Category Archives: Editorial

አለበለዚያ ዋ!ዋ!ዋ!!!!

በአማራ ክልል ከአዴፓ ጋር ሙግት የገባችሁ ፋኖዎች፣ አብን፣ ሌሎች እረፉ!! ህዝቡን እያዋረዳችሁት ነው። ህዝቡን አንገቱን እየሰበራችሁት ነው። ህዝቡን ከማይወጣው ቅርቃር ውስጥ እየከተታችሁት ነው። ሲቀነባበር ከነብረው፣ ከደረሰባቹህና ከተደገሰላቹህ ክፍት በላይ የናንተ ድንቁርና ያሳፍራል። ስለምንና በምን ምክንያት መተራመስን ለትመርጡ እንደወደዳቹህ ግልጽ አይደለም። ተደራጁ፣ ሃሳብችሁን ሽጡ። ምርጫ ሲመጣ አሸንፉና አገር ምሩ። ይህንን ስትከለከሉ ሌሎች አማራጮችን ተከተሉ። ከዚህ ውጭ ያለው አካሄድ የተገዢነት ወይም የሴራው አስፈጻሚ ከመሆን አይዘለምና ራሳችሁን አርሙ። የጅምላ ድጋፍ አለን በሚል አትክለፍለፉ። በስልታን ጥማት አትበዱ። ሰክናችሁ ጥሩ አምራጭ ሁኑ። እባክችሁን ሕዝቡን አታዋርዱት። አታሳፍሩት። እርቃኑን የቀረ መሪ አልባ አታድርጉት።

ኢትዮጵያ አገራችን አንድ ሆና እንድትቀጥል የማይፈልጉ ሃይሎች እያደቡና በግልጽ በዚህ አንድ ዓመት ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። በቀጥታና በተዛዋሪ ያላቀነባበሩት ሴራ የለም። ራሳቸውን በማደራጀት፣ ለዓላማቸው መሳካት የሚበጇቸውን በመልመል፣ በማሰልጠንና በማስታጠቅ ኢትዮጵያችንን ሊያፈራርሷት ብር ረጭተዋል፣ እየረጩ ነው። ወደፊትም ይረጫሉ።

በዲጂታል ሰራዊት ግንባታ ሃይል አሰልጥነው፣ በጀት መድበው፣ የመረጃ ኮማንድ ፖስት አደራጅተው፣ መሪና አጅነዳ አፍላቂ ካድሬ አሰማርተው የማተራመስ ተግባራቸውን ቀጥለዋል። እነዚህ ኢትዮጵያን የመበታተን ዓላማ ያላቸው ሃይሎች፣ ኢትዮጵያ አንድ ሆና በሰላም ከዘለቀች ዓላማቸው ስለሚመክን የሚችሉትን ሁሉ ሲያደርጉ ሌሎች አገራቸውን የሚወዱ በተመጣጠነ መልኩ ሲታገሏቸውና ሲጋፈጧቸው አይታይም።

ይልቁኑም ዜጎች በማውቅም ይሁን ባለማወቅ ” በሚፈበረከው” የሴራ አጀንዳ ተጠልፈው የነዚህኑ የሰለጠኑ፣ በዓላማ በሚራመዱና፣ መድረሻ ግባቸውን አውቀው በሚያተራምሱን ወገኖች ወጥመድ ውስጥ ገብተው ሲንቦጫረቁ ይታያል። በንቦጫረቅ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ለመብላት የተዘጋጀውን ጥንሥሥ በመጋት ሰክረው ሌላውን ሲያሰክሩ እያየን ነው።

ባለማውቅ የሚነዱት ሳይሆኑ ያውቃሉ፣ ልምድ አላቸው፣ ሴራው ነድፎና ለብልቦ አስተምሯቸዋል የሚባሉ ወገኖች ዛሬ ላይ እርጋታን ከመምረጥ ይልቅ በዚሁ የጥፋት አጀንዳ ውስጥ ብርሃን እንዳየች የሳት እራት በጥፋት ነበልባል ሲጫወቱና ጀግና መስለው ሲቀላምዱ እያስተዋልን ነው።

ከሁሉም ወገን በአብሮነት የኖረው ሰላማዊ ሕዝብ በሰከሩና የቆየ አላማ ባላቸው ሃይሎች ሴራ ሰላሙን እንዲያጣ፣ የሚኮራባት አገሩ ሰላም እንድትራብ፣ ወገኖቹ እንዲረግፉ፣ የማምለኪያ አሰዱ እንዲነድ፣  ወገኖች እንዲፈናቀሉ፣ እርስ በርስ እንዲጋጩ ተደርጓል። ገና ብዙ እቅድም አለ።

የተሞከረውን እያከሸፉ፣ ቀጣዩን እቅድ ለማክሸፍ የሚሰሩ ሃይሎችን በማጥላላት፣ በቀጥታ በመቃወም አገሪቱ ተቆርቋሪ አልባ እንድትሆን ሌት ተቀን በሚሰሩ እባቦች የተነደፉና አውቀው መርዛቸውን የበሉ አካላትን አደብ በማስገዛቱ ረገድ አብዛኞች ዝም ማለታቸው ” ምን እስከሚሆን ነው የሚጠበቀው” የሚል ጥያቄ ያስነሳል።

አገራችን አሁን ያለችበት ቁመና እጅግ አሳሳቢ መሆኑ እየታወቀ ፣ ከግል ፍላጎትና ጥላቻ በመነሳት አገሪቱ ባለችበት የአደጋ ቋፍ ላይ ቤኒዚን የሚያቀጣጥሉ ክፍሎችን አለመታገል፣ ምን አልባትም ኢትዮጵያ በዜጎቿ ዳተኛነት፣ ዝም ባይነትና ስምምነት የፈረሰች አገር በሚል ታሪክ መመዘገቧ የማይቀር እውነት ነው።

ዛሬ ኢትዮጵያን የሚመራት ያረጀው ኢህአዴግ በውስን የለውጥ ሃይሎች አማካይነት መሆኑ እየታወቀ፣ ለውንፊቱም ሆነ ለማንኪያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላይ የሚካሄደው ዘመቻ ያልገባቸው ወገኖች ካሉ ይህንን ማለት እንወዳለን።

ዛሬ ኢትዮጵያን በነበርችበት ለማስቀጠል እየደከሙ ያሉት እሳቸው እና እሳቸውን መሰል ጥቂቶች ናቸው። በዚህም ላይ የንጹሃን ምስኪን ዜጎች ጸሎት ሃይል እየደገፋቸው ነው። በመሆኑም ዶክተር አብይን ማዕከል ያደረገው የማቆሸሽ ዘመቻ እሳቸውን በመንቀል ላይ ያተኮረ ነው። እሳቸውን ሲነቀሉ አሁን ባለው ኢህአዴግ ውስጥ እሳቸው ለኢትዮጵያ የሚጨነቁትን ያህል የሚደክም የለምና ሁሉም ጉዳይ ለአገር ወዳዶች ህልም ይሆናል። ለሌሎች ደግሞ አሁን በአማራ ክልል በተካሄደው የሴራ ፖለቲካ ውጤት የጅመሩት የሰርግና ምላሽ ድግስ ይቀጥላሉ። እውነታው ይህ ነው።

በአማራ ክልል የረገፉት ውድ ልጆችም ሆኑ ድርጊቱን የፈጸሙት በሁለት መንገድ በተገመደ የሴራ ፖለቲካ መሆኑ እየታወቀ ዛሬም አማራ ክልል እንሰራለን የሚሉ ወገኖች ከዚህ ስህተት ለመማር አለመሞከራቸው ያሳዝናል። አንገት ያስደፋል። እንደ ሰው ሰላምሰባቸውም እንድንጠራጠር ያደርገናል።

ዛሬ ነገሮች ተቀየሩ እንጂ የሴራው አላማና ውጥን አማራ ክልል ብቻ የሚቆም አልነበረም። በዛው ቀን አራት የሚደርሱ ከፍተኛ መሪዎች እንዲገደሉና በመሃል አገር መፈንቅለ መንግስትና መተራመስ ለመፍጠር ነበር ዓላማው። እቅዱና ቅጥር ነፈሰ ገዳይነቱ በሰለጠኑ የሴራው ፖለቲካ አስፈሳሚዎች በደንብ የተከወነ ነበር። ነገሮች ወደ ባሰ መተራመስ እንዳያመሩ በመስጋት ሁሉም ጉዳይ ይፋ አልወታም እንጂ የሆነው ሁሉ አስደንጋጭ፣ አሳሳቢ፣ ዘግናኝ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ጠባቂው የማያንቀላፋ ብመሆኑ!!

የሴራው ጠንሳሾች መነሻና መድረሻቸውን አውቀው ሲሰሩ፣ ለዚሁ ዓላማቸው ልዩነታቸውን ወደጎን ትተው ሲማማሉ፣ ሌሎች አገራቸው ላይ ለተጣደው የክፋት ገንዳ እሳት ይቆሰቁሳሉ። አብዛኞች ዝም ብለው በግዴለሽነት ይመለክታሉ። ቢመችም ባይመችም አዲስ አበባን አስመልክቶ ለተነሳው የፍትሃዊነት ጥያቄ ድጋፍ ሰጪ መስለው ዶከተር አብይን የሚጨፈጭፉ ክፍሎችን መተባበር አገር ላይ ክህደት እንደመፈጸም ነው።

አዲስ አበባ ላይ ለተነሳው የፍትሃዊነት ጥያቄ ድጋፍ ሰጬ መስለው የሴራ ፖለትካ የሚያራምዱትን ማድመጥና መደገፍ በምንኛውም መስፈርት አያስኬድም። እነ እስክንድር ነጋም ቢሆኑ ሃሳባቸው እንዳይጠለፍና መከራ ሲበላ በኖረበት ያ ዘመን ሲናኙ በነበሩ የሰው መከራ በማይታያቸው እውሮች እንዳይቆሽሽ ደግመው ደጋግመው ሊያስቡና በራቸውን ሊያጠብቁ ይገባል። የሚቻል ከሆነ በሰላማዊ መንገድ ህዝብ የሚወስንበትን አግባብ ለማመቻቸት አግባብ ካላቸው ወገኖች ጋር በር ዘግቶ መወያየቱ ይበጃል።

ዛሬ ኢትዮጵያችን ሳስታለች፣ ታማለች፣ ነፍራለች…. ግን አለች። በአስገራሚ ሁኔታ የማትመክነው አገር ኢትዮጵያ በሶማሌ ክልል እንደ አቶ ሙስጣፋ አይነት ዘበኛ አግኝታላች። እየዋለ ሲያድር ሌሎችም ይመጣሉ። ኢትዮጵያን የጠላቹህ ወገኖችም እባክቹህን ከቻንቃዋ ላይ ውረዱ። ስለምን ከሷ በዘረፍችሁት ሃብት ታፈርሷታላቹህ!! ምስኪን ህዝብ አስታችሁ ስለምን ወደ ማይሆን የእልቂት አዙሪት ውስጥ ትከቱታላቹህ!! ህዝብ በየትኛውም ወቅት ጠላት ሆኖ አይውቅምና ለመታረቅ ጊዜ አያጠፋም። እርቅ ከተፈለገ ህዝቡን ለቀቁት። ካልሆነም ባላችሁበት ሁኑ!!

በአማራ ክልል ከአዴፓ ጋር ሙግት የገባችሁ ፋኖዎች፣ አብን፣ ሌሎች እረፉ!! ህዝቡን እያዋረዳችሁት ነው። ህዝቡን አንገቱን እየሰበራችሁት ነው። ህዝቡን ከማይወጣው ቅርቃር ውስጥ እየከተታችሁት ነው። ሲቀነባበር ከነብረው፣ ከደረሰባቹህና ከተደገሰላቹህ ክፍት በላይ የናንተ ድንቁርና ያሳፍራል። ስለምንና በምን ምክንያት መተራመስን ለትመርጡ እንደወደዳቹህ ግልጽ አይደለም። ተደራጁ፣ ሃሳብችሁን ሽጡ። ምርጫ ሲመጣ አሸንፉና አገር ምሩ። ይህንን ስትከለከሉ ሌሎች አማራጮችን ተከተሉ። ከዚህ ውጭ ያለው አካሄድ የተገዢነት ወይም የሴራው አስፈጻሚ ከመሆን አይዘለምና ራሳችሁን አርሙ። የጅምላ ድጋፍ አለን በሚል አትክለፍለፉ። በስልታን ጥማት አትበዱ። ሰክናችሁ ጥሩ አምራጭ ሁኑ። እባክችሁን ሕዝቡን አታዋርዱት። አታሳፍሩት። እርቃኑን የቀረ መሪ አልባ አታድርጉት።

እናንተ ሳይገባቹህ በወፍ በረር አገራችሁ ላይ የዘመታችሁ ነቁ። አሁን ያለን ብቸኛ ሃይል መከለከያችን ነውና እናክብረው!! አለበለዚያ ዋ!!ዋ!!ዋ!!

ዛሬ ይህ ሆነ፤ እዚህ ላይ ደረስን ፤ ነገስ? የዘር ፖለቲካ ድምር !!እዚህ በመድረሳችን ኩራት የሚሰማችሁ እንኳን ደስ አላችሁ!!

Genocide

በጋምቤላ በአንድ ጀንበር አምስት መቶ የሚደርሱ የአኝዋክ ልጆች ተሰየፉ፣ ተጨፈጨፉ፤ በቢኒሻንጉል በተመሳሳይና በተደጋጋሚ አማራዎች ተገደሉ፣ በበደኖ ገደል ውስጥ ተጣሉ በአርሲ፣ በወተር፣ በቆቦና በደደር እንዲሁም በዋተርና በሞያሌና አካባቢው ላይ ጭፍጨፋ ተካሂዷል። ደቡብ ክልልም የተለያዩ ቦታዎች እልቂት ተፈጽሟል፣ በአወዳይ ይኸው በስዕሉ እንደታየው የሰው ልጆች ተጨፈጨፉ፣ የሚጠየቅ የለም።

somali v oromiya

አሁን አሁን ጭፍጨፋ በአዋጅ ሁሉ ፈቃድ እየተሰጠው ንጹሃን እየተፈጁ ነው። የት ነው ማቆሚያው? እየባሰ እንጂ እየላላ የሚሄድ ነገር አይታይም። የፈለገው ክልል ተነስቶ ያፈናቅላል። የፈለገው ክልል ተነስቶ ድንበሩን ያሰፋል። የፈለገው ክልል ተነስቶ እንደ አገር ከሌላ አገር ጋር ስምምነት ያደርጋል፤ የፈለገ ክልል ተነስቶ ማንነትን በጥይትና በሃይል ያስቀይራል። የፈለገ ክልል ታሪክ እየገለበጠ ወደ ራሱ ይወስዳል። የፈለገ ክልል ያስራል፣ ይፈታል፤ ብዙ ብዙ የተወገዙ ድርጊቶች ይፈጸማሉ … ወዘተ አሁን የሚያሳስበው የነገው ነው። ለምን? ቢባል እየባሰ እንጂ እየለዘበ የሚሄድ ነገር አልታየምና!!

የዘር ፖለቲካ ሃሺሽ ነው። የዘር ፖለቲካ እንደ ሃሺሽ አቅል ያሳጣል። የዘር ፖለቲካ ከሰውነት ያወርዳል። የዘር ፖለቲካ ጠንሳሾቹን፣ አስፈጻሚዎችን፣ተከታዮችን፣ አገልጋዮችን፣ ሁሉንም አውሬ የሚያድርግና እንደ ተስቦ የሚተላለፍ በሽታ ነው። አሁን የደረስንበት መንገድም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው።

ይህንን ክስረትና ውድቀት ማየት ቢቻልም፣ አዝኖ እርምት ለመውሰድ እንኳን እድል በማይሰጠው በዚህ መጋኛ አስተሳሰብ አገርም ፣ ህዝብም፣ ተተኪው ትውልድም፣ የታጠቀውም፣ ያልታጠቀውም ተያይዞ ወደ ሞት እየጋለበ ነው። ማን ያስቁም? የትኞቹ መሪዎች ከዚህ አዙሪት ነጻ በመውጣት አገሪቱን ይታደጉ?

ተቃዋሚ የሚባሉት የራሳቸው ክሽፈት፣ ሽባበትና፣ ምክንያት የማይቀርብበት የእርስ በእርስ ውዝግባቸው እንዳለ ሆኖ፣ ከፍ ሲሉና ከዘር እሳቤ እርቀው ህዝብ ሲወዳቸው በሃይል ማፍረስ፣ በህግ ማፍረስ፣ ማሰርና ማጥፋት አማራጭ ሆኖ በመወሰዱ አገሪቱ ተተኪ አልባ እንድትሆን አድርጓታል። የዘረኛነት ፖለቲካ ሌሎች በነጻ እንዳያስቡም ጭምር የሚያግድ ጋንግሪን በመሆኑ በሁሉም ደረጃ ክሽፈት ተመዝግቦብናል።

አሁን የሚፈራ መሪ የለንም። የሚከበር የሃይማኖት አባቶች የሉንም። የምንመካባቸው አታጋዮች የሉንም። ነጻ ሆነው መንገድ ለማጽዳት ለሚተጉ እድል የለም፤ እና ምን ይሁን? ዛሬ ጥያቄው ማልቀ ሳይሆን ከዚህ አውሬ አስተሳሰብ እንዴት እንውጣ ነው? እንዴት ? በመፈክር እስከመቼ እንኖራለን? ዘጠኝ ሚሊዮን ርሃብተኞች ይዘን እንዲህ ያለው የዞረበትና መጨበጫ የሌለው የዘር ፖለቲካ ድምር ላይ መድረስ ለሚያኮራቹህ እንኳን ደስ አላችሁ!!

 

 

“ሙሉ ጋዜጠኞች” ነን? እንዴትስ ሙሉ እንሁን?

ዛጎል በይፋ ሃሳቧን መሰንዘር ስትጀምር አንድ ችግር “ጋዜጠኛ” ያደረጋት እህት ” ዲያስፖራውን የሚያስደስት ዘገባ ካላቀረባችሁ አንባቢ አይኖራችሁም” ስትል ምክር ቢጤ ሰነዘረች። መረጃን ማመጣጠን የሚባለው ዋና የ”ጋዜጠኛነት” መለኪያውስ? የሚለውን ጉዳይ አነሳን። ከዚያ በሁዋላ የነበረው እንቶ ፈንቶ ነውና አናነሳውም።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ዓለማት ይኖራሉ። ከማይፈለጉት በስተቀር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለመሆናቸው መስማማት ቢቻልም፣ ሁሉም ተመሳሳይ የፖለቲካ አቋምና እምነት አላቸው ብሎ ከቶውንም አይታሰብም። መንግስትን/ ኢህአዴግን ወይም ህወሃትን/ የሚቃወሙት እንኳ ተስማምተው ሲሰሩ አይታዩም። ይልቁኑም በተቃራኒው ሲሻኮቱ ነው ጊዚያቸውን የሚያሳልፉት። ተጋነነ ካልተባለ “የመቃወም ፖለቲካ የጥበብ መጀመሪያ እርስ በእርስ መጣላትና መሰዳደብ ነው” የሚል መተዳደሪያ ያላቸው የሚመስሉ አሉ።
እንግዲህ እንዲህ አይነት ውሉ የጠፋበት ማህበረሰብ ውስጥ ስንኖር አንዱን ወገን ማርካት እንዴት ይቻላል? ጋዜጠኛነት በራሱ ” ማርካትና፣ ማስቀየምን” አንግቦ የሚካሄድ የስራና የሙያ ዘርፍ ነው ወይ? ከዚያም በላይ ዲያስፖራው የተመጣጠነ መረጃ ማግኘት እንደማይፈልግ ማን አጠና? ማንስ ተመራመረ? እንዴትስ እዚህ ድምዳሜ ላይ ተደረሰ? ምክር ቢጤ ለሰነዘረችው ሴት የቀረቡ ጥያቄዎች ነበሩ። እሷም ሆነች ሌሎች ሊመስልሱት የማይችሉት ጥያቄ!!
ይህንን ጉዳይ ያነሳነው ወደን አይደለም። የመካሪዋንም ሃሳብ እርቃን ለማሳየት አላሰብንም። ይልቁኑም እንዴት መረጃ በማግኘት የተሟላ ሪፖርት ማቅረብ ይቻላል? የሚለው ጉዳይ ስላሳሰበን ነው። ኢህአዴግ በውጭ አገር ላሉ ሚዲያዎች ዝግ ነው። ለሚቀርባቸውና የራሱ ከሆኑት ውጪ ለሌሎች መርጃ ለመስጠት አያስብም። ይልቁኑም አሸባሪና አተራማሽ እያለ መፈረጅን ነው የሚመርጠው። በዚህ መነሻ የሚፈለጉትም የማይፈልጉትም ሁሉም የተባራሪ መረጃ ሰለባ ሆነዋል። እኛም እየሆን ነው። ለዚህ ችግር ዋና ተጠያቂ ኢህአዴግ ነው። ይህንን ችግር መፍታት ከፈለገ በውጪ አገር የመረጃ ዴስክ መክፈት ወይም አንድ መላ መፈለግ አለበት።
አገር እየመራ ያለው ኢህአዴግ የሚዘለፈውን ያህል ተቃዋሚ ፓርቲዎችንም በአግባቡ ጠይቆ፣ መርምሮና አረጋግጦ መውቀስም አይቻልም። አንዳንዶቹ ኢሜል እንኳን አይመልሱም። በራቸው ዝግ ነው። ሃስባቸውን ከራሳቸው የዌብ ሳይት አድራሻ ለመውሰድ እንኳን ቢታሰብ ” የሚይስቅ ጉዳይ ያጋጥማል” የተወሰኑት ጥሩ የሚባል የመረጃ የዌብ ገጽ ቢኖራቸውም ለተጨማሪ ጉዳይ የሚገኙ አይደሉም። በዚህ በኩል ተቃዋሚዎችም የኢህአዴግን ያክል ባይሆንም ለመረጃ ዝግ መሆናቸው አሳሳቢ ነው።
ዛጎል በዚህ አጭር ጊዚያት አራት ለሚደርሱ ድርጅቶች መርጃ እንደምትፈልግ ጠቀሳ ጠይቃለች። መልስ ግን አላገኘችም። ለወደፊቱም ቢሆን መረጃ ማግኘት የሚቀል መስሎ አይታይም። ታዲያ እንደ ጋዜጠኛ የሪፖርት ስራ እንዴት እንስራ? ወይስ ተባራሪ ወሬ እንሰብስብ? ወይስ ዳያስፖራው የሚፈልገው ያልተመጣጠነ መረጃ ነው ብለን በመደምደም የውስን ጸሃፊዎችን ሃሳብ እየተቀበልን እናሰራጭ።እዚህ ላይ በተደጋጋሚና ያለማቋረጥ ሃሳባቸውን ለሚያካፍሉ ወገኖች ያለንን አድናቆት ልንገለጽ እንወዳለን። ምክንያቱም “አያገባንም” በሚል አብዛኞች “አድፋጮች” ሆነው ቀርተዋልና።
ከላይ በተገለጹት ምክንያቶችና በሌሎችም ጉዳዮች እንደ ጋዜጠኛ የማያስወቅስ ስራ ለመስራት መቸገራችንን አስረግጠን ለማስገንዘብ እንወዳለን። አሁን ባለው አሰራር ጋዜጠኞች ነን ብልንም አናስብም። አሁን ላለው የመረጃ ክፍተት የተመጣጠነ ሪፖርት በማቅርብ የበኩላችንን ለመወጣት ብናስብም ሰባራ ሆነናል። አዲሱ የኮሙኒኬሽን ሚኒስትር አቅም ካላቸው ይህንን ሊያስቡበት ይገባል። ራሱ ኢህአዴግም ቢሆን በደፈናው ሚዲያዎችን ከማውገዝ በመቆጠብ ሳያዳላና ሳይመርጥ መረጃ ለሚፈልጉ ሁሉ መረጃ የሚደርስበትን ቀልጣፋና ግልጽ አሰራር ሊተገብር ይገባል። መረጃ የሌለው ጋዜጠኛ ሚዛኑን ለመጠበቅ ስለማይችል ሚዛን በሚጎድላቸው መረጃዎች ራሱን፣ አገርንና ህዝብን ይጎዳል። ሚዲያ ታላቅ ሃይል አለውና በወጉ እንጠቀምበት ዘንድ አስቸኳይ ምላሽ እንሻለን።
በሌላው ጎኑ ተቃዋሚዎች፣ ሲቪክ ድርጅቶች፣ አክቲቪስት ነን የምትሉ፣ ተመራማሪዎች እና ወዘተ… እናንተም ብትሆኑ መረጃ መስጠት ግድ መሆኑን በመረዳት ለሚፈልጋችሁ ሁሉ ደጃችሁ ክፍት ሊሆን እንደሚገባ ለማሳሰብ እንወዳለን። በተመሳሳይ ስም የተደራጃችሁ ቢያንስ ለመረጃ ፈላጊዎች አመቺ ይሆን ዘንድ መረጃ የሚፈስበትን መንገድ አመቻቹ። መረጃ የመስጠት ግዴታ አንዱ የስራችሁ አካል መሆኑን አትዘንጉ። ሌሎች የሚወቀሱበት መንገድ ውስጥ ሆናችሁ ከሌሎች እንደምትሻሉ መስበክ ታማኝ አያደርገምና ግብራችሁ የዴሞክራሲ ወዳድ ስለመሆኑ አንዱ ማረጋገጫ መረጃ ለመስጠት በርን መበርገድ ይሆናል። ሚስጢር ብሎ ነገር የለምና!!
ዛሬ አብዛኞች በዘርፉ የተሰማሩ ጽሁፎችን እየተቀባበሉ ከማተምና ከማሰራጨት ማለፍ ያለቻሉት በዚሁ በመረጃ ዝግነትና መቀራረብ ላይ በተመሰረት ግንኙነት ነው። ስለዚህ መርጃ ማግኘት መብት ነውና የተዘጉ በሮችን ለማስከፈት ተመሳሳይ ድምጽ እናሰማ። ዲያስፖራውም ሆነ አገር ቤት ያለው ህዝብ ተወደደም ተጠላም የመረጃ ጥማት አለበትና ለተመጣጠነ መረጃ እንትጋ። አለያ ግን አንካሳ ጋዜጠኛ ሆነን የሚፈለገውን ያህል ለማከናወን ይሳነናልና። በዚህ መልኩም መቀጠል አገራዊ ፋይዳም የለውም። ትርፉ ድካምና ድካም ብቻ ይሆናል። እኛም “ጋዜጠኛ” መባላችን ጥያቄ ውስጥ ይወደቃል። ፈተናውንም አናልፍም። ፈተናውን የማያልፍ …
አንዳንድ መረጃዎችን ከተለያዩ ሚዲያዎች በማሰባሰብ መስራት የሚቻልበት አግባብ ሊኖር ይችላል። እያደረግነውም ነው። ግን መረጃዎች ወደ ራስ አስተሳሰብ የመንጋደድ ዝንባሌ አላቸው። የመንግስት ሚዲያዎች በአብዛኛው አሞጋሾች ናቸው። በውጪ ያሉት ደግሞ ከላይ ባልነው ችግር የተነሳ ማመጣተኛ መርጃ ስለማያገኙና ሌሎች ምክንያቶች ታክለውበት ወደ አንድ ጽንፍ የማምራት ጉዳይ ይታያል። እንዚህን መረጃዎች እየቀዱ ማሰራጨት አሁንም ሙሉ ጋዤጠኛ አያደርግም። “ሙሉ ጋዜጠኛ መሆን” ለሚፈለጉና ለሚመኙ ሁለቱም መንገዶች ያስቸገራሉ። እና እንዴት እንቀጥል? እያነከስን? ጽሁፍ በመቀራመት? በግል አስተያየት? እንዴት ? ይህ በአጭር ጊዜ የታዘብነውና ብቻችንን ለንወጣው የማንችለው ችግር ሆኖብናል? እንዴት ” ሙሉ ጋዜጠኛ? እንሁን?