Category Archives: ህግ

ይህ ዓምድ ህግ ነክ ጉዳዮች ለግንዛቤና ለመረጃ ይረዳ ዘንድ የሚስተናገድበት ነው። ዓምዱ ቀደም ያሉ ብይኖችና የህግ አግባቦችን ያካትታል።

ለሕገ መንግሥት ሕልውና የሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ሚና

ሌላው ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ እያስፈለገ ነገር ግን ሳይደረግ የተፈጸመውንም ቢያንስ ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ ለእዚህ ጥሩ ማሳያው የድሬዳዋ አስተዳደር አፈጣጠር ነው፡፡ ድሬዳዋን ፖለቲካዊ ጭንቀት የወለዳት መስተዳድር ናት ማለት ይቻላል፡፡ አግጥጦ መጥቶ የነበረውን ችግር ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል ድሬዳዋ ትፈጠር ቢባል ኖሮ ምናልባት የኦሮሚያም ይሁን የኢትዮጵያ ሶማሊያ ክልል ምክር ቤቶች በዚያን ወቅት ሊስማሙ ይችል ነበር ብሎ ማሰብ ከባድ ነበር፡፡ VIA- Reporter

Continue reading ለሕገ መንግሥት ሕልውና የሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ሚና

ከፍተኛ የስንዴ ዱቄት እጥረት በሀገሪቱ ላይ እንዲከሰት አድርገዋል በተባሉ ሀላፊዎች ላይ ክስ ተመሰረተ

ዋዜማ ራዲዮ– ለገበያ ማረጋግያ አላማ የሚውል 400ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዥን በተመለከተ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 10 የቀድሞ የመንግስት ሀላፊዎች በቁጥጥር ስር ውለው ለምርመራ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡

የጊዜ ቀጠሮው ባበቃበት ሚያዝያ 24 ቀን 2011 ዓም የፌደራል ፖሊስ ሙስና ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክቶሬት ምርመራውን ማጠናቀቁን ተከትሎ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ መዝገቡን ተቀብሏል፡፡በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎትም የክስ ፋይል ከፍቶ ከሰዓት በኋላ አስሩን ተከሳሾች አቅርቧል፡፡

የመንግስት ግዥ እና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ይገዙ ዳባን ጨምሮ አቶ ተስፋዬ ብርሀኑ፣ አቶ ሰሎሞን በትረ፣ አቶ ሶሎሞን አይኒማዓር፣ አቶ ዮሴፍ ራፊሶ፣አቶ ተክለብርሀን ገ/መስቀል፣ አቶ ትሩፋት ነጋሽ፣ አቶ ዘሪሁን ስለሺ እና አቶ ጆንሴ ገደፋ የተባሉ የኤጀንሲው የቀድሞ ሀላፊዎችን እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን የቀድሞ ዋና ስራ አስፈፃሚ የነበሩት አቶ መንግስቱ ከበደ የተባሉት ናቸው የተካተቱት፡፡

የአቃ ህግ ክስ ዝርዝርም ወንጀሉ በ1996 ዓ የወጣውን የኢፌድሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 32(1)(ሀ) እና በ2007 ዓም የወጣውን የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 13(1)(ሐ) እና 2 ላይ ያሉትን ድንጋጌዎችን በመተላለፍ የተደረገ ነው ሲል ማብራርያውን ጀምሯል፡፡

ክሱ የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው ከ2010 እስከ 2011 ባለው ጊዜ መሆኑን የሚገልፅ ሲሆን ለገበያ ማረጋግያ እንዲሆን አለም አቀፍ የግዥ ጨረታ የወጣለት የ400ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ እንደነበር ይጠቅሳል፡፡

ለገበያ ማረጋግያነት እንዲሆን በኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽ እንዲገዛ የተጠየቀው ይህ ስንዴ ታድያ መጀመርያ ጥቅምት 19 በወጣው አለም አቀፍ ግልፅ ጨረታ ሻኪል ኤንድ ካምፓኒ የተባለ የፓኪስታን ኩባንያ 96.4 ሚሊየን ዶላር የሆነ ነዝቅተኛ ዋጋ በማስገባት አሸናፊ ሆኖ ነበር፡፡

ሁለተኛ የወጣው ፕሮሚሲንግ ኢንተርናሽናል ደግሞ ከእዚህ በሁለት ሚሊየን ዶላር የበለጠ ዋጋ ነበር ያስገባው፡፡ እናም አሸናፊው የፓኪስታን ካምፓኒ ስንዴውን ለማቅረብ ታህሳስ ላይ ውል ቢዋዋልም በ15 ቀን ውስጥ ግን የውል ማስከበርያ የሆነውን የባንክ ጋራንት ማስገባት አልቻለም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፓኪስታን ባንኮች ጋር ግንኙነት የለኝም በማለቱ ነበር፡፡ ሆኖም አቅራቢው ድርጅት ከሌላ ሶስተኛ ሀገር ባንክ ዋስትናውን ለማምጣት ተጨማሪ ቀን እንዲሰጠው ቀደም ብሎ የጠየቀ ቢሆንም ተከሳሾቹ በግዥ መመርያው መሰረት ተጨማሪ ቀን መስጠት የሚችሉ እንደሆነ እያወቁ ውሉን አቋርጠዋል መባሉን ክሱ ያስረዳል፡፡

ይህ ተግባር ከፍተኛ የስንዴ እረት አስከትሎ በመንግስት እና በህዝብ ላይ ጉዳት አድርሶ እያለ ወረሀ ጥር ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ጨረታ ወጥቷል፡፡ ይህ ጨረታ ግን በጨረታ ኮሚቴዎቹ መካከል የተፈጠረ የሀሳብ ልዩነትን ተከትሎ የጠራ የውሳኔ ሀሳብ አልቀረበም በሚል 110.7 ሚሊየን የዶላር የሆነ ዝቅተኛ ዋጋ ቢቀርብበትም ሚያዝያ ላይ እንዲሰረዝ ሆኗል፡፡

ይህን ተከትሎም በሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የስንዴ እጥረት የተከሰተ ሲሆን የስነዴ ግዥ በአፋጣኝ እንዲፈፀምለት የአደጋ ስጋት እና አመራር ኮሚሽን መጠየቁን ተከትሎ ከግዥ መመርያ ውጪ ፕሮሚሲንግ የተባለውን ድርጅት ለመጥቀም ሲባል ያለ ጨረታ 200ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ እንዲያስገባ የ1.6 ቢልዮን ብር ውል ፈፅዋል ይላል የአቃቤ ህግ ክስ፡፡

ይሁን እንጂ የውል ማስከበርያ ከቀደመው በተለየ ለሁለት ወራት ሳያስገባ ቀርቷል ፡፡ ቆይቶም የውጪ ምንዛሬ ብክነትን ለማዳን ያስቸል ዘንድ ማንኛውም የመንግስት ግዥ በኢትዮጵያ ንግድ መርከብ አገልግሎት በኩል እንዲሆን የሚያዘው የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት መመርያ አያዋጣኝም በማለት ስንዴውን ሳያቀርብ ውሉን ሰርዞታል፡፡
እናም ለዚህ ተግባሩ በሌላ ጨረታ እንዳይሳተፍ መታገድ ሲገባው ነሀሴ ወር ላይ ለ4ኛ ጊዜ በወጣው ጨረታ ፕሮሚሲንግ ኢንተርናሽናል በግል መርከብ 200ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴውን ጭኖ እንዲያስመጣ አስደርገዋል ሲል አቃቤ ህግ የወንጀል ድርጊቱን ዘርዝሯል፡፡

ይህን ተከትሎም ታድያ 5.8 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል ብሏል፡፡ በተጨማሪም ፕሮሚሲንግ ኢንተርናሽናል የተባለውን ድርጅት ከ101 ሚሊየን ብር በላይ እንዲጠቀም አድርገዋልም ብሏል፡፡

8 ገፆች ባሉት ክሱ ላይ አቃቤ ህግ በግልፅ የወንጀል ድርጊቶቹን ከብራራ በኋላ በተሰረዙ ጨረታዎች ሲከፈሉ የቆዩ የልዩነት ገንዘቦች እና የመርከብ ወጪውን ጨምሮ ከፕሮሚሲንግ ኢንተርናሽናል ጋር በመመሳጠር በመንግስት ላይ 24.9 ሚልዮን ዶላር ወይንም 688 ሚልዮን ብር ጉዳት አድረሰዋል ብሏል፡፡

በዚህ ላይም ከፍተኛ የሆነ የስንዴ ፣የዱቄትና የዳቦ እጥረት እንዲሁም የዋካ መናር እንዲከሰት በማድረግ በዋና ወንጀል አድራጊነት የመንግስትን ስራ በማያመች አኳኋን መርተዋል ብሏል፡፡ ለዚህም 19 የሚሆኑ ሰው ምስክሮች ዝርዝር እና 43 ገደማ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል፡፡

ከሶስት ተከሳሾች በቀር ሌሎቹ ጉዳያቸውን ለመከራከር መንግስት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው በመናገር ለዚህም የሚሆን በቂ ሀብት የሌላቸው ስለመሆኑ በመሀላ አረጋግጠዋል፡፡ ችሎቱ ተከላካይ ጠበቃ እንዲቆም የመደበላቸው ሲሆን በቀረበው ክስ ላይ ግንቦት 6 እንዲቀርቡ ሲል ቀጠሮ ይዟል፡፡

የፌደራል ፖሊስ በሶማሌ ክልል ሁከት የተሳተፉ ተከሳሾችን መያዝ እንዳልቻለ ገለፀ- የክልሉ ፖሊስ እንዲያግዘው ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ጠይቋል፡፡

ዋዜማ ራዲዮ– የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ሚያዝያ 24 ቀን 2011 ዓም የተለያዩ መዝገቦችን ለማስተናገድ ተሰይሞ ነበር፡፡
አስቀድሞ ባየው የሶማሌ ክልል የቀድሞ ባለስልጣናት ጉዳይም የፌደራል ፖሊስ አሁን በቁጥጥር ስር ከዋሉት 6 ተከሳሾች ባለፈ 2 ተፈላጊዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ አቅርቧል፡፡

በክልሉ በተለያዩ ስብሰባዎች እና በፌስቡክ ድህረ ገፅ ቅስቀሳ በማድረግ እና በጦር መሳርያ በመታገዝ ከሀምሌ 26-30 2010 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ለጠፋው የ59 ሰዎች ህይወት በርካታ አብያተ ክርስትያ መቃጠል እና ለበርካታ ሴት ልጆች መደፈር ተጠያቂ ናቸው የተባሉ የክልሉ የቀድሞ ከፍተኛ ሀላፊዎች እና ሄጎ የተባለ ቡድን አባላት ፤ በጥቅሉ 47 ሰዎች ላይ ክስ ተመስርቶ ነበር፡፡

ሆኖም እስካሁን የክልሉን የቀድሞ ርዕሰ መስተዳደር አብዲ መሀሙድ ኡመር እና ሌሎች 3 የቀድሞ አመራሮች እንዲሁም 2 የሄጎ አባል ናቸው የተባሉ ወጣቶች ብቻ ናቸው በቁጥጥር ስር የዋሉት፡፡

ችሎቱ የተሰየመው እስካሁን ባልተያዙት ላይ ፖሊስ የደረሰበትን ሪፖርት ለመመልከት ነበር፡፡ በዚህም መሰረት ፖሊስ ሁለት ተጨማሪ ሰዎችን መያዙን እነሱም አባስ ሞሀመድ እና ኮሚሽነር አብዱላሂ አህመድ የተባሉ እንደሆኑ ገልፆ ችሎት ፊት አቅቧቸዋል፡፡
እናም በወንጀለኛ መቅጫ የስነስርዓት ህጉ አንቀፅ 128 መሰረት ቀዳሚው የፍርድ ቤት ተግባር የተከሳሾችን ማንነት ማረጋገጥ ነውና ስለማንነታቸው ተጠይቀው ተረጋግጧል፡፡
የተከሰሱበት ጉዳይ ከመነበቡ በፊት ግን ጠበቃ እንዲቆምላቸው የጠየቁ ሲሆን ሁለቱም ተከሳሾች አቅም የሌላቸው መሆኑን እና መንግስት እንዲያቆምላቸው እንደሚፈልጉ ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ አቅም የሌላቸው ስለመሆኑ በመሀላ እንዲያረጋግጡ ሲጠየቁ አባስ ሞሀመድ የተባሉት ተከሳሽ አልምልም በራሴ ጠበቃ ቀጥሬ አቆማለው ሲሉ ሀሳባቸውን ቀይረዋል፡፡ በዚህም መሰረት ለኮሚሽነር አብዱላሂ ብቻ የመንግስት ተከላካላይ ጠበቃ እንዲቆምላቸው ታዟል፡፡

በሌላ በኩል እስካሁን ስላልተያዙት 39 ተከሳሾች አቃቤ ህግ የፖሊስን ሪፖርት ያብራራ ሲሆን በብዛት የስም መመሳሰል ስላለ ተከሳሾቹን እስካሁን ለይቶ መያዝ እንዳልቻለ ተገልፀዋል፡፡

ለዚህም ታድያ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንን እንዲተባበረው ቢጠይቅም ከበላይ አመራሮች ጋር ሳንነጋገር አይሆንም በማለት ለመተባበር ፍቃደኛ እንዳልሆነለት አብራርቷል፡፡
የክልሉ ፖሊስ ተፈላጊዎችን በመያዝ ረገድ እንዲያግዘው ትዕዛዝ እንዲሰጥለት የፌደራል ፖሊስ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

በቁጥጥር ሰር ያሉ ተከሳሾች ጠበቆች በበኩላቸው ፖሊስ ከዚህ ቀደም ማግኘት አልቻልኩም ማለቱን አስታውሰው በየጊዜው በቁጥጥር ስር ያልዋሉትን ለመያዝ እየተባለ የሚሰጠው ቀጠሮ የባለጉዳዮቻቸውን የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት እየተጋፋ መሆኑን ለችሎቱ ገልፀዋል፡፡

የፌደራል ፖሊስ በማንኛውም ቦታ በወንጀል የተፈለገን ግለሰብ የማምጣት ስልጣን እንዳለው በመግለፀም ምክንያቱ ተቀባይነት እንዳያገኝ የጠየቁ ሲሆን ያ ካልሆነ መዝገባችን ተለይቶ ቀጠሮ ይያዝበት ሲሉም ተቃውመዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ችሎቱ ታድያ የፌደራል ፖሊስን ጥያቄ በመቀበል የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽ በወንጀል የሚፈለጉትን ግለሰቦች አፈላልጎ በመያዝ ረገድ አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግ ጥዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

እናም ፖሊስ ተፈላጊዎቹ ካሉ እንዲያቀርብ ከሌሉም ደግሞ በአድራሻቸው ስላለመገኘታቸው ማረጋገጫ እንዲያመጣ የታዘዘ ሲሆን ለዚህ ቀጠሮም ሰኔ 3 2011 ዓም ይዟል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]

ኢትዮጵያ በአሜሪካ በሁለት ሰዎች ግድያ ተጠርጥሮ የሚፈለገውን አቶ ዮሃንስ ነሲቡን ለዋሽንግተን አሳልፋ ልትሰጥ ነው

ኢትዮጵያ በዩናይትድ ስቴትስ ቨርጂኒያ ግዛት በሁለት ኢትዮጵያውያን ላይ በተፈፀመ ግድያ ተጠርጥሮ በሀገሪቱ ፖሊስ የሚፈለገውን በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ደግሞ አሜሪካዊ የሆነውን አቶ ዮሃንስ ነሲቡ በዛብህን ለአሜሪካ መንግስት አሳልፋ ለመስጠት ወሰነች።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳስታወቀው፥ የአሜሪካ የፍትህ ቢሮ የወንጀል ጉዳዮች ዲቪዥን በአሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት በሁለት ሰዎች ሞት እና በሁለት የጦር መሳሪያን ያለአግባብ በመጠቀም ወንጀሎች ግለሰቡ መጠርጠሩን እና አሁን ላይ በኢትዮጵያ እንደሚገኝ በመግለፅ ተላልፎ እንዲሰጥ ጠይቋል።

በኢትዮጵያ በኩል ጥያቄውን ለመቀበል የሚያስችል ማረጋገጫ ከአሜሪካ መንግስት በኩል እንዲሰጥ መደረጉን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህዝብ ግኑኝነት ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት የተከናወነው የወንጀል ምርመራ ውጤትን በሰነድ በማያያዝ አሜሪካ ማቅረቧን ነው ያመለከቱት።

በሰነዱም ጠቅላይ አቃቤ ህግ በቨርጂኒያ ግዛት ፌርፋክስ ካውንቲ ፍርድ ቤት ግለሰቡ መከሰሱን እና በፈረንጆቹ መጋቢት 23 ቀን 2017 የእስር ትእዛዝ እንደወጣበት አረጋግጧል።

በአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀፅ 6 ንዑስ ቁጥር 12 በወንጀል ጉዳዮች ላይ ዓለም አቀፍ ግኑኝነት ትብብር እንዲያደርግ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሰረት ተጠርጣሪው ለአሜሪካ ተላልፎ እንዲሰጥ መጋቢት 25 ቀን 2011 ዓመተ ምህረት መወሰኑን አቶ ዝናቡ አስታውቀዋል።

ተላልፎ እንዲሰጥ ሲወሰንም  ተፈላጊው ግለሰብ ዜግነቱ አሜሪካዊ መሆኑ እና ግድያ የተፈፀመባቸው ሁለቱ ሰዎች ኢትዮጵያውያን  መሆናቸውን ከግንዛቤ በማስገባት መሆኑ ተመልክቷል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ የወንጀል ህግ መሰረት የተፈፀመውን ወንጀል የመዳኘት ስልጣን በዋናነት የኢትዮጵያ አለመሆኑ እና ግለሰቡ ተላልፎ ከተሰጠ በኋላ የሰብዓዊ መብቱ እንደሚጠበቅ ከአሜሪካ በኩል ማረጋገጫ መሰጠቱ ከግንዛቤ ተወስዷል።

እንዲሁም በኢትዮጵያ በኩል ተመሳሳይ የትብብር ጥያቄ ለአሜሪካ ከቀረበ የጉዳዩን ይዘት በማየት ትብብር ከዋሽንግተን በኩል እንደሚደረግ ማረጋገጫ በመሰጠቱም ውሳኔው ተላልፏል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሁለቱ ሀገራት መካከል በፍትህ ዘርፍ እየተደረገ ያለው ግኑኝነት እና የትብብር መንፈስ አወንታዊ መሆኑ ከግምት ውስጥ ገብቶ ግለሰቡ ተላልፎ እንዲሰጥ መወሰኑን አቶ ዝናቡ አስረድትዋል።

በአሁኑ ወቅት ተጠርጣሪው ግለሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን፥ አሳልፎ ለመስጠት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች እየተሟሉ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።

FBC

በ9 ወራት ከ182 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በቁጥጥር ስር መዋሉን የገቢዎች ሚኒስቴር ገለጸ!

ባለፉት 9 ወራት ከ182 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋዎር በቁጥጥር ስር መዋሉን የገቢዎች ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ባለፉት 9 ወራት 182 ሚሊየን 741ሺህ 382 ብር ዋጋ ያላቸው የተለያዩ ሀገራት ገንዘብ ኖቶች በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ በተለያዩ የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ተይዘዋል፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመላክተው በህገወጥ መንገድ ሲዘዋዎር ከተያዘው ገንዘብ ኖቶች መካከል 8ሚሊየን318ሺህ 543 ብር ወደ ሀገር ሲገባ የተያዘ ሲሆን÷ 174ሚሊየን 370ሺህ 819 ብር ዋጋ ያላቸውው የተለያዩ የውጭ ሀገራት ገንዘብ ኖቶች ደግሞ ከሀገር ሊወጡ ሲሉ የተያዙ ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ኤርፖርት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት 97 ሚሊየን 339ሺህ 421 ብር ዋጋ ያላቸው የተለያዩ የገንዘብ ኖቶችን በቁጥጥር ስር በማዋል ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዝ የጅግጅጋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት 74ሚሊየን 69ሺህ 892 ብር በቁጥጥር ስር በማዋል የሁለተኛ ደረጃን ይዟል፡፡

የአሜሪካን ዶላር፣ ብር፣ የጅቡቲ ፍራንክ፣ የሱዳን ፓውንድ፣ የሶማሌ ላንድ ሽልንግ አረብ ኤምሬትስ ድርሃም፣ የሳውዲ ሪያል፣ የካናዳ ዶላር፣ የናይጄሪያ ናይራና የሌሎች ሀገራት ገንዘብ ኖቶች በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋዎሩ የተያዙ መሆኑን ከሚኒሰቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

FBC

በደቡብ ፖሊስና በወላይታ ድቻ ጨዋታ ላይ ግጭት በመፍጠር የተጠረጠሩ 37 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በደቡብ ፖሊስና በወላይታ ድቻ ጨዋታ ላይ ግጭት በመፍጠር የተጠረጠሩ 37 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ባለፈው ቅዳሜ በደቡብ ፖሊስና በወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለቦች መካከል ሊካሄድ በነበረው ጨዋታ ላይ ግጭት እንዲፈጠር በማነሳሳት የተጠረጠሩ 37 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊ አቶ ደስታ ዳንጊሶ ጉዳዩን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል።

ሃላፊው በመግለጫቸው የራሳቸውን ፖለቲካዊ አጀንዳ የሚያራምዱ አካላት በሸረቡት ሴራ በዕለቱ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

በተፈጠረው ግጭትም አንዲት ሴት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባት ሆስፒታል እንደምትገኝና 17 ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል ጉዳት መድረሱን ገልፀዋል።

ከዚህ ባለፈም የ10 መኪናዎች መስታወት ሙሉ በሙሉ የተሰባበረ ሲሆን ፥ አንድ ግሮሰሪ ላይም ዘረፋ ተፈጽሟል ነው ያሉት።

ግጭቱ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎችና የፀጥታ አካላት በመቀናጀት ባደረጉት ርብርብ በቁጥጥር ስር ሊውል መቻሉንም አንስተዋል።

ስለሆነም መገናኛ ብዙሃን የተከሰተውን ችግር ከማጋነንና የተሳሳተ መረጃ ከማሰራጨት እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንም ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ በደቡብ ፖሊስና በወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለቦች መካከል የሚደረገውን ጨዋታ ጨምሮ ሀዋሳ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ ላልተወሰነ ጊዜ ማራዘሙ ታውቋል።

ቢኒያም ሲሳይ – አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 14፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ)

በአቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ ክስ ተመሠረተባቸው

በጥረት ኮርፖሬት የሀብት ምዝበራ ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታዬ የሚገኙት አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ በሙስና እና ስራን ባመች ሁኔታ ባለመስራት ወንጀሎች አራት ክሶች ተመሥርተውባቸዋል፡፡

ክሶቹም በችሎቱ ተነበዋል፡፡

በመጀመሪያው ክስ ሁለቱ ተከሳሾች ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር በመመሳጠር በጋራ ኢንቨስትመንት ስም የዳሽን ቢራን 50 ነጥብ 14 አክስዮን ድርሻ ያለአግባብ በመሸጥ በጥረት ኮርፖሬት ላይ ከ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል ተብሏል፡፡

በሁለተኛው ክስ ደግሞ ተከሳሾቹ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት የአዋጭነት እና የዳሰሳ ጥናት ሳይካሄድ አንዲሁም የቦርድ ውሳኔ ሳይሰጥ “ለስማርት ኤሌክትሪክ ውሃ ዊንድ ጄኔሬተር ኩባንያ” በድምሩ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ከጥረት ቢተላለፍም ኩባንያው ወደ ስራ አለመግባቱ ተነቧል፡፡

በ3ኛ ክስ ሁለቱ ተከሳሾች “ድቬንትስ ዊንድ” ለተሰኛ ኩባንያ የባንክ ዕዳ በጥረት የሂሳብ ቁጥር “አካውንት” አንዲከፈል አድርገዋል፡፡

በዚህም በጥረት ኮርፖሬት ላይ ከ46 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል ተብሎ ነው የቀረበው፡፡

በ4ኛው ክስ እንደቀረበው ደግሞ በጥረት ስር ያሉ አክስዮን ማኅበራት የብድር ዋስትና ግዴታ በመግባት ዕዳ የመክፈያ ጊዜያቸው ሲድርስ ከጥረት የሂሳብ ቁጥር “አካውንት” አንዲከፈል በማድረግ ከ102 ሚሊየን ብር በላይ ኪሳራ አድርሰዋል፡፡

ሁለቱ ተከሳሾች ከተለያዩ የግልና የመንግስት ባንኮች የተበደሩትን ገንዘብ የጥርት ኮርፖሬት እንዲከፍል ማድረጋቸው በክሱ መዝገብ ተነቧል፡፡

ተከሳሾቹ በቀረቡት ክሶች ላይ መቃወሚያቸውን ለፍርድ ቤቱ በጽሁፍ አቅርበዋል፡፡

የክስ ሂደቱ በፍጥነት አንዲታይላቸው ና ተለዋጭ ቀጠሮዎች እንዳይበዙባቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የ3ኛ ተከሳሽ ጠበቃ ደንበኛቸው ክሱ ተነጥሎ አንዲታይላቸው ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ፍረድ ቤቱ በክስ መቃወሚያው ና በተነሱ ጉዳዮች ላይ ብይን ለመስጠት ለግንቦት 2ቀን 2011 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ምንጭ፡- አ ብ መ ድ

ፍርድ ቤቱ በሙስና ወንጀሎች የተጠረጠሩ የሃያ አራት ግለሰቦችን ጉዳይ ተመለከተ

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ የወንጀል ችሎት በዛሬው ውሎው በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ከተፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 24 ግለሰቦችን ጉዳይ ተመለከተ።
ችሎቱ በዛሬ ውሎው በ5 የተለያዩ መዝገቦች በተለያዩ የመንግስት ተቋማት የስራ ሀላፊዎች የነበሩ የ24 ግለሰቦችን ጉዳይ ተመልክቶ በአራቱ መዝገቦች ውሳኔ አሳልፏል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራከሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን፣ የመድሀኒት ፈንድ እና አቅርቦት ኤጀንሲ እንዲሁም የንብረት ግዥ እና ማስወገድ አገልግሎት ኤጀንሲ የስራ ሀላፊ የነበሩ ግለሰቦች በዛሬው ችሎት ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች ውስጥም በአራቱ መዝገቦች የቀረቡት እና ከዚህ ቀደም በመርማሪ ፖሊስ እና በጠበቆች ክርክር ተካሂዶባቸው የነበሩት ጉዳዮች ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል።

ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሸን እነ አትክልት ተካልኝ፣ ከመድሀኒት ፈንድ አና አቅርቦት ኤጀንሲ እነ አቶ ሀይለስላሴ ብርሀን የሚገኙበት ሲሆን በአራቱ መዝገቦች የቀረቡት 24 ተጠርጣሪዎች በየተቋሞቻቸው የስራ ሀላፊዎች ሆነው ሲሰሩ በነበሩበት ወቅት በመንግስት ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል በሚል በቁጥጥር ስር ውለዋል።

መርማሪ ፖሊስ ከኢትዮጵያ ኮንስትራከሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን የስራ ሀላፊ የነበሩ 10 ግለሰቦች ጋር በተያያዘ 7 የምርመራ መዘገቦችን ለፍርድ ቤቱ ያቀረበ ሲሆን፥ አምስቱ የምርመራ መዝገቦች ከተጠርጣሪዎቹ ጋር ተያያዥነት ያላቸው መሆኑን አስረድቷል።

ከዚህ ውስጥም ከከሰም የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ከ2003 እስከ 2006 ዓ.ም ተፈፀመ የተባለ ወንጀል፣ ያለ አግባብ ተገዝተው ለጉዳት የተዳረጉ እቃዎችን ግዥ የተመለከተ እና ከአርማታ ብረት ግዥ ጋር የተያያዙ ወንጀሎች ይገኙበታል።

በእነዚህ የምርመራ መዝገቦችም መርማሪ ፖሊስ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን በመጥቀስ፥ ቀሪ የሚባሉ እና ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የሚያስፈልጋቸው እንደ ፎረንሲክ ምርመራ፣ የውስጥ ኦዲት ውጤት እንዲሁም ተጨማሪ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎስን ለማቅረብ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

በተጨማሪም መርማሪ ፖሊስ በእነ አቶ ሀይለስላሴ ቢሆን መዝገብ የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦችን እና በእነ አቶ ተስፋዬ ብርሀኑ የተጠረጠሩ 7 ግለሰቦችን በሚመለከትም ተጨማሪ የመርመራ ጊዜ እንደሚያስፈልገውም ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው የቀረቡት ምክንያቶች ተጨማሪ ጊዜ የማያስፈልጋቸው እና የተጠርጣሪዎቹንም የዋስትና መብት የማይከለክሉ መሆናቸውን በመጥቀስና ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ ቀሪ የተባሉትን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን ሊያሸሹ አይችሉም በማለት ጉዳያቸውን ውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ለፍርድ ቤቱ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ የተጠረጠሩበት ጉዳይ እስከ 10 አመት ሊያስቀጣ የሚችል እና ተጠርጣሪዎቹ ቢወጡ በመረጃ ማሰባሰብ ስራው ላይ ችግር ሊፈጥሩ እና ማስረጃ ሊያሸሹ ስለሚችሉ የዋስትና መብታቸው ሊፈቅድ አይገባም ሲል ተቃውሟል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤቱም በአራት መዝገብ የቀረቡ 21 ተጠርጣሪዎች ላይ መርማሪ ፖሊስ ቀሪ ያላቸውን ማስረጃዎች እንዲመረምር እና እንዲያቀርብ 14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።

በተያያዘም መርማሪ ፖሊስ በአምስተኛ መዘገብ አቶ ይገዙ ዳባን ጨምሮ ሶስት የቀድሞ የግዥ እና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ የስራ ሀላፊ የነበሩ 3 ተጠርጣሪዎች በመንግስት ላይ ከ48 ሚሊየን ዶላር በላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ለችሎቱ አስረድቷል።

ተጠርጣሪዎቹ በፍጥነት ገበያን ለማረጋጋት ይውል የነበረ እና ለገበያ መቅረብ የነበረበት 400 ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴን ለገበያ ማቅረብ ሲገባቸው ያለ አግባብ ጨረታውን ለአራት ጊዜ በማራዘም እና በመሰረዝ በአራቱም ጨረታዎች ላይ ፕሮሚሲንግ ኢንተርናሽናል የተባለ ኩባንያ እንዲያልፍ በማድረግ በመንግስት ላይ ከፍተኛ የገንዘብ ጉዳት እንዲሁም ስንዴውም በተባለው ጊዜ ተገዝቶ ለገበያ እንዳይውል ማድረጋቸውን ጠቅሷል።

ተጠርጣሪዎቹ በመጀመሪያው ጨረታ ላይ ከ19 ሚሊየን ዶላር በላይ፣ በሁለተኛው ጨረታ ከ17 ሚሊየን ዶላር በላይ፣ በሶስተኛው ጨረታ ላይ ከ4 ሚሊየን ዶላር በላይ እንዲሁም በአራተኛው ጨረታ ላይ ከ3 ሚሊየን ዶላር በላይ ጉዳት አድርሰዋልም ነው ያለው መርማሪ ፖሊስ።

እንዲሁም ስንዴው ከተጓጓዘበት መርከብ ጋር በተያያዘ ከ5 ሚሊየን ዶላር በላይ ያለአግባብ ወጪ እንዲወጣ በማድረግ በአጠቃላይ በመንግስት ላይ ከ48 ሚሊየን ዶላር በላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውም ተመልክቷል።

ከዚህ ባለፈም አሁን በሀገሪቱ ላይ የሚስተዋለው የስንዴ እና የዱቄት እጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ሆነዋል ያለው መርማሪ እስካሁንም ከ100 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የሚሆነው ስንዴ አለመግባቱን የሚያመላክት ማስረጃ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።

በዚህ መዝገብም ቀሪ ስራዎችን ለመስራት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በበኩላቸው ዋስትና እንዲፈቀድላቸው እና ቀሪ ለተባሉ ስራዎችም የተጠየቀው ተጨማሪ ጊዜ ብዙ በመሆኑና አጭር ቀን እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠ ሲሆን ብይን ለመስጠት ለነገ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በዙፋን ካሳሁን

ፋና ብሮድካስት

ስለ ‘ሕግ’ ሳይሆን ስለ ‘ሪፐብሊኩ’ አምላክ … መርጃ በጓሮ የሚሰጥበት ወቅት አክትሟል!!

አንዳንድ ጊዜ ማመን እስከሚያቅት ድረስ አንኳር ሚስጢሮች በውስን ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያ ሲሰራጩና ጉዳዮቹ በቀታይ ሲፈጸሙ እያየናቸው ነው። ይህ አሰራር መርጃውን የሚያሰራጩትን ውስን ወገኖች ” ጀግናና የበላይ” አስመስሎ እየሳላቸው ከመሆኑም በላይ ራሳቸውን መሪና ማን አለብኝ ስሜት ውስጥ እየከተቱ ነው። መረጃ ሆን ተብሎ እንዲራባ አስቀድሞ የሚሰጥበት አግባብ ቢኖርም፣ አሁን ያለው አሰራር ገደብ ካልተጣለለት ችግሩ የጎላ ሊሆን ይችላል።

በተለይም በአክቲቪስት ነነ ባዬች መካከል የትከሻ መለካኪያና  ” እኔ ልዩ ነኝ” የሚል ስሜት እየፈጠረ ስለመሆኑ መልክቶች አሉ። መቼም ሰው ነንና ይገባናል። አቶ ሙሼ ሰሙ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ በፌስ ቡክ ገጹ ከነገው ጽሁፉ ላይ ቆንጥሮ የሚከተለውን ለጥፏል። ጉዳዩ አግባብ ያለውና መድረስ ለሚገባው አካል መድረስ ስላለበት ቀርቧል።

በሀገራዊ ወይም መንግስታዊ ሚስጥርና በሕዝብ መረጃ የማግኘት መብት መካካል ያለው ቀይ መስመር ተጥሷል፡፡ መረጃ ለማን፣ እንዴት፣ ለምን፣ እንደሚሰጥ የጠራ አሰራር እንደሌለ ይናፈሳል። በ “ውስጥ አዋቂ ነን” ባዮች አማካኝነት ፌስ ቡክ ላይ ከሚናኙት መረጃዎች አሳሳቢነት ለመረዳት እንደሚቻለው፤ መረጃዎቹ የሚናኙት ሕግንና ፕሮቶኮልን ጠብቀው ሳይሆን እንደዋዛ በመቀራረብና በመተዋወቅ ጭምር እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም። በግልጽም የሚታይና ሊደብቁት የማይገባ እውነት ነው።

ፍርሃትና ስጋት በነገሰበት ማህበረሰብ ውስጥ በዚህ መልኩ የመረጃ ሞኖፖሊ ይዘው “ውስጥ አዋቂ ነን” የሚሉ አክቲቪስቶች፣ ግለሰቦችና ቡድኖች የሚያሰራጩት መረጃ ሁሌም ትክክለኛ ሆነው ባይገኙም መረጃዎቹ በሕዝቡ ውስጥ ያለውን የመረጃ ጥማትና ክፍተቶችን የሚሞሉ ናቸው። መረጃዎቹና ማስረጃዎቹ ማን እንደሚሾም፣ ከምርመራ በፊት ማን ላይ ምን ዓይነት ወንጀል እንደሚለጠፍ፣ እነማን እንደሚታሰሩና እንደሚታደኑ፣ ምን ዓይነት ግጭቶች እንደሚከሰቱ፣ ግጭቱን እነማን እንደሚመሩት፣ የግጭቱ ውጤቱ ወዴት ሊያመራ እንደሚችልና ግጭቱን የሚመሩት ኃይሎች እስከታጠቁት መሳርያ ድረስ በዝርዝር የሚዘልቁ ስለሆኑ የውስጥ አዋቂዎች፣ የአክቲቪስቶችና የፌስቡክ ተከታዮቻቸው ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሚገመተው በላይ እንዲጨምርና ፌስቡክ ለኢትዮጵያውያን በቀዳሚ የመረጃ (Main stream) ምንጭነት እንዲታጭ እያደረጉት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት የነበረውን ስርዓት (Order) ለመታገል ሲባል ለታማኝ ግለሰቦች፣ ለአክቲቪስቶች፣ ለውስጥ አርበኞች እና ለታዋቂ ሰዎች መረጃ በማሾለክ ትግሉን ማጧጧፍ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ዛሬ ላይ ትግሉ ከሞላ ጎደል ተደምድሟል፡፡ አሸናፊው ኃይልም የሪፐብሊኩና የክልል መሪ ሆኗል፡፡ እናም ለትግሉ ሲባል መደበኛ ባልሆነ መልኩ መረጃን የማሾለክ አሰራር ከዚህ በኋላ ጥቅሙ ግልጽ አይደለም። ሊቆምም ይገባል።
መንግስትም መንግስት ነውና ፣ የመንግስትነቱም ሚስጢሩ የቃለ መሐላ ውጤትም በመሆኑ፣  ሚስጥሩን የሕይወት ዋጋ ጭምር በመክፈል መጠበቅ ግዴታው መሆኑን ሊዘነጋ አይገባም።

“አክቲቪስትም” ሆነ “ብሎገር” በዚህ መልኩ በመሞዳሞድ በሚያገኘው መረጃ ላይ ተመስርቶ ሁከትና ብጥብጥ እንዲሁም ልዩነትና ዘረኝነት ወይም የአንድ ወይም የሌላ ብሔር የበላይነትን እንዲያሰፍን ሊፈቀድለት አይገባም ”
“ስለ ሕግ ሳይሆን ስለ ሪፐብሊኩ አምላክ በሚል ርዕስ አዲስ አድማስ ላይ ቅዳሜ ከሚወጣ ጽሑፍ የተቀነጨበ” ሙሉውን ነገ ነገ ይመልከቱ።