Category Archives: ህግ

ይህ ዓምድ ህግ ነክ ጉዳዮች ለግንዛቤና ለመረጃ ይረዳ ዘንድ የሚስተናገድበት ነው። ዓምዱ ቀደም ያሉ ብይኖችና የህግ አግባቦችን ያካትታል።

ፍርድ ቤቱ ከ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች መካከል ከ98 ቤቶች ውጪ ያሉት እንዳይተላለፉ የወጣው እግድ እንዲነሳ አዘዘ

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጦር ሀይሎች ምድብ ችሎት 8ኛ የፍትሃብሄር ችሎት እጣ ወጥቶባቸው የነበሩ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለባለ እድለኞች እንዳይተላለፉ ተጥሎ የነበረው እግድ ከ98 ቤቶች ውጪ ያሉት ቤቶች ላይ እግዱ እንዲነሳ አዘዘ።

መጋቢት 26 ቀን 2011 ዓመተ መህረት 98 100 በመቶ ክፍያ የፈፀሙ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተመዝጋቢዎች ከሳሾች እጣ የወጣባቸው ቤቶች እንዳይተላለፉ የጠየቁትን አቤቱታን ችሎቱ ሲመረምር ቆይቷል።

እጣ የወጣባቸው ከ18 ሺህ በላይ ቤቶች መሆናቸው የተመለከተው ፍርድ ቤቱ፥ በእነዚህ 98 ተከሳሾች ምክንያት ሌሎች ቤቶች ታግደው መቆየት የለባቸውም ሲል የሌሎችን ቤቶች እግድ አንስቷል።

ፍርድ ቤቱ 98 ቤቶች ማለትም 48 ባለ ሶሰት መኝታ፣ 43 ባለ ሁለት መኝታ እና ሰባት ባለ አንድ መኝታ ቤቶች ባሉበት ለማንም ሳይተላለፉ ታግደው እንዲቆዩ ፥ በቀሪዎቹ ቤቶች ላይ ግን እግዱ እንዲነሳ ሲል ትእዛዝ ሰጥቷል።

በተጨማሪም ችሎቱ የፍትሃብሄር ህግ 41 መሰረት በእነ ዘላለም መዝገብ በሚል በአሁኑ እጣ የወጣላቸው ከ50 በላይ እድለኞች በሶስተኛ ወገን በመዝገቡ ላይ ጣልቃ እንግባ ብለው የጠየቁትን ጥያቄ ተቀብሎ ፈቅዷል።

ሌሎች 100 በመቶ ቆጥበናል ብለው የቀረቡ 130 ሰዎች ጥያቄን ውድቅ ያደረገው ፍርድ ቤቱ፥ በሌላ መዝገብ እንደ አዲስ ክስ መመስረት ትችላላቹ ብሏል።

በሌላ በኩል 98 ቤቶች ለባለ እድለኞች እንዳይተላለፉ ትእዛዝ የወጣላቸው 98 ከሳሾች ክሳቸውን አሻሽለው እና ለተከሳሽ ኪሳራ ከፍለው እንዲቀርቡ ለግንቦት 28 ቀን 2011 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የጋራ መኖሪያ ቤቱን ለማግኘት ተመዝግበው 100 በመቶ የከፈሉ 98 ዜጎች ክስ መመስረታቸውን ተከትሎ ነው ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ የፍርድ ሂደቱ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ለባለ እድለኞች እንዳይተላለፉ አግዶ የነበረው።

ተመዝጋቢዎቹም የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒቴርን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝን እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ነው የከሰሱት።

በመመሪያው መሰረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዕጣ አውጥቶ ለእድለኞች ማከፋፈል ሲገባው የከተማ አስተዳደሩ መመሪያን በመጣስ 100 በመቶ የቆጠቡ ተመዝጋቢዎች እያሉ ከ40 በመቶ ጀምሮ የቆጠቡትን በእጣው በማካተት ዕጣውን በማውጣት ከሕግና ከውል ውጪ ቤቶቹ እጣ እንዳወጣባቸው በክሳቸው ላይ ጠቅሰዋል።

ባለፈው የካቲት 27 ቀን 2011 ዓመተ መህረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ18 ሺህ 576 የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ እጣ ማውጣቱ ይታወሳል።

በታሪክ አዱኛ –  (ኤፍ ቢ ሲ) 

በመቶዎች የሚቆጠሩ ማጅራት መቺዎች ተያዙ፤ መቶ ሃያ ሁለት ታርጋ አልባ ተሽከርካሪዎች ተገኝተውባቸዋል

ነዋሪዎች ክፉኛ ተማረው ነበር። በጠራራ ጸሃይ እየዘረፉ መንጎድ፣ ተመልሶ ማስፈራራትና ጡንቻን ማሳየት የየእለት ድራማ መሆኑ በርካቶችን ማሳዘን ከጀመረ ቆይቷል። በንጽህናዋና በውበቷ የምትታወቀው ሃዋሳ በንዲህ ያለው የቀን ተቀን ዝርፊያ ነዋሪዎቿ ቢማረሩም አሁን ነገሮች የተቀየሩ ይመስላል።

በተደጋጋሚ በህዝባዊ ውይይቶችና ራሱ መንግስት በሚያዘጋጃቸው መድረኮች ” መንግስት ህግ ያስከብር” የሚል ተደጋጋሚ ሮሮ የሚሰማውም በዚሁ መነሻ ነበር። መንግስት በተለይም የሰላም ሚኒስትሯ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ” አሁን ገደብ አልᎈል፣ ወደማንፈልገው እርምጃ እንገባለን፤” ብለውም ነበር።

ዛሬ የመንግስት መገናናዎች አንድ መቶ ዘጠና አራት ዘራፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ እንደተደተሰማው የተያዙት ዋናዎቹ ቁንጮዎች ናቸው። ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ እንዳሉት ከተያዙት መካከል የራሳቸው ጀሌና ቡድን፣ እንዲሁም አደረጃጀት ያላቸው ይገኙበታል። የእነሱ መያዝ ሰንሰለታቸው ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር እንዲውን ያስችላል።

የሃዋሳ ከተማ ነዋሪዎች በመንግስት ድንገተኛ ውሳኔና እርምጃ መገረማቸውንም እየገለጹ ነው። ለውጡን ያልተቀበሉና “የሴራ አስፈጻሚ” የነበሩ አካላትንና የጸጥታ ሃይላትን መልሶ ለማደራጀት የወሰደውን ጊዜ ተጠቅመው ዝርፊያ፣ ቅሚያና መረጋጋት እንዳይሰፍን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላት ዛሬ መያዛቸው ድንጋጤም የፈጠረባቸው እንዳሉ ተሰምቷል። ፋና የሚከተለውን ዘግቧል።

በሀዋሳ ከተማ በተለያዩ የዝርፊያና ስርቆት ወንጀሎች ላይ ሲሳተፉ የነበሩ 194 ተጠርጠሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። በትናትናው ዕለት በከተማዋ በሚገኙ ስምንት ክፍለ ከተሞች የፀጥታ አካላት ከማህበረሰቡ ጋር በሰሩት የተቀናጀ ስራ የተለያዩ የስርቆት ወንጀሎችን ሲፈፅሙ የነበሩ 194 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ቴዎድሮስ ወልደገብርኤል ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች ሞተር ሳይክሎችን በመጠቀም በከተማዋ የተለያዩ የስርቆትን ዝርፊያ ወንጀሎችን ሲፈፅሙ የነበሩ ናቸው።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ወንጀሉን ለመፈፀም ሲጠቀሙባቸው የነበሩ 122 ታርጋ የሌላቸው ባለ ሁለት እግር ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ነው ያሉት ኮሚሽነሩ።

ከዚህ ባለፈም በከተማዋ ነዋሪዎች በተደረገ ጥቆማ 4 መኪና የኮንትሮባንድ ዕቃ በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልፀዋል።

ማህበረሰቡ ተጠርጣሪዎችና ህገ ወጥ ነጋዴዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ያደረገውን አስተዋፅኦ ያደነቁት ኮሚሽነሩ፥በቀጣይም መሰል ተግባራትን ለመከላከል ከፖሊስ ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በኃይለየሱስ መኮንን

በሶስት የቤተሰብ አባላት ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ ጉዳት አደርሳ የተሰወረችው የቤት ሰራተኛ እየተፈለገች ነው

በአዲስ አበባ ገላን ኮንዶሚኒየም በሁለት ህፃናትና እናታቸው ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት ጉዳት አድርሳ የተሰወረችው የቤት ሰራተኛ እየተፈለገች ነው።

በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የቃሊቲ ፖሊስ መምሪያ ወንጀል ምርመራ ክፍል ሃላፊ ኮማንደር ተስፋዬ ወሰን የለህ ለፋና ብሮድካስቲግ ኮርፖሬሽን እንዳስታወቁት፥ የቤት ሰራተኛዋ ሁለቱ ህጻናቶችና እናታቸውን ከለሊቱ ሰባት ሰዓት ላይ በስለት በአሰቃቂ ሁኔታ ጉዳት ካደረሰች በኋላ ተሰውራለች።

የቤት ሰራተኛዋ የአንድ ዓመት ህጻኑን አንገቱ ላይ የሌላኛው ህጻን ደግሞ አይንና ጭንቅላት ላይ እንዲሁም የህፃናቱን እናት ጭንቅለቷ ላይ በስለት ጉዳት ማድረሷን ጠቁመዋል።

በቤት ሰራተኛቸው አሰቃቂ ወንጀል የተፈጸመባቸው እናትና ሁለት ህጻናት በአሁኑ ወቅት ለከፍተኛ ህክምና ከጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ወደ ሚኒሊክ ሆስፒታል መወሰዳቸው ተገልጿል።

ይህንን ጉዳት አድርሳ የተሰወረችውን የቤት ሰራተኛ በቁጥጥር ስር ለማዋል ከተጠርጣሪዋ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሶስት ሰዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል የመመርመር ስራ መቀጠሉንም ተናግረዋል።

የወንጀሉ መነሻ ጉዳይ እየተጣራ መሆኑንም ኮማንደር ተስፋዬ ተናግረዋል ።

በታሪክ አዱኛ – FBC

የመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኢጀንሲ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ ሰባት ሰራተኞች ላይ ክስ ተመሰረተ

የመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኢጀንሲ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ ሲሰሩ በነበሩ ሰባት ሰራተኞች ላይ ክስ ተመሰረተ።

በኢትዮጵያ የመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ በተለያዩ የስራ ኃላፊነት ሲሰሩ የነበሩ ሃይለስላሴ ቢሆን፣ የማነ ብርሃን ታደሰ፣ ሙከሚል አብደላ፣ ኢንጅነር አሸናፊ ሁሴን፣ ያሬድ ይገዙ፣ አንዳርጋቸው ሞግሪያ እና ያለው ሞላ በዛሬው ዕለት ክስ ተመስርቶባቸዋል።

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያመለክተው ተከሳሾች የኢትዮጵያ መድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ በተለያዩ የስራ ኃላፊነት ደረጃ ሲሰሩ በነበሩበት ወቅት የፌዴራል የመንግስት ግዥ አፈፃፀም መመሪያን ወደ ጎን በመተው የተለያዩ መድሃኒት ግዥዎችን ያለ ውድድር ከአቅራቢ ድርጅቶች በቀጥታ በመግዛት 14 ሚሊየን 855 ሺህ 391 ብር በመንግስትና በህዝብ ጥቅም ላይ ጉዳት በማድረስ ወንጀል መከሰሳቸውን ያስረዳል።

ተከሳሾች የወንጀል ሕግ አንቀፅ 32 (1) (ሀ) እና 411 (1) (ሐ)ና (2) የተቀመጠውን በመተላለፍ የመንግስት ስራን በማያመች አኳኋን በመምራት ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው መሆኑን የክሱ ጭብጥ ያስረዳል።

ተከሳሾች የፌዴራል መንግስት የግዥ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001 አንቀጽ 52 እንዲሁም በ2002 ዓ.ም የወጣውን የፌዴራል መንግስት የግዥ አፈፃፀም መመሪያ አንቀጽ 25 በተጨማሪም በመድሃኒት ፈንድ ኤጀንሲ የግዥ መመሪያ አንቀጽ 10.33ን በመጣስ ለሀገር መከላከያ ሚኒስቴር አገልግሎት የሚውል ልዩ ልዩ መድሃኒቶችን ከሲትረስ ኢንተርናሽናል የ13, ሚሊየን 855 ሺህ 391 ብር እንዲሁም ከአልኮል ላቦራቶሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አትሮፊን ሰልፌት አንድ በመቶ የአይን ጠብታ መድሃኒት የ1 ሚሊየን 406 ሺህ 281 ብር በድምሩ 15 ሚሊየን 261 ሺህ 672 ብር በመንግስትና በህዝብ ላይ ጉዳት በማድረስ በዋና ወንጀል አድራጊነት መከሰሳቸውን አብራርቷል።

በተመሳሳይ በሌላ መዝገብ ሃይለስላሴ ቢሆን፣ የማነብርሃን ታደሰ፣ ሙከሚል አብደላ፣ ሳፊያ ኑር እና ማስረሻ አሰፋ በመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ሰራተኛ ሆነው ሲሰሩ በነበሩበት ወቅት በጨረታ ተሸናፊ ከነበሩ ኢፋርም፣ ፋርማኪዩር እና ካዲላ ፋርማሲዩቲካል ከተባሉ ድርጅቶች የ104 ሚሊየን 47 ሺህ 316 ብር ግዢ በቀጥታ በማከናወን ሌሎች አቅራቢ ድርጅቶች ካቀረቡት በመብለጡና በመንግስትና በህዝብ ላይ 313 ሚሊየን 116 ብር ጉዳት በማድረስ መከሰሳቸውን የዐቃቤ ህግ ሪፖርት ያስረዳል።

በሁለቱም መዝገቦች ላይ የቀረቡት የተከሳሾች ጠበቆች የክስ መቃሚያ ለማቅረብ ጊዜ ይሰጠን በማለት የጠየቁ ሲሆን፥ ተከሳሾች በዋስትና ወጥተው ጉዳያቸውን እንዲከራከሩ ጠይቀዋል።

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ የጠየቁት የዋስትና ጥያቄ ተከሳሾች የተከሰሱበት የህግ ድንጋጌ የዋስትና መብት የሚያስከለክል በመሆኑ ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄዎቻቸውን ውድቅ እንዲያደርግ ጠይቋል።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ የወንጀል ችሎት ግንቦት 13 ቀን 2011ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሾች ለግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም የክስ መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ያስተላለፈ ሲሆን፥ የተከሳሾችን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው ማገዱንም አሳውቋል።

በአንደኛው መዝገብ ያልተያዙ ኢንጅነር አሸናፊ ሁሴንና አንዳርጋቸው ሞጎሪያ የፌዴራል ፖሊሲ በአድራሻቸው መጥሪያ በማድረስ ለግንቦት 23 ቀን 2011 ዓ.ም ፍርድ ቤት እንዲያቀርብ መታዘዙን ከፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

(ኤፍ ቢ ሲ)

የእነ በረከት የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ ውድቅ አደረገ። ከሳሽ አቃቤ ህግ ሚያዚያ 14 ቀን 2011 ዓመተ ምህረት በአቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ ላይ አራት ክሶችን ለፍርድ ቤቱ ማሰማቱ ይታወቃል።

ፍርድ ቤቱ በዛሬው እለት ሁለቱ ተከሳሾች በጋራ በፅሁፍ ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ በመስማት የአቃቤ ህግን መከራከሪያ መርምሮ ብይን ሰጥቷል።

ተከሳሾቹ በክስ መቃወሚያቸው የዳሸን ቢራ አክሲዮን ማህበር ጉዳይ ሀገራዊ እና ድንበር ተሻጋሪ ስለሆነ በክልሉ ፍርድ ቤት ሊታይ አይገባም ያሉ ሲሆን፥ ተፈፀመ የተባለው የሙስና ወንጀልም በፀረ ሙስና አዋጅ መሰረት ከመጋቢት 25 ቀን 2007 ዓመት ምህረት በፊት ስለሆን ልንከሰስ አይገባም ብለዋል።

ከጁቬንቱስ ቴክኖሎጂ አክሲዮን ማህበር ጋር በተያያዘ ተፈፀመ የተባለው የሙስና ወንጀል አንዱ ተከሳሽ የውጭ ሀገር ዜግነት ስላለው በክልሉ ፍርድ ቤት ሊታይ አይገባም፤ በተጨማሪም ተፈፀመ የተባለው የሙስና ወንጀልም በፀረ ሙስና አዋጅ መሰረት መጋቢት 25 ቀን 2007 ዓመት ምህረት በፊት ስለሆነ ልንከሰስ አይገባም የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል።

አቃቤ ህግ በበኩሉ የጥረት ኮርፖሬት ዋና መስሪያ ቤት ባህር ዳር የሚገኝ በመሆኑ እና የተፈፀመው የሙስና ወንጀል በክልሉ መሆኑን አስረድቷል።

ተከሳሾቹ ድርጊቱን የፈፀሙት በቁጥጥር ስር እስከሚውሉ ድረስ በመሆኑ በተጠቀሰው ፀረ ሙስና ወንጀል አዋጅ መሰረት ይመለከታቸዋል ብሏል።

የግራ ቀኙን ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ የዳሸን ቢራ አክሲዮን ማህበር እና የጁቬንቱስ ቴክኖሎጂ አክሲዮን ማህበር የአማራ ክልል ሀብት በመሆናቸው የተፈፀመው የሙስና ወንጀልም ከ2004 እስከ 2010 ስለሆነ የፀረ ሙስና አዋጁ ይመለከታቸዋል በማለት ያቀረቡትን መቃወሚያ ውድቅ አድርጓል።

አቶ በረከት ስምኦን የእምነት ክህደት ቃላቸውን የሰጡ ሲሆን፥ በተከሰሱባቸው ጉዳዮች በዝርዝር ለመናገር ፈቃደኛ አለመሆናቸውን እና ምንም ዓይነት ጥፋት እንዳልፈፀሙ እና እንደማይጠየቁ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

አቶ ታደሰ ካሳ በበኩላቸው ማቅረብ እንዲችሉ ለሰኞ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመስጠት መጠየቃቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ለፊታችን ሰኞ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በናትናኤል ጥጋቡ – FBC

ፍርድ ቤቱ አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ ያልተያዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጣሪዎች ተይዘው እንዲቀርቡ አዘዘ

ፍርድ ቤቱ በአቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ ክስ የተመሰረተባቸውና በቁጥጥር ስር ያልዋሉ አራት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተይዘው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጠ።

የፌዴራል ከፍተኛ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ 26 በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ ተከሳሾችን ጉዳይ ዛሬ ከሰዓት ተመልክቷል።

በዚህ መሰረትም በአቶ ጌታቸው አሰፋ የክስ መዝገብ ክስ ከተመሰረተባቸው ተከሳሾች ውስጥ ከ20 እስከ 26 ተራ ቁጥር ላሉት ተከሳሾች ክሳቸው በንባብ ቀርቧል።

ተከሳሾቹ የተነበበላቸውን ወንጀል እንዳልፈፀሙ ክድው ተከራክረዋል።

የተከሳሽ ተከላካይ ጠበቆች የደንበኞቻቸው የዋስትና መብት እንዲጠበቅላቸውና ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

አቃቤ ህግ በበኩሉ ተከሳሾች የፈፀሙት ወንጀል የዋስትና መብት የማያሰጥ በመሆኑና ተከሳሾች የዋስትና መብታቸው ቢከበርም መረጃ ያሸሹብኛል ብሏል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ የተከላካይ ጠበቆች የክስ መቃወሚያ ይዘው ያልቀረቡ በመሆኑና የዋስትና መብት ተገቢነትን መመርመር አስፈላጊ ሆኖ በማግኘቱ በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት ለግንቦት 8 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በተጨማሪም ለፌዴራል ፖሊስ አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ በሌሉበት ክሳቸው እየታየ ያሉ አራት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተይዘው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ በትናንትናው ዕለት ክስ ከተመሰረተባቸው 26 ተከሳሾች ውስጥ ከ1ኛ እስከ 19 ላሉት ተከሳሶች ክሳቸውን በንባብ ማቅረቡ ይታወሳል።

(ኤፍ.ቢ.ሲ)

”እያሉ” በሌሉበት የተከሰሱት አቶ ጌታቸው አሰፋን የትግራይ ክልል ለምን አሳልፎ አይሰጣቸውም ?

በወንጀል የተጠረጠረው ግለሰብ ማንም ይሁን ማን፤ ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረበት ወንጀል በፌደራል መንግሥት ስልጣን ስር የሚወድቅ እስከሆነ ድረስ፤ የፌደራል መንግሥቱ የማንንም ፍቃድ ሳይጠይቅ ወደ የትኛውም ክልል ሄዶ በወንጀል የተጠረጠረውን ግለሰብ በቁጥጥር ሥር የማዋል ስልጣን አለው

BBC Amharic – አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ በ26 የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ላይ ክስ መመስረቱን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ማክሰኞ ዕለት ማስታወቁ አይዘነጋም።

በቁጥጥር ሥር ያልዋሉት በከፍተኛ የሙስና እና ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም በሚሉ ወንጀሎች ክስ የተመሰረተባቸው አቶ ጌታቸው፤ በትግራይ ክልል እንደሚገኙ ጠቅላይ ሚንስትሩ እና የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ቀደም ሲል በተለያየ ጊዜ ጠቁመዋል።

ታዲያ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አሰፋ በትግራይ ክልል እንዳሉ እየታወቀ ለምን ”በሌሉበት” የሚል ክስ ተመሰረተባቸው የሚለው በርካቶችን አነጋግሯል። እኛም በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የሕግ ባለሙያው አቶ ዮሃንስ ወ/ገብርኤልን ጠይቀናል። አቶ ዮሃንስ የደርግ ከፍተኛ አመራሮችን ለመክሰስ ተቋቁሞ በነበረው ልዩ አቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት እንዲሁም በሥነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በዋና ዓቃቤ ሕግ ከዚያም በቀድሞው የኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን የሕግ ክፍል ሃላፊ ነበሩ።

• አቶ ጌታቸው አሰፋ ላይ ክስ ተመሰረተ

”በሌሉበት”

አቶ ዮሃንስ ”አንድ ተጠርጣሪ ሃገር ውስጥ ሳለ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በሕግ አስከባሪ አካል እንዲያዝ እና እንዲቀርብ ታዞ ሳይቀርብ ቢቀር እንኳ ተጠርጣሪው በሌለበት ጉዳዩ በፍርድ ቤት መታየቱ አይቀርም” በማለት ያስረዳሉ።

አንድ ተከሳሽ በሌለበት በፍርድ ቤት ውሳኔ ከተላለፈበት፤ ፍርደኛው ለፍርድ ቤቱ በሌለሁበት ጉዳዩ መታየቱ አግባብ አይደለም ብሎ ሊያመለክት ይችላል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ተከሳሹ ሆነ ብሎ አልያም መጥሪያው ሳይደርሰው ቀርቶም ከሆነ ፍርድ ቤት የሚያጣራው ጉዳይ ይሆናል። ተከሳሹ ሆነ ብሎ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ከቀረ የተላለፈበትን ውሳኔ የመከላከል እድሉን እንዳልተጠቀመ ተደርጎ ይወሰዳል። ይሁን እንጂ ተከሳሹ መከሰሱን ሳያውቅ ውሳኔ እንደተላለፈበት ፍርድ ቤቱ ካመነ፤ ተከሳሹ ማስረጃውን እና መከላከያውን ሊያቀርብ የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ የሕግ ባለሙያው አቶ ዮሃንስ ያስረዳሉ።

እሳቸው እንደሚሉት ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር ባይውልም የፍርድ ሂደቱ ይቀጥላል። ”ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ሕግን ምስክሮች መስማት ይጀምራል። በሌለበት ውሳኔ ይሰጣል። በተጨማሪም ተከሳሹ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ በጠበቃ ሊወከል አይችልም። በኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሰረት በእንዲህ አይነት ወንጀል ክስ የተመሰረተበት በውክልና ሊከታተል አይችልም።” ይላሉ።

አቶ ጌታቸው አሰፋን በተመለከተም፤ የወጣባቸው የእስር ትዕዛዝ እና ክስ በመገናኛ ብዙሃን በስፋት ተሰራጭቷል ተብሎ ስለሚታመን ተከሳሹ የፍርድ ቤቱ መጥሪያ ደርሷቸዋል ብሎ ፍርድ ቤቱ ሊደመድም እንደሚችል የሕግ ባለሙያው ይገልፃሉ።

”የትግራይ ክልል አሳልፎ አይሰጥም”

በሰብዓዊ መብት ጥሰት እና በከፍተኛ የሙስና ወንጀል የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸውን ከዚያም ክስ የተመሰረተባቸውን የቀድሞ የስለላ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋን የትግራይ ክልላዊ መንግሥት አሳልፎ ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆኑን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ከወራት በፊት አሳውቆ ነበር። ይህን ያሉት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ብርሃኑ ጸጋዬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመስሪያ ቤታቸውን የአምስት ወራት የሥራ ሪፖርት ይፋ ባደረጉበት ወቅት ነበር።

በወቅቱ የፌደራል መንግሥት ከትግራይ ክልል ፍቃድ እና እውቅና ውጪ ግለሰቡን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚያስችለው የሕግ አግባብ አለ? አቶ ጌታቸው አሰፋ በየትኛው የሕግ አግባብ ለፌደራል መንግሥት ተላልፈው ሊሰጡ ይችላሉ? የሚሉ ጥያቄዎችን ለሕግ ባለሙያዎች አቅርበን ነበር።

የፌደራል ፍርድ ቤቶችን ሥልጣን ለመወሰን በወጣው የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1996 አንቀጽ 4.3 መሠረት የፌደራል ፍርድ ቤቶች በሰው ልጆች መብት ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች የዳኝነት ሥልጣን እንዳላቸው ይደነግጋል።

የሕግ ባለሙያው አቶ አዲ ደቀቦ፤ በወንጀል የተጠረጠረው ግለሰብ ማንም ይሁን ማን፤ ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረበት ወንጀል በፌደራል መንግሥት ስልጣን ስር የሚወድቅ እስከሆነ ድረስ፤ የፌደራል መንግሥቱ የማንንም ፍቃድ ሳይጠይቅ ወደ የትኛውም ክልል ሄዶ በወንጀል የተጠረጠረውን ግለሰብ በቁጥጥር ሥር የማዋል ስልጣን አለው ይላሉ።

የፌደራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስልጣን ከሚኖረው የወንጀል እይነቶች መካከል፤ በሰው ልጆች መብት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ጨምሮ በውጪ ሃገራት መንግሥታት ላይ የሚፈጽሙ ወንጀሎች፣ የበረራ ደህንነትን የሚመለከቱ ወንጀሎች እና የመሳሰሉት በፌደራል ፍርድ ቤቶች የሚታዩ የወንጀል አይነቶች ናቸው።

አቶ አዲ አንደሚሉት አንድ ግለሰብ የፌደራል መንግሥት ሰራተኛ ሳለ ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረበት ወንጀል ካለ፤ የፌደራል መንግሥት የየትኛውንም ክልል ፍቃድም ይሁን ይሁንታ ሳያስፈልገው ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር አውሎ የመመርመር ስልጣን አለው ይላሉ።

በተመሳሳይ መልኩ ሌላው የሕግ ባለሙያ ሆኑት አቶ ኤፍሬም ታምራት አንድ የክልል መንግሥት በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠረን እና በፌደራል አቃቤ ሕግ ክስ የተመሰረተበትን ግለሰብ አሳልፌ አልሰጥም ቢል፤ ሕገ-ምንግሥቱን፣ የፌደራል የወንጀል ሕጉን፣ የፌደራል ፍርድ ቤቶችን ሥልጣን ለመወሰን የወጣውን የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅን፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉን እና የፌደራል ፖሊስ ማቋቋሚያ አዋጅን ይተላለፋል ይላሉ።

አቶ ኤፍሬም ሃሳባቸውን ሲዘረዝሩ፤ በሕገ-መንግሥቱ ሦስተኛው ምዕራፍ ላይ በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ የፌዴራል መንግሥትና የክልል ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚ እና የዳኝነት አካሎች የመብቶችና የነፃነቶች ድንጋጌዎችን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለባቸው ተጠቅሷል።

”የማክበር ግዴታ ማለት እራሱ የመንግሥት አካል ወንጀል እንዳይፈጽም መከላከል ሲሆን የማስከበር ማለት ደግሞ ወንጀል የፈጸመውን ግለሰብ የመመርመር እና ሕግ ፊት የማቅረብ ኃላፊነት ማለት ነው” ይላሉ።

አቶ ኤፍሬም የክልሉ ውሳኔ የፌደራል ፖሊስ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 720/2004 እንዴት እንደሚጻረር ሲያስረዱ፤ አንቀጽ 6 ሥር የተቀመጠውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንን ሥልጣን እና ተግባርን በመዘርዘር ያስረዳሉ። አቶ ኤፍሬም እንደሚሉት ከኮሚሽኑ ሥልጣን እና ተግባራት መካከል በፌደራል ፍርድ ቤቶች የሥልጣን ክልል ስር የሚወድቁ ወንጀሎችን ይከላከላል፤ ይመረምራል።

የፌደራል ፍርድ ቤቶችን ሥልጣን ለመወሰን የወጣውን የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1996 የፌደራል ፍርድ ቤቶች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ የተፈጸሙ የወንጀል ተግባራትን ማየት የሚችለው የፌደራል ፍርድ ቤት መሆኑን በመጥቀስ ለፌደራል መንግሥት የተሰጠ ስልጣን ክልሎች እንደማይኖራቸው የሕግ ባለሙያው ያስረዳሉ።

የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕጉም ማንኛውም ዜጋ በተግባሩ ጉዳት እስካልደረሰበት ድረስ፤ በወንጀል የተጠረጠረን ግለሰብ አሳልፎ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት እንደሚያትት የሚናገሩት የሕግ ባለሙያው የክልል መንግሥታትም ቢሆኑ ይህን የሕግ ኃላፊነት ከመወጣት ወደኋላ ማለት አይችሉም ይላሉ።

በወንጀል የሚፈለግን ግለሰብ አሳልፌ አልሰጥም ማለት በራሱ ፍትህን የማስተጓጎል ወንጀል ነው የሚሉት አቶ ኤፍሬም፤ ዛሬ ላይ በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠረን ግለሰብ አሳልፌ አልሰጥም የሚል የሕግ አስፈጻሚ አካል፤ ነገ ሰልጣንን ያለ አግባብ በመጠቀም በሚል በወንጀል ሊጠየቅ ይችላል ይላሉ።

ይህን ተግባራዊ ሊያደርግ የሚችለው የየትኛው የፌደራል አካል ነው?

የሕግ ባለሙያው አቶ አዲ ይህ ከወንጀል ምርመራ ጋር የተያያዘ ሰለሆነ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር የማዋል ስልጣኑ የፌደራል ፖሊስ ነው ይላሉ። የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመጣመር ሥራውን ሊያከናውን እንደሚችልም ይጠቁማሉ።

የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ለአቶ ጌታቸው አሰፋ ከለላ ሰጥቷል ለሚለው ክስ እስካሁን ምንም አይነት ይፋዊ ምላሽ አልሰጠም። ነገር ግን ቀደም ብሎ ከሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው እስር ጋር በተያያዘ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳደር የሆኑት ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ክስ እና እስሩን በመኮነን ጠንከር ያለ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።

የቀረቡት ክሶች በአንድ ወገን ላይ ያነጣጠረ መሆኑን አንስተው ”የኛ ሰው ለምን ታሰረ? አንልም።. . . ሁሉም መጠየቅ አለበት” በማለት እርምጃው ፖለቲካዊ አላማን የያዘ መሆኑን ተናገረዋል።

ጨምረውም ክሱ የተለየ ዘመቻ መሆኑንና ማንነታቸውውን በግልጽ ያላስቀመጧቸው ወገኖች እጅ እንዳለበት “ትግራይን ለማዳከም የውጪ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እየታየ ነው፣ በትግራይ ህዝብ ላይ አዲስ ዘመቻ ተጀምሯል” በማለት ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ክስ እና እስሩን ተቃውመውት ነበር።

ራሳቸውን የሸሸጉት እነ ጌታቸው አሰፋ ላይ ክስ ዝርዝር እየተሰማ ነው

ራሳቸውን በአገር ውስጥ ሸሽገዋል ወይም ከለላ ተሰጥቷቸዋል የሚባሉት አቶ ጌታቸው አሰፋና ባልደረቦቻቸውን ጨምሮ፣ እንዲሁም በቁጥጥር ስር በዋሉት ላይ ክስ መነበብ ቀጥሏል። ፋና እንደሚከተለው ዘግቦታል።

የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ኃላፊ በነበሩት በእነ አቶ ጌታቸው አሰፋ መዝገብ ከተመሰረቱት 46 ክሶች ውስጥ ከ7ኛ እስከ 34ኛ ያሉትን ክሶች የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ በንባብ አቅርቧል። በመዝገቡ ክስ ከተመሰረተባቸው 26 ተከሳሾች ውስጥ እስከ 19ኛ ላሉት ተከሳሾች ክሳቸው በንባብ ቀርቦላቸዋል።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የወንጀል ችሎት ክስ ተመስርቶባቸው ያልተያዙ ተከሳሾች ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት እና ቀሪ ክሶችን ለተከሳሾቹ በንባብ ለማሰማት ለነገ ከሰዓት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

አቃቤ ህግ የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት ኃላፊ የነበሩትን አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ በ26 ግለሰቦች ላይ በትናንትናው እለት ክስ መመስረቱ የሚታወስ ነው።

በቀድሞው የደህንነት የኢሚግሬሽን እና ስደተኞች ጉዳይ ባለስልጣን በአሁኑ ደግሞ የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ተቋም በተለያዩ የስራ ኃላፊነት ላይ ሲሰሩ በነበሩ ግለሰቦች ላይም አቃቤ ሀግ 46 ክሶችን መስርቶባቸዋል። ከተመሰረቱት ክሶች ውስጥም ስድስቱ ክሶች በትናንትናው ዕለት ለተከሳሾቹ በንባብ ቀርበዋል።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የወንጀል ችሎት በዛሬው እለት ቀሪ ክሶችን ለተከሳሾቹ በንባብ ለማሰማት ከሰዓት በኋላ ተሰይሞ ነበር። ተከሰው ፍርድ ቤት የቀረቡት ከ26ቱ ውስጥ 22ቱ ተከሳሾች ናቸው።

አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ አራቱ ተከሳሾች ማለትም 1ኛ ተከሳሽ አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ 9ኛ ተከሳሽ አቶ አፅብሀ ግደይ፣ 11ኛ ተከሳሽ አቶ አሰፋ በላይ እና 12ኛ ተከሳሽ አቶ ሽሻይ ልኡል ለጊዜው ያልተያዙ እና ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ናቸው።

በዛሬው ዕለትም አቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ ከመሰረተው 46 ክሶች ውስጥ ከ7ኛ እስከ 34ኛ ያሉትን ክሶች ፍርድ ቤቱ ችሎት ላይ ለተገኙት ተከሳሾች በንባብ አሰምቷል።

ዛሬ ፍርድ ቤት ከቀረቡት እና ክሳቸው በንባብ ከቀረበላቸው ተከሳሾች ውስጥም አቶ ያሬድ ዘሪሁን እና አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ይገኙበታል።

ፍርድ ቤቱ በንባብ ያቀረባቸው ክሶችም ተከሳሾቹ በተለያዩ የስራ ኃላፊነት በነበሩበት ወቅት በስልጣናቸው እና የስራ ኃላፊነታቸው በማይፈቅደው ህግን በመተላለፍ ከባድ የሙስና ወንጀል በተለያየ መጠን መፈጸማቸውን የሚያስረዱ ናቸው።

የተነበቡት ክሶች ግለሰቦቹ በመረጃ እና ደህንነት አገልግሎት በተለያየ ደረጃ የስራ ኃላፊ ተመድበው ሲሰሩ በህግ አግባብ የተሰጣቸውን ስልጣን መሰረት በማድረግ፥ ተቋሙ የተቋቋመለትን ጥራት ያለውን መረጃ በማቅረብ አስተማማኝ የደህንነት አገልግሎት በመስጠት የሀገሪቱን ብሄራዊ ደህንነት የመጠበቅ አላማን ከግብ በሚያደርስ ሁኔታ በስራ ኃላፊነታቸው መወጣት ሲገባቸው ይህን ወደ ጎን በመተው በሰዎች ህይወት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ለማድረግ በማሰብና በድርጊቱ በመሳተፍ በተለያዩ ግለሰቦች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈፅሙ እንደነበር ያስረዳሉ።

በግለሰቦች ላይ ተፈጸሙ ከተባሉ እና በክሶቹ ላይ ከቀረቡት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ውስጥም ተከሳሾቹ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ግለሰቦችን በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥራችኋል በማለት በመያዝ እና በተለያዩ የድብቅ እስር ቤቶች እንዲሰቃዩ ማድረግ፣ እንዲገረፉ እና መረጃዎችን በግድ እንዲያወጡ አድርገዋል የሚል ነው።

እንዲሁም በውክልና መረጃ እንዲሰጡ አስገድደዋል፤ በምርመራ ላይ እያሉም ህይወታቸው የጠፋ ግለሰቦች መኖራቸውን እና እስካሁንም እነሱ የያዟቸው ግለሰቦች የደረሱበት ያልታወቀ እና የጠፉም አሉ የሚሉት ይገኙበታል።

በአጠቃላይ ዛሬ የተነበቡት ክሶች ግለሰቦቹ ተበዳዮቹ ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈፀምባቸው ያደረጉ በመሆኑ በፈፀሙት በዋና ወንጀል አድራጊነት ተከፋይ በመሆን በስልጣን አላግባብ በመገልገል የሚፈፀም ከባድ የሙስና ወንጀል መከሰሳቸውን የሚያሳዩ ናቸው።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምደብ 1ኛ የወንጀል ችሎት ከ35ኛ እስከ 46ኛ ያሉትን ክሶች ለተከሳሾቹ በንባብ ለማሰማት እና አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ ያልተያዙ 4 ተከሳሾች ላይ ትዕዛዝ ለማስተላለፍ ለነገ ከሰዓት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

 (ኤፍ ቢ ሲ)

በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የኢትዮጵያ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ሰራተኞችና ነጋዴዎች ክስ ተመሰረተባቸው

በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የኢትዮጵያ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ሰራተኞችና ነጋዴዎች ላይ ክስ መመስረቱን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ።

ክስ የተመሰረተባቸው ተጠርጣሪዎችም አቶ ክፍሌ አብርሃም፣ አቶ ደጉ ተካ፣ አቶ ዕቁባይ ዮሐንስ፣ አቶ ጥጋቡ ኃይለ ኢየሱስ እና አቶ ይስሐቅ ወልደጻድቅ ናቸው።

ክስ የተመሰረተባቸውም ከርብ ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ፈጽመዋል ተብለው በተጠረጠሩበት ከባድ የሙስና ወንጀል መሆኑ ታውቋል።

ከላይ የተጠቀሱት ተከሳሾች የኢትዮጵያ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት የርብ ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሲሠሩ ከነበሩት ከአቶ ሽመልስ ገብረሥላሴና አቶ አሳየኸኝ ወልዴ ጋር በጥቅም በመመሳጠር የተለያዩ የአካፋ ልኬት ያላቸውን ኤክስካቫተር ማሽነሪዎችን ለኢትዮጵያ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት የርብ ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት ለማቅረብና አገልግሎት ለመስጠት በሚል ሰበብ ያልተገባ ውል በመዋዋል ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመው ተገኝተዋል ተብሏል።

ስለሆነም ተከሳሾቹ በልዩ ወንጀል አድራጊነት በፈጸሙት ከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው መሆኑን የክስ መዝገቡ ያስረዳል።

ዓቃቤ ህግ በተከሳሾች ላይ የመሰረተው የክስ ጭብጥ በችሎቱ ለቀረቡ ተከሳሾች ተነቦ እንዲረዱት የተደረገ ሲሆን ፥ ተከሳሾቹም በቀረበው ክስ ላይ ያላቸውን አስተያየት እንዲሰጡ በተጠየቁት መሰረት የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል።

ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ ተፈጸመ የተባለው ወንጀል የዋስትና መብትን የሚያስከለክል በመሆኑ የዋስትና መብት ሊፈቀድላቸው አይገባም በማለት ተቃውሞውን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15 ወንጀል ችሎትም በፍርድ ቤቱ ያልቀረቡ ሌሎች ተከሳሾችን የፌደራል ፖሊስ በቀጣይ ቀጠሮ ይዞ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት ለግንቦት 07 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰትጥቷል።

(ኤፍ ቢ ሲ)

አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ በ26 የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ላይ ክስ ተመሰረተ


በክሶቹ ውስጥ 22ቱ ተከሳሾች በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን፥ በሌላ በኩል የቀድሞ የአገልግሎቱን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ አቶ አጽብሃ ግደይ፣ አቶ አሠፋ በላይ እና አቶ ሽሻይ ልዑል በተባሉ የቀድሞ የአገልግሎቱ የሥራ ኃላፊዎች ላይ በሌሉበት ክስ ዛሬ ሚያዚያ 29 ቀን 2011 ዓ.ም በከፍተኛ ፍርድ ቤት ልዴታ ምድብ ችሎት ይመሰረትባችዋል።

በአቶ ጌታቸው ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1/ (ሀ) (ለ) እና 407/1/ (ለ) (ሐ) እና 407/3/ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል መፈጸም እንዲሁም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና ለ እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 /1/ (ለ) እና (ሐ) እና 9/3/ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

በሌሎቹ ሁሉም ተከሳሾች ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1/ (ሀ) (ለ) እና 407/1/ (ለ) (ሐ) እና 407/2/ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል መፈጸም እንዲሁም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና ለ እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 /1/ (ለ) እና (ሐ) እና 9/2/ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ሥልጣንን ያለአግባብ መገልገል ክስ ሊቀርብባቸው የቻለው ተከሳሾች በግልጽ ከተሰጣቸው ሥልጣን ወይም ኃላፊነት አሳልፈው በመስራት እንዲሁም ሥልጣናቸው ወይም ኃላፊነታቸው የማይፈቅድላቸውን በተለይም ሥልጣን ወይም ኃላፊነት ሳይኖራቸው በሌላ ሰው መብት ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማሰብ በተበዳዮች ላይ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈጸማቸው ነው።

በአቶ ጌታቸው ላይ በንዑስ አንቀጽ 3 መሰረት ክስ ሊቀርብባቸው የቻለው

1ኛ) በሚኒስትር ማዕረግ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ጀነራል የነበሩ በመሆናቸው የኃላፊነት ወይም የሥልጣን ደረጃቸው ከፍተኛ በመሆኑ

2ኛ) ኃላፊነታቸውን የጣሱበት ዓላማ ከባድ በመሆኑ እንዲሁም

3ኛ) በሕዝቦች ወይም በተጎጂዎች ላይ የደረሰው ጉዳት ከባድ በመሆኑ የተፈፀመውን ወንጀል ከባድ ሊያደርገው በመቻሉ ነው።

ቀሪዎቹ ተከሳሾች በሙሉ በንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት ክስ ሊቀርብባቸው የቻለው ከላይ ለአቶ ጌታቸው ወንጀል ከባድነት ከተጠቀሱት ምክንያቶች ውስጥ ቢያንስ አንዱ ተሟልቶ በመገኘቱ ነው።

አቶ ጌታቸውን ጨምሮ በአራቱ ተከሳሾች ላይ በሌሉበት ክስ ሊመሰረት የቻለው ደግሞ ተከሳሾች የቀረቡባቸው ክሶች ከባድ በመሆናቸው በህጉ መሰረት በሌሉበት ክስ ሊቀርብባቸው የሚገባ ስለመሆኑም ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል በሚል በፌደራል ፖሊስ ወንጀል መርማሪዎች ላይ፤ በማረሚያ ቤት የሥራ ኃላፊዎች ላይ እንዲሁም በብሔራው መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎች ላይ ሲካሔድ የነበረው የወንጀል ምርመራ ሲካሔድ መቆየቱ ይታወሳል።

በዚሁ መሰረት ዓቃቤ ሕግ በወንጀል መርማሪዎች ላይ፤ በማረሚያ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች ላይ እንዲሁም በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ላይ በሶስት የተለያዩ መዝገቦች ክስ ተመስርቷል።

በመርማሪዎች ላይ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተከፈተው እና በማረሚያ ቤት ኃላፊዎች በነበሩት ላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተከፈቱት መዛግብት የከስ ሂደቱ ቀጥሎ ምስክር ለመስማት መቀጠራቸውም ይታወቃል።

(ኤፍ.ቢ.ሲ)