“…ንፁሃን ሰዎችን እስር ቤት ወርውረው እንደ ትልቅ ጀብድ ነው የሚያዩት… ” አቶ በቀለ ገርባ

 

“…ከሳሼ ያቀረበውን ማስረጃ ትርጉሙን ሳያውቅ፤ ይዘቱ ምን እንደሆነ ሳያውቅ ነው እንዴ የከሰሰኝ? ትርጉሙን ሳያውቅ እንዴት ወንጀል ነው ብሎ ትርጉሙን በማያውቀው ማስረጃ ክስ ይመሰርታል? በእውነቱ በሃገራችን የፍርድ ሂደት አዘንን፤ እኛስ ትንሽ ነን በዚህ አይነት ስንት ሚሊዮኖች ናቸው መከራቸውን የሚያዩት? የኛ ጉዳይ ዝም ብለው ታስረው ይቆዩልን አይነት ነገር ነው። እቤታቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ቁጭ ብለው በኛ ስቃይ እና መከራ ይደሰታሉ። ማስረጃው እንደሚባለው ተተርጉሞ ቢቀርብ ለኔ ይጠቅመኝ ነበር። የኔን ንፅህና ነበር የሚያስረዳው። ጉዳዩ ከሚንጓተት ይቅርና በተሰሙት ማስረጃዎች ውሳኔ እንዲሳጥ ነው የምጠይቀው “

“ፍ/ቤቱ ሌሎች አማራጮችን ይጠቀም።” ኢብኮ

ስተርጓሚዎች ቀርበው ማስረጃው በችሎት እየታየ እንዲተረጎም ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጥ።” አቃቤ ህግ

የእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ ለሚያዚያ 2, 2009 ተቀጥሮ የነበረው አቃቤ ህግ በማስረጃነት ያቀረባቸው በኦሮምኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተሰሙ የድምፅ ከምስል ማስረጃዎችን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በፍርድ ቤቱ የስራ ቋንቋ ተርጉሞ እንዲያቀርብ ነው። ሆኖም እንዲተረጎሙ የተላኩትን ሶስት ሲዲዎች ለመተርጎም ሰፊ ጊዜ የሚወስዱ በመሆናቸው እና ባለሙያዎች የስራ መደራረብ ስላለባቸው ፍ/ቤቱ ሌሎች አማራጮችን እንዲጠቀሙ የሚገልፅ በ29/7/2009 ከኢብኮ የተፃፈ ደብዳቤ መቅረቡን ዳኞች ተናግረዋል። በተጨማሪም ለትርጉም ስራ ህጋዊ ፈቃድ አውጥተው የሚሰሩ አካላት እንዳሉ ከኢብኮ የተላከው ደብዳቤ ይጠቁማል።

አቃቤ ህግ በጉዳዩ ላይ ያለውን አስተያየት ሲጠየቅ፤ የእንግሊዘኛ እና የኦሮምኛ አስተርጓሚ ተፈልጎ ማስረጃው በድጋሚ በችሎት እየታየ እንዲተረጎም ጠይቋል። የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው የትርጉም ስራውን በተመለከተ ተደጋጋሚ ቀጠሮ እየተሰጠ መሆኑ ገልፀው፤ ከሳሽ አቃቤ ህግ ሃላፊነቱን እንዳልተወጣ እና ማስረጃዎቹን በፍ/ቤቱ የስራ ቋንቋ ተርጉሞ ማቅረብ እንዳልተፈለገ ተቆጥሮ ማስረጃው ውድቅ እንዲደረግ እና በቀረቡ ማስረጃዎች ብይን እንዲሰጥ ያመለከቱ ሲሆን ዘንድሮ ኢትዮጵያ ውስጥ የቻይንኛ ትርጉም እንኳን እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሁለት የቪዲዮ ማስረጃዎች የቀረቡባቸው የኦፌኮ ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር በቀለ ገርባ “እቤት ያሉ ሰዎች ንፁሃን ሰዎችን እስር ቤት ወርውረው እንደ ትልቅ ጀብድ ነው ሚያዩት። በሰው ስቃይ የመደሰት ነገር ነው የማየው። ከሳሼ ያቀረበውን ማስረጃ ትርጉሙን ሳያውቅ፤ ይዘቱ ምን እንደሆነ ሳያውቅ ነው እንዴ የከሰሰኝ? ትርጉሙን ሳያውቅ እንዴት ወንጀል ነው ብሎ ትርጉሙን በማያውቀው ማስረጃ ክስ ይመሰርታል? በእውነቱ በሃገራችን የፍርድ ሂደት አዘንን፤ እኛስ ትንሽ ነን በዚህ አይነት ስንት ሚሊዮኖች ናቸው መከራቸውን የሚያዩት? የኛ ጉዳይ ዝም ብለው ታስረው ይቆዩልን አይነት ነገር ነው። እቤታቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ቁጭ ብለው በኛ ስቃይ እና መከራ ይደሰታሉ። ማስረጃው እንደሚባለው ተተርጉሞ ቢቀርብ ለኔ ይጠቅመኝ ነበር። የኔን ንፅህና ነበር የሚያስረዳው። ጉዳዩ ከሚንጓተት ይቅርና በተሰሙት ማስረጃዎች ውሳኔ እንዲሳጥ ነው የምጠይቀው።” የሚል አስተያየታቸውን አቅርበዋል።

የኦፌኮ አመራር እና 2ኛ ተከሳሽ የሆነው ደጀኔ ጣፋም “የአቃቤ ህግን ማስረጃ ፍ/ቤት ያሰባስብ የሚል ህግ የለም። ፍ/ቤት እያደረገ ያለው ማረጃ የማሰባሰብ ነገር ነው። ማስረጃዎቹ በፍ/ቤት የስራ ቋንቋ ተተርጉመው መቅረብ የነበረባቸው ከክሱ ጋር ነው። የአቃቤ ህግ ማቋቋሚያ አዋጅ ክስ በቅንንነት መቅረብ እንዳለበት ይጠቅሳል። ማስረጃዎች የሚጎሉ ከሆነ ክሱን አለማቅረብ ይቻል ነበር። ተተርጉሞ እንዲቀርብ ፍ/ቤት ካዘዘ ቆይቷል። አቃቤ ህግም በባለፈው ቀጠሮ ማስረጃዎቹን ኢብኮ እንዲተረጉም መላኩን ተናግሯል። በሃገሪቷ የተቋም አለመታዘዝ አለ። የአቃቤ ህጉንም እጅ የጠመዘዘ እጅ አለ ማለት ነው። ጉልበቱ እና አቅሙ ካላችሁ ያንን እጅ ሰብስቡልን።” ብሏል። አቃቤህግ በማስረጃ አቀራረብ ሂደት ያሳየው ቸልተኝነት እንዳልነበረ ጠቅሶ ተደጋጋሚ ቀጠሮ መሰጠቱን በዚህም ተከሳሾች መንገላታታቸው የማይካድ መሆኑን ተናግሯል። ከክሱ ጋር የተያያዙ የሰነድ ማስረጃዎችን በተመለከተ በፍ/ቤቱ የስራ ቋንቋ ተተርጉመው ለተከሳሾች መድረሳቸውን ጠቅሶ የድምፅ ከምስል ማስረጃዎች ግን ከዚህ ቀደም በፍ/ቤቱ የተለመደው አሰራር በችሎት በሚታይበት ወቅት ከአስተርጓሚ ጋር የሚቀርብ እንደሚሆን ገልፇል። በዚህ መዝገብም የድምፅ ከምስል ማስረጃ በሚሰማበት ወቅት አስተርጓሚ እንዲቀርብ አድርጎ የነበረ መሆኑን አቃቤ ህግ አስታውሶ፤ በእለቱ ችሎቱ ማስረጃው ከተሰማ በኋላ ተተርጉሞ ቢቀርብ ይሻላል ብሎ በመወሰኑ እየተተረጎመ የመሰማት ሂደቱ እንደቀረ ተናግሯል። በመሆኑም ሌላ ቀጠሮ እንዲሰጥ እና ማስረጃው በችሎት እየታየ አስተርጓሚዎችም ቀርበው በችሎት እንዲተረጎም አቃቤ ህግ ጠይቋል።

ዳኞች የግራ እና የቀኙን ክርክር ከሰሙ በኋላ የነሱን አስተያየት እና ትእዛዝ ሰጥተዋል። አቃቤ ህግ ክስ ሲመሰርት የሰነድ ማስረጃዎችን ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ማስረጃ በፍ/ቤቱ የስራ ቋንቋ አስተርጉሞ ማቅረብ እንደነበረበት፣ ፍ/ቤቱ እየሰራ ያለው መረጃ ማሰባሰብ ሳይሆን የፍትህ ስርአቱን የማገዝ ስራ እንደሆነ እንዲሁም ኢብኮም የፍትህ ስርአቱን የመተባበር ግዴታ እንዳለበት ገልፀዋል። በዚህም መሰረት ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) የሚመለከተው ሃላፊ ሁለት አስተርጓሚዎችን(አንድ የኦሮምኛ እና አንድ የእንግሊዘኛ ቋንቋ) ይዞ በመጪው ሃሙስ (ሚያዚያ 5, 2009) እንዲቀርብ ጥብቅ ትእዛዝ መስጠታቸውን ተናግረዋል— ዳኞች። በተጨማሪም ተርጓሚዎቹ በቀጠሮው እለት ሲቀርቡ የትርጉም ስራውን በተቀላጠፈ እና በፍጥነት እንዲሰሩት የድምፅ ከምስል ማስረጃዎቹ ከቀጠሮው ቀደም ብሎ እንዲደርሳቸው ታዟል።

ምስጋና  ለየኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ፕሮጀክት

One thought on ““…ንፁሃን ሰዎችን እስር ቤት ወርውረው እንደ ትልቅ ጀብድ ነው የሚያዩት… ” አቶ በቀለ ገርባ”

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.