Category Archives: ኢኮኖሚ

ኢኮኖሚ ነክ ዘገባዎች የሚቀርቡበት ገጽ

አበዳሪ ተቋማት ሳይካከተቱ ኢትዮጵያ የሃብቷን ግማሽ ከሃያ አገራት ተበድራለች!!

ኢትዮጵያ ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ባሻገር ከ50 አገራት ብድር መውሰዷን እና መንግሥትም 830 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ብድር እንዳለበት የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በ2011 ዓ.ም ኢትዮጵያ ካለባት ብድር መካከል መንግሥት 22 ቢሊዮን ብር የከፈለ ሲሆን፤ በ2012 ዓ.ም ደግሞ 25 ቢሊዮን ብር ብድር ለመክፈል አቅዷል። የገንዘብ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክ ተር አቶ ሃጂ ኢብሳ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያም ከፋይናንስ ተቋ ማት በተጨማሪ ከተለያዩ 50 ሀገራትም ብድር አለባት። ከአጠቃላዩ የመንግሥት ብድር 80 በመቶው በረጅም ጊዜ የሚከፈል እና አነስተኛ ወለድ የያዘ ነው።

በ2011 ዓ.ም አነስተኛ ወለድ ሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ያለው ብድር መንግሥት መውሰዱን የገለጹት አቶ ሃጂ፤ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ለረጅም ዓመታት ከማዕከላዊ ባንክ እና ከውጭ አገራት የወሰደው ብድር 830 ቢሊዮን 641 ሚሊዮን ብር መድረሱን አስረድተዋል። የተለያዩ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች በበኩ ላቸው 729 ቢሊዮን 907 ሚሊዮን ብር ብድር እንዳለባቸው ተናግረዋል።

እንደ ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ከሆነ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የብድር መጠኑን ከአጠቃላይ የአገሪቷ ሀብት ውስጥ 49 በመቶ እንደሚደርስ እና በዓለም አቀፍ ምዘና እንደ ኢትዮጵያ ላለ ሀገር እስከ 55 በመቶ የሚደርስ ብድር ሊፈቀድ ይችላል። ኢትዮጵያም አስጊ ሁኔታ ውስጥ ባትገኝም የብድር ጫናዋን ለመቀነስ የሚያስችል አካሄድ ላይ ትገኛለች።

በዚህም መሰረት በ2010 እና 2011 ዓ.ም ብቻ 39 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለብድር ተከፍሏል። በቀጣይም 25 ቢሊዮን ብር ለመክፈል ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። ሊከፈል የታሰበው ገንዘብ የአንዳንድ ክልሎችን በጀት የሚያክል መሆኑ ሲታሰብ መንግሥት የብድር መጠኑን ለመቀነስ የያዘው አቋም ከፍተኛ መሆኑን መገመት ያስችላል።

ለተጨማሪ ንባብ ሊንኩን ይክፈቱ https://www.press.et/Ama/?p=16666

(ኢ.ፕ.ድ)

ኢትዮጵያ የ81 ነጥብ 77 ቢሊዮን ብር ነዳጅ ሸምታለች

•የአገሪቱን የነዳጅ የማከማቸት አቅም በዕጥፍ የሚያሳድግ ሥራም ተጀምሯል

 አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ደርጅት በ2011 በጀት ዓመት የ81 ቢሊዮን 770 ሚሊዮን 533ሺ 205 ብር ነዳጅ መገዛቱን አስታወቀ። የአገሪቱን የነዳጅ የማከማቸት አቅም በዕጥፍ የሚያሳድግ የነዳጅ ማከማቻ ዲፖ ግንባታ ለማካሄድ ሥራ መጀመሩንም ገልጿል።

የድርጅቱ ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ አለማየሁ ፀጋዬ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ በበጀት ዓመቱ ቤንዚን፣ ነጭ ናፍጣ፣ የአውሮፕላን ነዳጅ፣ ቀላልና ከባድ ጥቁር ናፍጣ በድምሩ ሦስት ሚሊዮን 889ሺ 609 ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ተገዝቷል። አፈፃፀሙም ከድርጅቱ ዕቅድ 93 በመቶ ያህል ነው። ድርጅቱ የሰባት በመቶ የእቅድ አፈፃፀም ጉድለት ያሳየው የአገሪቱ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች አፈፃፀም በመቀዛቀዙ፣ የዋጋ ማስተካከያ እስኪደረግ ሰው ሰራሽ የስርጭት መዋዠቅ በመከሰቱና በክልሎች የነዳጅ እጥረት በመኖሩ ነው።

እንደ አቶ አለማየሁ ማብራሪያ፣ የነዳጅ ግዥው የተከናወነው ድርጅቱ ዓለም አቀፍ ጨረታ በማውጣትና መንግሥት ከሱዳንና ከኩዌት ጋር ባደረገው ስምምነት ነው። የነጭ ናፍጣ 50 በመቶ፣ የቤንዚን 75 በመቶ እንዲሁም የአውሮፕላን ነዳጅ ሙሉ ግዥ የተከናወነው መንግሥት ከሱዳንና ከኩዌት ጋር ባደረገው ስምምነት ሲሆን፤ ቀሪው ግዥ ደግሞ ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ የተከናወነ ነው።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ነዳጁን ከገዛ በኋላ ሱዳንና ጅቡቲ ላይ ለ29 የነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶች እንደሚያስረክብ የጠቆሙት አቶ አለማየሁ፣ አሁን በሥራ ላይ ካሉት ድርጅቶች በተጨማሪ በነዳጅ ንግድ ወደ ሥራ ለመግባት በሂደት ላይ ያሉ ድርጅቶች እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ የነዳጅ ዋጋ በየወሩ መጨረሻ በሚስተካከልበት ወቅት ነዳጅ ማደያዎች በሚፈለገው ደረጃ ባለመሸጣቸው አሽከርካሪዎች ረጃጅም ሰልፎች መጠበቃቸውና በክልሎች በሚገኙ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የነዳጅ ስርጭት በሚፈለገው ደረጃ አለመሆኑ ድርጅቱ በበጀት ዓመቱ የገጠሙት ተግዳሮቶች መሆናቸውን ባለሙያው ገልፀዋል።

‹‹መንግሥትና ድርጅቱ ችግሩን ለመፍታት የነዳጅ የዋጋ ማስተካካያው በማይታወቅ ጊዜ እንዲሆን አድርገዋል። በአንዳንድ የክልል አካባቢዎች ያለውን የነዳጅ ዕጥረት ለመቅረፍ አዋሽ ከሚገኘው የማሰራጫ ዲፖ በቶሎ በማድረስ የነዳጅ አቅርቦቱን ወጥ ለማድረግ እየተሰራ ነው። ለውጦች ቢኖሩም አሁን ነጋዴዎች የዋጋ ማስተካከያ ይኖራል ብለው በሚጠረጥሩበት ጊዜ ሰልፍ ይታያል። ችግሩን በቋሚነት ለመፍታት የፌዴራልና የክልል አካላትን የያዘ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ ተገብቷል›› ብለዋል።

‹‹አገሪቱ ችግር በሚፈጠርበት ወቅት መጠባበቂያ የሚሆን በ13 የነዳጅ ማከማቻ ዲፖዎች 369ሺ ሜትሪክ ቶን የማከማቸት አቅም አላት። ይህ መጠን ከአገሪቱ ዕድገት አንፃር ዝቀተኛ ነው›› ያሉት አቶ አለማየሁ፣ የአገሪቱን የነዳጅ የማከማቸት አቅም በእጥፍ ለማሳደግ በዱከም 300ሺ ሜትሪክ ቶን የሚይዝ የነዳጅ ማከማቻ ዲፖ ለመገንባት እየተሰራ እንደሆነ ገልፀዋል።

ባለሙያው እንዳሉት፣ ድርጅቱ መሬት ተቀብሎ ዓለም አቀፍ ኩባንያ በመቅጠር የዲዛይንና የአፈር ምርመራ ሥራ እያካሄደ ነው። የዲዛይኑና የአፈር ምርመራና ሌሎች ዝግጅቶች እስከ ጥቅምት 2012 ዓ.ም ይጠናቀቃሉ። ዓለም አቀፍ ጨረታ በማውጣትም ግንባታው በሦስት ዓመታት ይከናወናል።

አቶ አለማየሁ ጊዜያዊ ማሰራጫ የሚሆን 30ሺ ሜትሪክ ቶን የሚይዝ ዲፖ በአዋሽ እየተገነባ እንደሆነ፣ በድሬዳዋም ትልቅ የነዳጅ ማከማቻ ዲፖ ለመገንባት ድርጅቱ መሬት ጠይቆ እየጠበቀ እንደሚገኝና ነዳጁን ከወደቦች በባቡር ለማመላለስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

አዲስ ዘመን ነሀሴ 15/2011

 አጎናፍር ገዛኸኝ

የአማራ ባንክ አክሲዮን ማህበር የአክሲዮን ሽያጭ በይፋ ተጀምሯል

በምስረታ ሂደት ላይ ያለው የአማራ ባንክ አክሲዮን ማህበር የአክሲዮን ሽያጭ በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀምሯል። ባንኩ በዛሬው ዕለት በሸራተን ሆቴል ባካሄደው ስብሰባ እስካሁን በተከናወኑ ተግባራት፣ውሳኔ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችና እና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ተወያይቷል።

በውይይቱ ወቅትም የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መላኩ ፈንታ የባንኩ መመስረት በሀገር እና በክልል ያለውን የልማት ፍላጎት ለማስፋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክት መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም የሚመሰረተው ባንክ ኢንቨስትመንት እና የውጭ ምንዛሪ ተቀማጭ እንዲኖርና ዳያስፖራውንም ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ መሆኑን አንስተዋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የአደረጃጀት ኮሚቴው የአማራ ባንክ አክሲዮን ማህበር የሥነ ምግባር ደንብ ይፋ አድርጓል። በዚህ መሰረትም የአንድ አክሲዮን መሸጫ ዋጋ አንድ ሺህ ብር መሆኑ ተገልጿል። አንድ ሰው መግዛት የሚችለው ዝቅተኛ የዕጣ ብዛት 10 ሲሆን፥ ከፍተኛው ደግሞ 100 ሺህ እንደሆነም ተነግሯል።

በሃይማኖት እያሱ

(ኤፍ ቢ ሲ)

በአማራ ክልል በ2012 በጀት ዓመት ከ14 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል

በአማራ ክልል በ2012 በጀት ዓመት 14 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ብዙዓየሁ ቢያዝን አስታወቁ፡፡

በዚህም በበጀቱ ዓመቱ ከመደበኛ ገቢ 12 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር እና ከከተማ አገልግሎት ገቢ 2 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ሃላፊዋ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

ይህን እቅድ ለማሳካት ቢሮው የሀይል ቅጥር መፈፀሙን የተናገሩት ወይዘሮ ብዙዓየሁ ለስራው ማነቆ የነበሩ መመሪያዎችን ከፌዴራል መንግስት ጋር በመሆን መፍታት እንደተቻለ ገልፀዋል፡፡

እቅዱ አሁን ያለው ውጫዊና ውስጣዊ መልካም የማህበራዊ፣ ፓለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ግምት ውስጥ በማስገባት የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡

እንዲሁም በክልሉ የኢንቨስትመንት ፍሰት እየጨመረ መምጣቱን ለእቅዱ መሳካት መልካም አጋጣሚ መሆኑን ሃላፊዋ ጠቁመዋል፡፡በተጨማሪም የአመራሩና የማህበረሰቡ ቀና አስተሳሰብ፣ የመልማት ጥያቄ እና ልማትን ለማፋጠን ያለው የባለቤትነት ስሜት እቅዱን ለማሳከት ሌላኛው አቅም ነው ተብሏል፡፡

ቢሮው በ2011 በጀት ዓመት 12 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 11 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር መሰብሰብ እንደቻለም ተነግሯል፡፡

በናትናኤል ጥጋቡ – ኤፍ.ቢ.ሲ)

በምዕራብ እና ሰሜን ጎንደር ዞኖች አብዛኛዎች አካባቢዎች የቴሌኮምና የመብራት አገልግሎት ይካሄዳል

በፓርኩ አካባቢ፣  በምዕራብ እና ሰሜን ጎንደር ዞኖች አብዛኛዎች አካባቢዎች የቴሌኮምና የመብራት አገልግሎት እንደሚሟላ ተገልጿል፡፡

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በስሜን ተራራዎች ብሄራዊ ፓርክ ባለፈው የእሳት አደጋ በደረሰበት ቦታ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ የተመራ ልዑክ፣ የኢትዮ ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ ኤሌክሪክ ኃይል የሥራ ኃላፊዎች ችግኝ መትከላቸው ይታወሳል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎችም የተንቀሳቃሽ ስልክ ‹‹ኔትወርክ›› እና የመብራት አገልግሎት እንዲሟላላቸው ጠይቀዋል፡፡ የስልክ አገልግሎት በፓርኩ ብቻ ሳይሆን በተለይ አዲስ በተዋቀሩት ሁለቱ ዞኖች (ምዕራብና ሰሜን ጎንደር) አብዛኛዎቹ አካባቢዎች እንደሌለ ነዋሪዎቹ አንስተዋል፡፡

ለችግኝ ተከላ እና የኢንቨስትመንት አካባቢዎችን ለመጎብኘት በአካባቢው የተገኙት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይዎት ታምሩ በቀጣይ በሁለቱም ዞኖች አገልግሎቱ ተደራሽ እንዲሆን እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ በተለይም በምዕራብ ጎንደር ዞን እየተስተዋለ ያለውን የሱዳን ሲም ካርድ ሽያጭ ለማስቆም ጥረት እንደሚደረግ ነው የተናገሩት፡፡ ከጎብኝዎች የሚገኘውን ገቢ ከፍ ማድረግ እንዲቻል ቅርሶች ባሉበት አካባቢ የቴሌኮም አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰሩም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ ከመብራት ተደራሽነት ጋር ተያይዞ የተነሳው ጥያቄ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ በሁለቱም ዞኖች የመብራት መስመር ዝርጋታ ለማከናወን ውይይት እየተደረገ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡

ዘጋቢ፡- ደስታ ካሳ – ከደባርቅ – (አብመድ)

በ150 ሚሊዮን ዶላር የተከፈለ ካፒታል የዳያስፖራ ባንክ ለማቋቋም እንቅስቃሴ ተጀመረ

የዳያስፖራ ባንኩን የመመሥረት ሐሳብ ያመነጩትና እያደረጁ የሚገኙት በአሁኑ ወቅትም በምሥረታ ላይ የሚገኘው የ‹‹ኢትዮጵያ ዳያስፖራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር›› ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ጋሻው የትአለ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ባንኩ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ካፒታል አቅም እንዲኖር ታልሞ፣ በ150 ሚሊዮን ዶላር የተከፈለ ካፒታል እንዲመሠረት ለማስቻል እንቅስቃሴ እየተደረገበት ይገኛል፡፡

ባንኩን መመሥረት ስላስፈለገበት ምክንያት ሲያብራሩም፣ በኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሠለፍ የሚያስችሏትን የግብርናና የኢንዱስትሪ ዘርፎች በመደገፍ ኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት ለማስመዝገብ አስፈላጊውን ሀብት ለማመንጨት እንዲቻል በማሰብ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ አንዱ መንገድ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚመሠርቱትና ኢንቨስት የሚያደርጉበት ባንክ መመሥረት ጊዜው የሚጠይቀው ሆኖ እንዳገኙት የሚገልጹት አቶ ጋሻው፣ ከሦስት ሚሊዮን ያላነሱ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በውጭ እንደሚኖሩ በማጣቃስ ይህ ኃይል ለኢትዮጵያ ማበርከት የሚችለውን ወሳኝ አስተዋጽኦ በመገንዘብ የዳያስፖራ ባንክ ለማደራጀት መነሳታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ባንኩ እንዲመሠረት የታሰበው ከፍተኛ የገቢ ምንጭና መተዳደሪያ ባላቸው በውጭ ባለአክሲዮኖች እንደሆነ ገልጸው፣ በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ከሚያስፈልገው ካፒታል በላይ በማሰባሰብ ቢያንስ በ150 ሚሊዮን ዶላር የተከፈለ ካፒታል ሊመሠረት እንደሚችል አቶ ጋሻው ይናገራሉ፡፡

ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ጀምሮ ባንኩን ለማደራጀት እንቅስቃሴ ሲካሄድ መቆየቱንና በአሁኑ ወቅትም መንግሥት ነባሩን የባንክ ሥራ አዋጅን የሚያሻሽል ረቂቅ ሕግ ማዘጋጀቱና፣ በዚሁ ሕግም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አሊያም በአገር ውስጥ ከሚኖሩ ዜጎች ጋር ባንክ ማቋቋም እንደሚችሉ የሚፈቅዱ የማሻሻያ አንቀጾችን ያካተተበትን ሕግ ለማውጣት ጫፍ መድረሱ የባንኩን የምሥረታ ሒደት እንደሚያፋጥነው አቶ ጋሻው ይጠቅሳሉ፡፡

ባንኩ የአንድ ቢሊዮን ዶላር አቅም የመፍጠር ራዕይ ከመሰነቁም ባሻገር፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይሁንታ ባንክ ነክ ባልሆኑ ሥራዎች ውስጥም ለመሳተፍ የሚችልባቸው ዕቅዶች እንደተዘጋጁለት አቶ ጋሻው ጠቅሰዋል፡፡ ለአብነትም የባንክ ባለሙያዎችን በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ደረጃ የሚያሠለጥን የባንክ ልቀት ማዕከል የሚሆን ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ፣ አዋጭ በሆኑ የመካከኛና ረዥም ጊዜ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ውስጥ በተለይም በሪል ስቴትና መሰል ዘርፎች ተሳትፎ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡

መንግሥት የባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ የውጭ ባንኮች እንዳይገቡ ዝግ ማድረጉ ዘርፉ በሚጠበቅበት ደረጃ እንዳያድግ ከማድረጉም ባሻገር፣ አገሪቱ ለምትተገብራቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች ተገቢውን የገንዘብ አቅርቦት በአገር ውስጥ የማመንጨት ዕድሏንም እንደጎዳው በመግለጽ፣ ወደ ፊት የዓለም ባንክ አባል ለመሆን በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲህ ያሉ ክልከላዎች መነሳታቸው አይቀሬ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ እንደሚመጣ በማመን ከወዲሁ በኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባለቤትነት የሚመሠረት ባንክ ማቋቋሙ ትኩረት ማግኘቱን አብራርተዋል፡፡ መንግሥት የፋይናንስ ዘርፉን ለትልውደ ኢትዮጵያውያን ብቻም ሳይሆን ለውጭ ባንኮችም ክፍት ማድረግ እንዳለበት የሚያሳስቡት አቶ ጋሻው፣ የውጭ ምንዛሪ ተመኑንም ለገበያው መተው እንዳለበት ይመክራሉ፡፡

ምንም እንኳ እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች እየተበራከቱ ቢመጡም፣ የውጭ ምንዛሪ ተመኑን ለገበያው ክፍት ማድረጉ ጥቁር ገበያውን ሊያከስመው እንደሚችልና በኢኮኖሚው ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን የውጭ ምንዛሪም በመደበኛው መንገድ እንዲዘዋወር ለማድረግ እንደሚያግዝ የመታመኑን ያህል፣ አቅርቦቱ ከፍላጎቱ ጋር በማይጣጣምበት ወቅት በተለይም ለዘመናት የቆየው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር ባልተቀረፈበት ወቅት የውጭ ምንዛሪ ተመንን በገበያ ዋጋ እንዲመራ ማድረጉ ከፍተኛ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር በማድረግና የምንዛሪ ተመኑን ዋጋም ወደ ላይ በመስቀል ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድር ሥጋታቸውን የሚገልጹ ባለሙያዎች አሉ፡፡ አቶ ጋሻው ግን የምንዛሪ እጥረቱን ሊፈቱ የሚችሉ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩና ወደ ውጭ ምርቶችን የሚልኩ ፕሮጀክቶች ከተስፋፉ የምንዛሪ ተመን ችግር እንደሚቀረፍ ይገልጻሉ፡፡

ይህም ሆኖ መሠረታዊ ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የሚጠቅሱት የዳያስፖራ ባንክ፣ በአሁኑ ወቅት የሕግ ሰውነት እንዲያገኝ ስያሜውን በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከማስመዝገብና ዕውቅና ከማግኘት ጀምሮ በብሔራዊ ባንክ ሕግ መሠረት ባንኩን ለማደራጀት የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን አቶ ጋሻው አስታውቀዋል፡፡ 

ብርሃኑ ፈቃደ ሪፖርተር  

በበጀት ዓመቱ 198 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ተሰበሰበ

በ2011 በጀት ዓመት 198 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር መሰብሰብ እንደተቻለ የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አስታወቁ፡፡የገቢዎች ሚኒስቴር የ2011 በጀት አመት እቅድ አፈጻጸምንና የ2012 በጀት አመት እቅድን በማስመለከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በ2011 በጀት ዓመት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅዶለት ከነበረው 213 ቢሊየን ብር ውስጥ 198 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡

የተሰበሰበው ገቢ ምንም እንኳ ከእቅዱ አንፃር ዝቅ ቢልም ከ2010 በጀት ዓመት አንፃር ሲታይ የ22 ቢሊየን ብር ብልጫ ወይም የ12 በመቶ እድገት ማሳየቱን አስታውቀዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የተሰበሰበው ገቢ የሚኒስቴሩ ገቢ የመሰብሰብ አቅም ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱን ያሳየ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ሚኒስትሯ ከተሰበሰበውን ገቢ ውስጥ የሀገር ውስጥ ገቢ ድርሻ 120 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር (61 በመቶ)፣ ከቀረጥ የተሰበሰበው ገቢ ድርሻ ደግሞ 77 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር (39 በመቶ) እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ገቢው ከትክክለኛው የኢኮኖሚ እድገት ጋር የተመጣጠነ ወይም በቂ ነው የሚባል ባይሆንም የሀገር ውስጥ ገቢ ከፍተኛውን ድርሻ መያዙ ሀገሪቱ የራሷን ወጪ በራሷ ገቢ ለመሸፈን የምታደርገው ጥረት በትክክለኛው መንገድ እየተጓዘ መሆኑን ያሳየ ነውም ብለዋል።

በቀጣዩ በጀት ዓመት ሚኒስቴሩ በፓርላማ እንዲሰበሰብ የፀደቀለት የገቢ ዕቅድ 224 ቢሊየን ብር ሲሆን ይህን ዕቅድ በማስፋት 248 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ወደ ተግባር መገባቱ ተነግሯል፡፡

 (ኤፍ.ቢ.ሲ)

ከሆንግ ኮንግ የመጡ የባለሀብቶች ቡድን የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርከን ሙሉ በሙሉ ሊረከቡ ነው

ከሆንግ ኮንግ የመጡ የባለሀብቶች ቡድን አክሲዮን ማህበር የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርከን ሙሉ በሙሉ ሊረከቡ መሆኑ ተገለፀ።

የኢንዱስትሪ ፓርኩን የሚረከቡ የባለሀብቶች ቡድን በጨርቃ ጨርቅ እና በልብስ ስፌት ላይ የተሰማሩ መሆናቸውም ተገልጿል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የፕሮሞሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ይሄነው ዓለም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳስታወቁት፥ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ርክክብ በነገው እለት የሆንግ ኮንግ ባለሀብቶች፣ ከፍተኛ የፌደራል እና የክልል የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ይካሄዳል።

አቶ ይሄነው ዓለም አክለውም፥ እስካሁን ባለው ሂደትም በባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርከ ውስጥ የ8 ሼዶች ግንባታ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ገልፀዋል።

ለኢንዱስትሪ ፓርኩ ለሚያስፈልገው የኤሌክትሪክ ኃይል የመስመር ዝርጋታ እየተካሄደ መሆኑን እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎች ዝርጋታ መጠናቀቁንም አክለው ገልፀዋል።

በታሪክ አዱኛ –  (ኤፍ.ቢ.ሲ)

የዋጋ ግሽበቱን አለመቆጣጠር እና እያስከፈለ ያለው ዋጋ

የዋጋ ንረቱን ወደ ነጠላ አሃዝ ለማውረድ ጥረት ቢደረግም ሊሳካ እንዳልቻለ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል። የዋጋ ንረቱን ወደ ነጠላ አሃዝ ማውረድ ለምን አልተቻለም? ወደ ነጠላ አሃዝ ለማውረድ በቀጣይ ምን መከናወን አለበት? መቆጣጠር ካልተቻለስ ምን መዘዝ ሊያስከትል ይችላል?

በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ላይ ጥናት በመስራት የሚታወቁት በዲላ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር ዳዊት ሀዬሶ እንደሚገልፁት፤ መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የሄደበት መንገድ የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ አላስቻለውም። መቆ ጣጠር ያልቻለው በቅድሚያ የችግሩን መንስኤ ለይቶ መንስኤውን መሰረት ያደረገ ተገቢ ሥራ ባለመሰራቱ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ዋጋ ግሽበት እንዲከሰቱ የሚያደርጉ ሁለት ነገሮች ናቸው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ኢኮኖሚው መሸከም ከሚችለው በላይ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚ መርጨት አንደኛው መንስኤ ነው ይላሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት ከባንኮች መበደር ያለበት የገንዘብ መጠን በህግ ያልተቀመጠ በመሆኑ መንግሥት ያለ ከልካይ ከግልና ከብሄራዊ ባንኮች በመበደር ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው ይረጫል። በየጊዜ ወደ ገበያው እንዲገባ የሚደረገው ገንዘብ ለዋጋ ግሽበቱና ለኑሮ ውድነቱ የራሱን ሚና እያበረከተ ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።

የመንግሥት የበጀት ጉድለት ለዋጋ መናር ሁለተኛው መንስኤ ነው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ይህን ጉድለት ለማሟላት ከሚጠቀምባቸው ዘዴዎች አንዱ ግብር መጨመር ነው። ግብር ሲጨመር በተለይም ቀጥተኛ ያልሆነ ግብር ሲጨምር የአገልግሎትና ምርት ዋጋ እንዲጨምር ያደርጋል፤ ይህም የዋጋ ግሽበት እንዲከሰት ምክንያት ሆኖ ብዙ ነገር ያዛባል።

ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ገበያው ከመርጨትና ከበጀት ጉድለት ጋር ተያያዢነት ያለው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የመዋቅር ችግር ያለበት መሆኑ ለዋጋ ግሽበቱ የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ኢኮኖሚው ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ- ከኢንዱስትሪ ወደ አገልግሎት መሸጋገር የነበረበት ቢሆንም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከግብርና ወደ አገልግሎት እየተሸጋገረ ነው ይላሉ። ኢንዱስትሪው ማደግ ባለበት ልክ አላደገም ያሉት መምህሩ ይህም መሆኑ ለዋጋ ግሽበት መንስኤ መሆኑን አስታውቀዋል።

የሀገሪቷ ኢኮኖሚ በዋናነት ከውጪ በሚገቡ ምርቶች ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ምክንያት ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ የዋጋ ግሽበት መኖሩንም ረዳት ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከውጪ ሀገር የገባ የዋጋ ግሽበት አለ በሚለው የረዳት ፕሮፌሰር ዳዊትን ሀሳብም የሚቃወሙት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህሩ ዶክተር ታደለ ፈረደ ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ዋጋ ግሽበት ዋነኛው መንስኤ የሀገር ውስጥ ችግር ነው በማለት ይከራከራሉ። የዋጋ ግሽበቱ ከውጪ የመጣ ነው የሚለው ሀሳብ መንግሥት ዜጎችን ለማባበል የሚጠቀምበት ነው በማለት የፀና አቋም አላቸው።

“መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ጥረት አድርጓል” የሚለውን የረዳት ፕሮፌሰር ዳዊትን ሀሳብ ሲቃወሙ መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የሰራው ሥራ የለም በማለት ነው። “እንዲያውም እጁን አጣጥፎ የተቀመጠ ይመስላል” ሲሉ መንግሥት ላይ ጣታቸውን ቀስረዋል። የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር በቅድሚያ ምክንያቶችን ማወቅ አስፈላጊ ቢሆንም መንግሥት ምክንያቶቹን ባለማወቁ መፍትሄ ማምጣት አልቻለም ሲሉ ይወቅሳሉ።

መንግሥት ኢኮኖሚውን በቅጡ ማስተዳደር አለመቻሉ የብዙ ችግሮች መንስኤ ነው የሚሉት ዶክተር ታደለ በፊትም ኢኮኖሚው በአግባቡ እየተዳደረ አልነበረም፤ አሁንም እየተዳደረ አይደለም ብለዋል። በዚህም ምክንያት የዋጋ ግሽበቱ እያሻቀበ መሄዱን ያነሳሉ።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው የፊሲካል እና ሌሎች የፖሊሲ አማራጮችን በመጠቀም የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲረጋጋ ማድረግ የመንግሥት ዋናው ኃላፊነት ነው። በመሆኑ መንግሥት ባለፉት አሥር ወራት የተረጋጋ የዋጋ እድገት እንዲኖር ጥብቅ የፊሲካል ፖሊሲ ተግባራዊ አድርጓል በማለት የዶክተር ታደለን ሀሳብ ይቃወማሉ።

‹‹የመንግሥት ወጪ በገቢው እንዲሸፈን፤ በእቅድ ከተያዘው በላይ እንዳይንር፣ የውጭ ብድር ጫናን የሚያረግቡ ተግባራትን አከናውኗል። የወጪ ጫና የሚፈጥሩ አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንዳይኖሩና የተጀመሩትም የሚጠናቀቁበት መንገድ በማመቻቸት የመንግሥት ወጪ በዋጋ ንረት ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የሚያስችል ሥራ ሰርቷል›› ሲሉ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

እንደ አቶ አህመድ ገለጻ አገራዊ አጠቃላይ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ 12.6 በመቶ ሆኗል። የዋጋ ንረቱን በአንድ አሃዝ እንዲገደብ ለማድረግ ያልተቻለ መሆኑን አስታውሰው በዝቅተኛው የሁለት አሀዝ እንዲረጋጋ ለማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።

ለዋጋ ግሽበት ምክንያት የሚሆኑ ለረጅም ዓመታት የቆዩ ከኢኮኖሚው መዋቅራዊ ችግሮች እስከ ሰው ሰራሽ መንስኤዎች አሁንም ቀጥሏል የሚሉት ዶክተር ታደለ፤ የግብርና ምርትና ምርታማነት በሚፈለገው ልክ ባለማደጉ የግብርና ምርቶች አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለው ክፍተት እየሰፋ መምጣቱም በተለይም የግብርና ምርቶች ዋጋ እንዲንር አንዱ መንስኤ ነው ይላሉ።

እንደ ዶክተር ታደለ ማብራሪያ በሀገሪቱ ውስጥ ባለው የኤሌክትሪክ ሀይል መቆራረጥ ምክንያት ፋብሪካዎች ማምረት ካለባቸው በታች እያመረቱ ናቸው። አገልግሎት ሰጪዎችም አገልግሎት ለመስጠት ተቸግረዋል። በዚህም ምክንያት የሰራተኛውን ወጪ ለመሸፈን የዕቃና የአገልግሎት የመሸጫ ዋጋ ጨምረዋል። አንዳንድ ድርጅቶች የራሳቸውን ጄኔሬተር እየገዙ ለማምረትና አገልግሎት ለማቅረብ እየሞከሩ ናቸው። ይህ ደግሞ ተጨማሪ ወጪ እያስወጣቸው በመሆኑ የዋጋ ንረቱን እያባባሰው መጥቷል ብለዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር ዳዊት እንደሚሉት፤ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ገንዘብን መሰረት ያደረገ ፖሊሲ መከተል መፍትሄ አይሆንም። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከ1970ዎቹ ጀምሮ ሲከተል የቆየውን የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ መፈተሸ አለበት። ይህን ያረጀ የፖሊሲ ማዕቀፍ በመቀየር የዋጋ ግሽበትን መሰረት ያደረገ ሞኒተሪ ፖሊሲ መከተል ይገባል። ግሽበትን መሰረት ያደረገ ፖሊሲ በመከተል በርካታ ሀገራት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ችለዋል። ኢትዮጵያም ይህንኑ ልምድ መቅሰም አለባት።

የዋጋ ግሽበቱን እንዲቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው ብሄራዊ ባንክ በብቃት የገበያ ዋጋ መቆጣጠር እንዲችል ሁለት ነገሮች ሊኖሩት ይገባል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ዳዊት፤ ገልተኛነቱን ማረጋገጥ አንዱ ሲሆን የአስተዳደራዊና የፖሊሲ ምርጫ ነጻነት እንዲኖረው ማድረግ ሁለተኛው መፍትሄ ነው ሲሉ አቅርበዋል።

እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ፤ የሀገሪቱን የንግድ ህግን ማስተካከልም አስፈላጊ ነው። የንግድ ስርዓቱ ውስጥ ፍትሃዊነትና ውድድር እንዲኖር በዘርፉ ያሉ ችግሮችን መቅረፍ ያስፈልጋል። ከሀገሪቱ የንግድ ዘርፍ 36 በመቶ የሚሆነው በኢ- መደበኛ ዘርፍ የተያዘ ነው። ይህ ኢ-መደበኛ ንግድ ወደ መደበኛ የሚመጣበትን ሁኔታ ማመቻቸትም የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር የራሱ እገዛ ይኖረዋል።

ዶክተር ታደለ ፈረደ በበኩላቸው፤ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ መፍትሄዎች ላይ በእቅድ መስራት ያስፈልጋል ይላሉ። በአጭር ጊዜ ገበያውን ለማረጋጋት መንግሥት እንደለመደው ከውጪ ሀገራት ምርት እያስገበ ገበያውን ለማረጋጋት መስራት አለበት ይላሉ።

የግብርና ምርትን በዓይነትና በጥራት የማቅረብ ሥራ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ግብ አስቀምጦ መስራትም ትኩረት ሊደረግበት ይገባል የሚሉት ዶክተር ታደለ፤ ከውጪ የሚገቡ የፋብሪካም ሆነ የግብርና ምርቶች በሀገር ውስጥ ለማምረት ጥረት መደረግ አለበት። ገንዘብ ያለው ሁሉ አስመጪ ከሚሆን ይልቅ ሀገር ውስጥ አምራች እንዲሆን በትኩረት ሊሰራ ይገባል ይላሉ።

ረዳት ፕሮፌሰር ዳዊት ሀዬሶ በበኩላቸው፤ የዋጋ ግሽበቱን መቆጣጠር ካልተቻለ የውጪ የሚመጡ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ይቀንሳል። ዜጎች እንዳይቆጥቡ ያደርጋል። ቁጠባ ከሌለ ደግሞ የወደፊት የሀገር ኢኮኖሚ እድገት እንዲገታ ያደርጋል። በሀገር ውስጥ ያሉ ባለሃብቶችና ኢንቨስተሮች መዋዕለ ንዋያቸውን በሀገር ውስጥ ከማፍሰስና ከመቆጠብ ይልቅ በውጪ ባንኮች መቆጠብን ይመርጣሉ። ባለሃብቶች ሀገር ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን የማያፈሱ ከሆነ ሥራ አጥነት ይበራከታል።

በአጠቃላይ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር ካልተቻለ ኢኮኖሚውም እድገቱን በጣም ይቀንሳል። ያ ማለት ከፍተኛ የሆነ ሥራ አጥነት፤ ከፍተኛ ከሆነ የኑሮ ውድነት ጋር ሲመጣ ዜጎች ትናንትና በአነስተኛ ወጪ ይኖሩ የነበሩትን ኑሮ ዛሬ እንዳይኖሩ ያደርጋቸዋል። ይህ ደግሞ ወደ ፖለቲካ ቀውስ የሚወስድበት ሁኔታም ሊፈጠር ስለሚችል በትኩረት መስራት እንደሚገባ ምሁራኖቹ አስገንዝበዋል።

አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2011

መላኩ ኤሮሴ

የቻይናው ሁጂያን ግሩፕ ፋብሪካዎቹን በጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲተከል ስምምነት ተፈረመ

የቻይናው ሁጂያን ግሩፕ በጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች የማምረቻ ፋብሪካዎቹን እንዲተክል የሚያስችል ስምምነት ዛሬ ተፈረመ።

በዛሬው እለት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አማካኝነት የኢንድስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እና ሁጂያን ግሩፕ መካከል ነው ስምምነቱ የተፈረመው።

ስምምነቱን የኢንዱሰትሪ ፓርኮች ልማክ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ሌሊሴ ነሜ እና የሁጂያን ግሩፕ ፕሬዚዳንት ዣንግ ሁዋሮንግ ናቸው የተፈራረሙት።

በዚህ ስምምነት መሰረትም ኩባንያው 100 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በሚሆን ካፒታል በጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ፋብሪካዎቹን ያለማል። ኩባንያው በፓርኩ ውስጥ የጫማ እና የግንባታ እቃዎች ማምረቻዎችን እንዲሁም፥ የቡና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ይተክላል።

በተለይም የቡና ማቀነባበሪያ ፋብሪካው 40 ሄክታር በሚሆን መሬት ላይ እንደሚያርፍ ነው በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የተመለከተው። ፋብሪካዎቹ ወደ ስራ ሲገቡም ከ12 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድልን ይፈጥራል ተብሏል።

1 ነጥብ 5 ሚሊየን ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ61 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ተገንብቶ ባለፈው ህዳር ወር ላይ ነበር የተመረቀው።

(ኤፍ.ቢ.ሲ)