Category Archives: opinion/ ምልከታ

ይህ ገጽ ሙሉ በሙሉ ነጻና የአዘጋጁን አቁዋም የማያንጸባርቅ ነው።

የትብብር ለህብረ-ብሔር ዲሞክራሲያዊ ፊዴራሊዝም ጥምረት – “ሁላችንም እኩል ነን፣ ነገር ግን አንዳንዶቻችን ከሁላችሁም የበለጠን እኩል ነን”

Continue reading የትብብር ለህብረ-ብሔር ዲሞክራሲያዊ ፊዴራሊዝም ጥምረት – “ሁላችንም እኩል ነን፣ ነገር ግን አንዳንዶቻችን ከሁላችሁም የበለጠን እኩል ነን”

“ኮሮና” እና የሽግግር መንግስት !

ከሽግግር መንግስት የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያተርፈው ምንድን ነው? እነማን ይሳተፋሉ? መመዘኛው ምንድን ነው ? የሕወሃት አጫዋች የነበሩና ለውጥ እንዳይመጣ ከሕወሃት ጎን ሆነው የታገሉትስ ይሳተፋሉን? ሕወሃትስ እንደ ደርግ/ኢሰፓ ይገለላል ? ወይንስ ይሳተፋል? ከ10 የማያንሱ የኦሮሞ ድርጅቶች እንዳሉ ይታውቃል። ለነዚህ የሚሰጠው ወንበር ከሕዝብ ቁጥር ፕሮፖርሽን አንጻር ይሆናል ወይንስ እንዴት ይደለደላል? ማን ምን ያህል ወንበር እንደሚያገኝ መመዘኛው ምንድን ነው?

ሲሳይ አጌና ————————-

በምርጫ 97 ወቅት ሰኔ 1 እንዲሁም ጥቅምት 23 እና 24 በዋናነት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተካሄደው ጭፍጨፋ ማን ምን ሚና ነበረው? የግንቦት 30ውን ወረቀትስ እንዴት ተቀነባበረ ? በማንስ ተበተነ ወዘተ የሚለው የማይታለፍ እንደሆነ ቢታወቅም ይህ ግን ለኔ ለግዜው ወቅታዊ አይደለም።

በተመሳሳይ ከ2010 ለውጥ ወዲህ ከተካሄዱ ፍጀቶች በስተጀርባ የማን ሚና ምን ነበር የሚለውን ጨምሮ የቅርቡ የ86ቱ ሟቾችም ጉዳይ በተመሳሳይ የማይታለፍ ቢሆንም ፥ አሁን ላይ ሰዎቹን ከሚጠረጠሩበት ጉዳይ ጋር እያይዞ ማንሳቱ ፋይዳ የለውም። ፋይዳ የማይኖረው የጥፋተኛነትም ሆነ የጸጸት ስሜት የሌለባቸውን ሰዎች በማያፍሩበት ምናልባትም በሚኮሩበት ጉዳይ ለመግጠም መሞከር የሚለውጠው ነገር ስለማይኖር ነው።

አንዳንዶች የሚገርማቸው ከዚያ ሁሉ ወንጀል እና ነውር በኋላ ግለሰቦች አደባባይ ሲወጡ በአደባባይ የሚደግፏቸው እና ፌስቡክ ላይ የሚያጨበጭቡላቸው ሰዎች መገኘታቸው ነው። መታወቅ ያለበት ለነዚህ ወገኖች ድጋፍ የሚሰጠው ጽንፈኛው ብሄርተኛ ሃይል መሆኑ ግልጽ ነው። ይህ ሃይል ደግሞ በጭፍን ብሄርተኝነት ድንዛዜ ውስጥ ያለ በመሆኑ መቃወሙን እንጂ ውጤቱ ምን እንደሚሆን አይረዳውም።

የሚገባው ወይንም የሚባንነው አዲስ አበባ አሌፖ፡ ኢትዮጵያም ሶርያ ሲሆኑ ነው። ይህ ሃይል በማናቸውም ሁኔታ ሥርዓት እንዲፈርስ የሚቋምጥ፥ በጥላቻም ሆነ በሌላ ተቃውሞ ለተባለ ነገር ሁሉ ድጋፍ የሚሰጥ በመሆኑ ይህን በድንዛዜ ውስጥ ያለ ሃይል በአምክንዮ ማንቃት አይቻልም።በዚህ ወይንም በዚያ ብሄር ሥር የተኮለኮለው ድንዛዜ ውስጥ ያለው ሃይል የጥላቻ ፡ የዘረፋ እና የሰቆቃ ፊታውራሪዎች የሆኑት ስብሃት ነጋ የአማራ ነጻ አውጪ ነኝ ብለው ቢመጡ የሚያጨበጭብ፡ አባይ ጸሃዬ ኦሮሞን ነጻ ላወጣ ነው ቢሉ የሚከተል ፥ ጌታቸው አሰፋ የደቡብ ብሄሮችን ልታድግ ነው ቢሉ ቀይ ምንጣፍ የሚዘረጋ ወዘተ መሆኑን የሚጠራጠር የድንዛዜያቸውን መጠን ያልተረዳ ብቻ ነው።

በመሆኑም ለማይሰሙ የሥልጣን ርሃብተኞች ሃጢያታቸውን ከማስታወስ፥ እንዲሁም በድንዛዜ ውስጥ ያሉ ተከታዮቻቸውን ለማንቃት ከመጨነቅ ግለሰቦቹ የትናንት ወንጀላቸውን እንዳይደግሙት መንግስት የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ሕጋዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ማሳሰቡ አስፈላጊ ይሆናል። እንደ ፓርቲ ለመመዝገብ አራት ሺህ ፊርማ ማሰባሰብ ያልቻሉ የት ይደርሳሉ የሚለው ንቀትም ተገቢ አይመስለኝም።

ግለሰቦቹ የራሳቸው ችግር ቢኖርባቸውም መንግስት በሕገወጥ መንገድ ሥልጣኑን የሚያራዝምበት ሁኔታ ውስጥ ከገባም በጉዳዩ ላይ መወያየቱ ክፋት የለውም። ለዚህ ምላሽ ለማግኘት ግን ሥልጣን ያለው መንግስት ምርጫውን ለማካሄድ ፍላጎት ነበረው ወይንስ አልነበረውም ? የሚለውን መጠየቅ ግድ ይላል። ቀን ተቆርጦ ዝርዝር መርሃ ግብር ወጥቶ ሂደቱ በቀጠለበት የኮሮና ቫይረስ መከሰቱ በፈጠረው ስጋት ምርጫው መስተጓጎሉ ግልጽ ሆኗል። በዚህ ሂደት ውስጥ መንግስት ምርጫው እንዲራዘም መፈለጉን የሚያሳይ ሁኔታ በግሌ አልታየኝም።

ይህ የመቶ ሺህዎችን ሕይወት የቀጠፈውና ሚሊዮኖችን የለከፈው ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) እንኳን ምርጫ አድርጋ የማታውቀውን ኢትዮጵያን በምርጫ ውስጥ ክፍለዘማናት ያስቆጠሩትን አጣብቂኝ ውስጥ አስገብቷል። እንኳንስ ግለሰቦች እና ቡድኖች ሕግ ሆነው በኖሩባት ኢትዮጵያ ይቅር እና ሕግና ሥርዓት ለዘመናት በገነባቸው አሜሪካ ሕገ መንግስት ላይ ኮሮና ቫይረስ እያንዣበበ ይገኛል። International Institute for Democracy and Electoral Assistance (IDEA) የተባለ ተቋም ይፋ እንዳደረገው እ/አ/አ ከየካቲት 21 እስከ ሚያዚያ 29 2020 ባለው ግዜ ውስጥ 52 ሃገራት የምርጫ ግዚያቸውን አሸጋሽገዋል።

ከዚህ ውስጥ 17ቱ ያሸጋገሩት ዋና ምርጫ እና ሪፈረንደም ሲሆን፣አሜሪካውያንም ከ175 ዓመታት በኋላ የምርጫ ቀን ልንቀይር ይሆን ወይ ? የሚል ጥያቄ ማንሳታቸው ይፋ ሆኗል። የአሜሪካው ዕጩ ፕሬዚዳንት ዴሞክራቱ ጆ ባይደን በመጪው ህዳር 3/ 2020 GC የሚካሄደውን ፕሬዚዳንታዊ ውድድር ትራምፕ በኮሮና አሳበው ሊያሻግሩት ይሞክራሉ ሲሉ ከሰዋል።

ይህንን ተከትሎም በአሜሪካውያኑ ዘንድ የህግ ክርክር ተነስቷል።በርግጥ የምርጫ ቀኑን የመለወጥ ስልጣን የፕሬዚዳንቱ ሳይሆን የኮንግረሱ መሆኑን ዋሺንግተን ፖስት የህግ ባለሙያዎችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል። ኮንግረሱም ቢሆን በየአራት ዓመቱ በህዳር ወር የመጀመሪያው ማክሰኞ ምርጫ ይካሄዳል የሚለውን ከ1845 ጀምሮ የተተከለውን የምርጫ ቀን ማሻሻል ቢችልም የምርጫ ቀኑን በሳምንታት መግፋት እንጂ ፥ ፕሬዚዳንት ትራምፕ እ/አ/አ ከጥር 20 /2021 ዕኩለ ቀን በኋላ በኋይት ቤተመንግስት ውስጥ እንዲቆዩ የማድረግ ስልጣን የለውም።

ሁኔታው ወደዚያ ካመራ ሕገመንግስታዊ ማሻሻያ የግድ የሚል መሆኑን አሜሪካውያኑ የህግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ምርጫቸውን በፖስታ ቤት ጭምር መላክ በሚችሉት አሜሪካውያን ላይ የኮረና ቫይረስ ተጽዕኖ የጎላ እንደማይሆን ቢታመንም 2/3 ኛ የሚሆኑት አሜሪካውያን ኮረና ቫይረስ የአሜሪካንን ፕሬዚዳንታዊ ምርጭ ሊያስተጓጉል እንደሚችል ስጋታቸውን መግለጻቸውን የአሜሪካውያኑ የጥናት ትቋም ፒው ሪሰርች ከ10 ቀን በፊት ይፋ አድርጓል። ኮሮና ቫይረስ ለዓለም ሕዝብ ምን ያህል ፈተና እንደሆነ በዝርዝር ማየቱ ያስፈለገው የኢትዮጵያን ሁኔታ ከዚያ አንጻር ለመመዘንም ጭምር ነው።ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ሕገመንግስት የፓርላማውም ሆነ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጣን ዘመን የሚያበቃው መስከረም 25 / 2013 ዓ.ም ነው። (እነ ጃዋር መስከረም 30ን ከየት እንዳመጡት አይገባኝም። ምክንያቱም ፓርላማው ስልጣኑ የሚያበቃው በ2013 ዓ.ም የመጨረሻው ሰኞ መስከረም 25 ነውና።) ፓርላማው የስልጣን ዘመኑ ከማብቃቱ በፊት ባለው አስገዳጅ ሁኔታ ስልጣኑን ለማራዘም ያለውን አማራጭ በተመለከተ መንግስት በባለሙያ ማስጠናቱን ይፋ አድርጓል።

ጥናቱን ያካሄዱት ባለሙያዎች መሆናቸው ከመነገሩ ባሻገር ያቀረቧቸው አማራጮች ሕገመንግስታዊ መሆናቸውን ሌሎች ገለልተኛ ባለሙያዎችም እየመሰከሩ ነው። የሽግግር መንግስት ብሎም ከዚያ አለፍ ያለ ጥሪ ለማድረግ በአንድ መድረክ በተገኙት ልደቱ እና ጃዋር መካከል እንኳን በዚህ ዙርይ አንድነት የለም። ልደቱ ሕገመንግስቱን በማሻሻል ማራዘም ሕጋዊ መሆኑን ተቀብሎ ግን በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ያስገምታል ሲል ጃዋር ደግሞ ምንም ሕጋዊ ምክንያት የለሚ ሲል ተደምጧል።

አውያዩ ግርማ ጉተማም ጉዳዩን ለማጥራት ያልፈለገው ለማስተተላለፍ በወሰኑት የጋራ መልዕክት ላይ ውዥንብር እንዳይፈጠር ይመሰለኛል።ህገ መንግስቱን ለማራዘም ህጋዊ መንገድ ካለ እና ይህም በአስገዳጅ ሁኔታ የተገባበት ከሆነ የሽግግር መንግስት ለምን ያስፈልጋል? ከሽግግር መንግስት የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያተርፈው ምንድን ነው? እነማን ይሳተፋሉ? መመዘኛው ምንድን ነው ? የሕወሃት አጫዋች የነበሩና ለውጥ እንዳይመጣ ከሕወሃት ጎን ሆነው የታገሉትስ ይሳተፋሉን? ሕወሃትስ እንደ ደርግ/ኢሰፓ ይገለላል ? ወይንስ ይሳተፋል? ከ10 የማያንሱ የኦሮሞ ድርጅቶች እንዳሉ ይታውቃል። ለነዚህ የሚሰጠው ወንበር ከሕዝብ ቁጥር ፕሮፖርሽን አንጻር ይሆናል ወይንስ እንዴት ይደለደላል? ማን ምን ያህል ወንበር እንደሚያገኝ መመዘኛው ምንድን ነው? የካቢኔ ቦታ የሚሰጣቸው ድርጅቶች እንማን ይሆናሉ ? በምንስ መመዘኛ? አንዳንዶቹ ተጽዕኖ ፈጣሪ ድርጅቶች እና ግለሰቦች መለያቸው ይበልጥ ረብሻ ኣና በግርግር ከመሆኑ አንፃር የሽግግር መንግስቱ እነሱን ቀና በማድረግ ሁከት ማንገስ እንጂ መረጋጋት እንዲመጣ ያደርጋልን ? ሃገራዊ ራዕይ እና ኢትዮጵያዊነት እየለመለመ አክራሪነት እየከሰመ ባለበት ሁኔታ ውስጥ አክራሪዎች የበዙበት የሽግግር መንግስት የትናንት ጭለማን ከመጥራት ውጭ ምን መፍትሄ ያመጣል?ለኢትዮጵያ መድህን የሚሆናት ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ነው። ለዲሞክራሲያው ምርጫ ደግሞ መረጋጋት ያስፈለጋል። ለመረጋጋት ደግሞ የተረጋጋ መንግስት ግድ ይላል። የተረጋጋ መንግስት እንዲቀጥል ደግሞ ሁላችንም ከሕግ በታች መሆናችንን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። በለውጡ ማግስት የተፈጠሩ ግርግሮች እንዳያገረሹ የሚያሳስበን ዜጎች ትግል እየሸጡ የከበሩ እና በብሄረሰብ ተሟጋችነት ሞት የሚነገዱትን የህወሓት ጉዳይ ፈጻሚዎችን እረፉ ልንላቸው ይገባል።

ህዝብ እኮ ስልጣን የራበው ሁሉ እየነቀለ የሚጥደው የቦና ጎመን አይደለም – በድሉ ዋቅጅራ

የጃዋርንና የልደቱን ውይይት አየሁት፤ ሰማሁት፡፡ ላየው የቀሰቀሰኝ ዋና ነጥብ አንድ ላይ ያመጣቸውን ጉዳይ የማወቅ ጉጉት ነበር፡፡ አገኘሁት፡፡ ያቀረቡበት መንገድ ነው ልዩነቱ፣ የጀዋር በፖለቲከኛ (ብስለትና መሰሪነት)፣ የልደቱ በወታደር (ጉልበትና ማስፈራራት) ከመቅረቡ በስተቀር፤ ‹መስከረም 30 የመንግስት ህጋዊ ተቀባይነት ስለሚያበቃ፣ መንግስት እኛ የምንለውን የማይቀበል ከሆነ ህዝቡ ከእኛ ጋር ቆሞ መንግስት እንዲቃወም- እንዲታገል› ነው፡፡ በጎው ነገራቸው፣ .. .

‹‹መንግስት ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሁኔታው ላይ መወያየትና መስማማት አለበት›› የሚለው ነው፡፡ በርግጥ መንግስት ይህን ማድረግ አለበት፤ ይህ ሕዝብ በኮሮና ድቀቱ ላይ፣ በፖለቲካ ምክንያት የሚፈጠር ነውጥን የሚሸከም ትከሻ አይደለም፤ የሚሰማ ጆሮ የለውም፡፡

የጃዋርና የልደቱ ትልቁ ችግር ህዝብን በኪሳቸው እንደያዙት ሳንቲም ሲፈልጉ ሊያስቀምጡት፣ ሲፈልጉ ደግሞ አውጥተው ሊጠቀሙበት፣ ደፍነው ለጅምላ ግዢ፣ ዘርዝረው ለችርቻሮ ሊያውሉት የሚችሉት አድርገው መቁጠራቸው ነው፡፡ ህዝቡን እውን ቢያውቁት የትላንቱን ውይይታቸውን ይዘውለት ለመቅረብ ባልደፈሩ ነበር፡፡ በተለይ አዚህ ላይ የልደቱ ድፍረት ለከት አልነበረውም፤ ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት ስብሰባ እንኳን ለመምራት፣ መብት እንደሌለው ሲናገር፣ ስለራሱ ሀገር የሚያወራ ፈጽሞ አይመስልም፤ በወረርሽኝ ምክንያት ምርጫ ስለተራዘመበት መንግስት ሳይሆን፣ ሀገር ለቅቄ እወጣለሁ ያለበትን ቀን ስላላከበረ ቅኝ ገዢ የሚያወራ ነው የሚመስለው፡፡

የሚገርመው ከወራት በፊት ልደቱ ‹‹ተቃዋሚ ፖርቲዎችን 10 ሺህ ፊርማ እንዲያሰባስቡ መጠየቅ፣ ፓርቲዎችን ማዳከምና እንዳይመሰረቱ ማድረግ ነው.. ባለበት አፉ ዛሬ 100 ሚሊየን ህዝብ ከጎኑ እንደሆነ በሙሉ ልብ ሲናገር መስማት ጤንነቱን ያጠራጥራል፤ . . . ህዝብ እኮ ስልጣን የራበው ሁሉ እየነቀለ የሚጥደው የቦና ጎመን አይደለም፡፡ .ውይይታቸውን ልብ ላለ የልደቱና የጀዋር ልዩነት (ምንም እንኳን ጃዋር የፓርቲያቸውን የመፍትሄ ሀሳብ ግልጽ ባያወጣውም) ለችግሩ የሚያቀርቡት የመፍትሄ ሀሳብ ላይ ነው፡፡

በግሌ የጃዋር ፓርቲ የሽግግር መንግስትን እንደመፍትሄ የሚያቀርብ አይመስለኝም፡፡ ዶ/ር መረራ እና ጃዋር እራሱ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪዎች በመሆናቸው እውቀታቸውን ተጠቅመው የተሸለ ሀሳብ ሊያቀርቡ ይችላሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡ .የልደቱ ‹‹የሽግግር መንግስት›› ሀሳብ ግን እንዳለው ቀድሞም በቀዳማዊ ኢህአዴግ መውደቅ ፍትጊያ (2009/10) የነበረ፣ ዛሬም ከኮረና ጋር ያለ ነው፡፡

ልደቱ ከፍተኛ የስልጣን ፍላጎት ያለው ይመስለኛል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የ97ቱ ምርጫ ህዝባዊ ቅቡልነቱን እንዳወረደውና የሚፈልገውን የስልጣን እርካብ እንደማያስረግጠው ያውቃል፡፡ በመሆኑም ፓርቲዎች በመዋጮ የሚያቋቁሙት የሽግግር መንግስት ነው ብቸኛ የማርያም መንገዱ፡፡ የኸው ነው፡፡

በርካታ ሀገሮች በኮሮና የተነሳ ምርጫ አራዝመዋል፤ የትኛው ሀገር ነው የሽግግር መንግስት የመሰረተው? የሽግግር መንግስት የተወሰነ ጊዜ ተሰፍሮለት የሚመሰረት ነው፡፡ አሁን ያጋጠመው ችግር ወረርሽኝ ነው፤ 6 ወር ወይም አመት ሊወስድ ይችላል፤ አናውቅም፡፡ .ለሁለቱም . . .ፖለቲከኛ መሆን ካሻችሁ ህዝቡን እወቁት፤ አክብሩት፡፡ አክብሮታችሁ ቀርባችሁ ከማወቃችሁ ይሁን፡፡ ህዝብን የማያከብር ፖለቲከኛ ህዝብን ሊመራ አይችልም፡፡ ህዝብን አክብሩ፡፡ ህዝብ ጉልበት ስትፈልጉ የምትገዙበት የሚስጢር ኪሳችሁ ሳንቲም፤ ስልጣን ሲርባችሁ እየነቀላችሁ የምትጥዱት የጓሮአችሁ ጎመን አድርጋችሁ አትኩጠሩት፡፡

ኢትዮጵያ ወዴት? ዘረኝነት: ተረኝነትና ስርዐት አልበኝነት!!!

– ሃይለገብረኤል አስረስ

ሃገራችን የምትጏዝበት የፖለቲካ ጎዳና የት እንደሚያደርሰን ከመቼውም ግዜ በላይ እርግጠኛ መሆን ያልቻልንበት ወቅት ቢኖር እሁን ነው:: ተስፉ የተጣለበት የለውጥ ጎዞ መስመሩን ስቶ ጽንፈኞች የነገሱበት ምዕራፍ ውስጥ ከቶናል::

ኢትዮጵያችን ወዴት እየተንደረደረች እንደሆነ የሚታይ ነው:: ከታላቅ ተስፋ ወደ አስፈሪ ስጋት!  ከለውጥ ወደ ነውጥ!  ከአንድነት ወደ መንደርተኝነት ::

ዲሞክራሲ ሰላምና ኢኮኖሚያዊ ለውጥን ከመገንባት  ይልቅ ወደ ውድመት ዘረፋና ማህበራዊ ቀውስ ተሸጋግሯል:: እኛነት ጠፍቶ እኔነት ነግሷል:: የጋራ ራዕይ ብርቅ የፖለቲካው ሁኔታ ውስብስብ ሆኗል:: የተረኝነት ስሜት ገኖ ልጏሙን በጥሷል::

ጠቅላይ ሚንስትሩና ካቢኔያቸው ሃገር ሊመራበት የሚገባ ፍኖተ ካርታ ግልጽ ማድረግ አልቻሉም:: ሕግና ስርዐትን የማስከበር አቅም አጥተዋል አለያም ሁን ብለው ትተውታል:: አስቸኳይ መፍትሄ የሚያስፈልጋቸውን ብሄራዊ ጉዳዮች ችላ ሲሉ ተስተውሏል:; የመንግስትና የጠቅላይ ሚንስትሩ ትኩረት ተራ የገጽታ ግንባታ ላይ መሆኑ ይታያል::

በሃገር ውስጥ በሕወሃት መሪነት የትግራይ ሕዝብን ከአማራው ጋር ወደ ለየለት ጦርነት ለማስገባት ዝግጅቱን ጨርሷል:: የጥላቻና ተከበናል ፕሮፓጋንዳው በስፋት ቀጥሏል:: በኦነግ ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው የሲዳማ እጀቶ የተባለ የሽብር ቡድን በክልልነት ጥያቄ ሽፉን ብሄር የለየ ጥቃትና ዘረፋ ፈጽሟል:: አብያተ ክርስቲያናትን አቃጥሏል:: በአዋሳ ከተማ ነዋሪዎችና በደቡብ ሕዝብ ላይ አስፈሪ ስጋት ደቅኗል::

ይህን የመሰለ ሃገር አውዳሚ ውጥረት በሚቻለውና በማንኛውም  አቅም አስቀድሞ ማስወገድ የነበረበት መንግስት ጉዳዩን በእርቀት ከማየት ውጪ ምንም ሲያደርግ አይታይም::ሃገሪቷ ይህን መሰል አደጋ ተሸክማ በምትቃትትበት ወቅት  “የእራሷ አሮባት የሰው ታማስላላች” እንዲሉ ጠቅላያችን  አንዴ አስመራ ሌላ ግዜ ካርቱም የሱዳን ተቃዋሚዎች አደራዳሪ መሆንን ቅድሚያ ሰጥተዋል::

Samira,* a displaced Ethiopian, holds one of her seven children in front of the tiny space she shares with other families at the Gedeb site

በባህር ዳር በአማራ ክልል መሪዎች እና በአዲስ አበባ የመከላከያ ኢታማጆር ሹሙ ላይ የተፈጸመው ግድያ የበዛ  ግልጽነት ይጎለዋል :: ይህም በፈጠረው ክፍተት ጠቅላይ ሚንስትሩንና ቡድናቸው ሕዝቡ እንዲጠራጠር በር ከፍቷል:: በመሪዎቹ ላይ የተካሄደው ግድያ በነጻና ገለልተኛ አካል ምርመራ ተካሂዶ የጋራ መግባባት ላይ እንዳይድረስ መንግስት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል::

ይባስ ብሎም አደጋውን አስታኮ በአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አባላትና አመራሮች : በጋዜጠኞችና : በአዲስ አበባ ም/ቤት (ባልደራስ) አባላት ላይ እራሳቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ በፓርላማ ያወገዙት የሽብር ሕግ : አመት ሳይሻገር መልሰው ንጽሃንን ማጥቂያ አድርገውታል:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ቃል ማጠፍና ተቃዋሚን በሃሰት መፈረጅን ከቀጠሉ ጥፍር ነቃይ መርማሪዎችንም ወደ ስራ ላለመመለሳቸው ምንም ዋስትና የለም ::

ለጌታቸው አሰፋ የእዮብን ትግስት ያሳየ መንግስት ሕወሃትን መንካት የፈራ ወይም ያልፈለገ አመራር:: የኦነግ አሃድ ትጥቅ አልፈታም ማለቱን 20 ባንክ  መዘረፉን አላውቅም ያለ መሪ :  አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች መረን የለቀቀ አካሄድን መቆጣጠር ያልቻለ ወይም ያልፈለገ መንግስት ከብዕር ውጪ ምንም የአመጽ መሳሪያ የሌላቸውን ሰላማዊ ታጋዮች በሽብር ሕግ  ማሰሩ ብዙዎችን አሳዝኗል:: በጠቅላይ ሚኒስትሩና በለውጡ ሂደት ላይ መጥፎ አሻራ አሳርፉል::

በአንጻሩ :  ከዶር አብይ ስልጣን ማግስት ከተደበቀበት ጎሬ ብቅ ያለው በሃምሳ አመት ታሪኩ አንዲት ጀብድ መስራት ያልቻለው ያነገበው ጠመንጃ  እላዩ ላይ እስኪዝግ ቁጭ ብሎ የኖረው ጨለምተኛና ጽንፈኛው የኦነግ መንጋ ሰማይና ምድሩን ጨረቃና ከዋክብቱ ሁሉ የኔ ለኔ በሚል ስስታም የኬኛ ዘመቻ የለውጡን ተስፋ አጨንግፎ የውጥረት አየር በሃግሪቷ ላይ እንዲነግስ የራሱን ሚና ተጫውቷል::

የበታችነት ስነልቦና  ያደቀቃቸውና የጥላቻ ስሜት የወጠራቸው እነዚሁ በታላቁ ኦሮሞ ሕዝብ ስም የሚነግዱ ጥቂት የእናት ጡት ነካሾች ዘመኑ ከደረሰበት የግሎባላይዜሽን ከፍታ ሃገራችንና ሕዝባችንን  ወደ ጋርዯሽ ዘመን ሊያወርዱ የጥላቻ ጉድጏድ በመቆፈር ተጠምደዋል::

በተዛባ የወራሪ ሰፋሪና መጤ የትርክት አሮጌ ጀልባ እየቀዘፈ ወሎ ለመድረስ የፈጠነው የኬኛ ሰራዊት በዚህ ግስጋሴው በስስት ንፋስ እየተገፋ ሕንድ ውቂያኖስ ገብቶ እንዳሰምጥ ሊመከር ይገባል::

ልክ ያጣው የተረኝነት ስግብግብ አጀንዳና መረን የለሽ ጥላቻ ያሳወረው የኦሮሞ ልሂቅ : ትላንት የኦሮሞ ሕዝብ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ስቃይ ሲፈጽሙ ከኖሩት የሕወሃት ፋሽስቶች ጋር ዳግም ለመሰልፍ አብቅቶታል::

ሕወሃቶች ላለፉት 28 አመታት እስር ቤቱን ኦሮምኛ ተናጋሪ ያደረጉበት ሃቅ ተዘንግቶ:: ትላንት ወለጋ ውስጥ ልጇ እሬሳ ላይ እንድትቀመጥ የተደረገችው እናት ሃዘን ሳይረሳ : እግራቸው በጭካኔ ተቆርጦ : የዘር ፍሬያቸው ፈርጦና : ጥፍራቸው ተነቅሎ በስቃይ ያሉት አያሌ ግፉዐን ወገኖቻችን  ቁስል ሳይደርቅ በኦሮሞ ሕዝብ ስም የሚምሉ ምሁር ተብዬ ጨለምተኞች ሕወሃት ጫማ ስር ተመልሰው ሃገር ለማፍረስና የብሄር ግጭት ለመፍጠር መሰማራታቸው የኦሮሞ ሕዝብን ክብር እጅግ የሚያወርድና  ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል ነው:;

ኢትዮጵያ የሁሉ ናት የአንዱ የግል ለሌላው የጋራ የሆነ ግዛትም ድንበርም ልዪ ተጠቃሚነትም ኖሮ አያውቅም ወደፊትም አይኖርም:: ሰሜኑም ምዕራቡም ደቡቡም ሆነ ምስራቁ የሁላችን የጋራ ሃገር እንጂ የአንዱ ወይ የሌላው አይደለም:: ጀግኖች አባቶቻችን በአራቱም ማዕዘን ድንበሯ ላይ ውድ ሕይወታቸውን የሰውት ለመንደርና ጎጣቸው ሳይሆን ለታላቋ ኢትዮጵያ ልዕልናና ለሁሉም ሕዝቧ ክብር ነው::

ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ ነው ፤ ኢትዮጵያም የኦሮሞ ናት! ይህን ሊፍቅና ሊያስቀር የሚችል ምንም ውሃ የሚቋጥር ምክንያት የለም። የኦሮሞ ልጆች ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና ለወሰኗ ክብርና ለሉዓላዊነቷ ወደር የሌለው መስዋዕትነት ሲከፍሉ ኖረዋል። በአለም የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ ብቸኛ የነጻነት ባለቤት የመሆን ከፍታ ላይ የደረሰ ዜግነት ያለው ኩሩ ሕዝብም ሆኗል::

የዛሬዎቹ የበታችነት ስነልቦና የተጫናቸውና ጥላቻ የተሞሉ የታሪክ ምሁር ተብዬዎችና ፖለቲከኞች የኦሮሞን ሕዝብ ከተሰቀለበት የክብር ሰገነት አውርደው  የክብርና የኩራት ታሪኩን ንደው የባርነትንና የተገዥነትን የሃሰት ማቅ ሊያለብሱት ይራወጣሉ:: የኦሮሞም ሆነ ሌላው ሕዝብ ችግሩና ጥያቄው ሰላም ልማት መልካም  አስተዳድርና ዲሞክራሲ እንጂ የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት አይደለም:: አንድ እግራቸውን ውጪ ያደረጉ አክራሪ ሃይሎች በሕዝብ ሰላምና በሃገር ሕልውና ላይ እያካሄዱ ያለውን አፍራሽ እንስቃሴ ኢትዮጵያዊው ኦሮሞ በግዜ ሊታገላቸው ይገባል::

ኢትዮጵያዊ እሳቤ ዛሬ ላይ ጠንክሮ የሚወክለው ወገን አጥቷል:: ትላንት በአንጋፉ ተቃዋሚነት ትግሉን ይመሩ የነበሩት የአሮጌው ፖለቲካ ሃይሎች ሕዝቡን ክደው ለገዥዎች አድረዋል:: ሚድያውም ሲቪክ ተቋማትም ከአደባባይ ጠፍተዋል አንዳዶቹም በአድርባይነት ተሰልፈዋል:: የአደባባይ ምሁራን ይባሉ የነበሩትም አድሃሪ ሆነዋል:: አንድነትን የሚሰብኩ አብሮነትን የሚያጸኑ ኢትዮጵያዊነትን የሚመሰክሩ ጉባዔዎች ነጥፈዋል:: በተለይ በውጭ ሃገራት ጨርሶ ተዳፍኗል::

ለዚህ ነው ኢትዮጵያ ወዴት የሚል የውይይት ፎረም ያስፈለገው:: ክፍተቱን ለማጥበብ ከማሰብ ነው::

ዛሬ በሃገራችን በመሆን ላይ ያለው የተረኝነት ስሜት የጥላቻ ቅስቀሳና የተዛባ ትርክት ዝም ከተባለ ሃገር ሊያፈርስና ሕዝብ ሊያጫርስ ወደሚችል ምዕራፍ እንዳይሸጋገር መሪዎቹን ለማሳሰብ ሕዝቡን ማንቃትና ማደራጀት አስፈላጊ በመሆኑ ነው:: ጭፍን ተቃውሞም ሆነ ጭፍን ድጋፍ ከሰለጠነ ማህበረሰብ የሚጠበቅ ባለመሆኑ በእውቀት በማስረጃና በሃቅ ላይ የተመሰረተ ሃገራዊ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው:: ይህን መሰሉን ፎረም ወደፊት በተጠናከረ ሁኔታ በተለያዩ ርዕሶች ላይ ማካሄዳችንን እንቀጥላለን::

ኢትዮጵያን እግዚያብሄር ይጠብቅልን!!

ኢትዮጵያ ወዴት? የውይይት ፎረም!

photo cover –OCHA/ Tinago Chikoto Internally Displaced Persons (IDPs) in Kercha, West Guji Zone, Ethiopia. 07 July 2018.

Subscribe to the  Zaggolenews online news magazine

28 ዓመት ሙሉ ሲገድለን፣ ሲፈልጠን፣ ሲያስረን ሲያንገላታን የነበረው ትህነግ በጓዳ በር

28 ዓመት ሙሉ ሲገድለን፣ ሲፈልጠን፣ ሲያስረን ሲያንገላታን የነበረው ትህነግ በጓዳ በር ዳግም ወደ ስልጣን ለመምጣት ከተገንጣይ ኦሮሞ ጽንፈኞች እና ያረጀ ያፈጁ ሌሎች ፖለቲከኞች ጋር ደፋ ቀና ሲል እኛ አሁንም የፖለቲካ መላቅጡ ጠፍቶን ቆሞ ተመልካች ሆነናል። እያንዳንድህ የጠሚ ዓቢይ አድናቂ የሆንክ ኦሮሞም ሆንክ ደጋፊና ተቃዋሚ አማራ በዚህ ሠዓት ትህነግ ከፖለቲካ አጋሮቿ ጋር የምታደርገውን ነገር እያየህ የፖለቲካ መስመሩ ካልገባህ ደንዝዘሃል ለማለት እገደዳለሁ።
.
በተለይ ከአማራው በኩል ይኼን የሚገነፍል ወጣት በተሳሳተ መንገድና እሳቤ በመምራት ቁዘማ ውሰጥ እንዲገባ ከማድረግ ይልቅ ወቅታዊና ተጨባጭ የፖለቲካ አሰላለፎችን ብጥርጥር አድርጎ ተንትኖ ለሕዝቡ ጠቃሚ አቅጣጫ የሚያሳዩ ጥቂት ሰወች መጥፋታቸው እጅግ የሚያበሳጭ ነገር ነው። ትህነግ እየቆፈረ ያለውን ጥልቅ ጉድጓድ ባለመረዳት አሁንም የጠሚ ዓቢይ መንግስትን ድክመትና የሚሰራቸውን ስህተቶች እየቆጠሩ እነሱኑ ማጮህ ላይ ትኩረት ያደረጉ ሜዲያወችና አክቲቪስቶች የዘነጉት ነገር ትልቁንና ለመምጣት ዳር ዳር እያለ ያለውን ዋና ጠላት ነው።
.
እያንዳንዱ ወገን የተፎካካሪ (የተወዳዳሪ) ትንተና አድርጎ በቅደም ተከተል የትኛውን ቀድሞ መዋጋትና ማሸነፍ እንዳለበት ካልተረዳ ገና አሁንም የማንም መጫወቻ መሆናችን አይቀርም። ከሁሉም የሚቀድመው ግን አሁን በሀገሪቱ ላይ ያለውን የፖለቲካ አሰላለፍን በጥንቃቄ መረዳት መቻሉ ላይ ነው። ትህነግ መቀለ ላይ ባደረገው ስብሰባ የውግዘት መዓት እየደረሰበት ያለው ADP እና ODP ናቸው። ለዚህ ውግዘት ተባባሪ ሆነው የቀረቡት ደግሞ የእነ ጃዋር አንጃ እና ሌሎች አሮጌ ፖለቲከኞች መሆናቸውን መረዳት ያስፈልጋል።
.
ጃዋር ከኦዴፓ ባለስልጣናት የተወሰኑት ጋር ሊሞዳሞድ ይችላል፣ ጃዝ እያለ እያስፈራራም ጉዳዩን ሊያስፈጽምና መረጃ ሊቀበልም ይችላል፣ ኦዴፓወችም ህዝብ ሊያሳምጽ ይችላል በማለት እሱ የሆነ ነገር ባለቁጥር ሊደናበሩ ይችላሉ ነገር ግን አንድ ነገር እርግጠኛ መሆን ያለብን ጃዋር የእነ ጠሚ ዓቢይን መንግስት አሽቀንጥሮ ለመጣል ከፍተኛ ጥረት እያደረገና ከትህነግ ጋር በአንድ ላይ አጀንዳ እየተቀባበለ መሆኑ ላይ ነው። 
.
እነ ጃዋርና መሰል ጽንፈኞች ጠሚ ዓቢይን የአማራ አጀንዳ አስፈፃሚ እያሉ ፕሮፖጋንዳ እየሰሩበት ነው፣ እነ ደረጀ ገረፋ የኦዴፓ ደጋፊ ነን በማለት የሚጽፉትን ተቃውሞ አስተውለህ ካላየህና የእነ ጠሚ ዓቢይና የጽንፈኛው ጃዋር አንጃ ልዩነት ካልገባህ ደንዝዘሃል ማለት ይቻላል። ትህነግ ስልጣን ለመያዝና ፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የምትችለው ኦሮሞውንና አማራውን በማጋጨት ነው፤ ይኼ ዘመን የማይሽረው አቅጣጫዋ ነው። ይኼን አቅጣጫዋን የሚከሽፍበት መንገድ እንዴት ነው የሚለውን ሁልህም ወደ ራስህ ተመልሰህ አስብ።
.
የጠሚ ዓቢይ መንግስት ብዙ ስህተቶችን እየሰራ አሳዛኝ ውሳኔዎችንም እያሳለፈ እየተመለከትን ነው፤ ይኼን መካድ የማንችለው በየቀኑ እየተፈጸመ ያለ ነገር ነው። ይኼን መተቸት፣ መገሰጽና እንዲስተካከል ለማድረግ ከመታገል ጎን ለጎን ግን ትህነግ እና አክራሪና ጽንፈኛው የኦሮሞው አንጃ የሚያደርጉትን ነገር መታገል እና የእነሱ መሳሪያ አለመሆንም ግዴታ ልናደርገው ይገባል። 
.
ጠሚ ዓቢይን በኢትዮጵያዊ አንድነት አመለካከታቸው ልንጠራጠራቸው አይገባም አድሎ ምናምኑ ሊኖር ይችላል። አማራ ተብሎ እንኳ ጎንደር ጎጃም እየተባለ ስንት ነገር እየተሰራ እያየን ያኛው ሊገርመን አይገባም። ምንም እንኳ ትክክል ያልሆነ እና መታገል ያለብን ነገር ቢሆንም፤ ያለውን ስህተት እየነቀፉና እየታገሉ ሌላኛውን ጭራቅ ግን አርቆ መቅበር አስፈላጊ ነው። በተለይ አንዳንድ ከትህነግ ጋር መደራደርና ተነጋግረን አብረን መስራት እንችላለን የምትሉ ቂላቂሎች ይህን የሞኝ እሳቤያችሁን ወዲያ በሉት።
.
ለማንኛውም 28 ዓመት ሕገ መንግስት ሲጥስ፣ የፌድራል መዋቅሩን እንደፈለገ ሲያበላሸው የነበረው ትህነግ ለህገ መንግስትና ለፌድራሊዝም ጠበቃ ሆኖ ባለፈው 27 ዓመት ሁሉም ነገር ጥሩ እንደነበርና አሁን ባለፈው 1 ዓመት ብቻ እንደተበላሸ ያለ ሀፍረት ሲደሰኩር እየሰማን ዝም ማለታችን አስነዋሪ ነው። ዝምታው በተለይ አስነዋሪ የሚሆነው በምስሉ ላይ የምትመለከቱት ዘረኛ፣ ሙሰኛ፣ ሞራለ ቢስ የአድዋው ዶ/ር መንበረ ጸሀይ ታደሰ ህገ መንግስቱ የረቀቀበት መንገድ ቅቡልነት ያለው ሲል ሰውየውን የምታውቁ የህግ ባለሙያወች ዝም ማለታችሁ ነው።
.
ዶ/ር መንበረ ጸሀይ ታደሰ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል በነበረ ጊዜም ሆነ የህግና የፍትህ ጥናት መስሪያ ቤት ኃላፊ በነበረ ጊዜ ሲሰራውና ሲያደርገው የነበረው ሳያሳፍረው አሁን በመድረክ መጥቶ የተበላሸውን አሮጌውን ጨካኝና ገዳይ ሥርዓቱን ለመመለስ ሲቀባጥር ልክ ልኩን መንገር ሲገባን ዝም ማለታችን አሳዛኝ ነው። በተለይ ደግሞ አሳዛኝ የሚሆነው የዚህን ሰው ሙስና፣ ወንጀል እያወቃችሁ የእሱ የዘረኝነት በትር ላረፈባችሁ የህግ ባለሙያወችና ዳኞች ነው።
.
መንበረ ጸሀይ ታደሰ ልጁ የምትሆን ሉዋም አሰፋ የምትባል ሴትን (ምኑ እንደሆነች ፈጣሪ ይወቅ) ከጠቅላይ ፍርድቤት ተሿሚነት ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ በውሽምነት ይዞ ውጭ ሀገር ድረስ እንድትማር በማድረግ እሱ መስሪያ ቤት ሲቀያይር አብሯት የሚዞር አሁንም በእሷ ስም ጥብቅና ፈቃድ አውጥቶ ብር የሚሰበስብ ሞራል የለሽ ሰው ነው። ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኝነት ተነስቶ ወደ ህግና ፍትህ ጥናት መስሪያ ቤት ሲመደብ ይቺኑ ሉዋም የምትባል ጸሀፊውን አብሮ አዛውሮ ክፍያዋን ደግሞ የሲቪል ሰርቪስ መደብ ዝቅ ስለሚል በፕሮጀክት መደብ ተመድባ ከፍ ያለ ክፍያና መኪና ጥቅማ ጥቅም እንድታገኝ ሲያደርግ ነበር። 
.
የጠሚ ዓቢይ መምጣትን ተከትሎ ከስልጣን ሲነሳ ይቺኑ ሉዋምን ከመስሪያ ቤቱ እንድትለቅ አድርጎ የጥብቅና ፍቃድ እንድታወጣ በማድረግ እሱ ራሱ ፈቃዱን እየነገደበት ይገኛል። እሱ ራሱ ፈቃድ ማውጣት እየቻለ በእሷ እንዲወጣ ያደረገው መንግስት ለጡረተኞቹ የሚሰጠው እጅግ ከፍተኛ ጥቅማጥቅምና ቤት እንዳይቀርበት ነው። መንበረጸሀይ ለዳኞችና ለአቃቢያን ሕግ ስልጠና የሚያገለግል ግንባታ በካናዳ መንግስት ድጋፍ ሲሰራ የሚሰራው ስልጠና ተቋም የዳይሬክተሩ ቢሮ ለሚሆን ቢውልዲንግ ማሰሪያ የሚሆነውን ገንዘብ ቅርጥፍ አድርጎ የበላ ሙሰኛ ነው። 
.
የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞችን ጣልቃ እየገባ እንደፈለገ ሲያወጣና ሲያወርድ፣ ከመለስ ዜናዊ ጋር እየተነጋገረ ፍርድ ቤት ዳኞችን ሲያባርር፣ ጣልቃ ሲገባና ፍርድ ቤቱን መጫወቻ ሲያደርግ የነበረ፣ ዳኞችን ሲያሸማቅቅ የነበረ በተለይ እንደ ዓሊ መሀመድ ዓይነት ምርጥ ዳኞችን ቁም ስቅላቸውን መከራ ሲያበላቸው የኖረ ሰው ነው። በዚህና መሰል ሌሎች ምክንያቶች የቀድሞው የፍትህ ሚንስቴር የብአዴኑ ብርሃን ኃይሉ በመሞገቱ ምክንያት ከስልጣኑ ተነስቷል።
.
እንዲህ ዓይነት አስቀያሚ ሪከርድ ያለው ግለሰብ ስለ ህገ መንግስትና ህግ ሲያወራ ቢያንስ እንኳን የግፉ ሰለባ የሆናችሁ ዳኞችና የህግ ባለሙያወች ዝም ማለታችሁ እጅግ አሳዛኝ ነው። የድሮው ዝምታ በአንባገነን መዳፍ ስር እየተዳደርን ስለነበር ግዴለም ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ሰው ሞራል ኖሮት ወደ መድረክ ወጥቶ ህግና ህገ መንግስት ሲል ዝም ማለታችሁና ህሊናችሁ መቻሉ አስገራሚም አሳዛኝም ነው።

By Brook Abegaz -satenaw


Subscribe to the  Zaggolenews online news magazine

ምርጫ ወይስ ተቋም ግንባታ… የቱ ይቀድማል? (በኤፍሬም ማዴቦ)

የጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድ መንግስት አገር ዉስጥና ከአገር ዉጭ የሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን ጋብዞ የአገራችንን ችግሮች አብረን እንፍታ የሚል ጥያቄ ካቀረበ በኋላ በነበሩት 16 ወራት ኢትዮጵያ ዉስጥ በአዳራሾች፥ በማህበራዊ ሜዲያ፥ በቴሌቭዥንና እንዲሁም በፖለቲካ ፓርቲዎችና በምርጫ ቦርድ መካከል በተደረጉ ዉይይቶች ዉስጥ ጉልህ ቦታ ከነበራቸዉ የዉይይት አርዕስቶች ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ የ2012ቱ ምርጫ ይራዘም ወይስ አይራዘም የሚለዉ ጥያቄ ነበር። ይህ ጥያቄ የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ በሁለት ሺ አስር ዓም ሐምሌ ወር ማለቂያ ላይ ከትግል አጋሮቹ ጋር ሆኖ አሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ ዉስጥ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በተገናኘበት ወቅት ካነሳቸዉ ጥያቄዎች ዉስጥ አንዱ ነበር። በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስት ለዚህ ጥያቄ የሰጠዉ መልስ ምርጫዉ በተያዘለት የግዜ ሰሌዳ መካሄድ የለበትም የሚል አሳማኝ ሃሳብ የሚመጣ ከሆነ ምርጫዉ የማይራዘምበት ምንም ምክንያት የለም የሚል ነበር።ጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከዋሽንግተን ከተመለሱ በኋላ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በተገናኙባቸዉ አጋጣሚዎች ሁሉ የምርጫዉ መራዘም አገርን የሚጠቅም እስከሆነ ድረስ የ2012ቱ ምርጫ ሊራዘም እንደሚችል ፍንጭ መስጠታቸዉ የሚዘነጋ አይደለም።

በቅርቡ ጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድ በወቅታዊ የአገራችን ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ ምርጫዉ ይራዘም እና መራዘም የለበትም የሚሉ የየራሳቸዉ ምክንያት ያላቸው የፖለቲካ ኃይሎች እንዳሉ ገልጸዉ የሳቸዉ ድርጅት ኢህአዴግ ግን ምርጫዉ ይራዘም የሚል አቋም እንደሌለዉ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፓሬሺን አስደምጦናል። አገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ ለምትገኝበት እጅግ በጣም አሳሳቢ ሁኔታ አያሌ ኩነቶችን አንደ ምክንያት መጥቀስ ይቻላል። ባለፉት ሰማንያ አምስት አመታት ኢትዮጵያ ዉስጥ የነበሩት መንግስታት የገነቡት የፖለቲካ ስርአት አግላይ የሆነ የጥቂቶች ስርአት መሆኑና እነዚሁ መንግስታት የዘረጉት የኤኮኖሚ መዋቅር አብዛኛዉን ህዝብ ድሃ ያደረገ ነጣቂ የኤኮኖሚ መዋቅር መሆኑ ኢትዮጵያ ዛሬ ለገባችበት አዘቅት ዋነኛዉ ምክንያት ነዉ። ከዜህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ዉስጥ በሶስቱም መንግስታት ዘመን የተወሰኑት ትላልቅ አገራዊ ዉሳኔዎች ሁሉ የተወሰኑት በጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች ብቻ መሆኑ ለዛሬዉ ችግራችን ምክንያት ነዉ።

ባለፉት ሃምሳ አመታት ዉስጥ አገራችን ኢትዮጵያ ለሶስተኛ ግዜ ምናልባትም ለመጨረሻ ግዜ ወሳኝ የሆነ የታሪክ መታጠፊያ ላይ ቆማለች። ይህ የታሪክ መታጠፊያ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባለድርሻዎች በሚቀጥሉት ሃምሳና መቶ አመታት አገራቸዉ ኢትዮጵያ የምትጓዝበትን አቅጣጫ የሚያመለክቱ ትላልቅ ዉሳኔዎችን የሚወስኑበትና ለዘመናት ላጨቃጨቁን የፖለቲካ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተው የአዲሲቱን ኢትዮጵያ መሰረት የሚጥሉበት አጋጣሚ ነዉ እንጂ ሁላችንንም ተሸናፊ ሊያደርግ ወደሚችል ምርጫ ሮጠዉ የሚገቡበት አጋጣሚ አይደም። እንደዚህ አይነቶቹን በዛሬዉ ትዉልድ ላይ ብቻ ሳይሆን በተከታታይ ትዉልድ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ትላልቅ አገራዊ ዉሳኔዎችን እንደትናንቱ ዛሬም አንድ ቡድን ብቻዉን የሚወስን ከሆነ ይህ ብዙዎችን ያገለለ የአንድ ወገን ዉሳኔ ይቺን በነጋ በጠባ ለዘላለም ትኑር እያልን ረጂም ዕድሜ የምንመኝላትን አገር ማፍረስ እንደሚችል ልንገነዘብ ይገባል። እርግጠኛ ነኝ ማናችንም አይናችን እያየ ኢትዮጵያ ትፍረስ ወይም አትፍረስ የሚል ዉሳኔ ለመወሰን ጠረቤዛ ዙሪያ የምንቀመጥ አይመስለኝም። በአገራችን የወደፊት ዕድል ላይ የጋራ ዉሳኔ ስንወስን ከባዱ ነገር አገራችን ትፍረስና አትፍረስ ከሚል ዉሳኔ አንዱን መምረጥ አይደለም። በጣም ከባዱ ዉሳኔ አገራችን ለዘላለም የምትኖርበትን መንገድ ከሚጠቁሙ ሁለት አማራጮች ዉስጥ አንዱን መምረጥ ነዉ። ከነዚህ ሁለት አማራጮች አንዱን መምረጥ አቅቶን እርስ በርስ ስንባላ ነዉ አገራችን የመፍረስ አደጋ ዉስጥ የምትገባዉ። አገራችን ኢትዮጵያን ከጥፋት የምናድነዉ በእኛም በኢትዮጵያም ህይወት ዉስጥ እጅግ በጣም ከባድ ነዉ የሚባለዉን ዉሳኔ በድፍረት፥ በብልሃትና በአርቆ አሳቢነት መወሰን ከቻልን ብቻ ነዉ። በአገር ላይ የሚወሰን ከባድ ዉሳኔ ደግሞ ከሌሎች ጋር መምከርንና በጥሞና ማሰብን ይፈልጋል እንጂ ለብቻ አይወሰንም። ይህ በታሪክ መታጠፊያ ላይ ቆመን የምንወስነዉ ታሪካዊ ዉሳኔ ድፍረት፥ብልሃት፥ማሰብና መምከር ብቻ ሳይሆን ሰፊ ግዜም ይፈልጋል።

የአንድ አገር ዲሞክራሲ ጥንካሬና ዘላቂነት አገሪቱ ከገነባቻቸዉ ዋና ዋናዎቹ የዲሞክራሲ ተቋማት አይነትና ጥንካሬ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነዉ። ዲሞክራሲ ዛሬ አለማችን ዉስጥ ካሉት ስርአቶች ሁሉ የተሻለዉ ስርአት ነዉ እንጂ እንከን የለሽ ስርአት አይደለም። ስለሆነም አገሮች ዲሞክራሲን ሲገነቡ ከአገራቸዉ ተጨባጭ ሁኔታዎች (ባህል፥ ታሪክ፥የፖለቲካ ልምድና ማህበራዊ አደረጃጀት) ጋር እያዛመዱ ነዉ መገንባት ያለባቸዉ እንጂ ሁሉም አገር  ዉስጥ የሚሰራ ወይም ለሁሉም አገር የሚመች አንድ ወጥ የሆነ ዲሞክራሲ የለም። ስለዚህ እኛም አገር ዉስጥ ምን አይነት ዲሞክራሲ ነው የሚያስፈልገን የሚለዉን ጥያቄ ለመመለስ፥አገራችን ዉስጥ ያለዉን ተጨባጭ ሁኔታ፥ የፓለቲካ ታሪካችንን፥ የዲሞክራሲ ባህላችንን፥ ማህበረሰባቸን ዉስጥ ያለዉን ፖለቲካዊ አሰላለፍና የማህበረሰባችንን የዕድገት ደረጃ በሚገባ መመርመርና መፈተሽ አለብን። የዚህ ምርመራና ፍተሻ ዉጤት ነዉ ምን አይነት ዲሞክራሲ ያስፈልገናል የሚለዉን ጥያቄ የሚመልስልን፥ ደግሞም ምን አይነት ዲሞክራሲ ያስፈልገናል ለሚለዉ ጥያቄ መልስ ካገኘን በኋላ ነዉ ወደ ምርጫ መሄድ ያለብን። ካለዚያ ከፈረሱ ጋሪዉ ይቀድምና መሄጃዉም መድረሻዉም ይጠፋናል።

ዲሞክራሲ ልምዱም ባህሉም በሌለባቸዉ አገሮች ዉስጥ ሊገነባ ይችላል (ጋና ቦትስዋና) ፥ ዲሞክራሲ ተገንብቶ በፈረሰባቸዉ አገሮች ዉስጥ እንደገና ሊገነባ ይችላል (ስፔን ጀርመን)፥ ዲሞክራሲ ለአመታት የእርስ በርስ ጦርነት በተካሄደባቸዉ አገሮች ዉስጥ ሊገነባ ይችላል (ቦስኒያ ሰርቢያ) ፥ ዲሞክራሲ የረጂም አመት የመብትና የነጻነት ትግል በተደረገባቸዉ አገሮች ዉስጥ ሊገነባ ይችላል። ዲሞክራሲ በአንድ በኩል ብዙ ማንነቶች እና የባህልና የሃይማኖት ስብስቦች ባሉባቸዉ አገሮች ዉስጥ፥በሌላ በኩል ደግሞ እራስን በራስ የማስተዳደር እና የመገንጠል ጥያቄ በተነሳባቸዉ አገሮች ዉስጥ ሊገነባ ይችላል።     አንዳንድ አገሮች ከሞላ ጎደል አንድ ወጥ ቋንቋና ባህል ያለባቸዉ አገሮች ናቸዉ፥ አንዳንድ አገሮች ደግሞ ብዛት ያላቸዉ የተለያዩ ማንነቶች፥ ቋንቋዎች፥ ባህልና ሀይማኖት ያለባቸዉ አገሮች ናቸዉ። አንድ አገር ዉስጥ የዲሞክራሲ ግንባታ መሰረት ከመጣሉ በፊት እነዚህ በአገሮች መካከል ያሉ ልዩነቶች በሚገባ መጤን አለባቸው።

ኢትዮጵያ የፈላጭ ቆራጭ የንጉስ አገዛዝ፥ ወታደራዊ አምባገነን አገዛዝ እና ብሄር ተኮር ፖለቲካ የተፈራረቁባትና ሁለት ስር ነቀል አብዮቶች በተከታታይ የተካሄዱባት አገር ናት። ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ለረጂም አመታት በመሳሪያ የታገዘ የመብትና የዲሞክራሲ ትግል የተካሄደባት ብቻ ሳትሆን የብሄር ጥያቄ፥ እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄና የመገንጠል ጥያቄ የተነሳባት አገር ናት። እነዚህ እዉነቶች እና የዛሬዉ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የሚነግረን አንድ ትልቅ ሀቅ አለ፥ እሱም ኢትዮጵያ እነዚህን ለዘመናት የተነሱ ጥያቄዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ሊመልስ በሚችል አገረ-ግንባታ ሂደት ዉስጥ ማለፍ እንዳለባት ነዉ። የዚህ አገረ-ግንባታ ሂደት አላማ ዛሬ የአገራችንን የተለያዩ ማንነቶች እና የወል ስብስቦች በእኩልነት ማስተናገድ የሚችልና የግለሰብንና የቡድንን መብት የሚያከብር ዲሞክራሲያዊ ስርአት መሰረት መጣል ከሆነ ዉጤቱን እናዉቀዋለንና የሚያሰጋን ነገር አይኖርም። በዚህ ለአገራችን እጅግ በጣም  አስፈላጊ በሆነ ሂደት ዉስጥ ከማለፋችን በፊት ምርጫ ችግራችንን ይፈታል በሚል ምርጫ ዉስጥ ብንገባ ግን የምርጫዉን ዉጤት ተከትሎ ምን ሊመጣ ይችላል የሚለዉን ጥያቄ መልስ ከወዲሁ ማውቅ አንችልም። የምናስባቸዉና የምንሰራቸዉ ስራዎች ሁሉ በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአገር ደረጃም ነዉና ዉጤቱን የምናዉቀው የተሻለ አማራጭ እያለ ዉጤቱን የማናወቀዉ አማራጭ ዉስጥ መግባት ያለብን አይመስለኝም።

የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ አላማ እንደ አገር አንድነታችንን አስጠብቀዉ የሚያስቀጥሉንን እና ሁላችንንም አቅፈዉ በእኩልነት የሚያኖሩንን ተቋሞች በጠንካራ መሰረት ላይ አቁመን ወደ ምርጫ ብንሄድ ይሻላል እንጂ የእነዚህ ተቋሞች መሰረት ሳይጣል ከምርጫዉ ሰሌዳ ጋር ሙጭጭ ማለት አደጋ አለዉ የሚል ነዉ። ገዢዉ ፓርቲ ኢህአዴግ እና ምርጫዉ በተያዘለት ሰሌዳ ካልተካሄደ ኢትዮጵያ ትበተናለች የሚሉ ሀይሎች ሊረዱት የሚገባ ነገር ቢኖር፥ በአገራችን የወደፊት ጉዳዮችም ሆነ በምርጫዉ ሰሌዳ ላይ ተቀራርበን መነጋገር ነዉ አገራችንን ከመበታተን የሚያድናት እንጁ በራችንን ቅርቅር አድርገን ዘግተን “ምርጫ ወይም ሞት”እያልን ብንጮህ ጩኸቱ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ መፈክሮች ያሰሙንን አምባገነኖች ያስታዉሰን ይሆናል እንጂ ሌላ ምንም የሚፈይደዉ ፋይዳ የለም። ዛሬ ሁላችንም የምንቆጨዉ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሤ እንዲህ አድርገዉ ቢሆን ኖሮ፥ ደርግ እንዲህ አድርጎ ቢሆን ኖሮ፥ ህወሓት/ኢህአዴግ እንዲህ አድርጎ ቢሆን ኖሮ እያልን ነዉ። ለመሆኑ እኛ ዛሬ ያለንበት ቦታ ምን አይነት ቦታ እንደሆነ ገብቶናል?  እኛኮ ያለነዉ ትናንት እነዚህ  ሰዎች በነበሩበት ቦታ ምናልባትም በተሻለና ከነሱም በላይ እጅግ በጣም ወሳኝ በሆነና ቆራጥ ዉሳኔ በሚፈልግ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ነዉ። የቀኃስ፥ የደርግና የህወሓት/ኢህአዴግ ስርአቶች ያጠፉት ጥፋት ደካማና የተከፋፈለች ኢትዮጵያን አስረክቦናል። እኛ የምናጠፋዉ ጥፋት ግን ለሚቀጥለው ትዉልድ የሚያስረክበዉ አገር አይኖርም!

ምርጫ ምትክ የማይገኝለትና የአንድ አገር ህዝብ ሉዓላዊነቱን የሚያረጋግጥበት ወይም ህዝብ ብቸኛ የፖለቲካ ስልጣን ምንጭና ባለቤት ለመሆኑ ማረጋገጫ መሳሪያ ነዉ። ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ምርጫዉ ይገፋ ወይም አይገፋ የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎችን እያጨቃጨቀ ያለዉ ይህንን እዉነት ማወቅና አለማወቅ አይደለም።  ኢትዮጵያ የምትገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ ለምርጫ አመቺ ነዉ ወይስ አይደለም? ነጻና ገለልተኛ የሆኑ ዲሞክራሲያዊ ተቋሞች ሳይኖሩን ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ እንችላለን ወይ? ጡዘቱ እንኳን እኛን ጎረቤቶቻችንን ያስጨነቀ ብሄረተኝነት በነገሰበት አገር ዉስጥ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ወይ? አንደ አገር የሚያስተሳስሩን ማህበራዊ እሴቶች በተናዱበትና ሌላ ቢቀር በሰንደቅ አላማዉ እንኳን የማይግባባ ህዝብ ባለበት አገር ዉስጥ በምርጫ ያሸነፈዉ ፓርቲ ምን አይነት አገር ነዉ የሚረከበዉ?በፌዴራል ስርአቱ ዉስጥ የፌዴራሉን ከፍተኛ ፍርድ ቤት  ትዕዛዝ የሚጥሱ፥የፌዴራሉ ፓርላማ የወሰነዉን ዉሳኔ አንቀበልም የሚሉና የኢትዮጵያን ህዝብ ቀርቶ እንመራዋለን የሚሉትን የራሳቸዉን ክልል ህዝብ የማይወክልም የማይመጥንም መግለጫ በየቀኑ የሚሰጡ የክልል መሪዎች ባሉበት አገር ዉስጥ ምን አይነት ምርጫ ነዉ የምናካሄደዉ? አገራችንን አላነቃንቅ ብለዉ ቀስፈዉ የያዙን ትላቅል ችግሮች ፊት ለፊታችን ላይ ተደቅነዉ፥ የባሰ ሊያበጣብጠን ወደሚችል ምርጫ ዉስጥ ካልገባን እያልን አፋችንን ሞልተን የምንናገር የፖለቲካ ሰዎች ከምርጫዉ የምንጠብቀዉ የራሳችን ጥቅም አለ፥ የችግሩ ስፋትና ጥልቀት አልገባንም ወይም ለወደፊቱ ትዉልድ ያለን አመለካከት ዝቅተኛ ነዉ። እነዚህን ከላይ  የተጠየቁትን አምስት ጥያቄዎች የዛሬዉን የራሳችንን የፖለቲካ ጥቅም እያሰብን ሳይሆን የነገዉን የአገራችንን ጥቅም ተመልክተን አግባብ ባለዉ መልኩ ሳንመልስ ህገ መንግስቱ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በየአምስት አመቱ በህዝብ ይመረጣሉ ተብሎ ስለተጻፈ ብቻ ሮጠን ወደ ምርጫ የምንገባ ከሆነ ሊመጣ የሚችለዉን ጥፋት ህገ መንግስቱ ላይ የተጻፉት 106 አንቀጾች አያቆሙትም።

ከረጂም ግዜ የርስበርስ ጦርነትና ግጭት የተላቀቁ አገሮች ሰላምና መረጋጋት ያመጣልናል በሚል ተቻኩለዉ ወደ ምርጫ እንደገቡና የምርጫዉ ዉጤት የባሰ ትልቅ ቀዉስ ዉስጥ ይዟቸዉ እንደገባ ከሶቭየት ህብረት መፈራረስ በኋላ ዲሞክራሲን የገነቡ አገሮች ታሪክ በግልፅ ያሳየናል።ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ቅቡልነት ያለዉ መንግስት አንዲፈጠር ስለሚያደርግ ለሰላምና መረጋጋት አስፈላጊ ስለመሆኑ ጥርጥር የለዉም። ነገር ግን ምርጫዉን ነጻና ፍትሃዊ ማድረግ የሚችሉ ተቋሞች ሳይኖሩ ምርጫዉ እንዴት ነጻና ፍትሃዊ ሊሆን ይችላል? በብዙ አገሮች ዉስጥ የተደረጉ ሳይንሳዊ ጥናቶች የሚነግሩን እዉነት ቢኖር፥ ጎራ ለይተዉ በታገሉ የፖለቲካ ባለድርሻዎች መካከል መግባባት ሳይፈጠር፥አገርን እንደ ሙጫ አጣብቀዉ የሚይዙ የዲሞክራሲ ተቋሞች ግንባታ ሳይጀመርና የዜጎች መብት፥ ነጻነትና እኩልነት መከበራቸውን የሚያረጋግጡ ተቋሞች ሳይኖሩ ወደ ምርጫ የገቡ አገሮች በቀላሉ ወደማይወጡት ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀዉስ ዉስጥ እንደገቡ ነዉ። በተለይ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ የብሄር ማንነት የሁሉም ነገር መለኪያ በሆነባቸዉ አገሮች ዉስጥ ምርጫን ማሸነፍና መሸነፍ ቀርቶ የብሄራዊ ፈተና ውጤትም ከብሄር ማንነት ጋር በቀጥታ ስለሚያያዝ የብሄር ፖለቲካ ተቋማዊ ልጓም ሳይበጅለት ምርጫ ዉስጥ ቸኩሎ መግባት መዘዙ ብዙ ነዉ።

ካምቦዲያ፥ቦስኒያ፥ ኮሶቮ፥ ኢራቅና አፍጋኒስታን ዉስጥ በግልጽ እንደታየዉ፥ በድህረ-ግጭት ማህበረሰቦች ዉስጥ ምርጫ የርስ በርስ ጦርነቶችን ያቆማል፥የታጠቁ ኃይሎችን ወደ ሰላማዊ ፓርቲ ፖለቲካ ይስባል ደግሞም የፖለቲካ ቅቡልነትን ይፈጥራል በሚል ሰላምና መረጋጋት ሳይኖር፥ ምን አይነት ዲሞክራሲያዊ ስርአት መገንባት እንዳለበት በፖለቲካ ባለድርሻዎች መካከል ስምምነት ሳይፈጠር፥ብሄረተኝነት በገነነበት እና የምርጫዉን ነጻና ፍትሃዊ መሆን የሚያረጋግጡ ተቋሞች ሳይኖሩ አገሮች ወደ ምርጫ እንዲገቡ የሚገፋፋዉ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ነዉ። ይህ የሚያሳየን አለም አቀፉ ማህበረሰብ በድህረ-ግጭት ማህበረሰቦች ዉስጥ ምርጫን የሚመለከተዉ የአገረ-ግንባታ ሂደቱ መልክ ከያዘ በኋላ ግዜዉን ጠብቆ መምጣት እንዳለበት አንድ ምዕራፍ ሳይሆን የአገረ-ግንባታዉ ሂደት መጀመሪያና መጨረሻ ቁልፍ አካል አንደሆነ አድርጎ ነዉ። በእርግጥ ምርጫ ቁልፍና ወሳኝ የሆነ የዲሞክራሲ ሂደት አካል ነዉ፥ ሆኖም ግን ምርጫ በአገረ-ግንባታ ሂደት ዉስጥ እንዴት፥ በማንና ለምን መካሄድ አለበት የሚሉ ጥያቄዎችን የሚመልሱ ተቋሞች ጥንስስ ከተጣለ በኋላ መምጣት ያለበት በአገረ-ግንባታ ሂደት ዉስጥ የአንድ ትልቅ ምዕራፍ (Milestone) መቋጫ ነዉ እንጂ የአገረ-ግንባታ ሂደት መጀምሪያ አይደለም፥ መሆንም አይችልም። በድህረ-ግጭት ማህበረሰቦች ዉስጥ የአገረ-ግንባታዉ ሂደት የሚፈለግበት ደረጃ ላይ ሳይደርስ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊት ተቻኩለዉ ምርጫ ያካሄዱ ኢራቅና አፍጋኒስታንን የመሳሰሉ አገሮች ዛሬም ድረስ የተረጋጋ ማህበረሰብ መፍጠር አልቻሉም።

የጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድ መንግስት ወደ ሥልጣን ከመጣበት ግዜ ጀምሮ የህወሓት/ኢህአዴግን መንግስት በሙሉ ኃይላቸዉ ሲረዱ የነበሩት ትላልቆቹ መንግስታትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ ሌሎችም  አለም አቀፍ ተቋማት በሚቀጥለው የአገራችን ምርጫ ላይ አሻራቸዉን ለማሳረፍ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው በተለያየ መልኩ ገልጸዋል። ሆኖም እነዚህ አካላት ከፍተኛ ትኩረት የሰጡት ኢትዮጵያ ምን አይነት ዲሞክራሲ ያስፈልጋታል ወይም ኢትዮጵያ የጀመረችዉን የአገረ-ግንባታ ሂደት እንዴትና በምን መልኩ ብንረዳ ነዉ የኢትዮጵያን ሰላምና ብልጽግና ማረጋገጥ የምንችለዉ በሚሉ ወሳኝ የረጂም ግዜ አገራዊ ግቦች ላይ አይደለም። ይልቁንም የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ትኩረት የሚቀጥለውን ምርጫ እንዴት ነዉ የምንረዳዉ በሚል የአጭር ግዜ ግቦች ላይ ነዉ። ይህ ነዉ ተብሎ ሊነገር የሚችል የዲሞክራሲ ልምድ በሌለባትና ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በሚኖርባት ደሃ አገር ዉስጥ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ ቀርቶ ዉጤቱ ከወዲሁ የታወቀ የይስሙላ ምርጫ ማካሄድም እጅግ በጣም ያስቸግራል። ስለዚህ አለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚቀጥለውን ምርጫ አስመልክቶ ሊረዳን በማሰቡ ልናመሰግነዉ ይገባል። ሆኖም ምርጫዉን ማካሄድ የምንችልበት ሁኔታ ሲፈጠር  ነዉ ማካሄድ ያለብን እንጂ ለምርጫዉ ስንል የረጂም ግዜ ጥቆሞቻችንን ትተን በአጭር ግዜ ጥቅሞቻችን ላይ ማተኮር የለብንም፥ ከትክክለኛ  ውክልና ይልቅ ብልጭ ብሎ ድርግም የሚል መረጋጋት ላይ ማተኮር የለብንም፥ የፖለቲካ ስምምነት ከሚፈጥረዉ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ይልቅ ታይቶ ወዲያዉ ሊጠፋ በሚችል የፖለቲካ ቅቡልነት (Political Legitimacy) ላይ ማተኮር የለብንም።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባለድርሻዎች ባለፈዉ ታሪካችን ላይ የሚያደርጉትን ማለቂያ የሌለዉ እሰጥ አገባ አቁመዉ የልጅ ልጆቻችን ባጠቃላይ መጪዉ ትውልድ የኔ ነዉ ብሎ የሚቀበለውን አዲስ ታሪክ መጻፍ መጀመር አለባቸዉ። የዚህ አዲስ ታሪክ የመጀመሪያዉ ምዕራፍ በፍትህ፥ በዲሞክራሲና በፖለቲካ ተቋሞች  ግንባታ መጀመር አለበት።ምን አይነት የፌዴራል አወቃቀር ነዉ የሚበጀን፥ምን አይነት የመንግስት ቅርፅ ነዉ የሚያስፈልገን (ፓርላማዊ፥ ፕሬዚደንታዊ፥ ግማሽ ፕሬዚደንታዊ) ምን አይነት የምርጫ ስርአት ነው የሚያስፈልገን (አብላጫ ድምጽ፥ተመጣጣኝ ) በሚሉ የአገራችንን የወደፊት አቅጣጫ በሚወስኑ ትላልቅ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባለድርሻዎች ዉይይት መጀመር አለባቸዉ፥ የኢትዮጵያ ህዝብም በዉይይቱ ላይ የራሱን ድምጽ የሚያሰማበትን መንገድ መፍጠር አለባቸዉ። በእነዚህ ትልልቅ የአገራችንን የወደፊት አቅጣጫ በሚወስኑ ተቋሞች ላይ የሚደረጉ ዉይይቶች ለነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ቅርፅና ይዘት የሚሰጡ ዉይይቶች ስለሆኑ፥ እነዚህ ዉይይቶች መጠናቀቅ ያለባቸው ወደ ምርጫ ከመግባቻችን በፊት ነዉ። የእነዚህ ትላልቅ ተቋሞች መሰረት ከተጣለ በኋላ ምርጫ ዉስጥ የመግባት ትዕግስቱ ቢኖረን መልካም ነዉ። ነገር ግን ይህ ሂደት ብዙ ግዜ ስለሚወስድ አደጋ አለዉ የሚሉ ኃይሎችን ስጋት እንጋራ ብንል እንኳን በእነዚህ ትላልቅ ጉዳዮች ላይ ሁላችንንም የሚያግባባ ስምምነት ላይ ደርሰን ወደ ምርጫ ብንሄድ የምርጫዉን ዉጤት ባንወደዉም ውጤቱን ተቀብለንና አክብረን ለሚቀጥለው ምርጫ እንዘጋጃለን እንጂ እርስ በርስ  የሚያናክስ ሁኔታ ዉስጥ አንገባም።

አገራችን ኢትዮጵያ ተደጋጋሚ የአገረ-ግንባታ ሂደቶች ተጀምረዉ ፍጻሜ ያላገኙባት አገር ናት፥ ኢትዮጵያ አክራሪ ብሄረተኝነት የነገሰባትና እንዲሁም ሰላምና መረጋጋት ያጣች አገር ናት። ኢትዮጵያ የማይግባቡና አንዳንዴም  የሚቃረን የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸዉ የፖለቲካ ባለድርሻዎች ያሉባት አገር ናት።ኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት የተካሄደባትና በአለማችን ዉስጥ መገንጠል በተግባር ከታየባቸዉ በጣት ከሚቆጠሩ አገሮች ዉስጥ አንዷ ናት። ኢትዮጵያ አሁንም መገንጠልን ያለ ምንም ቅደመ ሁኔታ እንደ ትልቅ መብት ህገ መንግስቷ ዉስጥ ያስቀመጠች “እኛ ያልነው ካልሆነ እንገነጠላለን” የሚሉ “ሃይለኞች” ያሉባት አገር ናት። ኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስቱን የሚገዳደር የታጠቀ ልዩ ሃይልና የራሳቸዉ የሆነ ሜዲያ ያላቸዉ በብሄር የተደራጁ ክልሎች የሚገኙባት አገር ናት።እነዚህ የኢትዮጵያን ህልዉና የሚገዳደሩ እጅግ በጣም አሳሳቢ ሁኔታዎች የመርገብ ምልክት ሳይታይባቸዉና በትልልቆቹ የአገራችን ጉዳዮች ላይ ምንም አይነት አገራዊ ስምምነት ላይ ሳይየደረስ ህገ መንግስታዊ ግዴታ ነው በሚል መርህና በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊት ምርጫ ዉስጥ ብንገባ ከምርጫዉ በኋላ ሊመጣ የሚችለዉን ጥፋት ሀገ መንግስቱም አለም አቀፉ ማህበረሰብም ሊያቆሙት አይችሉም። ኢትዮጵያን ከጥፋት ለማዳንና የዚችን ትልቅና ታሪካዊ አገር ቀጣይነት ለማረጋገጥ፥ህገ መንግስቱን ማሻሻል፥ እንደገና መጻፍ፥ ይህ ሁሉ የማይቻል ከሆነ ደግሞ አገር ለማዳን ሲባል ህገ መንግስቱን በከፊል ወይም በሙሉ እስከማገድ ድረስም መሄድ አለብን ብሎ የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ ያምናል። የኢትዮጵያን ህልዉና በተመለከተ ህገ መንግስቱ ለኢትዮጵያ መኖር ይኖራል እንጂ ኢትዮጵያ ለህገ መንግስቱ መኖር አትኖርምና የ2012ቱን ምርጫ ሰሌዳ በተመለከተ የምንወስነዉ ዉሳኔ ከኢትዮጵያ ህልዉና ጋር በቀጥታ የተያያዘ መሆኑን ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባል። ኢህአዴግ ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት ብቻ ሳይሆን አገራችን በለዉጥ እንቅስቃሴ ዉስጥ በቆየችባቸዉ ባለፉት 16 ወራት ዉስጥም የወሰናቸዉንና መወስን ሲገባዉ ያልወሰናቸዉን ዉሳኔዎች ስንመለከት በዚህ በአገራችን ታሪክ ዉስጥ እጅግ በጣም ወሳኝ በሆነ የሽግግር  ወቅት ትልልቆቹን አገራዊ ዉሳኔዎች ኢህአዴግ ብቻዉን እንዲወስን መፍቀድ 1966ን እና 1983ን መድገም ይሆናል። ይህንን የብቻ ዉሳኔ የኢህአዴግ ሰዎችም የሚፈልጉት አይመስለኝም፥ ደግሞም እንዲህ አይነቱን ከትዉልድ ወደ ትዉልድ የሚተላለፍ ታሪካዊ ዉሳኔ አንድ ወገን ብቻ እንዲወስነዉ መፍቀድ ኢህአዴግን ብቻ ሳይሆን ሁላችንንም ከታሪክም እኛዉ እራሳችን ደግመን ደጋግመን ካጠፋነዉ ስህተትም የማንማር የፖለቲካ ገለባዎች ያደርገናል። እኛ በአባቶቻችን እንደምንኮራ በእኛ መኩራት የሚገባዉና እኛን አባቶቼ ብሎ የሚጠራዉ መጪዉ ትዉልድ ታሪካችንን ሲጽፍ የመጽሀፉ መግቢያ ላይ የሚጽፈዉ “አባቶቻችን ከታሪክ የተማሩት  ጥፋትን መድገም ነዉ” የሚል አሳፋሪ ሀረግ ይሆናል።

emadebo@gmail.com    እዚህ ጽሁፍ ዉስጥ ያለዉ ሃሳብ ሁሉ የኔ የኔና የኔ ብቻ ነዉ!


  Subscribe to the  Zaggolenews online news magazine


 

የለውጥ ዕድሎች ለምን ይከሽፋሉ? – በፍቃዱ ሃይሉ

ትላንት በአዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚክ ኮሚሽን ለአፍሪካ አዳራሽ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ለውጥ ሒደት በተመለከተ ትልቅ ኮንፈረንስ ሲካሔድ ነበር፤ ኮንፈረንሱ ዛሬም ይቀጥላል። በኮንፈረንሱ ላይ ከቀረቡት የውይይት አጀንዳዎች መካከል ቀልቤን የሳበው “በኢትዮጵያ ታሪክ የተሳኩ እና የከሸፉ የለውጥ ሒደቶች” የሚለው ነበር። ውይይቱን የመሩት ገብሩ ታረቀ (ዶ/ር) የአንቶኒ ግራምሺን አባባል ተውሰው “የመጣበትን መመልከት ያልቻለ፥ የሚሔድበትን አያውቅም” በማለት ነበር ከታሪክ የመማርን አስፈላጊነትን ያስረዱት። እውነትም ግን ያለፉት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ዕድሎች ስለምን ከሸፉ? ዛሬስ ካለፈው ምን መማር እንችላለን።

ከፈረሱ ጋሪው እየቀደመ

አንጄሎ ዴል ቦካ የተባሉ ጣልያናዊ በደረሱት “ላ ንጉሥ” የተሰኘ መጽሐፍ ላይ የ1953ቱን የኢትዮጵያ መፈንቅለ መንግሥት እንዲህ የሚያስታውሱት “ሕዝቡ በገለልተኝነት የተመለከተው” ክስተት እንደሆነ አድርገው ነው። ይህ ገጠመኝ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ትዕይንት የሚገልጽ ነው። ብዙ ጊዜ ሕዝቡ የፖለቲካ ጥያቄዎች እና መልሶች ተመልካች እንዲሆን ከመደረጉ በስተቀር የሚማከርበት ዕድል አያገኝም። ማርቲን ሉተር ኪንግን ጨምሮ ብዙ ስኬታማ የሲቨል ነጻነት ንቅናቄ መሪዎች እንደሚናገሩት የሁሉም ነገር መጀመሪያ ሕዝብን ማንቃት ነው። ሕዝብ ትግሉ ለምን እንደሆነ ማወቅ አለበት። በመቀጠል መደራጀት እና መተግበር ነው። ሆኖም በኢትዮጵያ የተከሰቱ የለውጥ ዕድሎች በሙሉ በልኂቃኑ ይሁንታ የመጡ እና የሔዱ በመሆናቸው ሕዝቡ የኹነቱን ጥቅምና ጉዳት ሳይረዳ፣ ወደ ተግባር ለመሔድ የሚደረገው ጥረት ደጋፊ በማጣት ለክሽፈት ይዳርጋል።

የሕዝቦች ትግል እየተጠለፈ

በ1966ቱ ሕዝባዊ አብዮት የተጠናቀቀው በወታደራዊው መንግሥት ተጠልፎ ነው። ምንም እንኳን ዋናው የትግሉ መሪዎች እና የጥያቄዎቹ አቅራቢዎች የሠራተኛ ማኅበራት፣ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ማኅበራት እና የመሳሰሉት ቢሆኑም ደርግ በመጨረሻ ቤተ መንግሥት በመግባት እና የአብዮቱ ጠባቂ አድርጎ ራሱን በመሾም ከመሬት ላራሹ በቀር ሌሎች ጥያቄዎች ሊመለሱበት የሚችሉትን ሕዝባዊ መንግሥት የመመሥረት ሕልም አጨናግፏል። አሁንም በተመሳሳይ መንገድ ለዓመታት በተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ሲካሔድ የነበረውን ተቃውሞ የኦዴፓ እና አዴፓ ጥምረት እንደመሰላል ተንጠላጥሎበት የኢሕአዴግ አንድ ቡድን በአሸናፊነት እንዲወጣ እና በባለድልነት እንዲፎክር አድርጎታል። ይህም በተቃውሞ ጉልህ ተሳትፎ የነበራቸውን አካላት በመጪው የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ላይ ይህ ነው የሚባል ተሳትፎ የሚያደርጉበትን ዕድል እንኳን እንዳያገኙ አድርጓል።

አንድ ችግርና አንድ መፍትሔ እየተፈለገ

በ1966ቱ አብዮትም ይሁን በ1983ቱ የስርዓት ሽግግር ወቅት የታዩት ተመሳሳይ ክስተቶች ይኸው የኢትዮጵያን ችግር አንድ ብቻ፣ መፍትሔውም አንድ ብቻ አድርጎ ማየት ነው። የአብዮቱ መሪዎች ነን ያሉት ሰዎች የኢትዮጵያ ችግር የመደብ ጭቆና ነው በሚል የመሬት ላራሹን ጥያቄ ከመለሱ በኋላ ሌላውን ሁሉ አለባብሰው ለማለፍ ሞክረዋል። በ1983 ደግሞ የኢትዮጵያ ችግር የብሔር ጭቆና ነው በሚል አገሪቱን በብሔር ፌዴራሊዝም በማወቀር ምዕራፉ ተዘግቷል በማለት ለማለፍ ሞክረዋል። በዚህም ኢትዮጵያ እንደማንኛውም አገር በአንዴ በርካታ ችግሮች፣ እና ለነዚህም መፍትሔ የሚሆኑ በርካታ አማራጮች የሚኖሯት አገር መሆኗን ዘንግተዋል። እየመጡ የሚሔዱት አገዛዞች ችግሮቹን ለዘለቄታው መፍታት የተቸገሩባቸውና ለውጦቹ የከሸፉበት አንዱ ምክንያት ይኸው አንድ ችግር ብቻ አለ የማለት አባዜ ነው።

ሥር ነቀል ለውጥ እየተመረጠ

ያለፈው የኢትዮጵያ ታሪክ እንደሚያስተምረን የለውጥ ዕድሎች ከሚከሽፉባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንደኛው ቀስ በቀስ በመሻሻል እና የተገኘውን ድል ይዞ ለተጨማሪ በመታገል ፈንታ፥ ሁሉንም ነገር በአንዴ ለማግኘት በመሞከር አልያም የተገኘውን በመናድ የማፈራረስ ልምድ አንዱ ነው። በ1966ቱ አብዮት ወቅት ምንም እንኳን ግዙፍ ጭቆና የነበረበት የፊውዳል ስርዓት ቢገረሰስምና የገባሩ ስርዓት ቢቀርም፣ ዴሞክራሲያዊነትም፣ ሶሻሊዝሙም አሁኑኑ ካልሆነ የሚለው የልኂቃኑ ፍላጎት ግን የተገኘውን ድል እንኳን በቅጡ ሳያጣጥሙ የአንድ ትውልድ ልኂቃን በገፍ ለእልቂት እንዲዳረጉ አስገድዷል። በተመሳሳይ በ1997ቱ ምርጫ ወቅት በተለይ ተቃዋሚዎች ገዢው ቡድን ያመነላቸውን የፓርላማ መቀመጫ በመቀበል እና እየተደራደሩ በመቀጠል ፈንታ ሁሉንም ካላገኘን የትኛውም ይቅርብን የሚመስል ዓይነት ውሳኔ በመወሰናቸው እዚያ የታሪክ ነጥብ ላይ ለመድረስ የተሔደው መንገድ ሁሉ የባከነ ሆኖ እንዲያልፍ አድርጓል።

ልኂቃኑን ማሥማማት እየከበደ

በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት የትላንቱ ውይይት ላይ ዲማ ነጎ የተባሉት ታዋቂ ፖለቲከኛ የኢትዮጵያ ልኂቃን መሐከል ያለው ክፍፍል ለታሪካዊ የለውጥ ዕድሎች መክሸፍ አንድ መንስዔ መሆኑን ይጠቅሳሉ። እውነትም፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልኂቃን በኢትዮጵያ ታሪክ አረዳዳቸው፣ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በሚበይኑበት መንገድ እና ኢትዮጵያ ወደ የት፣ በየት በኩል መሔድ አለባቸው የሚሉት ላይ በብዛት አይስማሙም። ይህም የለውጥ ዕድሎችን ለሁሉም በሚበጅ መልኩ እንዳይጠቀሙ አስገድዷቸዋል።

የውጭ ኀይሎች ጣልቃ እየገቡ

የውይይቱ ተሳታፊ የነበሩት ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ እና አምባሳደር ዶ/ር ተቀዳ ዓለሙ ደግሞ በኢትዮጵያ ተከስተው ለነበሩ የለውጥ ዕድሎች መክሸፍ የውጭ ኀይሎች ጣልቃ ገብነት ቀላል እንዳልነበረ ይሥማማሉ። በርግጥም ከአቤቶ እያሱ በተፈሪ መኮንን መገልበጥ ጀምሮ በተከሰቱ የተሳኩ እና ያልተሳኩ የለውጥ አጋጣሚዎች ውስጥ ከእንግሊዝ እስከ አሜሪካ እስከ የተባበሩት ሶቪየት ኅብረት ያሉ አገራት ጣልቃ ገብነቶች ቀላል የማይባሉ ሚናዎችን ተጫውተዋል።

የፖለቲካ ታሪክ ተመራማሪዎች “ከታሪክ የምንማረው ከታሪክ እንደማንማር ነው” በማለት ፖለቲከኞች የታሪክን ስህተት እንደሚደግሙ በስላቅ ይናገራሉ። አሁን ጥያቄው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ መሪዎች እና ጠቅላላው የፖለቲካ ልኂቃን በኢትዮጵያ ከ2010 አጋማሽ ጀምሮ እያየነው የነበረውን አዎንታዊ ለውጥ፥ ከታሪክ ተምረው ያስቀጥላሉ ወይስ ያለፈውን ታሪክ በመድገም ያከሽፉት ይሆን? የወደፊቱ ታሪክ ውጤቱን ይነግረናል።

ለትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ተግባራዊነት የጋራ ርብርብ ያስፈልጋል

 በተለያየ ዘመን የኖሩ ፈላስፋዎች፣ የስነ ጽሁፍ ሰዎችና የትምህርት ባለሙያዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ወዘተ ትምህርት ምንድ ነው? ለሚለው የተለያየ ብያኔ ሰጥተዋል፡፡ የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንትና የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ‹‹ትምህርት ማለት እጅግ ሃይለኛው አለምን የመቀየሪያ መሣሪያችን ነው›› ብለውታል፡፡ እአአ ከ1844 እስከ 1922 የኖረው ፈረንሳዊ ጸሃፊና ገጣሚ አናቶሌ ፍራንስ ደግሞ ‹‹ትምህርት ማለት ምን ያህል ሸምድደን በእምሮአችን ይዘነዋል፣አለያም ምን ያህል የመጻህፍትን ክፍሎች አንብበናል ሳይሆን የምናወቀውንና የማናውቀን ምን ያህል መለየት ችለናል የሚለውን መመለስ የሚያስችል ነው›› ሲል ገልጾታል፡፡

በትምህርት ቤቶች የሚሰጥ ትምህርት ዋነኛ ግብ ያለፉት ትውልዶች ያደረጉትንና የተማሩትን ብቻ መድገም ሳይሆን ተማሪዎች አዳዲስ ነገሮች መስራትና ማበልጸግ እንዲችሉ ብቁ ማድረግ መቻል መሆን አለበት፡፡ ስለሆነም ሃገራትና መንግስታት እንደየሃገራቸው ተጨባጭ ሁኔታ ማሳካት የሚፈልጉትን ግብ ታሳቢ በማድረግ የትምህርት ስርዓት ቀርጸው ይሠራሉ፡፡ በዚህ ስርዓት የሚማሩ ተማሪዎችም አለምን ለመቀየር፣ ክፉና ደጉን ለመለየት፣ ሃገርንና ህዝብን ወደ ብልጽግና ለመምራት፣ ስነምግባሩ የተጠበቀ ማህበረሰብ እንዲኖር ለማደረግ፣ ወዘተ በእውቀትና ክህሎት ይታነጻሉ፡፡

በሃገራችንም ዘመናዊ ትምህርት ከተጀመረ አንስቶ በርካታ ምሁራን ማፍራት ተችሏል፡፡ እነዚህ ምሁራን በየዘመናቸው የየራሳቸውን ስራ ሰርተዋል፤ እየሰሩም ነው፡፡ እነዚህ ምሁራን ለማፍራትም ወቅቱና ሁኔታው የሚፈቅደው ስርዓተ ትምህርት ተተግብሯል፡፡ አሁን በስራ ላይ ያለው ስርዓተ ትምህርትም ሃያ አራት አመታትን አስቆጥሯል፡፡ ይህ ስርአተ ትምህርት ስኬትም ውስንነቶችም ነበሩት፡፡ ስኬቶቹን ለማስቀጠል ውስንነቶቹን ደግሞ ለመቀነስ እኤአ 2030 ድረስ የሚተገበር የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ተጠናቆ ለትግበራ ጫፍ ላይ ደርሷል፡፡

በስራ ላይ የቆየው የትምህርት ስርዓት 4ሺ የነበሩትን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ወደ 39 ሺ፣278 የነበሩትን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ወደ 3ሺ300፣ 16 የነበሩትን የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤቶች ወደ 1ሺ546፣ ሁለት የነበሩትን ዩኒቨርሲቲዎች ወደ 50 እንዲሁም 2 ሚሊዮን የነበሩትን ተማሪዎች ወደ 28 ሚሊዮን ማሳደግ አስችሏል፡፡ ይህ በመንግስት ብቻ በተሰራ ስራ ነው፡፡ በእነዚህ አመታት በትምህርት የተገኘው ውጤት ሃገሪቱ ለተከታታይ አመታት ላስመዘገበችው ባለሁለት አሃዝ ኢኮኖሚያዊ እድገት፣በጤናው ዘርፍ ለተገኘው ስኬት፣ወዘተ. የራሱ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ ይህ ስኬት እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ውስንነቶችም ነበሩበት፡፡

በትምህርት ተደራሽነት ላይ አበረታች ሥራዎች የተሠሩ ቢሆንም፣ በትምህርት ጥራቱና አግባብነቱ ላይ ገና በርካታ ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮች መኖራቸዉን መንግሥት፣ የትምህርት ባለሙያዎችና የማህበረሰብ አባላት በተለያዩ መድረኮች ሲያነሱና ሲጽፉ ቅሬታ ሲያሰሙ ቆይተዋል። ከውስንነቶቹ መካከል የተማሪዎች መሰረታዊ ክህሎትና እውቀት አለመያዝ፣ ተመርቀው ሲወጡም የብቃትና ክህሎት ውስንነት መኖር፣ የተግባቦትና የምክንያታዊነት ክህሎት  ውስንነት፣ ሀገር አቀፍና አለምአቀፋዊ ጉዳዮችን ያለማወቅና ያለመረዳት፣ የስራ ፈጠራ ዝግጁነትና ተነሳሽነት ጉድለት እንዲሁም የስነ ምግባርና ግበረገብነት ህጸጾች መታየታቸው ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በተካሄደ ጥናት ተለይቷል፡፡

ስለሆነም በዚሁ መሠረት ቀጣይ የትምህርት ሥርዓቱ እንዲሻሻል በመታመኑ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ጥናት ተካሂዶ በሰነዱም ላይ በሀገር ደረጃ (በሁሉም ክልሎች፣ ከተማ መስተዳድሮችና በፌዴራል ባሉ ሴክተሮች) ከምሁራን፣ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላትና ከሕዝብ ጋር ግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ በሁለንተናዊ እድገታቸው የበቁና የላቁ ዜጎችን ማፍራት እንዲቻልም የትምህርት ስርኣቱ ከአደረጃጀቱ ጀምሮ ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ መፈተሽና መሻሻል እንዳለበት ዝርዝር ምከረሃሳቦች ቀርበዋል፡፡

በምክረ ሃሳቡ መሰረትም ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል፡፡ ይህ ፍኖተ ካርታ ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ በክህሎትና እውቀት፣ በስነ ምግባርና ግብረ ገብ እንዲሁም በስራ ፈጠራ ዝግጁነትና ተነሳሽነት፣ በተግባቦትና ምክንያታዊነት ክህሎት ብቁ ዜጋ ለማፍራት የሚያስችል ነው፤ እስከ 2022 ዓ.ም/እኤአ 2030/ የሚተገበር ነው፡፡ ስለሆነም ውጤቱ በሂደት የሚታይ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ የሁሉም ድጋፍና ርብርብም ይፈልጋል፡፡

የትምህርት ፋይዳው ዜጎችን በማህበራዊ፣ ስነ-ባህሪያዊ፣ አካላዊ፣ መንፈሳዊ፣ ሙያዊና አእምሯዊ አቅም እንዲጎለብቱ፣ እንዲለሙ እና የላቁ እንዲሆኑ አካባቢያቸውን ሀገራቸውን ብሎም አለምን በበጎ እንዲለውጡ ማስቻል ነው። የኢትዮጵያ መንግስትም ሀገራችንና ህዝቦቿን ከድህነት ለማውጣት፤ የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ለማድረስ፡ ብቸኛው አማራጭ የሰው ሀይላችንን በማስተማርና በማሰልጠን መሆኑን በማመን ለትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ በጀት እየመደበ የዜጎችን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡

በዚህም መሰረት ፍኖተ ካርታው በተለይ በከፍተኛ ትምህርት በአእምሮ የጎለመሱ፣ በሙያቸው የበቁ፣ በመንፈሳቸው የተረጋጉ፣ በስነባህሪያቸው የበሰሉ፣ ምክንያታዊና ሚዛናዊ የሆኑ ስነምግባር ያላቸው የአገራቸውንና የማህበረሰባቸውን ታሪክና እሴቶች አውቀው በማክበርና በመጠበቅ ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ ለሀገራቸው እድገትና ለሕዝባቸው ልእልና የሚተጉና ለአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ከመዘጋጀት አልፈው የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች፣ አልሚዎች፣ ተግባሪዎች የሚሆኑ ዜጎችን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ተብሎ በትምህርት ሙያና በሌሎች ዘርፎች ምሁራን በጥናት የተለዩና በየደረጃው ሰፊ ዉይይቶች የተካሄደባቸውና ስምምነት የተገኘባቸውን የኮርሶች ስብስቦች ከነ ይዘታቸው ዝግጁ ሆነዋል፡፡

ከዩኒቨርሲቲ አመራሮችና ማህበረሰብ አባላት ጋር በተለይ ኮርሱን የሚሰጡ ባለቤት የትምህርት ክፍሎች ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ እነዚህም ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በአንደኛ አመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡ ስለሆነም ለትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታው ትግበራ ስኬት ተማሪዎች፣ ወላጆች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህበረሰብና መንግስት ተቀናጅተው ሊረባረቡ ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን ነሐሴ 14 ቀን 2011 ዓ.ም

ፌደራሊዝም እነርሱ ሲሉን እኛ ፌደራሊስም ስንል እና የአፓርታይድ ስርአት መንግስቱ ሙሴ

መንግስቱ ሙሴ

የዛሬ 69 አመት ህወሓት እና ኦነግ ከመፈጠራቸው 17 አመታት ቀደም ብሎ የደቡብ አፍሪካ የትቂት ነጮች አፓርታይድ መንግስት ለደቡብ አፍሪካ እና ለደቡብ ምእራብ አፍሪካ ሕዝቦች የራሳቸው ፌደራሊዝም ሰጥተው ነበር። የአፓርታይድ ነጮች የመሰረቱት ፌደራላዊነት ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለው አይነት የሚመሳሰል ፌደራላዊነት ነበር። የአፓርታይድ ነጮች 10 Ethno-linguistic (የዘር እና ቋንቋ) ተመሳሳይነት ለአላቸው የደቡብ አፍሪካ ጎሳወች Bantu homeland በሚል የራሳቸው የሆነ የዘር ክልሎች መስርተው ሰጧቸው። እነዚህ የባንቱስታን ክልሎች በተለያየ አመት የተከለሉ ሲሆን ትራንስካይ (Transkei) 1976, Bophuthatswana 1977, Venda 1979, Ciskei 1981 እና ሌሎች ስድስቱን ጨምሮ  Gazankulu, KwaZulu, Lebowa, KwaNdebele, KaNgwane እና Qwaqwa ን በተመሳሳይ አመት ከልለው ለጥቁሮች ከሰጡ በኋላ ባንቱስታ የጥቁር አፍሪካውያን ሆምላንድ በሚል የዘረኛ ስርአታቸውን አጠናክረው ነበር።

ህወሓት/ኢሕአዴግ በ 1987 አም ባጸደቁት ህገመንግስት የደቡብ አፍሪካ ነጮች በደቡብ አፍሪካ ጥቁሮችን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ጉዳይ ተሳትፎ ለማሳነስ እና ለትቂት ነጮች የተመቸ የማያስቸግር የስልጣን የበላይነታቸውን ማስቀጠል የሚያስችል በ 1950 እ ኤ አ ያደረጉት ህገመንግስት የባንቱስታን ወይንም Ethnic homeland ለአስር ጎሳወች የየራሳቸው ሆምላንድ ፈጥረው ሰጡ። ይህ የጎሳ ክልል በአለማቀፍ ማህበረሰብ የተወገዘ እና ፍጹም ዘረኛ የሆነ ስርአት ተብሎ የአፓርታይድ ነጮች እስከወደቁበት ተወግዟል። በሀገራችን በተለያዩ ጦርነቶች የተዳከመች ሀገራችንን ድል አድርገን ስልጣን ያዝን የያዙት የዘር ድርጅቶች አንዱ ሀገር ከፋፋይ እና ለእራሱ ከአልኋ ምላሽ በሚል ስሌት አስፋፊ ሌላው ከሀገር ገንጣይ በመሆን ድርሻ ድርሻቸውን ከወሰዱ በኋላ ቀሪዋን ኢትዮጵያ ልክ እንደአፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ የባንቱስታን ክልል ግዛቶች የተመሳሰለ Ethnic homeland መሰረቱ። ከጥንት ሲዋረድ የመጣውን የአገዛዝ ድንበር አንዴ ጠቅላይ ግዛት፣ ሌላ ግዜ ክፍለሀገር ይባል የነበሩትን አፍርሰው ቋንቋን እና ዘርን የተንተራሱ ዘጠኝ ክልሎች አድርገው ሰሯቸው። ልክ እደደቡብ አፍሪካ የጎሳ ባንቱ ግዛቶች ሁሉ ኢትዮጵያም ውስጥ ምልአተ ሕዝቡ ያልተሳተፈበት አግላይ የሆነ የፖለቲካ ፕሮግራም በማጽደቅ ሕገመንግስት አጸደቅን ብለው በ 8ኛው አንቀጽ የኢትዮጵያን ሉአላዊ ሀገርነት ሰርዞ ብሄር፣ ብሄረሰስቦች፣ እና ሕዝቦች ሏላዊ ናቸው የሚል ህግ ደነገጉ። ዘጠኙ የጎሳ ክልሎች ልክ እንደ ደቡብ አፍሪካ የባንቱ ክልሎች መስፈርታቸው ቋንቋ ሆነ። እነዚህን የቋንቋ ግዛቶችን ከፈጠሩ በኋላም እስከመለየት የሚያበቃ መብትም አንቀጽ 39 ብለው ጨመሩላቸው።

የደቡብ አፍሪካ ነጮች ነጻ ግዛት ለጥቁሮች ሰጠን በሚል የራሳቸው ስልጣን አላቸው በሚባሉ ስድስት የባንቱ ግዛቶች 1/3 ኛው የደቡብ አፍሪካ ጥቁር ተገዥወች እንዲኖሩበት ተደረገ። የውጭ ፖሊሲ፣ የወታደራዊ እና ደህንነት አለማቀፍ ግንኙነት እና አለማቀፍ ንግድ በትቂት ነጮች ስር ሆኖ የአፓርታይድ ነጮች በዘር እና ቋንቋ ከፋፍለው መላ የደቡብ አፍሪካን ግዛት በእነርሱ ቁጥጥር በማድረግ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ገዙ።

ኢሓዴጎች የሚሉት ፌደራሊዝም

በአይነቱ ልዩ የሆነ በየትኛውም አለም ያልተሞከረ ከላይ ካሳየሁት የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ መንግስት ውጭ በነጻ ሕዝቦችም ሆነ በነጻ ሀገራት ያልታየ ፌደራሊም የህወሓት/ኦነግ/ኢሕአዴግ ፌደራሊዝም ተብሎ ለኢትዮጵያ ስርአትነት ተደነገገ። ይህን ፌደራሊዝም ልዩ የሚያደርገው

The Constitution provides sovereign power to all nationals and people of Ethiopia.

The sovereignty can be determined by selecting representative as per Constitutional laws and by actively participating in the democratic process.

ይህ ማለት ህገመንግስቱ በኢትዮጵያ ውስጥ እራሳቸውን የቻሉ ሉአላዊ ሀገራት እና ሕዝቦች እናዳሉ መደንገጉ ነው። በአንድ ሀገር ውስጥ የተለያየ ሏላዊነት ሊኖር ግን አይችልም። በዚህ ሀገመንግስት ኢትዮጵያ ልክ እንደአፍሪካ ወይንም እስያ ክፍለ ሀጉር የብዙ ሏላዊ ሀገራት ስም መሆኗ ነው። የእነርሱ ፌደራላዊነት ማለት እንደደቡብ አፍሪካ ባንቱስታን የነገድ ግዛቶች ማለት ነው። የደቡብ አፍሪካ 10 የባንቱ ግዛቶች ሉአላዊ ናቸው የሚል የአፓርታይድ ህግ ነበረው። ይህ ልዩ የሆነ ህገመንግስት ልክ እንደአፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ የባንቱ ሆምላንድ ሁሉ በአንቀጽ 46 የክልል መንግስታት እና ድንበር የተወሰነው (የተከለለው) ቋንቋን መሰረት በማድረግ ነው ይላል። ልክ እንደ ባንቱ የደቡብ አፍሪካ ግዛቶች ሁሉ የአንቀጽ 46 ድንጋጌም በኢትዮጵያ የተከለሉት ግዛቶች ዘርን እና ቋንቋን መሰረት እንዳደረጉት ሁሉ ስማቸውም ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ አማራ፣ ሶማሌ ወዘተ በሚል ነው። ይህ ደግሞ ለምሳሌ በባንቱ የክልል አከላለል ስዋዙሉ የሚባለው ክልል የዙሉ ሕዝብ ክልል የተሰጠ ነው። ትራንካይ እና ሲስካይ የተባሉት የዘር ክልሎች ለ ዥሆሳ ለተባለ ዘር የተከለሉ ናቸው።

ህወሓት/ኢሕአዴግ እንደመከራከሪያ በኢትዮጵያ የተንሰራፋውን የዘር ከአፓርታይድ የሚመሳሰል ስርአት በሌሎች ሀገራትም አለ ለማለት የሕንድን፣ የካናዳን፣ የስዊዘርላንድን ያቀርባሉ። በመሰረቱ ይህ መከራከሪያቸውን ብዙ የሚያፈርሱ መሰረታዊ የሆኑ ነጥቦችን ለአንባቢ ለማሳየት እንዲህ እንየው። በአለም ላይ 195 ሉአላዊ ሀገራት እና 193ቱ የተባበሩት መንግስታት አባል ሲሆኑ ከነዚህ የአለም ሀገራት ውስጥ ፌደራል ነን የሚሉት 25 ናቸው። የኢትዮጵያው ባንቱስታን ክልሎች ፌደራል ተብለው ከተቆጠሩ 26 ሀገራት ማለት ፌደራላዊ ስርአት አላቸው ማለት ነው።

ሌሎች ዘርን እና ቋንቋን ያካለሉ ፌደራል ስርአት ዋና መሰረት ያደረጉ ሀገራት ናፓል፣ ፓኪስታን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዮጎዝላቪያ አይነቶች የመፍረስ እንጅ የመቀጠል እና ጥንካሬ የማሳየት የተረጋጋ ስርአት አይታይባቸውም ወይንም አልታየባቸውም አለያም ፈርሰዋል። ሕንድን እና ካናዳን እንደሞዴል የምትቆጥረዋ ዘረኛ የህወሓት መራሽ ኢሕአዴግ ሁለቱም በስልጣኔ እና በመረጋጋት የቀጠሉበትን አብይ ጉዳይ ለማሳየት እና ትምህርት ለመውሰድ ግን ፈቃዱም ሆነ ፍላጎቱ በሀገራችን ያሉ ጠባብ ብሄርተኞች ፈቃደኝነት አይታይም። ለምሳሌ ካናዳን አስመልክቶ ቋንቋን እና ዘርን ተኮር ፌደራል ስርአት ለመቀጠሉ ሁነኛ ጉዳይ ብዙሀኑ የካናዳ ሕዝብ ከእንግሊዝ በ16ኛው እና ከዚያ በኋላ የፈለሱ የአንግሎ ዝርያ ያላቸው እና እንግሊዝኛ ተናጋሪወች ስለሆኑ “የኩቤክ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ላቲኖች” የመለየትን ጥያቄ ከሁለት ግዜ በላይ አንስተው ከሁለት ግዜ በላይ ለሬፈረንደም በማቅረብ ሀሳባቸው በብዙሀን ተሸንፈው በአንድነት ለመቀጠል የተገደዱበት ሁኔታን አይተናል። ከካናዳ የምንማረው ልምድ የሚያሳየን Ethno-Federalism በተረጋጋች ካናዳ እድገት ባላት ሀገር እንኳን ምን ያህል የህብረተሰብ በሽታ መሆኑን እንጅ ጥሩ ምሳሌነቱን አይደለም። ደካማ፣ ወይንም ደሀ ካናዳ ብትሆን ኖሮ “ኩቤክ” የፈረንሳይኛ ተናጋሪ ክፍለሀገር እስካሁን እራሷን የቻለች ግዛት ልትሆን እንደምትችል ለማየት በቅርቡ የተደረጉ የሕዝበ ውሳኔወች ከባድ ጫና አሳድረው እንደነበር አሳይቷል። ያውም ያደጉት የአንግሎ ዝርያ ያላቸው ሀገራት አሜሪካንን እና እንግሊዝን ጨምሮ ምን ያህል በካናዳ አንድ ሆኖ መቀጠል ላይ እንደተረባረቡ የቅርብ ግዜ ትውስታ ነው። ካናዳ የታየው በእኛዋ ደሀ ሀገር ቢሆን ኩቤክ ከኢትዮጵያ ልክ እንደኤርትራ ከሄደች ሰነባብታ ነበር።

የሕንድ ተመክሮም እንዲሁ ከካናዳ የተለየ አይደለም። ይኸውም አንድ ትልቅ ጎሳ “ሒንዱ” ሀገሪቱን ሰብስቦ በመያዙ ቀሪወች ትንንሾቹ ምርጫ ኖራቸውም አልኖረ ስርአቱ የሰጣቸውን የተሻለ ምርጫ ይዘው ባይቀጥሉ እና ሁሉም ደካማ ጎሳወች ቢሆኑ ኖሮ የህንድ እንደሀገር መቀጠል የሚታሰብ አልነበረም። ይህም ሆኖ ሕንድ ጥሩ ምሳሌ ልትሆን ለኢትዮጵያ የዘር ፖለቲካ አትችልም። ሕንድ ነጻነቷን ባገኘች በ 1947 እ ኤ አ ማግስት ፓኪስታን እና ባንግላዴሽ የተባሉ የእስልምና ተከታይ ብዙሀን ያላቸው ግዛቶች ተገንጥለው እራሳቸውን የቻሉ ሀገራት እንደሆኑት ሁሉ።፡ለአለፈው ግማሽ ምዕተ አመት የካሽሚር እንቅስቃሴ አንዴ ሲግል፣ ሌላ ግዜ ሲበርድ የቀጠለ እንጅ ሕንድ የተረጋጋ እና ፍጹም ሰላም የሰፈነባት ሀገር ሆና አልቀጠለችም።

የካሽሚር የመገንጠል ጥያቄ እና ትግል ይዋል ይደር እንጅ ቀጣይ እና ንዑስ ክፍለሀጉሩን በቀጣይ ለጦርነት የሚያዘጋጅ እንደሆነ ግልጽ ነው። በሰሜን ምስራቅ ከ ሲንጃግ እና በምስራቅ ከቲቤት ጋር የምትዋሰነው ካሽሚር ጠቅላላ ሪጂኑን የሰላም እጦት ቀጠና እንዳደረገችው በየግዜው የሚወጡ ዜናወች ያስረዳሉ። በዘመናዊ አለም የዘር ፌደራሊዝም ይሰራል እያሉ የሀገራችን ዘረኞች የሚፎክሩበት በመሰረቱ የእኛ ፌደራላዊነት ከላይ እንዳሳየሁት የባንቱስታን አይነት ለብሄር በሄረሰብ እና ሕዝቦች ስለሚላቸው ሏላዊነት ሰጥቶ ለሽህ አመታት የዘለቀውን ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ያፈረሰ ብሎም አንዱ ከሌላው እንዳይገኛኝ ሆኖ የተቀረጸ ስርአት ነው።

ለምሳሌ የሕንድም ሆነ የካናዳ ፌደራል አሰራር ዴሞክራሲን መሰረት በማድረጉ ዜጎች የኩቤክ ክፍለሀገር ተወላጅም ሆነው ለካናዳ ሊመርጡ የሚችሉ እንጅ አንተ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ወይንም ላቲን ፍራንኮ ስላልሆንህ መምረጥ አትችልም ወይንም መመረጥ አትችልም የሚል መብት የነፈገ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ የታየው እና አሁን በስራ ላይ ያለው ለሚሊዮን አማርኛ ተናጋሪ ወይንም አማሮች በደቡብ እና በኦሮሚያ ለሚኖሩ ወይንም እዚያው ተወልደው ላደጉ ሳይቀር ድምጽ የነፈገ ስርአት ነው። ለምሳሌ ሀረር ከተማ ውስጥ ብዙሀን አማርኛ ተናጋሪ እንደመሆኑ እና በይበልጥም አማሮች እና ጉራጌወች ብዙሀን መሆናቸው ግልጽ ሆኖ እያለ ማንነታቸውን እንዲለውጡ አለያም ድምጽ አልባ እንዲሆኑ የተደረገ እና በየትኛውም የከተማዋ መንግስት ተሳታፊ እንዳይሆኑ የተገፉበትን ድምጻቸው የታፈነበት ሀገር ነው  ፌደራል ብለው የሚያሾፉብን።፡የኢትዮጵያ ስርአት ወይንም ፌደራል አስተዳደር ተብየው ዴሞክራሲ የሌለው በመሆኑ ከፌደራሊዝም ይልቅ ለአፓርታይድ ባንቱ ሆምላንድ እጅግ ቀራቢ ነው።

ፌደራሊዝም ስንል

ኢትዮጵያን ፌደራላዊ ማድረግ ችግር የለውም። ለመስማማት ሁሉም ሀሳብ ሊያቀርብ ይችላል ይገባልም። እንዴውም ለሦስት ሽህ አመታት የዘለቀው ንጉሳዊ ታሪካችን የሚያሳየኝ ነገስታቱ አንድ ንጉሥ ብቻ ሳይሆን ብዙ የአካባቢ ንጉሦች የነበሩባት እና ንጉሠ ነገስት የሚለው ስያሜ የዘመናዊ የፌደራል አውቶኖሚን የሚያሳይ የቆየ ስርአት እንደነበረን ያሳያል። ሆኖም ፌደራሊዝም ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እና አሰራርን የሚከተል ነው። ዴሞክራሲ ከሌለ ፌደራሊዝም ሊኖር አይችልም። በሀገራችን የተንሰራፋው የዘር ፖለቲከኞች የሚያሳዩን ባህርይ ግን በጭንቀት፣ ባለመረጋጋት እና ሰላም የለሽ የፈረሰች ሀገር ሆና እንድትቀጥል እና እነርሱ መገንጠልን ሳያውጁ ነጻ የሆኑባት የዘር ክልል የመፍጠር በመሆኑ ስለዴሞክራሲ አይጨነቁም። ይህን ስለዴሞክራሲ መኖር አለመኖር ጉዳያቸው አለመሆኑን ባሳለፍነው የህወሓት 27 አመታት አገዛዝ አይተናል። ትግሬ ገዛ ብላችሁ ነው የምትቃወሙን ይሉን የነበሩ ተራ የእኛ ብጤወች እንደነበሩ ማስታወሱ በቂ ነው። ዛሬ ኦሮሞ ስልጣን ላይ መቀመጡን እንጅ ስለዜጎች ሙሉ መብት መኖር ያለመኖር ወይንም ሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ሁለንተናዊ መዋቅር ይኑራት አይኑራት ጉዳያቸው ያልሆኑ ብዙ ሽሆች ዛሬ ኦሮሞ ስልጣን ስለያዘ ነው እንዲህ የምትሆኑት የሚሉ እንደተከሰቱ መገንዘብ በቂ ነው። እናም ዴሞክራሲ የሌለው ስርአት ፌደራሊዝምን ሊተገብር አይቻለውም እንላለን። ፌደራሊዝም ስንል ዴሞክራሲያዊ ሰፊ አስተዳደር ማለታችን ነው።

ይህን ስርአት የምንቃወም ዜጎች ስርአቱ አግላይ፣ ጨቋኝ፣ የሀገርን አንድነት አፍራሽ ብሎም ኢትዮጵያን አፍርሶ በሀገራችን የመጨረሻ መቃብር የቦልካን አይነት ትናንሽ ሀገራትን የመመስረት ሀሳብ እና ፍላጎታቸው ግልጽ እየሆነ መምጣቱን ስለአምናይ ነው። ፌደራሊዝም ስንል ዜጎች በየትኛውም ክልል ይኑሩ የመምረጥ እና የመመረጥ ሙሉ መንብት ይኑራቸው ማለታችን ነው። ፌደራሊዝም ስንል በየትኛውም ክልል የሚኖር ኢትዮጵያዊ መብቱ እኩል እንዲከበር ማለታችን ነው። ፌደራሊዝም ስንል የኔ የሚባል ክልል ሳይሆን የእኛ የጋራ ሀገር ብሎ ዜጋ በሙሉ ልብ አምኖ እና የመኖር መብቱም ያልተሸራረፈ ሆኖ፣ አንተ ከዚህ አይደለህም ውጣ የሚባልበት ሀገር መፍጠር ማለት አይደለም። እንደምሳሌ ለማንሳት የአሜሪካን የሁለቱ ፕሬዜዳንቶች የአባት እና ልጁ ቡሽ የትውልድ ሀገር ሜን የሚባለው በሰሜናዊ ምስራቅ አሜሪካ የምትገኝ ትንሽ ክፍለግዛት ስትሆን። የቡሾች የፖለቲካ፣ የማህበራዊ እና የሀብት እድላቸው የሰመረ ግን ቴክሳስ ወደተባለው የነዳጅ ዘይት ሀብት ወዳለበት ሄደው በመኖራቸው እና ሀብት እና ንብረት በማፍራታቸው ሆነ። ታላቁ ቡሽ ፕሬዜዳንት ከመሆኑ በፊት ቴክሳስን በኮንግረስማን እና በሴኔትነት በመመረጥ ያገለገለ ሲሆን። ልጅየው ቡሽ ባልተወለደበት ቴክሳስ ገዥ ሆኖ በመመረጥ አገልግሏል። እንደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ቢሆን ኖሮ ቴክሳስ በአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት ተቸናፊ ከሆኑት የደቡባዊ አሜሪካ የኮንፌደሬሽን ፈላጊ ተገንጣይ ግዛቶች አንዷ እና በያንኪ አሜሪካኖች እጅ ከባድ ቅጣት የደረሰባት ናት። ይህ ማለት አሸናፊው የእነቡሽ ቤተሰብ ወደተሸናፊው ተገንጣይ ክፍለሀገር ሄዶ ለስልጣን እና ሀብት መብቃት ባልቻለ ነበር። ዛሬ ኢትዮጵያ ቢሆን ኖሮ እንደቡሽ አይነቶቹ ነፍጠኛ/ትምክህተኛ ተብለው ሀገር ለማስተዳደር ሳይሆን ለመኖር የማይችሉበት ሁኔታ ይኖር እንደነበር የአርባ ጉጉ፣ ብሎም የቅርቡ የሲዳሞ እና የለገዳዲ ፍልሰት አስተምሮናል።

ፌደራሊዝም ለመጀመሪያ የተጀመረው በአሜሪካን ሲሆን አሜሪካኖቹ ከ1861-1865 ያጋጠማቸውን ከባድ የእርስ በእርስ መተላለቅ ተከትሎ የነበረውን ህገመንግስት በማስተካከል የፈጠሩት የሁለት መንግስት ስርአት ነው። ትንሹ መንግስት አካባቢ ነዋሪወች የሚመረጥ አስተዳደር ሲሆን፣ የፌደራሉ መንግስት በሁሉም ስቴቶች የሚመረጥ በማድረግ እና የአካባቢው መንግስት ነጻነቱን እና መብቱን አውቆ በፌደራሉ ስር እና በፌደራሉ ሕገመንግስት መሰረት የሚያስተዳድር ነው። በየስቴቱ የሚኖር ዜጎች ባሻው ሄዶ የመኖር፣ የመስራት፣ ሀብት የማፍራት፣ ብሎም የመመረጥ እና የመምረጥ መብታቸው የተከበረበት ስርአትም ነው። ዜጎች የሚዳኙት በአሜሪካዊነት እንጅ በየሚኖሩበት ክልል አይደለም። ለምን ወደዚህ ክልል መጣህ ብሎ የሚጠይቅ ወይም ለመጠየቅ መብት የተሰጠው ሀይል የለም።

አሜሪካ የመገንጠልን መጥፎ ገጠመኝ ስላየች በህገመንግቷ ቃሉ ከህግ ውጭ ነው። የሚያነሳ ካለ የሀገሪቱን ደህንነት የተፈታተነ በመሆኑ ጥያቄ ዴሞክራሲያዊ ሳይሆን የጠላት እና የሀገሪቱን ሕገመንግስት የሚጻረር ነው በሚል ለፍርድ ይቀርባል። የአሜሪካ ሕዝብ አንድ ሕዝብ ነው እንደዜግነት የአሜሪካ ሕዝቦች ግን አይደለም። ይህ የሚያሳየው አሜሪካን ውስጥ ያሉ ክፍለ ግዛቶች ምንም እንኳን በሀብት እና በስልጣኔ እጅግ የላቁ ቢሆንም ዜግነት አንድ እና አንድ ብቻ በመሆኑ እራሳቸውን አንድ ሕዝብ  አንድ ሀገር አድርገው ይቆጥራሉ።

ፌደራሊዝም ስንል ዘጠኝ ሀገራት ፈጥረን የተለያዩ ሕዝቦች የሚኖሩበት ማለት አይደለም። ፈደራሊዝም ለአስተዳደር እንዲመች፣ ዜጎችን በቅርብ የሚከታተል እና የሚታዘዝ መንግስት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ስርአት ማለት ነው። የዜጎችን ኢትዮጵያዊነት የሚተካ ሊሆን ግን አይችልም። ኢትዮጵያ አንድ ሀገር አንድ ሕዝብ ናት። በውስጧ ግን እንደሚመች የአስተዳደር ክፍፍል ሊኖራት ይችላል። ለነዚያ የአስተዳደር ክልሎች እንደሕዝቡ ፍላጎት በጋራ ህገመንግስት ተንተርሶ ሊተዳደሩ ግድ ይላል። ለምሳሌ ቋንቋን በተመለከተ ከአንድ ቀበሌ ሌላው ቀበሌ የተለየ ቋንቋ ተናጋሪ ሊበዛ ይችላል። ትምህርትቤቶችም ተማሪወችን በአፍ መፍቻ ሊያስተምሩ ይገባል። ለምሳሌ እዚህ በምኖርበት የቴክሳስ ግዛት እና በዳላስ ከተማ ብቻ የተወሰኑ ትምህርትቤቶች መክሲኮ ቋንቋ ሲማሩ ሌላው የከተማ ክፍል በእንግሊዝኛ ይማራሉ። አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ላቲኖች እና እንግሊዝኛ ተናጋሪወች እኩል በሆኑባቸው ስርአተ ትምህርቱ በሁለቱም ይሰጣል ይህ ማለት የግድ ክልል ይፍጠሩ የሚያስብል መንገድ የለውም ማለት ነው። ፌደራሊዝም ስንል ከመብት እና ግዴታ ጋር የተያያዘ እኩል ሁሉንም የሚያስተናግድ ስርአት ማለታችን ነው።

References

Bansal, P. (2018, August 29). Federalism in India – Analysis of the Indian Constitution. Retrieved from https://blog.ipleaders.in/federalism-in-india/

Legassick, M., & Wolpe, H. (2007). The Bantustans and capital accumulation in South Africa: Journal Review of African Political Economy, 3(7), 87-107. source  zehabesha 

አይ የኛ ፖለቲካ? የኢህአፓና መኢሶን ሽኩቻ ማንን ጠቀመ?

የኢህአፓና መኢሶን ሽኩቻ ማንን ጠቀመ? (በድጋሚ የተለጠፈ፣ ከተወሰኑ ማስተካከያወች ጋር) 

ይሄን ጽሁፍ ቀደም ሲል ለጥፌዉ ነበር። ምን ያክሉ ሰዉ አንቦ ግንዛቤ ወስዶበት እንደነበር ግን አላዉቅም። ብቻ ጽሁፉ የአማራ ፖለቲካ ሊገባበት የሚችለዉን ቅርቃር ቀድሞ የተነበየ ነበር። ነገር ግን ሰሚ በመጥፋቱ ፣ እነሆ ዛሬ ቅርቃር ዉስጥ ገብተናል።

ለሁሉም ይሄ ጽሁፍ፣ ገና በአየር ላይ ቢቆይ ሂወት እንደሚኖረዉ ስላመንኩ፣ ጓደኞቸ እንደገና በጥሞና ታነቡት ዘንድ፣ የተወሰኑ ነጥቦችን ጨማምሬ እንደገና ለመለጠፍ ወደድኩ። አንቡት።

በአገራችን የፖለቲካ ድርጅቶች ታሪክ ዉስጥ፣ የደርግ፣ ኢህአፖና መኢሶን ነገር መቸም አይረሳም። ሶስቱም የርስበርስ መጠፋፋት ጥሩ ተምሳሌቶች ናቸዉ። በወቅቱ አብዮቱን ለማስቀጠል ከደርግ ይልቅ፣ ኢህአፓና መኢሶን የተሻለ እድል እንደነበራቸዉ ይነገራል። ነገር ግን በተለይም መኢሶንና ኢህአፓ፣ ተባብሮ ከመስራት ይልቅ፣ መደማመጥ እንኳን የማይችሉ ድርጅቶች ሆነዉ አረፉት። ይህ አለመደማመጥም ከከፋ ጫፍ አድርሶ፣ሁለቱ ድርጅቶች እርስ በርስ ለመጠፋፋት ከመሞከራቸዉም በላይ፣ አንዱ ወገን ከደርግ ወግኖ ( በዚህ በኩል መኢሶን ነዉ የሚታማዉ ) ሌላዉን ለማጥፋትና ማስጠፋት ተንቀሳቀሱ።

ደረግ የሁለቱን ድርጅቶች አለመግባባት በሚገባ ተጠቀመባት። መጀመሪያ ላይ ሁለቱንም ድርጅቶች እንደ ስጋት ይመለከታቸዉ የነበረ ቢሆንም፣ ሁለቱ ሲጋጩለት ደግሞ፣ አንዱን እንደመሳሪያ በመጠቀም ሌላኛዉን(ኢህአፓን ) ለማጥፋት/ ለማዳከም እድሉን ተጠቀመበት። አያ ደረግ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ኢህአፓን እንዳይሆኑ አደረገዉ። መጨረሻ ለይ ደግሞ መኢሶንንም እንዳይሆኑ አድርጎ በላዉ። ከዚህ በሁዋላ፣ እድሜ ለመኢሶንና ኢህአፓ እንጅ ፣ ደርግ ለጊዜዉ በአገሪቱ ብቸኛዉና ሁነኛ ተቀናቃኝ አልባዉ ሀይል ሁኖ መዉጣት ቻለ። ደርግ ኢህአፖና መኢሶን በሰሩት ስህተት ተጠቅሞ ፣ ስልጣኑን ያደላደለ፣ ለ17 አመታት አገራችንን ክፉኛ አበሳቆላት። ደርግን ለዚህ እንዲበቃ/ ያበቁት ኢህአፓና መኢሶን፣ ዛሬም ድረስ ለሰሩት ስህተት በታሪክ ይወቀሳሉ፣ ገናም ሲወቀሱ ይኖራሉ። 

አሁን ላይ የአማራ ፓለቲካና ፖለቲከኞች፣ የመኢሶንንና የኢህአፓን ታሪክ እንዳይደግሙት እጅጉን እፈራለሁ። ዛሬ ሁሉም በአማራ ስም የተደራጁ ሀይሎች ከተቻለ ወደ አንድነት የሚመጡበት፣ ካልተቻለ ደግሞ ተቀራርበዉ ለጋራ ጉዳይ በጋራ የሚቆሙበት ወቅት እንጅ በትልቁም በቲንሹም ነገር መካሰስ የሚገቡበት ወቅት መሆን አልነበረበትም። ጊዜ ሲገኝ የሚፈታዉን ነገር ለጊዜ ሰጥቶ፣ አሁን ወሳኝ በሆኑ የአማራ ህዝብ ጥያቄወች ላይ ብቻ ማትኮር ይገባ ነበር።

አሁን ዛሬ እየታየ ያለዉ ሁኔታ፣ ትልቁ ቁምነገር ወሳኝ አማራዊ ጥያቄወች ላይ መሆኑ እየቀረ በደራሽና ወቅታዊ ፈተናወች/ ችግሮች መጠመድ ላይ ሁኗል። ይህ መሆኑም ባልከፋ ነበር። ችግሩን እያከፋዉ ያለዉ ነገር፣ የልዩነት እንቅስቃሴወቻችን ፣ ዉስጣዊ አንድነታችንን የሚጎዱ እየሆኑ መታየታቸዉ ነዉ። አሁን ትግሉ በመንግስትንና ህዉሀት ላይ ጫና ፈጥሮ የአማራን ወሳኝ ጥያቄወች (በተለይም የህገ መንግስት፣ ወሰንና ማንነት ጥያቄወች )እንዲመለሱ መስራት ላይ ሳይሆን፣ የራሳችንን የዉስጥ አቅም በሚያዳክም መልኩ መጓዝ ሁኗል። እጅግ ያሳዝናል። ብዙ ዋጋ የተከፈለበት አማራዊ ትግልና አንድነት ፣ በብቁና አቃፊ፣ አስተዋይና አርቆ ተላሚ መሪ መጥፋት ምክንያት፣ለጊዜዉም ቢሆን እንዲህ ተሽመድምዶ ማየት እጅግ ያናዳል። 

አሁን ወቅቱ ነገርን መሸፋፈን አይፈቅድልንም። ከገባንበት ቅርቃር ለመዉጣት ቸኛዉ መፍትሄ ሀቅን መዳፈር መጀመር ነዉ። ለዚህም የመጀመሪያዉ ጉዳይ፣ በአሁን ጊዜ ፣ ከዋናዉ አጀንዳችን በሚያስወጣን ጉዳይ እየተጠመድን መሆኑን ማመን ነዉ ። ሁለመናችን፣ ማን መጣ፣ ማን ሄደ፣ ለምን ይመጣል፣ ማን ታሰረ፣ ማን ተፈታ… ወዘተ የሚል ነገር ዉስጥ እየገባን ነዉ።

እኛ መተማመን ያለብን፣ በምንገነባዉ ብሄርተኝነት እና በጥያቄወቻችን ትክክለኛነት ላይ እንጅ ማንም ሰለመጣና ሰለሄደ፣ ግለሰቦች በስህተትም ቢሆን ስለተፈቱና ስለታሰሩ መሆን አልነበረበትም። እዉነትን በጃችን ሰናስገባ፣ሁሉም ይገለጥ ነበር።

ሌላዉ ችግር፣ ለኛ ድክመት ሌሎችን ማሳበብያ ከማድረግ ዛሬም አልተላቀቅንም። የብሄርተኝነት ግንባታችን ዋነኛ የችግር ምንጮች ሌሎችን አድርጎ መዉሰድ ዛሬም አልቆመም። ይህ ትክክል አይደለም።፤ ዛሬም እደግመዋለሁ፣ የኛ ችግሮች ዋነኛ ምንጮች እኛዉ ነን!! ይሄን ሀቅ ከተቀበልንና ለመፍትሄ ከተዘገጀን ብቻ እናገግማለን። የኛ የብሄርተኝነት ግንባታ ጎምርቶ መዉጣት ያለበት በሌሎች ተፈትኖና አሸንፎ እንጅ አንዲሁ ያለ ፈተና መሆን የለበትም ብየ አምናለሁ። ተፈትኖ ያላሸነፈ ትግል ለጊዜዉ በለስ ቢቀናዉ እንኳን፣ ብዙ ሊጓዝ እንደማይችል ግልጽ መሆን አለበት።

ስለሆነም፣ የአማራ ብሄርተኝነት ሊፈትኑት በሚፈልጉ አካላት ሁሉ ተፈትኖ እና አሸንፎ መዉጣት ያለበት ስለመሆኑ ስምምነት ሊያዝበት ይገባል። በዚህ መልኩ ያልተገነባ ብሄርተኝነት ደግሞ የእምቦይ ካብ ከመሆን አይድንም። ወይ ባልጀመርነዉ እንጅ፣ ከጀመርነዉ ደግሞ፣ ብሄርተኝነታችን እንዲህ እንዲሆን አንፈልግም። ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ ከፈለግን ደግሞ፣ መጠላላፍ ሳይሆን መደማመጥና አብሮ መስራት ያስፈልጋል። fb ተመቸኝ ተብሎ ፣ የሆነ ያልሆነ ነገር እየመዘዙ ሲቀባጥሩ ከመዋል መቆጠብን ይጠይቃል።

ስለሆነም፣ እዉነትም የአማራ ህዝብ አጀንዳወች፣ አጀንዳወቻችን ከሆኑ፣ አሁን እየገባንበት ካለዉ የርስበርስ መካሰስ ወጥተን ፣ በወሳኝ ጥያቄወች ላይ እናትኩር፣ የማያስማሙን ነገሮች ካሉ ቀን ሲገኝ እንፈታቸዋለን፣ አሁን ጊዜ የለም፣ እኛ ሳበዉ ጉተተዉ ስንባባል፣ እነ እንቶኔ አሻግረዉ እያዩንና እየሳቁብን፤ የራሳቸዉን ሽምጥ እየጋለቡ ነዉ።

የነገን ለነገ ትተን ለዛሬዉ በጋራ እንቁም፣ ዉስጣዊ አቅማችንን አናምክነዉ። ነገሮች እጅግ ፈጣን በሆነ ሁኔታ እየተቀያየሩ ነዉ። አማራዊ አንድነት ከመቸዉም ጊዜ በላይ አስፈላጊ የሆነበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። እንዲህም ሁነን መገኘት አለብን፣ ያለ በለዝያ ዉሀ ሲወስድ እያሳሳቀ ነዉ!! ይባላል። እርስ በርስ ስንካሰስ እና ስንሰዳደብ የምንዉልበትን ጊዜ፣ አቅም፣ገንዘብና ችሎታ፣ መግባባትና መተባበር ስለምንችልበት ሁኔታ እንጠቀምበት።

ማሳሰብያ:- ለአዴፓና አብን!!!!!!!!

ከይቅርታ ጋር አንድ ነገር በድፍረት ልወርፋችሁ ነዉ። ከተቀየማችሁ የራሳችሁ ጉዳይ፣ ነገ ነገሩ ሲገባችሁ ታመሰግኑኛላችሁ። ነገሩ እንዲህ ነዉ!
አሁን ያለዉን የሁለታችሁን ወቅታዊ ሁኔታ ሰገመግመዉ፣ የመኢሶንንና ኢህአፓን ታሪክ፣ ቢያንስ በአማራ ክልል የምትደግሙት ይመስለኛል። ማን በመኢሶን? ማን በኢህአፓ ሊመሰል ይችላል? ፈልጉት። የኔ ወቅታዊዉ እዉነተኛ ስሜት ግን ይሄዉ ነዉ። ብቻ ሟርት ሆኖ ይቅር በሉኝ።

ለምን እንዲህ ምርር ብየ እናገራለሁ? ምክንያት አለኝ። ይሄዉም በሁለታችሁ መካከል ያለዉ ወቅታዊ ሁኔታ አልጣመኝም። በተለይም የሰኔ 15 ጉዳይ ሁለታችሁ እንደ አንድ አማራዊ ሀይል በአንድ ለመቆም ያስቻላችሁ ስለመሆኑ ሲበዛ እጠራጠራለሁ። በዚህ ወቅት ታሳሪና አሳሪ ሆኖ መገኘት፣ ነገ ነገሮች ወደየት ሊያመሩ እንደሚችሉ ፣ ለአንድ ፖለቲከኛ ነገሮችን ለመተንበይ ምርምር አያስፈልገዉም። ስለሆነም በጋራ ቁሙ፣ መተማመን ፍጠሩ፣ ችግር ካለ ሁለታችሁም ስትምሉበት ለትምሉበት ህዝብ ይፋ አድርጉት። ህዝባችን ችግሩን ይፈታዋል።

እንዲሁም”የአማራ አክቲቪስት”ነን ለምትሉ። ሚኪ አማራ እንኳን የለሁበትም ብሏል። ሌሎቻችሁስ? ናችሁን? “አይነጋም መስሏት…. አለች” ይባላል። እረፉ። ነገ ሁሉም ሲገለጥ ለምታፍሩበት ነገር ባትሳሳቱ ጥሩ ነዉ። የማያልፍ ጊዜና መከራ የለም። ያልፋል። ከቻላችሁ ስለ አማራዊ አንድነት ሰበኩ፣ ካልቻላችሁ ከfb ዉጡና የግል ስራችሁን ሰሩ። አንዳንዱ እኮ fb ላይ ካልጻፈ ሌላ የኑሮ መሰረት ያለዉ አይመስልም።

ለወጣቶቻችን:- ራሳችሁንና የአማራን ህዝብ ብቻ ሁኑ። የማንም እርባና የለሽ አጀንዳ ማራገፍያ ላለመሆን የቻላችሁትን ሁሉ ጣሩ። የልጅ ታላቅ ሁኑ። ዛሬ ላይ ሁናችሁ ነገን ተመልከቱ።

አበቃሁ!!!!!

ቸር ሰንብቱ!

Chuchu Alebachew