Category Archives: የዛጎል- ማረፊያ

ይህ ገጽ ከተለያዩ መገናኛዎች ወይም ምንጮች እየተለቀሙ የሚቀርቡበት መዝናኛ ተኮር ሃሳቦች፣ ታሪክ ቀመስ ቅምሻዎች፣ ቀልዶች፣ ንግግሮች፣ አባብሎች፣ ግጥሞች፣ እንደ ሁኔታው አግባብ ያላቸው አነስተኛ ይዘት ያላቸው መጣጥፎች የሚቀርቡበት ነው። ማንም ይሳተፍበት ዘንድ የፌስ ቡክ ሊንኩን/ ማስፈንጠሪያውን በማያያዝ ቢያቀርብ ወይም ብታቀርብ ደስታችን ነው

የሞረዳ ልጅ አስገራሚው የብዕር ጓደኛ

የብዕር ጓደኛ – እኒህ ሰዉ ሙሉጌታ ረታ ዓለሙ ይባላሉ፡፡ ነፍሱን ይማረዉና የወንድማችን የአብርሃም ረታ ዓለሙ ታላቅ ወንድም ናቸዉ፡፡ እንዲህ እንደዛሬ ማኅበራዊ ሚዲያ በርቀት ያሉ የማይተዋወቁ ሰዎችን ሳያቀራርብ በፊት ፣ ያኔ ሰዎች ሐሳብ ይለዋወጡ የነበሩት በፖስታ ነበር፡፡ በብዕር ጓደኝነት፡፡ ብዙ ‹‹የብዕር ጓደኞች አለን›› ከሚሉት መሀከል አንዱ ነበርኩ፡፡

Image may contain: 1 person, smiling, beard
መምህር ሙሉጌታ ያኔ በአየር ጤና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያስተምሩ ነበር፡፡ ለመገኛነታችን ምክንያት የሆነዉ የእሑድ ጠዋት የራዲዮ ፕሮግራም ነዉ፡፡ እርሳቸዉ ፀሃፊ፣ እኔ ደግሞ ካለሁበት ሆኜ አድማጭ ነበርኩ፡፡ ዉሎ ሲያድርም በግል መፃፃፍ ጀመርን፡፡እ.ኢ.አ ከ1978 ጀምሮ ለአምስት ዓመት ያህል በአካል ሳንተዋወቅ ተፃፃፍን፡፡ በኋላም ወደሸገር ስዛወር በአካል ከመገኛነትም አልፈን ቤተሰብ ለመሆን በቃን፡፡ ( ከያኔም ጀምሮ አጠራሬ አንነቱንና አንተን የቀላቀለ ስለሆነ እዚህም ላይ…)
መልካም የቤተሰብ ኃላፊ፣ጎበዝ ጊታር ተጫዋች፣ብርቱ የተራራ ብስክሌት ጋላቢ ነበር፡፡ ያ የማቲዎች አባት ‹‹ እኔ ከሀዋሳ ሌላ የትም ለመኖር፣ የትም ለመሞት አልተፈጠርኩመ›› ይለኝ ነበር፡፡ 
እናም ዛሬ ከሀዋሳ ወጣ ብሎ ጎጆ ቀልሶ ከትዝታዉ ጋር ይኖራል፡፡ ብቻዉን ራሱን ይጦራል፡፡ ልጆቹ በሥራና በኑሮ ምክንያት በየቦታዉ ተበታተነዋል፡፡ 
ያን ሰሞን ወደሀገሬ መግባትን ሳስብ ‹‹ የግድ ማግኘት አለብኝ›› ብዬ ከወሰንኩኝ የልቤ ሰዎች መሀከል አንዱ ሙሉጌታ ረታ ነበር፡፡ ምኞቴ ተሳክቶም ከ17 ዓመት መለያት በኋላ ተገናኘን፡፡ አሪፍ ሽበታም፣ የሚያምር ጢማም ሆኗል፡፡
ሲበዛ ቁምነገረኛ ሰዉ ነዉ፡፡ ከመጀመሪያዉ ቀን ጀምሮ የፃፍኩለትን ደብዳቤዎች በቅደም ተከተል በፋይል አስሮ አቆይቷል፡፡ ‹‹ አሁን ጊዜዉ ነዉ›› አለና ደርዘን ደብዳቤዎቼን በክብር አስረከበኝ፡፡ ‹‹ ሥጦታዬ ነዉ›› ብሎ፡፡ አቻ የሌለዉ ስጦታ፡፡ 
አነበብኳቸዉ እንደገና፡፡ የዘመነ ጉርምስናዬን እኔነት አየሁባቸዉ፡፡ ያንን አዉቄ ልረሳዉ እምሞክረዉን ጊዜና አጋጣሚ ሳግ እየተናነቀኝ በሐሳብ ተመልሼ ዳከርኩበት፡፡ቀላል ይጣፍጣል? ‹‹እርሱስ ደብዳቤዎቼን አቆይቶ ሰጠኝ፡፡ እኔስ ምን ላድርጋቸዉ?ለማን ልስጣቸዉ?›› በሚል ሐሳብ ላይ ጣለኝ፡፡
አመሰግናለሁ ሙሌ፡፡ ቀሪዉን ዘመንህን ይባርከዉ፡፡ 71 ዓመት ምን አላት? ገና ያለወራነዉ ብዙ ትዝታ አለ፡፡ገናም እናወራለን፡፡  ሌሎች የዚያ ዘመን ደርዘን የብዕር ጓደኞቼ አሁን የት አላችሁ? ደብዳቤዎቼስ እናንተ ዘንድ አሉ ይሆን?

Befekadu Moroda ፌስ ቡክ

የምንኖርበትን ዘመን በ60ዎቹ በፃፋቸው መፃሕፍት የተነበየው ደራሲ

BBC AMHARIC – 1968 ላይ የተፃፈው ‘ስታንድ ኦን ዛንዚባር’ የተሰኘው ልብወለድ፤ ከብዙ በጥቂቱ ስለ ቫያግራ [ወሲብ አበረታች ክኒን]፣ ስለ ቪድዮ ስልክ ጥሪ፣ ስለተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ያወራል።

ይህ ልብ ወለድ መፅሐፍ የጆን በርነር ነበር፤ የሳይንሳዊ ልብ-ወለድ ደራሲው በርነር። እርሱ ይኖርበት በነበረበት ዘመን ገመድ አልባ የነበረው ነገር ያኔ አጀብ የተባለለት ራድዮ ነበር።

ጆን በርነር

በግሪጎሪጎሪሳውያን አቆጣጠር 1934 ዓ.ም. ኦክስፎርድ በተሰኘችው የእንግሊዝ ከተማ ጆን ሂውስተን በርነር የተባለ ጨቅላ ከነቃጭሉ ዱብ ይላል። ቤተሰቦቹ ‘ነብይ ልጅ ተወለደልን’ ብለው የሚደሰቱበት ወቅት አልነበረም። ዓለም በጦርነት የታመሰችበት ዘመን ነበርና።

የበርነር አያት አንዲት መፅሐፍ ነበረቻቸው። መፅሐፏን ጎናቸው ሻጥ አድርገው ካልዞሩ ሰላም አይሰማቸውም። ‘ዋር ኦፍ ዘ ዎርልድስ’ ትሰኛለች። ታድያ ይህች መፅሐፍ በርነር ገና የ6 ዓመት እንቦቃቅላ ሳለ ከእጁ ትገባለች።

በርነር፤ ከአያቱ መፅሐፍ ጋር ከተዋወቀ ወዲህ ነበር በሳይንሳዊ ልብ-ወለድ መፃሐፍት ፍቅር ቅልጥ ያለው። ዕድሜው 9 ሲረግጥ ከማንበብ አልፎ መሞነጫጨር ይጀምራል።

በ13 ዓመቱ አጠር ያለች አንድ ሳይንሳዊ ልብ-ወለድ ይዘት ያላት ፅሑፍ ለአንድ ጋዜጣ ይልካል። ‘አንት ታዳጊ ገና አልበሰልክምና አርፈህ ቁጭ በል’ የሚል ምላሽ ይደርሰዋል። ምላሹ ለበርነር የሚዋጥ አልነበረም።

በ17 ዓመቱ አሜሪካ ውስጥ ላለ አንድ ጋዜጣ ‘ዘ ዋቸርስ’ ሲል ርዕስ የሰጣትን ፅሑፍ ይልካል፤ ፅሑፏም ትታመለታለች። በርነር ይሄኔ የግል ትምህርት ቤት ተማሪ ነበር፤ ጉዞው ደግሞ ወደ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ። ‘ትምህርት ለምኔ’ ያለው በርነር አስኳላውን ትቶ ቁጭ ብሎ መሞነጫጨር ይይዛል።

ቢሆንም አንዳች ውስጣዊ ፍራቻ ሰቅዞ ይይዘዋል። ምናልባት ባይካልኝስ? ኦክስፎርድ ዪኒቨርሲቲ መማር እችል የነበርኩ ሰው እንዲሁ በዋዛ ስባትት ልኖር? የሚሉ ሃሳቦች ይመላለሱበታል።

ይሄን ብድግ ይልና በኤሌክትሪክ የምትሠራ ‘ታይፕራይተሩን’ ከፊቱ አመቻችቶ ይቀመጣል። ዘውጋቸው ሳይንሳዊ ልብ-ወለድ የሆኑ ፅሑፎችን ማምረትም ይጀምራል። ፅሑፎቹ ለተለያዩ ጋዜጣዎች የሚከፋፈሉ ናቸው።

በርነር በወጉ 25 ዓመት ሳይሞላው 80 ያክል ልብ-ወለድ ፅሑፎችን በስሙ አሳትሞ ነበር። በ14 ዓመት የምትበልጠው የፍቅር ጓደኛው ማርጆሪን ያገኛትም ጋዜጣ ላይ ‘ትዳር ፈላጊ’ የተሰኘው ዓምድ ላይ አይቷት ነው። በተገናኙ አራት ወራት ውስጥ የተጋቡት ጥንዶቹ በፍቅር ክንፍ ይላሉ።

ማርጆሪ እስከ ዕለተ ሞቷ ድረስ የበርነር አማካሪ፣ ወኪል እና የልብ ወዳጅ ሆና እንደቆየች ይነገርላታል።

‘ነብዩ በርነር’

ሰው ሰራሽ ልህቀት [አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ]፣ ዘረኝነት፣ ዕፅ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የሕዋ ጉዞ እና ቴክኖሎጂ የበርነር ሥራዎች ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ያላቸው ሃሳቦች ናቸው።

ሥራዎቹ ገደብ የለሽ ምስጠት የሚስተዋልባቸው ሲሆኑ አንዳንድ ልብ-ወለድ ትልሞቹ እንደው የማይሆን ነገር ተብለው ቢታለፉም በርካታ ታሪኮቹ አሁን የምንኖርበትን ዓለም ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው።

1972 ላይ የፃፈው ‘ዘ ሺፕ ሉክ አፕ’ የተሰኘው ልብ-ወለድ የሰው ልጆች ቁጥር በዝቶ ምድር በሕዝብ ብዛት ስትጨናነቅ እና አካባቢ ብክለት ዓለምን ወደ መጥፊያዋ ሲያቀርባት ያሳያል።

በርነር በጭስ የታፈነች ዓለም ብሎ የፃፈው 1975 ላይ ነበር፤ ይህ ፎቶ ሕንድ ውስጥ የተነሰው ደግሞ 2017 ላይ ነውImage copyrightGETTY IMAGESአጭር የምስል መግለጫበርነር በጭስ የታፈነች ዓለም ብሎ የፃፈው 1975 ላይ ነበር፤ ይህ ፎቶ ሕንድ ውስጥ የተነሰው ደግሞ 2017 ላይ ነው

1975 ላይ የሳለው አንድ ገፀ-ባሕርይ ደግሞ ዓለም ያጨበጨበለት የኮምፒውተር ሞጭላፊ [ሃከር] ነው። በበርነር ዘመን ‘ሃከር’ ምናልባት የኪስ ቦርሳ ሞጭልፎ የሚሮጥ እንጅ ከኮምፒውተር ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር አልበረም። ኮምፒውተሩንስ ማን በውል አውቆት።

ነገር ግን በርነር ከአታሚዎቹ ጋር ሰላማዊ ግንኙት አልነበረውም። ለፅሑፉ አርትዖት ከሚሰጡ ሰዎች ጋር ይጋጭ የነበረው ደራሲው የኋላ ኋላ አታሚ እያጣ ይመጣል። የሚስቱ በሞት መለየት ደግሞ ነገሮችን ‘በእንቅልፍ ላይ ጆሮ ደግፍ’ ያደርጉበታል።

ይሄኔ ነው ሎንዶን ውስጥ የነበረውን መኖሩያ ቤት ሸጦ ወደ አንዲት የገጠር መንደር መሰደድን የመረጠው።

‘ስታንድ ኦን ዛንዚባር’

በርነር ከሚታወቅባቸው ሥራዎች ጉምቱ ያሰኘው ‘ስታንድ ኦን ዛንዚባር’ የተሰኘው ልብ-ወለድ ነው። እዚህ መፅሐፍ ላይ በ2010 የዓለም ሕዝብ 7 ቢሊዮን እንደሚደርስ በርነር ፅፏል፤ ተንብይዋል ማለቱ ሳይቀል አይቀርም። የዓለም ሕዝብ 7 ቢሊዮን መድረሱ ይፋ የሆነው 2011 ላይ ነበር።

ልብ-ወለዱ ሁለት ኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ አፓርታማ ተጋርተው የሚኖሩ ሰዎችን ምናባዊ ታሪክ የሚከተል ነው። አንደኛው ነጭ ሰላይ፣ ሌላኛው ደግሞ አፍሪቃ አሜሪካዊ የንግድ ሰው። አክሎም መፃሐፉ የዓለም ኃያላን መንግሥታት ከሰው ልጆች የላቀ ዘረ-መል ለመፍጠር ሲያሴሩ ያስነብባል።

እንደ አውሮፓ ሕብረት ያለ አንድ ድርጅት እና ቻይና የአሜሪካ ተቀናቃኝ ሃገር ሆና መገኘት በበርነር ሥራዎች ውስጥ በ1960ዎቹ የተዳሰሱ ናቸው።

በርነር ሳይንሳዊ ልብ-ወለድ ሥራዎቹ የምንኖርበትን ዓለም ዓይነት ቅርፅ ይኖራቸው ዘንድ እንዲያግዘው በማሰብ የተለያዩ ክፍለ ዓለማትን ዞሮ ጎብኝቶ ነበር።

እስካዛሬ ያላየናቸው ነገር ግን በርነር የተነበያቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ። ወደፊትም አይፈጠሩም ብሎ መገመት ግን ከባድ ነው።

* ከላይ የተጠቀሱት ጊዜዎች ሁሉም በግሪጎሪሳውያን አቆጣጠር የተፃፉ ናቸው።

የጭፈራ ገንዘብ ፍለጋ ‘እገታ’ ያቀናበሩ ትንንሽ ልጆች ተያዙ

ጆስ የተባለችው የናይጄሪያ ከተማ ፖሊስ የ15 ዓመቱ ታዳጊ የታገተ በማስመሰል ከአባቱ የማስለቀቂያ ገንዘብ ለማግኘት ያደረገውን የእገታ ድራማ በዝርዝር ለማወቅ ምርመራ እያካሄደ ነው።

የከተማዋ ፖሊስ ቃል አቀባይ የሆኑት ቴርና ትዮፕቭ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ታዳጊው ያቀናበረው የእራሱ እገታ “በተጠናና በማያስታውቅ ሁኔታ የተካሄደ ነበር” ብለዋል።

አሁን በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኙት ታዳጊውና በእድሜ ከእርሱ ከፍ የሚሉት አራት ጓደኞቹ 1365 ዶላር የሚመነዘር 500 ሺህ ናይራ (የናይጄሪያ ገንዘብ) ‘ታጋቹን’ እንዲለቀቅ ጠይቀው ነበር ተብሏል።

የእገታ ድራማውን ያቀናበሩት ታዳጊዎች ይህንን ገንዘብ ትምህርት ሲዘጋ ለሚያዘጋጁት ድግስ (ፓርቲ) ሊያውሉት አስበው ነበር። ‘ከእገታው’ ሦስት ቀናት በፊት ‘የታጋቹ’ አባት የቤተሰባቸውን ወጪዎች ለመሸፈን ሲሉ መኪናቸውን ሸጠው እንደነበርም ተነግሯል።

የ15 ዓመቱ ‘ታጋች’ ይህንን የእገታ ድራማ ያቀናበረው አባቱ ከመኪና ሽያጭ ያገኙትን ብር ለመስረቅ ቤታቸውን ቢበረብርም አባት ከመኪናቸው ሽያጭ ያገኙትን የገንዘብ ክፍያ በቀጥታ ወደ ባንክ አካውንታቸው ስላስገቡት ሊያገኘው ስላልቻለ ነበር።

ከዚያ በኋላም ጓደኞቹ አጋቾችን መስለው በመቅረብ አባትየው ጋር ደውለው ልጁን ከከተማዋ ራቅ ወዳለ ቦታ መውሰዳቸውንና ለጸጥታ አካላት እንዳያሳውቁ አስጠንቅቀዋቸው ነበር። ነገር ግን አባት ነገሩ የከፋ መሆኑን ሲገነዘቡ ለፖሊስ ማሳወቃቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

የእገታው ድራማ ሊከሽፍ የቻለው ‘አጋቾቹ’ የማስለቀቂያ ገንዘብ ለመጠየቅ የደወሉበት ስልክ ከተማው ውስጥ በሚገኝ አንድ ህንጻ ውስጥ መሆኑ በመታወቁ ነው።

ፖሊስ ወደ ህንጻው በድንገት ሲገባ ጓደኛሞቹ እየተወያዩ ነበር የደረሰው። አባትየው በልጃቸው ድርጊት በጣም ያዘኑ ሲሆን ገንዘብም እንዳልጠየቃቸው ለፖሊስ ተናግረዋል።

ምንም እንኳን ‘የእገታው’ ሐሳብ የታዳጊው ይሁን እንጂ ድርጊቱ በጥንቃቄ እንዲፈጸም የ18 እና የ22 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ጓደኞቹ ተግባር ሊሆን እንደሚችል ፖሊስ ጠርጥሯል።

አሁን እስር ላይ ያሉት ወጣቶች ከፈጸሙት የታሰበበት ድርጊት በመነሳት ከዚህ በፊትም ገንዘብ ለማግኘት ተመሳሳይ እገታ ፈጽመው ከሆነ በሚል ጥርጣሬ ምርመራ እያደረገ ነው።

ናይጄሪያ ውስጥ እገታ በተደጋጋሚ የሚፈጸም ድርጊት ሲሆን የወንጀለኛ ቡድኖች ሃብታም ድሃ ሳይሉ እገታ በመፈጸም እስከ 150 ሺህ ዶላር ማስለቀቂያ ይጠይቃሉ። አንዳንድ ጊዜም ቤተሰቦቻቸው መክፈል ያልቻሉ ታጋቾችን ይገድላሉ። የፖሊስ አዛዡ ሞሃመድ አዳሙ እንደተናገሩት በጥርና ሚያዚያ ወራት ውስጥ 685 ሰዎች በናይጄሪያ ውስጥ እገታ ተፈጽሞባቸዋል።

BBC Amharic

ባልና ሚስት ከአንድ ወንዝ ይቀዳሉን እንጂ በተመሳሳይ ቀን ይወለዳሉንስ አልሰማንም ነበር!

የመድኃኒት ጥቂት ይበቃል እያለች፤
የምኒልክ እናት አንድ ወልዳ መከነች፡፡

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 11/2011 ዓ.ም (አብመድ) ንጉሠ ነገሥት ከንግሥት፤ እምዬ ምኒልክ ከእቴጌ ጣይቱ፤ ርሀቤ ምኒሊክ ከብርሃን ዘ ኢትዮጵያ ጣይቱ፤ በአራት ዓመታት ልዩነት ነሐሴ 12 ቀን 1836 እና ነሐሴ 12 ቀን 1832 ዓ.ም ሚስት እና ባል በቅደም ተከተል ከኢትዮጵያ ምድር ፈለቁ፡፡ በኢትዮጵያውያን ወግና ባሕል ብዙም ባልተለመደ መልኩ ሚስት ባልን አራት ዓመታት አስከንድተው ይበልጧቸዋል፤ በተመሳሳይ ቀን የተወለዱት የትዳር አጋሮችና የሀገር መሪዎች፡፡

የንጉሥ ሳኅለሥላሴ ልጅ ከሆኑት ልዑል ኃይለ መለኮት እና ከወይዘሮ እጅጋየሁ ለማ ከደብረ ብርሃን ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ አምስት ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ በምትገኘው የገጠር መንደር አንጎለላ ልዩ ስሟ እንቁላል ኮሶ መንደር ውስጥ ነሐሴ 12 ቀን 1836 ዓ.ም አንድ ሕጻን ይህችን ምድር ተቀላቀለ፡፡ ይህ ሕጻን ‹‹የኋላ ኋላ በአካልና በአዕምሮ ሞገስን አግኝቶና ነግሦ የሚመራው ጥቁር ሕዝብ በነጭ ዘር ላይ ድል ተቀዳጅቶ፣ የጥቁር አፍሪካውያን ሁሉ ትምክህት ይሆናል›› ብሎ ያሰበ ባይኖርም እንኳን ስሙን ግን ምኒልክ አሉት፡፡ 
ሕጻኑ ምኒልክ የመፃዒ ጊዜው መራሄ መንግሥትነቱ መክሊት ይገለጥ ዘንድ ግን ከ12 ዓመታት በላይ መጠበቅ አላስፈለገውም፡፡ ሕዳር 1 ቀን 1848 ዓ.ም ልክ በ12 ዓመታቸው የአባታቸው ኃይለመለኮት የቀብር ሥነ ስርዓት እንደተፈፀመ የአባታቸውን አልጋ በይፋ ተቀበሉ፡፡

ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ፤ ትልቁ ራስ ጉግሳ የጎንደሯን ባላባት ወይዘሮ ማሪቱን አግብተው ወይዘሮ ሂሩትን፣ ወይዘሮ ተክሌንና ወይዘሮ አስቴርን ይወልዳሉ፡፡ ወይዘሮ ሂሩት ከራስ ገብሬ እና ከወይዘሮ ሳህሊቱ የሚወለዱትን ደጃዝማች ኃይለ ማሪያምን አግብተው ደጃዝማች ብጡልን፣ ደጃዝማች መርሶንና ሌሎችንም ልጆች ይወልዳሉ፡፡ ደጃዝማች ብጡል ደግሞ የጎጃም ደብረ መዊዕ ባላባት የሆኑትን ወይዘሮ የውብዳርን አግብተው ነሐሴ 12 ቀን 1832 ዓ.ም ጎንደር ደብረ ታቦር እቴጌ ጣይቱን ወለዱ፡፡

እቴጌ ጣይቱ የአባታቸው አያት በሆኑት በወይዘሮ ማሪቱ በኩል የዓፄ ፋሲል ተወላጅ ከሆኑት ከዓፄ ተክለ ጊዮርጊስ (ፍፃሜ መንግሥት) የሚመዘዝ የዘር ሐረግ አላቸው፡፡ እናም እቴጌ ጣይቱ የዘር ሐረጋቸው ከጎንደር፣ ከጎጃም እና ከወሎ ይመዘዛል ማለት ነው፡፡ 
እቴጌ ጣይቱ በ13 ዓመታቸው አባታቸው በጦር ሜዳ በመሞታቸው ደብረ ታቦርን ለቅቀው ወደ እናታቸው አገር ጐጃም በመሄድ የእንጀራ አባታቸው በሚያስተዳድሩት ደብረ መዊዕ ቀደም ሲል ጐንደር ማኅደረ ማርያም ጀምረውት የነበሩትን ትምህርታቸውን እየተማሩ ተቀመጡ:: በትዳር ምክንያት ከጎንደር እስከ ትግራይ የተንቀሳቀሱት እቴጌ ጣይቱ በተደጋጋሚ የሞከሩት የትዳር ሕይወት በጦርነት ምክንያት አልሳካ ሲላቸው ወደ ጐጃም ተመልሰው በሞግዚታቸው እንክብካቤ እየተደረገላቸው በደብረ መዊዕ ቀድሞ ያቋረጡትን ትምህርት ቀጠሉ፡፡

እቴጌ ጣይቱ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በጥበብና በሕይወት ፍልስፍና የላቀ ችሎታ ባለቤት መሆናቸው እየታወቀ መጣ፡፡ ይህንን የጣይቱን ዝና ከሰሙ ልዑላን መካከል ወጣቱ ምኒልክ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በእርግጥ አንዳንዶቹ ምኒልክ በዓፄ ቴዎድሮስ ቤት በምርኮ ሳሉ ጣይቱን በደንብ ያውቋቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡ (የዓፄ ቴዎድሮስ ሚስት ጥሩወርቅ ውቤ ኃለማርያም እና ጣይቱ ብጡል ኃይለማርያም የወንድማማች ልጆች ስለነበሩ ይገናኙ ስለነበር፡፡)

ምኒልክ ስለ እቴጌ ጣይቱ ዝና የሰሙት አብረው ይኖሩ ከነበሩት አሉላና ወሌ ብጡል ከሚባሉት የእቴጌ ወንድሞች እንደሆነም ይነገራል፡፡ በወቅቱ የምኒልክ ሞግዚት የነበሩት ደጃዝማች ናደው ከሌሎች ቅርብ ሰዎቻቸው ጋር ተማክረው ጣይቱንና ምኒልክን ለማጋባት ሙከራ አድርገው ነበር፤ ምንም እንኳን በወቅቱ በተለያዩ ችግሮች ጋብቻው ቢዘገይም፡፡ በእርግጥ ለጋብቻው አለመስመር የዓፄ ቴዎድሮስ ልጃቸውን አልጣሽን ለምኒልክ ሚስትነት መፍቀድ እንቅፋት እንደነበር የሚናገሩም አሉ፡፡

ዘመኑ በደረሰ ጊዜ ግን ዓፄ ምኒልክ እቴጌ ጣይቱን አገቡ፡፡ ንጉሥ ምኒልክ ሚያዚያ 25 ቀን 1875 ዓ.ም በአንኮበር መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ከእቴጌ ጣይቱ ብጡል ጋር በቁርባን ጋብቻውን ፈፀሙ፡፡ አምስት ዓመታት ቆይቶም ጥቅምት 27 ቀን 1882 ዓ. ም ጣይቱ ብጡል ‹‹እቴጌ›› ተብለው ተሠየሙ፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሥ ምኒልክ ‹‹ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ›› ከተባሉ ሦስተኛ ቀናቸው ነበር፡፡ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በተሰኘው መጽሐፋቸው እቴጌ ጣይቱ ለዚህ ታላቅ ሥልጣን በበቁ ጊዜ የተፈጠረውን ስሜት ሲገልፁ ‹‹የሸዋ ቤተ መንግሥት ዓለሙ የዚህን ቀን ተጀመረ:: የሸዋ ቆሌ፣ የሸዋ ደስታ የዚህን ቀን ተጀመረ:: የሸዋ ቤተ መንግሥት ከጣይቱ በኋላ ውቃቢ ገባው፣ ግርማና ውበት ተጫነው፣ ጥላው ከበደ፣ የእውነተኛው አዱኛ፣ የእውነተኛው ደስታ ከጣይቱ ብጡል ጋር ገባ›› ሲሉ ጽፈዋል፡፡

እንዲያውም 
‹‹ፍጥረት ተጨንቆ አፈና ይዞት፣ 
ዓለም ተደሰተ ጠሐይ ወጣለት›› የሚል ቅኔ መዘረፉም ይነገራል፡፡

እቴጌ ጣይቱ ዓፄ ምኒልክን ካገቡ በኋላ ያልተሳተፉበት ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳይ አልነበረም፡፡ ዓፄ ምኒልክ አዳዲስ ሥልጣኔዎችን ለማስገባት ቁርጠኛ አቋም ይዘው በተንቀሳቀሱበት ጊዜ አጋራቸው እቴጌ ጣይቱ ነበሩ፡፡ በተለይም ዘመናዊ ትምህርት ቤት ሲያቋቁሙ፣ የባቡር ሃዲድ ሲዘረጉ፣ ውኃ በመዘውር እንዲቀዳ ሲያደርጉ፣ በቀጭኑ ሽቦ በስልክ ግንኙነት በተጀመረ ጊዜ፣ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ቤት በመጡ ጊዜ፣ የእህል ወፍጮ ሲተከልና ሌሎችም የቴክኖሎጂ ውጤቶች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ አጋዣቸው የነበሩት እቴጌ ጣይቱ ነበሩ፡፡

የእቴጌ ጣይቱን ስም ዘላለም ሲያስጠሩ ከሚኖሩ ተግባሮቻቸው መካከል ግንባር ቀደሙ አዲስ አበባ ከተማን መቆርቆራቸውና መጠሪያ ስሟንም ለመሰየም መቻላቸው ነው፡፡ እቴጌ ጣይቱ የመጀመሪያው ዘመናዊ ሆቴል መሥራች፤ የባልትና ሙያንና የሽመና ጥበብን ለቤተ መንግሥቱ በማስተዋወቅ ግንባር ቀደም ነበሩ፡፡

እቴጌ ጣይቱ በፖለቲካዊ ተግባራቸው ሲመዘኑም ሁሌም ሚዛን የሚደፋው ሥራቸው ጣሊያኖች በውጫሌ ውል ካሰፈሩት ነጥቦች በአንቀፅ 17 ስር የተቀመጠውን የጣሊያንኛ ትርጉም ኢትዮጵያን በሚጐዳ መልኩ ጥቅም ላይ ውሎ በተገኙ ጊዜ የያዙት የማያወላውል አቋም ነው፡፡

አንቶኔሊ የተባለው የጣሊያን ዲፕሎማት በቤተ መንግሥት ተጠርቶ ከአፄ ምኒልክና ከእቴጌ ጣይቱ ፊት ቀርቦ በውጫሌው ውል ከተካተቱት ነጥቦች መካከል በአንቀፅ 17 ሥር የሰፈረውን ትርጉም እንዲያስተካክል ሲጠየቅ የአገሩን መንግሥት ክብር የሚነካ ስለሚሆን ይህ እንደማይደረግ በግልፅ ተናገረ፡፡ በዚህ ጊዜ እቴጌ ‹‹ያንተ ፍላጐት ኢትዮጵያ በሌላ መንግሥት ፊት የኢጣሊያ ጥገኛ መሆኗን ለማሳወቅ ነው፤ ነገር ግን ይህን የመሰለው የምኞት ሐሳብ አይሞከርም፡፡ እኔ ራሴ ሴት ነኝ ጦርነት አልፈልግም፤ ነገር ግን ይህን ውል ብሎ ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ›› ሲሉ ተናገሩ፡፡
በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል እሰጥ አገባው ቀጥሎ ከቆየ በኋላ ጦርነቱ አይቀሬ ሆነና ዓፄ ምኒልክ ‹‹ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት›› ብለው ወደ ዓደዋ ጦርነት ሲዘምቱ ኑሯቸውም ሆነ ኅልፈታቸው ከባለቤታቸው ሊነጠል እንደማይችል የተገነዘቡት እቴጌ ጣይቱ በራሣቸው የሚመራ ሦስት ሺህ እግረኛ ጦር እና ስድሰት ሺህ ፈረሰኛ አስከትለው ከባለቤታቸው ጐን ተሰልፈው ውጣ ውረድ የበዛበትን የጦርነት ጉዞ በድል አድራጊነት አጠናቀቁ፡፡ በተለይም እቴጌ ጣይቱ የጠላትን ደካማ ጎን አጥንተው ያቀርቧቸው የነበሩ የማጥቃት ስልቶች ለዓድዋ ድል የጀርባ አጥንት ነበሩ፡፡

እቴጌ ጣይቱ በዚህ መልኩ አገራዊ ተልኳቸውን እየተወጡ እያሉ ባለቤታቸው ዓፄ ምኒልክ በጠና ታመሙና ከሕዳር ወር 1902 ዓ.ም ጀምሮ ከቤት ዋሉ፡፡ ታኅሳስ 3 ቀን 1906 ዓ.ም አፄ ምኒልክ በተወለዱ በ69 ዓመታቸው በዕለተ ዓርብ አረፉ፡፡ ‹‹ሕዝቡ የምኒልክን ሞት ከሰማ ይረበሻል›› ተብሎ በሕይወት አሉ እየተባለ እየተወራ እስከ ሰገሌ ዘመቻ ሁለት ዓመት ከ10 ወር ድረስ ሞታቸው ተደበቀ፡፡ በምኒልክ ሁኔታ ግራ የተጋባው ሕዝብም እንዲህ ሲል የንጉሡን ሁኔታ ይጠይቅ ነበር፡፡

‹‹አርባ ስድስት ዓመት የገዛኸው ንጉሥ፤
እንዳለህም ስጠኝ ከሌለህም ላልቅስ፡፡›› ሲባልም ነበር፡፡

በ1908 ዓ.ም ደግሞ በልጅ ኢያሱ ትዕዛዝ እቴጌ ጣይቱ በግዞት እንጦጦ ማርያም ወጥተው እንዲቀመጡ ተደረገ፡፡ እቴጌ ጣይቱ ዓፄ ምኒልክ ከሞቱ በኋላ ከቤተ መንግሥት እንዲወጡ በተጠየቁ ጊዜ ‹‹መከሬን ከትቻለሁ፤ እንግዲህ እኔ እዚህ ምን አለኝ ጌታዬ?! እኔም በተራዬ እከተልዎታለሁ›› የሚል ቃል መናገራቸው ይነገራል፡፡

እቴጌ ጣይቱ ከጥር ወር 1910 ዓ.ም ጀምሮ እንደዋዛ የጀመራቸው ሕመም ጠናባቸውና የካቲት 4 ቀን 1910 ዓ.ም ሌሊት በተወለዱ በ78 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ የማረፋቸው ዜና እንደተሰማ በቤተ መንግሥቱ 25 ጊዜ መድፍ ተተኮሰ፡፡
መልካም ልደት ለንጉሡ እና ለንግሥቲቱ!

በታዘብ አራጋው – አማራ ማስ ሚዲያ
ፎቶ፡- ከድረገጽ

ቻይና አሜሪካ ለታይዋን ለመሸጥ ያፀደቀችው የጦር መሳሪያ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ አፀፋዊ እርምጃ እንደምትወስድ ገለጸች

ቻይና አሜሪካ ለታይዋን ለመሸጥ ያጸደቀቸውን የጦር መሳሪያ ሽያጭ ተግባራዊ የምታደርግ ከሆነ ተመጣጣኝ አፀፋዊ እርምጃ የምትወስድ መሆኑን አስታውቃለች።

የአሜሪካውፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለታይዋን የሚከናወን የ8 ቢሊየን ዶላር የጦር መሳሪያ ሽያጭ ውልን በትናንትናው ዕለት አፅድቀዋል።

በውሉ መሰረትም ዋሽንግተን 8 ቢሊንየን ዋጋ የሚያወጡ ኤፍ 16 የተሰኙ ተዋጊ ጄቶችን ለታይፔ የምትሸጥ ይሆናል።

ይህን ተከትሎም ቻይና አሜሪካ ለታይዋን ለመሸጥ ያፀደቀችውን የጦር መሳሪያ ውል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንድትሰርዝ በድጋሚ አስጠንቅቃለች።

የቻይና  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሁዋ ቹኒንግ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት ፈጣን ምላሽ፥አሜሪካ ልታከናውነው ያፀደቀቸው የጦር መሳሪያ ሽያጭ የቻይናንና  አንድነት በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዳ ነው ብለዋል።

ስለሆነም አሜሪካ በቀጠናው ከምታከናውናቸው አፍራሽ፣ ተንኳሽና  መሰል  ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ልትቆጠብ ይገባል ነው ያሉት።

አሜሪካ ማሳሰቢያውን ወደ ጎን በመተው የመሳሪያ ሽያጩን ተግባራዊ የምታደርግ ከሆነ  ቻይና ጠንከር ያለ አጸፋዊ እርምጃ የምትወስድ መሆኑን ነው የገለጹት።

በዚህ ምክንያት ለሚፈጠረው ችግር  አሜሪካ ሃላፊነቱን ትወስዳለች ያሉት ሁዋ ቹኒንግ፥ ይህ ከመሆኑ በፊት ዋሽንግተ ጉዳዩን በድጋሜ እንድታጤነው አሳስበዋል።

ቻይና አሜሪካ ለታይዋን ጦር መሳሪያ ለመሸጥ ስታቅድ ጀምሮ ድርጊቱ ተግባራዊ እንዳይሆን ስታስጠነቅቅ መቆየቷ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ አሜሪካ የቻይናን ማስጠንቀቂያ ወደ ጎን በመተው የጦር መሳሪያ ሽያጩን ተግባራዊ ለማድረግ መንቀሳቀሷ በበሀገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት  ይበልጥ ሊያሻክረው እንደሚችል ተጠቁሟል።

ቻይና ራስ ገዝ የሆነውችውን ታይዋን የራሴ ግዛት ናት ብላ የምታምን ሲሆን፥ ይህን ለማሳካትም የተለያዩ ዘዴዎችን በመተግበር  ወደ ግዛቷ የማጠቃለል ፍላጎት አላት።

ምንጭ ፥presstv.com – (ኤፍ ቢ ሲ)

የአዶልፍ ሂትለር ወጥ ቀማሽ የነበሩ ሴቶች አስደናቂ ታሪክ

እያንዳንዷ የምግብ ገበታ የእርስዎን በሕይወት መኖርና አለመኖር የምትወስን ብትሆንስ? የሚቀርብልዎ ቁርስ፣ ምሳ ወይም እራት፤ የሞትዎ ዕጣ የሚመዘዝበት እድልን የሚፈጥር ነገር ግን እምቢ ማለት ደግሞ የማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ የሚኖርን ሰው አስቡት። ይህ ልብ ወለድ አይደለም። የሂትለር ወጥ ቀማሾች የየቀን እውነታ እንጂ።

የሁለተኛው ዓለም ጦርነት የመጨረሻዎቹ 30 ወራት አካባቢ ሂትለር እያንዳንዷ ወደ አፉ የምትገባ ነገር በሌላ ሰው መቀመስ ነበረባት።

• ለልጃቸው “ሂትለር” የሚል ስም የሰጡ እናትና አባት ተፈረደባቸው

የጀርመን ጠላቶች ወይም የእርሱ ምቀኞች እንደው በምግብ መርዘው ፍፃሜውን እንዳይቀርቡበት የሰጋው ሂትለር፤ ጀርመናዊ ጉብሎች አስመልምሎ ሲያበቃ ‘ወጥ ቀማሽ’ አደረጋቸው።

የእኒህ ሴቶች አስገራሚ ታሪክ ለጆሮ የበቃው የዛሬ 6 ዓመት ገደማ ነው፤ ታሪኩን ለሰሚ ያደረሰችው ደግሞ የ95 ዓመቷ የያኔዋ የሂትለር ወጥ ቀማሽ የነበረችው ማርጎ ዎክ ናት።

የማርጎ ዎክ ታሪክ ‘የሂትለር ወጥ ቀማሾች’ በሚል ርዕስ ተከሽኖ ትያትር ሊሆን በቅቷል።

ሁሉም ተዋንያን ሴቶች ናቸው። ጭብጡ የሚያጠነጥነው ደግሞ አራት የሂትለር ወጥ ቀማሽ የነበሩ ወጣት ሴቶች ላይ ነው።

ማርጎ መጀመሪያ ታሪኳን ያጫወተችው ሚሼል ብሩክስ ለተሰኘች ጋዜጠኛ ነበር። «መቼም ይህን ታሪክ ትፅፊዋለሽ?» የብሩክስ ጥያቄ። «እኔ አልፅፈውም የምትይ ከሆነ፤ እመኚኝ እኔ መፃፌ አይቀርም።»

• የሂትለር ሥዕሎች ለምን አልተሸጡም?

ብሩክስ ታሪኩ እጅግ አሳዛኝና ጨለም ያለ መሆኑን ብታውቅም ‘ትራጃይኮሜዲ’ አድርጋ ለመሥራት ነበር የወሰነችው። እኒህ ወጥ ቀማሽ ሴቶች በዚያ ጨለማ ወቅት እንዴት ጓደኛሞች ሆነው መዝለቅ እንደቻሉ እንዲያትት አድርጋ ነው ትያትሩን የፃፈችው።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ጀርመናዊያን በከባድ ችጋር ተመተው በርካቶች በረሃብ አለንጋ የተገረፉበት ዘመን ነበር። ነገር ግን እኒህ ሴቶች በቀን ሦስት ጊዜ ለሂትለር ተብሎ የበሰለ በቅመም ያበደ ምግብ ያገኙ ነበር።

ወቅቱን የምትዘክረው ማርጎ፤ ሂትለር ሥጋ መመገብ ብዙም የማይወድ ሰው ነበረ ትላለች። አትክልት፣ ሩዝ፣ ፓስታ እና ፍራፍሬ የሰውዬው ምርጫዎች ነበሩ። እኒህን ምግቦች በዚያን ጊዜ ማግኘት ቀርቶ ማሰቢያ የሚሆን አቅም የሚሰጥ ምግብ ማግኘት የከበደበት ዘመን ነበር።

አዶልፍ ሂትለርና ሙሶሊኒ 'የዎልፍ ሌር' በተሰኘው የሂትለር መሸሸጊያ ስለጦርነቱ ሲመክሩImage copyrightGETTY IMAGESአጭር የምስል መግለጫአዶልፍ ሂትለርና ሙሶሊኒ ‘የዎልፍ ሌር’ በተሰኘው የሂትለር መሸሸጊያ ስለጦርነቱ ሲመክሩ

«ምንም እንኳ የሚቀርቡት የምግብ ዓይነቶች በዓይን የሚበሉ ቢሆኑም እኛ ግን በሰቀቀን ነበር የምንመገባቸው።»

«በርካታ ሴቶች ምግቦቹን የሚመገቡት እያለቀሱ ነው። በጣም ይፈሩ ነበር። የቀረበለንን ጥርግ አድርገን መብላት አለበን። ከዚያ ቢያንስ ለአንድ ሰዓት ያክል መጠበቅ አለብን። ብዙዎቻችን ከአሁን አሁን ታመምን እያልን እናለቅስ እንደነበር አስታውሳለሁ» ስትል ወቅቱን ታስታውሳለች።

የሂትለር የወጥ ቤት ሰዎች ሴቶቹ ከተመገቡ አንድ ሰዓት በኋላ ነው ምግቡን በዓይነት በዓይነቱ ለአዛዣቸው ያቀርቡ የነበረው። በሴቶቹ ቅምሻና በሂትለር የምግብ ሰዓት መካከል ያለችው 60 ደቂቃ ምጥ ነበረች። ቁጭ ብሎ ሞትን የሚጠባበቁባት

ከምግብ ቀማሾቹ መካከል ተመርዛ የሞተች ሴት ያለች እንደሁ የሚታወቅ ነገር የለም፤ ማርጎ ዎክ «እኔ በነበርኩበት ወቅት ማንም ተመርዞ የሞተ የለም» ትላለች። የዛሬ ስድስት ዓመት ማርጎ ዎክ ታሪኳን እስከተናገረችበት ወቅት ድረስ ግን ስለ ወጥ ቀማሾቹ ሴቶች የሚታወቅ ነገር አልነበረም።

የሩሲያ ወታደሮች ወደ አዶልፍ ሂትለር ቤተ መንግሥት መቅረብ ሲጀምሩ አንድ ባለማዕረግ ወታደር ማርጎን አሾልኮ ያስወጣትና ወደ በርሊን የሚሄድ ባቡር ላይ ያሳፍራታል። ሌሎች ሴቶች ግን እምጥ ይግቡ ስምጥ ማርጎ የምታውቀው ነገር የለም። ምናልባትም የሩሲያ ወታደሮች በፈጸሙት ጥቃት ተገድለው ይሆናል ስትል ትገምታለች።

• አዶልፍ ሂትለርን በሳምሶናይት ቦምብ ያቆሰለው መኮንን

ሰው ለመኖር ይመገባል። ማርጎ እና ወጥ ቀማሽ ጓደኞቿ ግን ይመገቡ የነበረው ለመሞት ነበር፤ ሞትን ከሂትለር ቀድሞ ለመቅመስ። እንዴት ይህን የመሰለ ታሪክ ‘አስቂኝ ትያትር’ ይሆናል? «እኔም ገርሞኛል» ትላለች ማርጎ።

«ሰዎች ወደ እኔ መጥተው እንዴት አድርገን ነው ይህን ትያትር የምናየው? እንዴትስ ጥርሳችን ይስቅልናል? ሲሉ ይጠይቁኛል። ነገር ግን ትያትሩን ብታዩት ይገባችኋል። እኛ እኮ ከሂትለር ጋር ምንም ግንኙነት የለንም። እንደውም እንደተቀረው ሰው በጣም እንጠላው ነበር [ሳቅ]።»

Credit – BBC Amharic

የኢትዮጵያ ታዳጊ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ወደ ኤርትራ ያቀናል

ከ15 ዓመት በታች ታዳጊ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በኤርትራ የሚደረገው የምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ቀጣና ሻምፕዮና (ሴካፋ) ውድድር ሊሳተፍ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ቡድኑ ከ20 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በኤርትራ የሚጫወት የኢትዮጵያ ቡድን እንደሚሆን ኢብኮ ዘግቧል፡፡ በምድብ ሁለት ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን በቅድሚያ ከኡጋንዳ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ጋር ነገ ይጫወታል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የፕሬስ ኃላፊ ባሕሩ ጥላሁን “ይህ ለእኛ የተጠፋፋ ቤተሰብ እንደመገናኘት የሚቆጠር ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“ኤርትራ ውስጥ በተዘጋጀው ውድድር ተደስተናል፤ ከ20 ዓመታት በላይ ተለያይተናል። ይህም ኤርትራ ውስጥ ከሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ዘላቂ ወዳጅነት የምንመሠርትበት መልካም አጋጣሚ ይሆናልም” ብለዋል።

በውድድሩ ላይ አስተናጋጇ ኤርትራ በምድብ አንድ ከሚገኙት ቡሩንዲ፣ ኬንያ፣ ሱዳን እና ሶማሊያ ጋር ትጫወታለች። ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከየምድባቸው ማለፍ ከቻሉ አብረው የመጫወት ዕድል ሊኖራቸው እንደሚችልም ቢቢሲን ጠቅሶ ኢብኮ ዘግቧል፡፡

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 10/2011 ዓ.ም (አብመድ)

ሩሲያ ነፃ ምርጫ እንዲካሄድ ለመጠየቅ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ 1 ሺህ ተቃዋሚዎችን አሰረች

በሩሲያ በዋና ከተማዋ ሞስኮ  ነፃ ምርጫ እንዲካሄድ ለመጠየቅ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ 1 ሺህ ተቃዋሚዎች መታሰራቸው ተገለፀ፡፡ በሰላማዊ ሰልፉ ምክንያት ለእስር ከተዳረጉት መካከል የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እና ለሞስኮ ምክር ቤት ምርጫ በእጩነት የቀረቡ ግለሰቦች እንደሚገኙበት ነው የተነገረው፡፡

በመቶዎች የሚቆጠሩ አድማ በታኞች እና የብሄራዊ ዘብ አባላት  የሞስኮን መሀል መቆጣጠራቸው እና ተቃውሞ በሚደረግበት አካባቢ የሚገኝን መንገድ መዝጋታቸው ነው የተነገረው፡፡

ታዋቂ ፓለቲከኞች ሰልፉ ከመጀመሩ በፊት ለእስር እንደተዳረጉ የተነገረ ሲሆን 3 ሺህ 500 ሰዎች  በሰልፉ ላይ እንደነበሩና  ለእስር የተዳረጉት ሰዎች ቁጥርም ከፍ እያለ መምጣቱ ተጠቁሟል፡፡

የተቃውሞ ሰልፉ በሳምንት ውስጥ ሁለተኛው ጊዜ ሲሆን ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ 20 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ነፃ ምርጫ እንዲካሄድ ጠይቀዋል፡፡

ይህም በ2011- 12 ፕዚዳንት ቭላድሜር ፑቲን በድጋሜ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት መሆናቸውን ተከትሎ ከተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ በኋላ ትልቁ ነው ተብሏል፡፡

ምንጭ፡- አልጀዚራ – (ኤፍ ቢ ሲ)

አምስት ቀናትን በመፀዳጃ ቤት

አንዳንድ ጊዜ የምንሰማቸው አንዳንድ መረጃዎች ወይም ዜናዎች አስቂኝ፣ አስደንጋጭ፣ አስፈሪ፣ አዝናኝ ወይም ከዚህ በተለየ ሁኔታ አስተማሪም ሊሆኑ ይችላሉ። በተለይ ከፖለቲካው ወሬ ውጭ የምናገኛቸው አንዳንድ ዜናዎች በአብዛኛው አስገራሚ የሚሆኑባቸው አጋጣሚዎች ይስተዋላሉ።

ሰሞኑን ኦዲቲ ሴንትራል የተባለውና ለስላሳ ዜናዎችን በመዘገብ የሚታወቀው ድረገጽ ይዞ የወጣው ዜናም ትንሽ ለየት ያለ በመሆኑ ልናካፍላችሁ ወደድን።

መቼም በዚህ ዘመን በሰለጠኑ አገራት የሚገኙ አንዳንድ ሰዎች የሚፈጽሟቸው ተግባራት አስገራሚም አስደንጋጭም የሚሆኑባቸው ሁኔታዎችን አልፎ አልፎ አንመለከታለን። በተለይ ለየት ያለ ሥራ ሰርተው ስማቸውን በወርቃማው የጊነስ መዝገብ ለማስመዝገብ አስቂኝና አንዳንዴም የሞኝ ሥራ የመሰሉ ሥራዎችን ሰዎች ሲያከናውኑ እንሰማለን።

በርግጥ በአገራችንም በጊነስ መጽሐፍ ላይ ስማቸውን ያሰፈሩ ጥቂት ግለሰቦች እንዳሉ አይዘነጋም። ለምሳሌ የሳቁ ንጉሱ በላቸው ረጅም ሰዓት በመሳቅ ስሙን በጊነስ መዝገብ ማስፈር የቻለ ኢትዮጵያዊ ነው። እነኃይሌ ገብረሥላሴን የመሳሰሉት አንጋፋ አትሌቶቻችን ደግሞ በርካታ ሪከርዶችን በመሰባበር በላባቸው ስማቸውን በታላላቅ መዝገቦች ያሰፈሩ መሆናቸውን እናውቃለን።

ሰሞኑን የ48 ዓመቱ ጂሚ ዴ ፍሬኔ የተባለ ቤልጅየማዊ ያስመዘገበው የዓለም ሪኮርድ ግን ከዚህ ቀደም ከምንሰማው ለየት ያለና የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ነው። ጂሚ ሪከርዱን ያስመዘገበው ረጅም ሰዓት መፀዳጃ ቤት በመቀመጥ ነው። ኦዲቲ ድረገጽ እንደዘገበው ዴ ፍሬኔ ለአምስት ተከታታይ ቀናት መፀዳጃ ቤት በጎድጓዳው የመጸዳጃ ሳህን ላይ በመቀመጥ ነው ሪኮርዱን ያስመዘገበው።

ዴ ፍሬኔ ከዚህ ቀደም በዚህ ዘርፍ የሚደረግ ውድድር መኖሩን ምንም ግንዛቤ አልነበረውም። ሆኖም በዚህ ዘርፍ ለ100 ሰዓታት መፀዳጃ ቤት ውስጥ በመቀመጥ ሪከርድ ስላለው የቀድሞው የሪከርዱ ባለቤት በሰማበት ወቅት «እኔስ ይህንን እንዴት ማድረግ ያቅተኛል» በሚል መነሳሳቱን ገልጿል። በዚህም መሠረት 168 ሰዓት ወይም ለአንድ ሳምንት በመፀዳጃ ቤት በመቀመጥ የራሱን ሪከርድ ለመያዝ ወሰነ። ሆኖም ለ116 ሰዓት በመፀዳጃ ቤት ከተቀመጠ በኋላ ሰውነቱ ከዚህ በላይ መቀመጥ ስላልቻለ ከመፀዳጃ ቤት ቢወጣም ሪከርዱን ግን መጨበጥ ችሏል።

ዴ ፍሬኔ በውድድሩ ወቅት በእያዳንዱ አንድ ሰዓት ለአምስት ደቂቃ እረፍት የሚፈቀድለት ሲሆን ይህንንም እንደ እንቅልፍ ሰዓት ይጠቀምበት እንደነበር አስታውሷል። በዚህም መሠረት በአምስቱ ቀናት በአጠቃላይ ከሦስት ሰዓት ያልበለጠ የእረፍት ጊዜ ወይም የእንቅልፍ ሰዓት ብቻ እንደነበረው ለማወቅ ተችሏል። በዚህ ወቅት የጊነስ ሪከርዱን የሚዘግብ ሰው ባይገኝም ምስክሮችና የአካባቢው ሰዎች እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል።

አዲስ ዘመን ሀምሌ 15/2011

 ወርቁ ማሩ