Category Archives: ህግ

ይህ ዓምድ ህግ ነክ ጉዳዮች ለግንዛቤና ለመረጃ ይረዳ ዘንድ የሚስተናገድበት ነው። ዓምዱ ቀደም ያሉ ብይኖችና የህግ አግባቦችን ያካትታል።

በከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ላይ ሰኔ 15 የተፈጸመው ግድያ ዓቃቤ ሕግንና ተጠርጣሪዎችን እያወዛገበ ነው

በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ በመከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹምና በጓደኛቸው ላይ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በተቀራራቢ ሰዓታት ውስጥ የተፈጸመው ግድያ፣ ዓቃቤ ሕግንና ከግድያው ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የታሰሩ ተጠርጣሪዎችን ማወዛገቡ ቀጥሏል፡፡

ግድያው በተፈጸመ ማግሥት ከሰኔ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በቁጥጥር ሥር ውለው በተለያዩ ጊዜያት ፍርድ ቤት ሲቀርቡ፣ የተጠረጠሩት ከግድያው ጋር በተያያዘና የሽብርተኝነት ሕግን አዋጅ ቁጥር 652/2001 በመተላለፍ በሽብር ተግባር ወንጀል ተጠርጥረው መሆኑን የሚናገሩት ቁጥራቸው ከ30 በላይ የሚሆኑት ተጠርጣሪዎች፣ ግድያውን በሚመለከት የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥት አመራሮች የተናገሩትና ያሰራቸው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የሚናገረው የተለያየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ከፍተኛ አመራሮች ግድያን በማቀነባበርና በመሳተፍ ተጠርጥረው፣ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበው በፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ 28 ቀናት የምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸው ቢፈቀድም፣ ፖሊስ በተሰጠው ጊዜ ምንም ዓይነት ማስረጃ ሊያቀርብባቸው ባለመቻሉ፣ ፍርድ ቤቱ ሰፊ ትንታኔ በመስጠት በዋስ እንዲለቀቁ ውሳኔ ሰጥቶ እንደነበር ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አስረድተዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በጠበቆቻቸው አማካይነት ነሐሴ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ባቀረቡት ክርክር እንዳስረዱት፣ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያቀረቡት የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዝርዝር ትንታኔ በመስጠት ለደንበኞቻቸው የጠበቀላቸውን ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብት፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያላግባብ ስለነፈጋቸው ነው፡፡ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ሕገ መንግሥታዊ የሆነውን የዋስትና መብት የነፈጋቸው፣ ተቋሙን በማይመጥንና የዳኝነትን ብቃት ግምት ውስጥ ሊያስገባ በሚችል ሁኔታ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይኼውም አንድ የፀረ ሽብር ተግባር ወንጀል ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረ ዜጋ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 20 (3) ድንጋጌ መሠረት ምርመራ ሊፈቀድበት የሚችለው 28 ቀናት ሆኖ ተደንግጎ እያለ፣ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በደንበኞቻቸው ላይ የተሰጠው የምርመራ ጊዜ 42 ቀናት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይኼ ደግሞ የሕጉን ድንጋጌ ከመጣሱም በላይ፣ ምንም ዓይነት ማስረጃ ያልቀረበባቸው ተጠርጣሪዎችን ከሕግ አግባብ ውጪ እንዲታሰሩ ማድረግ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ዓቃቤ ሕግ፣ የፖሊስ አባል፣ የአብን አመራሮችና አባላት፣ የተቋማት ሠራተኞችና ሌሎችም ሲሆኑ፣ በመዝገብ ቁጥሮች 181966፣ 181965፣ 182124፣ 182129 እና በመዝገብ ቁጥር 182150 ተካተው በአምስት መዝገቦች ከ30 በላይ ተጠርጣሪዎች የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔን በመቃወም በሰባት ጠበቆች ተወክለው ሰፊ ክርክር አድርገዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥትና የአማራ ክልል የመንግሥት አመራሮች በአማራ ክልል አመራሮች ላይ የተፈጸመው ግድያ ‹‹የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው›› እያሉ በይፋ ከዕለቱ ጀምሮ በመገናኛ ብዙኃን ጭምር ገልጸው እያለ፣ ደንበኞቻቸውን በሽብር ተግባር ወንጀል መጠርጠር እርስ በርሱ የሚጣረስና ሕዝብንም እምነት የሚያሳጣ መሆኑን ጠበቆቹ ገልጸዋል፡፡

ፖሊስ ደንበኞቻቸውን በሽብር ተግባር ወንጀል ጠርጥሯቸዋል ቢባል እንኳን፣ በተፈቀደለት የ28 ቀናት ጊዜ ውስጥ ማን በማን ላይና ምን ዓይነት ወንጀል እንደፈጸመ በመለየት በዝርዝርና በተናጠል ለፍርድ ቤት ማቅረብ እንዳለበት በሕጉ ተደንግጎ ቢገኝም፣ 28 ቀናት ቆይቶ ፍርድ ቤት ሲቀርብ ምንም ዓይነት የምርመራ ውጤት አለማቅረቡን አስረድተዋል፡፡

የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤትም የፖሊስ ምርመራ መዝገቦችን አስቀርቦ ከመረመረ በኋላ፣ ምንም ዓይነት ለሽብር ተግባር ወንጀል የጥርጣሬ መነሻ ነገር ባለማግኘቱ፣ ተጠርጣሪዎቹ ከ2,000 ብር እስከ 5,000 ብር በሚደርስ ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ ውሳኔ መስጠቱንም ገልጸዋል፡፡ ፖሊስ ‹‹በሽብር ተግባር ወንጀል ጠርጥሬያቸዋለሁ›› በማለት ላሰራቸው የአብን አባላት ያቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ማንን ነው የምትረዱት? ማነው ያሰማራችሁ?›› የሚሉና ‹‹ጠርጥሬያችኋለሁ›› ካለበት መነሻ ሐሳብ ጋር የማይገናኝ መሆኑንም ጠበቆቹ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የአዲኃን ሥልጠና ወስዳችኋል፣ ከእነ ዘመነ ካሴ ጋር ግንኙነት አላችሁ›› የሚሉ የግለሰቦች ወይም የተወሰነ ቡድን ፍላጎትን የሚያንፀባርቁ ጥያቄዎች እንጂ፣ ከሰኔ 15 ቀን የከፍተኛ አመራሮች ግድያ ጋር የሚያያዝ ምንም ዓይነት ምርመራ እንዳልተካሄደባቸውም አስረድተዋል፡፡

አንዳንዶቹ በተለይ ዓቃቤ ሕግ አቶ የወግሰው በቀለና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባልደረባና የልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ መርማሪ ዋና ሳጅን ሞገስ በቀለ፣ የባልደራስ ምክር ቤት አባል መሆናቸውን ደርሰንበታልና መረጃ ያቀብላሉ›› ከሚል ምርመራ በስተቀር፣ የሽብር ወንጀል ተሳትፏቸው ምን እንደሆነ ያቀረበው የጥርጣሬ መነሻ ማስረጃ እንደሌለም ገልጸዋል፡፡

‹‹የከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ዋስትና የከለከላቸው አቋም ይዞ ነው፤›› የሚሉት የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች፣ ይኼንንም ሊያስብላቸው የቻለው በዋስ እንዲወጡ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት እያንዳንዳቸው የ5,000 ብር ዋስትና ማቅረብ እንዳለባቸው ውሳኔ የተሰጠላቸው፣ አቶ የወግሰው በቀለና ዋና ሳጅን ሞገስ በቀለ፣ ዋስትናቸው ወደ 200,000 ብር ማሳደጉ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ዋስትና ከተፈቀደላቸው ሳምንት ቢሞላቸውም፣ አቅማቸውን ያላገናዘበ ዋስትና በመሆኑ ከእስር ሊለቀቁ እንዳልቻሉም አክለዋል፡፡ ሌላው ጠበቆቹ ያቀረቡት ክርክር ሕጉ ግልጽ ሆኖ ሳለ፣ ለምን ተለጥጦና ለተጠርጣሪ በማይጠቅም ሁኔታ እንደሚተረጎም እንዳልገባቸው ጠቁመው፣ ከሰኔ 15 ቀን የእነ ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ግድያ ጋር በተያያዘ፣ ‹‹የገዳዩ ሚስት ናት›› የተባለችና ከግድው ጋር ምንም ግንኙነት የሌላት ሴትም ታስራ እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡ ዳኞቹ የሚሠሩት ለህሊናቸውና ለሕግ ተገዥ ሆነው ቢሆንም፣ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአግባቡ የሰጠውን ውሳኔ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ያገደበትና ከሕጉ ውጪ የሥራ ቀናትን ብቻ በመቁጠር በአጠቃላይ 42 ቀናት የፈቀደበት ሒደት፣ ከሕግ አግባብ ውጪ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ፖሊስ ራሱ ጠይቆ የነበረው 28 ቀናት እንደሚበቃው ገልጾ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ 42 ቀናት መፍቀዱ ለምንና በየትኛው የሕግ አግባብ እንደሆነ ግልጽ አለመሆኑንም አክለዋል፡፡ አዴፓ ‹‹እርስ በርሳችን ተጠፋፋን›› እያለ ከ30 በላይ ንፁኃን ዜጎችን ማሰር፣ ተገቢ አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡ መፈንቅለ መንግሥት መሆኑ የተገለጸበትን ድርጊት የሽብር ተግባር ወንጀል በማለት ዜጎችን ያላግባብ ማሰር ሆን ተብሎ ሰብዓዊ መብታቸውን ላለማክበር የተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ጠበቆችን ጭምር በነፃነት እንዳይከራከሩና እንዳይናገሩ ጫና በማድረግ፣ በክርክሩ ወቅት ያነሷቸውን መከራከሪያ ሐሳቦች እንኳን እንዳልመዘገበላቸውም አስረድተዋል፡፡ በአጠቃላይ ደንበኞቻቸው ታስረው የሚገኙበት ጉዳይ እንኳን በሽብር ተግባር ወንጀል፣ በተራ ወንጀል  እንኳን ሊያስጠረጥር እንደማይችል የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በክርክራቸው አስረድተዋል፡፡

ከሰኔ 15 ቀን ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ግድያ ጋር በተያያዘ በሽብር ተግባር ወንጀል ተጠርጥረዋል ስለተባሉትና ይግባኝ ስለጠየቁት ተጠርጣሪዎች፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርቦ ምላሽ የሰጠው (የተከራከረው) የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መርማሪ ሳይሆን ዓቃቤ ሕግ ነው፡፡ በዕለቱ የቀረቡት ሁለት ዓቃቢያነ ሕግ እንዳስረዱት፣ እያንዳንዳቸው ተጠርጣሪዎች ከሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በፊት ሲደራጁ ቆይተው፣ በተለያዩ አቅጣጫዎች በመንቀሳቀስ ግድያው እንዲፈጸም አድርገዋል፡፡ ይኼ ሁኔታ በተፈጸመበትና ፖሊስ ስለሁኔታው በማጣራት ላይ እያለ፣ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተጠርጣሪዎቹ በዋስ እንዲወጡ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ድርጊቱን ‹‹ተራ የፖለቲካ ሽኩቻ ነው›› በማለት የዳኛውን ገለልተኛነት የሚያጠራጥር መሆኑንም አክለዋል፡፡ ዓቃቢያነ ሕጉ እንዳብራሩት የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የምርመራ መዝገቡን ወስዶ ለሳምንት ማቆየቱና አልመልስም በማለቱ፣ እጃቸው ላይ በነበረ ሰነድ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብለው፣ የተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብት እንዲታገድ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ በተለይ አራት ተጠርጣሪዎች በኅቡዕ ጦር እየመሩ እንደነበርና መረጃ ሲለዋወጡበት የነበረን ማስረጃ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጠይቀው በመጠባበቅ ላይ እያሉ፣ ዋስትና መፍቀድ ተገቢ አለመሆኑንም ዓቃቢያነ ሕጉ ተናግረዋል፡፡

በግለሰብ እጅ ሊገባ የማይችል የጦር ሜዳ መነጽር መገኘቱንም ገልጸዋል፡፡ በአዲስ አበባ በወታደራዊ አመራሮች ላይ ግድያ ሲፈጸም የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲቋረጥ ግዳጅ የተሰጣቸው፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሠራተኞች መያዛቸውንም ገልጸዋል፡፡ የጦር መሣሪያ መግዛቱንና 6,000 ጥይቶች ቢኖሩትም ከጎንደር እንዴት እንደሚያሳልፈው ምክክር ሲያደረግ የነበረ ተጠርጣሪና ሌሎችም፣ በኅቡዕ ተደራጅተው በእነማን ላይ ዕርምጃ እንደሚወስዱ ሥልጠና ጭምር የወሰዱ ተጠርጣሪዎች መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ይኼ ሁሉ ባለበት ገና በምርመራ ላይ እንደሆኑ እየገለጹ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዋስትና መፍቀዱ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ ከሰኔ 15 ከፍተኛ አመራሮች ግድያ ጋር በተያያዘ የሽብር ተግባር ስለመፈጸሙ ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ጋር እየሠሩ እያለ፣ የወንጀል ተግባሩን በመቀየር ዋስትና መስጠቱም ተገቢ አለመሆኑን ዓቃቢያነ ሕጉ ደጋግመው አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በመሀል፣ ‹‹በመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት በእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ላይ ለወንጀል ጥርጣሬ መነሻ የሚሆን የምርመራ ውጤት አቅርባችሁ ነበር?›› የሚል ጥያቄ ለዓቃቢያነ ሕጉ አቅርቦላቸው፣ ማን ከማን ጋር ግንኙነት እንደነበረው በቂ መጠርጠሪያ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ ቀሪ መረጃና ማስረጃ በመሰብሰብ ላይ እንደሆኑም ማስረዳታቸውን ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከባንክ፣ የባልደራስ ምክር ቤትን እንደ ሽፋን በመጠቀም ወንጀል መፈጸማቸውን ለማሳየት ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መረጃ መጠየቃቸውን ቢገልጹም፣ ፍርድ ቤቱ እንዳልተቀበላቸው አስረድተዋል፡፡

ከፍተኛው ፍርድ ቤት ግን ያቀረቡትን የይግባኝ አቤቱታ በሚገባ ከተመለከተ በኋላ፣ ዋስትናውን እንደሻረውም አክለዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በመቀጠል፣ ‹‹እናንተ (ዓቃቢያነ ሕጉ ወይም ፖሊስ) 28 ቀናት የምርመራ ጊዜ ጠይቃችሁ ከፍተኛው ፍርድ ቤት እንዴት ከዚያ በላይ ሊፈቅድ ቻለ?›› በማለት ሲጠይቃቸው፣ ችሎቱ የበዓል ቀናትን ትቶ የሥራ ቀናትን ብቻ በመቁጠር መስጠቱን ጠቁመው ስህተት ከሆነ ሊታረም እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በመቀጠል፣ ‹‹ከሰኔ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በምርመራ ላይ ከሆናችሁ እንዴት እስካሁን አልጨረሳችሁም? አሁንስ በምን ላይ ናችሁ?›› የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸው፣ ተጠርጣሪዎቹ ሲዘጋጁ የከረሙት ከጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ ዋና ከተማ በአሶሳና በአዲስ አበባ የተፈጸመውን ሁሉ ማጣራት ስላለባቸው፣ እየሠሩና የጠየቁት ለመረጃ እስከሚመጣላቸው እየጠበቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በተሰጣቸው ድጋሚ የመከራከሪያ ዕድል እንዳስረዱት፣ ዓቃቤያነ ሕጉ የምርመራ መዝገቡ በመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ስምንት ቀናት በዳኛ ዕግድ መቆየቱን ለችሎቱ መግለጻቸው፣ ከአንድ ከፍተኛ የሕግ ተቋም የማይጠበቅ ምላሽ ከመሆኑም ባለፈ ግምት ውስጥ የሚከት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ፖሊስ የራሱን ዋና የምርመራ መዝገብ ይዞ ለፍርድ ቤት የሚያቀርበው ደግሞ ግልባጩን (ኮፒ) መሆኑን ጠቁመው፣ መዝገቡ ዳኛው ዘንድ ስምንት ቀናት መቆየቱንና ‹‹አልሰጥም አሉኝ›› የሚል ሰበብ ማቅረብ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሌላው ዓቃቢያነ ሕጉ የምርመራ መዝገቡ አካል ያልሆነን ጉዳይ ‹‹አሶሳ ከተማ የተፈጸመን ድርጊትም እየመረመርኩ ነው›› ማለቱ የማይገናኝ ነገር ለማገናኝት መሞከር መሆኑንም አክለዋል፡፡ የጦር ሜዳ መነጽር ይዘው ተገኝተዋል በማለት ዓቃቢያነ ሕጉ ተጠርጣሪዎቹን ለመወንጀል ያደረገው ጥረት፣ ‹‹መነጽር አይደለም ታንክ ይዘው ቢገኙ ሽብር ነው ማለት ነው?›› በማለት ጠይቀው፣ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን አስቀርቦ እንዲያይላቸው ጠይቀዋል፡፡ ተገኘ የተባለው የጦር ሜዳ መነጽር የዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያና ከመምህር ቤት የተገኘ መሆኑንም አክለዋል፡፡ በኅቡዕ ተደራጅተው ጦር ሲመሩ ነበር የተባሉት ደንበኞቻቸው ጫማ የሚጠርጉ ሊስትሮዎች፣ የቤት ሠራተኞችና የፖለቲካ ድርጅት አባላት መሆናቸውንም አክለዋል፡፡

ግድያው ሰኔ 15 ቀን ተፈጽሞ ደንበኞቻቸው ሰኔ 16 ቀን መያዛቸው የሚገርም እንደሆነ የገለጹት ጠበቆቹ፣ ይኼ የሚያሳየው እነሱን ለመያዝ ዝርዝር ተይዞና ቀደም ብሎ ዝግጅት መኖሩ የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሽብር ተግባር ወንጀል አያስቀጣም ሳይሆን፣ በአዋጅ ቁጥር 652/2011 አንቀጽ (19) መሠረት ሊያስጠረጥራቸው የሚችል ማስረጃ እንዳልተገኘባቸው ወይም ፖሊስ በተሰጠው የ28 ቀናት የምርመራ ጊዜ ሊያቀርብ እንዳልቻለ መግለጹ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ዓቃቢያነ ሕጉ ተጠርጣሪዎቹ የጦር ሥልጠና ሲያደርጉ እንደነበር መግለጻቸው ስህተት መሆኑን ጠበቆቹ ጠቁመው፣ መንግሥት ራሱ በጀት መድቦ ሲያሠለጥናቸው የነበሩ መሆናቸውን አክለዋል፡፡ በአጠቃላይ ፖሊስ እንኳን ማስረጃ ሊያቀርብባቸው ቀርቶ ቃላቸውን እንኳን እንዳልተቀበላቸውም ጠቁመዋል፡፡

ተጠርጣሪው ዓቃቤ ሕግ አቶ የወግሰው በቀለ ለሥር ፍርድ ቤቶች ከታሰረ 50 ቀናት እንደሞላው ሲያስረዳ፣ ፍርድ ቤቱ ለምን ምርመራ እንዳልጨረሰ ፖሊስን ሲጠይቀው፣ የባልደራስ ምክር ቤት አባል መሆኑን ስለደረሰበት እያጣራ መሆኑን እንደገለጸም አስታውሰዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለነሐሴ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ሪፖርተር (ታምሩ ጽጌ)

በእነ ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ የምርመራ መዝገብ ላይ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ

የባህርዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ አቃቤ ህግ በእነ ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ የምርመራ መዝገብ የቀረበውን ይግባኝ ለማየት ለነሃሴ 21 ቀን 2011 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጠ፡፡

ፍርድ ቤቱ በትናንት ውሎው አቃቤ ህግ በእነ ተፈራ ማሞ የምርመራ መዝገብ ላይ ያቀረበውን የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ይግባኝ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለዛሬ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

በዛሬው ውሎው አቃቤ ህግ በተጠርጣሪዎቹ የምርመራ መዝገብ ላይ የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ይግባኝ ውሳኔ ለመስጠት ያቀረበው መረጃ የተበጣጠሰ በመሆኑ የምርመራ መዝገቡ ተደራጅቶ ለነሃሴ 21 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲቀርብ አዟል፡፡

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው በምርመራ መዝገቡ መረጃ የተገኘው አራት ሰዎች ላይ ሆኖ ሳለ ደንበኞቻችን ያለአግባብ እየተጉላሉ ነው ሲሉ ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡

የብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ማሞ እና ሌሎች ሁለት ተጠርጣሪዎች የሂሳብ ደብተሮች ከህግ አግባብ ውጭ መታገዳቸውንም ገልጸዋል፡፡

አቃቤ ህግ በበኩሉ የደንበኞች የሂሳብ ደብተሮች መያዛቸውን እንደማያውቅ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

ግራ እና ቀኙን የተመለከተው ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪዎች የሂሳብ ደብተሮች እና ከምርመራ መዝገቡ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ቁሳቁሶች እንዲመለሱላቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በናትናኤል ጥጋቡ – FBC

የአውሮፓውያኑ የቅኝ ግዛት መርዝ የሚያፋጃቸው ካሜሮናውያን

ሕዝቦቿን በባርነት ለመግዛትና የተፈጥሮ ሀብቷን ለመዝረፍ አፍሪካን በቅኝ ግዛት የተቀራመቱት አውሮፓውያን አህጉሪቷን በወንጌል ቃል ለማቅናትና ለመጎብኝት በሚል ሰበብ ወደ ቀየው ዘልቀው የገቡ ሲሆን፤ በሂደት ግን የአፍሪካውያንን የሰው ኃይልና ተፈጥሮ ሀብትን በመዝረፍ ታላቅ ስብራት ጥሎ ያለፈና ይሄ ነው ተብሎ ሊገመት የማይችል ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ታሪካዊ ቀውስና ክስረት ያጎናጸፈ መራር የጨለማ ዘመን ታሪክ ሆኖ አልፏል።

አፍሪካውያን ወይም በአጠቃላይ ጥቁር ህዝብ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ስብዕና የላቸውም ብለው የሚያምኑት አውሮፓውያን አፍሪካን በቅኝ ግዛት በተቀራመቱበት ዘመቻ፤ ጥቁር ህዝቦችን ከሰውነት ተራ በማውረድ በገዛ መሬታቸው ባይተዋር አድርገዋል። አፍሪካዊያንም የተፈጥሮ ሀብታቸው ተዘርፎ፤ ባህላቸው ተንቆ፤ ለዘመናት ያፈሩት ስልጣኔያቸው፤ ታሪካቸውና ቅርሳቸው የእነርሱ እንዳልሆነና “ጥቁር ህዝብ እንዲህ ዓይነት የረቀቀና የመጠቀ ስልጣኔ ባለቤት አይሆንም” በሚል እኩይ አስተሳሰብ ቅርሶቻቸውንና ታሪካቸውን ወደ አውሮፓ ቤተ-መዘክሮችና ዐውድ ርዕዮች ተግዘው ለእነርሱ ከፍተኛ የገቢ ማስገኛ ምንጮች ሲሆኑ፤ እነርሱ በገዛ ታሪካቸውና ቅርሳቸው ባይተዋር ሆነው ታሪክና ቅርስ አልባ የሆኑበትን ዘግናኛ የመከራና የሰቆቃ ዘመን በአፍሪካ ትልቅ የታሪክ ጠባሳ ጥሎ አልፏል።

በዚህ ግፍና መከራ ኅሊናቸው የቆሰሉ አፍሪካውያን ይሄን ግፈኛ ስርዓት ከጫንቃቸው አሽቀንጥሮ ለመጣል ሲሉ ነበር በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ የጸረ- ኮሎኒያሊስት እንቅስቃሴ ያቀጣጠሉት፤ በተለይም ደግሞ በደቡብ አፍሪካ በነበረው የአፓርታይድ ዘረኛና ከፋፋይ ሥርዓት ክፉኛ የተቆጡና የህዝባቸው ውርደትና ሰቆቃ በእጅጉ እንቅልፍ የነሳቸው አፍሪካውያን፤ ይህን ሥርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ታሪክ ሊያደርጉት ከዛሬ መቶ ዓመት በፊት የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ African National Congress Party (ANC) ን አቋቋሙ።

ከዚህ ፓርቲ መቋቋም በኋላ በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ በርካታ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ተላቅቀው ነጻነታቸውን አውጀዋል። ከነዚህ አገራት መካከል ካሜሮን በፈረንሳይና በእንግሊዝ ለሁለት ተከፍላ በቅኝ ግዛት ስር ወድቃ የነበረች ሲሆን፤ አገሪቱ ከነዚህ አገራት የቅኝ ግዛት የመከራና የግፍ ይዞታ ወጥታ እኤአ በ1961 ሁለቱ ግዛቶች ተጣምረው አንድ አገር መስርተዋል።

ምንም እንኳን ዛሬ ላይ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ግዛት ቢላቀቁም ቅሉ፤ አውሮፓዊያኑ ዛሬም በእጅ አዙር በኢኮኖሚና በፖለቲካው እያደቀቁ አፍሪካን በመዳፋቸው ስር አድርገው ይገኛሉ። እንዲሁም ትናንት አውሮፓውያን አፍሪካን በቅኝ ግዛት ተቆጣጥረውበት በነበረው ወቅት፤ ለአገዛዝ እንዲያመቻቸው ባሰመሩት ድንበር፤ እንዲሁም ባሰረጹት ቋንቋ እና ኃይማኖት ዛሬም አያሌ አፍሪካውያን ወንድማማቾች ጦር እየተማዘዙ ህይወታቸው ያልፋል። በመሆኑም፤ አውሮፓውያኑ በአህጉሪቷ በረጩት የመለያየት መርዝ የአህጉሪቷ ህዝቦች መግባባትና መተባበር ተስኗቸው በስልጣኔና በቴክኖሎጂ ኋላቀር ሆነው በድህነትና በኋላ ቀርነት እንዲማቅቁ ሆነዋል።

በአህጉሪቷ ይህ የአውሮፓውያኑ የመለያየት መርዝ ጥላው ያጠላባት ካሜሮን፤ ህዝቦቿ ከፈረንሳይና ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የተላቀቁበትን 56ኛ ዓመት እኤአ ጥቅምት 2017 ባከበሩበት ወቅት፤ በተለይ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበሩት የአገሪቱ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ህዝቦች ብዙ የህዝብ ቁጥር ባለው የአገሪቱ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝብ “መድልዎና መገለል ይደርስብናል” በማለት የእንግሊዘኛ ቋንቋ በሚነገርባቸው ግዛቶች በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች የተቃውሞ ድምጽ አሰምተው ነበር።

በወቅቱም ተቃውሞው ተቀጣጥሎ በሁሉም የእንግሊዝኛ ተናጋሪ በሆኑ የካሜሮን ግዛቶች የተቃውሞ ሰልፍ የተካሄደ ሲሆን፤ ሰልፈኞቹም ከተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት መስሪያ ቤቶች መገለል ደርሶብናል፤ እንዲሁም ፈረንሳይኛ ቋንቋን እንድንናገር የአገሪቱ ህግ ግዴታ ጥሎብናል። በአንድ አገር አንድ መንግስት ሁሉንም ዜጎች በእኩል አይን ባለማየቱ በአገሪቱ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል የለም በሚል ለዓለም ህዝብ ድምጻቸውን አስተጋቡ።

በኋላ ላይ የተቃውሞ ሰልፉ መልኩን ቀይሮ ነጻነትን እንፈልጋለን የሚሉ ተምሳሌታዊ የሆነ የነፃነት አዋጆችንም በዚሁ አጋጣሚ ተቃዋሚዎች ያሰሙ ጀመር። ተቃዋሚ ሰልፈኞቹም በዚህ ሳያበቁ የእንግሊዘኛ ተናጋሪ በሆኑ ግዛቶች በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች ይወክለናል ያሉትን ሰንደቅ ዓላማ አውለበለቡ።

በተቃራኒው የአገሪቱን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝብ ተቃውሞችንና የነጻነት ጥያቄዎችን በመንቀፍ መንግስትን በመደገፍ “አንድ ካሜሮን” በሚል መፈክር በዱዋላ ከተማ የአገሪቱ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ዜጎች ለተቃውሞ የወጡ ሲሆን፤ በወቅቱ በሁለቱ ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል በተደረገ ግጭትና መንግስት የተገንጣይ አመለካከት አለባቸው ብሎ ባመነባቸው ዜጎች ላይ በወሰደው እርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች ህይወታቸውን ሲያጡ፤ ከ500 ሺህ በላይ ህዝብ ከሚኖሩበት ቀየ ተፈናቅሏል።

እንዲሁም፤ ከተቃውሞ ሰልፉ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ የካሜሮን መንግስት ህዝባዊ የሆኑ ስብሰባዎችን እንዲሁም ጉዞዎችን የእንግሊዝኛ ተናጋሪ በሆኑ የካሜሮን ግዛቶች አግዶ የነበረ ቢሆንም፤ ህዝባዊ አመጽና ሁከት በእንግሊዝኛ ተናጋሪ በሆኑ የአገሪቱ ግዛት በማየሉ የአገሪቱ መንግስት ብዙ ቁጥር ያላቸውን ተቃዋሚዎችን ዘብጥያ አውርዷል። የካሜሮን ወታደሮችም ብዙዎቹን ገድለዋል። በዚህም የሰብአዊ መብት አቀንቃኞች መንግስት ሰፊ ቁጥር ላላቸው የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ዜጎች ያደላል በሚል የኮነኑ ሲሆን፤ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾቹም የታሰሩ ሰዎች እንዲለቀቁ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው እየተቃወሙ ይገኛሉ።

ይህ ለመብት የተጀመረው እንቅስቃሴ አሁን ላይ እስከ መገንጠል ጥያቄ ተቀይሯል። በዚህም፤ በማዕከላዊቷ አፍሪካ አገር ካሜሮን በሁለት እንግሊዝኛ ተናጋሪ ግዛቶች ውስጥ እኤአ ጥቅምት 2017 ጀምሮ የመገንጠል ጥያቄ መቀንቀን የጀመረ ሲሆን፤ የመገንጠል ጥያቄውንም በወቅቱ ያቀጣጠሉት አዩክ ታቤ የተባለ ሰው ነበር። እርሱም ራሱን የ“አምባዞኒያ”(በአገሪቱ በሰሜንና በደቡብ ምዕራብ የሚገኙ የሁለቱ የእንግሊዝኛ ተናጋሪ ግዛቶች) ፕሬዚዳንት እኔ ነኝ በማለት ሲጠራ ቆይቷል። ይህ ሰው ግዛቷ በዓለም ህዝብ እውቅና ባይቸራትም ራሷን የቻለች አገር ናት በማለት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።

ነገር ግን፤ በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ እለት ኢስት አፍሪካ በድረገጹ እንዳስነበበው፤ ይህ ራሱን የአንግሎፎን መሪ ነኝ ብሎ የሚጠራው ሰው በአገሪቱ ወታደራዊ ፍርድ ቤት “በሽብርተኝነት እና በመገንጠል” ክስ የቀረበበት ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ እርሱንና ዘጠኝ ግብር አበሮቹን ጨምሮ የእድሜ ልክ እስራት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል ብሏል።

በአገሪቱ የህግ ባለሙያ የሆኑት ማርቲን ሉተር አቼት ለኤ ኤፍ ፒ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ “በአገሪቱ ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ፍራንኰፎን ሲባሉ እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች አንግሎፎን ተብለው ይጠራሉ። አንግሎፎኖች በአገሪቱ ዝቅተኛውን ቁጥር የሚይዙ ሲሆን፤ 24 ሚሊዮን ከሚሆነው የካሜሮን ህዝብ አምስት በመቶውን ይይዛሉ። እነዚህ ህዝቦችም በአገሪቱ በሰሜንና በደቡብ ምዕራብ ግዛቶች የሚገኙ ሲሆን፤ ከፈረንሣይ ተናጋሪ ግዛት ጋር የተካተቱት ከስድስት አስርት ዓመታት በፊት ካሜሮን ነጻነቷን ባወጀችበት ወቅት ነው።

“ነገር ግን አንግሎፎኖች ፍትሃዊ የሆነ የሀብት ክፍፍልና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ፤ እንዲሁም በትምህርት እድል እና በኢኮኖሚ ተጠቃሚነታችን በፍራንኮፎን የፖለቲካ የበላይነት በመያዙ ፍትሃዊ ፍርድና የሀብት ክፍፍል አላገኝንም በሚል ለዘመናት እየተቃወሙ ይገኛሉ። በመሆኑም እራሱን የአንግሎፎኖች ነጻ አውጪ ነኝ ብሎ የሚጠራው አዩክ ታቤ፤ የአንግሎፎኖች መሪና የአምባዞኒያ አስተዳዳሪ እኔ ነኝ ብሎ አውጆ አገሪቱን ለመገንጠል ሲንቀሳቀስ ነበር፤” ብለዋል።

ይህ ሰው እራሱን “የአንግሎፎኖች መሪና የአምባዞኒያ አስተዳዳሪ እኔ ነኝ” ብሎ ቢያውጅም፤ የካሜሮን መንግሥት የመገንጠል ጥያቄዎችን ውድቅ በማድረጉ በዓለም ዙሪያ ለዚህ ሰው የተሰጠው እውቅና አልነበረም። በመሆኑም፤ የአገሪቱ ወታደራዊ ፍርድ ቤት እራሱን የአምባዞኒያ አስተዳዳሪ ነኝ ብሎ የሚጠራውን ይህን ሰው በአቀረባበት የሽብርተኝነትና የመገንጠል ክስ ዘጠኝ ተከታዮቹን ጨምሮ ጥፋተኛ ሲል በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ቀጥቷል ብለዋል።

ነገር ግን፤ ባለፈው ወር የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የአገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች ግድያዎችን እና ከመጠን በላይ ኃይልን መጠቀምን ጨምሮ በዜጎች ላይ “አስነዋሪ ወንጀሎች” ፈጽመዋል፤ ሲሉ የከሰሱ ሲሆን፤ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾቹም ይሄንን የወታደራዊ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ “የነጻነትን ጥያቄ ለማፈን የተደረገ ፍርድ” ሲሉ አጣጥለው አውግዘውታል።

ካሜሮን በእንግሊዝና በፈረንሳይ ለሁለት ተከፍላ በቅኝ ግዛት የተገዛች ሲሆን፤ እኤአ በ1961 ሁለቱ ግዛቶች ተጣምረው አንድ አገር መስርተዋል። ሆኖም የእንግሊዝኛ ተናጋሪዎች ብዙ የህዝብ ቁጥር ባለው የፈረንሳይኛ ተናጋሪ መድልዎ ይደርስብናል በሚል እራሳቸውን ችለው አገር ለመመስረት እየታገሉ ይገኛሉ።

 አዲስ ዘመን ነሀሴ 17/2011

ሶሎሞን በየነ

ለአንድ ዓመት ፖሊስ ሲያሳድደው የነበረው የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ በቁጥጥር ስር ዋለ

ከፍርድና ከህግ በመሸሽ ለአንድ ዓመት ራሱን ሸሽጎ የነበረው የቀድሞው የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ በፖሊስ ቁጥጥር ሰር መዋሉን የመንግስት ሃላፊዎች አስታወቁ።

ራሱን ሸሽጎ የነበረው ከንቲባ ቴዎድሮስ ገቢባ ከሰኔ 05 እስከ ሰኔ 12 ቀን 2010 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ የወላይታና ሲዳማ ብሔሮችን በማጋጨት ለሰው ሕይወት መጠፋት እና ንብረት መውደም ምክንያት በመሆኑ፣ የዕርስ በርስ ግጭት በማነሳሳትና በመጠንሰስ በዋና ወንጀል አቀነባባሪነት ተከሶ በተገኘበት በህግ ጥላ ስር እንዲውል የፍርድ ቤት ማዘዣ የተቆረጠበት ተጠርጣሪ ነበር።

33 ሰዎች በተከሰሱበት የክስ መዝገብ ለአንድ ዓመት በፖሊስ ሲፈለግ የነበረው የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ቴድሮስ ገቢባ በትናንት እለት በቁጥጥር እንደዋለ ከመገለጹ ውጪ እንዴትና የት እንደተያዘ የመንግስት ሃላፊዎች አላብራሩም።

የፌዴራል ፖሊስ ባደረገው ክትትል ከዓመት በሁዋላ ነሃሴ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ለህግ የተንበረከከው ቴዎድሮስ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 13ኛ የወንጀል ችሎት ሆሳዕና ተዘዋዋሪ ችሎት መቅረቡን የመንግስት ሚዲያዎች አስታወቀዋል።

የፌደራል ፖሊስን ወደ “ማፊያነት” የሚቀይረው አዋጅ!

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንን እንደገና ለማቋቋም የወጣ ረቂቅ አዋጅ (ለአስተያያት የቀረበ – ረቂቅ አዋጁን ይህን ማያያዣ በመጫን ማውረድ ይቻላል)

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንን እንደገና ለማቋቋም የወጣውን ረቂቅ አዋጅ ለማዘጋጀት የሚከተሉት ሁኔታዎች በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፦

 • የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን እንዲሁም ህገ መንግስቱን መሠረት አድርገው የሚወጡ ሕጎችን እና ኢትዮዽያ የተቀበለቻቸውን አለምአቀፍ ስምምነቶች የማክበርና የማስከበር ተልዕኮውን በተሻለ ሁኔታና ብቃት በመወጣት የዜጎችን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስከበር እንደገና ማደራጀት አስፈላጊ በመሆኑ፤
 • በተለያዩ ተቋማት ሲሰሩ የነበሩትን ተልዕኮዎች ማለትም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የገቢዎች ሚኒስቴር፤ በፌዴራል የስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲሁም በንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ሲሰሩ የነበሩ የምርመራ ስራዎች ለአገልግሎት አሰጣጥና ለቁጥጥር አመች ይሆን ዘንድ በአንድ ማእከል ማለትም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እንዲከናወኑ በመንግስት በመወሰኑ እና በኮሚሽኑ አዋጅ ማካተት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
 • የኮሚሽኑ ተልእኮ እየሰፋ በመምጣቱ እና በሀገራችንና በአካባቢው ሀገራት ያለውን ነፃ የገበያ ውድድር የሚያቀጭጨውን ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድ የሚቆጣጠር የተጠናከረ የጉምሩክ፤የቱሪዝም፤ የድንበር ፖሊስ እንዲሁም የምድር ባቡርና የማዕድን ደህንነት ጥበቃ ለማረጋገጥ ይህንን የሚመጥን የፖሊስ ሀይል ማደራጀትአስፈላጊ በመሆኑ፤
 • የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፌደራል ፖሊስ ተጠሪነት ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሰላም ሚኒስቴር እንዲሆን በአዋጅ ቁጥር በ1097/2011 በመወሰኑ ይህንንም በኮሚሽኑ አዋጅ ማካተት አስፈላጊ በመሆኑ፤
 • እንዲሁም በሀገራችን የመጣውን ዙሪያ መለስ ለውጥ እና የደረስንበትን የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ እድገት በሚመጥን መልኩ ሕብረተሰቡን በእኩልነት የሚያገለግል፣ በፖሊሳዊ ሥነ-ምግባሩ የታነፀ፤ ብቃትና ጥራት ያለው አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል የፖሊስ ሰራዊት ለማደራጀትና ለማዘመን የተቋሙን ስልጣንና ሀላፊነት በዚያው ልክ ማሻሻልና ሊካተቱ የሚገባቸውን ማካተት አስፈላጊ በመሆኑ፤
 • በአጠቃላይ የሀገርና የህዝብ ደህንነትና ሠላምን ማስፈን፤ አገራዊ ልማትን ለማፋጠን ዘላቂ ሰላምና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተቋሙን ህግና አደረጃጀት ከለውጡ ጋር ማስተካከል አስፈላጊ በመሆኑ፤
 • በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 55(1) መሠረት የሚከተለው ታውጇ፡፡

በአዋጁ የመጀመሪያ ክፍል የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንን እንደገና ለማቋቋም የወጣ አዋጅ ቁጥር … “በኢትዮጵያ የግዛት ወሰን ሆኖ በፌደራል መንግስቱ ስልጣን ስር በሚወድቁ ፖሊሳዊ ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚ ይሆናል” ተብሎ ተደንግጓል። በአዋጁ ሁለተኛ ክፍል ደግሞ “የኮሚሽኑ ዋና መስሪያ ቤት በአዲስ አበባ ከተማ ሆኖ እንደ አስፈላጊነቱ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን በማንኛውም የኢትዮጵያ ግዛት ሊያቋቁም ይችላል” በሚል ይደነግጋል።

በአዋጁ አንቀፅ 7 ስር ኮሚሽኑ የህብረተሰቡን ፍላጎትና ተሳትፎ ያረጋገጠ መረጃ መር ወንጀል የመከላከል መርህን ተከትሎ የሚሰራ እንደሆነ በመጥቀስ ከዘረዘራቸው ሥልጣንና ተግባራት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡-

 • 14) የሽብርተኝነት ድርጊት ሊፈፀም እንደሚችል ለመጠርጠር በቂ ምክንያት ሲኖርና ድርጊቱንም ለመከላከል ድንገተኛ ፍተሻ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ሲታመንበት በተጠረጠረው አካባቢ የተገኙ ተሽከርካሪዎችና እግረኞችን በማስቆም ድንገተኛ ፍተሻ ያደርጋል፤ ተጠርጣሪ ሰዎችና ማስረጃዎችን በመያዝ ይመረምራል፤
 • 15) በሽብርተኝነትና ሌሎች በፌደራል ፍርድ ቤቶች ስር በሚወድቁ ወንጀሎች ድርጊት የተጠረጠሩ ግለሰቦችንና ቡድኖችን በፍርድ ቤት ትእዛዝ በማንኛውም ክልል ገብቶ የመያዝ ስልጣን አለው፡፡
 • 16) የሀገርን ብሔራዊ ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመመርመር የሚረዳ መሆኑ የታመነበትን መረጃና ማስረጃ ከማንኛውም ሰውና ተቋም የመውሰድ ስልጣን ይኖረዋል፤
 • 29) በፌዴራሉ መንግሥት ሲታዘዝ በክልሎች ጣልቃ በመግባት ሕግና ሥርዓትን ያስከብራል ዝርዝሩ በመመሪያ ይወሰናል፤
 • 37) ለሥራ ክፍሎቹና ለፖሊስ አባላትና ሲቪል ሰራተኞች አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ቢሮዎች፤ ካምፖችና የመኖሪያ ቤቶች እንዲገነቡ ያደርጋል ዝርዝሩ በደንብ ይወሰናል፤

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀኔራሉን ስልጣንና ተግባር በሚደነግገው አንቀፅ 9 ንዑስ አንቀጽ (2) የሚከተሉት ይገኙበታል።

 • ሠ. በሽብርተኝነትና በሙስና ወንጀል እንዲሁም በሀገር ደህንነት ላይ ከፍተኛ ሚስጥር በማባከን የተጠረጠሩ ግለሰቦችን የሂሳብ ስቴትመንት እንዲመረመር እንዲሁም ካለፍርድ ቤት ትእዛዝ ከ7 ቀናት ላልበጠ ጊዜ እንዲታገድ ትእዛዝ ይሰጣል፣ አስፈላጊውም ሲሆን የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች እንዲጠለፉ ያደርጋል፣
 • ረ. አስፈላጊ በሆነ ወቅትና ሁኔታ ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ በአንድ አካባቢ ወይም በሁሉም አካባቢ ድንገተኛ ፍተሻ እንዲደረግ ሊያዝ ይችላል፣
 • ቸ. ኮሚሽኑ የወንጀል መከላከልና መመርመር ሀላፊነቱን እንዳይወጣ ሊያደናቅፍ የሚችል ሚስጥራዊ የሆኑ የሂሳብ መዛግብትና ሰነዶች፤ የክፍያ ማስረጃዎችን ለማንኛውም አካል እንዳይገለፁ ሊያደርግ ይችላል፤ ዝርዝሩ በመመሪያ ይወሰናል፤

የኮሚሽኑ አስተዳደር አስመልክቶ በአዋጁ ክፍል ሶስት ስር ከተደነገጉት መካከል በአንቀፅ 17 (ለ) እያንዳንዱ የፖሊስ አባል ከተመረቀበት ጀምሮ 7 አመት ለተቋሙ የማገልገል ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል። በዚያው ክፍል አንቀፅ 18 መሠረት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፌደራል ፖሊስ ውስጥ አገልግሎት ላይ የሚገኝ የፖሊስ አባል አግባብ ባለው የውስጥ ደንብ እና መመሪያ መሠረት ቀለብ፣ የመኖሪያ ቤት፤ የደንብ ልብስ፣ የመጓጓዣና የህክምና አገልግሎት በነፃ የማግኘት መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡
ከክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች ጋር ስለሚኖር ግንኙነትን የሚደነግገው አንቀፅ 24 የሚከተሉትን ንዑስ አንቀፆች አካትቷል፦

 1. ኮሚሽኑ እና የክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች የሚኖራቸው አደረጃጀት እንደተጠበቀ ሆኖ በመካከላቸው የሚኖረውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል የጋራ ጉባኤ ያቋቁማሉ፡፡
 2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) መሠረት የሚቋቋመው የጋራ ጉባኤ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ሰብሳቢነት ይመራል፡፡
 3. የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽኖች ተጠሪነታቸው ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የኮሚሽነሮች የጋራ ጉባኤው አባል ይሆናሉ፡፡

በአንቀፅ 24 ንዑስ አንቀፅ 3 መሠረት የሚቋቋመው “የጋራ ጉባኤው” ያሉትን ሥልጣንና ተግባራት አስመልክቶ በአንቀፅ 25 ከተዘረዘሩት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

 • ሀ) በፖሊሳዊ ሙያና ሥነ-ምግባር የታነፁ አባላትን ያቀፈና በተገቢው ቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊ የፖሊስ ተቋም በየክልሉ የሚገነባበትን ሁኔታ ያመቻቻል፤
 • ሐ) በክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች ሊኖር የሚገባውን አደረጃጀት እና ትጥቅ በተመለከተ ይወስናል፣ ይከታተላል፣
 • ቀ. ከክልሎች አቅም በላይ በሆኑ ጉዳዮች ኮሚሽኑ በመንግሥት ውሳኔ መሠረት በክልሎች ውስጥ ጣልቃ ገብቶ በሚሠራበት ወቅት የሚመለከታቸው የክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች ትብብር የማድረግ ግዴታቸውን በተገቢው መወጣታቸውን ይከታተላል፣ ውሳኔ በማስተላለፍ ለሚመለከተው አካል ያቀርባል፡፡
 • በ. በኮሚሽነሮች ጉባኤ የተወሰኑ ውሳኔዎች በሁሉም የፖሊስ ኮሚሽኖች ተግባራዊ መደረጋቸውን ይገመግማል፣ በክፍተቶቹ ላይ አቅጣጫ ያስቀመጣል፣ ለሚመለከተው የመንግስት አካልም ያቀርባል፣

በመጨረሻም ረቂቅ አዋጁ በአንቀፅ 27 “ስለ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽኖች” እንደሚከተለው ይደነግጋል፦

 1. የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ፖሊስ ኮሚሽኖች ተጠሪነት ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ሆኖ እንደገና በዚህ አዋጅ ተቋቁመዋል፤
 2. በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (1) የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ኮሚሽኑ በሚሰጠው ውክልና መሠረት ተጠሪነታቸው ለየከተሞቻቸው አስተዳደር እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል፡፡
 3. የከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽኖቹ ዓመታዊ ዕቅዳቸውንና የሥራ አፈፃፀማቸውን ሪፖርት ለኮሚሽኑና ለየከተሞቻቸው አስተዳደር ያቀርባሉ፤ ሆኖም በጀታቸው በየከተሞቻቸው አስተዳደር ም/ቤቶች ይወሰናል፡፡
 4. የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽኖች የበላይ ኃላፊዎች በሚኒስትሩ አቅራቢነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሾሙ ሆነው የሁለቱም ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽኖች ምክትል ሀላፊዎች በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል አቅራቢነት በሚኒስትሩ ይሾማሉ፡፡

ethiothinkthank

አብዲ ኢሌን አስመልክቶ የተሰራጨው ዜና ሃሰተኛ መሆኑ ተጠቆመ፤ ዜናውን ያሰራጨው ሚዲያ እንዲያስተባብል ተጠየቀ

አብዲ ኢሌን ለማስፈታት የሞከሩ አካላት በቁጥጥር ስር ዋሉ በሚል የተሰራጨው ዜና የተሳሳተ ጭብጥ የተካተተበት የሃሰት ዜና መሆኑ ተጠቆመ። ዜናውን ያሰራጨው ሪፖርተር ጋዜጣ እንዲያስተባብል መጠየቁም ተመልክቷል።

ምንጮች እንደነገሩት በመግለጽ አብዲ ኢሌን ለማስመለጥ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት አካባቢ ዝግጅት ያደረጉ አካላት መያዛቸውንና አንድ ሰው መሞቱን ነበር ሪፖርተር ታስታወቀው። ሁለት ግለሰቦች መካከል በተከሰተ አለመግባባት አንድ ሰው መገደሉን ያመለከተው ማረሚያ ቤቱ ግጭቱም ሆነ ግድያው ከአብብዲ ኢሌ ጋር ግንኙነት እነደሌለው ይፋ አድርጓል። ዜናውን የጻፈው ሪፖርተር ማስተባበያ እንዲሰራ መጠየቁንም አመልክተዋል። የሪፖርተር ዜና ከታች ያለው ነበር።

ከሐምሌ 26 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማና ሌሎች ከተሞች ላይ በተፈጸመ ግድያ፣ አካል ማጉደል፣ ማፈናቀል፣ አብያተ ክርስቲያናትና የንግድ ተቋማትን በማቃጠል ምክንያት ክስ የተመሠረተባቸውን የሶማሌ ክልል የቀድሞ ፕሬዚዳንትን ለማስለቀቅ ሴራ አቀነባብረው የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ፡፡

ድርጊቱ ሊፈጸም የነበረው ሰኞ ሐምሌ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ሲሆን፣ ተከሳሹ የቀድሞ ሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት የነበራቸውን ቀጠሮ ጨርሰው ወደ ማረሚያ ቤት ሲሄዱ እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ቃሊቲ ማረሚያ ቤት መግቢያ አካባቢ መኪና አዘጋጅተው ነበር የተባሉት ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች የተከሳሹን መምጣት በመጠባበቅ ላይ እያሉ፣ ያቆሙትን መኪና ከማረሚያ ቤቱ አካባቢ እንዲያነሱ በትራፊክ ፖሊስ ሲጠየቁ ‹‹አናነሳም›› የሚል ምላሽ መስጠታቸውንም ምንጮች አስረድተዋል፡፡

በዚህ ጊዜ የቆመው መኪና እንዲፈተሽ ሲጠየቁ በፈጠሩት አታካራ ሳቢያ ተኩስ መለዋወጣቸውንና ከየትኛው ወገን እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም፣ አንድ ሰው መመታቱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ከግለሰቦቹ መካከል የተወሰኑት ሲያመልጡ አንዲት ሴትን ጨምሮ አብዛኞቹ በቁጥጥር ሥር ውለው በምርመራ ላይ መሆናቸውንም ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡

ግለሰቦቹ በማረሚያ ቤቱ አቅራቢያ ቤት ተከራይተው እንደነበርና በርካታ የጦር መሣሪያዎችም በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ምንጮች አስረድተዋል፡፡

ድርጊቱ በተፈጸመበት ጊዜ ተከሳሹ አቶ አብዲ ከፍርድ ቤት ወደ ማረሚያ ቤት አለመመለሳቸውን ከምንጮች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ተፈጽሟል የተባለውን ሙከራ በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተርን በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ለማግኘት ቢቻልም፣ በኔትወርክ ችግር ምክንያት መነጋገር ባለመቻሉ ሙሉ መረጃውን ማካተት አልተቻለም፡፡