣ በየማዕዘኑ በዘር ጥላቻ ተሰነካክለን ፣ለአዲሱ ትውልድ የምናቀርብለት ስጦታ ዱባ ሲባል ቅል፣ ሎሚ ሲባል ዕምቧይ እየሆነ የዓለም መዘባበቻና የትውልዶች ማፈሪያ የመሆናችን ነገር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ 
ወገኖቼ ! በጎሳ ተለያይቶ በጋራም ይሁን በተናጥል ስኬታማ መሆን እንደማይቻል ለመረዳት፣ በቂ ጎጂና ከንካኝ መክሸፎች በየዘመናቱ አስተናግደናል፡፡ ግን የሚበቃን መቼ ይሆን ? አሸናፊ በሌለው የርስ በርስ ጦርነት መቆራቆሳችን ምን አተረፈልን ? ግዴለም አባቶቻችን ወዳቆዩልን ወደ ቀድሞ ፍቅራችን እንመለስ፡፡ ይሄ አማራ፣ኦሮሞ ፣ትግሬ፣ሱማሌ ፣ሲዳሞ፣ ወላይታ አፋር በመባባል፣ ከዚህም ዝቅ ብለን ከኦሮሞም ጉጂ ቦረና፣ ወለጋ አሩሲ፣ ከአማራም ሸዌ ጎንደሬ፣ ወሎ ጎጃሜ፣ ዝቅ ሲልም ቡልጌ ተጉለቴ፣ ዳሞት ጋይንቴ፣ በአፋሩም በሱማሌውም በሌላውም ሁሉ እንዲህ በሽርፍራፊ እየተቀናነስን፣ በወረደ አስተሳሰብ መነታረኩ እስከመቼ ?? ከታሪክ በመማር ቀደምቶች ያቆዩልንን መልካሙን በመኮትኮት፣ የቆሰለውን በማከም፣ ክፉውንም በመንቀል እንትጋ፡፡ ከሁሉም በላይ በኛና በልጆቻችን የወደፊት በተስፋ ላይ እንስማማ፡፡ በፍቅር አንድ ከሆንን ፣በሠላምና በብልጽግና ፣ከነበረውም የተሻለ በዓለም ፊት እናበራለን፡፡ በልጆቻችንና በልጅ ልጆቻችንም ፊት ሞገስ ይሆንልናል፡፡
ልብ በሉ ! በምጥ የፈሰሰው የወላድ እናቶቻችን ደም፣ በዚህች ምድር ሰርጓል፡፡ በጀግንነት፣ በፍቅር፣ በክብር፣ በችግርና በሀዘንም የኖሩና ያረፉ አባቶቻችን፣ ወንድምና እህቶቻችን አጽም በአፈሯ ውስጥ አለ፡፡ ሕይወት አስተሳሳሪ እትብታችንም በዚህች ቅድስት ሀገር ተቀብሯል፡፡
ኢትዮጵያውያን ልባችን በፍቅር፣ በተስፋና ትዝታ ሠንሠለት፣ከሀገራችን ሁለንተና ጋር በብርቱ ተቆራኝቷል፡፡ ለዚህ ነው ሞትን ያህል የፍጻሜ ዕዳን በናቀ ጽኑ ጀግንነት የምንወድቅላትና፣ሌሎችን ግር በሚያሰኝ ትንግርት አብዝተን የምንወዳት፡፡ ለዚህ ነው ዕጅ ለዕጅ ተያይዘን ትውልዳዊ ቁም ነገር ለመሥራትና ቋሚ አሻራ ለመተው በአንድነትና በፍቅር ደፋ ቀና የምንልላት፡፡ ‹‹..ፍቅር የሁሉ ነገር በኩርና ማሰሪያ ነው፡፡›› እንዲል መጽሐፍ፡፡
የዛሬ ኢትዮጵያውያን ቀደምት ወላጆቻችን ያቆዩልንን፣የአብሮነት ውበትና ኃይል፣ለዘመናት ደክመው በውስጣችን ያነጹት፣ ጉራማይሌ ሕብረ-ብሔራዊ ማንነት፣የዕውቀትና ንጹሕ የሰብዓዊ አመለካከት ትሩፋቶች፣ በውስጣችን ምንጊዜም ይኖራሉ፡፡ለልጆቻችንና ለልጅ ልጆቻችን ካላስተላለፍናቸው ግን ይጠፋሉ፡፡ ስለዚህ ዘወትር በምንምና በማንም በማይነዋወጽ ሥጋዊና መንፈሣዊ ሕይወት፣ እርስ በራሳችን እንከባበር፣እንዋደድ፡፡ ሌሎችንም እንዲሁ በፍቅር፣በእውነትና በአክብሮት እንቅረብ እንያዝም፡፡ ለሺህ ዘመናት ከተቀመመ ኢትዮጵያዊነት የወረስነው መለያ ቅርሳችን ይሄው ነውና፡፡
በመጨረሻም ! በሥጋ ባልተወለድንበት፣ በአያት ቅድመ-አያቶቻችን ዘመን፣ እኛን በፀነሰ የኅልውናቸው ማኅጸን ውስጥ ነበርን፡፡ በዚህም አማካይነት የእነሱንና የሀገራችንን ፍቅርና በረከት ሁሉ፣ ልክ አብረን ያለን ያህል ተቋድሰናል፡፡ የዚህን እውነተኛ ትስስራዊ የፍቅር ምሥጢር ልባችን በትክክል ያውቀዋል፡፡ ወደፊትም በማንኖርበት የትውልዶች ዕድሜ፣በሥጋዊ አካል ባንኖር እንኳን፣በልጅ ልጆቻችን የመንፈሥና የደም ጽኑ ኢትዮጵያዊ ቅስም ውስጥ፣በግልጽና በስውር በታሪክ ዘላለም እንኖራለን፡፡