አማራ በራሱ ልጆች ዳግም ይከብራል – ስሜታዊነትን በማስወገድ

አማራ – “በራሱ ልጆች” የሚደማ፣ የሚዋረድ ሕዝብ ” በሚል ርዕስ ምገስ ሰውየው የተባሉ በዚሁ ገጽ የጻፉትን እንዳነበብኩ ይህንን አጠር ያለ መልዕክት / ሃሳብ  ለማስተላለፍ ወደድኩ። እኔም እንደ ጸሃፊው ጉዳዩን በቅርብ የምከታተል የአዲስ አበባ ነዋሪ የመተከል አካባቢ ተወላጅ በዜግነት ኢትዮጵያዊ፣ በብሄር ደግሞ ዛሬም ሆነ ትናንት መከራ እየደረሰበት ካለው የአማራ ወገን ነኝ።

ጽሁፉ አንድ ተቆርቋሪ፣ የተናደደና እልህ የተናነቀው ሰው የጻፈው ይመስላል። ከጥቅል ሃሳቡ ለመረዳት እንደቻልኩት በአማራ ክልል ውስጥ ያሉ ሁለት ወይም ከዛ በላይ ድርጅቶች እንዴት አብረው መስራት አቃታቸው? የሚለውን የበርካቶች ሃሳብ ለማጉላት በሚል በከረሩ ቃላቶች ጭምር ይራገማል። ችግር ያላቸውን አብይ ጉዳዮች በማንሳት ህብርት ለመፍጠር ከዚህ የተሻለ አጋታሚና አስገዳጅ ምክንያት ሊኖር እንደማይችል በመጥቀስ ግራ መጋባቱን ያትታል። አክሎም በአማራ ላይ ይህ ሁሉ ጉድ እየደረሰ እርስ በእርስ ለመግባባት አለመቻሉ ስሌት አልባ እንደሚሆበት እሳት ሆኖ ይጠይቃል። የግንቦት ሰባትንም ሆነ የሌሎች ጡረተኛ “ፓርቲዎችን” ስም አላነሳም። አብን ሲል ግን ጣቱን ቀስሯል።

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ / አብን ተቃዋሚም አይደለሁም። ነገር ግን ተደራጅተው ለአማራው ህዝብ አማራጭ ሆነው መቅረባቸውን አደንቃለሁ። ይሁን እንጂ ዛሬ ዓለም የሸሸውን፣ ያረጀውን፣ የሚያሳንሰውን፣ ከሰውነት አቅል ውጪ የሚያደርገውን ብሄር ላይ የተመሰረተ እርምጃቸውን ብዙም አልወደውም። የተሳካ ውጤት የሚያመጡ መስሎ አይታየኝም።

ከግል ስሜቴ ሰወጣና ለመሰንዘር ወደፈለኩት ሃሳብ ሳመራ ጸሃፊው አብን የኮረኮሙበትና ክልሉን እየመራ ያለውን ድርጅት ያዩበት መነጽር የተመጣጠነ መስሎ አልታየኝም። አብን አዲስና በወጣቶች የተገነባ ድርጅት ነው። እነሱ እንደሚሉት በዘውግ የተደራጁት ዓማራው ላይ እየደረሰ ባለው ግፍ የተነሳ ከለላና ጠባቂ ለመሆን ሲሉ ነው። በዚሁም አመለካከታቸው በአጭር ጊዜ ሰፊ መነቃቃት ፈጥረዋል። የወደፊቱ ባይታወቅም ለጊዜው ሰፊ ድጋፍና ሃይል አላቸው። ይህ ብቻውን ሊወደስ የሚገባ ሲሆን፣ ሃላፊነቱን ወስደው ይህንን የሰሩትም አካላት አቶ ክርስቲያንን ጨምሮ መመስገን አለባቸው። ከዚህ የዘለለ ማለት አልችልም።

ጸሃፊው ይህንን አድንቀው ወደ ወቀሳቸው ቢዛወሩ ሃሳባቸው ሙሉ ይሆን ነበር። ወደፊት ከንዴት ነጻ ሆነው የተመጣጠነ አስተያየት እንደሚሰጡ ልባዊ ተስፋ አደርጋለሁ።

ብአዴን፣ የዛሬው አዴፓ የህወሃት የበኩር ልጅ ሆኖ ክልሉን ሲመራ የሰራው ጥፋት መጠን የለውም። አሽከርነቱም ወሰን አልነበረውም። አንዳንዶቹ ሰው ስለመሆናቸው ጭምር እስኪያጠራጥር ድረስ በአጎብዳጅነት ሁለት አስርት ዓመታትን አሳልፈዋል። በዚህ ሁሉ ጊዚያት አማራው ቁልቁል ሄዷል። እኩል ተጠቃሚነት ሳይሆን ያለውን እንዲያጣ ተደርጓል። እንደ ጫጩት እየታፈሰ በየስፍራው ሲወረወርና ሲፈናቀል ተከራካሪ አልነበረውም። በራሱ “ወኪሎች” ትምክሀተኛ፣ ነፍጠኛ፣ የድሮ ስርዓት ናፋቂ እየተባለ ይፈረጅ ነበር።

ሌሎች አየር ላየር የሚመላለሱበት ጎዳናና የኢንዱስትሪ ባለቤት ሲሆኑ አማራው የጠርብ ድልድይ የሚሰራለት አጥቶ በገመድ እየተንጠላጠለ ወንዝ ይሻገራል። ልጆቹ እንኳን ምርጥ ትምህርት ቤት ሊገነባላቸው በየዛፍ ጥግና በወላለቀ ፍራሽ ስር እንዲማሩ ተፈርዶባቸዋል። መክነዋል። ተፈርጀው በጥላቻ እንደ ጠላት እንዲታዩ ተደርገዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን ብአዴን ሬሳ ነበር። ይህን ሃቅ ማንንም አይክደውም። ዛሬም ሆነ ቀደም ሲል ቤኒሻንጉል ጉምዝ ኮሽ ባለ ቁጥር አማራው ላይ ቀስት የሚወረወረው ከተዘራው ጥላቻ የተነሳ አማራ ጠላት ተደርጎ በመታየቱ ነው። ምስክርነቴን ልስጥ።

በወያኔ የተፈበረከው የጎሳ ፌደራሊዝም ይፋ ሲሆን ቢኒሻንጉል ጉምዝ ” የናንተ፣ የትወላጆች ናት” ተብሎ ተነገራቸው። አማራ ወራሪ ተድርጎ ሲፈረጅ በረከት የሚመራው፣ አዲሱ የሚከተለው ብአዴን ቁጭ ብሎ እያየና እያስፈጸመ ነበር። ህገ መንግስቱ በቁጥር በክልሉ ካሉ ጎሳዎች ሁለተኛ ደረጃ የያዘው አማራ ህዝብ ባይተዋር ሲያደርግ ብአዴን የቤት ስራ አስፈጻሚ እንጂ ተቆርቋሪ አልነበረም። በዚሁ የተነሳ ዛቻ ተጀመረ። በድንገት በገበያ ቀን አድፍጠውና መክረው ፭፮ ሰዎችን ጨፈጨፉ።

የኬሚሴ ኦሮሞ፣ ወላይታው፣ ሃድያው፣ ከንባታው … በአማራ ስም ተሰየፈ። የ፬፮ ቀበሌ ታጣቂ ሚሊሻ እሳት ጎርሶ ለጣናበለስ ፕሮጀክት ሃላፊዎች በጣሊያን ባለሙያዎች በተገነቡት አርባ ቪላ ቢቶች ውስጥ የሚኖሩ አመራሮችን ወረረ። እጅ እንዲሰጡ ጠየቀ። ኤሌክትሪክ አቋርጦ፣ ውሃ ዘግቶ አስገድዶ ከቀናት በሁዋላ ቤታቸው የነበሩትን እጃቸውን ያዞ ረሸናቸው። የሺናሻ ተወላጅ የሆነው ዋና አስተዳዳሪ አሰፋ ኢናቡን ስምንት ኪሎ ሜትር ግድም ጫማውን አስወልቀው በባዶ እግሩ ከነዱት በሁዋላ፣ አልሙ መንደር ሰባት ” አፋፋሙበት” በውቅቱ ፌደራል ፖሊስ፣ መከላከያ ቢኖሩም የሕዝቡን ቁጣ ለመቋቋም እንደማይችሉ በማመን ዳር ቆመው ትዕንቱን ሲያዩ ነበር። በነገራችን ላይ ወርቅ የሚዝቅበት ከማሼ ዞን ላይ ግን ምንም ጸብ የለም። ለምን የሚለውን አቶ ሞገስ በነካ እጅዎ ይግቡበት።

ይህንን ያነሳሁት ለጀብድ አይደለም። የወቅቱ የአማራ ክልል መሪዎች እንዴት አድረገው በሂደት ይህን ህዝብ ራሱን እንዳይከላከል ሽባ አደረጉት የሚለውን ቁጭት ለመግለጽ ነው። አቶ ሞገስ እንዳሉት ይህ ሁሉ ሲሆን የሚንገበገቡና የሚቆጩ የድርጅቱ አባላት እንደሚኖሩ ጥርጥር የለውም። ያ ቁጣና መቆርቆር አድጎ ከሕዝብ አመጽ ጋር እንደተቀላቀለ አብዛኞች ይስማማሉ።

እንደተባለው ከለወጡ በሁዋላ በአማራ ክልል የሚታየው አለመረጋጋት አሳሳቢ ነው። ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ አንድ ሆኖ መመከት ካልተቻለ መከራው እንደሚበረክት ጥርጥር የለውም። የተናጠል ትግልና የእርስ በእርስ ሽክቻ ትርፍ የለውም። በፖለቲከኞቹ ቋንቋ ያሰብት ስፍራ አይደርስም። በመሆኑም ከላይ የተቀመጠው ማመጣጠኛ ሃሳብ እንዳለ ሆኖ፣ ለግዜው የእርስ በርስ ሽክቻን ወደ ጎን በማድረግ በህብረት የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ መጣበቅ ያስፈልጋል። በዚህ ወቅት ስለ ልዩነት ማስላት ህዝቡን ይባስ ተጠቂ ያደርገዋል።  በሞራልም ሆነ በማህበራዊ ቀውስ እንዲደቆስ ያደርገዋል።

አገር ሲረጋ ምርጫ አለ። በምርጫ ህዝብ የሚወስነው ውሳኔ እንደ ከረመው ዘመን በሌብነት የሚጭበረበር አይደለም። ስድቡ፣ የእርስ በእርስ ሽክቻ ፣ መወቃቀስ የዛኔ ከደረስን ለምርጫው ጊዜ ይቀመጥልን። አሁን ባለበት ወቅት የተፈናቀሉትን መርዳት፣ ተጨማሪ መፈናቀል እንዳይኖር መረባረብ፣ የብልጠት ፖለቲካ ማራመድ፣ የብአዴንን ልምድ መቅሰም፣ የሚያሻግር ዓላማና ግብ በመያዝ ” ፖለቲከኛ ” መሆን ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።

ዝንጀሮ ቅድሚያ መቀመጫዬ እንዳለችው አብን የመጎሻሸም ትግሉን ለጊዜው ጋብ በማድረግ አሁን ቁጭት ከሚያንገበግባቸው የአዴፓ አመራሮችና አባላት ጋር ይህንን ችግር ለማለፍ ሲባል በጋራ ሊሰራ ይገባል። አብን ዓላማው የአማራን ሕዝብ መታደግ ከሆነ ዛሬ ነገ ሳይባል ይህንን ችግር ለምናልፍበትን መንገድ ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል። ወንበር በህዝብ ይሁንታ በጊዜ ገደብ የሚሰጥ በመሆኑ በየትኛውም ጊዜ አይቀርም። ከዚህ ውጭ እርስ በእርስ በመካሰስ ከማያገገም ኪሳራ ላይ እንዳንወድቅ እንጠንቀቅ። በርካታ መስመር ያልያዙ ጉዳዮች ባሉበት ሁኔታ ከህዝብ ይሁንታ ውጪ ወደ መንበር ለመምጣት ሙከራና ቅስቀሳ ማድረግ ማንንም አሸናፊ አያደርግም። ከተሞከረም ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ላናገግም እንወድቃለን የሚል ፍርሃቻ እንዳለኝ ለመግለጽ እወዳለሁ።

ውድ አዲስ ሃይል የሆናችሁ ኣብን አባላት፣ ዛሬ በለውጥ ውስጥ ዳግም ስማችሁን ለማደስ እየሰራቹህ ያላቹህ የአዴፓ አመራሮች፣ በክልሉ የምትንቀሳቀሱ ድርጅቶችና ታዋቂ ሰዎች ጊዜው የህብረት እና የአንድነት በመሆኑ ተደጋግፋቹህ ይህንን ጨለማ ታልፉት ዘንድ እንደ አንድ ተወላጅና ዜጋ እለምናለሁ። ክልሉ ላይ እጃችሁን የምታነሱ ቅጥረኞችም አደብ ግዙ። እጃችሁን ከንጹሃን ላይ አንሱ። ስሜታዊነትን በማስወገድ የአማራ ህዝብ ሰላሙን እንደሚያውጅ አትጠራጠሩ።

መልካሙ አስማማው

ዝግጅት ክፍሉ – ይህ ጽሁፍ የጸሃፊው ሃሳብ እንጂ የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያንጸባርቅም

 

ሐገር ከብሔርም ሆነ በዩቲዩብ ከሚገኝ ዶላር በላይ ነች…

ቴዲ ምን እያለን ነው?

«ዘውድአለም ታደሠ»

#Ethiopia : ጎበዝ እኛ ሳንሰማ የርእዮቱ ቴዎድሮስ ፀጋዬ አደገኛ ፖለቲከኛ ሆኖ የለንዴ? 😀 መቼስ ይሄ ለውጥ ፖለቲከኛ ያላረገው የለም! ያኔ ከተቃዋሚ ጋር ሻይ ለመጠጣት ይፈራ የነበር ሁላ ዛሬ ደርሶ ቼጉቬራ ቼኩቬራ እየተጫወተ ነው!

ቴድሮስ ፀጋዬ ጥሩ ወረኛ ነው። ጋዜጠኛ እንዳልለው ሬዲዮና ቴሌቭዥን ላይ ያወራ ሁሉ ጋዜጠኛ አይባልም። ጋዜጠኝነት የራሱ መርህና ዲስፕሊን፣ ያለው የከበረ ሙያ ነውና!

ቴዲ ጨለምተኝነትን ሙያ አርጎ የሚኖር ልጅ ነው። ውስጡ ያለውን ጥላቻ በየቀኑ እያዘመነው የሚሄድ የስነልቦና ቁስለኛ። ዛሬ ሳይሆን ድሮ ካምፓስ ሆኖ የኦርጋን ኬብል ሁን ብሎ እየደበቀ ሰውን መከራ ከሚያበላበት ግዜ ጀምሮ አውቀዋለሁ።

ያ የጉርምስና ተንኮል ቢመስለኝም የልጁን ጭካኔ የተረዳሁት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳን ከፌስቡክ በለቃቀሙለት አጫጭር ግጥሞች መሳለቂያ አድርጎ ራሱን እንደአዋቂ ሊያሳይ ሲሞክር ነው! የምር የዚያን ቀን ለአንድ ደቂቃ አይኑ በርቶ እኛ አዛውንት ፊት ላይ የሚታየውን ስሜት ቢመለከት ብዬ ተመኝቼ ነበር። የትኛውም አባት ያሳደገው ወጣት በዚያ ደረጃ አንድን አዛውንት መሳለቂያ ለማድረግ አይሞክርም። «እሱ አናቱን በኩርኩም ብመታው እንደቃ ፈጥኖ ባይመልስም እያደር ግን ነቃ» የሚል እንቶ ፈንቶ ግጥም እንዳልፃፈ እኛን አዛውንት «ግጥምዎ ተራ ወሬ ነው» እያለ ሲያናንቃቸው ሳይ የጭካኔውን ጥልቀት ተረዳሁ!

ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ ልጁ ወያኔ የጠመደችውን በመጥመድ ሱስ እንደተለከፈ ያየሁት የቴዲ አፍሮን አልበም የሽፋን ስእል ወገቡን ይዞ ሲተች በመስማቴ ነው! እኔ ለአይነስውራን ትልቅ ክብር አለኝ። ልበብርሃን መሆናቸውንም አውቃለሁ። ነገር ግን የፈለገ ውስጣዊ ብርሃን ቢኖራቸው ለስእል ሂስ መስጠት ይችላሉ ብዬ አላምንም። ሁሉን ቻዩ ቴዲ ግን አደረገው! የቴዲ አፍሮን የአልበም ስእል ህዝብ እየሰማ ተቸ። 😀

አሁን ደግሞ ቴዲሻ ወሬው ሁሉ አብይን መስደብና ማናናቅ ሆኗል። ትናንት ህውሃት ከጓደኞቿ ጋር ከአራት መቶ በላይ ጋዜጠኛና የነፃነት ታጋዮችን ወህኒ አጉራ ስታሰቃይ ስለፍቅርና ስለግጥም ያወራ የነበረው ቴዲ፣ ትናንት በየቦታው ህፃናት በጥይት እሳት ሲቀነጠሱ እሱ ፍቅሬ ቶሎሳን ሲሰድብ የነበረው ቴዲ፣ ትናንት ሴቶች በየማረሚያ ቤቱ ሲደፈሩ፣ እናት የልጇ ሬሳ ላይ ተቀመጭ እየተባለች ስትደበደብ የቴዲ አፍሮን አልበም በመተቸት ላይ ተጠምዶ ህውሃትን አንድ ቃል ለመናገር የማይደፍር የነበረው ቴዲ ዛሬ በመከራው ዘመን ድምፅ የሆኑን እነሲሳይ አጌናን «አድርባይ» እያለ በድፍረት ይሳደባል! ትናንት ወጣቶች በሃሰት ተከሰው ሲፈረድባቸው፣ የሃገሪቱ ሃብት አለቅጥ ሲመዘበር የሐገሩ ሁኔታ ያላሳሰበው ቴዲ ዛሬ ለሐገር ተቆርቋሪ ሆኖ ብርሃኑ ነጋን ይሰድባል! ዛሬ ቴዲ ከታማኝ በየነ በላይ ለሐገሬ አስባለሁ እያለን ነው! ምክኒያቱም ቴዲ የሐገሩ ህልውና ያሰጋው ህውሃት መቀሌ ስትገባ ነው። 😀

ቴዲያችን ዛሬ ምክኒያታዊ ነው ለመባል ህውሃትንም ከአብይ ጋር ጨምሮ ለመውቀስ ይሞክራል። አሁን ምን ያረጋል የወደቀን ስርአት መተቸቱ? ያኔ ህውሃት ስልጣኑን በሞኖፖል የያዘችው ግዜ ምነው አፉ ተለጎመ? ወይስ ባለተራው የሱ ዘመድ እስከሆነ ድረስ ችግር የለውም? ወይስ የአብይ መንግስት የአንድ አመት አኪያሄድ ከህውሃት የሃያሰባት አመት ጉዞ በላይ አስግቶት ነው?

ቴዲ አይነስውሩ ዳንኤል ብርሃኔ ነው! ልዩነቱ ቴዲ እንደዳንኤል በግልፅ ወያኔን አይደግፍም። ይልቁንስ ያው ምንም እንኳ ቢያረፍድም ህውሃትን ለመተቸት ይሞክራል፣ ኢትዮጵያ ምናምን ብሎ የህዝቤን ልብ ይሰቅልና የፈረደበት አብይን መርገምና ማብጠልጠል ይጀምራል።

እኔ አብይ አይተች የምል ደነዝ አይደለሁም። ነገር ግን ትናንት በዚያ ግፍና መከራ ውስጥ ጭጭ ያለ ሰው ዛሬ ለህዝባቸው ዋጋ የከፈሉ ሰዎችን በድፍረት እየዘረጠጠ ሲውረገረግብኝ ለምን? ብዬ እጠይቃለሁ! ታጥቦ ከተቆላ ምላስ ጀርባ ያለው አላማ ምንድነው? ብዬ እጠይቃለሁ። እንደመርፌ የሾለው ምላስ አንድ አቅጣጫ ላይ ብቻ ካነጣጠረ «ይሄ ነገር እንዴት ነው?» ብዬ አስባለሁ።

ለማንኛውም ይሄን ፅሁፍ ወዳጆቹ ካነበቡለት አንድ ነገር ልለው እፈልጋለሁ። ሐገር ከብሔርም ሆነ በዩቲዩብ ከሚገኝ ዶላር በላይ ነች!

«ዘውድአለም ታደሠ» Facebook

የጋህአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ በጋምቤላ ከተማ ስብሰባ ጀምሯል

የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋህአዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ስብሰባውን እያካሄደ ነው፡፡ የዛጎል ምንጮች እንዳሉት በጋምቤላ የእርስ በእርስ ግጭት ለማስነሳት ዝግጅት መኖሩ አስቀድሞ በመታወቁ ስብሰባው ከወዲሁ ለጥንቃቄ የሚሆኑ እርምጃዎችን ለመውሰድ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

ይህንኑ በሚያጠናክር መልኩ “የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ስብሰባው ሲጀመር እንዳሉት ስብሰባው በክልሉ ወቅታዊ  ጉዳዮች ላይ ለመወያየት የተጠራ ነው።በዚህም በወቅታዊ የሰላም፣ የፀጥታና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ በስፋት ይመክራል ” ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

መነሻቸውን ከኡጋንዳ ያደረጉ ተካላኪዎች የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ እያሴሩ መሆናቸው በመታወቁና ግጭት ለመፈጥር በጎሳ መካከል እሳት ለመጫር ከዚህ ቀደም የተሞከረው ሴራ መክሸፉን ያስታወሱት የዜናው ምንጮች፣ ጉዳይ በጥንቃቄ መያዙን ገልጸዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

የኢትዮጰያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚ ስልጣኔን ለማስረከብ ዝግጁ ነኝ አለ!

የኢትዮጰያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚ ኃላፊነቱን ለማስረከብ ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ።

ስራ አስፈጻሚዉ ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ ለሰላም እና ህዝበ ሙስሊሙ አጥብቆ ለሚሻዉ አንድነት ሲባል ነገ በሚካሄደዉ የኡለማዎች የምክክር መድረክ ላይ በሚቀመጠዉ አቅጣጫ መሰረት ሀላፊነቴን አስረክባለሁ ብሏል።

የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼህ መሀመድ አሚን ጀማል ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት ሁሉም የስራ አስፈጻሚ አባላት ኃላፊነታቸውን ለማስረከብና ለአንድነት የተጀመረዉን ለዉጥ ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ትላንት የምክር ቤቱ 15ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሂዶ በአቋም መግለጫው እንደተገለጸዉ ሁሉ፤ ኡለማዎች በሚያስቀምጡት አቅጣጫ በየትኛዉም ሰዓት ለማስረከብ ስራ አስፈጻሚው ከስምምነት ላይ መድረሱን እና በምክክር መድረኩ ላይ ለሚነሱ የመፍትሄ ሃሳቦች እና ለሚቀመጠዉ አቅጣጫ ተገዥ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ አንድነት የጋራ ኮሚቴ ባቀረበዉ ምክረ ሀሳብ ነገ ለሚካሄደዉ የምክክር መድረክም ከወዲሁ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን እና ለበርካታ ኡለማዎች ጥሪ መደረጉንም ተናግረዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸዉ ኡለማዎችም የነገዉ መድረክ ለሙስሊሙ አንድንትን ለማምጣት የሚጠቅም መሆኑን ተናግረዋል።

ነገ በሸራተን አዲስ የሚካሄደዉ የኡለማዎች የምክክር መድረክ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አቀራራቢነት ለተቋማዊ ለዉጥ እና አንድነት የተቋቋመዉ ኮሚቴ ባቀረበዉ ምክረ ሀሳብ የሚካሄድ ነዉ።

በመድረኩም ከ300 በላይ ኡለማዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ፣ለሰላም እና ለሙስሊሙ አንድነት የታገሉ ግለሰቦች ይሳተፋሉ።

በሀብታሙ ተክለስላሴ – FBC

 የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች ወግ!! አስገራሚው የኑሮ ልዩነት ትዝታ

በአገራችን ልማድ ሆኖ ብዙ የሚነገርለት ሲሞት ነው። ነጋሶ ማለፋቸው ከተሰማ ወዲህ የሚአውቋቸው ሲናገሩ መስማት በዛሬ ዘምን ካለው መሰሪነት ጋር ተዳምሮ ያማል። ምስክሮቻቸው በሙሉ ከሴራ የጸዱ፣ ቀና፣ ደግ፣ አሃሜት የሚባል የማያውቁ፣ ፊትለፊት ተናጋሪ፣ የመርህ ሰው፣ እንደ ሌሎች ባለስልጣናት ከህዝብ የሚለዩ ሳይሆኑ ህዝብን የሚቀርቡ፣ ለጥቅም የማይደለሉ፣ ከፕሬዚዳንትነታቸው ሲለቁ አንድ መኪናና መኖሪያ ቤት እንዲሁም ገንዘብ ያልነበራቸው፣ በታክሲ እየተጋፉ የሚጓዙ አሳዛኝ ነገር ግን አስደናቂ ባለ ጀዝም ነበሩ። ቢቢሲ አማርኛ ከአቻቸው መቶ አለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ጋር አመዛዝኖ ኦክቶበር ፫ ቀን ፳፩፯ ላይ ይህንን ጽፎ ነበር። ለትዝብትና ለትዝታ ይሁን!!

የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳና ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የተለያየ የኑሮ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። በቀድሞ ሁለት ፕሬዝዳንቶችን መኖሪያ ቤት ተገኝተን ባነጋገርናቸው ወቅት የሚገኙበት የኑሮ ሁኔታ ሰፊ ልዩነት ያለው መሆኑን ለመረዳት አላዳገተንም። በኑሯቸው ብቻም አይደለም፤ ግንኘነታቸውም ያን ያህል እንደኑሯቸው የተራራቀ ነው።

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ነበሩ።

አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ደግሞ መንበረ ሥልጣኑንን ከዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በመቀበል ሃገሪቷን ለ12 ዓመታት በርዕሰ ብሔርነት አገልግለዋል።

ዛሬ ላይ በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ?

ዶ/ር ነጋሶ ሃገሪቷ የምትመራበት መንገድ ሳያስማማቸው ቀርቶ ስልጣን በራሳቸው ፍቃድ ከለቀቁ አስራ ስድስት ዓመታት አልፈዋል። የመጀመሪያዎቹን አራት ዓመታት መጸህፍት በማንበበ እንዳሳለፉና ከዚያም በኋላ በተለያዩ የማህበራዊና ፖለቲካዊ አንቅስቃሴዎች ውስጥ ለረጅም ዓመታት ንቁ ተሳትፎ እንደነበራቸው ይናገራሉ።

በ 1997 ዓ.ም በተካሄደው ሃገራዊ ምርጫ በግል ዕጩነት የሕዝብ ድምጽ አግኝተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እንደነበሩም ይታወሳል።

ዶ/ር ነጋሶ እንደሚሉት ከሆነ ከሶስት ዓመታት በፊት ከፖለቲካ ፓርቲያቸው ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሙሉ በሙሉ ፖለቲካን እርግፍ አድረገው እንደተዉ ይናገራሉ።

ዶ/ር ነጋሶ እንደነገሩን በአሁኑ ሰዓት ብቸኛው የገቢ ምንጫቸው ለተለያዩ አካላት ስርተው የሚያቀርቧቸው ጥናታዊ ጽሁፎች ናቸው።

አጭር የምስል መግለጫ
አቶ ግርማ በንጉሱ ዘመንም በተለያዩ የስልጣን እርከኖች ላይ ህዝብና ምንግሥትን አገልግለዋል
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ዘመን የፓርላማ አባል የነበሩት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ አሁንም ቢሮ መግባታቸውን አላቆሙም።

ግርማ ወ/ጊዮርጊስን የሚያሳይ ምስል

በቅርቡ ዘጠና ሁለት ዓመት የሚሞላቸው አቶ ግርማ፤ ”ከፕሬዝዳንትነት በኋላ ላለፉት አራት ዓመታት ሕዝብን ይጠቅማሉ ብዬ ያሰብኳቸውን ሥራዎች ስሰራ ቆይቻለው” ይላሉ።

ስልጣን ላይ ከነበርኩበት ወቅት ይልቅ አሁን ብዙ ሥራ እየሰራሁ እንደሆነ ይሰማኛል
ግርማ ወ/ጊዮርጊስ, የቀድሞ ፕሬዝዳንት
”ዲጂታል የሆነ ቤተ-መጻህፍት ለሕዝብ ገንብቻለሁ። ሥልጣን ላይ ከነበርኩበት ወቅት ይልቅ አሁን ብዙ ሥራ እየሰራሁ እንደሆነ ይሰማኛል” የሚሉት አቶ ግርማ ሆላንድ ኤምባሲ አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ቅጥር ግቢ ውስጥ ያሰሩት ቤተ-መጻህፍት በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምር ነግረውናል።

ኑሮ ከስልጣን በኋላ

ከሃላፊነት የተነሱ የሀገርና የመንግሥት መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የምክር ቤት አባሎችና ዳኞች የሚያገኟቸውን መብትና ጥቅሞች ለመወሰን በወጣው በአዋጅ ቁጥር 653/2001 ዓ.ም መሠረት ተሰናባች ፕሬዝዳንቶች የደሞዝ፣ የመኖሪያ ቤትና ቢሮ፣ የጤና አገልግሎት፣ የጥበቃና የመጓጓዣ አገልግሎቶችን ጨምሮ በርካታ ጥቅማጥቀሞችን የማግኘት መብት እዳላቸው ይደነግጋል።

ይሁን እንጂ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ስልጣን ከለቀቁ ከአራት ዓመታት በኋላ በፖለቲካ ውስጥ በነበራቸው ተሳትፎ የተነሳ ያገኙት የነበረው ጥቅማጥቅም እንዲቋረጠባቸው መደረጉን ይናገራሉ።

የፖለቲካ ተሳትፎ ከማድረጌ በፊት በወቅቱ የነበሩትን የምርጫ ቦረድ ሃላፊዎች አማክሬ የፖለቲካ ፓርቲ እስካልተቀላቀልኩ ድረስ በግል በማደርገው የፖለቲካ ተሳትፎ ምክንያት የማገኛቸው ጥቅማጥቅሞች እንደማላጣ አረጋግጠውልኝ ነበር ይላሉ ዶ/ር ነጋሶ።

ከዚያ በኋላ ተሻሽሎ የወጣውም አዋጅ የማገኛቸውን ጥቅማጥቅሞች ለማስቀረት እንደወጣ ይሰማኛል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዶ/ር ነጋሶ በመኖሪያ ቤታቸው ቅጥር ግቢ ውስጥ

አጭር የምስል መግለጫ
ዶ/ር ነጋሶ ብስራተ ገብርኤል አከባቢ ከሚገኘው መንግሥት ከሰጣቸው ቤት እንዲወጡ ቢነገራቸውም እየኖሩበት ይገኛሉ
ዶ/ር ነጋሶ በአሁኑ ወቅት ብስራተ ገብርኤል አካባቢ በሚገኝ የመንግሥት ቤት ውስጥ ይኖራሉ። ”ይህን ቤት ለቅቄ እንድወጣ ከአንድም ሁለት ጊዜ ደብዳቤ ተጽፎልኛል። አንድ ቀን መጥተው ከዚህ ቤት ሊያስወጡኝ ይችላሉ” ይላሉ።

ዶ/ር ነጋሶ የሚኖሩበት ግቢ እጅጉን ጭር ያለ ነው። ምግብ ከምታበስልላቸው የቤት ሰራተኛቸውና የተለያየ ሥራ በመስራት ከሚያግዛቸው አንድ ግለሰብ ውጪ በግቢው ውስጥ ማንም አይታይም። ጀርመናዊቷ ባለቤታቸውም አሁን በሃገር ውስጥ አይገኙም።

ከቤታቸው ጀርባ ያለው የቴኒስ መጫወቻ ሜዳም ሳር በቅሎበት ይታያል።

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ከ1987-1994 ዓ.ም ድረስ የሃገሪቱ ርዕሰ ብሔር ነበሩ።
አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ደግሞ ከ1994 – 2006 ዓ.ም ድረስ ርዕሰ ብሔር ሆነው አገልግለዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በቀድሞ ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ መኖሪያ ግቢ ውስጥ 3 መኪኖች ቆመው ይታያሉ። የሚኖሩበት ቅጥር ግቢ እጅ ሰፊ የሚባል ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት ለአቶ ግርማ የቤት ኪራይ ወጪ የሚደረገው የገንዘብ መጠን ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

በዚህ ሰፊ ግቢ ውስጥ የመኖሪያ ቤት፣ ቢሮዎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ ቤተ-መጻሓፍት፣ ማዕድ ቤቶች እንዲሁም የሰራተኛ መኖሪያ ክፍሎች ይገኛሉ።

የአቶ ግርማ መኖሪያ ቤት

አጭር የምስል መግለጫ
የአቶ ግርማን ህይወት ቀላል የሚያደርጉ የተለያዩ ወጪዎችን መንግሥት ይሸፍናል
መኖሪያ ቤታቸው 24 ሰዓት ጥበቃ ይደረግለታል። ግቢያቸውም እጅግ ንጹህና ያማረ ነው።

ምንም የቀረብኝ ነገር የለም። መንግሥት የሚያስፈልገኝን ሁሉ አሟልቶልኛል
ግርማ ወ/ጊዮርጊስ, የቀድሞ ፕሬዝዳንት
”ምንም የቀረብኝ ነገር የለም። መንግሥት የሚያስፈልገኝን ሁሉ አሟልቶልኛል። በህግ የተሰጠኝን መብት ሙሉ በሙሉ እየተጠቀመኩበት ነው። ከዚህ በላይ ደግሞ ምንም አልፈልግም” ይላሉ አቶ ግርማ።

ይህ ሁሉ ልዩነት ለምን?

ዶ/ር ነጋሶ በ1997 ዓ.ም የደምቢዶሎን ከተማ ሕዝብ በመወከል በግል እጩነት የተወካዮች ምክር ቤት ወንበርን ካገኙ በኋላ ያገኟቸው የነበሩት ጥቅማ ጥቅሞች እንደተቋረጡባቸው ይናገራሉ።

”መጀመሪያ ላይ በቤቱ ውስጥ የሚረዱኝ ሦስት ሰዎች፣ አትክልተኛና ሁለት መኪኖች ከአሽከርካሪ ጋር እንዲሁም ሁሉን የሚያቀናጅልኝ አንድ ሰው ነበር። አሁን ግን ይህ ሁሉ የለም” ይላሉ ዶ/ር ነጋሶ።

አጭር የምስል መግለጫ
ስልጣን ከለቀቁ በኋላ መንግስት ለኔ ምንም የሚበጅ ነገር እያደረገልኝ አይደለም ይላሉ
ዶ/ር ነጋሶና አቶ ግርማ ተገኛኘተው ያውቁ ይሆን?

”ብዙም አንገናኝም” ይላሉ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ግርማ።

ዶ/ር ነጋሶም ተመሳሳይ መልስ ነው ያላቸው፤ ከዚህ በፊት ቢበዛ ለሦስት ጊዜ ያክል ብቻ እንደተያዩ ያስታውሳሉ። ከአቶ ግርማን ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኘነው ፕሬዝዳንት ሳሉ ነበር።

”በአዋጁ ምክንያት የተቋረጠብኝን ጥቅማጥቅም ለማስመለስ ፕሬዝዳንት ግርማን ባማክራቸውም ሳይሳካልኝ ቀርቷል።” የሚሉት ዶ/ር ነጋሶ፤

”በጥያቄዬ እንደማይስማሙ ነገሩኝ ከዚያም በኋላ ተስፋ በመቁረጥ ሳልጠይቃቸው ቀርቻለሁ” ይላሉ ዶ/ር ነጋሶ።

የሚገባኝን ጥቅማጥቅም ለማስመለስ ለህዝብ ተወካዮች መክር ቤት አፈ-ጉባኤ ሶስት ግዜ ደብዳቤ ብጽፍም መልስ አላገኘሁም የሚሉት ዶ/ር ነጋሶ ጥቅማጥቅሞቼ እስኪመለሱልኝ ድረስ አስፈላጊውን ጥረት አደርጋለው ብለዋል።

ሁለቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች ሃገሪቱን በተመሳሳይ የሃላፊነት ቦታ ላይ ያገለገሉ ቢሆንም ከሥልጣን በኋላ በሚያገኙት ጥቅም ግን ተለያይተዋል።

አማራ – “በራሱ ልጆች” የሚደማ፣ የሚዋረድ ሕዝብ…

“ብሔርተኝነት አማራጭ የሌለው መድሃኒት ነው እያሉ ስለተጎጂነታቸው ሲተርኩ የሚውሉ የተወጉ ሰዎችን የስቃይ ፎቶ ለመለጠፍ ቀዳሚ ናቸው። ከነሱ መሃል አንድም ሰው ስለማይገደል ምን ቸገራቸው! የፖለቲካ ነጋዴዎች ናቸው። ችግሮችን ለማራገብ አንደኛ፤ አዛኝ ለመምሰል አንደኛ፣ ሌላውን ለመኮነን አንደኛ፣ ጥፋተኞቹ ሁልጊዜ አዴፓ፣ ኦዴፓ፣ ኢህአዴግ፣ የዜግነት ፖለቲካ፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ መከላከያ ወዘተ። በእነዚህ ጭንቅላት ነው እንዴ ሰው የሚመራው? ምንም ይሁን ምን የአውሬነት አስተሳሰብን በፖለቲካ መዋቅር ወይም በወታደር ሃይል ማስተካከል አይቻልም። በቻርለስ ዳርዊን ሃሳብ ግዙፍ፣ ጠንካራ ወይም ምጡቅ ስለተሆነ ብቻ ህልውና አይረጋገጥም። ሕልውናን ለማስጠበቅ ከጊዜና ከሁኔታዎች ጋር መለወጥና መጓዝ መቻል ብቸኛው መፍትሔ ነው። ብሔርተኝነት ኋላ ቀር አስተሳሰብ በመሆኑ በዓለም ተሸንፏል። ሌላ ቦታ የለም። ማስቆም ካልተቻለ ከብዙ እልቂት በኋላ በራሱ ይቆማል” ልጅ ግሩምበፌስ ቡክ ገሳቸው የጻፉት ነው።

ከለውጡ በሁዋላ አማራ ክልል ላይ የሚስተዋሉት ጉዳዮች አግባብነት የጎደላቸው ናቸው። ክልሉ ታሟል። ክልሉ በሆያሆዬና በቀረርቶ እየተናጠ ነው። ክልሉ ውስጡ እየነፈረ ነው። በክልሉ ሰላም አሳሳቢ እየሆነ ነው። በክልሉ የሰላም ዋስትና ጥያቄ እየከረረ ነው። ክልሉ በዚህ ከቀጠለ ሙሉ በሙሉ ሊናጋ ይችላል። ይህ ፈጠራ ሳይሆን ገፈት ቀማሹ ህዝብ በገሃድ በየአቅጣጫው የሚናገረው፣ የሚሰለፍበትና የሚያነባበት ጉዳይ ነው።

ከክልሉ ውጪ በ “አጎራባች” ክሎችና በሌሎች ስፍራዎች በሰላም የሚኖሩ የብሄሩ አባላትም እየታወኩ ነው። በማያዋጣ ቀረርቶና ፉከራ በየአቅጣጫው ጠላት እንዲጨመርለት እየሆነ ነው። ከየትኛውም የህበረተሰብ ክፍል ህጋዊ የህዝብ ውክልና ሳይኖር በስልጣን ጥማት ህዝቡን መማገድና የፖለቲካ ትርፍ ለማግበስበስ የሚደረገው ሩጫ ምስኪኖችን ማቅ እያለበሰ ነው። በሚታወቅና በማይታወቅ ማንነት በውል በጥቅም የሰከሩ ከሩቅና ከቅርብ ሆነው በየማህበራዊ ሚዲያው የሚያስታውኩ እርኩሶች የምስኪኖችን ቤት በሃዘን አጥምቀው ” እንታጠቅ” በሚል መዋጮ ለመሰብሰብ ይቀሰቅሳሉ።

በማውቅም ይሁን ባለማወቅ እነዚህን ክፍሎች የሚከተሉ፣ የእነሱን መፈክርና ቀረርቶ እያራቡ፣ እነሱ በአውቶሞቢል እየተንፈላለሱ የሚያሰሙትን የክተት ጥሪ ዜማ የሚያራቡ ሁሉም ምስኪኑን ህዝብ ለከፋ ጥቃት እየዳረጉት ነው። የሌሎች ክፋትና ሴራ ሳያንሰው የአማራ ህዝብ ከውስጡ ወጣን በሚሉ ማቅ ለብሶ እያነባ ነው። ሃዘን ትከሻውን እንዲሰብረውና በልዩ ስትራቴጂ ሲያሽመደምዱት ለኖሩት መሳቂያና መሳለቂያ፣ እንዲሁም የከበሮ ማሟሟቂያ እያደረጉት ነው።

ሰክኖ፣ መርምሮና ወቅቱን አገናዝቦ የሚበጅ መንገድ በመምረጥና በመከተል ” የፖለቲካ ተኩላ” በመሆን ከመስራት ይልቅ በየሚዳው በመትፋት፣ በማቅራራት፣ የሌለ ስዕል በመሳል በባዶ ሜዳ የራሳቸውን ህዝብ የሚበሉና የሚያስበሉ ቢኖሩ አማራ ክልል ውስጥ ናቸው። ራስን አጥርቶ፣ አትራፊ የፖለቲካ ሂሳብ በመቀመር ተንቀሳቅሶ ይህን ለዓመታት የሞት ድግስና የጥላቻ አታሞ ሲመታበት የኖረን ህዝብ ለመታደግ የማይስማሙ ክፍሎች በየትኛው መስፈርት ወገንተኛ ሊባሉ ይችላሉ?

ከለውጡ በሁዋላ ራሱን እንደገና እያደራጀ ያለውን የክልሉን መንግስትና  አመራሮች በማሸማቀቅ ድጋፍ አልባ ማድረግ፣ ግልጽ ባልሆኑ ጉዳዮች ማጠልሸት፣ መዋቅራቸውን መሰባበር፣ ከሕዝብ ጋር መነጠል፣ ክልላቸውን እንኳን መከላከል እንዳይችሉ ሽባ ማድረግ በስፋት የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው። አሳሳቢና እንቅልፍ የሚነሳም ነው። ለጊዜው እስኪረጋ ካለው መንግስት ጋር ልዩነትን በስልት በማራመድ አንድ ሆኖ ከመስራት ይልቅ ጭልጥ ባለ ብሄርተኛነት መንጎድ አዋጪነቱን የሚአስረዳና ማሳመን የሚችል ሃይልም የለም።

አሁን የሚታየው በግብታዊነት ራስን አማራጭና የሕዝብን ሰላም አስጠባቂ ሃይል ለማድረግ የሚደረግ የአካፑልኮ አይነት ፊልም ነው ። ዝም ብሎ ቀረርቶ፣ ሽለላ፣ ውግዘት፣ በሄዱበትና በረገጡበት ሁሉ መናከስ፣ ጠላት ማብዛትና የአዞ እንባ ማንባት ነው የሚስተዋለው። በነበረው የረመጠ ቂምና ጥላቻ ላይ ነዳጅ በማርከፍከፍ ምስኪኑን ህዝብ አሳር ማብላት፣ ማስመታት፣ ማስጨፍጨፍ የትኛውን ወገን እንደሚጠቅም የማይረዱ ክፍሎች እንዴትስ አማራጭ ሆነው ለወደፊቱ ካርድ ይከማችላቸዋል?

አዴፓ / ብአዴን ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በአብዛኛው ለተፈጠሩበት ህዝብ ደንታ በሌላቸውና ማንነታቸው በማይታወቅ ተላላኪዎች ሲመራ ነበር። ሃፍረት በሌለው መልኩ ከሰውነት ተራ የወረዱ ባንዳዎች የህዝቡን ክብርና ልዕና ሽቅጠውበታል። ለመታገል የሞከሩትን ራሳቸው እየጠቆሙ አስመትተዋል። መካሞች፣ ጉዳዩ ቶሎ የገባቸውና የተጋፈጡ የመኖራቸውን ያህል፣ ተጠፍጥፈው የተሰሩና የሰው ጠረን የሌላቸው  በዕቅድ የተነደፈውን ክልሉንና ህዝቡን ለይቶ የሚያጠቃ ስልት አስፈጻሚ እንደነበሩ አሁንም በዛው አቋማቸው ያሉ አሉ። እነዚህን እሥሥቶች በህብረት ነቅሶ ለማውጣት ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ መግለበለብ መመረጡ ህዝቡን ይባስ ዋጋ እያስከፈለ፣ እስስቶቹም ቆዳቸውን እንዳሻቸው እነዲቀያይሩ እየረዳ ነው።

እንደ ድርጅት ለውጡ እውን ከመሆኑ ዓመታት በፊት ውስጥ ውስጡን በጋመ ትግል ሲያራምዱት ከነበረው የተቀነባበረ አክሳሪ መንገድ ነጻ ለመውጣትም በግንባር ቀደምትነት ዋጋ የከፍሉ አሉ። ተጸጽተው ከቀድሞ መንገዳቸው የተመለሱ አሉ። ካኮረፈው ህዝብ ጎን መቆማቸው፣ ለውጡን እውን ለማድረግ ከለውጥ ሃይሎች ጋር መስራታቸው፣ በገሃድ ሚና ለይተው መንቀሳቀሳቸውንም ማጣጣል አይቻልም። ይሉቁኑም እነሱን ከአድርባዩ በመለየት በአማራ ህዝብ ላይ የተጫነውን ቀንበርና የጥላቻ ዘመቻ በአስተዋይነት፣ በፍቅር፣ በስትራቴጂና፣ አርቆ በሚያልም ዓላማ ለመግፈፍ መትጋት ሲገባ ተመልሶ የተራመጠውን ስትራቴጂ ቆስቁሶ ማንደድ በየትኛው የፖለቲካም ሆነ የብሄርተኛነት ስሜት መረዳት አዳጋች ነው።

ከለውጡ በሁዋላ በተገኘው አጋጣሚ በክልሉ አብን የሚባል ድርጅት ተቋቁሟል። ይህ ድርጅት የአማራ ብሄርተኛነትን በማጉላት ሰፊ ንቅናቄ ፈጥሯል። ይህ ድርጅት የፖለቲካ ስራ እንዳይሰራና ራሱን እንዳያደራጅ የያዘው የለም። ጫና ተደረገብን ሲሉም አይሰማም። ይህ ከሆነ በማስተዋልና ወቅቱን ባገናዘበ መልኩ አደረጃጀታቸውን ወዳታች ማስረግ አስቸጋሪ አይሆንባቸውም። የክልሉ አስተዳደር አብሮ ለመስራት ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል። ሲመሰረቱ ጀምሮ ድጋፍ በመስጠት፣ የሚዲያ ደጁን በመክፈት መተባበሩን ሕዝብ አይቷል። ሰምቷል። የራሱን ግምትም ወስዷል። ችግር ካለ በመነጋገር መፍታትና ማስተካከል የሚከብድ አይመስልም።

እውነታው ይህ ከሆነ አብን አዴፓ ላይ ዕለት ከዕለት የሚዘምትበት ምክንያት ግልጽ አይደለም። ጊዜው የምርጫ ዘመቻ የሚደረግበት ባለመሆኑ ክልሉን የሚመራው ፓርቲ መካሙን ከባንዳው የመለየቱ ችግሩ እንዳለ ሆኖ ስራውን እንዳይሰራ፣ መሰናክል መሆኑ ከስትራቴጂ አንጻር ማንን ይጠቅማል? የሚለው ጉዳይ የሰከኑ የህብረተሰቡ ክፍሎችን እያስገረመ ነው።

ራስን አደራጅቶ አማራጭ በመሆን በምርጫ ስልጣን ለመያዝ ከመስራት በዘለለ እግራቸው በረገጠበት ሁሉ ደም የሚፈሰው ለምንድን ነው? በሚል ጥያቄ የሚያነሱ በርካታ ናቸው። የክልሉን ገዢ ፓርቲ መዋቅር መሰባበርና ልምሻ ማድረግ ፖለቲካዊ ፋይዳው ምን ይሆን? በሸዋ፣ በጎንደር፣ በመተከል፣ አማራ እየረገፈ ነው። አማራ በተዘራበት የማጠልሸት ዘር እየተሰቃየ ነው። ሲፈናቀል ኖረ። ሲዘረፍ ኖረ። አሁንም በተመሳሳይ ይሞታል። ይፈናቀላል። ይሰቃያል። እስከመቼ በዚህ ይቀጥላል? ይህ ሁሉ እየሆነ ለፖለቲካ ድል ቡድን ለይቶ መዘላለፍ እንዴትስ ቅድሚያ ይሰጠዋል?

እንደነ አቶ ክርስቲያን አይነቱ ፖለቲከኛ ትናንት “ብአዴን ወይም ሞት” በሚል አብረዋቸው ሲሰሩ ከነበሩት የእናት ፖርቲያቸው መሪዎች ጋር እንዴት በሰከነ መንገድ መነጋገር ይሳናቸዋል? አማራው እንደ ቅጠል እየረገፈ በልዩነት ዘፈን አታሞ መምታት፣ ማሽካካት፣ ደርሶ አዛኝ ለመምሰል የሃዘን መግለጫ ለማውጣት መሸቀዳደም ምን የሚሉት ወገንተኛነት ይሆን?

አዋቂዎችን እንተዋቸው ህጻናት አይሳዝኑም? ወንዶችን እንተዋቸው እናቶች፣ ነፈሰጡር፣ እመጫቶች አያሳዝኑም? ይህ ሁሉ ከሚሆን ስልጣን ቢቀርስ? ስምና ዝና ቢቀርስ? ሁሉም ነገር ቢቀርስ?

ከዛሬ አስራ ሁለት ዓመት በፊት በጉጂ ኦሮሞና በሲዳማ መካከል የወንዶ ገነት አካባቢ ላይ ባለው ከፍተኛ የጫት ገቢ ምክንያት የባለቤትነት ግጭት ተነሳ። ሲኮራኮሙ ቆዩ። አንዴ ሲበርድ፣ አንዴ ሲግል ከረመ። አንድ ቀን ግን እንደዚህ ሆነ። ከሲዳማ የተነሱ በዘፈን ታገዘው እየሸለሉ የጉጂዎችን ቤት አነደዱ። አወደሙ። እየለዩ ሳይሆን በጅምላ አመድ አደረጉት። የደረሰው ጉዳት ክፉ ነበር። ዛሬ መረጃ የማግኛ በር ስለተበረገደ የአሁኑ ቀውስ ይራገባል እንጂ፣ በወቅቱ የደረሰው ቀውስ ክፉ ነበር። ከጀርባ የፖለኢስ አዛዦች፣ አመራሮችና ካድሬዎች እጅ ነበረበት። ከጫት ቀረጥ የሚገኘውን ገቢ ለመብላት ህዝብ ተማገደ። ከርሳም ፖለቲከኞች ህጻናት ሲሞቱ፣ ሴቶች ሲነገላቱና ሃብት ሲወድም ትርፋቸውን ያሰሉ ነበር። መጨረሻ ላይ በህዝበ ድምጽ ወደ ቦታው ኦሮሚያ ተካተተና ነገሩ ተቋጨ። ወደፊት የሚሆነው የሚታይ ነው። ዛሬ እንጃዋር ሲዳማ ሲዳማ የሚሉት ለዚህ ይሆን? ከርዕሴ ላለመውጣት ላቁመው።

ዛሬ መአማራ ክልል የጠራራ ዝርፊያ ገደብ የሚያበጅለት አልተገኘም። ዛሬ አማራ ክልል ተሽከርካሪዎች እንዳሻቸው አይንቀሳቀሱም። ዛሬ አማራ ክልል ተፈናቃዩ በርክቶ ለቁጥር እየታከተ ነው። ዛሬ አማራ ክልል መንግስት ሙሉ አቅሙን ሊጠቀም አልቻለም። ከግራና ቀኝ፣ ከውስጥና ከመካከል ተውጥሮ ለሌሎች የሚመች ዱኩማን ሆኗል። ይህንን የተረዱ እንዳሻቸው ይዘፍኑበታል። የደንሱበታል። ዳግም ወደ ህብረት እንደማይመጣ እርግጠኞች ሆነው ያሽሟጥጡታል። ለክፉም ለደጉም ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ስራቸው ገብተዋል። አማራ ክልል እንኳን ወደ ሰራ ገብቶ የህዝብ ጥያቄ ሊያስተናግድ ከራሱ ወገኖች የሚሰነዘርበትን በትርና ማጠልሸት በወጉ መመከት የቻለ አይመስልም። የዚህ ሁሉ ድምር ዛሬ እንደምናየው ሃፍረትና ሃፍረት ብቻ ነው።

ቤኒሻንጉል አማራ በቀስት ይወጋል። በከሚሴና በማጀቴ አማራ ስጋት ላይ ነው። በጎንደር ወኪሉን መግለጽ ባያስፈልግም  አማራው ክፉኛ ተጎድቷል። እርጥባን ለማኝ ሆኗል። ሜዳ ላይ እንደ ፍልፈል ተበትኗል። እድሜ ለዚህ ዘመን ልጆቹ ሃፈረት ለብሷል። እድሜ ለዛሬው ትውልድ በቀዬው አንብቷል። እድሜ ለዚህ ትውልድ በጀግኖች ስም ቀረርቶ እየተከፈተለት አከርካሬው ተመቷል። እድሜ ለዚህ ትውልድ…

ዛሬ እገሌ ከገሌ ሳይባል እጅ ለእጅ በመያያዝ የክልሉን ሰላማና ጤና ማስጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጥበት ወቅት ነው። በመደጋገፍ ዳግም ለማበብ አድፍጦና ” ተኩላ” ሆኖ መስራት የሚያስፈልግበት ውቅት ነው። ይህ ካልሆነ ሃዘኑም፣ ውርደቱም፣ ልመናውም፣ ዱላውም፣ ሞቱም ይቀጥላል። ከዚያም ታሪክ ሆኖ መቅረት የመጨረሻው አማራጭ ይሆናል።

የክልሉ ገዢ ፓርቲም የሚቻለውን ሁሉ ወደፊት በመሄድ የማስተባበሩን ስራ ሊሰራ ይገባል። ህዝብ በተልይም ወጣቱ  ሁሉም ወገኖች ወደ ህብረት እንዲመጡ ሊያስገድድ ግድ ይላል። በተራ ቀረቶና በፊስ ቡክ አድማ አንድም እርምጃ መራመድ አይቻልም። ሃዘን በተሰማ ቁጥር ” RIP” የምትሉ፣ ” ያማል” እያላችሁ የምታላዝኑ አቁሙ። የጦርነት አታሞና ቀረቶ የሚያሰሙ፣ እንኳን ጥይት ጮሆ መናገር በሚከለከልበት አገር የሚኖሩትን አዝማቾች ሞግቱ። እንደ ሰው በማሰብ ተከራከሩዋቸው። እንደ ጋማ ከብት ዝም ብላቹህ ሲጭኗቹህ አትጫኑ። ጥንቃቄ ውሰዱ። ሁሉም ሃላፊነት መውሰድ ካልቻለ እንዲሁ እያየነው ተረት እንሆናለን። ከተረት ብናመልጥ ከውርደትና ከመቀጥቀጥ አንወጣም። ቀረርቶና ፉከራ ይቁም። በጩኸት የተሰራ አገር የለም።

ሲቋጭ ከላይ ልጅ ግሩም እንዳሉት ነውና ይታሰብበት።

ሞገስ ሰውየው አዲስ አበባ ፴/፬/፳፩፱

ምስል አልጀዚራ

ዝግጅት ክፍል – ይህን ጽሁፍ የጸሃፊው ሃሳብ እንጂ የዝግጅት ክፍሉን እምነት አያንጸባርቅም

 

የአይሲስ መሪ ከአምስት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ታየ

የኢስላማዊ ታጣቂ (አይ ኤስ) ቡድን መሪ አቡ ባክር አልባግዳዲ ድምጹን ካጠፋ ከአምስት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተንቀሳቃሽ ምስል መልዕክቱን አስተላልፏል። ቡድኑ ለተነጠቃቸው ይዞታዎችም የበቀል እርምጃ እንደሚወስድ ዝቷል። በአውሮፓውያኑ 2014 ሞሱል በተባለችው የሶሪያ ከተማ ውስጥ ሆኖ በሶሪያና ኢራቅ ላይ እስላማዊ ካሊፌት መመስረቱን ካወጀ በኋላ እምጥ ይግባ ስምጥ ሳይታወቅ ቀርቶ ነበር።

በተንቀሳቃሽ ምስሉ በቅርቡ በባጉዝ ያጋጠማቸውን ሽንፈት ያመነ ሲሆን መልዕክቱ መቼ እንደተቀረጸ ግን እርግጠኛ መሆን አልተቻለም። ቡድኑ በበኩሉ ተንቀሳቃሽ ምስሉ በያዝነው ሚያዚያ ወር ላይ የተቀረጸ እንደሆነ አስታውቋል። አልባግዳዲ በመልዕክቱ ከሁለት ሳምንት በፊት በስሪላንካ የፋሲካ በዓል ዕለት ለደረሰው የቦምብ ጥቃት ኃላፊነቱን የወሰደ ሲሆን ባጉዝ ላይ ላጋጠማቸው ሽንፈት ምላሽ እንደሆነ አስታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪም አልባግዳዲ የሚመራው ቡድን በቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ፣ ሱዳንና አልጄሪያ ባሉ የአፍሪካ ሃገራት ስላለው ወታደራዊ ግንኙነትና መታወጅ ስላለበት ኢስላማዊ ጂሃድ መልዕክቱን አስተላልፏል። ቡድኑ ምንም እንኳን በተለያዩ ግዛቶች ሽንፈትን ቢቀምስም የዚህኛው ተንቀሳቃሽ ምስል ዋነኛ ግቡ ሽንፈቶቹን ለመቀበል ሳይሆን አልባግዳዲን ለገደለ 25 ሚሊየን ዶላር ሽልማት ከመኖሩ ጋር ተያይዞ ብዙዎች ሳይሞት አይቀርም ማለታቸውን ለማስተባበል ይመስላል። BBC Amharic

የእርቀ ሰላም ኮሚሽን በቀጣይ ጊዜያት እውነትና ፍትህ ላይ መሰረት ያደረገ እርቅ ለማውረድ እንደሚሰራ ገለፀ!

የእርቀ ሰላም ኮሚሽን በቀጣይ ጊዜያት እውነትና ፍትህ ላይ መሰረት ያደረገ እርቅ ለማውረድ እንደሚሰራ ገለፀ። የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ሰብሰባቢ ብፁእ ካርዲናል ብርሀነ ኢየሱስ፥ የኮሚሽኑን የእስካሁን ሂደት አስመልክተው በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥተዋል።

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ በሰጡት መግለጫም፥ ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ የማህበረሰባዊ እና ፖለቲካዊ ግጭቶች ምክንያት በህዝቦች መካከል የተደራረቡ የቁርሾ ስሜቶችን ለማከም፣ እውነትና ፍትህ ላይ መሰረት ያደረገ እርቅ ማውረድ አስፈላጊ መሆኑን በማመን ከኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት የተጣለበትን ሀላፊነት ለመወጣት ቅድመ ሁኔታዎችን እያሟላ መሆኑ ተመልክቷል። እርቀ ሰላም ኮሚሽኑ በአዋጅ ከተሰጠው ስልጣንና ተግባር በመነሳት ለቀጣይ ሶስት ዓመታት የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው በግጭቶቹ መሰረታዊ መንስኤዎች ላይ እንደሆነም ተገልጿል። ይህም ኮሚሽኑ ከመቋቋሙ ቀደም ብሎ እና ከተቋቋመ በኋላ እየተንፀባረቁ ያሉትን የግጭቶች ቅፅበታዊ መንስኤዎች እና ክስተቶች ለማስተናገድ የሚያስችለው እንደሚሆንም መግለጫው አመልክቷል።

ይህም እርቀ ሰላም ኮሚሽኑ የሚያተኩረው በእሳት ማጥፋት ላይ ሳይሆን በመረጃ ላይ የተመሰረተ ስልትን በመከተል ችግሮችን ከምንጫቸው ማድረቅ ላይ መሆኑንም ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው። እስካሁን ባለው ጊዜም የህዝቦች ዘላቂ ሰላምና በእውነትና በፍትህ ላይ የተመሰረተ እርቅ ለማምጣት የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታዎችን ከመለየት ጀምሮ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት የሚያስችሉ ግብአቶችን እስከ ማሟላት የሚደርሱ ልዮ ልዩ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።

በዚህም መሰረት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሾሙት የፅህፈት ቤት ኃላፊ አማካኝነት ልዩ ልዩ አስተዳደራዊ መዋቅሮች እና እቅዶች ለመንግስት ቀርበው በጀት እንዲመደብ መጠየቁንም ገልጿል። በተለያዩ ጊዜያት የእርቀ ሰላም ጥሪ አንዲደረግ ጥረት ከሚያደርጉ ልዩ ልዩ አካላት ጋር መደበኛ እና መደበኛ ያልሆኑ ምክክሮች መካሄዳቸውም በመግለጫው ተመልክቷል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በኩል የቀረቡ አቤቱታዎችን መነሻ በማድረግ የዜጎችን የመደመጥና በተገቢው ሁኔታ ፍትህ የማግኘት ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የሚያስችል የባለሙያ ስብስብ ለማቋቋም በዝግጅት ላይ መሆኑንም አስታውቋል።

የእርቀ ሰላም ሂደቱ የተሳካና ውጤታማ ለማድረግ ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ልዩ ልዩ የመገናኛ አውታሮችን በመጠቀም አስተዋፅኦ በማበርከት ያላቸውን ፍላጎት በመግለፃቸውና ኮሚሽኑን ለመደገፍ ላሳዩት ቁርጠኝነት አበረታች መሆኑንም ገልጿል። ኮሚሽኑ በመግለጫው የኢትዮጵያ ወዳጆች ከሆኑ መንግስታት ሳይቀር የእርቀ ሰላም ኮሚሽኑን ለመደገፍ የታየው ቁርጠኝነት ከፍተኛ መሆኑን በመግለፅ ምስጋናውን አቅርቧል።

ስራውን በአግባቡ መወጣት ይችል ዘንድም መንግሰት አስፈላጊውን አስተዳደራዊ ድጋፍ በተገቢው ጊዜ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ሊያረጋግጥ ይግባል ያለው ኮሚሽኑ፥ አስፈላጊውን ነገር በማሟላት እና የኮሚሽኑን ስራ ለማሳለጥ ዝርዝር መመሪያዎች እና ደንቦችን ማዘጋጀትም እንደሚገባ ነው ያመለከተው። ወደ ሚፈለገው ዘላቂ ሰላም፣ እውነትና ፍትህ ላይ የተመሰረተ እርቅ፤ አንዲሁም ብሄራዊ አንድነት ወዳላት ኢትዮጵያ ለመድረስ የምናደርገው ጉዞ በመደማመጥ፣ በመከባበር እና በመተማመን ላይ የተመሰረተ ሊሆን አንደሚገባ አመልክቷል።

በመሆኑም ሌሎች አካላት ለእኛ እንዲያደርጉ የምንፈልገውን ለሌሎች በማድረግ፤ በእኛ ላይ አንዲደረግ የማንፈልገውን በሌሎች ላይ ከማድረግ በመቆጠብ በጋራ የጀመርነውን የተሻለ ነገ የመፍጠር ሂደትን ከዳር እንዲደርስ ጠይቋል። የአርቀ ሰላም ኮሚሽኑ በህዝብ እና በህግ የተሰጠውን ተልእኮ በተገቢ መልኩ አንዲያከናውን የሀገሪቱ ህዝቦች እና በየደረጃው ያሉ ባለ ድርሻ አካለት ድጋፍ አንዲያደርጉም ነው ኮሚሽኑ ጥሪ ያቀረበው።

በባሃሩ ይድነቃቸው

FBC

የህግ ጥሰት የሚፈፅሙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ለመቆጣጠር የሚያስችል የስነ ምግባር መመሪያ ወደ ተግባር መግባቱ ተገለፀ

የህግ ጥሰት የሚፈፅሙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ለመቆጣጠር የሚያስችል የስነ ምግባር መመሪያ ወደ ተግባር መግባቱን የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትበዛሬው እለት ባካሄደው 37ኛ መደበኛ ስብሰባው የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የ9 ወራት አፈፃፀምን ገምግሟል።

የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ባቀረቡት ሪፖርትም፥ የትምህርትና ስልጠና ተደራሽነት፣ ፍትሃዊነት፣ ጥራት ቁጥጥር ላይ ያተኮረ ነው። በዚህም የህግ ጥሰት ፈጽመው የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ለመቆጣጠር የሚያስችል የስነ ምግባር መመሪያ ወደ ተግባር መግባቱን በሪፖርታቸው አስታውቀዋል።

በከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነትን ከማረጋገጥ አንጸር የጥራት ማስጠበቂያ መንገዶችን በመጠቀም የተሰራው የክትትልና ድጋፍ ስራ አበረታች መሆኑም ገልፀዋል። በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ድንገተኛ ግምገማዎች ተደርገው በ46 ተቋማት ላይ የተለያዩ ክፍተቶች መስተዋላቸውንም በሪፖርታቸው አመላክተዋል።

ከእነዚህም ወስጥ 24 የግል ከፍተኛ የግል ተቋማት የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወስዱ፣ 3 ተቋማት ላይ ክስ የመመስረት ሂደት እንዲሁም በቀሪዎቹ ላይ ደግሞ ተጨማሪ የማጣራት ስራ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል። የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና በዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማስፋን የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን ነው ሚኒስትሯ በሪፖርታቸው ያስታወቁት። የሴቶች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥም ባለፉት 9 ወራት የተሰሩ ስራዎች ውጤት ማስገነታቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል።

የመምህራንን ቁጥር እና አቅም ለማሳደግ እየተሰራ ባለው ስራም በአሁኑ ወቅት ከ15 ሺህ በላይ መምህራን ከ1ኛ እስከ 3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆኑን ገልፀዋል። ተመራቂ ተመሪዎችን ስራ የመያዝ መጠንን ለመለየት በተሰራው ጥናትም ባሳለፍነው ዓመት ከተመረቁት ውስጥ 58 ነጥብ 5 በመቶ ተመራቂዎች ስራ መያዛቸው መለየቱንም ነው ያስታወቁት። ተመራቂ ተማሪዎች የሚመረቁበት የትምህርት ዘርፍ ከገበያው ጋር የተጣጣመ መሆን እንዳለበት መለየቱንም ነው ሚኒስትሯ በሪፖርታቸው ያመላከቱት።

በምስክር ስናፍቅ – FBC

Kenya and Ethiopia Are Strategic Partners, Not Competitors

opinion

In the past one year, Ethiopia and Kenya have witnessed a re-awakening of bilateral relations, which by extension have revitalised and re-energised a new development chapter for both countries.

This is against the backdrop of historical similarities between the two countries, which for a long time had either been accorded little significance or played second fiddle to other competing goals.

STRATEGIC PARTNERS

The moment is now ripe to explore development opportunities for the betterment of our people. The clarion call of Prime Minister Abiy Ahmed to regional neighbouring countries is to integrate. This is because the destiny of the Horn of Africa countries is intertwined. For Ethiopia and Kenya, our destiny is cemented permanently. Together, we should pursue a collective and complimentary outcome to the betterment of over 150 million people in the two countries.

In order to realise gainful deeds from above, we should on the one hand understand that Ethiopia and Kenya are strategic partners not competitors, and on the other hand, we should identify comparative advantages that are a stock of our countries. How well we utilise both ends will determine the success of bilateral partnership.

Yet, there are areas where Ethiopia is technically and resourcefully endowed and possesses strong comparative advantage, and can in effect benefit Kenya’s Big Four agenda. A classic example is in manufacturing, the leather industry being a case in point. In comparison, Kenya is lionised as the ‘Silicon Valley’ of Africa, subsequently, Ethiopia can benefit from the ICT superiority of Kenya in many ways

Image result for Meles alem

MAXIMUM BENEFITS

In addition, the entrepreneurship spirit of Kenyans on various sectors complimenting the pursuit of the Big Four, compounded with the vibrant role of media in nation building is a good example for Ethiopia to learn from. The government of Prime Minister Abiy has made great strides to actualising the concept Madamar, a call for unity, synergy and harmony, which is also timely and applicable to present setting of Kenya.

Unlike in yester-years, 2018 and 2019 has seen summit meetings between the leaders of Ethiopia and Kenya acquire new traits. The reciprocal meetings, complete with befitting delegations have rendered a boost to among others, re-awakening of the Special Status Agreement of 2012 between the two countries and ascertained the fact that infrastructure development is a common enabler of the economies of both countries, a fact that cannot be gainsaid.

During the summit meetings, both heads of state made bold commitments complete with clear cut time frames to implement. For instance, it was agreed that logistics for the One Stop Border Post be put in place by the end of the second quarter of 2019; both heads of state also agreed to jointly inspect and supervise the Lamu-Garissa-Moyale and Moyale-Hawassa-Addis Ababa road network.

Yet again, the Lamu Port-South Sudan-Ethiopia Transport Corridor (Lapsset) project and the Moyale Joint city and Economic Zone project are areas where upon completion will help countries reap maximum benefits and demonstrate the power of bilateral relations.

FUTURE PURSUIT

The construction of three berths is completed from 62 to 99 per cent. All three berths will be completed and ready by December 2020, signifying that Lapsset is not a pipedream but deliverable project.

Ethiopia and Kenya are at a juncture whereby success in realising development aspirations is detrimental to the level of coordination and partnership between the two. To realise the full benefits of the Ethio-Kenya trade relations therefore calls for a deliberate commitment to the course.

On the one level, prevailing regional security challenges and development needs present a rife opportune to be acted upon. On the other level, Ethiopia and Kenya have between them required needs to tackle the above and elevate their countries up and above economic wants.

In sum, relations between Ethiopia and Kenya are not only symbiotic, but also bear identical similarities which should be utilised to the betterment of one another. If effectively coordinated, interpreted and implemented, the chapter on the pursuit of Ethio-Kenya relations will set a precedence to the future pursuit of bilateral relations.

Tellingly, successful pursuit of the Ethio-Kenya relations will demonstrate that both countries are partners, and not competitors. Albeit in the marathons.

The author is the Ethiopian Ambassador to Kenya.

Kenya

Read the original article on Nation.